Saturday, 12 January 2013 09:50

ሬዲዮኖቻችን እንደ ባቢሎን ግንብ እንዳይሆኑ!

Written by  ኃይለገብርኤል እንደሻው gizaw.haile@yahoo.com
Rate this item
(1 Vote)

ባለፈው ታህሣሥ 20 ቀን 2005 ዓ.ም ቅዳሜ ረፋዱ ላይ፣ ለመስክ ስራ ገጠር እያለሁ ከመዲናችን አዲስ አበባ በ97.1 የኤፍ.ኤም. ሬዲዮ ጣቢያ ይተላለፍ የነበረን የስፖርት ዝግጅት አዳምጥ ነበር፡፡ ዝግጅቱ የአማርኛ ቢሆንም፣ የስፖርት ጋዜጠኞቹ የሬዲዮ መልዕክቱን የሚያቀርቡት እንግሊዝኛ ቅይጡ ባየለበት ጉራማይሌ ቋንቋ ነበር፡፡ በጣም ስለደነቀኝ፣ የእንግሊዝኛዎቹን ቃላትና ሐረጎች በብጣሽ ወረቀት ላይ እንደ ቀልድ መመዝገብ ያዝኩ፡፡ በመጨረሻም የሁለት ሰዓቱ የስፖርት ዝግጅት ሲጠናቀቅ የመዘገብኳቸውን የእንግሊዝኛ ቃላት ብቆጥራቸው፣ ስድሳ ያህል ሆነው አገኘኋቸው፡፡  በዚሁ ዕለት በጠቀስኩት የሬዲዮ ዝግጅት ላይ ከተደመጡት የእንግሊዝኛ ቃላትና ሐረጎች መካከል፣ emerging, departure, provisional, focus, surprise, destiny, semi-final, cope up, why not, in to consideration, squad, rationally, inspire እና coach የተሰኙትይገኛሉ፡፡ 

በዚህ ዓይነት እንግዳ ወይም ባዕድ ቃላትን በሬዲዮ ላይ መጠቀም እንደ ችግር የሚቆጠር ጉዳይ ነው፡፡ ኧረ ለመሆኑ፣ በአማርኛ በሚተላለፍ ዝግጅት ላይ ቁጥራቸው የበዛና ትርጉማቸው ለአብዛኛው የሃገራችን የሬዲዮ አድማጭ እንግዳ የሆኑ የእንግሊዝኛ ቃላትንና ሐረጎችን መጠቀሙ አግባብ ያለመሆኑን ወጣት ጋዜጠኞቹ ይረዱታል ወይ? በሬዲዮ ዝግጅት ላይ የሚደመጡ መሰል ችግሮችስ ማብቂያቸው መቼ ይሆን? በተለይ በሬዲዮ፣ በጥቅሉ ደሞ በኤሌክትሮኒክ የመገናኛ ብዙሃን፣ የስራ መስክ ከጀማሪ ዘጋቢነት /ሪፖርተርነት/ እስከ ዋና አዘጋጅነት የተሰማሩ ዜጎች የዚህ ዓይነት ችግሮች መከሰታቸውን አስተውለው ይሆን? አይመስለኝም፡፡ እንዴት ቢባል፣ ችግሩ ተመልካች ቢኖረው ኖሮ፣ እየተሻሻለ መጥቶ በጠፋ ነበር፡፡ ግን አልሆነም፡፡
ይሄ ችግር ከዕለት ወደ ዕለት እየተባባሰ ሄዶ በሃገራችን የኤፍ. ኤም. ሬዲዮኖችና በአድማጮች መካከል እንደ ባቢሎን ግንብ ታሪክ ያልተፈለገ መደነጋገርንና አለመግባባትን ከመፍጠሩ በፊት የሚመለከተው አካል የበኩሉን እርምጃ ቢወስድ ይበጃል ባይ ነኝ፡፡ ‹ያለውን የወረወረ ንፉግ አይባልም› ነውና እኔም ችግሩን በመፍታት ረገድ ሊያግዙ ይችላሉ ብዬ የማስባቸውን አንዳንድ ነጥቦች ብጠቋቁም ማለፊያ ይመስለኛል፡፡እናንተ በሬዲዮ ስራ ላይ የተሰማራችሁና ሌሎችም ጉዳዩ የሚመለከታችሁ ወገኖቼ ሆይ፣ ይህችን አነስተኛ ማስታወሻ ትኩረት ሰጥታችሁ ታነቧት ዘንድ የምጠይቃችሁ በታላቅ ትህትና ነው፡፡
አንድ በሬዲዮ የሚተላለፍ ዝግጅት ዓቢይና ተቀዳሚ ግቡ አድርጎ የሚነሳው ወደ አድማጩ መድረስን ነው፡፡ ይሄ ከታወቀ በኋላ ደሞ እንዴት ተደርጎ ነው ወደ አድማጭ መድረስ የሚቻለው የሚለው በተከታይ የሚታይ ይሆናል፡፡ ጋዜጠኛው ጽሑፉን በሬዲዮ ከማሰራጨቱ በፊት የሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ ዝግጅቱን ሊያጠናቅር ይገባል፡፡ እንዴት አድርጌ ነው ለአድማጬ የምናገረው? በምን ዓይነት ሁኔታ ነው ጽሑፉን የማቀናብረው? የትኛውን ዓይነት የቋንቋ አጠቃቀም ስልት ብከተል ይሻላል? እንዴት አድርጌ በአድማጬ አዕምሮ ውስጥ ስዕልን መፍጠር እችላለሁ?... የሬዲዮ ዝግጅት እነዚህንና ሌሎችንም መሰል ጉዳዮች መሰረት አድርጎ ቢሰራ በእጅጉ ውጤታማ ይሆናል፡፡
ሬዲዮ ስናዳምጥ ተናጋሪው ጋዜጠኛ እኛን በቀጥታ የሚያዋራን ያህል ሆኖ ይሰማናል፡፡ ይሄ ዓይነቱ ስሜት በይበልጥ ስኬታማ ሊሆን የሚችለው፣ አቅራቢው ጋዜጠኛ የኛን ቋንቋ ባግባቡ የተጠቀመ እንደሆነ ብቻ ነው፡፡ የእኛን ቋንቋ ስንል በዕለት ተዕለት ኑሯችን ላይ የምንጠቀምበትን መግባቢያ ማለታችን ነው፡፡
ሬዲዮ የሚያዳምጠው የህብረተሰብ ክፍል በዕድሜ፣ በእውቀት፣ በልምድ፣ በሃይማኖትና በፆታ የተለያየ ስለሆነ፣ ልንጠቀምበት የሚገባው መደበኛውን ወይም ከላይ እንደተጠቀሰው የዕለት ተዕለት መግባቢያ ቋንቋውን ሊሆን ይገባል፡፡ ቀበልኛ፣ የአራዳ፣ ወይም ኢ-መደበኛ ቋንቋን በሬዲዮ ዝግጅት ላይ መጠቀም ተገቢ አይደለም፡፡ ቀበልኛ፣ የአራዳ ወይም ኢ-መደበኛ ቃላት በአንድ በተወሰኑ አካባቢዎች ብቻ የሚነገሩና የሚታወቁ ስለሆነ፣ እነሱን በሬዲዮ መጠቀም በአድማጭ ዘንድ ግርታን ይፈጥራል፡፡
እንደቀይ፣ ለስላሳ፣ ንጹህና ሌሎች መሰል ገላጭ ቃላት፣ ወይም በቋንቋው የሰዋሰው አጠራር ቅጽሎች፣ አድማጩ በአዕምሮው የሚቀርፃቸውን ምስሎች ግዘፍ ነስተው በማቅረብ ረገድ አስተዋጽኦ ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ፣ ግሦች ወይም ድርጊትን የሚገልጹ ቃላት የሌሉባቸውና ቅጽሎች ብቻ የታጨቁባቸው ጽሑፎችና በሬዲዮ የሚተላለፉ ንግግሮች ወዝ የሌላቸው ደረቅ መነባንቦች ናቸው፡፡
ቅጽሎች መጠንን ወይም ዓይነትን አስቀድመው የመግለጽ ባህርይ ስላላቸው፣ የሬዲዮ አድማጩ በራሱ ሚዛን ነገሮችን እንዳያይ ወይም እንዳያመዛዝን አስቀድመው መንገድ ይዘጋሉ፡፡ አድማጩ ሬዲዮውን በሚያዳምጥበት ጊዜ፣ ይሄ ጥሩ ነው ወይንም ያኛው ጥሩ አይደለም፣ ብሎ በራሱ እንዳያዳንቅና እንዳያንኳስስ ያደርጉታል ለማለት ነው፡፡ ስለዚህ ቅጽሎችን በሬዲዮ ዝግጅት ላይ አብዝቶ ከመጠቀም መቆጠብ ይመከራል፡፡
ይልቁንም የሬዲዮ አዘጋጁ የድርጊት ቃላትን ወይንም ግሦችን አበርክቶ እንዲጠቀም ይመከራል፡፡
ግሦች ምስል ከሳች በመሆናቸው፣ አድማጩ የሚነገረውን ነገር አስመልክቶ ባይምሮው ምስሎችን እንዲፈጥር ያስችሉታል፡፡ ለምሳሌ፣ በሁለት እግሮች የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን በተለያዩ ግሦች ብንገልጻቸው፣ ድርጊቱን ባይምሯችን ጓዳ የማየቱ አጋጣሚው ይፈጠርልናል፡፡ ተራመደ፣ ሮጠ፣ ዘለለ፣ ጡብ ጡብ አለ፣ ተንጎራደደ፣ ዱብ ዱብ አለ፣ ተንቀረፈፈ፣ ሰገረ፣ …እነዚህ ግሦች ምስልን ባይምሮ የመከሰት አቅም አላቸው፡፡ውታፎችን (fillers) በተቻለ መጠን ለማስወገድ ጥረት ማድረግ ሌላው በሬዲዮ አዘጋጁ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ዓቢይ ጉዳይ ነው፡፡ ውታፎች እንደ፣ ‹‹እ…እ…እ፣ አዎ፣ ቅድም እንደጠቀስኩት፣ በመሰረቱ፣ ስለዚህ፣ እናም፣ ይሄን ካልኩ በኋላ፣ ብሎም ቢሆን ታዲያ…፣›› ዓይነቶቹ አላስፈላጊ መሙያዎች ናቸው፡፡ውታፎች ባመዛኙ የሚከሰቱት የሬዲዮ ጋዜጠኛው ያለበቂ ዝግጅት ስራውን ለአድማጮች ሲያቀርብ ነው፡፡
ባዕድ ቃላት፣ ሳይንሳዊና እንግዳ ቋንቋዎች፣ አዳዲስ አባባሎችና የውጭ ቋንቋዎች የተቀየጡባቸው ዝግጅቶች የሚተላለፈውን የሬዲዮ መልዕክት አድማጩ በትክክል እንዳይገነዘብ እንቅፋት ይሆናሉ፡፡ስኪ በሞቴ፣ ከላይ በዚህ ጽሑፍ መግቢያ ላይ የተጠቀሱትን፣ እንደ departure፣ cope up፣ rationally፣ in to consideration፣ destiny እና provisional ዓይነቶቹን በአማርኛ የሬዲዮ ዝግጅት የተላለፉ ባዕድ ቃላትና ሐረጎች ስንቶቹ ስፖርት - ወዳድ የሃገራችን ሕፃናት፣ ታዳጊ ወጣቶችና አዛውንቶች ተረድተዋቸው ይሆን? በትምህርት ቤቶች በራፍ ያለፍነውም ዜጎች ብንሆን፣ እንደነዚህ ዓይነቶቹን ከባድ ከባድ የእንግሊዝኛ ቃላት ፍቺያቸውን ለመረዳት መዝገበ ቃላትን ማማከር ሳያስፈልገን አይቀርም!
ቁጥሮችን ወይም አሃዞችን በሬዲዮ በሚተላለፉ ዝግጅቶች ላይ መከታተል አስቸጋሪ ነው፡፡ ስለዚህ የሬዲዮ አዘጋጁ ቢችል ባይጠቀምባቸው፣ ካልቻለም አቅልሎና አለስልሶ ቢያቀርባቸው የተሻለ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ፣ 15-02-2005 (በሬዲዮ ሲነገር ደሞ፣ አስራ-አምስት፣ ዜሮ ሁለት፣ ሁለት ሺህ አምስት) የሚለው ቀን፣ ወርና ዓመተ-ምህረትን አመልካች የቁጥሮች ስብስብ፣ ትናንት፣ ዛሬ፣ ከትናንት በስቲያ፣ የዛሬ-ዓመት በዚህ ቀን … በሚሉት ቢተካ የተሻለ ይሆናል፡፡ በተጨማሪም፣ ሰዓትን ለማመልከት፣ 2፡45 (ሁለት ከአርባ-አምስት) ከማለት ይልቅ፣ ለሶስት ሩብ ጉዳይ ቢባል መልካም ይሆናል፡፡ ሁለት ሰዓት ከሃያ-ስምንት (2፡28) የሚለውንም የሰዓት ገለጻ በማጠጋጋት፣ ሁለት ሰዓት ተኩል ወይንም ጧት ስራ በመግቢያ ሰዓት ላይ፣ በሚለው አቅልሎ ማቅረብ ይመረጣል፡፡ የስታትስቲክስ አሃዞችንም አቅልሎ በሬዲዮ መናገር ከአድማጩ የተሻለ ግንዛቤን ያስገኝልናል፡፡ ለምሳሌ፣ ከ9,000 መራጮች 3,000 ያህሉ (በሬዲዮ ሲነገር፣ ከዘጠኝ ሺህ መራጮች ሦስት ሺህ ያህሉ) ከማለት፣ ጠቅለል አድርጎ፣ አንድ-ሶስተኛው መራጭ፣ ቢባል የተሻለ ይሆናል፡፡ ሌሎችንም ንጽጽርን ማስጨበጫ ስልቶችን በተመሳሳይ ሁኔታ መጠቀም እንችላለን፡፡ ለምሳሌ፣ የኳስ ሜዳን ያህል ስፋት ያለው ቦታ ብንል፣ በስኩዌር ሜትርና በኤከርስ ከምንገልፀው በተሻለ አድማጮቻችን ግንዛቤን ያገኛሉ፡፡የሬዲዮ ስራ ጣዕምና ጥሩ ተቀባይነት እንዲኖረው ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ያስፈልጋል፡፡ የፈጠራ ክህሎት፣ የተመረጡ ቃላት እንዲሁም አጭርና ቀላል የሆኑ ዓ. ነገሮች ለሬዲዮ ዝግጅት በእጅጉ አስፈላጊ ግብአቶች ናቸው፡፡ ያልተደከመበትና በደንብያ ልታሰበበት ዝግጅት ከሆነ ደሞ፣ በአድማጭ ዘንድ የሚኖረው ተቀባይነት ሊቀንስ ይችላል፡፡ አንድ ጋዜጠኛ እጅግ በጣም ጥሩ የሆነ ፅሑፍ ቢያዘጋጅና ማለፊያ ድምፅ ቢኖረውም፣ ከላይ የተጠቀሱትን ነጥቦች መሰረት አድርጎ ዝግጅቱን ካልሰራ፣ በሬዲዮ የሚያስተላልፈው መልዕክት የተፈለገውን ግብ ላይመታለት ይችላል፡፡
ባጠቃላይ ግልፅ በሆነ ቋንቋና ሳይፈጥን በዝግታ በሬዲዮ የሚሰራጭ መልዕክት ባድማጮች ዘንድ ጥሩ ተቀባይነትን ያገኛል፡፡ ይሄ ዓይነቱ ጥንቃቄ ያልተለየው ዝግጅት ሬዲዮኖቻችንን የባቢሎን ግንብ ከመሆን ያድናቸዋል፡፡

Read 6237 times