Saturday, 05 January 2013 10:49

የዘንድሮ የገና ገበያ ዋጋ ከዓምናው የተሻለ ነው ተባለ Featured

Written by  መልካሙ ተክሌ እና ሠላም ገረመው
Rate this item
(4 votes)

ሸማቾች በጤፍ ዋጋ መናር ተማርረዋል
የጤፍ ዋጋ ያልቀነሰው ምርቱ ከተመጋቢው ጋር ባለመመጣጠኑ ነው - መንግስት
በመዲናዋ የተለያዩ የገበያ ስፍራዎች ያገኘናቸው ሸማቾች የዘንድሮ የገና በዓል የገበያ ዋጋ ከዓምናው እንደሚሻል የገለፁ ሲሆን የጤፍ ዋጋ መናር ግን እንዳስመረራቸው ተናግረዋል፡፡ ለጤፍ ከ2ሺ ብር በላይ መናር ምክንያቱ በዋናነት የመንግስት ቸልተኝነት ነው ሲሉም ወቅሰዋል - ሸማቾች፡፡ ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ሰሞኑን በፓርላማ ለተቃዋሚ ፓርቲ ተወካይ አቶ ግርማ ሰይፉ አስተያየት በሰጡት ምላሽ፤ የጤፍ ምርት በ20 በመቶ መጨመሩን ጠቁመው፤ ዋጋው ሊቀንስ ያልቻለው ምርቱ ከጤፍ ተመጋቢው ጋር ባለመመጣጠኑ ነው ብለዋል፡፡
በአላትን ከቤተሰቦቻቸው ጋር በስፋት ማክበር እንደለመዱ የገለፁት አስር ቤተሰብ የሚያስተዳድሩት ወ/ሮ ዕፀገነትመንግስቴ፤ የዘንድሮ የገና ገበያ ዋጋ ከዓምናው መቀነሱን ይናገራሉ፡፡

ባለፈው አመት ለገና በዓል 180 ብር የገዙትን ቅቤ አሁን በ160 ብር ማግኘታቸውንና ሽንኩርትም ከዓምናው የ4 ብር ቅናሽ ማሳየቱን ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡ በሾላ ገበያ ያገኘናቸው የአራት ልጆች እናት የሆኑት /ወሮ ኤልሳቤጥ ግን በዚህ አይስማሙም፡፡ የዘንድሮው የገበያ ዋጋ ከዓምናው የተሻለ አይደለም ፤ አምና እንደውም የአቅርቦት ችግር አልነበረም ብለዋል፡፡ ዓምና ዘይት በቀበሌና በኢትፍሩት ይሰጥ እንደነበር ያስታወሱት ወ/ሮ ኤልሳቤት፤ ዘንድሮ ግን በሸማቾች ማህበር ብቻ እንደሚሰጥና  ኢትፍሩትም ቢሆን የአቅርቦት እጥረት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ ከገርጂ ገበያ በሁለት መቶ ሃያ ብር የገዟቸውን ሁለት ዶሮዎች ይዘው ያገኘናቸው የአራት ልጆች እናት የሆኑት ወ/ሮ ሀና ይልማ፤ የአምናውና የዘንድሮን ገበያ ዋጋ ልዩነት እንደማያስታውሱት ተናግረዋል፡፡ “አንዳንድ ጐረቤቶቼ ሲያማርሩ እሠማለሁ፤ እኔ ቤቴ ጐድሎ ስለማያውቅ ስለመወደዱ የማውቀው ነገር የለም” ብለዋል፡፡ 
የገና በዓል የገበያ ዋጋን ለማወቅ በመርካቶ፣ ገርጂ እና ሾላ ገበያ ተዘዋውረን በቃኘነው መሰረት፤ በመርካቶ አንደኛ ደረጃ ቀይ ሽንኩርት በኪሎ 5 ብር ከ20 ሲሸጥ፤ በሾላ ከ5.50 - 6ብር፤ በገርጂ ደግሞ ከ7.50 - 8 ብር እየተሸጠ መሆኑን አረጋግጠናል፡፡ በአትክልት ተራ ደግሞ ቀይ ሽንኩርት በኪሎ ከ5-5.50ብር፣ ነጭ ሽንኩርትከ15-20ብር እየተሸጠ ነው፡፡ በመርካቶ ቅቤ በረንዳ አንድ ኪሎ ለጋ ቅቤ በ160ብር፤ መካከለኛ ቅቤ በ145 ብር፤ በሳል ቅቤ በ130ብር ሲሸጥ፤ በገርጂ ገበያ ለጋ ቅቤ በ170ብር፤ መካከለኛው 150 ብር፤ በሳሉ 140 ብር እየተሸጠ ነው፡፡ በሾላ ገበያ ደግሞ ለጋ ቅቤ 160 ብር፤ መካከለኛ 145 ብር፤ በሳል ቅቤ 135 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡ በጎጃም በረንዳ የጎጃም ለጋ ቅቤ 130 ብር፣ የሸኖ 140ብር፣ የወለጋ ከ110-120ብር፣ የግንደበረት ቅቤ በኪሎ 125 ብር እየተሸጠ ሲሆን የጎጃም በረንዳው ገበያ የተቀዛቀዘ ይመስላል፡፡ የአካባቢው ነጋዴዎች እንደሚሉት፤ የሕዝቡ የመግዛት አቅም በማሽቆልቆሉ ነው የቅቤ ገበያ የተቀዛቀዘው፡፡  የዘይት ዋጋ እንደአይነቱ የሚለያይ ሲሆን ሞጆ ዘይት በሊትር 42 ብር፤ የኑግ ዘይት 55 ብር ፤ የታሸገ የፓልም
ዘይት ባለ ሦስት ሊትሩ 81 ብር እየተሸጠ እንደሆነ ታውቋል፡፡ በኤልፎራ ዶሮ 81 ብር፤ በመርካቶ አውራ ዶሮ 90 ብር፤ በሾላ ደግሞ እስከ 100 ብር፤ በገርጂ ገበያ ከ100-110 ብር ይሸጣል፡፡ አንደኛ ደረጃ ነጭ ሽንኩርት በመርካቶ ኪሎው 15 ብር፤ በሾላ ገበያ እንዲሁ 15 ብር፤ በገርጂ 20 ብር እየተሸጠ ነው፡፡ ሁለተኛ ደረጃ ነጭ ሽንኩርት በመርካቶ ከ14-13 ብር፤ በሾላ 14ብር፤ በገርጂ ገበያ ደግሞ ከ17-18 ብር በመሸጥ ላይ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በሾላ ገበያ ፍየል ከ700ብር - 5ሺ ብር፤ በግ ከ1ሺ ብር - 2ሺ ብር፤ በሬ ደግሞ 11ሺ ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡ እዚያው ገበያ አይብ 45ብር፣ ማር ከ60 -70 ብር እየተሸጠ ነው፡፡በሾላ ገበያ የዓመት በዓል ሸመታ ሲያከናውኑ ያገኘናቸው የየካ ሚካኤል አካባቢ ነዋሪ ወይዘሮ ታደለች አይቼው በሰጡን አስተያየት፤ “ዘንድሮ ሁሉም ነገር ጥሩ ነው” ብለዋል፡፡ በዚሁ ገበያ እየሸመቱ ያገኘናቸው ሌላዋ ወይዘሮ አልማዝ ዘውዴ፤“ቀይ ሽንኩርት ቢረክስም ቅቤም አልቀመስ ብሏል፤ ጤፍ የተወደደው ሳይጠፋ ነው፤ መንግስት እንደ ዘይት ዋጋ እጁን ማስገባት አለበት፣ በነፃ ገበያ ስም ዝም መባል የለበትም፡፡ ሚሊዮን ብር ቢኖረኝ እንኳን በዋጋ መናር የተነሳ ላይበቃኝ ይችላል፡፡ ነጋዴው ማንም ከልካይ ስለሌለበት በ30 ብር ያመጣውን ዶሮ በመቶ ብር ይሸጣል፡፡ የጤፍ ዋጋ ከ1700 ብር በልጦ እየሞትን ነው፣ ለመኖር ግን እንገዛዋለን” ብለዋል፡፡ከ20 ዓመት በላይ በቅቤ ንግድ የሚተዳደሩት አቶ ብርሃኑ ያደቴ፤ “የቅቤ ዋጋ ቢረጋጋም ጤፍ 2300 ብር ሲገባ መንግስት ለምን ዝም ይላል? አምና ብዙ የአመት በዓል ሸመታ መሸመት አቅቶን ነበር፤ ዘንድሮ ደግሞ ዋነኛው የጤፍ ዋጋ አልተቻለም” ብለዋል፡፡ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ እህል ነጋዴ፤ በቆሎ 700 ብር በኩንታል፣ ስንዴ ከ800-900ብር፣ ጤፍ ከ1013-1600 ብር እየሸጡ መሆናቸውን ገልፀው፣ በተለይ ጤፍ ከእለት ወደ እለት እየናረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ “ጤፍ ከዚህ የበለጠ ቢጨምር ለነጋዴም ጥሩ አይደለም፣ ከሚመጣበት ነውየሚጨምረው፣ እኛ ጋ ብቻ አይደለም፡፡ መንግስት ይኼን መቆጣጠር ተስኖታል” የሚሉት ነጋዴው፤ የመንግስት አካላት በጉዳዩ ዙርያ እያወያዩዋቸው እንደሆነ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡ በሌላ በኩል የበሬ ዋጋ በየጊዜው እየናረ መምጣቱን የበሬ ስጋ በቅርጫ የመከፋፈል ልምድ ያላቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡ አቶ ፍቅረስላሴ ስለሺ ለበርካታ አመታት በተለይ ደግሞ ለገናና ለፋሲካ በአላት ቅርጫ በመግባት ስጋ ለቤተሰባቸው ያስገቡ እንደነበር ይገልፃሉ፡፡ የዛሬ ሦስት አመት 400 ብር ይገዙት የነበረው አንድ ሙሉ መደብ ቅርጫ፤ በየጊዜው እየጨመረ አሁን አንድ ሺህ ብር መድረሱንና በፊት ለአራትና ለአምስት የሚከፋፈሉትን አንድ በሬ ዘንድሮ ለአስርና ለአስራ ሁለት ሆነው እንደሚከፋፈሉ ተናግረዋል፡፡ ለብዙ ዓመታት የለመዱት ባህል በመሆኑ እንጂ እንዲህ ተወድዶ ቅርጫ ባይገቡ እንደሚመርጡ ገልፀዋል፡፡ 
የበሬ ዋጋ በጣም መናሩን የሚናገሩት የካዛንቺስ ነዋሪው አቶ መርድ አድነው፤ በፊት 4500 ብር ይሸጥ የነበረ በሬ አሁን 12 ሺህ ብር መግባቱንና በዚህም የተነሳ እያንዳንዱ ሰው ለቅርጫ 1200 ብር እንደሚያዋጣ ተናግረዋል፡፡ “ይሔ መካከለኛው በሬ ነው፤ ትልቁ 15ሺ ብር ደርሷል” የሚሉት አቶ መርድ፤ ዋጋው የሚጨምረው ያለ ምንም ምክንያት ነው፣ ይሔንን መንግስት መመልከት አለበት ብለዋል፡፡

Read 6327 times