Saturday, 19 January 2013 15:26

የከሸፈው ማነው?ኢትዮጵያ ወይስ የፕሮፌሰሩ አስተሳሰብ?

Written by  አማኑኤል መሓሪ
Rate this item
(5 votes)

በፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም የተፃፈውና ሰሞኑን ለንባብ የበቃው “መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ” የተሰኘው መጽሐፉ ሀ ብሎ ሲጀምር እንዲህ በሚል ያልተለመደ ማስጠንቀቂያ ይንደረደራል፡፡

“ቁም! በመጀመሪያ ለአንባቢው አንድ ማስጠንቀቂያ ልስጥ፡፡ መጽሐፉ በጠቅላላ በተለይ ይህ መቅድም የከረረ ንዴት መግለጫ ነው፡፡ በኢትዮጵያ አጠቃላይ ሁኔታ ያልተናደደ፣ የማይናደድና ያልተበሳጨ ወይም ደልቶት የሞቀው ይህንን መጽሐፍ በተለይም ይህንን መቅድም አያንብበው። የረጋውን መንፈሱን ያስሸብረዋል” የሚል ማስጠንቀቂያ በማስፈር መጽሐፉን ንዴተኞች እና ብስጩ ሰዎች ብቻ እንዲያነቡት ቢጋብዙም፣ ይህንን መፈክር መሰል አጥር በማለፍ በተለይም የመጽሐፉን መቅድም ማለትም የከረረውን ንዴት ማንበብ ጀመርኩ፡፡ መቼም መግቢያው ላይ እንደሰፈረው፤ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሁኔታ የሚናደድ ወይም በኢትዮጵያ አጠቃላይ ሁኔታ የሚደሰት ሰው ማግኘት በራሱ ትልቅ ጥያቄ የሚያስነሳ ቢሆንም በግሌ በአጠቃላይ ሁኔታ የምናደድ ወይም በአጠቃላይ የሀገሬ ሁኔታ የምደሰት እንዳልሆንኩ ለመግለጽ እፈልጋለሁ፡፡ በአጠቃላይ ሁኔታ ደስተኛ ነኝ የሚል ሰው በጭፍን ፍቅር የታወረ መሆኑን ለመገንዘብ የምችለውን ያህል፣ በአጠቃላይ የሀገሪቱ ሁኔታ የከረረ ንዴት እና ብስጭት ውስጥ ነኝ ባዩም የጭፍን ጥላቻ ውጤት መሆኑን ለመረዳት ብዙ የሚያስቸግር አይመስለኝም፡፡

በመሆኑም ከጭፍን ንዴትና ደስታ ወጣ ብዬ የመስፍን ወልደማርያምን መጽሐፍ መቅድም ሳነብ የፈጠረብኝን ንሸጣ እንደሚከተለው ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡
መጽሐፉ በመቅድሙ በስፋት ካነሳው የመክሸፍ ታሪክ ከመዳሰስ አልፎ በርካታ የታሪክ እና የፖለቲካ ርዕሰ ጉዳዮችን የሚያነሱ ምዕራፎች ቢኖሩትም፣ አብዛኞቹ አንዱን ንጉስ ለማወደስ ሌላውን ንጉስ የማንቋሸሽ የወንዝ ልጅነት አባዜ እና የግል ዝንባሌ የሚታይባቸው፣ በጥላቻ የታጨቁ የንዴት ውጤቶች በመሆናቸው፣ ለዛሬው መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ የተሰኘው የመጽሐፉ ዋነኛ ድርሰት ላይ አተኩራለሁ፡፡

ንዴተኛ እና ብስጩ ሰዎች ብቻ እንዲያነቡት የሚገልፀውን ማስጠንቀቂያ በማስከተል የመክሸፉን ምንነት እና ትርጓሜ በመስጠት የሚጀምረው የመስፍን ወልደማርያም መጽሐፍ፤ በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ስለሚከሰተው መክሸፍ አንድም የታሪክ ምሁር ትኩረት ሰጥቶ ጽሑፍ ጽፎ እንደማያውቅ በምሬት በመጥቀስ፣ በምሳሌነት ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ የለውጥ ፈር ቀዳጆች በማለት በእንግሊዝኛ የፃፉትን መጽሐፍ ይተቻሉ። ይተቻሉ ያልኩት መደበኛውን አገላለጽ ለመጠቀም ያህል ነው፡፡ መስፍን ሁልጊዜ እንደሚያደርጉት እዚህ መጽሐፍ ውስጥ የሚያነሷቸውን ምሁራን ሃሳባቸውን ብቻ ሳይሆን የሚተቹት ግለሰባዊ ማንነታቸውን ጭምር ነው የሚዘልፉት፡፡
“ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ አንዱ አስተማሪው ያስታጠቀውን” ብለው ጀምረው “ባህሩ የፈረንጅ ትምህርት ፍሬ በመሆኑ የጥንቱን ላያውቀው ይችላል፡፡
ታዲያ ሊቅነት የማያውቁትን ለማወቅ መጣር አይደለም እንዴ?” በማለት ያሳርጋሉ፡፡ እንደሁልጊዜው ያልኩት በቅርቡ ለፕ/ር ገብሩ ታረቀ የሰጡትን ከተነሳው ሃሳብ ጋር የማይገናኝ “የባህር ማዶ” ሰው የሚል መልስ የሚያስታውስ ያስታውሰዋል በማለት ነው፡፡

እዚህ ላይ ምሁራኑ ላይ ያወረዱባቸውን ናዳ ትተን ታሪክ ፀሐፊዎቻችንን የተቹበትን መንገድ ሳናደንቅ ማለፍ ያለብን አይመስለኝም፡፡
በተለይም በታሪክ ምሁራኖቻችን ላይ የሚታየውን ለሕዝባቸው በሚገባ ቋንቋ እና በሚደርስ መልኩ ታሪክን ከመፃፍ ይልቅ በባዕድ ቋንቋ ባዕዳንን በሚያስደስት መልኩ ለከፈላቸው ብቻ የመፃፉን አዝማሚያ መተቸታቸው ከመቅድሙ የምናገኘው ጠንካራ የመጽሐፉ አካል ነው ብል ማጋነን አይሆንብኝም፡፡ ባህሩ ዘውዴ ከዚህ ወቀሳ የዘለሉ በአማርኛም ሆነ በእንግሊዝኛ በርካታ ጽሑፎችን ያቀረቡ መሆናቸው ሳይዘነጋ፡፡

በመቀጠል ትኩረት ሰጥተው በተከታታይ አንቀፆች ያስቀመጧቸው ነጥቦች ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ ለመነሳት እየሞከረች የከሸፈችበትን ምክንያት ነው። በተለይም በየጊዜው እና አሁንም ድረስ ባንዳዎች እያደረሱባት ያለውን ኪሳራ በከረረ ንዴት ለመግለጽ በመጽሐፉ ሽፋን ላይ ያስቀመጡትን “ኢትዮጵያ ሀገሬ ሞኝ ነሽ ተላላ የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ” የሚለውን አስተሳሰብ አጽንኦት ሰጥተውይሞግታሉ፡፡

“በትክክል ባላውቅም በግምት እንደ ኢትዮጵያ አርበኞቹን የገደለ አገር በአለም ላይ ያለ አይመስለኝም፡፡ እነ በላይ ዘለቀ፣ አበበ አረጋይ፣ ራስ ስለሺን እና ስንትና ስንት አርበኞች ገለናል” የሚሉን መስፍን ወልደማርያም፤ “ባንዳን እያደነቁና እያከበሩ አርበኞችን እየናቁ ለአደጉ ትውልዶች አዘንሁ፤ ለኢትዮጵያ አዘንሁ፤ ስለዚህም የአሁኑ ባንዳ አክባሪ ትውልድ በአጥንት ላይ መቆሙን እንዲገነዘብ ለማድረግ ፎቶግራፎች ትንሽ ይረዳሉ ብዬ አሰብኩ” በማለት በመጽሐፉ መጨረሻ ገፆች ላይ የጣሊያን ወታደሮች በኢትዮጵያውያን ላይ ያደረሱትን ስቃይ የሚያሳይ ፎቶግራፍ የማስቀመጣቸውን ምክንያት ይገልፃሉ፡፡ መግለፃቸው ባልከፋ “የአሁኑ ባንዳ አክባሪ ትውልድ” የሚለው አገላለጽ ግን ምን ለማለት ተፈልጐ እንደገባ ቢያንስ ለኔ ግልጽ አይደለም፡፡ ሌላው ቢቀር ለበላይ ዘለቀ ከዚህ ትውልድ በላይ የዘፈነለት፣ ውዳሴ ያጐረፈለት፣ ቅኔ የተቀኘለት እና የተወነለት ትውልድ ያለ አይመስለኝም፡፡ ከሸሹበት ሀገረ እንግሊዝ ተመልሰው በላይ ዘለቀን የሰቀሉት ኃ/ሥላሴ “ግርማዊነትዎ” እየተባሉ ለምን ይወደሳሉ የሚል ጥያቄ ቢሆን የተነሳው ክርክር ሊገባን ይችላል፤ ነገር ግን እዛው እነ በላይን ገደልን በሚሉበት አንቀጽ ላይ ለኃ/ሥላሴ ሀውልት እንዳይሰራ ነፈግናቸው በማለት ለገዳዩም ለተገዳዩም ጥብቅና ሲቆሙ እናገኛቸዋለን፡፡ በዚህ ሰዓት የአሁኑ ባንዳ አክባሪ ትውልድ የት እንዳለ ይጠፋብናል፡፡ ይባስ ብለው ወደሃያ የሚጠጉ የአፄ ኃ/ሥላሴ ባለስልጣናትን ስም ጠቅሰው፤ የኢጣሊያ ገባሮች ሆነው የወር ደሞዝ የሚያገኙ ባንዳዎች እንደነበሩ በመግለጽ የሚያቅለሸልሻቸውም እውነት “አንገታቸውን የሚደፉ የአርበኞች ልጆችና ደረታቸውን የሚነፉ የባንዳ ልጆች መታየታቸው” እንደሆነ ከዚህም የሚበልጥ መክሸፍ እንደሌለ ይገልፃሉ፡፡

በባንዳነት ከተጠቀሱት መካከል አቶ ከበደ ሚካኤል፣ አቶ ብርሃኑ ድንቄ፣ ሼክ አሊ ሆጀሌ፣ ራስ ስዩም መንገሻ፣ ሱልጣን መሐመድ ሀንፍሬ፣ ነጋድራስ አፈወርቅ ገብረየሱስ እና አቶ ይልማ ደሬሳ ይገኙባቸዋል፡፡ ልጆቻቸው መቼ ደረታቸውን እንደነፉብን ግን አላውቅም። አንዳንዶቹ በአንድ ወቅት የጣሊያን አገልጋይ የነበሩ መሆናቸውን ብናውቅም የአንዱን ሰው የአንድ ወቅት ቁራጭ ሕይወት እንደ አጠቃላይ የሕይወቱ ተልዕኮ አድርጐ በመውሰድ ከበደ ሚካኤልም ሆኑ ይልማ ደሬሳ፤ አፈወርቅም ሆኑ ብርሃኑ ድንቄን ጠቅልለን የጥላቻ ወይም የአድናቆት ቅርጫት ውስጥ መክተት ያለብን አይመስለኝም፡፡
ያጠፉትን ጥፋት ብቻ ጠቅሰን ግለሰቦቹ ያበረከቱትን መልካም ተግባራት ለማን ልንሰጥ ይሆን? በቅርቡ ፖስታ ቤት የአፈወርቅ ገ/እየሱስን ፎቶ ከሌሎች ደራሲያን ጋር በማሳተሙ የተነሳውን አቧራ ሁላችንም የምናውቀው ነው፡፡

በዛ ላይ ይህን ወቀሳ የሚደረድሩት የመጽሐፉ ደራሲ፤ ስልሳዎቹ የአፄው ባለስልጣናት በሞት ሲቀጡ የሸንጐ አባል የነበሩ ሲሆኑ ይህ አልበቃ ብሏቸው ልጆቻቸው ዘነጡብን ብሎ ለሌላ በቀል መነሳሳት ምን ይሉታል፡፡ የአፄው ስርዓት እነዚህን ባንዳዎች አክብሮ ልጆቻቸው አሁን በምንኖርበት ዘመን ደረታቸውን መንፋታቸው የሚያቅለሸልሻቸው መስፍን፤ የአሁኑ ባንዳ አክባሪ ትውልድ በማለት ወደ ገለፁት ዘመን መለስ ብለው ሀይለኛ ወቀሳ የሚያሳርፉት የኃ/ሥላሴን መልካም ጅምሮች ማስቀጠል ባለመቻሉ ነው በማለት ጭርሱኑ የባሰ መደናቆርና ግራ መጋባት ውስጥ ይከቱናል፡፡
“በምንኖርበት ዘመንም ቢሆንም የኢትዮጵያን ውድቀት ለመረዳት ብዙም ጊዜ አይፈጅም፡፡ የትልቅነትና ታሪካዊ ምልክቶች ሁሉ ደብዛቸው እንዲጠፋ እየተደረገ ነው፡፡ የብሔራዊ መዝሙሩ ሁለት ጊዜ ተለውጧል፡፡ በሰንደቅ አላማው በአየር መንገዱ፣ በቴሌ የአንበሳ ምልክት እየተነቀለ ተጥሏል” በማለት ቁጭታቸውን ይገልፃሉ፡፡
መቼም አንድ በዚህ ዘመን የሚኖር የሰለጠነ ዕውቀት ያለው ኢትዮጵያዊ፤ “የሁሉ ነገራችን መሠረት ንጉሳችን ነው” የሚል መዝሙር ለምን ተቀየረ ብሎ የሚቆጭ አይመስለኝ፡፡
“ኢትዮጵያ ሆይ ደስ ይበልሽ በአምላክሽ ሀይል በንጉስሽ” ብሎ ጀምሮ “ድል አድራጊው ንጉሳችን ይኑርልን ለክብራችን” የሚለውን መዝሙር የአሁኑ “ባንዳ አምላኪ ትውልድ” መወቀስ ካለበት መዝሙሩን ባይቀይረው ኖሮ እንጂ በመቀየሩማ ሊወደስ ነው የሚገባው፡፡

ባንዲራዉ ላይ የነበረው ዘውድ የጫነ አንበሳስ ግልፅ አይደለም፡፡ አንበሳው እኮ ዘውድ ብቻ አይደለም ጭኖ የሚታየው በአንዱ እጁ የጨበጠው መስቀልም ጭምር እንጂ፡፡ ሙስሊሙ እና ክርስቲያን ያልሆነው ወገናችን የማይከበርበት ግርማ እንዴት ነው የኢትዮጵያዊነት ግርማ እየተነቀለ ተጣለ ሊባል የሚችለው?
የመስፍን ወልደማርያም ያለፈውን ዘመን መናፈቅ እና የአሁኑን ዘመን የመርገም አባዜ በዚህ ቢያበቃ ጥሩ፡፡
በአንዱ በኩል ባንዳዎችን አከበረ የሚሉት የኃ/ሥላሴ ስርዓት፤ በሌላ በኩል አሁን ካለው ትውልድና ሥርዓት የተሻለ እንደሆነ ለማሳመን ያቀረቡት ምክንያት የእውቀት ነው ወይስ የጤና ችግር ብዬ እንድጠይቅ አስገድዶኛል፡፡ በጭፍን ጥላቻ እና በከረረ ንዴት የተዋጠ ሰው፣ ጤናማ አመለካከቱ ጥያቄ ውስጥ መግባቱ አይቀሬ መሆኑ መቼም አይካድም፡፡

የሚከተለውን ማብራሪያ ስትመለከቱ እንደኔ እጅግ መደንገጣችሁ እና መገረማችሁ አይቀርም የሚል እምነት አለኝ፡፡ “በስንት ዘመናት ጥራትና በሰለጠነ የሰው ሀይል የተገነቡና የአገር ኩራት የነበሩ መስሪያ ቤቶች ተንኮታኩተዋል፡፡ ያሉትም ቢያንስ ሠላሳና አርባ ዓመት ወደኋላ ተመልሰዋል ወይም ጭራሹኑ ጠፍተዋል፤ ሆነ ተብሎ በስልት ከተዳከሙት ውስጥ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርስቲ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን፣ የኢትዮጵያ መብራት ኃይል ይገኙበታል። እነዚህ ሁሉ በመክሸፍ ላይ የሚገኙ ናቸው” በማለት እጅግ በጣም ድፍረት የተሞላበት ትንታኔ ይሰጣሉ፡፡

እየተስፋፉ ያሉትን ዩኒቨርሲቲዎች የትምህርት ጥራት ጥያቄ በይደር እናቆየውና የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ቴሌ እና መብራት ኃይል በምን አይነት አዕምሮ ነው ወደ ኋላ ሠላሳና አርባ አመት ተመልሰዋል ሊባሉ የሚችሉት፡፡ ልብ በሉ መስፍን ወደ ኋላ ተመልሰዋል ብቻ አይደለም የሚሉት “ጭራሽኑ ጠፍተዋል” ነው ያሉት፡፡ ይህን ጊዜ ነው የከሸፈው የመስፍን አስተሳሰብ ወይስ የኢትዮጵያ እውነት ብለን ለመጠየቅ የምገደደው፡፡

እንዲህ አይነቱን ተራ እጅግ በጣም በዘለፋ የተሞላ መፅሐፍ ፅፎ “በኢትዮጵያ አጠቃላይ ሁኔታ ያልተናደደ እና ያልተበሳጨ ሰው ይህንን መፅሐፍ በተለይም ይህንን መቅድም አያንብበው፤ የረጋውን መንፈሱን ያስሻክረዋል” ማለትስ ምኑ ሊገባን ነው ለኛ? ለምንድነውስ በሀገራችን ሁኔታ የተበሳጨ እና የተደሰተ በሚል ከሁለት ሊከፍሉን የተነሱት፡፡
እንዴትስ ያለ ዜጋ እና እውቀት ነው በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሁኔታ የሚበሳጭ እና የሚደሰት? ሌላው ቢቀር ከድህነት ወለል ለመላቀቅ በትግል ላይ ያለች፣ ከእርዳታ እና ከብድር ያልተላቀቀች፣ በሥራ አጥነትና በብዙ መሰል ችግሮች የተተበተበች ሀገር ይዞ እንዴት ሰው በአጠቃላይ ሁኔታ ሊደሰት ይችላል? በምንስ ሁኔታ ነው ኢትዮጵያ የምታደርገውን የኤሌክትሪክ ሀይል ግንባታ እና ግድብ ሥራ፣ ከፍተኛ የሆነ የትራንስፖርት እና የመንገድ ግንባታ እንዲሁም የጤና እና የትምህርት ሽፋን እንቅስቃሴ እየተመለከተ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሁኔታ የተናደደ ሰው ፍለጋ የምንወጣው? ከጭፍን ፍቅርና ከጭፍን ጥላቻ ይሰውረን ከማለት በቀር ሌላ ልንለው የምንችለው ነገር ይኖር ይሆን?

Read 4656 times