Saturday, 19 January 2013 11:48

ኢትዮጵያዊ መልኮች በአሜሪካ

Written by  ጽዮን ግርማ tsiongir@gmail.com
Rate this item
(6 votes)

መልክአ ኢትዮጵያ ፩

ከከተማ ወጣ ካልኩ ጥሬ ሥጋ አሊያም ጥብስ መብላት ያስደስተኛል፡፡ ይኸው ዛሬ ከአዲስ አበባ ወጥቼ የሚያስጐመዥ ምርጥ ሥጋ እያወረድኩ ነው፡፡ ብቻዬን ግን አይደለሁም፤ ሶምሶን ከተባለው ዘመዴ እና መላኩ ከሚባለው ጓደኛው ጋር ነኝ፡፡ ጥሬ ሥጋ ደስ የሚለው ከሰው ጋር ስብስብ ብለው ሲበሉት ነው፡፡ ሳሚ የሥጋ ቤቱ ደንበኛ ስለሆነ ለዘመድ የሚሆን ምርጥ ሥጋ ነው ያስቆረጠልን፡፡ ሥጋው ለስላሳ ነው፤ ጣዕሙ ደግሞ የጉድ ነው፡፡ መላኩ ቶሎ በልተን እንድንነሳ ስለፈለገ ደጋግሜ ጨዋታ ለመጀመር ያደረኩትን ሙከራ አከሸፈብኝ፡፡ “ቶሎ ቶሎ ብሉ እንጂ” ይላል - እየደጋገመ ጦርነት የመጣ ይመስል፡፡ ከፊት ለፊታችን በትልቅ ረከቦት የቡና ስኒ ተደርድሮ፣ ሣሣ ባለ የዕጣን ጢስ ታጅቧል፡፡ የፈላ ቡና መዓዛ አካባቢውን አውዶታል፡፡የሀገር ባህል ልብስ የለበሰችው የጠይም ቆንጆ ቡናው ተንተክትኮ እስኪወጣለት ትጠባበቃለች፡፡ከዚህ ጀበና ላይ አንድ ስኒ ቡና ለመጠጣት ጐምዥቼ ነበር፡፡ መላኩ ግን ትዕግሥት አልነበረውም፡፡ የደንቡን ለማድረስ እንደተጣደፈ አልጠፋኝም፡፡ “በቃ፣ቡናውን እዚያው ታመጣልናለች እንግባ” አለ፡፡ “ቡናችን ከመጣ ምን ቸገረኝ” ብዬ አብሬው ተነሳሁ፡፡ ሳሚም ተከተለን፡፡ ከነበርንበት ክፍል ወጥተን በስተግራ በኩል ባለው ኮሪደር ዘወር እንዳልን በርካታ ክፍሎች ተደርድረው ተመለከትኩ፡፡ በስተቀኝ በኩል መሀል በሩ ወለል ብሎ የተከፈተ መጸዳጃ ቤት አየሁ፡፡ በመጸዳጃ ቤቱ ወለል ላይ አገልግሎት የሰጠ የመጸዳጃ ቤት ወረቀት በግዴለሽነት ተጥሏል፡፡ የመፀዳጃ ክፍሉ ሽታ ቆይቶም ቢሆን መረበሹ አይቀርም በሚል ያዝ አድርጌ ለመዝጋት ሞከርኩ፡፡ መዝጊያው የተገጠመ መስሎ ተመልሶ ተከፈተ፡፡ ሳይበላሽ አልቀረም፡፡ መላኩ ከተደረደሩት ክፍሎች የአንደኛውን መዝጊያ ገፋ አድርጎ ዘው አለ፡፡ ሳሚም ተከተለው፡፡ እኔም እያመነታሁ ገባሁ፡፡ ክፍሉ ጢቅ ብሎ ሞልቷል፡፡ መጅሊስ ላይ የተቀመጡት በሙሉ አፈጠጡብን፡፡ እንግዳ በመሆኔ ብዙ ዓይኖች ያረፉት እኔ ላይ ነበር፡፡ ከእነዚያ ዓይኖች ለመሸሽ ቀረብ ያለኝ ቦታ አረፍ አልኩ፡፡ ጥቂት ከተረጋጋሁ በኋላ ቀስ ብዬ ዙሪያ ገባውን ማማተር ያዝኩ፡፡ ሳሚ እንደ መላኩ ቤተኛ አለመሆኑ ያስታውቃል፡፡ መላኩ ግን ከሁሉም ጋር ያወራል፡፡ ከፊት ለፊቴ በመጋረጃ የተከለለ ክፍት በር ይታየኛል፡፡ ከመጋረጃው ጀርባ ሌላ ክፍል እንዳለ ገባኝ፡፡ ከበሩ በስተኋላ ፊታቸውን ለእኛ የሰጡ ወጣቶች ተቀምጠዋል፡፡ ነፍሷን በጨርቅ ያንጠለጠለች የምትመስል ቀጭን ልጅ ጉልበቷን ከደረቷ ጋር ገጥማ ተጣጥፋ ተቀምጣለች፡፡ በመልክም በአለባበስም የሚመሳሰሉ ሴትና ወንዶች በመጅሊሱ ላይ ተሰይመዋል፡፡ ከሴቶች ይልቅ የወንዶች ቁጥር በርከት ይላል፡፡ በክፍሉ በስተግራ ጥግ ላይ 42 ኢንች የሚጠጋ ፍላት ስክሪን ቴሌቪዥን ከመሬት ትንሽ ከፍ በምትል ማስቀመጫ ላይ ጉብ ብሏል፡፡ አጠገቡ ከተቀመጠ ተለቅ ያለ የሲዲ ማጫወቻ የአብዱ ኪያርን “እቴ ሜቴ የሎሚ ሽታ” ዘፈን በቀስታ ያጫውታል ቤቱ ውስጥ ጐልቶ የሚሰማው ግን ዘፈኑ ሳይሆን ሌላ ድምፅ ነው፡፡ “…ዱቅ…ዱቅ…ዱቅ” ያደርጋሉ የቤቱ ታዳሚዎች - በየተራ፡፡ አንዱ ሲያቋርጥ ሌላው ይቀጥላል፡፡ ከአፋቸው የሚወጣው ወፍራም ጭስ ቤቱን በከፊል አዳምኖታል፡፡ ሁሉም ሺሻ እያጨሰ ነው፡፡ በየሰው ፊት ባለው ጠረጴዛ ላይ የኮካ ጠርሙሶች እና ውኃ የያዙ ፕላስቲኮች ተቀምጠዋል፡፡ ነጭ የሻይ ሲኒዎች ከማንኪያ ጋርም ይታያሉ፤ ሻይ መስሎኝ ነበር፡፡ ግን አይደለም፡፡ ምን እንደሆነ ለማወቅ ጓጉቼአለሁ፡፡ ቀጠን ያለች ጠይም አስተናጋጅ ሁለት የሺሻ ጠርሙሶች አምጥታ አጠገባችን አኖረች፡፡ ‹‹ሙአሰል›› ተሞልተው ፎይል የተጠቀለሉ ቡሪዎች (የሚጨሰው ነገር ተሞልቶ አናታቸው ከተበሳ በኋላ ከጠርሙሱ ላይ የሚቀመጡ ሸክላዎች) አምጥታ አስቀመጠችበት፡፡ ያመጣችውን እሳት በቀጭን መቆንጠጫ እያነሣች ቡሪው ላይ አደረገች፡፡ ሺሻውን አዘጋጅታ ከጨረሰች በኋላ ፊት ለፊታችን ተቀምጣ ትምገው ጀመር፡፡ በአጫሾች ቋንቋ ማቀጣጠል (ማፈንዳት) ይባላል፡፡ አንዱን ሺሻ ልቧ እስኪጠፋ ስባ ጭስ ማውጣት ሲጀምር፣ ለአንዱ አጫሽ አቀበለችው እና ሁለተኛውን ተያያዘችው፡፡ እኛ በተቀመጥንበት መደዳ በስተግራ በኩል ካለው የኋላ በር ቀጭን፣ ፀጉሩን ወደ ላይ ያቆመ ወጣት እሷ ያመጣችው ዐይነት የእሳት ማቀጣጠያ ፍም ከመሰለ እሳት ጋር ይዞ ወጣ፡፡ ፊቱ ላይ አመድ ቦኖበታል፡፡ እሳት ሲያቀጣጥል እንደነበር መገመት አላቃተኝም፡፡ ሳሚ እና መላኩ ሺሻቸውን እየሳቡ ጨዋታ ይዘዋል፡፡ እስካሁን የነገርኳችሁ ሁሉ የተከሰተው ኢትዮጵያ ውስጥ ከአዲስ አበባ ወጣ ብሎ በሚገኝ አንድ አካባቢ ሊመስላችሁ ይችላል፡፡ ነገር ግን አሜሪካ ነው፡፡ ሺሻ ቤቱም ያለው ቁርጥ ሥጋ ካወራርድንበት ቤት በስተኋላ፡፡ በጆርጂያ ግዛት አትላንታ ከተማ ውስጥ ነው፡፡ ********* ቅድም ሻይ ከመሰለኝ ብርጭቆ ነገር ውስጥ አንድ ሁለቱ የቤቱ እንግዶች በማንኪያ እያወጡ ወደ አፋቸው ሲልኩ ተመለከትኩ፡፡ ሺሻ እያጨሱ በየመሃሉ በማንኪያ የሚበሉት ነገር ምን እንደሆነ መላኩን ጠየቅኹት፡፡ “ሺሻው በደንብ ይሙቅ ብለን ነው እንጂ እኛም አለን እኮ፤ እንደውም ቆይ ላምጣው” አለና ተነሥቶ ወጣ፡፡ መላኩ በላስቲክ ይዟት የመጣውን የታሰረች ትንሽ ነገር ተቀብዬ ፈታኹት፡፡ ክው ብሎ የደረቀ ኮሰረት የሚመስል ነገር ነው፡፡ የአሜሪካ አገር ‹‹ጫት›› ይሄ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከደረቀ በኋላ በተለያየ መንገድ ወደ አሜሪካ እንደሚገባ ተነገረኝ፤ አስመጪዎቹም ሻጮቹም በአብዛኛው ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ ኤርትራውያን፣ ሶማሌዎች እና ጥቁር አሜሪካውያንም የዚህ ንግድ ተሳታፊዎች መሆናቸውን ሰምቻለሁ፡፡ እንደኔ ለምለም ጫት እያየች ላደገች የድሬ ልጅ “የደረቀ ኮሰረት” የመሰለ ነገር “ጫት” ነው ብሎ ለመቀበል ያዳግታል፡፡ ያ ቀልቡ የራቀው አስተናጋጅ በሻይ ቅመም የፈላ ውኃ በሻይ ብርጭቆ ከሻይ ማንኪያ ጋር አምጥቶ ለመላኩ ሰጠው፡፡ እሱም ያንን የደረቀ ጫት ብርጭቆ ውስጥ ከቶ በማንኪያ ገፋ ገፋ እያደረገ ወደ ውስጥ አስገባው፡፡ ከጥቂት ደቂቃ በኋላ “ጫቱ ራሰ” ተባለና በማንኪያ እያወጣ መጉረስ ጀመረ፡፡ ሳሚ ግን የራሰውን አልፈልግም ብሎ ደረቁን እንደብስኩት ከሽ ከሽ እያደረገ ያኝከው ገባ፡፡ ሰዓቱም እየገፋ ወጪ ገቢውም አንዴ እየቀነሰ አንዴ ደሞ እየጨመረ ቀጠለ፡፡ ጆንያ መሳይ ጣራ ያላት የአትላንታዋ ጫትና ሺሻ ቤት እየጋለችና እየታፈነች መጣች፡፡ አሁን እኔም ከማላውቃቸው ወጣቶች ጋር ትውውቅ ፈጥሬ ወሬ ጀምሬአለሁ፡፡ ድንገት ከመጋረጃው ውስጥ ሁለት ወጣቶች እየተጨቃጨቁ ወጡ፡፡ አንዱ የሌላኛውን ወጣት ስልክ በእጁ ይዟል፡፡ “ክፈለኝ፣ አለበለዚያ ይህን ስልክ አልሰጥም፤ በ163 ዶላር እሸጠዋለሁ” ሲለው ችግር እንዳለ ገባኝ፡፡ “ከፈለግህ ሽጠው እንጂ እኔ ያለኝን ገንዘብ ጨርሻለኹ” አለ ሌላኛው ወጣት፡፡ ስልኩ የተያዘበት ልጅ የሚቀልድ እንጂ ከልቡ የሚያወራ አይመስልም፡፡ አንደኛው ወጣት በእጁ የያዘውን ‹‹አይፎን 5›› ስልክ ወደ ላይ ከፍ አድርጎ “ይህን ስልክ በ163 ዶላር የሚገዛ?” ሲል ጠየቀ፡፡ ነገሩ ምን እንደሆነ ባይገባኝም “እኔ” ብዬ እጄን አወጣኹ -እንደ ልጅነቴ፡፡ ሁሉም ሰው ዓይኑን እኔ ላይ ወረወረ፡፡ ግማሹ ፈገግ ሲልልኝ፤ ከፊሉ ደግሞ ኮስተር አለብኝ፡፡ ልጁ ቀጥ ብሎ ወደኔ በመምጣት ስልኩን አቀበለኝና ወደባለቤቱ እያሳየኝ፤ “እኔ ስጭው ሳልልሽ እንዳትሰጪው፤ ገንዘቡን ካላመጣ ባልኩት ዋጋ ትወስጂዋለሽ” አለኝ - ኮስተር ብሎ፡፡ ሳላስበው የማላውቀው አጉል ጨዋታ ውስጥ እየገባሁ እንደሆነ ተሰማኝ፡፡ ልጁ ዞር ሲልልኝ ፊቴን ወደ መላኩ መልሼ “እዚያ ክፍል ውስጥ ምንድነው የሚሠሩት?” ስል ቀስ ብዬ ጠየኩት፡፡ ባለስልኮቹ ወደወጡበት ክፍል እየጠቆምኩት፡፡ “ቁማር እየተጫወቱ ነው” አለኝ ዘና ብሎ፡፡ ነገሩ እንግዳ የሆነብኝ እኔ እንጂ ለእርሱ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ “የምን ቁማር?” ስል ጠየቅኹት፤ “የገንዘብ ነዋ! አንዱን መደብ በ50 ዶላር እያስያዙ ቁማር በካርታ ይጫወታሉ፡፡ ቀኑን ሙሉ እዚህ የሚውሉ አሉ፤ ከሥራ የሚመጡ አሉ፤ ክፍተት ሲያገኙም ሥራ አቋርጠው የሚመጡ አሉ፤” በማለት አስረዳኝ፡፡ መላኩ የቤቱን ደንበኞች አንድ በአንድ ያውቃቸዋል፡፡ ሱሰኞች የሚባሉትን ለይቶ አሳየኝ፡፡ “በጓሮ በር ወጣ ገባ የሚሉት ደግሞ የያዙት ገንዘብ ሲያልቅባቸው ከካርዳቸው ላይ በማሽን ለማውጣት የሚሄዱ ናቸው፡፡ሁሉንም ሲጨርሱ እንደ ልጁ ስልክ ያስይዛሉ” አለኝ፡፡ “ወይ የቁማር ነገር!” አልኩኝ ለራሴ፡፡ አኩርፈው የሚቀመጡት ደግም ብዙ ገንዘብ የተበሉ እንደሆኑ መላኩ ነገረኝ፡፡ ልጁ የሰጠኝ ስልክ እጄ ላይ እንዳለ ሲጠራ ለባለስልኩ ልሰጠው ስል ከግራ ቀኝ ጮኹብኝ፤ “ስጪ ሳትባይ መስጠት የለም” እያሉ፡፡ አሁን ቁማሩ የምር እንደሆነ ገባኝ፡፡ እነሱ ወደሚጫወቱበት ክፍል መግባት ፈለግኹ፡፡ ለባለሺሻ ቤቱ የመቀመጫ 5 ዶላር፣ የመደብ ደግሞ 50 ዶላር ከፍዬ የካርታው አባል ካልሆንኩ መቀላቀል እንደማልችል ሳሚ ሹክ አለኝ፡፡ ስልክ ያዡም አስያዡም ተመልሰው ወደ ቁማር ክፍሉ ሲገቡ አየኋቸው፡፡ እኔ ስልኩን እንደያስዝኩ ከተቀሩት ጋር ጨዋታዬን ቀጠልኩ፡፡ መላኩ የታክሲ ሹፌር ቢኾንም የከተማው ከንቲባ ነው የሚመስለው፡፡ ሁሉንም ያውቃቸዋል፡፡ ከቤቱ ደንበኞች ጋር ያለውን ትውውቅ ነገረኝ፡፡ “እነዚህ ጅንስ ቲሸርት ምናምን የለበሱት የታክሲ ሹፌሮች ናቸው፣ ከሴቶቹ ውስጥ ሁለቱን ነው የማውቃቸው፤ አንዷ የሬስቶራንት አንዷ ደግሞ የናይት ክለብ አስተናጋጆች ናቸው፤ ዛሬ ዕረፍታቸው ነው መሰለኝ…” አለኝ፡፡ ሌሎቹን ሴቶች ግን አያውቃቸውም፡፡ የአንደኛቸው ጓደኞች ሳይሆኑ እንደማይቀሩ ግምቱን ነገረኝ፡፡ ሌሎች ሁለቱ ደግሞ በሚሊዮን ዶላር የሚያንቀሳቅሱ እንደሆኑ ነገረኝ፡፡ የገንዘብ ምንጫቸው ምን እንደሆነ ባይታወቅም፡፡ ሐሺሽ ይነግዳሉ እየተባሉ እንደሚታሙ አልደበቀኝም፡፡ “ሱፍ የለበሱትስ?›› ስል ጠየቅሁት -ወደ ጎልማሶቹ እያየሁ፡፡ ‹‹የሊሞዚን ባለቤቶች ናቸው፡፡ ሊሞዚን የሚነዳ ሰው ሙሉ ሱፍ መልበስ ግዴታው ነው” ሲል መለሰልኝ፡፡ “እንደዚህ ቁጭ ብለው እየዋሉ ምን ሰዓት ነው የሚሠሩት?” ስል ጠየቅሁት “የታክሲ እና የሊሞዚን ሥራ ቁማር ነው፤ አንዳንዴ ይኖራል አንዳንዴ ደግሞ ይጠፋል፡፡ ልምዱ ያለን ልጆች ሥራው ላይ ችክ አንልበትም፡፡ ስለምናውቀው ሥራ ሲኖር እንወጣለን፣ ከሌለ ደግሞ ዘና እንላለን፡፡ ባለሊሞዚኖቹም ሥራ ሲኖር ይደወልላቸዋል፡፡ በዛ ላይ ብቅ ብለን ጨስ ጨስ አድርገን ውልቅ እንላለን እንጂ እንደቁማርኞቹ አፋችን ላይ ተክለን አንውልም” አለኝ፡፡ ፓርኪንግ እና ነዳጅ ማደያ የሚሠሩ እንዲሁም የት እንደሚሠሩ የማይታወቁ ደንበኞችም እንደሚመጡ አጫወተኝ፤ ወደ ሳሚም ዞር ብሎ “ለምሳሌ እሱ እኔ ይዤው ካልመጣኹ ብቻውን አይመጣም፡፡ እዚህ ከሚመጣ ቤቱ ቁጭ ብሎ ከሚስቱ ጋር ቢያጨስ ነው የሚመርጠው” አለኝ፡፡ ሳሚ ሣቅ አለ፡፡ ሺሻ በአሜሪካ እየተስፋፋና እየተለመደ የመጣ ነገር እንደሆነ ተገነዘብኹ፡፡ መላኩ ልክ ነበር፤ ሳሚ ከሚስቱ ጋር ቁጭ ብሎ ሲያጨስ ቤቱ አይቸዋለሁ፡፡ አሁን ያለሁባት ቤት ከእነዚያ ትለያለች፡፡ መተሐራ ካየኋት ጋራ ትመሳሰላለች፡፡ ከአዲስ አበባ ወደ ምሥራቅ በተለይ በምሽት የሚጓዝ ሰው መተሐራን ሳይረግጥ አያልፍም፡፡ እኔም በዛ መንገድ ላይ በምሽት እየተወነጨፉ በሚሄዱት ሚኒባሶች ተሳፍሬ ብዙ ጊዜ ተመላልሻለሁ፡፡ በመኪና መንገዱ ላይ በከተማዋ እንብርት በሚገኙት ምግብ ቤቶች ተመግቤያለሁ፡፡ ወደ ጓሯቸውም ዘወር ብዬ ሺሻ ቤቶቻቸውን ጐብኝቻለሁ፡፡ ከዕለታት በአንዱ ቀንም ስለነሱ ጽፌያለሁ፡፡ የመተሐራ ሺሻ ቤቶች አብዛኛዎቹ ደንበኞች የሚኒባስ፣ የአይሱዙ፣ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች እንዲሁም በምሽት ቡና ቤቶች እና ዳንስ ቤቶች የሚሠሩ አስተናጋጆች ናቸው፡፡ የሚያወጡት ገንዘብ በብር እና በዶላር ካልተለያየ በስተቀር የአትላንታ እና የመተሐራዎቹ ደንበኞች የሥራ ዐይነት ተመሳሳይ ነው፡፡ የመተሐራው ሺሻ ቤቶች አሠራር የተዳከመ ይዞታ ያለው ሲሆን የአትላንታው ደግሞ ዘመናዊ ገጽታ አለው፤ የሁለቱም ቤቶች የመቀመጫ አደራደር ግን አንድ ዓይነት ነው፡፡ የመተሐራዎቹ ሺሻ ቤቶች ለአንድ ቡሪ 10 ብር ሲያስከፍሉ፣ የአትላንታዎቹ ደግሞ ለአንድ ቡሪ 15 ዶላር(280 ብር) ያስከፍላሉ፡፡ ያገመትኩትን የኢትዮጵያውያ የአትላንታ ውሎ በማየቴ ተገረምኩ፤ሱስን ይዞ መሰደድን ምክንያት አጣሁለት ምናልባት አንዳንዶቹ የለመዱት እዛው ሊሆን ይችላል፡፡ ጥቅሙን መጠየቅ ምክር ቢጤም መለገስ አምሮኝ ነበር ‹‹ይኼ እኮ መብት የሚከበርበት አገር ነው›› የሚል አጭር እና ግልጽ መልስ ተሰጠኝ፡፡ የቤቱ ጨዋታ ደርቷል፡፡ የቁማር ቤቱ መጋረጃ ተከፈተ፤ ስልክ ያስያዘኝ ልጅ ስልኩን ለባለቤቱ እንድሰጠው ነገረኝ፡፡ ድጋሚ ተበላልተዋል ማለት ነው አልኩ፡፡ ስልኩን ለባለቤቱ እየመለስኩ፤ “እኔ ደግሞ ስልክ በርካሽ አገኘሁ ብዬ” በማለት ለመቀለድ ሞከርኩ፡፡ “ስልክ ትፈልጊ ነበር እንዴ?” ሲል መላኩ ጠየቀኝ፡፡ ሳሚ ቀደም አለና፣ “ለሷ ነበር እኮ ፈልግ ያልኩህ?” አለው፡፡ ግራ ተጋብቼ ሁለቱንም እየተዟዟርኩ አየሁዋቸው፡፡ ከየት ነው የሚፈልጉልኝ? በርግጥ ዘመናዊ ስልክ መግዛት ፈልጌ ነበር፤ ግን በምድረ አሜሪካ የስልክ መሸጫ ሱቆች ሞልተው እነሱ ከየት ነው የሚፈልጉልኝ? “እኛ ጋ እኮ ስልክ አይጠፋም፡፡ ተሳፋሪ ጥሎ ስለሚወርድ ሁሌ እናገኛለን፡፡ እኔ አገር ቤት ለመላክ ያዘጋጀሁት ነው እንጂ አራት አይፎን ነበረኝ” አለኝ - መላኩ፡፡ ከዚያ ወደ ጓደኞቹ ፊቱን መልሶ ስልክ እንዳላቸው ጠየቀ፡፡ “እስካሁን ለምን አልነገርከንም፤ እኔ የለኝም ቆይ እንትና አለው …” እያሉ ስልካቸውን መጠቅጠቅ ጀመሩ፡፡ “ባለታክሲዎች ዘንድ ስልክ አይጠፋም” አለ፤ቀጠን ያለው የመላኩ ጓደኛ፡፡ “አስቀድመህ ብትነግረኝ ኖሮ ጥሩ ነበር፡፡ ከትናንት በስቲያ ነው ሁለት አይፎን አገር ቤት የላክኹት፡፡ ታገሠኝና ሰሞኑን እንፈልጋለን” አለው፡፡ እናፈላልጋለን የሚሉት እኮ ከደንበኞቻቸው ኪስ ሾልኮ የሚወድቀውን ነው፡፡ “አንዳንዴ ስልክ ሲጠርብኝ ከኋላ ተቀምጠው የሚሳሳሙ ሰዎች ከጫንኹ አውቄ አወዛውዛቸውና ከኪሳቸው እንዲወድቅ አደርጋለኹ” ሲል እየሣቀ ነገረኝ፡፡ ለካ እነሱ “ሿሿ እየሠሩ የሚልኩትን ስልክ ነው እኛ በሿሿ የምንሰረቀው” አልኩ በሆዴ፡፡ የስልኩ ጨዋታ ወደሌላ ጨዋታ ይዞን ነጐደ፡፡ የሚሳሳሙት ደንበኞቻቸው ወንድ እና ሴት ብቻ አይደሉም፡፡ አንዳንዴ ወንድና ወንድ ሌላ ጊዜ ደግሞ ሴትና ሴት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በዲሲ፣ በሳንፍራንስሲስኮ፣ በቺካጐ እና በአትላንታ ጉብኝቴ ወንድ ለወንድ እና ሴት ለሴት ሲሳሳሙ በዐይኔ ተመልክቻለሁ፡፡ ድርጊቱን ማየት እንደመስማት እና ማውራቱ ቀላል አይደለም፤ለእንደኔ ዓይነቷ ሊብራል ነኝ ባይ እንኳን መሣቀቁ ነፍስን ከሥጋ ያላቅቃል፡፡ ግን ደግሞ ያየሁትን ጽፌ ለማስነበብ ጓጉቼ ስለምጓዝ እየተሳቀቅኹም ቢሆን እንዲህ ያሉትን ቦታዎች ጐብኝቻለሁ፡፡ ኢትዮጵያውያኑም አንዳንዶች እነርሱን ሆነውና መስለው፣ ሌሎቹ ደግሞ ለእነርሱ ተሣቀው፣ ከፊሎቹ ከእነርሱ ጋር እየሠሩ፣ወላጆች ደግሞ ለልጆቻቸው እየሰጉ፣ ጥቂቶች ምንም እንዳልተፈጠረ እየቆጠሩ አብረው ይኖራሉ፡፡ አንድ ማታ እርቃናቸውን የሚደንሱ ሴቶች ያሉበት ዳንስ ቤት ጐራ ብዬ አንዲት ሐበሻ መልክ ደናሽ አይቼአለሁ፡፡በእርግጥ የዜግነቷ ጉዳይ በደንብ የለየለት አይመስልም፡፡ ኢትዮጵያውያኑ ኤርትራዊ ነች ሲሏት፤ ኤርትራዊያኑ ደግሞ ኢትዮጵያዊት ነች ይሏታል፡፡ ይቺ ሴት እርቃን ገላዋን አጋልጣ ሲያሻት በወንዶቹ ሲላት ደግሞ ከሴቶቹ ጋር እየተሻሸች ዶላር ስትሰበስብ ተመልክቻለሁ፡፡(ይቀጥላል)

Read 3945 times Last modified on Friday, 15 March 2013 07:48