Saturday, 05 January 2013 11:17

“ማንነትን ፍለጋ” በልቦለድ፣ በግጥም እና በዘጋቢ ፊልም

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(5 votes)

ወደ ኋላ አይተን ለምን ፊት አንሆንም?
ያን ለማድረግ እኮ ምንም አላጣንም!
የበሀ ድንጋዮች በምድር ሮሐ፣
ፀሐይ ይንቃቃሉ እስኪጠሙ ውሀ፣
ጐቦዱራ መንደር ድንጋዮች እንዳሉ፣
“የእንቅልፍ ዘመናት መጡብን!” እያሉ፣
ጠራቢ ፍለጋ ያማትራሉ አሉ፡፡
ድሬ ሼህ ሁሴን ላይ የኖራ ምሥጢሩ፣
ይተርፍ የለም እንዴ ለሀገር ለምድሩ!?
(“ድንጋይ መፅሐፍ ነው”)


በዛሬው ፅሁፌ ባለፉት አራት ወራት ለህብረተሰቡ ከቀረቡ የጥበብ ሥራዎች መካከል “ማንነትን ፍለጋ” ላይ ያተኮሩትን ሦስቱን መርጬ ለማስቃኘት አስቤአለሁ፡፡ የመጀመርያው በእርቅይሁን በላይነህ ተፅፎ ለንባብ የቀረበው “ታዳኤል” የተሰኘ ረጅም ልቦለድ መጽሐፍ ነው፡፡ የመጽሐፉ ታሪክ የሰውን ልጅ ዘላለማዊ ሊያደርግ የሚችል የዛፍ ፍሬን ለማግኘት የሚደረግ ጥረትን ከማስቃኘቱም ባሻገር ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ከፍ አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡
ታሪኩ ከመስከረም 19 ቀን 2004 እስከ የካቲት 4 ቀን 2004 ዓ.ም ባለው የስድስት ወር ጊዜ ውስጥ የሚከናወን ነው፡፡ ሆኖም የሰውን ልጅ “ሕያው የሚያደርገው” የዛፍ ፍሬ ሚስጢር ከ982 ዓ.ም ጀምሮ ኢትዮጵያ መግባቱን፤ በተለያየ ትውልድ የጥበቃና ቅብብሎሽ ሥራ መሰራቱን እንዲሁም ወደ ማንነቱ መመለስ የሚፈልግ ትውልድ ተጠቃሚ እንደሚሆን በርካታ ሃይማኖታዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮችን በምልሰት እየጠቃቀሰ ያስቃኛል፡፡
ደራሲው መፅሃፉን ያሳተመው “ኢትዮጵያዊ ትውፊትን የማሳየት ፍላጐት” ስላለው እንደሆነ በመግቢያ ላይ ጠቅሷል፡፡ “…ኢትዮጵያ ዓባይን እገድባለሁ ብላ ተነሳች፡፡ እኔ ደግሞ ግድብሽን ከጥፋት እጅ የሚታደግ፤ወደ ብልፅግና ማማ የሚያስመነድግ፤ዓለም ለክብርሽና ለታላቅነትሽ እንዲያጎበድድ የሚያደርግ ፀጋ አለሽ … እሱን እነግርሻለሁ ብዬ ተነሳሁ” ሲልም የማንነት ጥያቄ ዋና ርዕሰ ነገሩ መሆኑን ያሳያል፡፡
የመጽሐፉ ዋና ገፀባሕርያት የተማሩ ኢትዮጵያዊያንና ኢትዮጵያዊነት ናቸው፡፡ ኢትዮጵያንና ከፍ የሚያደርገውን ሚስጢር ለማግኘት በአገሪቱ የተለያዩ ቦታዎች ተበታትነው የተቀመጡና እርስ በእርስ ሲናበቡ ሙሉ መረጃ የሚሰጡ የብራና ጽሑፎችን ፈልጎ ማግኘት ወሳኝ ነበር- በታሪኩ ውስጥ። ለዚህ ደግሞ የመንግሥት ትብብር አስፈላጊ በመሆኑ በውስጥ ብቻ ሳይሆን ከውጭ መንግሥታት ጭምር የመጠላለፍና የመጋጨት ሁኔታዎች ያጋጥማል፡፡
ሁለተኛው መጽሐፍ ሐሙስ ታህሳስ 18 ቀን 2005 ዓ.ም በቅርስ ጥበቃና ምርምር ባለስልጣን አዳራሽ የተመረቀው “ድንጋይ መጽሐፍ ነው” የተሰኘው የግጥም መድበል ነው፡፡ ገጣሚዋ በመጽሐፏ ውስጥ ስለ ማንነት የሚያነሱ ጥቂት የማይባሉ ሥራዎች አሏት። በጽሑፌ መግቢያ ላይ ያቀረብኩት ግጥም አንዱ ነው። ለኑሮ ብለው ዜግነታቸውን ለቀበሩ ኢትዮጵያዊያን መታሰቢያ እንዲሆን የቋጠረችው ግጥም ደግሞ “እመኑኝ ኢትዮጵያ ነኝ” የሚል ነው፡፡ በዚህ ግጥም ውስጥ የማንነት ጥያቄ ነፍሱን ያስጨነቀው ሰው ጩኸት ይደመጣል፡-
አውቃለሁ ኃጢያቴ በዝቷል፣ ጉስቁልዋን ጠልቼ፣
ለባዕድ ተገዝቻለሁ ለመኖር ብዬ በልቼ፡፡
ከፎቅ ላይ ብንጠለጠልም ርቄ ብዙ ሳልሰማ፣
ዘወትር የሚታየኝ ግን የ’ረኝነቴ ያ ማማ፣
አስሬ ውሃ ብጠጣም ስርቅታ አልተውም ያለኝ፣
ናፋቂ ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡
የራሱን ማንነት ያላገኘ ለመኖር ብሎ ከአገሩ ተሰዶ በባዕድ አገር ይኖራል፡፡ በእርግጥ ማንነቱን ያገኘም ሌላውን ዓለም ለማወቅ ይተጋል፡፡ ገጣሚዋ በመድበሏ መግቢያ ላይ ይሄንን እውነታ የሚያፀኸይ ፅሁፍ አስፍራለች፡፡ የእኛን ታሪክና ማንነት በማጥናታቸው ምክንያት በስማቸው ጎዳና ስለተሰየመላቸው ስለ ፕሮፌሰር ኢኖ ሊትማን እንዲህ ብላለች፡-
“ከአክሱም ከተማ ዋናው የሐውልቶች መንደር ወደ አፄ ካሌብ መቃብር የሚወስደው መንገድ “ኢኖ ሊትማን ጐዳና” እየተባለ ይጠራል፡፡ መንገዱ ስያሜውን ያገኘው በ19ኛው ክፍለ ዘመን መግቢያ ላይ በአክሱምና በአካባቢዋ የሚገኙ የድንጋይ ላይ ጽሑፎችን ጨምሮ በርካታ ጥናቶችን ያካሄደው የጀርመን ጥናትና ምርምር ቡድን አባል ከነበሩት ከፕሮፌሰር ኢኖ ሊትማን ነው፡፡”
እኛ ማንነታችንን ፈልገን ለማግኘት ባንተጋም በአባቶቻችን የተሰሩት ሥራዎች፤ቀድመው ለዓለም ደርሰዋል የምትለው ገጣሚዋ፤ታሪካችንን አጥንተው በፎቶግራፍ፣በመጽሐፍ፣ በኮምፒዩተር … ለዓለም ሕዝብ እንዲደርስ ለተጉት ባለውለተኞች መጽሐፏ መታሰቢያ እንዲሆንላቸው ፈቅዳለች፡፡
ማንነት እንዳይጠፋ የተጉትን የምታመሰግነው አፀደ፣ለማንነታቸው መቀጠል ደንታ ቢስ የሆኑትን ትተቻቸለች - በግጥሟ፡፡ “ሄሎ አልዩ አምባ” የሚለው ግጥሟ ተጠቃሽ ነው፡፡ “አልዩ አምባ የመጀመሪያዋ የጉምሩክ ከተማና የቀረጥ ሀገር፤ የመጀመሪያው የስልክ ቤትም ያለበት ሀገር መሆኗን ሰምቼ፣ዛሬ ግን ምንም ሳይኖርባት ባየኋት ጊዜ የተፃፈ” ባለችው ግጥም ማንነትን የማስቀጠሉ ሥራ ብዙ ትጋት እንደሚጠይቅ ጠቁማለች፡-
ያ…ኔ…ቀጭን ሽቦ፣
ከአንኮበር ተስቦ፣
ባንቺ አልፎ ነው አሉ እንጦጦ የሄደ፣
ታዲያ ምነው አሁን ያ ሁሉ ወረደ!?
እኔን የሚያሰጋኝ፡-
መኖርሽ ተረስቶ ድር እንዳታደሪ፣
የሚሰማሽ ካለ አሁንም ተጣሪ፡፡
እነሱ እንደሆነ፡-
እንኳንስ ኢትዮጵያን ከመጭው ዘመን ጋር
ሊያገናኙ ቀርቶ፣
መቀጠል አልቻሉም የተበጠሰውን
ካንቺ እስከ እንጦጦ፡፡
ሦስተኛው ቅኝቴ ቅዳሜ ታህሳስ 20 ቀን 2005 ዓ.ም በብሔራዊ ቴአትር የተመረቀውና “የአባቴ ቤት” በሚል ርዕስ በራሄል ሽባባው የተዘጋጀው ጥናታዊ ፊልም ነው፡፡
ዘጋቢ ፊልሙ በመንፈሳዊ ሰዎች ዘንድ ያለውን ማንነት የመፈለግ ጥረት አመላካች ነው። የምናመልክበት ቅዱስ መጽሐፍ አንድ እንደሆነው ሁሉ ቤተ ክርስቲያኖቻችን ለምን አንድ አልሆኑም? የሚል ጥያቄ ያነሳል - ፊልሙ፡፡
“የእግዚአብሔር ቤት ምንድነው? የእግዚአብሔር ማደሪያስ የት ነው?” ለሚለው መሠረታዊ ጥያቄ ከመጽሐፍ ቅዱስ፤ ከተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት ምላሽ የሰጡ ሰዎችን አስተሳሰብና ግንዛቤም ያመለክታል፡፡
ከኦርቶዶክስ፣ ከካቶሊክ፣ከሉተር ተከታይ ወንጌላዊያን ቤተክርስቲያናት ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ የሚኖሩ የተለያዩ አገራት ዜጎች (የግሪክና የእንግሊዝ) አብያተ ክርስቲያናት የሃይማኖት አባቶች በጋራ የሚስማሙበት ምላሽ የእግዚአብሔር ቤት ሰውና የሰው ልብ መሆኑን ነው፡፡ እውነታው ይህ ቢሆንም ሰዎች በተለያየ አብያተ ክርስቲያናት የተለያዩበት ምክንያት ምንድነው የሚል ጥያቄ ያነሳችው ራሄል ሽባባው፤ የማንነት ጥያቄ ርዕሰ ጉዳዩ ያደረገ ዘጋቢ ፊልም እንድታዘጋጅ አነሳስቷታል፡፡
ባለፈው ቅዳሜ ዘጋቢ ፊልሙ በተመረቀበት ዕለት ንግግር እንዲያደርጉ ከተጋበዙ እንግዶች መካከል ጋዜጠኛ ሄኖክ ያሬድ፤ ከሌሎች አገራት በተሻለ በኢትዮጵያ የሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ገናን፣ ጥምቀትንና የፋሲካ በዓላትን በአንድ ጊዜ በማክበር ለአንድነት ያላቸውን ቅርበት ጠቁሟል፡፡
ከካቶሊክ ቤተክርስቲያን የተጋበዙት ዶ/ር አባ ዳንኤል አሰፋ በበኩላቸው፤ ማንነት ከአባልነት እንደሚለይ፤ ከአባልነት በላይ ማንነት ከፍ እንደሚል ሲያመለክቱ፤ ከወንጌላዊያን አብያተ ክርስቲያን የተጋበዙት ዶ/ር ወዳጄነህ ማዕረግነህ በበኩላቸው፤ የማንነት ጥያቄ በሁሉም ሰው ነፍስና ስጋ ውስጥ የሚመላለስ መሆኑን ጠቁመው፤ ሉተራዊያን ተገንጥለው ስለወጡበት የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ማንነት የማወቅ ፍላጎት እንዳላቸው ሁሉ ሌሎችም ትላንት ውስጥ ምን እንዳለ የማወቅ ጉጉት አላቸው ብለዋል፡፡

 

Read 6550 times Last modified on Saturday, 05 January 2013 11:48