Saturday, 05 January 2013 11:00

የአራፋት የሞት መንስኤ ከ8 ዓመት በኋላ አልታወቀም

Written by  ባየህ ኃይሉ ተሰማ bayehailu@gmail.co
Rate this item
(4 votes)

የአሜሪካ ማዕከላዊ የስለላ ድርጅት (CIA) የኩባ ፕሬዚደንት የነበሩትን ፊደል ካስትሮን ለመግደል ከሁለት ደርዘን በላይ ሙከራዎች ማድረጉ ተደጋግሞ ተገልጧል፡፡ የእሥራኤል የስለላ ድርጅት (ሞሳድ) በጥይትና በቦምብ ብቻ ሳይሆን በመርዝም ጭምር የአይሁዳዊቷን ሀገር ህልውና የሚፈታተኑ ጠላቶቿን የማስወገድ ልምድ እንዳለው የሚጠቁሙ ፍንጮች አሉ፡፡
ጠላትን፣ ተፎካካሪንና ተቀናቃኝን በመርዝ የመግደል ታሪክ ከሰው ልጅ የመግደል ታሪክ የማይተናነስ እድሜ አለው፡፡ መርዝ የማይታይ፣ ድምፅ የሌለውና አሻራም የማይተው ረቂቅ እንደመሆኑ በተለይ የስለላ ድርጅቶች ተመራጭ የመግደያ መሣሪያ በመሆን ዘመን የማይሽረው አገልግሎቱን ሲያበረክት ኖሯል፡፡

በሩስያ የፀጥታ መሥሪያ ቤት ስር “የመርዝ ጥናትና ምርምር ቢሮ” በመባል ይታወቅ የነበረው ክፍል ግኝቶቹንና ዘዴዎቹን በቀጥታ ለሌኒን ሪፖርት ያደርግ እንደነበር መዛግብት ያመለክታሉ፡፡ አደገኛ መርዞች የሶቭየት የስለላ ድርጅቶች (KGB) ተወዳጅ የመግደያ መሳሪያዎች ሆነው የፓርቲውና የመንግሥት ጠላቶችን ሲያስወግዱ ቆይተዋል፡፡ ኬጂቢ የመርዝ አጠቃቀምን ወደ አንድ ደረጃ ከፍ በማድረግ፤ እንደ ሳይናይድ እና ሬሲን ያሉ አደገኛ መርዞችን የሚተኩሱ “ጠመንጃዎች” አዘጋጅቶ ከሩስያ ድንበር ክልል ውጪ ሳይቀር ጠላቶቹን ሲቀስፍበት ቆይቷል፡፡
የአሜሪካ ማዕከላዊ የስለላ ድርጅት (CIA) የኩባ ፕሬዚደንት የነበሩትን ፊደል ካስትሮን ለመግደል ከሁለት ደርዘን በላይ ሙከራዎች ማድረጉ ተደጋግሞ ተገልጧል፡፡ የእሥራኤል የስለላ ድርጅት (ሞሳድ) በጥይትና በቦምብ ብቻ ሳይሆን በመርዝም ጭምር የአይሁዳዊቷን ሀገር ህልውና የሚፈታተኑ ጠላቶቿን የማስወገድ ልምድ እንዳለው የሚጠቁሙ ፍንጮች አሉ፡፡
ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው እ.ኤ.አ በ1997 ዓ.ም በሐማስ መሪ ካሊድ ሜሻል ላይ በዮርዳኖስ ርዕሰ ከተማ አማን ውስጥ በሞሳድ የተደረገበት በመርዝ የመግደል ሙከራ ነው፡፡ ካሊድ ሜሻልን መርዘዋል ተብለው የተጠረጠሩ የሞሳድ ሰራተኞች ወዲያውኑ ዮርዳኖስ ውስጥ በቁጥጥር ስር በመዋላቸው የሐማስን መሪ መርዞ የመግደሉ ሴራ ተደረሰበት፡፡ የዮርዳኖሱ ንጉስ ሁሴን በምስጢር ከእሥራኤል ጋር ባደረጉት ድርድር የተያዙትን የሞሳድ ሠራተኞች በመርዙ ማርከሻ ከእሥራኤል ጋር በመለዋወጣቸው የካሊድ ሜሻል ህይወትን ለማትረፍ ችለዋል፡፡
ይህ የሞሳድ እርምጃ የእሥራኤል ተቃዋሚዎች ራሳቸውን መጠበቅ የሚባቸው ከእሥራኤል መተሬ ተኳሾች (snipers)፣ ቦምብ እና ሚሳኤል ጥቃት ብቻ ሳይሆን ከረቂቁ የመመረዝ አደጋም ጭምር እንደሆነ የሚያመላክት ነው፡፡ የፍልስጤም ነፃ አውጪ ግንባር ሊቀመንበር የነበሩት ያሲር አራፋት በድንገት ታመው ከሞቱበት ጊዜ ጀምሮ የተገደሉት በእሥራኤል የስለላ ድርጅት (ሞሳድ) ተመርዘው ነው ሲባል ቆይቷል፡፡
እ.ኤ.አ ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ እሥራኤል በሀገሯ በተደጋጋሚ ይፈፀም የነበረውን የአጥፍቶ ጠፊዎች ተከታታይ ዘመቻ የሚያስተባብሩትና የሚመሩት ያሲር አራፋት ናቸው ስትል ከስሳ ነበር፡፡ መቀጣጫ እንዲሆናቸውም ከመሞታቸው በፊት የነበሩትን ወራት ራማላ ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው እንዳይወጡ በእሥራኤላውያን ታግተው እያለ፤ እ.ኤ.አ በጥቅምት ወር 2004 ዓ.ም በድንገት መታመማቸው ተሰማ፡፡
አራፋት ፈረንሳይ አገር ተወሰደው ፓሪስ ከተማ ውስጥ በሚገኘው የፔርሲ ወታደራዊ ሆስፒታል ተኝተው መታከም ጀመሩ፡፡ ህመማቸው በወቅቱ ይሄ ነው ተብሎ ያልተገለፀ ሲሆን የጤና ደረጃቸው አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደደረሰ ግን በጊዜው መገናኛ ብዙሃን በተከታታይ ዘግበዋል፡፡ እኒህ አንጋፋ ታጋይ ከአንድ ወር በላይ ሲታከሙ በቆዩበት በዚህ ሆስፒታል ውስጥ ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው የተገለጠው እ.ኤ.አ በህዳር ወር 2004 ዓ.ም ነበር፡፡
አራፋትን በአጭር ጊዜ ውስጥ አጣድፎ ለሞት ያበቃቸው ህመም ምን አይነት እንደነበር ከቤተሰባቸውም ሆነ ከሐኪሞቻቸው መግለጫ ሳይሰጥበት እስካሁን ቆይቷል፡፡ የአራፋት ሚስት ወይዘሮ ሱሐ በባለቤታቸው አስከሬን ላይ ምርመራ (autopsy) እንዲደረግ ባለመፍቀዳቸው የተነሳ የአራፋትን ሞት ትክክለኛ ምክንያት ለማወቅ ሳይቻል ቀርቷል፡፡ በወቅቱ የፍልስጤም ነፃ አውጪ ግንባር ወታደራዊ ክንፍ የሆነው ፋታህ ግን ለአራፋት ሞት ሙሉ በሙሉ ተጠያቂዋ እሥራኤል ነች በማለት መግለጫ አውጥቶ ነበር፡፡
አራፋት ከሞቱ ከስምንት አመታት በኋላ ተመርዘው ተገድለዋል የሚለውን የቆየ ክስ እንደ አዲስ ወደ መድረክ ያመጣው፤ አልጀዚራ ቴሌቪዥን ባለፈው ሐምሌ ወር ያሰራጨው በያሲር አራፋት አሟሟት ላይ ያተኮረ ጥናታዊ ፊልም ነበር፡፡ አልጀዚራ በጥናታዊ ፊልሙ ላይ ባቀረበው ዘገባ፤ በያሲር አራፋት ልብሶች እና የግል መጠቀሚያ ዕቃዎች ላይ ጨረራ አመንጪ አደገኛ ንጥረ ነገር በምርመራ መገኘቱን ጠቁሞ፤ የሞታቸው መንስኤ የጨረራ ምረዛ ሊሆን ይችላል ብሎ ነበር፡፡
አልጀዚራ ይህንን ጥናታዊ ፊልም በማዘጋጀት ላይ ሳለ፣ ያሲር አራፋት ፔርሲ ወታደራዊ ሆስፒታል ውስጥ ተኝተው በሚታከሙበት ጊዜ ይጠቀሙባቸው የነበሩትን የውስጥ ሱሪ፣ ጓንት፣ ኮፍያ እና የጥርስ ብሩሽን ለምርመራ ከወይዘሮ ሱሐ ተቀብሎ ነበር፡፡ አልጀዚራ ይህንን የአራፋትን ስብስብ ስዊዘርላንድ አገር፣ ሎዛን ከተማ ለሚገኘውና (Institute of Radiation Physics) ለተባለ ከፍተኛ የጥናት ተቋም ልኮ እንዲመረመርለት አድርጓል፡፡ ተቋሙ በአራፋት መገልገያዎች ላይ ባደረገው ምርመራም ከፍተኛ መጠን ያለው (Polonium) የተሰኘ ጨረራ አመንቺና ለሰው ህይወት በጣም አደገኛ የሆነ ንጥረ ነገር በናሙናዎቹ ላይ መገኘቱን አረጋጧል፡፡
ይህ የአልጀዚራ ጥናታዊ ፊልም ሲሰራጭ፣ አስቀድሞ አራፋትን መርዛ የገደለችው እሥራኤል ናት ለሚሉት ፍልስጤማውያንም ሆነ አረቦች የግምታቸውን ትክክለኛነት ያረጋገጡበት ማስረጃ ሆኖ ታይቷቸዋል፡፡ እሥራኤል አራፋት የሞቱት በሞሳድ ተመርዘው ነው የሚለው ክስ አዲስ ባይሆንባትም፣ አልጀዚራ ያሰራጨው ጥናታዊ ፊልም ግን ለአሮጌው ክስ አዲስ መሰረት ስለሰጠው፣ አራፋት በሞቱበት ጊዜ በስልጣን ላይ የነበሩ እሥራኤላውያን ሹማምንት በግድያው እጃችን የለበትም በማለት ተራ በተራ እንዲያስተባብሉ አስገድዷቸዋል፡፡
የአልጀዚራ ጥናታዊ ፊልም በተጨማሪም የፈረንሳይ ባለሥልጣኖችን በአረፋት አሟሟት ላይ አዲስ ምርመራ እንዲጀምሩ ያስገደዳቸው ሲሆን የአረፋት ባለቤት ወይዘሮ ሱሃ ደግሞ የፔርሲ ወታደራዊ ሆስፒታል የባለቤታቸው የደምና የሽንት ናሙና ለምርመራ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡ ይሁን እንጂ ሆስፒታሉ ከአራት አመት በፊት ናሙናውን ማስወገዱን እንደገለፀላቸው ታውቋል፡፡
የአልጀዚራ ጥናታዊ ፊልም ተፅእኖ በዚህ ሳያበቃ ከሁሉም አቅጣጫ የአራፋት አስከሬን ይመርመር የሚል ከፈተኛ ግፊት ለመፍጠር አስችሏል፡፡ ስለሆነም የአራፋት ባለቤትና የፍልስጤም አስተዳደር በአራፋት አስከሬን ላይ ምርመራ እንዲደረግ ለመስማማት ተገደዋል፡፡
በዚህም መሰረት ሕዳር 18 ቀን 2005 ዓ.ም ራማላ የሚገኘው የአራፋት መቃብርን ፍልስጤማውያን መርማሪዎች ቆፍረው 20 የሚደርስ ናሙና ከአራፋት ቅሪተ አካል ላይ ከወሰዱ በኋላ፤ ከስዊዘርላንድ፣ ከፈረንሳይና ከሩስያ ለተውጣጡ የዓለም አቀፍ ተመራማሪዎች ቡድን አስረክበዋል፡፡
የዓለም አቀፉ ተመራማሪዎች ቡድን በሚያደርገው ጥናት፤ አራፋት የሞቱት ጨረራ አመንጪ በሆነው ፖሎኒየም ተመርዘው መሆን አለመሆኑን ለማረጋገጥ እንደሚያስችል ተስፋ ተጥሎበታል፡፡ በአራፋት አልባሳትና ዕቃዎች ላይ ቀዳሚ ምርምሩን ያደረገው የሎዛን ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል ቃል አቀባይ ለሮይተርስ የወሬ ምንጭ እንደጠቆሙት፤ የአስከሬን ምርመራውን ውጤት ለማግኘት እስከ መጪው መጋቢት ወይም ሚያዝያ ወር ድረስ ሊያስጠብቅ ይችላል ብለዋል፡፡
አራፋትን መርዞ ቀስፏል የተባው ፖሎኒየም በተፈጥሮ የሚገኝ ጨረራ አመንጪ ንጥረ ነገር ነው። ፖሎኒየም መጀመሪያ የተገኘው እ.ኤ.አ በ1898 ዓ.ም ሜሪ ኩሪ በተባለች ተመራማሪ አማካይነት የነበረ ሲሆን በዓለም ላይ እንደልብ ከማይገኙ ንጥረ ነገሮች ውስጥ የሚመደብ ነው፡፡ ለምሳሌ ትልቋ የፖሎኒየም አምራች ሩስያ ስትሆን አመታዊ ምርቷ ግን 100 ግራም እንኳን አይሞላም፡፡ ፖሎኒየም በሰው ሰራሽ ዘዴ ሊፈጠር የሚችል ቢሆንም የማምረት ተግባሩ ግን የኒኩልየር ማብላያ ስለሚያስፈልገው ሂደቱ ውድና ውስብስብ ነው፡፡
የፖሎኒየም ቅንጣት፤ ጨረራ አመንጪና ረቂቅ እንደመሆኑ ለሰው ህይወት በጣም አደገኛ ነው። መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ አንድ ማይክሮ ግራም (የአንድ ግራም አንድ ሚሊዮንኛ) የሚሆን መጠን ያለው ፖሎኒየም ወደ ሰውነት ውስጥ ከገባ በሌሎች ውስጥ ያለውን (DNA) በማዛባት፣ ሌሎችን በመግደል ወይም ወደ ካንሰርነት በመቀየር አጣድፎ ለመግደል ይችላል፡፡ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው እ.ኤ.አ በ2006 ዓ.ም አሌክሳንደር ሌቲቪኔንኮ በተባለ ግለሰብ ላይ በንጥረ ነገሩ የደረሰ መመረዝ ነው፡፡
ሌቲቪኔንኮ በለንደን የሚኖር ሩስያዊ የቭላድሚር ፑቲን ተቃዋሚ ሲሆን በድንገት በደረሰበት ህመም ሰውነቱ ሟሽሾ ፀጉሩ መርገፍ ጀመረ፡፡ የተደረገለት ምርመራም መቅኒውም መሟጠጡን ጠቆመ። ሐኪሞች የሌቲቪኔንኮ ህመም በጨረራ መለከፍ ነው ብለው ስለጠረጠሩ የሽንቱን ናሙና ብሪታኒያ የአቶሚክ ጦር መሣሪያ ማዕከል በመላክ እንዲመረመር አደረጉ፡፡ የማዕከሉም የምርመራ ውጤት ሌቲቪኔንኮ በፖሎኒየም መመረዙን አረጋገጠ፡፡ ሊቲቪኔንኮ ሆስፒታል ከገባ ከ23 ቀናት በኋላ ያረፈ ሲሆን መራዡ የሩስያ የስለላ ድርጅት (FSB) ነው ተብሎ ተገምቷል።
ፖሎኒየም ውድ እና ረቂቅ እንደመሆኑ የሚገኘው በሚያመርቱትና በሥራ ላይ በሚጠቀሙበት አገሮች እጅ ብቻ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ፖሎኒየምን በቀላሉ ለማግኘት ስለማይቻል ተራ ወንጀለኞች ለእኩይ ስራቸው ይጠቀሙበታል ለማለት በጣም ያዳግታል። ስለዚህም ይህን ንጥረ ነገር ሰዎችን ለመመረዝ ሊያውሉት የሚችሉት መንግሥታዊ ድጋፍ ያላቸው የስለላ ድርጅቶችና አጋሮቻቸው ናቸው ተብሎ ይታመናል፡፡
ምንም እንኳ ይህ እንደልብ የማይገኝ ንጥረ ነገር በአራፋት የግል መጠቀሚያዎች ላይ መገኘቱ ተመርዘው ሊሞቱ መቻላቸውን የሚያመላክት ቢሆንም፤ የዓለም አቀፍ ተመራማሪዎቹ የጥናት ውጤት በይፋ እስኪገለጥ ድረስ፣ አራፋት የሞቱት በፖሎኒየም ተመርዘው ነው ብሎ አፍን ሞልቶ ለመናገር አይቻልም፡፡ በተጨማሪም የምርመራውን ሂደት ሊያውክ ይችላል ተብሎ የተፈራ ቴክኒካዊ ችግር እንዳለ ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ተመራማሪዎች ይናገራሉ፡፡ ይኸውም በሰውነት ውስጥ የገባ ፖሎኒየም በመሬት ውስጥ የመፈራረስ ባህሪ ስላለውና፤ ስምንት አመትም የንጥረ ነገሩን ቅንጣት ለማግኘት የመጨረሻው የጊዜ ገደብ በመሆኑ ተጨባጭ ማስረጃ ከአራፋት ቅሪተ አካል ላይ ላይገኝ ይችላል የሚል ስጋት አለ፡፡
አፍቃሬ እሥራኤል የሆነው (thetrumpet.com) የተሰኘው ድረ አምባ፤ ባሳለፍነው የፈረንጆች ወር መጀመሪያ ላይ “አራፋት አሁንም እሥራኤልን እያሸበሩ ነው” በሚል ርእስ ባቀረበው ሐተታ፤ መላውን የአራፋት አስከሬን ምርመራ ጥያቄ ውስጥ የሚከት አንኳር ነጥብ አንስቷል፡፡ ድረ አምባው በዚህ ሀተታው እንደጠቆመው፤ ብዙ ተስፋ የተጣለበት የምርመራ ውጤት ከተሳካለት ለማሳየት የሚችለው “አራፋት በምን ተመርዘው እንደሞቱ ነው እንጂ ማን እንደመረዛቸው አይደለም” ብሏል፡፡ እውነት ነው! ቀድሞውንም መርዝ ለመግደያ መሣሪያነት የሚመረጠው ኢላማውን ያለ ምንም ዱካና ፍንጭ ለማስወገድ እንደመሆኑ፣ ከመርዙ ጀርባ ያለው ማን እንደሆነ ማግኘቱ ሁልጊዜ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡
ፍልስጤማውያን ተወዳጅ ታጋይ መሪያቸው የሞቱበትን ሁናቴ ለማወቅ የሚያስችለውን የአስከሬን ምርመራ በአንክሮ ይከታተሉታል፡፡ አራፋት የሞቱት በፖሎኒየም ተመርዘው መሆኑ ከተረጋገጠ፤ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ወገኖች ቀጣይ ፈተና ደግሞ “የመረዛቸው ማን ነው?” ለሚለው ከባድ ጥያቄ ትክክለኛ መልስ ማግኘት ይሆናል፡፡ መልሱም በአራፋት መቃብር ውስጥ የሚገኝ አይመስልም - ለዚያውም ከስምንት አመታት በኋላ፡፡

Read 6352 times