Print this page
Saturday, 19 January 2013 15:02

ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያምን ያስቀየመው ኩባዊ ደራሲ

Written by  ባየህ ኃይሉ ተሠማ bayehailu@gmail.com
Rate this item
(3 votes)

የኩባ ፕሬዚዳንት የነበሩት ፊደል ካስትሮ ሩዝ፣ ከኢትዮጵያ ጋር በነበራቸው አፍላ የወዳጅነት ጊዜ፣ “የኢትዮጵያ አብዮት እውነተኛ አብዮት ነው፤ መሪውም ትክክለኛ አብዮተኛ ነው” ብለው ማለታቸው በደርጉ ዘመን ተደጋግሞ ይጠቀስላቸው ነበር፡፡ ካስትሮ በተጨማሪም የኢትዮጵያ አብዮት በባህሪው ከፈረንሳይና ከቦልሼቪክ አብዮት የተቀየጠ ነው ሲሉም የአድናቆት ምስክርነታቸውን ሰጥተው ነበር ይባላል፡፡ በዚያን ዘመን በኢትዮጵያ በተከሰተው ለውጥ የተደነቁትና የተሳቡት ኩባዊ ፊደል ካስትሮ ብቻ አልነበሩም፡፡ በዚች አፍሪካዊት አገር በተካሄደው ለውጥ አትኩሮታቸው ከተሳበው አብዮተኞች መካከል ኩባዊው ጋዜጠኛ፣ ደራሲና ዲፕሎማት ቫልዲስ ቪቮ አንዱ ነበር፡፡ ይህ ሰው ወደ ሥራ ዓለም የተሠማራው፣ እነፊደል ካስትሮን ወደ ሥልጣን ያመጣው የኩባ አብዮት ከመቀጣጠሉ 13 ዓመት ቀደም ብሎ፣ “ሜላ” በተሰኘ መጽሔት ላይ መጻፍ ሲጀምር ነበር፡፡ አምባገነኑ የባቲስታ አገዛዝ የ “ሜላ” መጽሔት እንዳይታተም እስካገደበት ጊዜ ድረስ፣ ቫልዲስ ቪቮ ደረጃ በደረጃ እያደገ ሄዶ የመጽሔቱ ዋና አዘጋጅ እስከመሆን ደርሶ ነበር፡፡ ከእገዳው በኋላም የቫልዲስ ቪቮ ዕጣ ፈንታ እሥርና ስደት ሆነ፡፡

እነካስትሮ የመሩት የትጥቅ ትግል የባቲስታን የግፍ አስተዳደር እስኪያስወግድ ድረስም ኩባ ለዚህ ሰው ወሕኒ ቤቱ ነበረች፡፡ የኩባ አርበኞች ግፈኛውን ባቲስታን ድል ነስተው ሶሻሊዝምን ሲያውጁ፣ ቫልዲስ ቪቮና መሰሎቹ በአዲሲቷ ኩባ ብሩሕ ቀን ወጣላቸው፡፡ ድህረ አብዮት ቫልዲስ ቪቮ ሥራ የጀመረው “ሆይ” በተሰኘ መጽሔት ላይ ሲሆን እስከ ምክትል ዋና አዘጋጅነት ደረጃ በመድረስ ለስምንት ዓመታት ያህል በስራው ላይ ቆይቶበታል፡፡ ከዚህ በኋላም ወደ ኩባ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ተዛውሮ እ.ኤ.አ ከ1967 ዓ.ም እስከ 1974 ዓ.ም ድረስ በካምቦዲያ እና በቬትናም ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ የኩባ ዲፕሎማሲ እንደራሴ (አምባሳደር) ሆኖ ሰርቷል፡፡ ቫልዲስ ቪቮ በኩባ ውሥጥ ከዲፕሎማትነቱ ይልቅ በይበልጥ የሚታወቀው ግን በበርካታ መጻሕፍት ደራሲነቱ ነው፡፡ ከዋና ዋና ሥራዎቹም መካከል The Blind Blacks, The Brigade and the Mutilated Man, አጫጭር ታሪኮች ከደቡብ ቬትናም፣ የጫካ ውስጥ ኤምባሲ፣12 የቬትናም አጫጭር ታሪኮች፣ Angola: an end to Merceneries Myth የተሠኙት የሚገኙበት ሲሆን መጻሕፍቱ በስፓኒሽ ቋንቋ ታትመው በኩባና በሌላው ዓለም ተነብበውለታል፡፡ ቫልዲስ ቪቮ ስለ ኢትዮጵያ ማሰብ የጀመረው፣ ከባምቦዲያ የኩባ አምባሳደር ሆኖ ሲሰራ፣ ዐጼ ኃይለ ሥላሴ ካምቦዲያን በይፋ በጎበኙበት ጊዜ እንደነበር ያስታውሳል፡፡ ወደ ቬትናም ከተዘዋወረ ወዲህ ደግም በኢትዮጵያ ሕዝባዊ ተቃውሞ ተቀስቅሶ በስተመጨረሻም ለዐጼ ኃይለ ሥላሴ ከሥልጣን መውረድና ለዘውድ ሥርዓት ፍጻሜ ምክንያት ሲሆን በሩቅ ተመልክቷል፡፡ የታሪክ አጋጣሚ፣ አገሩን ኩባንና አፍሪቃዊቷን ጥንታዊ አገር ወንድማማች ሲያደርጋቸው ደግሞ በዚች አገር ይካሄድ የነበረውን ለውጥ በቅርብ ለመመልከት አስችሎታል፡፡

ቫልዲስ ወደ ኢትዮጵያ የመጣበት ትክክለኛ ጊዜን ለማወቅ ባይቻልም፣ ኩባ ያለማወላወል ከኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ጎን የቆመችበት ጊዜ ተደርጎ ከሚቆጠረው (ደርግ የውስጥ ተቃዋሚዎቹን በቤተ መንግሥት ከደመሰሰበት) ከጥር 26 ቀን 1969 ዓ.ም ወዲህ ይመስላል፡፡ ቫልዲስ በኢትዮጵያ ጉብኝቱ በዘመኑ አጠራር “አብዮቱ የመጣላቸው” የሚባሉት ጭቁኖችንና እና “አብዮቱ የመጣባቸው” የተሠኙትን ባላባቶችና አድሀሪዎችን ተመልክቷል፡፡ የወዳጅ አገር ከፍተኛ ባለሥልጣን እንደመሆኑም ስለአብዮቱና ስለ ለውጡ ይፋ ያልሆኑ መረጃዎችን ለመሰብሰብ ሳይችል አልቀረም፡፡ ቫልዲስ ቪቮ በኢትዮጵያ ጉብኝቱ ያገኛቸውን ጥቂት መረጃዎችና ምልከታዎች በመቀመርም፤ ስለ አብዮቱ በውጭ ተመልካቾች ከተጻፉት የመጀመሪያው ሊባል የሚችለውን መጽሐፍ እ.ኤ.አ በ1978 ዓ.ም (ኢትዮጵያ፤ ያልታወቀው አብዮት) Ethiopia: the Unknown Revolution በሚል ርእስ ኩባ ውሥጥ አሳተመ፡፡ ዘጠኝ ምዕራፎችና 147 ገጾች ያሉት ይህ መጽሐፍ መጀመሪያ የታተመው በስፓኒሽ ቋንቋ ሲሆን፤ በኋላ በኩባ የትርጉም ማዕከል ወደ እንግሊዝኛ ቋንቋ ተመልሶና ታትሞ ለሰፊው የዓለም አንባቢ ቀርቦ ነበር፡፡ ቫልዲስ ቪቮ ይህንን መጽሐፍ ባሳተመበት ጊዜ የኩባ ኮሙኒስት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የፓርቲው የውጭ ጉዳዮች ኃላፊ ነበር፡፡ “ያልታወቀው አብዮት” ከየካቲት 1966 ዓ.ም እስከ መስከረም 1967 ዓ.ም የነበረውን ጸረ ዘውድ ሕዝባዊ እንቅስቃሴ እንዲሁም ከለውጡ ወዲህ በነበሩት ሶስት “የአብዮት ዓመታት” ላይ አተኩሮ የተጻፈ መጽሐፍ ነው፡፡ ደራሲው ራሱ አብዮተኛ እንደመሆኑ በኢትዮጵያ የተፈጸሙ ድርጊቶችንና ኩነቶችን የተመለከተውና የተነተነው በዚያው ማርክሳዊ በሆነ መነጽር ነው፡፡ ይሁን እንጂ የአንድን አገር ርዕዮተ ዓለምም ሆነ መሪዎቿን በቅርብ ማወቅ ብቻውን ያንን አገር ለመረዳትም ሆነ ስለዚያ አገር ለመጻፍ አይጠቅምም፡፡ ቫልዲስ ቪቮም የዚህ ችግር ሰለባ ነበር፡፡

ስለ ኢትዮጵያ በሚያውቃቸው ጥቂት ነገሮች ላይ ብቻ ተመስርቶ መጽሐፍ ለመጻፍ በመነሳቱ የተነሳ፤በአገሪቱ በተካሄደው ሥር ነቀል የለውጥ ሂደት ውሥጥ ግልጽና በጣም መሠረታዊ የሆኑ ክስተቶችና ሐቆችን አዛብቶ ለማቅረብ ችሏል፡፡ ለምሣሌ ዐጼ ኃይለ ሥላሴ ከሥልጣን ወርደውበታል ተብሎ በመጽሐፉ የተገለጸው ሁናቴ ከእውነተኛው ታሪክ ጨርሶ የራቀ ነው፡፡ ቫልዲስ ቪቮ እንደሚለው፣ መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም ጃንሆይ ከሥልጣን መውረዳቸው የተገለጸላቸው መጀመሪያ ከቤተ መንግሥታቸው በሶስት ወታደሮች ወደ አንድ ጦር ሠፈር በቮልስዋገን መኪና ተወስደው አንድ ሰፊ ክፍል ውሥጥ ካረፉ በኋላ ነበር፡፡ እንዲሁም ሉሉ የተሠኘችው የጃንሆይ ለማዳ ውሻ የተቀበረችው በወርቅ ከታነጸ መቃብር ነበር ማለቱን፣ በተጨማሪም የቤተ መንግሥቱ መጸዳጃ ቤት መቀመጫ እና የጃንሆይ ብስክሌት ፍሬም የተሠራው ከንጹህ ወርቅ ነበር ብሎ ያለ ማስረጃ መጻፉ ከተራ የፕሮፓጋንዳ ጽሁፍነት ማለፍ የሌለበት ነበር፡፡ ደርግ የተሠኘው የንዑስ ወታደራዊ መኮንኖች ስብስብ፣ ባቀረቡት የተለየ አስተያየት ብቻ ያለ ፍርድ እየጨፈጨፈና እያረደ የትም የጣላቸውን ኢትዮጵያውያን አስመልክቶ ቫልዲስ በመጽሐፉ የሠጠው አስተያየት፣ ደርግን ለመደገፍ ሲል ከሠብዓዊ አስተያየትና ከሚዛናዊነት አምባ ምን ያህል እንዳፈነገጠ የሚጠቁም ነው፡፡ ደራሲው ይህንን አስተያየቱን የገለጠው “በአብዮቱ እንዲረሸኑ የተፈረደባቸው ከፍተኛ ሚኒስትሮችና ጀነራሎች ቁጥር በዐጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የነበሩ ባለመሬቶች (ባላባቶች) በአንድ ወር ይፈጇቸው ከነበረው ጭሰኞች ጋር ሲነጻጸሩ ቁጥሩ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም” በማለት ነበር፡፡ ደርግ፣ የሕዝባዊውን ፀረ ዘውድ ተቃውሞ አመራር መጀመሪያ በዘዴ፣ በኋላ ደግሞ በጉልበት ጠልፎ የሥልጣን ኮርቻን የተቆናጠጠ የወታደሮች ቡድን መሆኑ ቀርቶ ሕዝባዊውን አብዮት ያቀጣጠለ፣የመራና ለሥልጣን ያበቃ ልዩ አካል ተደርጎ በመጽሐፉ ቀርቧል፡፡ ይህም ኢትዮጵያውያን ከሚያውቁትና ከለመዱት የደርግ የጭካኔ ባሕሪና መልክ ፍጹም ርቆ የቀረበ አጉል ውዳሴ “የኢትዮጵያ አብዮት” ለተባለ ፊልም የተጻፈ ስክሪፕት ይሆን እንደሆነ እንጂ የታሪክ ማስታወሻ ተደርጎ ሊቆጠር የሚችል አይደለም፡፡ “ያልታወቀው አብዮት” ደርግን እና መሪዎቹን ያለ ተግባራቸውና ውሏቸው እያሞጋገሰ “የኢትዮጵያ አብዮትንም” ከዓለም ታላላቅ አብዮቶች ተርታ እያሰለፈ በጸዓዳ ሸራ ላይ ባማረ ቀለም ያሰማመራቸው ቢሆንም ከንቱ ውዳሴው ፈሩን ስቶ የደርጉን ሊቀመንበር ማስቀየሙ አልቀረም፡፡ ቫልዲስ ሊቀመንበሩን የማስቀየም ስሕተት የሠራው፣ የአብዮቱ ቀያሾች ናቸው ያላቸው የደርግ መሪዎች እንደሌላው አፍሪካ በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን የተቆናጠጡ ሳይሆኑ ብዙኃኑን፣ የተገፋውንና የታችኛውን መደብ የሚወክሉ እውነተኛ የአብዮት መሪዎች አድርጎ ለማቅረብ ሲሞክር ነበር፡፡

በተለይ ኮሎኔል መንግሥቱን ቅር ያሰኘው በመጽሐፉ ምዕራፍ ሁለት ከገጽ 30 እስከ 31 በሠፈረው አንቀጽ አንድ ሐረግ ላይ ነበር፡፡ የአንቀጹ ትርጉም እንዲህ ይነበባል፡፡ “[ቅድመ አብዮት] በኢትዮጵያ ማርክሲዝም ሌኒኒዝም ሥር ሰዶ ንቅናቄ ለመፍጠር ወይም ፓርቲ ለመመሥረት ባይችልም፤ የሶሻሊስት ፍልስፍና ሁለንተናዊነት ግን በጦር ሠራዊቱ መካከለኛው የመኮንኖች መደብ ለመዝለቅ ችሎ ነበር፡፡ ከመካከላቸው አንዱ፣ የባርያ ልጅ የሆነው፣ እጩ መኮንን ሳለ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ለትምህርት በተላከበት ጊዜ የዘር መድልዎ ሰለባ ሆኖ ነበር፡፡ ይህ መኮንን በቬትናም ስለተደረገው ጦርነት፣ ብዙኃን ጥቁሮችን ስላስቆጣው የዲትሮይት ተኩስ፣ እንዲሁም ስለ ተማሪዎች አመጽና ስለ ዋተር ጌት ቅሌት ጠንቅቆ ያውቅ ነበር፡፡ በዩናይትድ ስቴስት በነበረው ልምድ የተነሳ መንግሥቱ ኃይለማርያም አሁን ባለው ዓለም እየጨመረ ስለመጣው ከቁጥጥር ውጪ የሆነ አብዮት፣ አመጽና ግጭት ጥርት ያለ ምልከታ ሊኖረው ቻለ” ቫልዲስ በዚህ አንቀጽ “የባሪያ ልጅ” በማለት የጻፈው ሐረግ መንግሥቱ ኃይለማርያምን “እውነተኛ አብዮት የወለደውና” ከታችኛው መደብ የፈለቀ የሕዝብ ልጅ አድርጎ ለመግለጽ ፈልጎ እንጂ ሊቀመንበሩን ዝቅ ለማድረግ ወይም ለማዋረድ አስቦ እንዳልሆነ ግልጽ ነው፡፡ ከላይ የቀረበው አገላለጽም ለጓድ ሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለ ማርምምም ሆነ፤ በግዙፍ ሠሌዳ ላይ ምስላቸው በሥዕል ሲሰራ እንኳን ተፈጥሮ የሠጠቻቸው ገጽታ ተስተካክሎ እንዲሰራ ትዕዛዝ ለሚሰጡት ጓደኞቻቸው የሚዋጥ አልነበረም፡፡ መጽሐፉ በአንድ በኩል ይህ “ይቅር የማይባል እንከን” የሚታይበት ቢሆንም በሌላ በኩል ደግሞ ደርጋውያንን፣ መሪያቸውን እና የጠለፉትን አብዮት አለመጠን እያሞጋገሠ እና እያወደሠ ያቀረበ በመሆኑ የመጽሐፉን ሥም ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገቡ ከተከለከሉ የውጪ መጽሐፎች ዝርዝር ውሥጥ ለማስገባት አልተፈለገም፡፡ በመሆኑም “ዐሣውም እንያልቅ ውሃውም እንዳይደርቅ” እንደሚባለው፣ደርጋውያን ከመጽሐፉ ላይ “እንከኑን” የመንቀስ ሀሳብ መጣላቸው፡፡ ይህ ሐሳብ የመጽሐፉን ዝውውር ሳይከለክልና ስርጭቱን ሳያግድ ቅሬታ የፈጠረውን ሐረግ የሚያስወግድ በመሆኑ ተቀባይነት አገኘ፡፡ በዚህም መሠረት ወደ ኢትዮጵያ የገባው የ “ያልታወቀ አብዮት” ቅጂ አንድ በአንድ እየተገለጠ “የባሪያ ልጅ” የሚለው ሐረግ በጥቁር ቀለም ከተሠረዘ በኋላ መጽሐፉ ለሕዝብ እንዲሰራጭ ተደረገ፡፡ ይህ አስገራሚ ሥራ በደርጉ ዘመን ኢትዮጵያ ሐሳብን በነጻ የመግለጽ መብት ላይ የተጣለበት ገደብ ምን ያህል ጠንካራ እንደነበረ እና ሳንሱርም ለታተመ መጽሐፍም እንኳን ቢሆን እንደማይራራ ያስመሰከረ ታሪካዊ ክሥተት ነው፡፡ ደርጎች ሳንሱርን አንድ እርምጃ ወደፊት በማራመድ በመጽሐፍት ሕትመት ታሪክ ውሥጥ ያልታየ አዲስ የሐሳብ ጭቆና ድርጊት የሆነውን ድሕረ ሕትመት ሳንሱር ለዓለም በማስተዋወቃቸው ታሪክ ያስታውሳቸው ይሆናል፡፡ ቫልዲስ ቪቮ በመጽሐፉ ላይ የተደረገበትን ድሕረ ሕትመት እርማት ያወቀው አይመስልም፡፡

መጽሐፉ ከታተመ በኋላ ወደ ኢትዮጽያ በመጣበት ጊዜ ግን ሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለማርያም ሊያነጋግሩት ስላልፈቀዱ ሳያገኛቸው ወደ አገሩ መመለሱ ታውቋል፡፡ ምንም እንኳ በኢትዮጵያ ስለተካሄደው አብዮት በውጭ ተመልካቾች ከተጻፉት መጻሕፍት ውሥጥ የቫልዲስ ቪቮ ሥራ ቀዳሚ ቢሆንም ሐቅ፣ ሚዛንና ገለልተኝነት ተዛብተውና ተጣመው የቀረቡበት በመሆኑ ሥራዉ የታሪክ መጻሕፍትን መስፈርት ቀርቶ የጋዜጣ መጣጥፍን ሚዛን የሚደፋ መስሎ አይታይም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ “ያልታወቀው አብዮት” ሲታተም በኢትዮጵያ የተካሄደው ለውጥ ገና ሶስት ዓመት እንኳን ያልሞላው በመሆኑ፣ እንቅስቃሴው በመላ አገሪቱና በሕዝቧ ላይ ያመጣውን ለውጥ ለመገምገም ጊዜው በጣም አጭር ነበር፡፡ እንዲያውም ቫልዲስ ቪቮ መጽሐፉን ባቀረበበት ጊዜ፣ ደርግ የተነሳበትን ተቃውሞ ለማዳፈን በኢትዮጵያ ታይቶ የማይታወቅ አዲስ የጅምላ ጭፍጨፋ ታሪክ የሚሰራበት ጊዜ ስለነበር ቆም ብሎ ለውጡን ለመገምገም የሚያስችል ስክነት በአገሪቱ በጭራሽ አልሰፈነም ነበር፡፡ በተጨማሪም ደራሲው ክስተቶችን ከሶሻሊስት አብዮት አንጻርና በማርክሲስት ርዕዮት መነጽር ብቻ ማየቱ የአመለካከት አድማሱን እንደገደበበት በመጽሐፉ ከቀረቡ ቁንጽል፣ የተጋነኑና ሐሰተኛ ታሪኮች መረዳት ይቻላል፡፡ የመጽሐፉ ሚዛን አጋድሎ ለተጻፈለት ለደርጉም ቢሆን ታሪኩ ለስላሳና ያማረ ግምጃ እንዳልሆነለት፣ መጽሐፉ ታትሞ ኢትዮጵያ ውሥጥ ከገባ በኋላ የደረሰበት ድህረ ህትመት ሳንሱር ታላቅ ማስረጃ ነው፡፡

Read 7635 times Last modified on Saturday, 19 January 2013 15:24