Saturday, 12 January 2013 09:53

የአክሱማውያን የጥልፍ ጥበብና የጳውሎስ ኞኞ ዝክር - በዩኒቨርስቲ

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(2 votes)

የጳውሎስ ኞኞ ዝክር - በዩኒቨርስቲ
ባለቅኔ አያልነህ ሙላቱ በ1985 ዓ.ም “ጥገት ላም” በሚል ባሳተሙት የግጥም መጽሐፋቸው “ሕዝባዊ ፈጠራ” የሚል ርዕስ የሰጡት ግጥም አላቸው፡፡ በዚህ ግጥማቸው ውስጥ የጥንት ሕዝቦች፤ትምህርትና ዕውቀት ባልተስፋፋበት ዘመን፤ ከቅጠላ ቅጠልና ፍራፍሬ ጠቃሚውን ከጎጂ እየለዩ ቀጣዩ ትውልድ ለሺህ ዓመታት እየተመገበ ያለውን የምግብ ዘር አኑረውለታል፡፡ የብዙ ፈጠራዎች ባለቤት የሆነውን “ሕዝብ” ለማስተማር ከፈለግን ከእሱም ለመማር ዝግጁ እንሁን፣ሕዝብ የጀመረውን እናሳድግለት፣ባህላዊውን እናዘምንለት በሚል በፃፉት ግጥም ውስጥ የሚከተሉት ስንኞች ይገኙበታል፡-
ሕዝብን እናስተምር እንማር ከሕዝቡ
ተዝቆ የማያልቅ የብስ ነው ጥበቡ
ተጨልፎ የማያልቅ ባህር ነው ሃሳቡ፡፡

እና የእኛም ትውልድ አይሁን ቀንድ አውጣ
የልሒቅ ጠላ አይናቅ የእሱን ሳያጠጣ
እስቲ ለእንጀራ ሊጥ አንድ ፎርሙላ ያምጣ?
እስቲ ለጠጅ ብቅል አንዲት ቁጥር ያውጣ?
ጥንት ለተፈጠሩ ለአረቄ ለጠላ
እስቲ ተመራምሮ ይስጣቸው ፎርሙላ?
በሕዝብ ፈጠራ ላይ የእሱን ጥበብ ይሙላ
ይህ ነው ከሕዝብ መማር ሕዝብ ማስተማር ኋላ፡፡ ይህንን ግጥም ያስታወሰኝ ታህሳስ 25 ቀን 2005 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም የተከናወነው ዝግጅት ነው፡፡ በዕለቱ ከቀረቡ ዝግጅቶች መካከል የአክሱማዊያን የጥልፍ ሥራ ጥበብን የሚያስቃኘው አውደ ርዕይ አንዱ ነበር፡፡ በተቋሙ ሙዚየም ለአንድ ወር ለሕዝብ ክፍት ሆኖ የሚቆየው አውደርዕይ ስብስብ ከትግራይ በውሰት እንደመጣ ታውቋል፡፡ በአውደ ርዕዩ መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የተቋሙ ዳይሬክተር ዶ/ር አህመድ ሀሰን፣ “አገራችን ብዙ ባህልና ጥበብ አላት” በማለት፣በአክሱማዊያን ስልጣኔ ውስጥ አንጥረኝነትና ሽመና ትልቅ ስፍራ እንደነበረው ገልፀዋል፡፡ የተቋሙ የተለያዩ ኃላፊዎችም ተጨማሪ ማብራሪያ አቅርበዋል፡፡
በጥልፍ ሥራ፣ በሸማ ምርትና በጥጥ እርሻ ጀማሪነት ላይ የተለያዩ አመለካከቶች እንዳሉ በዕለቱ ተነግሯል፡፡ ጅማሬውን ለግብፁ የሚሰጡ አሉ፡፡ በተቃራኒው የጥጥ ምርት እንደ ቡና ሁሉ በመጀመሪያ የታወቀው በኢትዮጵያ ነው ብለው መከራከሪያ የሚያቀርቡም አልጠፉም፡፡
የጥንት ነገሥታት የሚለብሱት አልባሳት ልዩና ድንቅ የሆነውም የሸማ ማምረቻው ቴክኖሎጂ ባለቤት ስለነበርን ነው ሲሉ እንደማስረጃ ይጠቅሳሉ፡፡ መሐል ላይ የተቋረጠ ነገር ስላለ እውነታው ላይ ለመድረስ ሰፊ ጥናት ማካሄድ እንደሚገባም በአጥኚዎች ተጠቁሟል፡፡
ከኢትዮጵያዊያን የአገር ባህል አልባሳት አንዱ የሆነው የሻማ ምርትና የጥልፍ ሥራ በተለያየ አካባቢ የየራሱ የሆነ የተለየ አሰራር እንዳለው የአክሱማዊያን የጥልፍ ሥራ ጥበብ አንዱ ማሳያ በመሆን በሙዚየሙ ለዕይታ ቀርቧል፡፡
የጥልፍ ዲዛይኖች መልዕክትና ትርጉም እንዲኖራቸው ተደርገው መሰራታቸውን ለማሳየትም መጠሪያቸው እንደማስረጃ ቀርቧል፡፡ ጥንታዊ ታሪክና ስያሜ ከያዙት መሐል “ኢዛና”፣ “ዘውዱ” የሚል ስያሜ ያላቸው የጥልፍ ዲዛይኖች ይገኙባቸዋል፡፡
በተቃራኒው ወቅታዊ ክስተቶችን ተከትለው ስያሜ ከተሰጣቸው የጥልፍ ዲዛይኖች መካከል “ሸራተን”፣ “ሚሊኒየም”፣ “መቀሌ እመሪልኝ”፣ “እንኳን ደስ ያለን” … የሚሉት ይገኙባቸዋል፡፡ እዚህ ያቀረብኩት የአማርኛ ትርጉማቸውን ሲሆን ባለሙያዎቹ በክልላቸው ቋንቋ ነው የሰየሙት፡፡
ከትግራይ ክልል በውሰት የመጡት የጥልፍ ሥራ ጥበብ ውጤቶች ጉብኝት ካበቃ በኋላ ሁለተኛው ዝግጅት በራስ መኮንን አዳራሽ ቀጠለ፡፡ ይህንን ዝግጅት የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም፣ ከኢትዮጵያ ወዳጆች ማህበርና ከኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ጋር በትብብር ያሰናዱት ሲሆን ርዕሰ ጉዳዩ ጋዜጠኛና ደራሲ ጳውሎስ ኞኞን የሚያስታውስና የባለታሪኩን መፃሕፍትና ሽልማቶች ለተቋሙ የማበርከት ፕሮግራም ነበር፡፡ የዕለቱን መድረክ የመምራት ኃላፊነት የተሰጣቸው የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው በለጠ፣ በ1953 ዓ.ም የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበርን ከመሠረቱት አንዱ ጳውሎስ ኞኞ መሆኑንና በተራ ቁጥር 40 ላይ ሥሙ ሰፍሮ መገኘቱን ተናግረዋል፡፡ ጳውሎስ ኞኞን በተመለከተ ንግግር እንዲያቀርቡ የተጋበዙት ደራሲና ሐያሲ አስፋው ዳምጤ በበኩላቸው፣ ጳውሎስ በ59 ዓመት የሕይወት ዘመኑ ብዙ ሥራዎች መስራቱን ገለፁ፡፡ በብርቱ አንባቢነቱ ምክንያት ኢንሳይክሎፒዲያ እስከማዘጋጀት (ያልታተመ) መድረሱን በማስታወስም፣ እናቱ ከቦታ ቦታ ይንቀሳቀሱ ስለነበር በአንድ ቦታ ተረጋግቶ ትምህርቱን ለመከታተል እንቅፋት እንደሆነበት ጠቁመው፣ ሆኖም “እናቱ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያነብላቸው ፊደል እንዲማር ማድረጋቸዉ በኋላ ለታወቀበት ፀሐፊነቱ መሠረት ጥለውለታል” ሲሉ የትምህርት ታሪኩን አስረድተዋል፡፡ ጋዜጦች ላይ መስራቱና ብርቱ አንባቢነቱ ለደራሲነት አብቅተውታል ያሉት ተናጋሪው፣ ከጳውሎስ ሥራዎች አንዱን በመምረጥም የሚያነሳቸው ርዕሰ ጉዳዮች ምን ይመስሉ እንደነበር ለታዳሚው አብራርተዋል፡፡
ሌላኛው ንግግር አቅራቢ የጳውሎስ ኞኞ የሥራ ባልደረባና የቅርብ ጓደኛ የነበሩት ጋዜጠኛ አጥናፍሰገድ ይልማ፣ “ከእኔ በተሻለ ስለ ጳውሎስ መናገር የሚችል አለ ለማለት አልደፍርም” ካሉ በኋላ “ስለ ጳውሎስ እንድናገር ስጋበዝ ምኑን አንስቼ ምኑን እንደምተው እቸገራለሁ” በማለት ንግግራቸውን ጀምረዋል፡፡
በንጉሡ ዘመን የነበርነው ጋዜጠኞች የቱንም ያህል ብንሳሳትም ሆነ ብናጠፋ ያን ያህል ከባድ ቅጣት አይፈፀምብንም ነበር ያሉት አቶ አጥናፍሰገድ፣ እንዲህም ሆኖ ብርሃኑ ዘሪሁንና ጳውሎስ ኞኞን የመሳሰሉ ደፋርና ኃይለኛ ጋዜጠኞች በተለያየ መልኩ መቀጣታቸውን ሲናገሩ፣ “ጳውሎስ ኞኞ በገንዘብ የተቀጣበት ጊዜ ነበር፣ ከሥራ ቦታ እንዲቀይር ተደርጓል፣ ተፈርዶበት ታስሯል፣ ይግባኝ ጠይቆ ዳኞች ባሳዩት ልዩ አክብሮት ፍርዱ ተሽሮለታል” ብለዋል፡፡
ከጳውሎስ ኞኞ ሥራና ተግባራት ጋር በተያያዘ የሚያስታውሷቸው ልዩ ልዩ ገጠመኞችንም አቅርበዋል፡፡ በ1953 ዓ.ም በንጉሡ ላይ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ሲደረግ ጓደኞቹን ጠርቶ ዝም ብለን ማየት የለብንም በማለት “አዲሱ መንግሥት ግፋ ወደፊት!” የሚል መፈክር እያሰማና ሰልፉን እየመራ ጥቂት እንደተጓዙ በቅርብ ርቀት ወታደሮች ቆመው ሲመለከት፣ መፈክሩን በመለወጥ “ኃይለሥላሴ ድረስ በነፍሴ!” በማለት ጉዳዩን ወደ ቀልድና መዝናኛ መለወጡ ብዙዎቹን የሥራ ባልደረቦቹን አስገርሟቸው እንደነበር እንደ አንድ ገጠመኝ አስታውሰውታል፡፡
ሌላው ገጠመኝም ከንጉሡ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ጳውሎስ ኞኞ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ “አንድ ጥያቄ አለኝ” በሚለው ዓምድ የሚያወጣቸውን ጽሑፎች ዘወትር ከሚያነቡለት አንዱ አፄ ኃይለሥላሴ ነበሩ፡፡ በአንዱ ዕለት “እስላምና ክርስቲያን መጋባት ይችላሉ ወይ?” በሚል ለቀረበለት ጥያቄ “አዎ ይችላሉ” የሚል መልስ ይሰጣል፡፡ በዚህ ጥያቄና መልስ አፄ ኃይለሥላሴና ራስ መስፍን ስለሺ ይከራከራሉ፡፡ ሁለቱ መግባባት ሲያቅታቸው እንዴት እንደሚቻል ጳውሎስ ኞኞ መልስ እንዲሰጣቸው ቤተመንግሥት ድረስ ተጠርቶ ይሄዳል፡፡ በምላሹም አፄ ኃይለሥላሴ የክርስቲያኑም የእስላሙም ንጉስ እንደሆኑት ሁሉ እሱም በጋዜጠኝነት ሙያው ለሁሉም በእኩል እያገለገለ፣ አንድነትና ዕድገት ለማምጣት እንደሚሰራ ገለፀላቸው፡፡ በዚህ ምላሹም የታይፕራይተር ሽልማት ተሸልሟል፡፡
ሌሎች የዝግጅቱ ተሳታፊዎችም ስለ ጳውሎስ ኞኞ የሚያውቁትን ተናግረዋል፡፡ በመጨረሻም የጳውሎስ ኞኞ ልጅ ሐዋርያው ጳውሎስ፣የአባቱ ሠርተፊኬቶች፣የእጅ ጽሑፎችና የግል ንብረቶች በተቋሙ ጥበቃ ስር እንዲቆዩ አበርክቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የጳውሎስ ኞኞ የሕይወት ታሪክ በጓደኛው በአቶ አጥናፍሰገድ ይልማ እየተዘጋጀ መሆኑም በዕለቱ ተገልጿል፡፡

Read 5454 times