Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 12 January 2013 10:00

ኢትዮጵያ ያለችበት 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ 1 ሳምንት ቀረው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በደቡብ አፍሪካ አስተናጋጅነት የሚካሄደው 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ የዛሬ ሳምንት በጆሃንስበርግ ሶከር ሲቲ ስታድዬም ደቡብ አፍሪካ ከኬፕቨርዴ በሚያደርጉት ጨዋታ የሚጀመር ሲሆን ዘንድሮ በቡድኖች መካከል ተመጣጣኝ ፉክክር እንደሚታይ ተጠብቋል፡፡ ደቡብ አፍሪካ በ5 ከተሞች በሚገኙ አምስት ስታድዬሞች ይህን የአፍሪካ ዋንጫ ለማዘጋጀት እስከ 53.3 ሚሊዮን ዶላር አውጥታለች የስታድዬም መግቢያ ትኬቶች ሽያጭ ከ340ሺ በላይ እንደሆነም ተገልጿል፡፡ 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በ200 አገራት የቀጥታ ስርጭት እንደሚኖረው የሚጠበቅ ሲሆን ከ700 በላይ የሚዲያ ተቋማት ፈቃድ አግኝተው ከመላው ዓለም በመሰባሰብ ለውድድሩ ሽፋን ለመስጠት ደቡብ አፍሪካ ይገባሉ፡፡ይህ በእንዲህ እንዳለ ባለፈው ሰኞ ከቱኒዚያ ብሄራዊ ቡድን ጋር በኳታር ዱሃ ላይ 1-1 የተለያየው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ትናንት ከታንዛኒያ ብሄራዊ ቡድን ጋር አዲስ አበባ ላይ ሶስተኛውን የወደጅነት ጨዋታ አደረገ፡፡

ጨዋታው ብሄራዊ ቡድኑ ለህዝቡ አቋሙን አሳይቶ ወደ 29ኛው አፍሪካ ዋንጫ የሚያቀናበት ሆኗል፡፡ዋልያዎቹ በአፍሪካ እግር ኳስ ጠንካራ አቋም እንዳላቸው ከሚነገርላቸው እና ለዘንድሮው ሻምፒዮናነት ግምት ከተሰጣቸው የቱኒዚያ ‹የካርታጌ ንስሮች› ጋር በተጋጠሙበት ወቅት በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በፍፁም ቅጣት ምት በተቆጠረበት ጎል ሲመሩ ነበር፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ በ64ኛው ደቂቃ ላይ ግን ጌታነህ ከበደ ያሳለፈለትን ኳስ ሳላዲን ሰይድ ከመረብ በማገናኘት አቻ ለመለያየት በቅተዋል፡፡በሌላ በኩል የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ብሄራዊ ብድናችን ለአፍሪካ ዋንጫ እንዲያልፍ ላደረጉ ተጨዋቾችና ድጋፍ ሰጪ ባለሙያዎች ከ2.9 ሚሊዮን ብር በላይ ሽልማት ከወር በፊት መስጠቱ የሚታወስ ነው፡፡ ዛሬ ደግሞ በሚሊኒዬም አዳራሽ ከ2500 በላይ እንግዶችን በማሳተፍ በሚከናወነው የእራት ግብዣ ቀደም ሲል የተከበሩ ሼህ መሃመድ ሁሴን አላሙዲ ለዋልያዎቹ እና ለሉሲዎች ቃል የገቡት 10 ሚሊዮን ብር እንደሚሰጥ ይጠበቃል፡፡ በዝግጅቱ ለብሄራዊ ቡድኑ የሚሆን እስከ 20 ሚሊዮን ብር ገቢ ለማሰባሰብ በተያዘ እቅድ ከእራት ግብዣው ጋር ጎን ለጎን እንቅስቃሴዎች እንደሚደረጉም ታውቋል፡፡ በተያያዘም ‹‹እኛም በሙያችን ለብሄራዊ ቡድናችን›› በሚል ከ50 በላይ ታዋቂ አርቲስቶች ያለአንዳች ክፍያ በበጎ ፈቃደኝነት እንሰራዋለን ብለው ቃል የገቡት የሙዚቃ ኮንሰርት ነገ በአዲስ አበባ ስታድዮም ይደገሳል፡፡ ይህን የሙዚቃ ኮንሰርት አዲካ እንደሚያዘጋጀው ሲታወቅ በዝግጅቱ ከትኬት ሽያጭ ባሻገር በስፖንሰሮች ገቢ ለማግኘት መታቀዱንም ለማወቅ ተችሏል፡፡

ዋልያዎቹ በድረገፆች እና በሶሻል ሚዲያዎች
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በተለያዩ የኢንተርኔት የማህበረሰብ ድረገፆች በተለይም በፌስቡክ ዋና የመነጋገርያ አጀንዳም ሆነዋል፡፡ እንደጉጉል አይነት ድረገፅ ላይ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዙርያ በሚጠየቅ መረጃ የዜና፤ የዘገባ እና የምስል መረጃዎችን በሚሊዮን ብዛት ማግኘት የሚቻልበት ደረጃ ተደርሷል፡፡ ኢትዮጵያን እንደግፋለን በሚል ቲምኢትዮጵያ በሚል ከ5 ወራት በፊት የተከፈተ የፌስቡክ ገፅን የሚከታታሉ አድናቂዎች ቁጥር ሰሞኑን 35682 የነበረ ሲሆን በሚቀጥሉት ቀናት ከ40ሺ በላይ ሊሆን እንደሚችል ተጠብቋል፡፡

ሞምቤላ እና ሮያል ባፎኬንግ
ኢትዮጵያ በምድብ 3 ከምታደርጋቸው ጨዋታዎች ሁለቱ ከዛምቢያ እና ከቡርኪናፋሶ ጋር የምትገናኝባቸው በኔልስፑሪት ባለው የሞምቤላ ስታድዬም ሲደረጉ የምድቧን የመጨረሻ ጨዋታ ከናይጄርያ ጋር የምትፋለመው ደግሞ በሩስትንበርግ በሚገኘው የሮያል ባፎኬንግ ስታድዬም ይሆናል፡፡
በ140 ሚሊዮን ዶላር የተገነባው የሞምቤላ ስታድዬም ከ40ሺ በላይ ተመልካች የሚያስተናግድ ሲሆን በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ 7 ግጥሚያዎችን ያስተናግዳል፡፡ ግጥሚያዎቹ በምድብ 3 ዛምቢያ ከኢትዮጵያ፤ ናይጄርያ ከቡርኪናፋሶ፤ ዛምቢያ ከናይጄርያ እንዲሁም ቡርኪናፋሶ ከኢትዮጵያ የሚገናኙባቸው እና የምድብ 4 የመጨረሻ ጨዋታ ኮትዲቯር ከአልጄርያ የሚፋለሙበት ነው፡፡ በሞምቤላ ስታድዬም የሚደረጉት ሁለቱ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ደግሞ በሩብ ፍፃሜ የምድብ 3 አንደኛ ከምድብ 4 ሁለተኛ የሚገናኙበትና ሌላ የግማሽ ፍፃሜ ፍልሚያ ናቸው፡፡ በምድብ 3 የመጨረሻ ጨዋታ ኢትዮጵያ እና ከናይጄርያ የሚገናኙበት በሩስተንበርግ በሚገኘው የሮያል ባፎኬንግ ስታድዬም 42ሺ ተመልካች የሚይዝ ነው፡፡ ስታድዬሙ የምድብ 4 አራት ግጥሚያዎችንና አንድ የሩብ ፍፃሜ ግጥሚያን ያስተናግዳል፡፡

የአፍሪካ ብራዚል ነበረች!?
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከሚገኙ አገራት በፊፋ አባልነት በግንባር ቀደምነት ስትጠቀስ በፊፋ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያም ላይ በመካፈል ቀዳሚዋ ናት፡፡ ዘንድሮ ከ31 ዓመታት መራቅ በኋላ ለ10ኛ ጊዜ በአፍሪካ ዋንጫ የምትሰለፈው ኢትዮጵያ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ለዓለም ዋንጫ ለማለፍም በሚደረገው የማጣርያ ውድድር ምድቧ ደቡብ አፍሪካ፤ መካከለኛው አፍሪካ እና ቦትስዋናን በማስከተል እየመራች ትገኛለች፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በፊት በአፍሪካ ዋንጫ ለ9 ጊዜያት ተሳትፏል ለመጀመሪያ ጊዜ የተካፈለው በ1957 እ.ኤ.አ ላይ ውድድሩ በይፋ ሲመሠረት ነበር፡፡ በ1962 እ.ኤ.አ ላይ ደግሞ ብሔራዊ ቡድኑ የአፍሪካ ዋንጫን ኢትዮጵያ ስታስተናግድ በሻምፒዮናነት ዋንጫውን አግኝቷል፡፡ ሌሎች ያስመዘገባቸው ውጤቶች ደግሞ በ1957 እ.ኤ.አ ሁለተኛ ደረጃ፣ በ1959 እ.ኤ.አ ሦስተኛ ደረጃን በ1963 እና በ1968 እ.ኤ.አ አራተኛ ደረጃ ያገኘባቸው ናቸው፡፡
በኢትዮጵያ እግር ኳስ በተስፋፋባቸው የመጀመሪያዎቹ 25 ዓመታት በተለይም በ1960ዎቹ አስደናቂ ታሪክ መመዝገቡ አይካድም ነበር፡፡ ያኔ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአህጉራዊ ውድድሮች ባሳየው ብቃት በተለያዩ አጋጣሚዎች በመገናኛ ብዙሐናት የአፍሪካ ብራዚል በሚል ተሞካሽቷል፡፡ በዚያ ዘመን ለታየው የኢትዮጵያ እግር ኳስ አስደናቂ ለውጥ የክቡር ይድነቃቸው ተሰማ አስተዋኦ ቀላል የሚባል አልነበረም፡፡ ይድነቃቸው በእነዚያ ኃያአምስት አመታት በኢትዮጵያ እግርኳስ እንቅስቃሴ በፌዴሬሽን አመራርነት፣ በብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝነትና በቡድን መሪነት፤ በብሔራዊ ቡድን ተጨዋችነትና አምበልነት እንዲሁም በቅዱስ ጊዮርጊስ ተጨዋችነትና አሰልጣኝነት ሠርተዋል፡፡
በአፍሪካና በአውሮፓ የተለያዩ መገናኛ ብዙሀናትም በዘመኑ ስለነበረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ድንቅ ብቃትና ውጤት ብዙ ጽፈዋል፡፡
ከክቡር ይድነቃቸው ተሰማ ማህደር የተገኙት መረጃዎች በ1960ዎቹ ስለ ኢትዮጵያ እግር ኳስ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ጋዜጠኞች በስፋት ሲዘገብ እንደነበር ያመለክታሉ፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በ6ኛው አፍሪካ ዋንጫ ላይ ተካፍሎ ያለዋንጫ ከቀረ በኋላ ነው፡፡ ሮበርት ቨርባኔ የተባለ የስፖርት ጋዜጠኛ ስለ ኢትዮጵያ በሜዳዋ ዋንጫ ስለማጣቷ አልነበረም የዘገበው ..የአውሮፓ ቡድኖች ለወዳጅነት ጨዋታ የ6ኛው አፍሪካ ዋንጫ ሻምፒዮኗን ኮንጐ - ኪንሻሳ ይጋብዙ ይሆናል፡፡ ግን አውሮፓውያን አቋማቸውን ለመፈተን ካቀዱ ትኩረታቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ቢሆን እመክራለሁ.. በማለት ፉትቦል መጋዚን በተባለ ህትመት ላይ በፌብርዋሪ 1967 እ.ኤ.አ አስፍሯል፡፡ አራተኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ለናይሮቢው ዴይሊ ኔሽን ይዘግብ የነበረው ብራያን ማርስዴን በበኩሉ በወቅቱ ኬንያ እና ኢትዮጵያ አድርገውት ከነበረው ጨዋታ በመነሳት ሲዘግብ እንዲህ በማለት ነበር ..ኬንያና ኢትዮጵያ በድንበር የተዋሰኑ አገሮች ናቸው፡፡ የእግር ኳስ ወሰናቸው ግን ምናልባትም በብርሃን ዘመን የሚለካ ነው፡፡.. በማለት ኖቬምበር 13 ቀን 1963 እ.ኤ.አ ላይ በዴይሊ ኔሽን እትም አትቷል፡፡
በግዜው የነበረ የስፖርት ጋዜጠኛ ኖለስ ጆንሰን የሚባል ጋናዊ ሲሆን በጋና ዋና ከተማ እ.ኤ.አ በ1963 የተደረገውን የአፍሪካ ዋንጫ ተከታትሎ በሻምፒዮናው ኢትዮጵያ ቱኒዚያን 4ለ2 ካሸነፈች በኋላ በኋላ ኖቬምበር 29 ላይ በጋናያን ታይምስ ጋዜጣ ላይ... .....በአክራ ስፖርት ስታድዬም ነው፡፡ ኳስ ለ90 ደቂቃ በኢትዮጵያ ቁጥጥር ስር ነበረች፡፡ እውነተኛ ሻምፒዮን እንዲህ ይጫወታል፡፡..
ሲል ዘገባውን ለአንባቢዎቹ አቅርቧል፡፡ ጂዮን አፍሪኬ በተባለ ታዋቂ የፈረንሳይ ጋዜጣ የፃፈው ጋዜጠኛ ደግሞ በ1960ዎቹ መግቢያ ላይ የነበሩትን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾች የአፍሪካ ስፖርት አባሳደር በማለት አወድሶአቸዋል፡፡ በ4ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ በኢትዮጵያና በሴኔጋል መካከል ከተደረገው ጨዋታ በኋላ ላይ ታዋቂው የሴኔጋል ጋዜጣ ..ዳካር ዴይሊ.. በኖቬምበር 22 እትሙ- ..የኢትዮጵያ ቡድን በግጥሚያው የቡድን ጨዋታንና አጥቅቶ የመጫወትን ብቃት ለሴኔጋል አቻው አስተምሯል፡፡ በቴክኒክም በስነልቦናም የሴኔጋል ተጨዋቾች በኢትዮጵያ ተበልጠዋል፡፡ ስታድዬም የገባነው ኳስን ለማየት ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ጨዋታ አየነው.. ሲል በአበይት ዘገባው አትቷል፡፡
እንደ ይድነቃቸው ተሰማ የግል ማህደር በ1960ዎቹ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አህጉራዊን ትኩረት ባጭሩ በእንዲህ መልኩ የሳበ ነበር ፡፡ ክቡር ይድነቃቸው ተሰማ በ1958 እ.ኤ.አ ላይ በስዊድን ተደርጐ የነበረውን ዓለም ዋንጫ በስፍራው በመገኘት መከታተል ከቻሉ በኋላና ያገኙትን ተመክሮ ወደ ሀገራቸው ይዘው በመመለስ የብራዚልን የእግር ኳስ አጨዋወት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንና ለቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ማስተዋወቃቸውን ታሪካቸው ይነገራል፡፡
የብራዚል እግር ኳስ አጨዋወትና ታሪክ በይድነቃቸው አማካኝነት በሀገራችን በተዋወቀበት በዚህ ዘመን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ከፍተኛ ለውጥ ሊያሳይ የቻለ ነበር፡፡ በኳስ ችሎታቸው በአካል ብቃታቸው በጥንካሪያቸው፣ በፍጥነታቸው በሌሎችም የብቃት መስፈርቶች በተለይ ከጐረቤት አገሮቻቸው ከኬንያ ከኡጋንዳና፣ ከታንዛኒያ በእጅጉ የተሻሉ ነበሩ፡፡ ከ50 ዓመታት በፊት ከምዕራብና ከሰሜን አፍሪካ ቡድኖች ጋርም በተቀናቃኝነት የሚቀርብ ቡድን ኢትዮጵያ ነበራት፡፡ ብዙዎች ለዚህ ምክንያቱ የኢትዮጵያ እግር ኳስ በወርቃማው ትውልድ በመገኘቱ መሆኑን የሚጠቅሱ ቢሆንም ሀገሪቱ አሪፍ ተጨዋቾችን በማፍራት ረገድ ዛሬም ቢሆን ችግር የለባትም፡፡ በ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በዋልያዎቹ የሚመዘገብ ውጤት ኢትዮጵያን ወደ አፍሪካ የእግር ኳስ ካርታ የሚመልሳት፤ ለተጨዋቾች የፕሮፌሽናል እድል የሚፈጥርና አገሪቱ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ በ2014 እኤአ ላይ በብራዚል ለሚደረገው 20ኛው የዓለም ዋንጫ የምታልፍበትን እድል የሚያጠናክር እንደሚሆን ተስፋ ይደረጋል፡፡
ሴላ ሴላ እና ካቴሎጐ
የ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ኦፊሴላዊ ዜማ (ሴላ ሴላ)ወይም አብረን እንደንስ በሚል ትርጓሜ የተሰራ ነው፡፡ አሜሪካዊቷ ዛሃራ እና ደቡብ አፍሪካዊው ዌስ ማይኮ የሚጫወቱትን ይህን ዜማ ኢሩሳ ሙዚቃ ኢንተርቴይመንት የሰራው ሲሆን በእንግሊዝኛ እና በባንቱ ቋንቋዎች ተቀናቅኗል፡፡ ሰላምና አንድነት አብሮ መደሰትን በስንኞቹ ያንፀባርቃል፡፡ የ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ግጥሚያዎች ላይ የምታገለግለው ኳስ ካቴሎጎ የምትባል ናት፡፡ ይህች ኳስ ለአፍሪካ ዋንጫ ተብሎ በአዳዲስ ለ4ኛ ጊዜ ተመርታለች፡፡ በ2008 እ.ኤ.አ በጋናው 26ኛው የአፍሪካ ዋንጫ “ዋዋ አባ”፤ በ2010 እ.ኤ.አ በአንጎላ 27ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ጃቡላኒ፤ በ2012 እ.ኤ.አ በኢኳቶሪያል ጊኒ እና በጋቦን በጣምራ ባዘጋጁት 28ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ኮሜክዋ የተባሉ የአዲዳስ ኳሶች ነበሩ፡፡

የሻምፒዮናነት የኃይል ሚዛን
ላለፉት 56 ዓመት በተደረጉት 28 የአፍሪካ ዋንጫዎች ሻምፒዮን ለመሆን የበቁ አገራት 14 ብቻ ናቸው፡፡ 7 ጊዜ ግብጽ፣ 4 ጊዜ ካሜሮንና ጋና፣ 2 ጊዜ ኮንጐና ናይጀሪያ፣ 1 ጊዜ ዛምቢያ፣ አልጀርያ፣ ኮንጐ ብራዛቪል፣ ኢትዮጵያ፣ አይቬሪኮስት፣ ሞሮኮ ደቡብ አፍሪካ፣ ሱዳንና ቱኒዚያ ናቸው፡፡ የሰሜን አፍሪካን የወከሉ አገራት 10 ጊዜ ዋንጫውን በማንሳት የሚመሩ ሲሆን እነሱም 7 ጊዜ የበላችው ግብፅ እና እያንዳንዳቸው አንድ ጊዜ ሻምፒዮን ለመሆን የበቁት አልጄርያ፤ ሞሮኮ እና ቱኒዝያ ናቸው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ በመካከለኛው እና በምእራብ የአፍሪካ ክፍል የሚገኙ አገራት 7 ዋንጫዎችን በመውሰድ ይጠቀሳሉ፡፡ ከመካከለኛው አፍሪካ 4 ጊዜ ሻምፒዮን የሆነችው ካሜሮን፤ ሁለት ጊዜ ያሸነፈችው ዲ ሪፖብሊክ ኮንጎ እና 1 ጊዜ ዋንጫው ያነሳችው ኮንጎ ናቸው፡፡ ከምእራብ ደግሞ የአራት ጊዜ አሸናፊዋ ጋና፤ ሁለት ጊዜ ሻምፒዮን የሆነችው ናይጄርያ እና አንድ ጊዜ ዋንጫውን ለማንሳት የሆነላት ኮትዲቯር ናቸው፡፡ የምስራቅ እና የደቡብ አፍሪካ አገራትም እያንዳንዳቸው ሁለት ሁለት ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫን ወስደዋል፡፡ ከምስራቅ አፍሪካ ሁለቱን የአፍሪካ ዋንጫ ድሎች ያጣጣሙት ኢትዮጵያ እና ሱዳን ሲሆን ከደቡብ ደግሞ የ29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅ ደቡብ አፍሪካ እና የ28ኛው የአፍሪካ ዋንጫን ድል ያደረገችው ዛምቢያ ናቸው፡፡

የአራዊት መናሐርያ
በዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ በሚሳተፉ 16 ብሄራዊ ቡድኖች ቅፅል ስያሜዎች ውድድሩ በአራዊት እንደ ዙ መቆጠሩ ግድ ሆኗል፡፡ ከ16ቱ ብሄራዊ ቡድኖች ከአራዊት ወይም ከእንስሳ ስም የራቀ ቅፅል ስም ያላቸው 4 ቡድኖች ብቻ ናቸው፡፡ የተቀሩት 12 ብሄራዊ ቡድኖች አራቱ በአጋዘን ዝርያዎች፤ 3ቱ በተለያዩ የንስር ዝርያዎች እንዲሁም ዝሆን፤ አንበሳ እና አቦሸማኔን ስያሜ በማድረግ 29ኛው የአፍሪካ ዋንጫ በቅፅል ስያሜዎች የአራዊት መናሐርያ አድርገውታል፡፡ በምድብ 1 አዘጋጇ ደቡብ አፍሪካ ባፋና ባፋና በሚል ቅፅል ስያሜዋ ብትለይም ኬፕቨርዴ ሰማያዊ ሻርኮች፤ አንጎላ ጥቁር አጋዘኖች እንዲሁም ሞሮኮ የአትላስ አናብስት በሚል ቅፅል ስማቸው የሚጠሩ ናቸው፡፡
በምድብ 2 ጋና ቡድኗን ጥቋቁሮቹ ክዋክብቶች ብላ ብትሰይምም ማሊ ንስሮች፤ ኒጀር መና በተባለ የአጋዘን ዝርያ እንዲሁም ዲ ሪፖብሊክ ኮንጎ አቦሸማኔ ተብለው በቅፅል ስማቸው ይጠቀሳሉ፡፡
በምድብ 3 ደግሞ ሻምፒዮና ዛምቢያ የመዳብ ጥይቶች ተብላ ብትጠራም ናይጄርያ ንስሮች፤ ቡርኪናፋሶ ፈረሰኞች እንዲሁም ኢትዮጵያ ዋልያዎች በሚለው ቅፅል ስያሜያቸው ይታወቃሉ፡፡
በምድብ 4 አልጄርያ ብቻ የበረሃ ጦረኞች የሚል ስያሜ ቢኖራትም ኮትዲቯር ዝሆኖቹ፤ ቱኒዚያ የካርታጌ ንስሮች እንዲሁም ቶጎ ትናንሽ ጭልፊቶች ተብለው ይቆላመጣሉ፡፡


Read 10460 times