Saturday, 05 January 2013 10:36

የሆስተሷን አይን አጥፍቷል የተባለው በይግባኝ 20 አመት ተፈረደበት

Written by  ሠላም ገረመው
Rate this item
(2 votes)

ከፍተኛው ፍ/ቤት 14 አመት ፈርዶበት ነበር
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ አስተናጋጅ የነበረችውን ሆስተስ አበራሽ ሀይላይን አይን አጥፍቷል ተብሎ ከፍተኛ ፍ/ቤት የ14 ዓመት እስር በይኖበት የነበረው የቀድሞ ባለቤቷ ፍስሃ ታደሰ፤ አቃቤ ህግ ለጠቅላይ ፍ/ቤት ባቀረበው ይግባኝ ትላንትና የ20 አመት እስር ተፈረደበት፡፡ ለጠቅላይ ፍ/ቤት ባቀረበው ይግባኝ የስር ፍ/ቤት የህግ ስህተት አለበት ያለው አቃቤ ህግ፤ ተከሳሹ ጋብቻቸው 
በፍቺ ከተጠናቀቀ በኋላ ሆን ብሎ ሰው ለመግደል ማሰቡ፣ የእድሜ ታናሹንና የቀድሞ ባለቤቱን በአሰቃቂ ሁኔታ ለመግደል መሞከሩ፣ ድርጊቱን መፈፀሜን አላስታውስም ብሎ በመካድ መከራከሩ እንዲሁም በተለያዩ የሰውነት ክፍሎቿ ላይ የፈፀመው ጉዳትና ድርጊት ሲታይ የስር ፍ/ቤት የሰጠው ውሳኔ አነስተኛ መሆኑን ይጠቁማል ብሏል፡፡

የስር ፍ/ቤት ያቀረበው የቅጣት ማክበጃንም በተመለከተ ካቀረበው ሠባት የቅጣት ማክበጃ ውስጥ የስር ፍ/ቤቱ አንዱን ብቻ መያዙ ተገቢ አይደለም ሲል የተከራከረው አቃቤ ህግ፤ የተበዳይ አይን መጥፋቱ በተለይም የተሰማራችበትን የበረራ አስተናጋጅነት ስራ በዘላቂነት ማሳጣቱ እየታወቀ ተከሳሹ ያቀረበውን ሦስት የቅጣት ማቅለያ የስር ፍ/ቤት ተቀብሎ ውሳኔ መስጠቱ ተገቢ አይደለም ይላል፡፡ ተከሳሽ ኤች አይቪ ፖዘቲቭ መሆኑን በዋናነት ለቅጣት ማቅለያ ማቅረቡን የጠቀሰው አቃቤ ህግ፤ ይህም የሚያሳየው አስቀድሞ በማይድን በሽታ መያዙን እንደሚያውቅ ነው በማለት ተከሳሹ በሞት ወይም በዕድሜ ልክ እስራት መቀጣት ነበረበት ብሏል፡፡ የተከሳሽ ጠበቆች በበኩላቸው፤ የስር ፍ/ቤት ውሳኔ የሰጠው ህጉን ተከትሎ መሆኑን ጠቅሰው፤ ተከሳሽ ተጐጂዋ 
ህይወቷ እንዳያልፍ ተገቢውን ጥረት ማድረጉን፣ ድርጊቱንም የፈፀመው በከፍተኛ የክህደት ስሜት ውስጥ ባለበት ሁኔታ እንደሆነና ወንጀሉም በሙከራ ደረጃ የቀረ በመሆኑ፣ የቅጣቱ መነሻ የዕድሜ ልክ እስራት እንዲሆን ህጉ እንደሚያዝ ገልፀዋል፡፡ አቃቤ ህግ ያቀረበው የሞት ቅጣት በህጉ ያልተቀመጠ መሆኑን የጠቆሙት ጠበቆች፤ የሙከራ ወንጀል የቅጣት ጣሪያው ዕድሜ ልክ መሆኑን እና ይህንንም በመያዝ የስር ፍ/ቤቱ ማቅለያዎችን ወስዶ እርከኖችን በመቀነስ 14 አመት መወሰኑ ተገቢ ነው ሲሉ ተከራክረዋል፡፡ የሁለቱን ወገኖች ክርክር የተመለከተው የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት፤ ተከሳሹ የፈፀመውን የወንጀል ድርጊት ተበዳይ ስታስረዳ፤ በህክምና ህይወቷ ባይተርፍ ኖሮ ተከሳሽ ህይወቷ እንዲተርፍ እንዳልሳሳላት መገንዘቡን ገልፆ፤ ትዳራቸውን ተስማምተው ከተፋቱ በኋላ በስቃይ እንድትሞት በማሰብ የፈፀመው ድርጊት በመሆኑ እንዲሁም እንደዚህ አይነት ድርጊት በተደጋጋሚ የማይፈፀም እና ከብዙ አመታት አንድ ጊዜ የሚከሰት መሆኑ የድርጊቱን 
ክብደት ያሳያል ብሏል፡፡ ፍ/ቤት አቃቤ ህግ ካቀረበው የቅጣት ማክበጃ ውስጥ ድርጊቱ በሌሊት መፈፀሙ፤ ድርጊቱን በቀድሞ ባለቤቱ ላይ 
እያመነችው ማድረጉና የድርጊቱ ቦታ ቤቷ ውስጥ መሆኑ የሚሉትን ወስዶ የስር ፍ/ቤቱ የሰጠውን ውሳኔ በመሻር፣ 
ተከሳሹ እጁ ከተያዘበት ጊዜ ጀምሮ በ20 አመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኗል፡፡

Read 3901 times