Saturday, 19 January 2013 14:38

“የተበላሸውን ለማስተካከል ያልተበላሸውን እንጠብቅ”

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(1 Vote)

በገና በዓል ዋዜማ ወደተለያዩ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች፣ ሆስፒታሎች፣ ባንክ ቤቶች፣ ትምህርት ቤቶች … የሄዱ ሰዎች በዋናው መግቢያ በር ወይም በእንግዳ መቀበያ ክፍል ቀልባቸውን የሳበና በተለያየ አንፀባራቂ ነገሮች የተጌጠ የገና ዛፍ ስለማየታቸው በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡ ወቅትን ጠብቀው የልብስ አሰቃቀላቸውን የሚያሳምሩት ቡቲኮችም የገና አባትን ልብስ ሰቅለው በብዛት ታይተዋል፡፡ በመስቀለኛ መንገዶች ቀይ መብራት ያስቆማቸው መኪኖች ስር እየተሽለኮለኩ "የአባባ ገና"ን ልብስ ለብለው ተመሳሳዩን ግዙን የሚሉ ወጣቶችም ቁጥራቸው ጥቂት የሚባል አልነበረም፡፡
ባለፈው ሳምንት ባየው ነገር የተገረመ አንድ የሥራ ባልደረባዬ ትዝብቱን የገለፀው "አባባ ገና እማማ ገናን እየጨቆናት ነው" በሚል ነበር፡፡
ድንቅ ነው፣ ልዩ ነው፣ በሌሎች ዘንድ አይገኙም … የሚባሉትና ኢትዮጵያዊ መልክ ካላቸው የበዓል አከባበሮች መካከል አንዱ የገና በዓል ነበር፡፡ በአዲስ አበባና በአንዳንድ ከተሞች የሚታየው ጅማሬ መላ አገሪቱን ይወክላል ማለቱ ቢከብድም በመዲናችን እየታየ ያለው የገና በዓል አከባበር ግን "አባባ ገና" ያሳደረብን ተጽዕኖ ከባድ መሆኑን ጠቃሚ ነው፡፡
በተቃራኒው ደግሞ ዛሬ የምናከብረው የጥምቀት በዓል አገራዊ የአከባበር መልክና ሥርዓቱን እንደያዘ አሁን ላይ ከመድረሱም ባሻገር በተለይ የብሔር ብሔረሰብ አልባሳትን በመልበስ ወጣቶች በማንነታቸው እንደሚኮሩ ማሳያ መድረክ እየሆነም መጥቷል፡፡ ባለፉት ዓመታት በተደጋጋሚ እንደታየው በየጥምቀተ ባህሩ በተለያዩ ብሔረሰቦች ባህላዊ አልባሳትና የፀጉር አሰራር አጊጠው ለበዓሉ ተጨማሪ ድምቀት እየፈጠሩ ያሉ ወጣቶች ቁጥር እየተበራከተ መጥቷል፡፡
በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ በሚከበሩት በሁለቱ በዓላት ውስጥ የሚታየው እውነት በተቀላቀለ መስመር ላይ መሆናችንን ያሳያል፡፡
በአንድ በኩል በማንነት መኩራትና ማንነትን የማስጠበቅ ተግባር ሲታይ፤ በሌላ ጎን የራስን ጥሎ የሌላውን የማንሳት ፍላጎት ይንፀባረቃል፡፡
በተቀላቀሉት ነገሮች ውስጥ ባለው ትግል ማንኛው ያሸንፋል? አሸናፊው ምን ጠቃሚ ነገር ያስገኝልናል? የሚያስከትልብን ጉዳትስ ምንድነው? በትግሉ ተሸንፎ ከሚጠፋውስ ምን ጠቃሚና መልካም ነገርን እናጣለን? የሚሉ ጥያቄዎች ያስነሳሉ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሴቶች፣ የህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ የሰራውን ጥናት ሰሞኑን ይፋ አድርጓል፡፡ "መጤ ባህሎችና ልማዳዊ ድርጊቶች በአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በተለይም፤ በወጣቶችና ሴቶች ላይ እያስከተለ ያለው አሉታዊ ተፅዕኖ" በሚል ርዕስ በቀረበው ጥናት ላይ የመገናኛ ብዙኃንና የኪነጥበብ ባለሙያዎች ለሁለት ቀናት እንዲወያዩበት ተደርጓል፡፡
ጥር 3 ቀን 2005 ዓ.ም በራስ ሆቴል በተሰናዳው መድረክ ላይ የጥናቱ ባለቤትና በሥራው የተሳተፉ ባለሙያዎች ስለ ባህልና ልማድ ምንነት፤ መጤ ልማድና ባህሎች በማህበራዊ፣ ስነልቦናዊ፣ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ስለሚያስከትሉት አደጋ፤ለመጤ ድርጊቶች መስፋፋት ግሎባላይዜሽን፤መገናኛ ብዙኃንና የመረጃ መረቦች ስላላቸው አስተዋጽኦ፤በተለያየ አተገባበር ተፈፃሚ የሚሆኑት መጤ ልማድና ባህሎች በአሁኑ ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ እየታየ እንዳለና ችግሩን ለመከላከል ያሉት ዕድልና አማራጮች ምን እንደሆኑ ባለሙያዎቹ ማብራርያ ሰጥተውበታል፡፡
መጤ ባህልና ልማዶች በአዲስ አበባ ከተማ ከመስፋፋቱ ጋር በተያያዙ ሱስ አስያዥ ዕፅ ተጠቃሚው መበራከቱን፣የቀንና የምሽት የራቁት ጭፈራ ቤቶች መብዛታቸውን፣ ግብረሰዶማዊነት መስፋፋቱን፣ "እኔን ይመቸኝ እንጂ ለሌላው ግድ የለኝም" የሚል የግለኝነት ስሜት እየጨመረ መምጣቱንና ሌሎች መሰል ችግሮች ዙሪያ ገለፃ ከተሰጠ በኋላ መድረኩ ለአስተያየትና ጥያቄ ክፍት ሆነ፡፡
"ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ" የሚለውን ብሂል አስቀድመው አስተያየት መስጠት የጀመሩት የማስታወቂያ ባለሙያው አቶ ውብሸት ወርቃለማሁ ነበሩ፡፡ የግብረ ገብ ትምህርት መቋረጡ ለችግሮቹ መከሰት አንድ ምክንያት መሆኑን የጠቀሱት አቶ ውብሸት፣ብዙ ዜጎቻችን የኤችአይቪ/ኤድስ ሰለባ ከሆኑ በኋላ ጥናቱ ተሰርቶ የቀረበው መንግሥት ወይም የሚመለከታቸው አካላት የት ከርመው ነው? የሚል ጥያቄ አንስተዋል፡፡
በጥናቱ ወረቀት የቀረበው ቀደም ብለን እንሰማው የነበረን ጉዳይ ነው ያሉት አቶ ውብሸት ወርቃለማሁ፣የነገ አገር ተረካቢ ወጣት ትውልድን ለመታደግ እንዲህ ዓይነት ጥናት፣ የተግባር እንቅስቃሴና እሳት የማጥፋት ሥራ በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን ናዝሬት፣ ሐዋሳ፣
ባህርዳርና በመሳሰሉት ከተሞችም በአፋጣኝ ተግባራዊ እንዲሆኑ አሳስበዋል፡፡
"ለችግሩ መፍትሔ የሚሰጥልን ማነው ብለን በተጨነቅንበት ሰዓት፤ የዘገየ ቢሆንም ይህ ጥናት መሰራቱ አስደሳች ነው" በማለት ንግግር የጀመረው ደግሞ ጋዜጠኛ በፍቃዱ አባይ ነው፡፡
"ማርፈድን ባላበረታታም ከመቅረት ማርፈድ ይሻላል" እንደሚባለው ዘግይቶ የቀረበው ጥናት፣ ሕብረተሰባችን እየተፈራራ እንዲሄድ ያደረጉትን ችግሮች ይቀርፉለታል" በሚል ምሳሌዎችን ሲያቀርብ "ዛሬ ጋብቻ ለመመሥረት ፍርሐት ላይ ባንወድቅም ልጅ መውለድ ግን የብዙዎች ፍርሐት ሆኗል፡፡ በቀድሞ ዘመን ልጅን ለጎረቤት በአደራ ሰጥቶ የመሄድ መልካም ባህል ነበር፡፡
ዛሬ ልጄን ጠብቅልኝ ብሎ ለጎረቤት የሚሰጥ ሰው ካለ፣ልጄ ምንም ሳይሆን መልሼ አገኘሁ ይሆን? ከሚል ፍርሃትና ስጋት ጋር ነው፡፡"
የመንግሥት መዋቅርና የልማት አካሄድ ሰውን ትኩረት ያደረገ አይመስልም ያለው ጋዜጠኛው፤ መገናኛ ብዙኃን የሕብረተሰቡን የእኔነት ስሜት ሲገድሉ ይታያል፡፡ ማንቼና አርሴ ለእኛ ሕብረተሰብ ምንድን ናቸው? ሲልም ጠይቋል፡፡ ሕብረተሰቡ ማንነቱን እንዲያጣ የከበቡት ችግሮች በጥናት ወረቀት ከቀረበውም በላይ ሰፊና ጥልቅ ነው ያለው ጋዜጠኛ በፍቃዱ፣ ተተርጉመው እየቀረቡልን ያሉት የፍልስፍና መፃሕፍት አስተሳሰባችንን እያናጉትና ብዙዎችን የትም ወድቀው እንዲቀሩ እያደረጉ መሆኑን ገልጿል፡፡
የመፃሕፍት የፊት ገፅ ሽፋን የሴቶችን እርቃን ገላ የሚያሳይ መሆኑ፣ ስለ መሳሳም ጥበብ፤ ሴትን በፍቅር ስለማንበርከክ፤ የወንዶችን ትኩረት ስለመሳብ ችሎታ … በሚል የሚቀርቡት መፃሕፍትም የከበበን አደጋ አንዱ ማሳያ ናቸው ያለው ጋዜጠኛው፣ "ሕብረተሰቡ ይሄ የእኔ ጉዳይ አይደለም ብሎ ራሱን እስኪከላከል ድረስ የሚጠብቀው ያስፈልገዋል" ብሏል፡፡ የማስታወቂያ ባለሙያው አቶ ተስፋዬ ማሞ በበኩሉ፣ በኑሮ አስገዳጅነት ብዙ ወላጆች በቀን ከ12 ሰዓት በላይ በሥራ ላይ ከመቆየታቸው ጋር በተያያዘ የወላጆች ከልጆቻቸው ጋር የመገናኘት ዕድል እየጠበበ መምጣቱን የራሱን ገጠመኝ ሲያቀርብ "በሳምንቱ ውስጥ ልጆቼን የማገኝበት ጊዜ ስደምረው ከ20 ሰዓት እንዳማይበልጥ አስተውያለሁ" ካለ በኋላ ትውልዱ ልዩ ጥበቃ እንደሚያስፈልገው ጠቁሟል፡፡
ካፒታሊዝም ሁሉንም ነገር እየሸጠ ሁሉንም ነገር የሚያጠፋ ሥርዓት ነው ያለው አቶ ተስፋዬ፣ በስመ ኢንተርናሽናል ሥም በከተማችን እየተስፋፉ የመጡት ትምህርት ቤቶች አንዱ የችግር ምንጭ ሆነዋል ብሏል፡፡ ለዚህ ችግር ከመንግሥት ባልተናነሰ ማህበራዊ ኃላፊነትን መሸከም የሚችል የኪነ ጥበብና የመገናኛ ብዙኃን ያስፈልጋል፡፡ ሕብረተሰብ ተለይቶ የማይታወቅ ነገር ስለሆነ የወላጆች ካውንስል በአገር አቀፍ ደረጃ በማቋቋም መንግሥት ሕጉ እያለ ማህበረሰቡን መከላከል ያልቻለበትን ምክንያት መሞገት ይኖርባቸዋል ብሏል፡፡
"የተበላሸው ነገር ብዙ ነው፡፡ ያልተበላሸው ነገራችንን ለማዳን ብንሰራ የሚል ሀሳብ አለኝ" ያለችው የኢትዮጵያ ሴት ደራሲያን ማህበር ፕሬዚዳንት ወ/ሮ የምወድሽ ስዩም በበኩሏ፣ በዚህ ዓላማ መሰረት እሷ የምትመራው ማህበር ስላከናወናቸው ተግባራት፤ በተመሳሳይ ርዕሰ ጉዳይና ገጠመኞቿ ዙሪያ እርሷም በግሏ ስላከናወነቻቸው ተግባራት ማብራሪያ ከሰጠች በኋላ፣ ስለ ኒውዮርክ ያቀረበችው ምሳሌ እኛስ ወዴት እየሄድን ነው? የሚያስብል ነው፡፡ "ኒውዮርክ በዓለማችን ትንሿ የሲኦል ምሳሌ ናት፡፡ አገሪቱ እናትና ልጅ ባል የሚቀማሙባት በመሆኗ ክስተቱ የውይይት ርዕሰ ነገር ሆኖ በቶክ ሾው ይቀርባል፡፡ ባል ሴት ፍለጋ፣ ሚስት ወንድ ፍለጋ አገልግሎቱን ወደሚሰጡ ተቋማት በሄዱበት ይገናኛሉ፡፡ በእኛስ አገር አሁን የሚታየው ጅማሬ በዚያ ደረጃ አያድግም ወይ?" ብላለች - የምወድሽ፡፡
አርቲስት ፈለቀ ጣሴ በበኩሉ፣ "ከጥቂት ዓመታት በፊት በትምህርት ቤቶች ግቢ መኖሪያ ቤት ያላቸው ሰዎች ጠላ ንግድ መጀመራቸው አነጋጋሪ ነበር። ዛሬ የዕፀ-ፋሪስ ተጠቃሚዎች መበራከት መነጋገሪያ ሆኗል፡፡
የዛሬ 20 ዓመትም በአዲስ አበባ ከተማ የእርቃን ዳንስ ቤቶች ነበሩ፡፡ልዩነቱ አሁን ተበራክተዋል፡፡

በጥናት ከቀረበው በላይ የግል ሚዲያዎች በችግሩ ዙሪያ በስፋት ሰርተዋል፡፡ ከእናንተም በተሻለ እነሱ መረጃው አላቸው፡፡ ዕፀፋሪስ በመርፌ የሚወሰድባቸው አካባቢዎች አሉ። የእናንተ ጥናት ይህንን የደረሰበት አይመስልም፡፡ በጥናታችሁ የተቀመጠው የሱስ አስያዥ ስሞችና የመሸጫ ዋጋ አሁን በከተማው ካለው ጋር በጣም ይለያያል። ከዚህ ችግር ጋር በተያያዘ በተለያየ ጊዜ ሕግና መመሪያዎች ወጥተዋል። ሕጉ ግን ችግሩን ሲቀርፍ ሳይሆን ሕግ አስፈፃሚዎችን ሲጠቅም ነው የታየው" ብሏል፡፡
ከፊልም ሰሪዎች ማህበር የመጡት አቶ ደሳለኝ ኃይሉ፣የዓለም ኀያላን መንግሥታት ዛሬ በኢኮኖሚ ያልበለፀጉ አገራትን የሚወሩት እንደ ቀድሞ ዘመን ጦር በማዝመት ሳይሆን በቴክኖሎጂ ውጤቶች መሆኑን እንደማሳያ ያቀረበው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን መመልከት ትቶ ወደ ዲሽ ስርጭቶች ትኩረት ያደረገውን ሰው ብዛት በመጥቀስ ነው። ስለዚህ የመንግሥት ትኩረትም ሆነ ልማት ሰውን ማዕከል ያደረገ መሆን አለበት ሲል አስተያየቱን አቅርቧል፡፡ ጥናቱን ያሰራውና መድረኩን ያሰናዳው ቢሮ፤ችግሮቹን ለመቅረፍ ከማንም በተሻለ የኪነጥበብና የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ትልቅ ሚናና ድርሻ ይኖራቸዋል በሚል እምነት መድረኩን ማሰናዳታቸውን በማጠቃለያቸው አስምረውበታል - አቶ ደሳለኝ፡፡ ደራሲና ጋዜጠኛ የምወድሽ ስዩም "የተበላሸውን ለማስተካከል ያልተበላሸውን እንጠብቅ" እንዳለችው በእጅ ያለውን ወርቅ ማክበር በኋላ ከመቆጨት ያድናል፡፡
አባባ ገና ጭቆና የደረሰባት እማማ ገናን ነፃ ለማውጣት ብዙ ሥራ ይጠይቃል፡፡ የአባባ ጥምቀት ጭቆና ያላረፈባት እማማ ጥምቀትን መጠበቅ ግን ያን ያህል ከባድ አይደለም፡፡ በየጥምቀተ ባህሩ በብሔር ብሔረሰብ ልብሶቻቸው ተውበው የሚመጡትን ወጣቶች ማድነቅ ተገቢ የሚሆነውም ለዚህ ነው፡፡ መልካም የጥምቀት በዓል!

Read 3992 times