Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 12 January 2013 09:35

“ከሳቅህ ዓለም አብሮህ ይስቃል፡፡

Written by 
Rate this item
(4 votes)

ከአንኮራፋህ ብቻህን ትተኛለህ!” - ኖዌል ካዋርድ
የሀገራችን ደራሲና ተርጓሚ የሆነ ፀሐፊ በቅርቡ የስኮትላንዳውያንን ባህሪ አስመልክቶ ባሳተመው ቁም ነገር - አዘል የቀልድ መጽሐፍ የሚከተለው ይገኝበታል
ስኮትላንዳዊው በጣም ተቸግሯል፡፡ የንግድ ሥራው ተሰነካክሎ ከፍተኛ የፋይናንስ ቀውስ ውስጥ ነበር፡
በቀቢፀ - ተስፋ ተውጦ ፈጣሪውን፣
“እባክህን እርዳኝ፤ የመጠጥ ግሮሰሪዬ ተሸጠ፡፡

አሁንም ቶሎ ገንዘብ ካላገኘሁ ቤቴ በሀራጅ መሸጡ አይቀርም፡፡ ስለዚህ እባክህን ሎተሪ እንዲደርሰኝ እርዳኝ” እያለ ተማፀነው፡፡ 
ሎተሪ በወጣበት ምሽት ግን እድሉ ለእርሱ ሳይሆን ለሌሎች ሰዎች ደረሰ፡፡
ተስፋ ሳይቆርጥ “አምላኬ፣ እባክህን እርዳኝ፤ የመጠጥ ግሮሰሪዬን፣ ቤቴንና መኪናዬን ሁሉ አጥቻለሁ!” ብሎ እያለቀሰ ለመነ፡፡
ሆኖም በቀጣዩ ጊዜም ሎተሪ አልደረሰውም፡፡
ነገር ግን አሁንም ልመናውን አላቋረጠም፡፡
“ግሮሰሪዬ፣ ቤቴ፣ መኪናዬ፣ የቤት ዕቃዎቼ በሙሉ ተሸጡ፡፡ አሁን ደግሞ ቤተሰቤ እየተራበ ነው፡ ከዚህ ቀደም እምብዛም አስቸግሬህ አላውቅም፡፡ ታዛዥህ እንደሆንኩም ታውቃለህ፡፡ እባክህን ሎተሪ እንዲደርሰኝና እንድቋቋም እርዳኝ!” እያለ በመደጋገም ፈጣሪውን ተማፀነው፡፡
በመጨረሻ ኃይለኛና የሚያጥበረብር ብርሃን ታየ፡፡
እግዚአብሔር መንበሩ ላይ እንደተቀመጠ እያናገረው ነበር፡፡
“ሰውዬ፣ ቢያንስ ግማሽ መንገድ እንኳን መጥተህ ልትቀበለኝ በተገባ፡፡ እስኪ በመጀመሪያ የሎተሪ ቲኬት ግዛ!” አለው፡፡
***
ቤት ንብረት በሀራጅ ከሚያስሸጥ ድህነት ይሰውረን፡፡ በሎተሪ ከሚያሳምን የገጠመኝ ዘመን ያውጣን፡ ከሁሉም በላይ ግን ለመለመን እንኳ ጥቂት የራስ መንቀሳቀስ እንደሚያሻን መገንዘቢያ የሚሆነን ልብ ይስጠን!!
በሀገራችን ከድህነት እኩል የሚፈታተነን ችግር፤ ቢያንስ ግማሽ መንገድ እንኳ ሄዶ ለመደራደር ዕውቀቱን፣ ጥበቡን አሊያም ቀና ልቡናውን ማጣታችን ነው፡፡ ግማሽ መንገድና (Come half way እንደማለት) የመቻቻል፣ ልዩነትን የማስተናገድ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን የመልመድ ትልቅ ፀጋ ነው፡፡
አገር በኔ ብቻ ተመርታ አገር አትሆንም ብሎ፤ ኃይለኛውና አሸናፊው ከወጣበት መሠላል ዝቅ ብሎ፤ ግማሽ መንገድ ወርዶ እንነጋገር፣ እንወያይ የማለት ባህል፤ ተሸናፊውም ከቁጭቱ፣ ከቂሙ፣ ለመጣል እንጂ አብሮ ለመቀመጥ አልፈልግም የሚልበትን ግትር አቋም ትቶ፤ እኔም የሀገር ጉዳይ ያገባኛል፣ “እንድትሰፉ እንጂ እንደትጠፉ አልፈልግም” ብሎ፤ መንገድ መሻት ያሻዋል፡፡
በርተን ሮሼ የተባለ ፀሀፊ “እንደ ሔዋን ባዶነት ተሰማኝ፡፡ ያለምንም የኋላ ታሪክ ከአዳም ግራ ጎን ሙሉ ሰው (አዋቂ) ሆና ስትፈጠር ምን ያህል ባዶነት እንደተሰማት የገባኝ አሁን ነው” ይለናል፡፡ የኋላ ታሪክ የሌለው የሚያውቀው ዛሬን ብቻ ነው፡፡
የአንድ ቀን ታሪክ የሌለው የሚያውቀው ዛሬን ብቻ ነው፡፡ አንድ ቀን ባዶነት መሰማቱ አይቀርም፡፡ ከሌላ አካል ተከፍሎ መፈጠር ዕድሜ ልክ ሙሉነት ሳይሰማን እንድንኖር ማድረጉ አሌ አይባልም፡፡ ራስን ችሎ፤ በራስ ተማምኖ ለመኖር ራስን ሆኖ መፈጠርን ይጠይቃል፡፡
በሀገራችን በፖለቲካ መከፋፈል እንጂ ተስማምቶ መጓዝ አይሆንልንም፡፡ ከረዥም ጊዜ ጀምሮ እንደባህል የተያዘ ፈሊጥ ነው፡፡ “አይጥና ድመት የታረቁ ለታ ባለግሮሰሪው/ባለንብረቱ ወዮለት!” ይላሉ ፐርሺያውያን፡፡
አይጥና ድመት እንኳ ታርቀው ጠላታቸውን የሚያጠቁበት ቀን ይመጣል ነው ፐርሺያውያን የሚሉን፡፡
“የማይለወጥ ነገር የለም - ከለውጥ ህግ በስተቀር” (Everything changes, except the law of change) ታሪካችንን ወደኋላ ብንመረምር ምን ያህል እንደተለወጥን ወይም እንደተለዋወጥን መገንዘብ ቀላል ነው፡፡
ስለተሰሩ መንገዶች፣ ስለፈረሱ ቤቶችና ስለተሠሩ ህንፃዎች፣ ስለታሰሩ ሰዎችና ስለተፈቱ ሰዎች፤ ስለተፃፉ ደንቦችና ስለተጣሱ ህጐች፤ ስለማይሸጡ መሬቶችና በሊዝ ስለተወሰዱ መሬቶች፤ ስለማይነኩ ሰዎችና ኋላ ስለተወረወሩ ሰዎች፡፡ ለውጥ አይቀሬ ነው፡፡ ህገመንግስቱን እንኳን “የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል አይደለም ሰው ነው የፈጠረው ሰው ይለውጠዋል፡፡” ብለው ነበር የቀድሞው መሪ፡፡ የብሔር ብሔረሰብ አካሄዳችንም ወደ ኢንዱስትሪ ልማት የሚሸጋገርበት ቀን ሊመጣ ይችላል፡፡
አየርላንዳውያን፤
“ዕድሜ ሙሉ ከመሞት ለአንድ ደቂቃ ፈሪ መሆን ይሻላል” ማለታቸውን አንርሳ፡፡ “ዘለዓለም ውሻ ሆኖ ከመኖር አንድ ቀን አንበሳ ሆኖ መሞት” የሚለውን መዘንጋትም ተገቢ አይሆንም፡፡ ሁሉም ወቅት ወቅት አለውና! ሁኔታዎችን እንደየአመጣጣቸው መመዘን፣ እንደየልኬታቸው ዓይነተኛ መፍትሔ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ በደስታ ሰዓት ደስታችንን መግለጽ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ የሚያዘናጉንን ሁኔታዎች፤ ይሆነኝ ብሎ ማሰብ ወሳኝ ነው! ይሄ በፖለቲካም፣ በኢኮኖሚም፣ በባህልም፣ በሥነ አዕምሮአዊ ሂደትም፤ ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡ መንግሥትም፣ ፓርቲም፣ ግለሰብም ተሁኖ ቢታሰብ፤ ዋናው ነገር ይሄው ነው፡፡ “ከሳቅህ ዓለም አብሮህ ይስቃል፡፡ ካንኮራፋህ፤ ብቻህን ትተኛታለህ!” የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ እንዳንተኛ አናንኮራፋ!

Read 7099 times