Saturday, 12 January 2013 09:38

የገና ጥቁር እንግዳ

Written by  ኤርምያስ ፍቅሬ
Rate this item
(0 votes)

እንግዳ መሆን እንዴት ደስ ይላል? እኛ ከመቶ በላይ የምንሆን የዲላ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነት እና ኮሙኒኬሽን የሁለተኛ እና የሶስተኛ ዓመት ተማሪዎች በአዲስ አበባ የሚገኙ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት እንግዶች ለመሆን ከአንድ ወር በላይ ስንዘጋጅ ቆይተናል፡፡ በንድፈ ሃሳብ የተማርነውን ጋዜጠኝነት በተግባር ልናየው፤ነገ ባለቤቶቹ የምንሆንበትን ሙያ በእንግድነት ልንጐበኘው፤ታሕሳስ 19 ቀን 2005 ዓ.ም ከረፋዱ 5፡40 ላይ በሶስት መምህራኖቻችን ፊታውራሪነት በሁለት ሽንጠ ረጃጅም አውቶብሶች ተሰይመን ጉዞአችንን ጀመርን፡፡
ከመነሻችን የጌዴኦ ዞኗ ዲላ ከተማ የሲዳማዎቹን ጩኮ፣ ይርጋለም አፖስቶን ጨምሮ ሌሎች ትናንሽ የገጠር ከተሞች አቆራርጠን ሃዋሳ ለመድረስ ከሁለት ሰዓት ያልበለጠ ጊዜ ነበር የፈጀብን፡፡ ሻሸመኔ፣ ዝዋይ፣ መቂን ጨምሮ የምዕራብ አርሲ እና የደቡብ ሸዋ ከተሞችን አቆርጠን አዳማ ለመግባት፣ ሞጆን ወደ ግራ ትተን ቀኛችንን ስንይዝ፣ ፀሐይዋ የማደሪያዋን በር ለማንኳኳት እጇን ሰድዳ ነበር፡፡

እንግድነታችን አሃዱ ብሎ የጀመረው በማግስቱ ቅዳሜ ታሕሳስ 20 ቀን 2005 ዓ.ም አዳማ ከሚገኘው የኦሮሚያ ሬዲዮና ቴሌቭዥን ድርጅት ነበር፡፡ የኦሮሚያ ሬዲዮና ቴሌቭዥን ድርጅት በዘመናዊ መሳሪያ የተሟላ ስቱዲዮ ያለው ሲሆን ከክልሉ አልፎ በመላ ሀገሪቱ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ስርጭቱን እያስተላለፈ እንደሚገኝም ተገልፆልናል፡፡ 
በግማሽ ቀን ጉብኝታችንም ጋዜጠኛ ማለት አንባቢ፣ ፀሐፊ ወይም ደግሞ ዘጋቢ ብቻ አለመሆኑን በተግባር አይተናል፡፡
(ሁሉን ቢናገሩት…ሆኖብኝ ሁሉንም ለመዘርዘር ባልችልም እንደው የእንግድነታችንን ያየነው ለማካፈል ያህል ሁሉን በጨረፍታ ነውና ብዙው ከውስጣችን እንደቀረ ይታወቅልኝ፡፡)
ሁለተኛው ጉብኝታችን የቀጠለው ከአንድ ቀን እረፍት በኋላ ነበር፡፡ እሁድን ያሳለፍነው አዳማ ዩኒቨርሲቲን በመጐብኘት፣ ሶደሬ በመዝናናትና እና ከተማዋን በመቃኘት ነበር፡፡
ሰኞ እለት የጎበኘነው አዲስ አበባ የሚገኘውን ፋና ብሮድካስት ኮርፖሬትን ሲሆን ግዙፉ ባለ ቢጫና ሰማያዊ ቀለም የኮርፖሬቱ ህንፃ ከኮሚኒኬሽን ኦፊሰሩ ገለፃ ጋር ተቀበሎናል፡፡ ቡድናችን ለሁለት የተከፈለበት ጉብኝታችን የተጀመረው ከአስረኛ ፎቅ ነበር - ከኤፍ ኤም ማሰራጫ ስቱዲዮው፡፡ ጋዜጠኝነት በትምህርት ብቻ የሚገኝ ሳይሆን የተፈጥሮ ስጦታ ጭምር እንደሆነ እዚያው ፋና ውስጥ በሌላ ሙያ ተመርቀው በጋዜጠኝነት የሚሰሩ ባለሙያዎች አረጋግጠውልናል፡፡ በፋና የተመለከትናቸው ዘመናዊ የመገናኛ ቴክኖሎጂዎች ጋዜጠኝነት ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር መጣመር እንዳለበት ጥሩ ግንዛቤ አስጨብጠውናል፡፡
(መቼም “ዶሮ ብታልም …” ነውና የሚያስተምረን ዩኒቨርስቲ እንደው በትንሹ አንድ የሚዲያ ተቋም ምን እንደሚመስል በናሙና መልክ የሚያሳይ ክፍል ቢኖረው ወደሙያው ስንገባ ግር እንዳይለን ያግዘናል የሚል ሃሳብ አለኝ)
ወደ ፋና ልመልሳችሁና በአሁኑ ወቅት ፋና በሬዲዮና በኢንተርኔት ፕሮግራሞቹን እያቀረበ ሲሆን በቅርቡ የቴሌቭዥን ስርጭት ለመጀመር በዝግጅት ላይ መሆኑ ተነግሮናል፡፡
ሶስተኛው ጉብኝታችን ደግሞ በአንጋፋው የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ነበር - ማክሰኞ እለት (ሃያ አራት ሰዓት የሚሰራ ድርጅት አይደክመውም አልኩ ለራሴ) ወደ ውስጥ ስንገባ ከፓርላማ የጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ ንግግር በቀጥታ ስርጭት እየተላለፈ ነበር፡፡ ይህም አጋጣሚ ስለ ቀጥታ ስርጭት በቀጥታ ትምህርት ለመውሰድ አስችሎናል- በሬዲዮና በቴሌቭዥን፡፡
(በአንድ መስኮት ብቅ ለሚል ምስል ዕዳው ለካ ብዙ ነው!) ኢሬቴድ እንደ አንጋፋነቱ አንዳንድ የሚጠቀምባቸው መሳሪያዎችም አንጋፋ እንደሆኑ በጉብኝታችን ወቅት ታዝበናል፡፡ በአብዛኛው በቴክኒክ ክፍሎችና ስቱዲዮ ላይ ያተኮረው ጉብኝታችን የቴሌቭዥን ፕሮዳክሽንን ውስብስብነት አሳይቶናል፡፡
(የግል ቴሌቪዥን ጣቢያ ያልተፈቀደው ውድና አድካሚ ስለሆነ የሚያቋቁሙት ባለሃብቶች እንዳይቸገሩ ታስቦ ይሆን?ማለቴ አልቀረም)
በልጅነቴ ኢዜአ ምንድነው እያልኩ እጠይቅ ነበር፡፡ የረቡዕ ዕለት ጉብኝታችን ከሰሜን ሆቴል ከፍ ብሎ በቆመው ዝምተኛው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ውስጥ ነበር፡፡ ጉብኝታችን አጭር እና ፈጣን ነበር፡፡ የኢትዮጵያ የወሬ ምንጭ ይባል የነበረው ይህ የመንግስት ኤጀንሲ ዋነኛ ተግባሩ ዜናዎችን ሰብስቦ ለተለያዩ ሚዲያዎች ማሰራጨት እንደሆነ ተገልጾልናል፡፡
የዜና ምንጭ ሆኖ ያገለግላል ማለት ነው፡፡ ኤጀንሲው የራሱን የሚዲያ ተቋም ለመክፈት ጥናት በማድረግ ላይ እንደሆነና እንደቀድሞው የተሟሟቀ ሁኔታ ላይ አለመሆኑን አስጐብኛችን ገልፀውልናል፡፡
የሀሙስ ጉብኝታችንን ለየት የሚያደርገው ከሰዓት በኋላ መሆኑ ብቻ ሳይሆን የምንጎበኘው የግል ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል መሆኑም ጭምር ነበር፡፡
ካዛንቺስ ከሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚ/ር በግምት 200 ሜትር ገባ ብሎ በሚገኘው የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ተገኝተንም የሚጎበኘውን ሁሉ ጎብኝተናል፡፡ እስከአሁን ካየናቸው ሚዲያዎች አንድ ፎቅ ያለው እና የዝግጅት ክፍሉን በኪራይ ቤት ውስጥ ያደረገ ብቸኛ ተቋም ነው፡፡ ስራው ጋዜጣ ማሳተም ብቻ የሆነው ይህ የግል ሚዲያ ተቋም፣ የራሱ ዌብሳይት እንዳለው ተገልፆልናል፡፡ እዚህ እንደ ሌሎች ሚዲያዎች ብዙ ሰራተኞችና በርካታ ክፍሎች እንዲሁም ጥብቅ ፍተሻ አልገጠመንም፡፡ በዝግጅት ክፍሉ ያየነው ሌላው ለየት ያለ ነገር በጋዜጣው ጠንሳሽ በአቶ አሰፋ ጐሳዬ የተሰየመው የህዝብ ቤተመፅሀፍት ነው፡፡ እንደ ጉብኝታችን ማሳረጊያም ከዋና አዘጋጁ ነቢይ መኮንን የረጅም አመት ልምድ እና እውቀት ተካፍለናል፡፡
ከሁሉ በሚልቅ መልኩ ጋዜጠኝነት ሁለገብ ሙያ እና መስጠትን የሚሻ መሆኑን ከሙያ አባታችን ቀስመናል፡፡ ቴክኖሎጂው፣ ኮምፒውተሩ፣ ካሜራው፣ መቅረፀ ድምፁ ወዘተ ተቀፅላዎች ናቸው፣ ለጋዜጠኛው ዋናው እና መሰረታዊ ነገሩ ማወቅ፣ ማስተዋል፣ አካባቢን ማየት፣ ህዝብን ማዳመጥ፣ ካዩት፣ ካወቁትና ከዳሰሱት ዕውቀትን መካፈል፣ ልምድ መውሰድ መሆኑን ጋሽ ነቢይ ከተመክሮው ጨልፎ አቃምሶናል
የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ ከተመክሮው ሲያካፍለን አድማሶች ምስላችንን በቪዲዮ ካሜራ ሲቀርፁ የነበረ ሲሆን ለማስታወሻነትም የአዲስ አድማስ አርማ ያረፈበት ብዕር (ለኔ አልደረሰኝም ቅሬታ ግን አይደለም) እና የቁልፍ መያዣ አበርክተውልናል፡፡ በዚህ አጋጣሚ የጋዜጣው የታህሳስ 27 ቀን 2005 ዓም እትም የዜና ገፅ ላይ “የገና ዋዜማ እንግዶች” በማለት ለእንግድነታችን እውቅና ስለሰጡን ምስጋናዬን በጓደኞቼ ስም አቀርባለሁ፡፡
የመጨረሻው ጉብኝታችን አርብ ማለዳ፣ ሀያ ሁለት ማዞሪያ ከጌታሁን በሻህ ህንፃ ወረድ ብሎ በሚገኘው ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ነበር፡፡ በግል ተቋምነት የሚመደበው እና የመንግስትን ፖሊሲ እንደሚደግፍ የተነገረን ዋልታ፣ እንደ ኢዜአ ሁሉ የዜና ምንጭ በመሆን እንደሚሰራ ተገልጾልናል፡፡ በተጨማሪም እንደ “ሀገሬ” ያሉ የተለያዩ ዶክመንተሪ ፊልሞችን እንደሚሰራ እና ለትርፍ የተቋቋመ መሆኑም ተነግሮናል፡፡ የራሱ የሚዲያ ተቋም ለመክፈት እቅድ እንዳለው፣ እስከዚያው ግን በኦሮሚያ ቴሌቪዥን በየሣምንቱ እሁድ ከቀኑ 5፡00 - 7፡00 ለሁለት ሰዓታት የራሱን ፕሮግራም እንደሚያቀርብ ከአስጎብኛችን ገለፃ ለመረዳት ችለናል፡፡
ጉብኝታችን በመገናኛ ብዙኃን ላይ ያተኮረ ቢሆንም ከተለያዩ የሀገሪቷ ክፍል የተውጣጣነው የዲላ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሚኒኬሽን ተማሪዎች በእንግድነታችን ወቅት፣ ብዙ ነገሮችን አይተናል ታዝበናል፡፡ የ104 የወደፊት ጋዜጠኞች አይን ምን ያህል ሊያይ፣ ሊታዘብ፣ ሊፅፍ እና ሊናገር እንደሚችል እናንተ አስቡት፡፡ የሆነ ሆኖ የ2ኛ እና የ3ኛ አመት የጋዜጠኝነት እና ኮሙኒኬሽን የትምህርት ክፍል ተማሪዎች ቡድን፣ ቅዳሜ ማለዳ በመጣበት አኳኃን ወደ ዲላ ዩኒቨርስቲ ተመልሶ በሰላም ገብቷል፡፡ ምንም እንኳ እኔ የገናን አውዳመት ሰበብ አድርጌ እዚሁ አዲስ አበባ ብቀርም ልቤ ግን አብሮ ዲላ ገብቷል - ወደፊት ጋዜጠኛ ሆኖ ሊመለስ ተስፋ ሰንቆ፡፡
እኔ የምለው አድማሶች የጥምቀት ጥቁር እንግዳችሁ ደግሞ ማን ይሆን? መልካም የስራ ጊዜ እመኝላችኋለሁ!
(ኤርምያስ ፍቅሬ የዲላ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነት እና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ክፍል የ2ኛ ዓመት ተማሪ ነው፡፡ ፀሃፊውን This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. የኢሜይል አድራሻው ማግኘት ይቻላል)


Read 4200 times