Print this page
Saturday, 26 January 2013 12:08

ካሚላት ላይ አሲድ ደፍተናል ያሉ ወጣቶች ቃላቸውን ሰጡ:: ፖሊስ ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል

Written by  ሠላም ገረመው
Rate this item
(11 votes)

በካሚላት መህዲን ላይ አሲድ ደፍቷል በመባል የተከሰሰው እና የዕድሜ ልክ እስራት የተፈረደበት ደምሰው ድርጊቱን እንዳልፈፀመና “የፈፀምነው እኛ ነን” ያሉ ወጣቶች ሰሞኑን ለፖሊስ ቃል መስጠታቸውን ምንጮች ጠቆሙ፡፡ ከዛሬ ስድስት ዓመት በፊት የፍቅር ጓደኛው በሆነችው ካሚላት ላይ የአሲድ ጥቃት ማድረሱ በሰው ምስክርና በማስረጃ ተረጋግጧል ተብሎ የተከሰሰው ደምሰው፤ጉዳዩን እንዳልፈፀመ በመናገር ቢከራከርም በሰውና በሠነድ ማስረጃዎች ተረጋግጧል በማለት ፍ/ቤት በሞት እንዲቀጣ ወስኖ ነበር፡፡

ተከሳሽ ይግባኝ ጠይቆ ቅጣቱ ወደ 20 ዓመት ዝቅ ብሎለት የነበረ ቢሆንም ዐቃቤ ሕግ እና የሕግ ባለሞያ ሴቶች ማኅበር ይግባኝ በማለት ተከሳሹ በዕድሜ ልክ እስራት እንዲቀጣ መወሰኑ ይታወቃል፡፡ ከስድስት ዓመታት በኋላ ሰሞኑን “ድርጊቱን እኛ ነን የፈፀምነው” ያሉ ግለሰቦች መገኘታቸውን የተከሳሹ ወላጅ እናት ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መጠቆማቸውን የሚናገሩት ምንጮች፤ የተባሉት ሦስት ወጣቶች ጫት ቤት ተቀምጠው የፈፀሙትን ድርጊት እያነሱ ሲያወሩ የሰሙ ሰዎች፣ ለተከሳሽ ቤተሰብ በመንገር ጉዳዩ ክትትል እንዲደረግበት ጥቆማ መሰጠቱን ገልፀዋል፡፡ የተባሉት ወጣቶችም ተይዘው በሰጡት ቃል፤ ድርጊቱን መፈፀማቸውን አምነው ቃላቸውን መስጠታቸውን እና ትላንት ደምሰው ከማረሚያ ቤት ወጥቶ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ቃሉን ሰጥቶ መመለሱን ምንጮቻችን ተናግረዋል፡፡ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጉዳዩን እያጣራ በመሆኑ መረጃ ለመስጠት እንደማይችል ገልፆልናል፡፡

Read 7598 times Last modified on Saturday, 26 January 2013 17:06