ይኸው ዳግም ተጠርቼ፣
ልቤ ልብህ ውስጥ ተገኘ፡፡
መስቀሌ ብዙ ነው
በመስቀል ብዛት፣
ጌታ እበልጥሃለሁ፡፡
ዕረፍትን አላውቅም፡፡
እስከ ዕውቀቴ ድረስ፣
ዕድሜዬን በሙሉ፣
ተንጠልጥዬ አለሁ፡፡
እንዳንተ ደፍሬ፣
መሞት እያቃተኝ፣
ጐልጐታዬ በዝቶ፣
ሁሌ እሰቀላለሁ፡፡
ነፍሴን አልሰጥ ብዬ፣
እንዳልኖር ቁስሉ፣
እንዳልሞት ድፍረቱ፣
ደስታ እያናጠቡኝ፣
የታመመ ኑሮ፣
ሠርክ እቀጥላለሁ፡፡
መኻልነት ለምዶኝ፣
ሳልደፍር ሳልፈራ፣
ሳይዘልቀኝ ሚስማሩ፣
ትንሣኤ ከየት ይምጣ?
ፈርሠው ካልተሠሩ!
ፍቅር ፈቀደ
ቀሰቀስከኝ ተቀሰቀስሁ
ይኸው ነቃሁ እንደ ልምዴ፡፡
ለካ እኔ ሁሌም ተኚ ነኝ!
ንቃት አልለመደም ልቤ፡፡
ትዝታህን በትራሴ፣ ለመኝታ ተደግፌ፣
ሳልነቃ እንደ ረፈደ፣
ንጋቴ ከእጄ ቢያመልጥም፣
ትራሴ ተነቃነቀ፡፡
Published in
የግጥም ጥግ