Saturday, 26 January 2013 11:56

የተቃዋሚዎች በምርጫው መሳተፍና አለመሳተፍ ትርፍም ኪሣራም እንደሌለው ኢህአዴግ ገለፀ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(2 votes)

ከሁለት ወራት በኋላ ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው የአዲስ አበባ አስተዳደርና የአካባቢ ምርጫ ላይ የተቃዋሚ ፓርቲዎች መሣተፍና አለመሳተፍ ለኢህአዴግ ትርፍም ኪሳራም እንደሌለውና የሚያጐድለው ነገርም እንደማይኖር ኢህአዴግ ገለፀ፡፡ የኢህአዴግ ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ሬድዋን ሰይድ ትናንት በፅ/ቤቱ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት፤ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአብዛኛው በአካባቢ ምርጫ ተሳትፈው አያውቁም፡፡ በአካባቢ ምርጫ የሚገኝ ሥልጣን በአብዛኛው ለታይታና ለወሬ የማይመች እና ሥራ ላይ ትኩረት ያደረገ በመሆኑ ተቃዋሚ ፓርቲዎቹ ፓርላማ መግባትን የመዋደቂያ ነጥብ አድርገው ሲንቀሣቀሱ ይታያሉ ብለዋል፡፡ የፓርቲዎቹ በምርጫው ላይ መሣተፍና አለመሳተፍ ትርፍም ኪሣራም የለውም ያሉት አቶ ሬድዋን፤ ለሥርዓቱ ግን መሣተፋቸው ጠቃሚ ይሆን እንደነበርና በምርጫው ውስጥ መሣተፋቸው ራሳቸውን ለማየትና ለመማር እንዲችሉ ያደርጋቸው እንደነበር ተናግረዋል፡፡

ከተቃዋሚ ፓርቲዎች አንዳንዶቹ አንድ ግለሰብ በአራት ማህተም የሚያንቀሣቅሣቸውና በህይወት በሌሉ፣ የመጀመሪያውን ማህተም ባልመለሱ ሰዎች የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች እንደ ፓርቲ ተቆጥረው ምርጫ ውስጥ ገቡ አልገቡ ሊያሰኝ እንደማይችል ገልፀዋል። ብዙዎቹ ፓርቲዎች አባልም፣ ፅ/ቤትም እንደሌላቸው የተናገሩት ኃላፊው፤ እነዚህ ፓርቲዎች በምርጫው ቢሣተፉ ምንም እንደማይጠቅሙ ጠቁመው፤ ቀድሞውኑ የሚያንቀሣቅሱት ዓላማ ስለሌላቸው፤ ባይሣተፉ ደግሞ ምንም እንደማያጐሉ ምክንያቱም ቀድሞውኑ ያልነበሩ ስለሆነ ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በምርጫው ውስጥ የብዙ ፓርቲዎች መሣተፍ የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መገለጫ አይደለም ወይ በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም፤ ምርጫው በ29 ፓርቲዎች መካከል የሚካሄድ ምርጫ መሆኑን አስታውሰው፣ ሃያ ዘጠኝ ፓርቲዎች የሚርመሰመሱበት ምርጫ ያለው ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ እንደሆነና በአሜሪካንም ሆነ በእንግሊዝ ሁለት ፓርቲዎች ብቻ የሚወዳደሩበት ምርጫ እንደሚካሄድ ተናግረዋል፡፡ የምርጫ ዲሞክራሲያዊነት የሚለካው ምን ያህል ፓርቲ በምርጫው ውስጥ ይርመሰመሳል በሚል እንዳልሆነና መለኪያው ህዝቡ በነፃነት ውሣኔ ይሰጣል ወይ፣ የቀረበው አጀንዳ ለህዝቡ ምን ያህል ፋይዳ አለው የሚሉ መመዘኛዎች እንደሆኑ አቶ ሬድዋን ጨምረው ገልፀዋል፡፡ በእኛ አገር ኪዎስክ ከመክፈት በላይ ፓርቲ መመስረት ቀላል ነው ያሉት አቶ ሬድዋን፤ ሕጉ እስከዚያ ድረስ ቀላል እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የአንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ከምርጫ ራሳቸውን ማግለል አስመልክተው ሲናገሩም፤ በታላቁ መሪያችን ሞት ምክንያት ህዝቡ ስሜቱን የገለፀበትን መንገድ በማየታቸውና በምርጫው እንደማያሸንፉም ስለተረዱ ነው ብለዋል፡

፡ ኢህአዴግ በአዲስ አበባ ውስጥ 100ሺ አባላት እንዳለው የተናገሩት አቶ ሬድዋን፤ ከእነዚህ አባላቱ ውስጥ የምርጫው ጊዜ እየተቃረበ መምጣቱንና የካርድ መውሰጃው ጊዜ ሊጠናቀቅ መቃረቡን የማስታወስ ተልእኮ ለአባላቶቹ መሰጠቱን ገልፀዋል፡፡ ማንኛውም ተቃዋሚ ፓርቲ ይህን ተልዕኮ ለአባላቶቹ የመስጠት መብት አለው ሲሉም ተናግረዋል፡፡ ኢህአዴግ ለመጪው ሚያዝያ ወር ምርጫ ያዘጋጃቸውን እጩዎች በቀጣዮቹ ቀናት ይፋ እንደሚያደርግም አቶ ሬድዋን በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ተናግረዋል፡፡

Read 3031 times Last modified on Saturday, 26 January 2013 12:20