Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 05 January 2013 11:38

የሱዳን ተቃዋሚዎች የአልበሽርን ጥሪ አጣጣሉት

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የሱዳኑ ፕሬዚዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽር በአገሪቱ በሚረቀቀው አዲስ ህገ መንግስት ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሙሉ እንዲሳተፉ ጥሪ አቀረቡ፡፡ አልበሽር ሰሞኑን ለተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ መሳሪያ ለታጠቁ ሃይሎች እና የሲቪል ማህበር ድርጅቶች ባቀረቡት ጥሪ፣ “አሁን መተባበር ያቃተን በውስጣዊ ችግሮቻችን ላይ ነው፣ አገራችን በጣም ሰፊ ናት፣ ለሁላችንም ትበቃለች፣ ስለዚህ መሳሪያ መሸከም አያስፈልግም፣ አገራችን እንዴት መመራት እንዳለባት በጋራ እንወስን” ብለዋል፡፡ በህገ መንግስት ማርቀቅ ሂደቱ ላይ ማንም ወገን አይገፋም ያሉት አልበሽር፣ ህገመንግስቱ የሁሉንም ወገኖች ይሁንታ የሚያገኝ እንደሚሆንም ገልፀዋል፡፡

ብዙዎቹ የአገሪቱ የፖለቲካ ተዋናዮች ግን የአልበሽርን ጥሪ አልተቀበሉትም፡፡ በተለይ ፕሬዚዳንቱን ከሚቃወሙ ግለሰቦች፣ ከብሄራዊ መግባባት ኃይሎች ጥምረት፣ ከብሄራዊ ኡማ ፓርቲ እና ከሱዳን አብዮታዊ ግንባር ከረር ያለ ተቃውሞ እንደገጠማቸው ተዘግቧል፡፡ አልበሽር ወደ ስልጣን ሲመጡ አጋራቸው የነበሩትና ከዚያም የኡማ ፓርቲ መሪ የሆኑት ሳዲቅ አልማሀዲ፣ ፓርቲያቸው የአልበሽርን ጥያቄ እንደማይቀበለው በይፋ አስታውቆ፤ ጥሪውን ከቀድሞው ያልተለየ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
“ባለፈው መስከረም ወር የቀረበው ተመሳሳይ ጥሪ ያልተሳካው ያልተመለሱ ጥያቄዎች በመኖራቸው ነው፡፡ አብዛኞቹ ተቋማት በተዘጉበት በአሁኑ ወቅት ይህን ጥያቄ ማቅረብ ቀልድ ነው” ያለው ፓርቲው፣ የሱዳን ህገመንግስት መረቀቅ ያለበት በትክክለኛ ብሄራዊ የሽግግር መንግስት እንጂ በአልበሽር ሊሆን አይችልም ሲል ጥያቄውን ውድቅ አድርጐታል፡፡
በአገሪቱ የሰላም፣ የደህንነት፣ የነፃነትና የሰላም ችግሮች ባሉበትና የአልበሽር ፓርቲ በስልጣን ላይ ተቀምጦ ህገመንግስት ማርቀቅ የሚታሰብ አይደለም ያለው የሱዳን አብዮታዊ ግንባር በበኩሉ፤ “አሁን ቅድሚያ የሚሰጠው ለፍትህ ነው፣ ይህ ደግሞ በዘር ማጥፋት ወንጀል ተጠርጥሮ በአለም አቀፍ ፍ/ቤት እየተፈለገ ባለ ሰው ሊመጣ አይችልም፡፡ በዚህ የህገ መንግስት ማርቀቅ ስራ ላይ ለመሳተፍ የሚሹ ወገኖች ካሉም እየሰመጠ ያለ ታንኳ ተሳፋሪዎች ናቸው” ብሏል፡፡
የሱዳን አዲስ ህገ መንግስት ሙሉ በሙሉ ኢስላማዊ እንደሚሆን አልበሽር ቀደም ሲል ተናግረው የነበረ ሲሆን በዚህ ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ያሉት ነገር የለም፡፡

Read 6273 times