Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 29 December 2012 09:32

ውሸትን ፍለጋ!

Written by 
Rate this item
(7 votes)

“በጣም አዝናለሁ መክሊት…ባለቤትሽ መብራቱ በደረሰበት የመኪና ግጭት የተነሳ በጣም የሚያሳዝን እና…ምናልባትም የሚያስገርም ሊባል የሚችል የአንጐል ጉዳት እንዳጋጠማው ማረጋገጣችንን ስገልጽልሽ በእውነት በእውነት እያዘንኩ ነው” አላት የአእምሮ ሀኪሙ ሙልተዘም አንገቱን ግራ ቀኝ እየነቀነቀ፡፡ ባለቤቷ መብራቱ በመኪና አደጋ በደረሰበት አደጋ በሆስፒታሉ ውስጥ ለሶስት ወር ተኝቶ ሲታከም ቆይቷል። ሙሉ አካላዊ ጤንነቱ ቢመለስም በጭንቅላቱ ላይ የደረሰበት ግጭት የተወሰነ የባህሪ ለውጥ እንዳመጣበት ዶክተር ሙልተዘም ተገንዝቧል፡፡ ይኼንኑ ለሚስቱ ለመንገር ነበር ቢሮው ጠርቷት እያነጋገራት የነበረው፡፡

“የሚያስገርም አይነት ስትል?” አለች መክሊት ግራ ተጋብታ፡፡ 
“ላንቺ ቀለል ባለ ቋንቋ ለማስረዳት…እ…ምን ማለቴ መሰለሽ?...መብራቱ በጭንቅላቱ ላይ በደረሰበት አደጋ የተነሳ ከአሁን በኋላ እንደማንኛውም ሰው የሚያስበውን ነገር ወይም ስሜቱን መደበቅ አይችልም። ለምሳሌ መዋሸት አይችልም፡፡ ወይም ደግሞ ሁልጊዜ እውነተኛ ስሜቱን ነው የሚያንፀባርቀው፡፡” አላት ሀኪም ሙልተዘም አንገቱን አቀርቅሮ፡፡
“ዶክተር ይኼ ታድያ እንዴት ችግር ሊሆን ይችላል? ማለቴ እውነተኛ መሆን እና ስሜትን በግልጽ መናገሩ…እንደውም ጥሩ እኮ ነው….” መክሊት ግራ ተጋብታ ንግግሯን አንጠልጥላ ተወችው፡፡
“እሱ ልክ ነሽ፡፡ ሁላችንም እውነተኛ መሆን እና ግልጽነት እንፈልጋለን፡፡ ነገር ግን…በህይወታችን ውስጥ የተወሰነ ውሸት…ማለት ራሳችን ጋር የምናስቀራቸው ነገሮች ሊኖሩ ይገባል፡፡ የምናስበውን ነገር ሁሉ የምንናገር ከሆነ ትንሽ አስቸጋሪ ነው፡፡ ያው ማህበራዊ ህይወት ለመኖር አለ አይደል…” ዶክተር ሙልተዘም እንዴት አድርጐ እንደሚያስረዳት እርግጠኛ አልነበረም፡፡
መክሊት በመኪና አደጋው ምክንያት ባለቤቷ ላይ ተፈጠረ የተባለው የአእምሮ ጉዳት ሊገባት አልቻለም፡፡ ከእንግዲህ መዋሸት አይችልም ብሎ በሽታ እንዴት ያለ ነው? እውነተኛ መሆንን ማን ይጠላል?
“ዶክተር ይቅርታ አድርግልኝና ያጋጠመውን ጉዳት እንደችግር ልወስደው አልቻልኩም፡፡ ምናልባት ስላልገባኝ ይሆናል፡፡ ግን እውነተኛ መሆን የሚበረታታ እንጂ የሚጠላ ነገር አልመሰለኝም” አለች መክሊት ድምጿን ሥጋት እየተጫነው፡፡
ዶክተር ሙልተዘም ከዚህ በላይ ሊያስጨንቃት አልፈለገም፡፡ በራሷ ጊዜ ሁኔታውን እንደምትደርስበት ገመተ፡፡
“አሁን ባለቤትሽን ለማግኘት ዝግጁ የሆንሽ ይመስለኛል፡፡ ብቻሽን ነው እንዴ ልትወስጅው የመጣሽው?”
“አባቴ እና እናቴም አብረውኝ መጥተዋል፡፡ ውጪ ሆነው እየጠበቁን ነው…” አለችው መክሊት፡፡
ዶክተር ሙልተዘም የእናት እና አባቷን መምጣት የወደደው አልመሰለም፡፡ ፊቱን ቅጭም አድርጐ ሲያስብ ከቆየ በኋላ፣ ትከሻውን ምንም ሊደረግ አይችልም በሚል ስሜት ሰብቆ፣ መክሊትን ባለቤቷ ወደተኛበት ክፍል ይዟት ገባ፡፡ መብራቱ ውስጠኛው ክፍል ውስጥ ጋቢ ከላይ ደርቦ አንድ ወንበር ላይ ቁጭ ብሏል፡፡
መክሊት እንዳየችው ወደሱ ሮጣ አንገቱ ላይ ተጠመጠመችበት፡፡ ጭንቅላቱን በመኪና አደጋ ሲገጭ ለብዙ ቀናት ያህል ማንንም ለመለየት ከማይችልበት ሁኔታ ላይ ደርሶ ነበር፡፡ አሁን ግን ሙሉ በሙሉ የተሻለው ይመስላል፡፡
“መክሊትዬ በጣም ነበር የናፈኩሽ…” ብሎ አንገቷ ስር ውሽቅ አለ፡፡
መክሊት የባለቤቷ ሁኔታ አንሰፈሰፋት፡፡ እሷም በጣም ናፍቃው ነበር፡፡ ተቃቅፈው ለደቂቃዎች ቆዩ፡፡ በዶክተሩ አስታዋሽነት ተላቀው ከሆስፒታሉ ህንጻ ወጡ።
ዶክተር ሙልተዘም የመብራቱ ሁኔታ በጣም ያሳሰበው ይመስላል፡፡ የሆስፒታሉን ህንጻ ለቀው ሲወጡ፣ ከኋላ አተኩሮ ሲያስተውላቸው ቆየና አንገቱን እየነቀነቀ ወደቢሮው ገባ፡፡ መክሊት መብራቱን ከላይ እስከታች ቃኘችው፡፡ ጉስቁልቁል ብሏል፡፡ አንጀቷን በላት፡፡ የሆዷን በሆዷ ይዛ ልታጽናናው ፈለገች፡፡
“በጣም አምሮብሃል መብሬ” አለችው፡፡
“አዎ ያው ተኝተን ይኼን ሾርባ እየጠጣን…ለዚህ ይሆናል ያማረብን …” አላት
“እኔስ ተለወጥኩ?” አለችው፡፡
መብራቱ ከላይ እስከታች ቃኛት፡፡
“አንቺም ምንም አትይም፤ ግን ቦርጭ ጨመርሽ…ደሞ ቁመትሽ አጭር ስለሆነ ቦርጭ አያምርብሽም…” አላት ኮስተር ብሎ፡፡
መክሊት እየቀለደ መስሏት መጀመሪያ ፈገግ አለች። ፊቱ ላይ ቀልድ ስታጣ እና ከልቡ መሆኑን ስታውቅ ድንግጥ አለች፡፡ ቦርጫም መባል እንደማትወድ ስለሚያውቅ ስለቦርጭ እሷ ፊት ሲያወራ ተጠንቅቆ ነበር፡፡ አሁንም ጥሩ ነው ያለሽው ምናምን እንዲላት ነበር የጠበቀችው፡፡ የዶክተር ሙልተዘም ማስጠንቀቂያ በጆሮዋ ማንቃጨል ጀመረ፡፡
“እማማ እና አባባ እኮ ክበቡ ጋ እየጠበቁን ነው…እንዴት ናፍቀውሃል መሰለህ…? እማማ በተለይ በጣም ነው የናፈቀችህ…መብራቱ እንዲህ ብሎ እንዲያ ብሎ እያለች ከአፏ ነጥላህ አታውቅም፡፡” አለች መክሊት አይኑን በስስት እያየችው፡፡
“የእሳቸውን መናፈቅ እንኳን ተይው … እንደውም አይናቸውን ባላይ ደስ ይለኝ ነበር” አለ መብራቱ ክፍት ብሎት፡፡
“ለምን የኔ ጌታ? እንደ ልጇ እኮ ነው የምትወድህ መብርዬ…” መክሊት የምትናገረው ጠፋባት፡፡
“ወይ እንደልጅ መውደድ! እናትሽ እኮ በጣም ባለጌ ናቸው!” አለ መብራቱ በቅያሜ ፊቱን ቅጭም አድርጐ፡፡
“እንዴት?” አለች መክሊት ተደናግጣ
“ስንት ጊዜ መሰለሽ ያልሆነ ነገር እንድናደርግ የጠየቁኝ፡፡ በጣም ቅሌታም ናቸው፡፡ እኔማ “የልጅዎ ባል አይደለሁም እንዴ… እንዴት እንደዚህ ይጠይቁኛል?” ስላቸው ምን እንዳሉ ታውቂያለሽ… “ቀረብህ!” አይሉኝም መሰለሽ…በጣም ነው የምጠላቸው፡፡ አባትሽ ግን ደግ ናቸው፡፡ እንደውም ባገኛቸው ቆይ እነግራቸዋለሁ…” መክሊት ትንፋሽ አጠራት፡፡ ኡ! ኡ! ብላ መጮህ አማራት።
እናት እና አባቷ ከሆስፒታሉ ክበብ እነሱ ወዳሉበት አቅጣጫ ሲመጡ አስተዋለች፡፡ አባቷ መብራቱ የሚናገረውን ቢሰሙ የደም ብዛታቸው ተነስቶ እዛው ፍግም እንደሚሉ ጥርጥር የለውም፡፡ ወደነሱ እየቀረቡ ሲመጡ አንድ ነገር ማድረግ እንዳለባት ቆረጠች፡፡
መብራቱን እያዋከበች ከሆስፒታሉ ህንጻ ኋላ ወሰደችው፡፡ በጓሮ በኩል አድርጋ ወደ ዋናው መንገድ ወጡ፡፡ ሚኒባስ ታክሲ ስትመጣ መክሊት በፍጥነት አስቁማ መብራቱን እያቻኮለች ወደ ውስጥ ገቡ፡፡ ደንግጣለች!
ዶክተር ሙልተዘም ያለው ነገር አሁን በደንብ ገባት። በእናቷ ቅሌት አፍራ ኢምንት አከለች፡፡ መብራቱ ይኼን ሁሉ ችሎ መቀመጡ ለሱ ያላትን ክብር ከፍ ቢያደርገውም እናቷን ግን ጠላቻቸው፡፡ ቅናት አይሉት ቁጣ በጭንቅላቷ ውስጥ ተቀጣጠለ፡፡
“ባልሽ የልጅነት ወዳጄን ይመስላል፡፡ አባትሽን ከማግባቴ በፊት የነበረኝን ወዳጅ! አይ እንደው ዋ ምን ያደርጋል! ኮርያ ዘማች ሆኖ እዛው ድፍት ብሎ ቀረ እንጂ…እንደው ሁለ ነገሩ፤ አሳሳቁ፣ አረማመዱ፣ አበላሉ…” የሚሉት አባባላቸው አሁን ላይ ሆና ስታስበው በንዴት አንጨረጨራት፡፡ ከእናቷ ጋር ያላት ግንኙነት እስከወዲያኛው ሲበጣጠስ ታወቃት፡፡ በቀጣይ ምን ማድረግ እንዳለባት እያሰበች ሳለ፣ ከታክሲው ኋለኛ ወንበር ሞቅ ያለ ሰላምታ ሰምታ ዞር አለች፡፡
“እንዴ መብሬ! እንዴ መብሬ! እንኳን ለዚህ አበቃህ የኔ ጌታ!...መቼ ከሆስፒታል ወጣህ?” አለ አንድ ወፍራም ቦርጫም ሰውዬ፤ ከተቀመጠበት ወንበር ጀርባ ሆኖ እጁን ለሰላምታ እየዘረጋ፡፡
“ዛሬ ወጣሁ!” አለ መብራቱ ረጋ ብሎ ሰውዬውን እየጨበጠው፡፡
“እንኳን እግዜር አተረፈህ ወንድሜ፡፡ ሌላውን ቀስ ብለህ ትደርስበታለህ…” አለ ሰውዬው በማዳነቅ፡፡
“ኧረ ተመስገን ነው፡፡ በህይወት መትረፉማ ነው ትልቁ ቁም ነገር!” አለ መብራቱ ረጋ ብሎ፡፡ መክሊት ደስ አላት፡፡ አነጋገሩ የተመጠነና የተረጋጋ በመሆኑ ቅድም የተከሰተው አይነት ችግር የሚፈጠረው ሁልጊዜ ላይሆን እንደሚችል አሰበች፡፡ ከሰውዬው አነጋገር ከመብራቱ ጋር አንድ መስሪያ ቤት እንደሚሰሩ ገምታለች፡፡
“ሥራ በቅርቡ ለመጀመር አሰብክ ታዲያ?” አለ ሰውዬው ወደ መብራቱ ጠጋ ብሎ፡፡
“እስቲ አንድ ሁለት ሳምንት ልረፍና አስብበታለሁ፡፡ አንተስ እየሰራህ ነው?” አለ መብራቱ
“አዎ! ይመስገን መቼስ ኑሮ እንደምታየው ተወዷል። ብቻ ተመስገን ነው ልጆቻችንን አናስርብ ብቻ!” አለ ሰውዬው ተለሳልሶ፡፡
“እንዴ አንተም እንደዚህ ትላለህ? አንተማ ተመስገን በል፡፡ የመንግስት ሰራተኛ ሆነህ ከአንድም አራት ቤት አዲስ አበባ ውስጥ አለህ አይደል እንዴ? ለዛውም ጂ ፕላስ ቱ! በየቦታው የያዝከውስ መሬት?”
“አይ መብራቱ! የዘመድ ያንተ ሊሆን አይችልም እኮ!” አለ ሰውዬው ሌላ የሚያውቀው ሰው በታክሲ ውስጥ እንዳለ ለማረጋገጥ ተጨንቆ እየተገላመጠ፡፡
“እንዴ የዘመድማ አይደለም፡፡ ያንተ የራስህ ነው!...እዛ ጉምሩክ ኤክስፓየርድ ያደረገ ዘይት ለማስገባት 10 ሚሊዮን ብር ነጭተህ የለም እንዴ?...” አለ መብራቱ ተራ ወሬ እንደሚያወራ ሆኖ፡፡ የመብራቱን ንግግር በታክሲው ውስጥ ይሰሙ የነበሩ ሰዎች ወደሰውዬው ዞር እያሉ ገልመጥ አደረጉት፡፡
“አንተ ነህ ለካ በተበላሸ ዘይት ሆዳችንን እያተራመስከን ያለኸው! ቆይ ነብር አየኝ በል…” የሚሉ ይመስላሉ በውስጣቸው፡፡
ሰውዬው ተጨነቀ፡፡ ሃሳብ ቢያስቀይርልኝ ብሎ፤
“ማነህ ረዳት…የሶስት ሰው ሂሳብ ተቀበል..” ብሎ እጁን ሲዘረጋ ረዳቱ መክፈሉን ነገረው፡፡
“እንዴት ነው አሁንም ሙስና እየበላህ ነው?” አለ መብራቱ ወደሰውዬው ዞሮ፡፡
ሰውዬው በድንጋጤ አመዱ ቡን ብሎ “ወራጅ! ወራጅ!” ብሎ ጮኸና ከታክሲው ዘሎ ወረደ፡፡
መክሊት የምትገባበት ጨንቋት ተሳቀቀች፡፡ ዶክተሩ የነገራት ችግር እስከዚህ ይደርሳል ብላ አልገመተችም ነበር፡፡ ሌላ ሰው ሳያገኙ ሰፈራቸው እንዲደርሱ መፀለይ ያዘች፡፡ ደግነቱ ምንም ችግር ሳያጋጥማቸው ሰፈር ደርሰው ከታክሲው ወረዱ፡፡
መክሊት የሰፈራቸውን መግቢያ በሰቀቀን ቃኘች። ብዙም የሚያውቁት ሰው የለም፡፡ “እፎይ!” አለችና ከመብራቱ ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘው በሰፈራቸው መግቢያ ላይ ወዳለው ድልድይ መሄድ ጀመሩ፡፡ ከአፍታ በኋላ ከመንገዱ ጥግ ካለ ግቢ፣ የነፍስ አባታቸው መምሬ ስብሀት ወጥተው ከፊት ለፊታቸው ድቅን አሉ፡፡ መክሊት መብራቱን እያቻኮለች እንዳላየች ለመሄድ ስትጣደፍ መምሩ የክርስትና ስሟን እየጠሩ ተከተሏት፡፡
“እህተማርያም! እህተማርያም!...ወዴት ነው ችኮላው? እንዴ ወልደትንሳኤም ተሽሎት ለዚህ በቃ? ጐሽ!!” እያሉ መምሩ መጡ፡፡ መብራቱን ወልደትንሳይ እያሉ በክርስትና ስሙ ነው የሚጠሩት፡፡
“መምሩ…” ብሎ መብራቱ ወደሳቸው ዞረ፡፡ መክሊት እየተሳቀቀች አየችው፡፡
መምሩ መስቀል አውጥተው ካሳለሟቸው በኋላ፣ ስለ መብራቱ ጤንነት እየጠየቁ አብረዋቸው ወደ ቤታቸው መግቢያ አመሩ፡፡ መክሊት መምሩን እንዴት እንዲለዩዋቸው ማድረግ እንደምትችል ግራ ገብቷት ፍዝዝ ብላ ትከተላቸዋለች፡፡
“እኔ ምለው መምሩ…ምነው በጠዋቱ ጋን ጋን ይሸታሉ…ትንሽ እንኳን ረፈድ ቢልልዎ ምን ነበረበት?” አለ መብራቱ በድንገት፡፡ መምሩ ድንግጥ አሉ “ሀሀሀሀሀ… አይ ልጄ! የክርስትና እኮ ነው፡፡ ጉሽ ጠላ ምናለው ብለህ ነው፡፡ ገብስ እኮ ነው፡፡ መጽሐፉም ቢሆን ወይን ያስተፈስህ ልበሰብ አይደል የሚለው? ወይን እስኪገኝ ድረስ ጠላው ምን ይላል ብለህ ነው? ደሞ አልሰከርኩ!” መምሩ በድንገተኛው አስተያየት ተደናብረው ነገሩን ለማድበስበስ ሞከሩ፡፡
“አይ መምሩ ስንቴ ሰክረው ሲወላገዱ ሀገር ያይዎት የለ እንዴ? ከሰከሩ እንደመምሩ ሲባል አልሰሙም?” መብራቱ ልክ እንደ ተራ ወሬ ነበር የሚያወራቸው፡፡
መምሩ ቱግ አሉ፡፡ “ደግ አደረኩ! አጠጣኝ አልኩህ ታዲያ? ብጠጣስ ምን አለበት? …አሾ አበጀሁ! እስቲ ምን ትሆን? ምን ያለው ነው አያ!...እርም ደጃችሁን ብረግጥ!” ብለው መምሩ ጭራቸውን እየነሰነሱ ተቆናጥረው ሄዱ፡፡
መክሊት መግቢያ ቀዳዳው ጠፋት፡፡ መብራቱን እየጐተተች ወደ ቤታቸው ትጣደፍ ያዘች፡፡ የባለቤቷ ነገር ግራ ገብቷታል፡፡ እንዴት ብሎ ነው ወደፊት ሥራውን የሚሰራው? እንዴት አድርጐ ነው ከሰው ጋር የሚኖረው? ዶክተር ሙልተዘም ራሳችን ጋ ሊቀር ይገባል ያለውን ውሸት እንዴት አድርጐ መመለስ ይቻላል? መክሊት መጪው ጊዜ በጣም ፈታኝ እንደሚሆን አውቃለች፡፡ ሰዎችን እውነተኛውን ነገር እየተናገረ ብግን እንደሚያደርጋቸው አስባለች፡፡
ድንገት አንድ ሰይጣናዊ ሃሳብ በአእምሮዋ ላይ ውልብ አለባት፡፡
“መብሬ በትዳራችን ላይ ወስልተህ ታውቃለህ?” ብላ ለመጠየቅ አሰበችና በእጆቿ አማተበች፡፡ “አዎ! አስር ሴቶች…” ቢላትስ? “በስማም!” ብላ በድጋሚ አማተበች እና ትኩር ብላ አየችው! ባሏ ከሌላው ጊዜ የበለጠ የሚፈልጋት ሆኖ ተሰማት፡፡ እንደ አምስት አመት ጨቅላ ህጻን በውሸት ከተውተበተበው ማህበረሰብ ልትጠብቀው ይገባል፡፡
ህመሙ ተሽሎት እንደሁልጊዜው የውሸት መኖርን እስኪለምድ ድረስ ከሰው እንዳይገናኝ ማድረግ እንዳለባት ወሰነች፡፡
ውሸትን ፍለጋ
መሽቶ እስኪነጋ፣
ክረምት ከበጋ
ሰርክ ድካም፣
ውሸትን ፍለጋ…

Read 7256 times Last modified on Saturday, 29 December 2012 11:08