Print this page
Saturday, 12 January 2013 09:18

ጅማ ዩኒቨርሲቲ በአዲስ አበባ በማስተርስ ደረጃ ማስተማር የሚያስችለው ስምምነት ተፈራረመ

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(0 votes)

ጅማ ዩኒቨርሲቲ በአዲስ አበባ በህብረተሰብ ጤናና በቢዝነስ አስተዳደር በማስተርስ ደረጃ ለማስተማር የሚያስችለው ስምምነት ትናንት ተፈራረመ፡፡ ዩኒቨርሲቲው የስምምነት ሰነዱን የተፈራረመው ኤቢኤች ሰርቪስ ከተባለና በስልጠና፣ በጥናትና ምርምር፣ በጤናና በማህበራዊ ሳይንስ ዘርፎች እንዲሁም በፕሮግራምና ፕሮጀክት ትግበራ ላይ ከሚሠራ የግል ኩባንያ ጋር ነው፡፡
የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍቅሬ ለሜሳና የኤቢኤች ሰርቪስ ኤክስክዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ማርቆስ ፈለቀ፤ የስምምነት ሰነዱን ትናንት በሸራተን አዲስ በተካሄደ ስነ ስርዓት ተፈራርመዋል፡፡

በስምምነቱ መሠረትም፤ ዩኒቨርሲቲው በአዲስ አበባ ከተማ በህብረተሰብ ጤናና በቢዝነስ አስተዳደር ትምህርት ዘርፍ በድህረ ምረቃ ደረጃ ትምህርት እንደሚሰጥ በዚሁ ጊዜ ተገልጿል፡፡ የድህረ ምርቃ ፕሮግራሞቹን ሥርዓተ ትምህርት ጅማ ዩኒቨርሲቲ በመቅረፅ የሚመራ ሲሆን ኤቢኤች ሰርቪስ የተባለው ኩባንያ በኢንፎርሜሽንና ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት የሚሰጡ ቤተመፃህፍትና የትምህርት መርጃ መሣሪያዎችን በማቅረብና የስልጠና ቦታዎችን በማመቻቸት በጋራ እንደሚሰሩ በመግባቢያ ሠነዱ ላይ ተገልጿል፡፡ 
የፕሮግራሙ በአዲስ አበባ መጀመር ሥራቸውን እየሰሩ ራሳቸውን በትምህርት ለማሳደግ ለሚፈልጉ ወገኖች ትልቅ እድል ያመቻቸ መሆኑንና በህብረተሰብ ጤናና በቢዝነስ አስተዳደር የተጀመረው ትምህርት ሌሎች የትምህርት ዘርፎችን ጨምሮ ወደ ዶክትሬት ድግሪ ደረጃ የማሳደግ እቅድ እንዳለ ታውቋል፡፡
ጅማ ዩኒቨርሲቲ በ1992 ዓ.ም የተመሰረተና ዋናው ካምፓስ የግብርና እና የእንስሳት ህክምና ኮሌጅ፣ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅና የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በሚባሉ አራት ካምፓሶች ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ላይ የሚገኝ የመንግስት ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡

Read 4518 times