Saturday, 19 January 2013 14:58

“ደስታ መንደር ...”

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ (ከኢሶግ)
Rate this item
(1 Vote)

ለዚህ እትም በርእስነት የቀረበው ...ደስታ መንደር... የአንድ መንደር መጠሪያ ነው፡፡ መንደሩ ከአዲስ አበባ ወደ 17/ ኪሎሜትር የሚርቅ ሲሆን ታጠቅ እየተባለ በሚጠራው ገፈርሳ መኖ በሚባለው አካባቢ የተመሰረተ ነው፡፡ የዛሬ 53/ አመት ገደማ ዶክተር ሄግ እና ዶ/ር ካትሪን ሐምሊን የተባሉ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስቶች ወደኢትዮጵያ ለስራ መጡ፡፡ እነዚህ ባልና ሚስት በኢትዮጵያ ሳሉ በወሊድ ምክንያት ሴቶች ፌስቱላ የተባለ ከፍተኛ የሆነ የጤና ጉዳት ሲደርስባቸው ለመመልከት ቻሉ፡፡ ስለዚህም እነዚህ ባልና ሚስት አንድ ነገር ወሰኑ፡፡ እሱም በኢትዮጵያ የፌስቱላ ታማሚዎችን በደንብ ማከም የሚያስችል ተቋምን መመስረት ነበር፡፡

በውሳኔያቸው መሰረትም በአዲስ አበባ ሐምሊን ፊስቱላ ሆስፒታልን መስርተው እነሆ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ መስተዳድሮችም ቅርንጫፍ ሆስፒታሎች ተከፍተው አገልግሎቱ በመሰጠት ላይ ናቸው፡፡ ፌስቱላ የሚከሰተው ሴቶቹ በምጥ ወቅት በፍጥነት ወደሐኪም ቤት ሳይደርሱ ለቀናት በመሰቃየት ምክንያት በሚፈጠር የአካል መቀደድ ምክንያት ሽንትን ያለመቆጣጠርና የመሳሰሉት ችግር ሲገጥማቸው ነው፡፡ ዶ/ር ሄግ ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን ሚስታቸው ዶ/ር ሐምሊን ካትሪን ግን እስከዛሬም ድረስ ታካሚዎችን በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡ ለዛሬው እትም ለንባብ ያቀረብነው ደስታ መንደር የተሰኘውን በሐምሊን ሆስፒታል አማካኝነት የተመሰረተውን መንደር ሁኔታ ነው፡፡ በሐምሊን ፌስቱላ ኢትዮጵያ የመንደሩ ስራ አስኪያጅ የሆኑትን ወ/ሮ በለጥሻቸው ታደሰን ለዚህ እትም ጋብዘናል፡፡ ኢሶግ/ ደስታ መንደር ማለት ምን ማለት ነው? ስ/አ ደስታ መንደር ማለት በፊስቱላ ሕመም ምክንያት የተሰቃዩ እና ለተወሰነ ጊዜ ወይንም ለዘለቄታው የሀኪም ክትትል ያስፈልጋቸዋል የተባሉ ችግሩ ጠባሳ ትቶባቸው ያለፉ ሴቶች የሚቆዩበት ነው፡፡ ደስታ መንደር ሲባልም በዚህ መንደር እስከአሉ ድረስ ተስፋ የሚፈነጥቅላቸው ስለሌላ ነገር ወይንም ችግር ሳያስቡ ኑሮአቸውን በደስታ ሞልተው ስለቀጣይ ሕይወታቸው በማቀድ እንዲኖሩ የሚፈለግበት እና ጥረት የሚደረግበት ነው፡፡ ኢሶግ/ የፌስቱላ ታማሚዎች በሕክምናው ሙሉ በሙሉ መዳን ይችላሉን? ስ/አ የፌስቱላ ታማሚዎች ሙሉ ለሙሉ የሚድኑ ቢኖሩም ግን ሁሉም መቶ በመቶ ይድናሉ ማለት አይቻልም፡፡

በእርግጥ አንዳንዶች ታክመው ድነው ወደመጡበት ሕብረተሰብ የሚመለሱ ሲሆን አንዳንዶቹ ደግሞ ጭርሱንም ከሐኪም እርቀው መኖር የማይችሉ ይሆናሉ፡፡ ከ 4-5 ኀየሚሆኑት የፌስቱላ ታካሚዎች በምጥ ወቅት በጣም የተጎዱ ስለሚሆኑ ሊድኑ አይችሉም፡፡ ስለዚህ ከውስጥ አካላቸው ውጭ የሆነ ለመጸዳዳት የሚያገለግል የላስቲክ ቦርሳ ከሰውነታቸው ጋር ተያይዞ እንደሽንት የመሳሰለውን እንዲቀበሉበት ይሆንና በሕይወት እስከአሉ ድረስ እራሳቸው እየፈቱ እየገጠሙ እንዲገለገሉበት ከልብሳቸው ስር ይቀመጣል፡፡ ይህንን አይነት ሕክምና የሚሰጣቸው ሴቶች ወደመጡበት መንደር ተመልሰው እንዲሄዱ አይመከርም፡፡ ምክንያቱም የሽንት መቀበያውን ቦርሳ ሲያወጡ ሲያስገቡ ኢንፌክሽን ሊፈጠር ከመቻሉም በላይ የሚቀላቀሉት ሕብረተሰብ ሁኔታውን በምን ደረጃ እንደሚቀበለው ስለማይታወቅ የመገለል እጣ ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በገጠር ያለው የአኗኗር ዘዴ ለእንደዚህ ያሉ ታካሚዎቸ አመቺ ባለመሆኑ የበለጠ ጉዳት ሊደርስባቸው እንደሚችል ይገመታል፡፡ ከምንም በላይ ግን ከሕክምናም እርቀው እንዲሄዱ አይመከርም፡፡ ኢሶግ / በከፍተኛ ሁኔታ የታመሙትን ሴቶች ለዘለቄታው ለመርዳት ምን እርምጃ ተወሰደ? ስ/አ እነዚህ ከ4-5 ኀየሚሆኑ በከፍተኛ ደረጃ የህክምና እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሴቶች በየአመቱ ቁጥራቸው እየጨመረ ሲሄድ ለሆስፒታሉ መስራች ሐምሊን ካትሪን እና አብረዋቸው ለሚሰሩ ባልደረቦች አሳሳቢ ነበር፡፡ በእርግጥ ስልጠና እየተሰጣቸው በሆስፒታሉ ውስጥ የተለያዩ ስራዎችን እንዲሰሩ ቢመቻችም ከአመት አመት ቁጥራቸው እየጨመረ ሲመጣ የስራ እና የስልጠና ቦታው ግን በቂ ሊሆን አልቻለም፡ ፡ በዚህም ምክንያት ሁኔታውን ለመንግስት ማመልከት ግዴታ ነበር፡፡ መንግስትም ችግሩን ተረድቶ ከአዲስ አበባ 17/ ኪሎ ሜትር እርቀት ገፈርሳ መኖ ቀበሌ ላይ 60/ ሄክታር መሬት ሰጥቶ የዛሬ 9/ አመት የደስታ መንደር ተመሰረተ፡፡

ኢሶግ/ ይህ የደስታ መንደር ዘለቄታዊ መኖሪያ ነውን? ስ/አ የደስታ መንደሩ ስራ ሲጀምር በእርግጥ ታስቦ የነበረው ለዘለቄታው ተጎጂዎች እንዲኖሩበትና እንዲቋቋሙበት ነበር ፡፡ ነገር ግን ሰዎችን በተቋም ደረጃ ነጥሎ ማኖር ትክክል ካለመሆኑም በላይ ሰዎቹ እራሳቸውን መርዳትና ኑሮአቸውን መመስረት እንደሚገባቸው እንዲሁም በሕመሙ ምክንያት በቀጣይነት ለሚመጡት ሴቶች ቦታ መልቀቅ እንዳለባቸው ይታመናል፡፡ በእርግጥ የሚፈለገው ነገር ከሆስፒታል እንዳይርቁና ክትትል እንዲደረግላቸው ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ ለመጸዳጃ የሚገለገሉበት የላስቲክ ቦርሳ በየሳምንቱ ይሰበሰባል፡፡ ከሕክምናው ጋር በተያያዘ የሚኖረውን የደም ግፊት እንዲሁም የኩላሊት የመሳሰለውን ጤናቸውን እንዲከታተሉ ከማድረግ አንጻር የጤና ሁኔታቸው እስኪስተንከል እና ጎን ለጎንም ስልጠናቸውን እስኪያጠናቅቁ የሚቆዩበት መንደር ነው፡፡ በእርግጥ ለዘለቄታው እንዲኖሩ የሚወሰንላቸው ጥቂት ሴቶች ይኖራሉ፡፡ ኢሶግ/ ለዘለቄታው በመንደሩ የማይኖሩት ምን ድጋፍ ደረግላቸዋል? ስ/አ አንዲት ሴት ደስታ መንደር ስትመጣ በቀጥታ መደበኛ ወደ አልሆነው የጎልማሶች ትምህርት እንድትገባ ይደረጋል፡፡ ትምህርቱም አምስት ሞዱሎች አሉት፡፡ 1/ እራራሴንና ችግሬን ማወቅ፣ 2/ የህይወት አማራራጮች፣ 3/ እስቲ ልሞክረው፣ 4/ የህይወት ክህሎት፣ 5/ የንግድ ክህሎት እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት አምስት ሞዱሎች ለፌስቱላ ታማሚዎች የተዘጋጁ ናቸው፡፡

የረጅም ጊዜ ወይንም ለዘለቄታው ከህክምናው መራቅ የለባቸውም የተባሉ የፌስቱላ ታማሚዎች በደስታ መንደር ገብተው ይህንን ስልጠና ለመጨረስ በትንሹ እስከ አንድ አመት ተኩል ድረስ ጊዜ ይወስድባቸዋል፡፡ በደስታው መንደር ቁጭ ብለው በሚማሩበት ጊዜ ሙሉ ወጪዋን ሐምሊን ፌስቱላ ሆስፒታል ይሸፍናል፡፡ ኢሶግ/ ፌስቱላ ታማሚዎች ስልጠናውን ሲጨርሱ ቀጣዩ ሂደት ምን ይመስላል? ስ/አ ማንኛዋም በደስታ መንደር እንድትቆይ የተደረገች ሴት አንድ አመት ተኩል ያህል ስልጠናውን ከወሰደች በሁዋላ ተግባራዊ ልምምድ እንድትቀጥል ይደረጋል፡፡ ተግባራዊ ልምምዱም በግቢው ውስጥ ባሉት የዶሮ...ከብት እርባታ..ካፌ እና የጉዋሮ አትክልት በመሳሰሉት ስራዎች ላይ እንድትሳተፍ እና በወደፊቱ ሕይወትዋ የትኛውን መርጣ እንደምትሰማራ የእራስዋን ምርጫ ጠብቀን የማቋቋም ስራ እንሰራለን፡፡ በልብስ ስፌት ወይንም በጥልፍ ስራ መሰማራት ለሚፈልጉ ሁኔታዎች ተመቻችተው ስልጠና እየተሰጠ ነው፡፡ ባጠቃላይም በየትኛው ዘርፍ የበለጠ ውጤታማ ትሆናለች የሚለውን እና በሰልጣኝዋ በእራስዋ ፍላጎት ለማቋቋም ከክልሉ መስተዳድር መሬት እየተሰጠን እንዲሰማሩ በማድረግ ላይ ነን፡፡ ለምሳሌ... በግብርናው ዘርፍ የከብት ማርባት ስራ የጀመሩ አሉ፡፡ እንዲሁም የካፌ ስራ መስራት ለሚፈልጉም የኦሮሚያ ክልል ቦታ ሰጥቶን ያስጀመርናቸው አሉ፡፡ በደስታ መንደር ውስጥ ባለው ካፌም የሚሰሩት እነዚሁ ሴቶች ናቸው፡፡ ሁለት ሴቶችም የልብስ ስፌት ስራን እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ ኢሶግ/ ከደስታ መንደር ወጥተው በህብረተሰቡ ውስጥ ተደባልቀው ኑሮ የሚመሰርቱ ይገኛሉን? ስ/አ በእርግጥ ለሕክምናው ቅርብ እንዲሆኑ ሲባል በዚህ መንደር ሰልጥነው በዚሁ መንደር ወይንም በየመስተዳድሩ የፌስቱላ ሐኪም ቤቶች እና አካባቢያቸው ላይ ብቻ በስራ ይሰማራሉ ማለት አይደለም፡፡

ከባድ የሆነ የስራ ጫና በሌለበት ሁኔታ ...ለምሳሌ ከባድ እቃን መሸከም ወይንም ቀና ጎንበስ የሚያደርግ እንደቁፋሮ ያለ ስራ በሌለበት ሁኔታ ሌላውን የእለት ተእለት እንቅስቃሴ እያደረጉ ኑሮአቸውን የመሰረቱ አሉ፡፡ ከዚህ ወጥተው ትዳር የመሰረቱም ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ሴቶች በከፍተኛ ደረጃ ጥንቃቄ ማድረግ ያለባቸው በመውለድ ሁኔታ ላይ ነው እንጂ ወሲብን በመፈጸም ረገድ ብዙም ችግር የለባቸውም፡፡ በእርግጥ እንደጉዳታቸው አይነት ነገሮች እንደሚለያዩ መገመት አያስቸግርም፡፡ ነገር ግን በምንም ምክንያት ያለሐኪም እርዳታ ለመውለድ ማሰብ አይጠበቅባቸውም፡፡ ዋናው ከእነሱ የሚፈለገው ነገር ከሕክምናው አለመራቅ ነው፡፡ በእርግጥ በከፍተኛ ሁኔታ የተጎዱት ሴቶች ከሕክምናው ብቻም ሳይሆን ከመንደሩም እርቀው እንዲኖሩ አይፈቀድም፡፡ ኢሶግ/ የደስታ መንደር በ9/ አመት ጊዜው ምን ያህል ሴቶችን ተቀብሎ አስተናግዶአል? ስ/አ ቀጣይነት ላለው የህክምና ክትትል ወደ ደስታ መንደር የሚገቡ ሴቶች ከአመት አመት ቁጥራቸው ቢለያይም ከተቋቋመ እና ስራ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ወደ መቶ የሚሆኑ ሴቶችን ተቀብሎ አስተናግዶአል፡፡ እነዚህን ሴቶችም በማሰልጠን ለተለያዩ ክህሎት ብቁ እንዲሆኑ በማድረግ ከአንድ አመት ተኩል ጊዜያቸው ጀምሮ እንደአቅማቸው በአዲስ አበባና በየመስተዳድሩ ባሉ የፌስቱላ ሐኪም ቤቶች እንዲሁም በኮሌጁ ባሉ የስራ እድሎች እንደችሎታቸው ተቀጥረው የሚሰሩ ሲሆን በተጨማሪም በግላቸው በንግድና በመሳሰሉት ስራዎች ተሰማርተው የሚኖሩ መጠነኛ ቁጥር ያላቸው ሴቶች አሉ፡፡

Read 4899 times