Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 05 January 2013 14:03

ሞኝ ሸንጐ ተሰብሳቢ አገኘሽ ቁርስ የሌለው ቡና አፈላሽ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

አንዳንድ ተረቶች ካልተደጋገሙ አይሰሙም፡፡ “ተናገርን ማንም ስለማይሰማ፤ ደግመን እንናገረዋለን” ብሏል አንድ ፀሐፊ፡፡ (We said it; as no one listens, we will say it again) አወጋጉን እንለውጠው እንጂ ወጉ የዱሯችን ነው!
ከዕለታት አንድ ቀን ሁለት ደገኞች ጐረቤታሞች ነበሩ ይባላል፡፡ የኑሮ እሽክርክሪት አልለወጥ ብሏቸዋል፡፡ ያርሳሉ፤ ያርሳሉ፤ ያርሳሉ፡፡ ኑሮ አልገፋ አላቸው፡፡ እንደውም አንዳንዴ እየከፋ፣ እየባሰ ይመጣ ጀምሯል፡፡
ከጥቂት ጊዜ በኋላ አንደኛው ገበሬ በድንገት በልጽጐ ታየ፡፡

የሣር ክዳን ጐጆው ቀረችና ቆርቆሮ አስመታ፡፡ በአጋም ታጥሮ የነበረው አጥሩ ከዳር ዳር በፍልጥና በሽቦ ታጠረ፡፡ ጠዳ ጠዳ ያለ ልብስ ይለብስ ጀመር፡፡ ባልተቤቲቱም እንደዚያው ወደአደባባይ የምትወጣው ድር በድር ለብሳ ሆነ፡፡ ግቢያቸው ከነአትክልቱ ዐይን ይስብ ጀመረ። 
እንደሌላው የመንደሩ ሰው ሁሉ ያ ጐረቤቱ ገበሬ፤ ለውጡ ግርም ብሎታል፡፡
በሆዱ፤ “እንዴት ለእኔ ሳይነግረኝ” አለና ተቆጨ፡፡ “ይሄ ሁሉ ሀብት መቼም ያለነገር አልመጣም! በእኛ አገር ወይ ዕቁብ ካልተገኘ፣ ወይ ውርስ ካልመጣ፣ አሊያም ሙግት ረትቶ እርስት ካልወሰደ፤ አለበለዚያም ካልዘረፈ፤ ሰው ከመሬት ተነስቶ ዲታ አይሆንም!” አለ። ጐረቤቴ፣ ወዳጄ ነው፡፡ ለምን ሄጄ አልጠይቀውም?” አለና ወደጐረቤቱ ሄደ፡፡ ከዚያም፤
“ወዳጄ፤ ደህና ሰነበትክ?” አለው፡፡
“ደህና ነኝ፡፡ አንተስ እንዴት ከረምክ ወዳጄ?” አለ ጐረቤት፡፡
“ጐረቤቴ ሆነህ እንደው ባንድ ጊዜ ይሄን ሁሉ ካብት ስታፈራ ምነው ሳትነግረኝ?”
ጐረቤትየውም፤
“አይ ወዳጄ፤ እንደው ደፋ ቀናው በዝቶብኝ ነው እንጂ ላንተ የምደብቀው ሆኖ አይደለም”
ገበሬ፤
“በጄ፤ እንዴት እንዴት አድርገህ ንብረት አበጀህ?”
ጐረቤት፤
“ምን አደረግሁ መሰለህ፡፡ ከእጅ ወዳፍ የሆነው ኑሮ ሲመረኝ፤ አንድ ቀን ለምን እስከዛሬ የምኖርበትን ዘዴ አልለውጠውም? ብዬ አሰብኩልህ፡፡ በሬዎቼን ሸጥኩ፡፡ ከዚያ ወደቆላ ገበያ ወረድኩና ብረታ ብረት ገዛሁ፡፡ እንደምታውቀው፤ የኛ የደጋው ሰው ብረታ ብረት፣ ማጭድም፣ ዶማውም፣ አካፋውም፣ ማደሻውም ይቸግረዋል፡፡
ከቆላ ያመጣሁትን ብረታ ብረት ቸበቸብኩለት፡፡ እየተሻማ ገዛና ጨረሰው፡፡ ደሞ ሌላ ገዛሁ፡፡ እሱንም ሸጥኩ፡፡ ሌላ ሌላም ሸቀጥ እየገዛሁ ማምጣት ጀመርኩ፡፡ ከዚያ ምኑ ቅጡ። ሣር ቅጠሉ ብር ሆነልኝ!” ገበሬው ተገርሞ ካዳመጠ በኋላ ጐረቤትየውን አመስግኖ ወደ ቤቱ ሄደ፡፡ በሬዎቹን ከታሠሩበት ፈትቶ ገበያ አወረዳቸው፡፡ የሚያርስባቸውን ብቻ ሳይሆን በተለዋጭነት ያኖራቸውንም አውጥቶ ሸጠ፡፡ ከዚያ በገበያው ያለ አንድ ብረት ሳይቀረው ልቅም አድርጐ ገዛና መጣ፡፡
ወደቆላ ሲሄዱ መንገዱ ቀና ነው ቁልቁለት ነው! ሲመለሱ ግን ዳገት ነው፡፡ አጅሬ ያገር ብረታ ብረት ተሸክሞ ያን ዳገት ተያያዘው፡፡ ሆኖም ግማሽ መንገድ እንደሆነ ወገቡ ቁምጥ ብሎ ተሽመድምዶ ወደቀ፡፡
መንገደኞች መንደርተኞቹ ወደቆላ ሲወርዱ በላብ ተዘፍቆ አገኙት፡፡
“ምነው አያ እገሌ ምን ገጠመህ? ምን ነካህ?” አሉና ጠየቁት፤ ከወደቀበት ቀና እያደረጉት፡፡
“አዬ ወዳጆቼ!
ያ ጐረቤቴ፤ አያ እገሌ የሠራኝ ሥራ ለጠላትም አይስጠው! ትርፉን ነግሮ መከራውን ሳይነግረኝ ጉድ አደረገኝ!” አላቸው፡፡
* * *
በዛሬ ጊዜ በአዲስ አበባ ድንገት በአንድ ጀንበር አላግባብ በልጽገው የሚገኙ ሰዎች አሉ፡፡ “እነድንገቴ!” ይባላሉ በአዲሳባኛ፡፡ በፖለቲካውም ድንገት የሚከሰቱ ፖለቲከኞ አሉ - እነሱም “እነድንገቴ” ናቸው፡፡ ስንቱ የሸቀለበትን ንግድ ከመሸ የሚዳክሩበት እንዳሉ ሁሉ የከሰረ ፖለቲካም የሚሞክሩ አሉ፡፡ የሁለቱም የተበላ ዕቁብ (depleted business) ነው፡፡
እገሌ ሱቅ ከፈተ ብሎ መክፈት፣ እከሌ ፖለቲከኛ ከሆነ ምን ያንሰኛል? ማለትና የሰሙትን ሁሉ መኮረጅ፤ ማጣፊያው ሲያጥር አደጋ ላይ ይጥላል፡፡ መቼውንም ቢሆን የፓርቲ መንገድ፤ ሲገቡ ቁልቁለት፣ ሲወጡ አቀበት ነው! መንገዶቹ ሁሉ አልጋ በአልጋ አይደሉም እንደማለት ነው፡፡
ትርፉን ነግሮ መከራውን ሳይነግረኝ የምንልባቸው አያሌ ጉዳዮች አሉ፡፡ የፓርቲም፣ የድርጅትም፣ የማህበርም፣ የቢሮም … የህይወትም፡፡ በተለይ ምርጫው አፋፉ ላይ በደረሰበት በአሁኑ ሰዓት ሁለቴ ሶስቴ ማሰብ ያለብን ነገሮች ቀላል አይደሉም፡፡
በዛሬው የገና በዓል ደስታችንን ብቻ ሳይሆን መከራችንንም እናስታውስ! እያንዳንዱ ስብሰባችን በግራም ቆመን ይሁን በቀኝ፤ እየተንቀሳቀስንም ሆነ ቆመን፤ አንድ ነገር ልብ እንበል፡- በመሰብሰባችን ለህዝባችንና ለአገራችን ምን አፈራን? ነው ወይስ በባዶ ሆዳችን በኢኮኖሚ ጉዳይ ተሰብስበን፤ ህዝቡ ያምነን ይመስል ስለ ህዝቡ አውርተን፤ ምን ፈየደን? ብለን መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ አለበለዚያ፤ “ሞኝ ሸንጐ ተሰብሳቢ አገኘሽ፤ ቁርስ የሌለው ቡና አፈላሽ” መባል ነው ውጤቱ - “ነከብኸም ዮከርያ ጋዋ ሸከትኸም፤ ሳፍራ ኤኖ ቃዋ” ማለት ነው፡፡

Read 8781 times