Print this page
Saturday, 05 January 2013 11:00

የ‘ፈረንጅ ረቡዕና ዓርብ’ አባዜ…

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(2 votes)

እንኳን ለብርሀነ ልደቱ አደረሳችሁማ!
እግረ መንገዳችንን እየከሰሙ ያሉና ‘ዳግም ልደት’ የሚያስፈልጋቸው ነገሮችን ዳግም ልደት ይስጥልንማ!
ሰውየው ለሚስቱ ሁልጊዜ የገና ስጦታ ይሰጣት ነበር፡፡ አንድ ዓመት በሆነ ምክንያት በሚስቱ ብሽቅ ይልባታል፡፡ እሷ ግን ምንም እንዳልተፈጠረ ሁሉ “…የእኔ ወለላ፣ ዘንድሮ ለገና ምን ስጦታ ነው የምትሰጠኝ?” ትለዋለች፡፡ እሱም “ዓይኖችሽን ጨፍኚ…” ይላታል። እሷም ትጨፍናለች፡፡ “ምን ይታይሻል!” አላት፡፡ እሷም “ምንም!” ትለዋለች፡፡ ባል ሆዬ ምን ቢላት ጥሩ ነው…“የምሰጥሽ ስጦታ እሱን ነው፣ ምንም!” ዘንድሮ ብዙ ባሎች ለሚስቶቻቸው “ምንም!” የሚል መልስ ቢሰጡ አይገርምም፡፡ ብቻ ዓለም ባንኮች እንዳይሰሙኝ። ቂ…ቂ…ቂ…

አሀ…“ምን ለማለት ፈልገህ ነው? ከሁለቷ ዲጂት ሽርፍራፊ እንኳን አልደረሰኝም ልትል ነው!” የሚል ጥያቄ ሊኖር ይችላላ!
እኔ የምለው፣ እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ይቺን ታሪክ ስሙኝማ…የአንድ ወዳጃችን እናት በቅርቡ ወደ አሜሪካ ይሄዳሉ፡፡ እንግዲህ እናቶች አሜሪካ ሲሄዱ ብዙ አስቸጋሪ ነገሮች አሉ፡፡ በተለይ እዚህ የለመዱትን ማህበራዊ ኑሮ ማጣቱ ለብዙዎች አስቸጋሪ ነው፡፡ እናላችሁ… እኝሁ የወዳጃችን እናት በጣም ጿሚ ናቸው። ሆኖም እዛ ሄደው ጾማቸውን ለመቀጠል ግን ችግር ሆነባቸው፡፡
እንዴት መሰላችሁ…አንድ ጥያቄ አቀረቡ፡፡ “ለመሆኑ እዚህ አገር ምንና ምን ቀን ሲሆን ነው ረቡዕ እና ዓርብ የሚውሉት?” ብለው ጠየቁ፡፡ ያልተጠበቀ ጥያቄ ነበር። ወዳጃችንም ነገራቸው፡፡ ለምሳሌ እነሱ ያሉበት ስቴት ማክሰኞ ሲሆን ኢትዮዽያ ረቡዕ ገብቷል፡፡ እና ምን ቢሉ ጥሩ ነው “በኢትዮዽያ አቆጣጠር ነው የምጾመው።” ስለዚህ እዛ አገር ማከሰኞ ቀን ሲጾሙ የኢትዮዽያን የረቡዕ ጾም ጾሙ ማለት ነው፡፡ አሪፍ አይደል!
ልክ ናቸዋ! ጾሙ የእኛ፣ ረቡዕው የእኛ!…እና ምን ዕዳ አለባቸው የሀበሻ ረቡዕ እያለ በፈረንጅ ረቡዕ የሚጾሙት? ለነገሩ በአሜሪካ አስቸጋሪ ኑሮ የእሳቸው አጿጿም ትንሽ አስቸጋሪ ስለሆነ ትንሽ ቆይተው በፈረንጅ ረቡዕና ዓርብ የሀበሻን ጾም መጾም ጀመሩ፡፡
የምር ግን…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…መደነቅ ያለባቸው እናት ናቸው፡፡ ጉንፋን ሲይዘው እንኳን የፈረንጅ ሳል ሊስል የሚዳዳው ሰው በጸጉር ልክ ሊሆን ምንም ባልቀረበት ዘመን ‘ጾሜ እንደ አገሬ’ ማለታቸው አሪፍ አይደል!
እናላችሁ…እህ ብለን ለምንሰማ አሪፍ ነገር ነው ያሉት፡፡ ልክ ነዋ…ዘንድሮ እኮ እያስቸገረን ያለው…አለ አይደል… በፈረንጅ ረቡዕና ዓርብ መጾም የስልጣኔ ምልክት የሚመስለን መብዛታችን ነው፡፡
ስሙኝማ…‘የታንክስ ጊቪንግ’ ጠበል ጠዲቅ እየበዛ ያለበት አገር ነው፡፡ ኮሚኩ ነገር ምን መሰላችሁ… ታንክስ ጊቪንግ ዴይ የሚባለውን ከምናከብር ውስጥ አብዛኛዎቻችን ምንነቱን እንድንናገር ብንጠየቅ የምናውቀው ነገር አለመኖሩ ነው፡፡ የሚታየን ነገር ቢኖር ምን መሰላችሁ…‘በፈረንጅ ረቡዕና ዓርብ’ መጾማችን፡፡
የአገሩ ሱቅና ካፌ ሁሉ በ‘ፈረንጅ አፍ’ የሚጠራው ለምን መሰላችሁ…‘በፈረንጅ ረቡዕና ዓርብ’ የመጾም አባዜ ነች፡፡ (ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…የብዙዎቹን ‘የፈረንጅ አፍ’ ስሞች ‘ስፔሊንግ’ ምናምን እዩልኝማ! የምር…የቋንቋ ሊቆች ነገሬ ብለው ቢያዩዋቸው “በታሪክ ብዙ መረጃ የማይገኝለት ግን እንደጠፋ ተቆጥሮ የነበረ ቋንቋ ተናጋሪዎች አዲስ አበባ ውስጥ ተገኙ…” ምናምን ብለው ናሽናል ጂኦግራፊ ቻነል ላይ ባይለቁት ነው! ስታንድ አፕ ኮሜዲያኖቻችን ይቺን፣ ይቺን ነገር እዩልንማ!)
ታዲያላችሁ…ምን መሰላችሁ…‘በፈረንጅ ረቡዕና ዓርብ’ የመጾም አባዜ አልለቅ እያለን ‘ቫለንታይንስ ዴይ’ የሚሉት ነገር አሁን ከየክለቡና ከየካፌው ወጥቶ ኤፍ ኤሞቻችንን እያጨናነቃቸው ነው፡፡ የምር…በ‘ፈረንጅ ረቡዕና ዓርብ የምንጾም ሰዎች እየበዛን የተክልዬ ጠበል ጠዲቅ ቀርቶ ‘የታንክስ ጊቪንግ’ ጠበል ጠዲቅ ካላንደር ላይ በቀይ ቀለም ሊጻፍ ጥቂት ዓመታት ብቻ የቀሩ ይመስላል፡፡
የጣልያን ሙሉ ልብስና የስፔይን ጫማ አድርገው የፈረንሣይ ሽቶ በተቀቡ ሰዎች የአገር ውስጥ ምርት ባለመግዛታችን እየተኮንን ያለንበት አገር ሁሉ በኮሜዲ እየተጥለቀለቀ ያለበት ዘመን ነው፡፡
ስሙኝማ…ድሮ ሰው እንቅፋት ሲመታው “ወይኔ!” ምናምን ሲባል በግል ሰውየውን አወቀም፣ አላወቀም በአካባቢ ያለ ሰው “እኔን!” የሚልበት ዘመን እዚህ አገር እንደነበር ታውቃላችሁ? (ስለመኖሩ ግጥም አድርጌ እጅ መምታት እችላለሁ፡፡) አሀ…መጠየቅ አለብና! በአሁን ዘመን “እኔን! እኔን!” የሚል ሰው ከተገኘ መጀመሪያ ጥርጣሬ ውስጥ የሚገባው የአእምሮ ጤንነቱ ነው!
ሌላ ደግሞ ምን አለላችሁ…“ዋው!” የሚሉት ነገር! አንድ ሰሞን በየማስታወቂያው ሲበዛ “ኽረ እባካችሁ…” ብለን ሳይበቃን “ዋው!” በቃለ መጠይቁ ሁሉ እየገባ ነው፡፡
’በፈረንጅ ረቡዕና ዓርብ የምንጾም’ በዛና!
እናማ…እኛ ቀደም ብለን ያነሳናቸው እናት “እኔ በአገሬ ረቡዕና አርብ ነው የምጾመው!” ሲሉ እንደ ዘመኑ ባንዲራ ለብሶ ጠጅ ቤት የሚገባበት አይነት የ‘ካሜራ ፓትሪዮቲዝም’ ምናምን ነገር ሳይሆን እውነተኛ ‘አይዴንቲቲ’ ማወቅ ነው፡፡ በ‘አገር ረቡዕና ዓርብ መጾም’ ኋላ ቀርነት የሚመስላቸውና “የተማረ ይግደለኝ” የሚለውን ተረት ውሀ እየደፉበት ያሉ ‘ልሂቃን’ እየበዙ ባለበት ዘመን እንዲህ አይነት ስሜታቸው ’በፈረንጅ ረቡዕና ዓርብ ጾም’ ያልተበረዙ ሰዎች ማግኘት አሪፍ ነው፡፡
ስሙኝማ…አንዳንድ ሰዎች አሁን፣ አሁን በቃለ መጠይቅም ሆነ በምንም ሲመጡ ምን እያሰኙን መሰላችሁ… “ኦ! ኖት አጌይን!” (እኔም በፈረንጅ ረቡዕና ዓርብ የማልጾምሳ!) የሚቀርብበትን ሳህን ብቻ እየለወጡ ያንኑ የጣዕምም የመጠንም ለውጥ የሌለበት ወጥ መመገብ አልሰለቻችሁም! የምር እኮ…እንዲህ አይነት ነገር ሲገጥመን…አለ አይደል… “ምነው አንዷ የሆሊዉድ አክተር ባረገዘችና የአየር ሰዓቱን በሞላችው!” ለማለት ምንም አይቀረን፡፡
የማርገዝ ነገር ከጠቀስን አይቀር ይቺን ስሙኝማ…ልጅቱ ለቤተሰቦቿ ብቸኛ ልጅ ነች፡፡ እናም ምን ብላ ጸለየች አሉ መሰላችሁ…“እግዚአብሔርዬ ለራሴ ምንም አልለምንህም፡፡ ለእናቴ ግን እባከህ ለልጇ ባል ላክላት!” አሪፍ ጸሎት ነች፡፡
እናላችሁ…ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ፣ ይቺን ስሙኝማ…ታክሲ ላይ አንድ ወዳጄ ያነበበውን ሲነግረኝ ነበር፡፡ ምን የሚል ጥቅስ ተለጥፏል መሰላችሁ… “ሂሳብ ከመከፈሉ በፊት አትስረቁ፡፡” አንዳንድ ጊዜ ይህች አገር የምርም ወዴት እየሄደች እንደሆነ ግራ እየገባን ነው! በህዝብ ትራንስፖርት ላይ እንዲህ አይነት ነገር ሲለጠፍ ምን ይባላል!
የምር ግን… ካለፉት ጥቂት ወራት ወዲህ በተደጋጋሚ እንደምንሰማቸው ነገሮች ከሆነ… ይቺ ከተማ “ዘ ሞስት አንሴፍ ሲቲስ” የሚባሉ ከተሞች ዝርዝር ውስጥ ገብታ ዩ ቲዩብ ምናምን ላይ እንዳይለቁብን የሚያሰጋ ነገር ነው። ይሄ ሁሉ ነገር እየተወራ ባለበት የሆነ…አለ አይደል…‘ቄሱም መጽሐፉም ዝም’ ነገር ሲሆንብን ‘ኦፊሺያል ሳይለንስ’ ምናምን ነገር ያለ ሊመስለን ሁለት ሐሙስ እንደቀረን ልብ ይባልልንማ!
ታዲያላችሁ…በ‘ፈረንጅ ረቡዕና ዓርብ’ የምንጾም እየበዛን…ነገራችን ሁሉ…አለ አይደል… መስቀለኛ መንገድ ላይ ደርሰን ወዴት አቅጣጫ እንደምንዞር ግራ የገባን አይነት ነው፡፡ የምርም ‘መለያ ቀለማችን’ ቀስ በቀስ እንዳልነበረ እየሆነ ነው፡፡
መልካም የበዓላት ሰሞን ይሁንልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!


Read 6489 times