Saturday, 29 December 2012 09:21

የፕላጃሪዝም ሰለባ የሆነው “የአማርኛ ሥነ ግጥም” መጽሐፍ!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(5 votes)

አቶ አለም እሸቱ ያዘጋጁት “መሰረታዊ የምርምርና የዘገባ አጻጻፍ” የተሰኘው መጽሃፍ ስለ ፕላጃሪዝም እንዲህ ይላል:- “ፕላጃሪዝም ማለት የሌላውን ሰው ሃሳብ ወይም አገላለፅ ምንጩን ሳይጠቅሱ እንዳለ ወስዶ በራስ ስራ ውስጥ አስገብቶ መጠቀም ነው…ፕላጃሪዝም የሌላውን ሰው የአእምሮ ውጤት ምንጩን ሳይጠቅሱ ገልብጦ የራስ አስመስሎ የማቅረብ ነገር ስላለበት ነው ከመስረቅ ወይም ከማጭበርበር የሚያንስ አይደለም መባሉ፡፡ እንዲያውም ካለማወላወል ፕላጃሪዝም ሌብነት ነው ቢባል ትክክል ነው፡፡”እኔም በግሌ ይህንን ወንጀል በሩቁ ለመሸሽ ብዙ ጊዜ ጋዜጦችና መጽሄቶች ላይ ስጽፍ ያነበብኳቸውን ጽሁፎች ባለቤትና የመጽሃፍቱን ስም እጠቅሳለሁ፡፡ ምክንያቱም ሃሳቡ የራሴ ስላልሆነ ለባለቤቱ መስጠት ያለብኝ ዋጋና ክብር አለና!! 

ሰሞኑን ግጥም ላይ፣በተለይ ብዙ ገጣሚያን ላይ ክፍተት ፈጥሯል ያልኩትን “የግጥም ሙዚቃ”ን በሚመለከት ለመጻፍ የተለያዩ የውጪ መጻህፍትን ሳገላብጥ ነበር፡፡ በተለይ የሮበርት ሂሊየር፣ የሎውረንስ ፔሬኔ፣ የግሪኒንግ ላምቦርንንና የኤክስ ጄ ኬኔዲን ሥራዎች በጥልቀት ከመረመርኩ በኋላ ከሃገሬ ልጅ ደግሞ የተለየ ሃሳብ ባገኝ በማለት ወደ አቶ ብርሃኑ ገበየሁ “የአማርኛ ሥነ ግጥም” መጽሃፍ ለንባብ ተመለስኩ፡፡ ይህ የአቶ ብርሃኑ ገበየሁ መጽሃፍ በሚጣፍጥ ቋንቋ የተጻፈ፣ የገለጻ ብቃቱ የሚያስደምም በሳል መጽሃፍ ብቻ ሳይሆን፣ በዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች ደረጃ የስነ ግጥም ማስተማሪያ እስከ መሆን የዘለቀ ነው፡፡ እኔ በግሌ ለመጽሃፉ ደራሲ ያለኝ አድናቆትም እጅግ የላቀ ነው፡፡ ዋና ጉዳዬም ሙዚቃ ስለነበር የሎውረንስ ፔሬኔን “sound and sense –introduction to poetry” እና የአቶ ብርሃኑን “የአማርኛ ሥነግጥም” መጽሐፍት ለማስተያየት ሞከርኩ፡፡ ከሌላው ጊዜ በበለጠ በጥልቀት ስመረምረው የመመሳሰል ብቻ ሳይሆን ከዚያም ያለፈ መቀራረብ (መቀዳዳት ብለው ይሻላል) አየሁባቸውና ትንሽ ግር አለኝ - ደነገጥኩም። ልብ አላልኩትም እንጂ ከዚህ ቀደምም የግጥምን ዜማና ምት በተመለከተና በሌሎች ጉዳዮች “ይህንን ነገር ያነበብኩት የቱ መጽሃፍ ላይ ነበር ” የሚል ግርታ ተፈጥሮብኝ ነበር፡፡ እስቲ ግር ያሰኘኝን ነገር አብረን እንመልከት፡፡ 
በኔ ግምት አቶ ብርሃኑ ታታሪና ለሃገራችን ስነ ግጥም የደከሙ ምሁር ናቸውና ያየሁትን ማመን ተቸገርኩ፡፡ ይሁን እንጂ ስህተቶቹ በዚህ ጽሑፍ የጠቀስኳቸው ብቻ አይደሉም፤መላው የፔሬኒ መጽሃፍ በአቶ ብርሃኑ እጅ ተነካክቷል፡፡ ከሁለት ንዑስ ርዕሶች በስተቀር፡፡ ሁሉን በቅጡ መርምሬ አቶ ብርሃኑ መሳሳታቸውን ከተገነዘብኩኝ በኋላ በጣም እያዘንኩ በቅርቤ ያሉ ሰዎችን ምን ማድረግ እንደሚሻል ምክር ጠየቅሁ፡፡ የሁሉም ምላሽ ግን ተመሳሳይ ነበር፡፡ ከሁሉም እውነት ይበልጣል፤ የሚል!…ታዲያ አቶ ብርሃኑ ያንን እጅ የሚያስቆረጥም ድንቅ መጽሃፍ የጻፉትን የሎውረንስ ፔሬኔን ስም በዋቤ መጽኃፍት ተርታ እንኳ ሳያስቀምጡ በቀጥታ የተጠቀሙበት ምክንያት ምን ይሆን ብዙ ግራ የሚያጋቡ ነገሮች ይመጡብናል፡፡ የሚሰራ ሰው ይሳሳታል፤ ብለን ልንተወው እንችል ይሆን የሚቻል አልመሰለኝም፡፡
እስቲ ስለዜማና ምት አቶ ብርሃኑና ፔሬኔ ያሉትን እንመልከት፡፡ አቶ ብርሃኑ ገበየሁ “ዜማ፣ምት እና ቤት አመታት” በሚለው ርዕስ ስር እንዲህ ጽፈዋል፡-
“ህይወትን ልብ ብለን ብናጤናት የማይቋረጥ ዜማ ናት…….የልባችን አመታት፣የደማችን ዝውውር፣ የአየር አተነፋፈሳችን በተወሰነ በጊዜ መጠን ሳይቋረጡ የሚደጋገሙ ሂደቶች ናቸው፡፡ በጸጥታ ውስጥ የምናዳምጠው የሰዎች እርምጃ ዜማ አለው፡፡ የግርግዳ ሰዐት የሚያሰማው እኩል የጊዜ መጠን የጠበቀ ድምጽ ዜማ አለው፡፡ ዝናብ ሲዘንብ የምንሰማው ዜማ አለ፡፡ በአጠቃላይ አካባቢያችን በዜማ የተሞላ ነው፡፡
ሎውረንስ ፔሬኔ ደግሞ በመጽሃፋቸ”ው “Musical Devices” በሚለው ንኡስ ርዕስ ስር እንዲህ አስቀምጠዋል፡-“… outflow it is related to the beat of our hearts ,the pulse of our blood, the in take and of air from our lungs. Everything that we do naturally and gracefully we do rhythmically….our clocks go tick-tick-tick-tick, but we hear them go tick-tock, tick-tock in an endless trochaic.
እስቲ ልዩነታቸው ምንድነው የኔ ግራ መጋባት በነዚህ ሃሳቦች መመሳሰል ብቻ አይደለም፡፡ በርግጥ ይህ ያየነው ቀጥተኛ ትርጉም ነውና ያስደነግጣል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አጠቃላይ የመጽሃፍቱ አወቃቀር፣ርዕስ አሰጣጥ ብቻ ምኑም-ምኑም ሳይቀር ሲመሳሰል ግር ማለቱ አይቀርም፡፡ ሁለቱም መጻህፍት አንድ አይነት የንዑስ ርዕሶች አከፋፈል አላቸው፡፡ እያንዳንዱ ርዕስ ስር ያሉት ሃሳቦች በሙሉ አንድ ናቸው፡፡ ምናልባት የአማርኛ ግጥሞች ለትንታኔ ባይገቡበት ትርጉም ነው ለማለት ከንፈር አያነቅፍም ነበር፡፡ ይህ መመሳሰል ደግሞ ከሌሎቹ ስለ ስነ ግጥም ከተጻፉት መጻህፍት ሁሉ በተለየ ሁኔታ ብቻቸውን አንድ የሆኑበት ነው። ለምሳሌ ሁለቱም መጽሃፍት ሲጀምሩ “ስነ ግጥም ምንድነው ”What is poetry” በሚል ነው፡፡ ቀጥለው ደግሞ አቶ ብርሃኑ ”ሥነግጥምን ማንበብና ማድነቅን መማር” ሲሉ ሎውረንስ ፔሬኔ ደግሞ “Reading the poem” በሚል ርዕስ ጽፈዋል፡፡ ማን ከማን ቀድቶ ይሆን?
በዚህ ርዕስ ስር ያሉትንም ክፍፍሎችም እንመልከት፡-
2.1.1 በድምጽ ማንበብ
ሁለት የንባብ አይነቶች አሉ፡፡ እነዚህም የለሆሳስና የድምጽ ንባብ ናቸው፡፡ ለሆሳስ ንባብ የአንደበት አባላት ሳይንቀሳቀሱና ድምጽ ሳይሰማ የሚደረግ ንባብ ነው፡፡
5.practice occasionally reading a poem aloud.
the two extremes which oral readers often fall into are equally deadly. One is to read as if one were reading a tax report or a rail road time table, un expressively ,in a monotone. The other is to elocute, with artificial flourishes and vocal histrionics.
2.1.2 ደጋግሞ ማንበብ
1.Read a poem more than once.
የሚታወቁም ሆኑ የእንግዳና አዲስ ቃላትን ሁሉ ፍቺ መመርመር፤
…የአዳዲሶቹን ቃላት ፍቺ ከመዝገበ ቃላት ወይም ከአውደ ጥበብ መርምሮ መድረስ..
2.Keep a dictionary by you and use it.
-A few other reference books will also be valuable.
ሌላው ምሰላን በሚመለከት የተጻፈው ሃሳብ የፕላጃሪዝምን ጥያቄ ያስነሳል፡፡ የአቶ ብርሃኑ መጽሃፍ እንዲህ ይላል፡-“ሥነ ግጥም የሚሰሙና የሚታዩ ብቻ ሳይሆን የሚነኩ፣የሚቀመሱ፣ የሚሸተቱ ነገሮችን ወደ አንባቢ ስሜቶች ለማድረስ የሚችል ጥበብ ነው፡፡”
-Imagery may also represents a sound; a smell; a taste; a tactile experience,
ዘይቤያዊ ቃላት፡-
ጠቃሽ ዘይቤ
ታሪክ ጠቃሽ
ስነጽሁፍ ጠቃሽ
መጽሃፍ ቅዱስ ጠቃሽ
Figurative language
-Allusion
For an allusion:-a reference some thing in;
-History
-previous literature
-biblical allusion.
እውነት ለመናገር አቶ ብርሃኑ መጽሃፍ ውስጥ ያሉትንና ከፔሬኔ መጽሃፍ ጋር የሚገናኙትን ጽሁፎች ከመጠቆም ይልቅ ለአንባቢ ራሱ እንዲፈትሸው መተው የሚሻል ይመስለኛል፡፡ አንባቢ ድንገት መጽሃፉ ቢያጋጥመው ዱካ ለማጥፋት ይመስላል አንዳንድ የቦታና የቅርጽ ለውጥ ሊደረግላቸው የተሞከሩ ሃሳቦች አሉ፡፡ አቶ ብርሃኑ ከጥቂት አረፍተ ነገሮች ያልዘለሉ ሃሳቦችን (ለዚያውም ቁብ የሌላቸውን) ተውሻለሁ ብለው የኤስ ኤች በርተንን መጽሃፍ ዋቢ መጽሃፍት ተርታ ሲያስቀምጡ ለምን የፔሬኔን ሙሉ መጽሃፍ ተውት አይ ኤ ሪቻርድን ሲጠቅሱስ እንዴት ሙሉ ሃሳብ የገለበጡበትን መፅሃፍ ይዘነጉታል እኔ በግሌ ይህን ነገር ፈጽሞ ባላይና ባልሰማ ደስ ባለኝ ነበር፤ግን ምን ይደረግ…እውነት - እውነት ነው!! ሌሎች መንገዱን እንዳይለምዱት ይህንን መንገድ በእሾህ ማጠር ግድ ይላል፡፡
አሁንም ወደ ዜማ፣ምትና ቤት አመታት እንምጣና በቀጥታ የተወሰዱትን እንይ፤
An essential element in all music is repetition ,in fact ,we might say that all art consists of giving structure to two elements; repetition and variation. All things we enjoy greatly and lastingly, indeed have these two elements. we enjoy the sea endlessly because it is always the same, yet always different …Our love of art, then, is rooted in human psychology .
We are familiar, we like variety, but we combined them if we get too much sameness, the result is bewilderment and confusion.
ለማንኛውም ሙዚቃዊ ዜማ መሰረቱ ድግግሞሽ ነው፡፤በመሰረቱ ማንኛውም ዓይነት ኪን ሁለት ከሁለት አላባዊያን ጥምረት መዋቅራዊ ስርዓትን ያበጃል፤ ከድግግሞሽና ከልዩነት፡፡ በህይወታችን በእጅጉ የምንደሰትባቸው ነገሮች ድግግሞሽና ልዩነት ቅንጅቶች ናቸው፡፡ ጨረቃን የምንማረክባት ሁልጊዜ ያው በመሆኗ እንደገናም ሁልጊዜ አዲስና ብርቅ በመሆኗ ነው፤ለኪነጥበብ ያለን ፍቅር በእጅጉ ስነልቡናዊ ነው፡፡ ሰዎች ሁሉ የለመድነውንና የምናውቀውን ነገር እንወዳለን፤ሰዎች ስንባል ለየት ያለና ብርቅዬ ነገር እንወዳለን፤እንዲሁም ሰዎች ስንባል የነባር አዲስ እንወዳለን፤የሁለቱን ቅልቅል፡፡ የምናውቀውና የለመድነው ነገር እጅ እጅ ይለናል፤ይሰለቸናል፡፡ ወዲያው ወዲያው የሚቀያየሩ ልዩ ልዩ ነገሮች፣ወይም የማይመሳሰሉና ፍጹም እንግዳና አዲስ ነገሮች ሲበዙ ደግሞ ግር ይለናል፤ግራ እንጋባለን፡፡
ከላይ የተቀመጡት የአቶ ብርሃኑና የፔሬኒ አንቀጾች ተመሳሳይ ናቸው፡፡ ልዩነታቸው ፔሬኒ “ባህር”ያሉትን አቶ ብርሃኑ “ጨረቃ” ማለታቸው ብቻ ነው፡፡ ለመሆኑ አቶ ብርሃኑ የመጽሐፋቸውን መዋቅር፣እንዲሁም አብዛኞቹን መግቢያና ማብራሪያ፣ እንዲሁም አጠቃላይ መዋቅር የወሰዱባቸውን ደራሲ መጽሃፍ ጭራሽ ያልጠቀሱት ለምን ይሆን ለሚለው ጥያቄ መልስ ላገኝለት አልቻልኩም፡፡ ይሁን እንጂ በአማርኛ ስነጽሁፍ ያደረጉት ጥናት በእጅጉ የሚደነቅ ነው፤ሳያነብቡ ኦና መጽሃፍ ከሚያሳትሙ ሰነፎች የአቶ ብርሃኑ ከመጽሃፍት የቃረሙትን ዕውቀት ማካፈል ይመረጥ ነበር፤ግን ደግሞ ከአንድ መጽሃፍ ወረሱ እንጂ ብዙ መጽሃፍት አልዳሰሱም፡፡ ይሁንና በማንበባችን አንጎዳም፤ እንጠቀማለን፡፡ መጠየቃችን ግን አይቀርም፡፡ ለፔሬኔ ለምን የባለቤትነት ዋጋ ከለከሉ ለምንስ ይሆን የሃገራቸውን አንባቢ ሊደርስበት አይችልም ብለው የናቁት? የሆኖ ሆኖ ዓላማዬ ሙት ወቃሽ መሆንና አሪፍ የሰሩትን ምሁር ማጣጣል ሳይሆን እውነቱን ገልጦ ሌላው ከእሳቸው ስህተት እንዲማር ማድረግ ብቻ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ከዩኒቨርስቲ ምሁራኖቻችን ፕላጃሪዝምን ማበረታታት ፈጽሞ አንጠብቅም፡፡ እባካችሁ አንባቢን እናክብር እያልኩ ፅሁፌን እቋጫለሁ፡፡

Read 9616 times