Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Print this page
Saturday, 05 January 2013 10:36

የቀድሞ ባለቤቱን ጨምሮ 4 ሠው የገደለው ተጠርጣሪ አልተያዘም Featured

Written by 
Rate this item
(3 votes)

በሠሜን ሸዋ ዞን መርሃቤቴ ወረዳ ልዩ ስሙ ጭራሮ ማርያም በተባለ ቦታ የቀድሞ ባለቤቱን ጨምሮ የባለቤቱን ወላጅ እናት፣ ወንድም እና የትዳር ጓደኛዋን በጥይት ደብድቦ የገደለው ተጠርጣሪ እስካሁን እንዳልተያዘ ተገለፀ፡፡ ተጠርጣሪው ታህሳስ 11 ቀን 2005 ዓ.ም ከምሽቱ 1፡30 ገደማ ነው ግድያውን የፈፀመው ተብሏል፡፡ በእለቱ በተፈፀመው ግድያ ወላጅ እናታቸውን ወ/ሮ ዘነበች አደፍርስን፣ ወንድማቸውን አቶ ችሮታው መኮንንን እንዲሁም እህታቸውን ወ/ሮ አበሬ መኮንን እና ባለቤቷን አቶ ተጫነን በአንዲት ጀንበር ያጡት አቶ አሻግሬ መኮንን፤ ይህን ሁሉ ሠው የገደለው ግለሠብ እስካሁን በፖሊስ ቁጥጥር ስር አለመዋሉ የፈጠረባቸውን ስጋት በመግለፅ ወደግድያ ላመራው ጠብ መነሻ የሆነው የንብረት ክፍፍል ጉዳይ መሆኑን ገልፀውልናል፡፡

“ተጠርጣሪው ግለሰብ ከወ/ሮ አበሬ መኮንን ጋር በነበረው አጭር የፍቅር ጊዜ አንድ ልጅ ያፈሩ ሲሆን ህጋዊ ትዳር አልመሠረቱም” የሚሉት አቶ አሻግሬ፤ ሟችና ገዳዩ በፍቅር መዝለቅ ተስኗቸው ከተለያዩ በኋላ ሟች ወ/ሮ አበሬ ሌላ ትዳር መመስረቷንና ተጠርጣሪውም ንብረት አካፍይኝ በማለት ጥያቄውን በሽማግሌዎች በኩል ማቅረቡን 
ተናግረዋል፡፡ ወ/ሮ አበሬም “እኔ የምኖረው በአባቴ መሬት ላይ ነው፤ እሡን ላካፍልህ አልችልም፤ በጋራ ያፈራነውን ንብረት ግን ላካፍልህ እችላለሁ በማለቷ መስማማት አልቻሉም፡፡ በዚህም ተደጋጋሚ ዛቻና ማስፈራሪያ ሲያደርስባት ነበር፡፡ ሁኔታው ያሰጋት ሟች ለፖሊስበማመልከት የተከሳሽነት መጥሪያ አምጥታ ትሠጠዋለች፡፡ ተጠርጣሪውም መጥሪያውን በእለቱ ተቀብሎ አረቄ ቤት ይሄዳል” ያሉት አቶ አሻግሬ፤ ከምሽቱ 1፡30 ሲሆን ተመልሶ በመምጣት፣ በሩን በሃይል በርግዶ በመግባት በመጀመሪያ ባሏን፣ ቀጥሎ እሷን ከዚያም እናቴን በመጨረሻም ወንድሜን ገድሏል፡፡” ሲሉ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡ ይህ ሁሉ ሲፈፀም የሟችና የገዳይ ልጅ የሆነው የ10 አመቱ ታዳጊ በቤት ውስጥ ተደብቆ ይመለከት እንደነበር ያስታወሡት አቶ አሻግሬ፤ ታዳጊው ባየው ነገር ስነ ልቦናው ክፉኛ በመጐዳቱ ስለ ድርጊቱ አንድ በአንድ ለፖሊሶች ማስረዳቱን ተናግረዋል፡፡ ግድያው ሲፈፀም ታጣቂዎች በአካባቢው ነበሩ ተብያለሁ፣ ተጠርጣሪው ድርጊቱን ፈፅሞ ከወጣ በኋላም ከበውት እንደነበር ተነግሮኛል የሚሉት አቶ አሻግሬ፤ ታጣቂዎቹ “ለምን አልያዛችሁትም” ሲባሉ “ምሽት ስለሆነ መለየት አልቻልንም” የሚል ምላሽ መስጠታቸውን እንደሰሙም ገልፀዋል፡፡ የሟቾች የቀብር ስነስርዓት በአካባቢው በምትገኘው ጭራሮ ማርያም ቤተክርስቲያን በአንድ ቀን እንደተፈፀመ አቶ አሻግሬ አስረድተዋል፡፡ ከሚኖርበት አዲስ አበባ አቃቂ አካባቢ ሚያዝያ 14/2004 ዓ.ም ለስራ ምክንያት ወደ አካባቢው ሄዶ የነበረው አንደኛው ሟች አቶ ችሮታው መኮንን፣ ባለትዳርና የ3 ልጆች አባት መሆኑም ተገልጿል፡፡ 
የሟች ባለቤት ወ/ሮ ብዙነሽ መንግስቱ፤ ከሟች ጋር ታህሣሥ 11 ቀን 2005 ዓ.ም ግድያው ከመፈፀሙ ከአንድ ሠዓት በፊት በግምት 12፡30 አካባቢ በስልክ ተገናኝተው እንደነበር፣ ለበአል እንደሚመጣ እንደነገራትና በኋላም ከምሽቱ 3፡30 አካባቢ የባለቤቷንና የቤተሠቦቹን መገደል በስልክ መስማቷን ገልፃለች፡፡ ድርጊቱ ሲፈፀም የተመለከተው የ4ኛ ክፍል ተማሪና የ10 አመት ታዳጊ የሟችና የገዳይ ልጅ ዳኜ ወርቁ፤ ስለ ድርጊቱ የተመለከተውን ሲናገር፤ “ምሽት ላይ የቤታችን አጥር እና የቤቱ በር ክፍት ነበር፤ መጀመሪያ እንደገባ ያገኘው ባልየውን ነው፣ ከዚያ ጓዳ ወደነበረችው እማዬ ጋ ሄዶ ታፋዋን ሲመታት ስትደፋ ደግሞ መታት፤ ከዚያ አያቴ ጋ በበራፉ አሾልኮ ግንባሯን በጥይቱ ሁለቴ መታት፣ ከዚያም ችሮታውንም መንገድ ላይ አግኝቶ መታው” ብሏል፡፡ ሠዎቹን ከገደለ በኋላ መሣሪያውን ወደሡም እንዳነጣጠረበት፣ ነገር ግን አልጋ ስር ገብቶ በመደበቁ መትረፉንም ታዳጊው ገልፆልናል፡፡ ታዳጊው እናቱን ማትረፍ ባይቻለውም በጥይቱ ተመትታ ከወደቀች በኋላ አንገቷን አቅፎ ያለቅስ እንደነበር ተናግሯል፡፡ የቤተሠቦቻቸው ገዳይ እንዲያዝ ከፖሊሶቹ ጋር በመተባበር ላይ እንደሚገኙ የነገሩን አቶ አሻግሬ በበኩላቸው፤ የአካባቢው ፖሊሶች ለጉዳዩ ተገቢውን ትኩረት ባለመስጠታቸው ተጠርጣሪው እስካሁን እንዳልተያዘና በአካባቢውም እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡ ፖሊሶቹ ጥቆማ ብንሠጣቸዉ እንኳ ለመቀበል እምብዛም ፈቃደኛ አልሆኑም የሚሉት አቶ አሻግሬ፤ በሚዲያ እንኳ ወጥቶ የኢትዮጵያ ህዝብ ይፍረደኝ ብትል ምን ያደርጋል? ጥቅም የለውም፣ ጠቡም የቤተሰብ ጉዳይ ነው” የሚል ምላሽ እንደተሠጣቸው ነግረውናል፡፡  ተጠርጣሪው ከዚህ በፊትም ሶስት ሠዎችን ገድሎ ለተወሰኑ ዓመታት ከታሠረ በኋላ የተፈታ መሆኑን ከሟች ቤተሰቦች ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ 

 

Read 7654 times Last modified on Saturday, 05 January 2013 11:00

Latest from