Saturday, 29 December 2012 09:16

“ዶፍ ዝናብ ከሚወርድባቸው ይልቅ የሞቱት የተባረኩ ናቸው” የሃፍቶም የጅቡቲ በር መከራና ስቃይ!

Written by  አልአዛር ኬ.
Rate this item
(3 votes)

ካለፈው የቀጠለ
ሃፍቶም ግደይ ከፊት ለፊቱ የተዘረጋው ከተማ ጅቡቲ መሆኑን ሲያውቅ፣ ወደዚህ ለመምጣት የደከመው ድካምና የከፈለው መስዋዕትነት ሁሉ ባንዴ እንደ ጉም ተኖ ተረሳው፡፡ ልቡንና ቀልቡን ሰቅዞ የያዘው፤ ለወራት የቀንና የሌሊት ቅዠትና ህልም ሆናበት ወደ ከረመችው ጅቡቲ የመግባት አጣዳፊ ስሜት ብቻ ነበር፡፡ ተንጠላጥሎበት የነበረው የጭነት መኪና መፈተሽ ሲጀምር፣ እሱም የመኪናው አሽከርካሪና ረዳት ቀድመው ሳያዩት በፊት፣ ተሽቀዳድሞ ከመኪናው ላይ ዘሎ ወረደ፡፡ በጥድፊያ ተወጥሮ ስለነበር እግሩ የት ላይ እንዳረፈ እንኳ በወጉ አላየውም፡፡ ብቻ እግሩ መሬት እንደነካ ሱሪውንና ካናቴራውን በከፊል ያለበሰውን አቧራ አጐንብሶ አራገፈና ቀና ሲል፣ ከፊት ለፊቱ ከቆመና በመርማሪ ጥቃቅን አይኖቹ ትኩር አድርጐ ከሚያየው አንድ ቀጭን ረጅም ሰውዬ ጋር ፊት ለፊት ተገጣጠሙ፡፡

ሰውየው ቡናማና ግራጫ ቀለም ያለው የወታደሮች ሬንጀር ልብስ ለብሶ፣ ነጠላ ጫማ አድርጓል፡፡ በግራ ትከሻው ክላሽንኮቭ ጠመንጃ አንግቷል፡፡ የለበሰው ሬንጀር ሸሚዝ ከጉልበቱ በታች መርዘሙና የሱሪውም ያለመጠን ሰፍቶት መንጀላጀሉ፣የወንድነትና የወታደርነት ሞገሱን ጨርሶ ነጥቆታል፡፡ ከታጠቀው ጠመንጃ በቀር ወታደር የሚያስመስል አንዳችም ነገር የለውም፡፡ ይሁን እንጂ ሰውየው የእለቱን ስራውን በከተማው የመግቢያ ኬላ ላይ በማከናወን ላይ የነበረ የጅቡቲ የፖሊስ ሠራዊት አባል ነው፡፡ 
ፖሊሱ ሀፍቶም የጭነት መኪናው ረዳት እንደሆነ ፍፁም ሳይጠራጠር በጠራ አማርኛ “ሰላም” ካለው በኋላ፣ የሶማሊኛና የፈረንሳይኛን ቋንቋ እያፈራረቀ ወደ ጅቡቲ የሚገቡ ሁሉም አሽከርካሪዎችና ረዳቶቻቸው የሚይዙትን መታወቂያና የመግቢያ ፈቃዱን እንዲያሳየው ጠየቀው፡፡ ሀፍቶም ግን ፖሊሱ ምን እያለው እንደሆነ አልገባውም። ያኔ እንኳን በማያውቀውና ጨርሶም በማይገባው ቋንቋ አናግረውት ይቅርና፣ አፉን በፈታበት በትግርኛ ቋንቋ ቢያነጋግሩትም የሚሰማበት ጆሮ አልነበረውም። ልቡ እንደተሰቀለው ሁሉ ጆሮውም ኬላውን በፍጥነት በማለፍ ወደ ጅቡቲ ለመግባት ያለመጠን በመጣደፉ፣ የማዳመጡን ስራውን ትቶት ነበር፡፡ እናም ፖሊሱ ላቀረበለት ጥያቄ ምንም አይነት መልስ ሳይሰጥ “ተወኝ ልሂድበት” በሚል አይነት እንዲያሳልፈው በእጁ ትንሽ ወደ ጐን ገፋ አደረገውና፣ ሩጫ በቃጣው ፈጣን እርምጃ አልፎት ለመሄድ ሞከረ፡፡ ይሁን እንጂ ገና እግሮቹ ሁለት እርምጃ እንኳ ሳይራመዱ፣ ፖሊሱ የጃኬቱን የግራ ጐን ኮሌታ ጨምድዶ በመያዝ አስቆመው፡፡ ፖሊሱ ሀፍቶም የአሽከርካሪው ረዳት እንዳልሆነ ተጠራጠረና በቀኝ እጁ ጨምድዶ የያዘውን የሃፍቶምን የጃኬት ኮሌታ ይበልጥ አጥብቆ እየያዘና በግራ ትከሻው ያነገተውን ክላሽንኮቭ ጠመንጃ አውርዶ በመያዝ፣ እየጐተተ ወደ አስፓልት ጠርዝ አወጣውና፣ አሁንም በሶማሊኛና በፈረንሳይኛ ቋንቋ እያፈራረቀ “ረዳት ነህ ወይስ ምንድን ነህ? እስኪ መታወቂያህን አሳየኝ?” እያለ በተደጋጋሚ ጠየቀው፡፡ ሃፍቶም ግን በተደናገረ ስሜት ፖሊሱን አተኩሮ ከማየት በስተቀር ለተጠየቀው ጥያቄ መልስ መመለስ አልቻለም። ፖሊሱ መጠየቁን አላቋረጠም፡፡ “ረዳት ነህ?” ሀፍቶም አሁንም አልመለሰም። የጭንቀት ላብ የራሱን ቦይ እየሠራ በግንባሩ ይወርዳል፡፡
ጅቡቲ ለመግባት በዚያ ሐሩር ፀሐይ በእግሩ የተጓዘውና የደከመው ድካም ሁሉ ሲሠናከልበት ታየውና፣ ልቡ በጭንቀት ሊፈርስ የደረሰ መሰለው። ወዲያውኑም ማጅራቱን አንቆ ይዞ በጥያቄ የሚያጣድፈውን የጅቡቲ ፖሊስ አንጀት በሚበላ ድምጽ “እባክህ የእኔ ጌታ፣ ወንድማለም ጅቡቲ ያልፍልኛል ብዬ አገሬን ጥዬ የተሰደድኩ ድሃ ነኝ! እባክህን ልቀቀኝ። ጅቡቲ ልግባ!” እያለ ተማፀነው፡፡ አሁን ንግግሩን ያለመረዳትና መልስ ለመስጠት የመቸገሩ ተራ የፖሊሱ ሆነ፡፡ ነገር ግን ፖሊሱ ሃፍቶም የተናገረው ነገር ሁሉ እንዳልገባውና ይልቁንስ ዝም ብሎ ከመቀባጠር ይልቅ በጠየቀው መሠረት፣መታወቂያውንና የመግቢያ ፈቃዱን እንዲያሳየው በሶማሊኛና በፈረንሳይኛ መናገሩን አላቆመም ነበር፡፡
አስቸጋሪ ሁኔታዎች አስቸጋሪ ውሳኔዎችን ይጋብዛሉ፡፡ ሀፍቶም የገጠመውና የገባበት ሁኔታ በቀላሉ የሚወጣው እንዳልሆነ በሚገባ ተረዳው፡፡ አዕምሮው ከገባበት አስቸጋሪ ሁኔታ ሊወጣ የሚችልበትን ዘዴ በዚያች አጭር ጊዜ ለማውጠንጠን ቢሞክርም ብልጭ ያለለት ነገር አልነበረም፡፡ ድንገት ግን ያሰበውና ያለመው ሁሉ እንዳልነበረ ሆኖ እግሩ ስር ሲንኮታኮት በድጋሚ ታየውና፣ እንደውሃ በሚቆጠር ከፍተኛ የጭንቀት ትኩስ ላብ ተጠምቆ የነበረው መላ ሰውነቱ ሲቀዘቅዝ ተሰማው። ወዲያውኑም ያለ የሌለ ሃይሉን አሰባስቦ የጃኬቱን ኮሌታ ጨምድዶ የያዘውን ፖሊስ እጅ፣ በቀኝ እጁ ቡጢ መትቶ በማስለቀቅ ወደፊቱ በሩጫ ተፈተለከ፡፡
ያለመጠን የሰፋና የረዘመ የሬንጀር ልብስ ለብሶ የተንጀላጀለ የመሰለውና ቀጫጫው ፖሊስ ግን በዚያው ቅጽበት አስደናቂ ድርጊት ፈፀመ፡፡ ከጠቅላላ አቋሙ አንፃር ሲታይ ሊያደርገው ይችላል ተብሎ በማይገመት ሁኔታና እጅግ በሚያስደንቅ ፍጥነት ተፈናጥሮ በመሮጥና ከየትኛው ኪሱ እንዳወጣው ያልታወቀ ከፕላስቲክ የተሠራ፣መጠነኛ ውፍረት ያለው የተጠቀለለ ገመድ በማውጣት፣ከመቅጽበት ጥቅልሉን ፈትቶ እንደ ወንጭፍ በማሽከርከር የሃፍቶምን እግር ጠለፈው፡፡ ሀፍቶም እግሮቹ ተጠላልፈው አስፓልቱ ላይ ተጠቅልሎ ወደቀ፡፡
ከዚህ በኋላ ያለው ታሪክ ለመተረክ ደስ የሚል አይደለም፡፡ ፖሊሱ ሃፍቶምን አስፓልቱ ላይ እንደወደቀ እስኪበቃው ድረስ በእግሩ ረገጠው፡፡ ሁኔታውን ያዩና የጭነት መኪኖቻቸውን አቁመው የፍተሻ ተራቸውን ሲጠባበቁ የነበሩ ኢትዮጵያውያን አሽከርካሪዎችና ረዳቶቻቸው ሲከቧቸው፣ ፖሊሱ ሃፍቶምን መርገጡን አቆመና ማጅራቱን አንቆ ከወደቀበት አስነሳው። ከአሽከርካሪዎቹና ከረዳቶቹ የተወሰኑት አንዳቸው ባንዳቸው ላይ እየደራረቡ “ምንድነው አንተ? ምን አድርገህ ነው?” በማለት በጥያቄ አፋጠጡት፡፡ “ዋ! ዝም ብሎ እሱ ዋ! ባካችሁን ለኔ አስለቅቁኝ! እኔ ምስኪን ደሀ ነኝ!” ሀፍቶም ተማፀናቸው፡፡
የተወሰኑት አሽከርካሪዎችና ረዳቶቻቸው ሀፍቶም ምን አድርጐ እንደሆነ የያዘውን ፖሊስ እያነጋገሩት ሳለ፣ አንድ ከሁሉም ነገሩ ይልቅ ከደረቱ ላይ የተንጠለጠለ የሚመስለው ትልቅ ቦርጩ ጐልቶ የሚታይ አሽከርካሪ፣ ሀፍቶምን ከየት እንደመጣና ምን እንደሚሠራ ጠየቀው። ሀፍቶም ምንም ስራ እንደሌለውና ያልፍልኛል በሚል ከአዲስ አበባ ተነስቶ ግማሹን በእግሩ የቀረውን እየለመነና የጭነት መኪና ላይ በመንጠላጠል እዚህ እንደደረሰ ነገረው፡፡ አሽከርካሪው ደገመና፣በየትኛው የጭነት መኪና ተሳፍሮ እንደመጣ ሀፍቶምን ጠየቀው፡፡ ሀፍቶም በጣቱ አሳየው፡፡ አሽከርካሪው በመገረም “ይሄ እኮ የእኔ መኪና ነው፡፡ እኔ ደግሞ አልጫንኩህም” አለውና ዘወር ብሎ ረዳቱን “ተመስገን ጭነኸዋል እንዴ?” ብሎ ጠየቀው። ረዳቱ የተጠየቀውን ከመመለሱ በፊት ግን ሀፍቶም አሽከርካሪውም ሆነ ረዳቱ ሳያዩት በጭነት መኪናው የኋላ ክፍል ላይ ተንጠላጥሎ እዚህ ድረስ እንደመጣ በፍፁም ገራገርነት መለሠ፡፡ አሽከርካሪውም በመገረም ጭንቅላቱን እየነቀነቀና የቀኝ እጁን ሌባ ጣት ሀፍቶም ላይ እያወዛወዘ “ይሄ አዲስ አበባን ያሠለቸ ሌባ ሳይሆን አይቀርም” አለው፡፡
ሀፍቶም ከጅቡቲው ፖሊስ እርግጫ ይልቅ የዚህ ኢትዮጵያዊ አነጋገር የበለጠ ዘልቆ ተሠማው፡፡ እናም ኮስተር ብሎ “ክላ! ዙም ብሎ ለይባ ይላላ እንዴ ለእኔ? አነስ ድሀ ነይ እንጂ ለይባ አይደለሁም፡፡ ንሰብ ማንነትስ ሳታውቅ ዝም ኢልካ አይትዛረብ” በማለት መለሰለት፡፡ እልህ ጉሮሮውን እየተናነቀው አይኖቹም እንባ አቅርረው ነበር፡፡ አሽከርካሪውና ሀፍቶም በዚህ አይነት ሁኔታ እየተመላለሱ ባሉበት ወቅት የጃኬቱን ኮሌታ ጨምድዶ ይዞት የነበረው ፖሊስ፣ ጃኬቱን ለቀቀና ድንገት ሳያስበው ሀፍቶምን ፊቱ ላይ ሀይለኛ ጥፊ ደረገመበት፡፡
ሀፍቶም ለአፍታ ያህል ሰማይ ምድሩ ዞረበትና እይታው ሲጠራለት፣ በአንዱ እጁ ግማሽ ፊቱን ከልሎ በመያዝና ባልተከለለው በኩል የመታውን ፖሊስ አጋድሞ እያየ “እዋይ! አታ! ሱቅ ኢልካ ትፀፍኧኒ?” እንታይ ኢዲኡ?” (አንተ ዝም ብለህ ትማታለህ እንዴ? እንደማለት) አለው፡፡ የፖሊሱ መልስ ግን ቀላልና ፈጣን ነበር፡፡ እንደገና በሙሉ እጁ ፊቱ ላይ በጥፊ ደረገመው፡፡ በዚያው ቅጽበትም ወፍራም ደም ከሀፍቶም አፍንጫ ዠረር ብሎ መፍሰስ ጀመረ፡፡
ሀፍቶም ባፍንጫው የሚንዠቀዠቀውን ደሙን በእጁ ጠረገና አየው፡፡ ወዲያው ሁሉም ነገር ጥቁር ደመና የለበሰ መሰለው፡፡ ወዲያውኑም “ወዲዛ ለማኒት” አለና የቀኝ እጁን ቡጢ ጨብጦ የእውር ድንብር አይነት ፖሊሱ ላይ በመሰንዘር፣ እስኪያስለው ድረስ ደረቱን ደለቀው፡፡
ፖሊሱ የተሰነዘረበትን ሀይለኛ ምት እንደምንም ተቀብሎ፣አንዳች አይነት የአፀፋ እርምጃ ሳይወስድ የሀፍቶምን የቀኝ እጅ በጀርባው በኩል አጥፎና ጠምዝዞ ከያዘው በኋላ፣ የፖሊሶች የጥበቃ ማማ ወዳለበት ቦታ እየገፈተረ ይዞት ሄደ፡፡ እዚያ እንደደረሱም ከአንድ ሌላ የፖሊስ ባልደረባው ጋር በመተባበር ሃፍቶምን እንዳይሞት እንዳይሽር አድርገው ለሰአታት ቀጠቀጡት፡፡ ድብደባቸውን ያቆሙትም ሀፍቶም ራሱን ሲስት የሞተ ስለመሠላቸው ነበር፡፡ ተቀያሪ ፖሊሶች ከመምጣታቸው በፊት ከጥበቃ ማማው ትንሽ ራቅ አድርገው ጥለውት የሄዱትም ገና ራሱን በደንብ ከማወቁ በፊት ነበር፡፡
ሀፍቶም የተሠበረ አፍንጫው አብጦ መተንፈስ ከልክሎት፣ በአፉ እያለከለከና በድብደባ ብዛት ድቅቅ ያሉት እግሮቹ፣እጆቹና የጐድን አጥንቶቹ ክፉኛ እያንሰፈሰፉት ከወደቀበት ሳይነሳ ሁለት ቀናት አሳለፈ፡፡ በሶስተኛው ቀን ረሃብና በተለይ ደግሞ ውሃ ጥሙ ክፉኛ ሲያንገበግቡት በስንት ትግልና ጣር ከወደቀበት በመነሳት፣ ከመንፏቀቅ ባልተለየ ሁኔታ እግሩ ወደመራው አቅጣጫ መንኳተት ጀመረ፡፡ በዚህ ሁኔታ ላይ እያለ መጀመሪያ ያጋጠመው ሰው ተራ የጅቡቲ ነዋሪ ሳይሆን ሌላ የጅቡቲ ፖሊስ ነበር። ይሄኛው ፖሊስ ሃፍቶምን እንዳገኘው በቋንቋ በቀጥታ መግባባት ባይችሉም ምን አይነት አደጋ እንደደረሰበት በምልክት ጠየቀው፡፡ ሀፍቶምም ከሚያሰቃየው ህመም ጋር በብርቱ እየታገለ፣በፖሊሶች መደብደቡንና በረሃብና በጥም እየተሰቃየ እንደሆነ በምልክት ለማስረዳት ሞከረ። ፖሊሱም ሀፍቶምን እንዲጠብቀው ነግሮት በመጣበት አቅጣጫ ተመልሶ፣ ከትንሽ ቆይታ በኋላ በስስ ፌስታል ሩዝና በአሮጌ የፕላስቲክ ጣሳ ውሃ ይዞለት በመምጣት እንዲበላ ካቀረበለት በኋላ ጥሎት ሄደ። ፖሊሱ ሲሄድ ግን ባዶ እጁን አልነበረም፣የሀፍቶምን ኪስ እየገለበጠ ፈትሾ ምንም ነገር ሲያጣ፣ ጫማውን በማውለቅና ኮምቦልቻ የቀን ስራ ሲሰራ በሁለት ብር ሎተሪ የደረሰውን ሴኮ የእጅ ሰአቱን ፈትቶ በመውሰድ ነበር፡፡
የሚንሳጠጥ በር እድሜው ረዥምና ቻይም ነው። ሃፍቶም ደግሞ የሚንሳጠጥ በር ነበር፡፡ ከአድማሱ ማዶ ያለውን ሰማያዊ ሰማይ አሻግሮ እያየ የተሰጠውን ሁሉ ችሎ የሚኖር ፍጥረት! ጅቡቲ ያጋጠመው ህይወት ከዚህ በፊት ካሳለፈው ሁሉ የከፋ ቢሆንበትም ቀጣዩ ቀን የተሻለ እንደሚሆንለት ተስፋ እያደረገ፣ ያልተፈለፈሉት ጫጩቶቹን በሃሳቡ እየሳለና በምኞቱ መዝገብ ላይ እየቆጠረ፣ለአንድ ዓመት ከሶስት ወር ያህል ጊዜ ጅቡቲ ውስጥ ተቀመጠ፡፡
የውሃ ነጠብጣብ የማታ ማታ ጥቁር አለት ይፈረክሳል፡፡ ሃፍቶምም ጅቡቲ ያልመው እንደነበረው ሰርቶ የሚከብርባት አሊያም ወደ ሳኡዲ አረቢያ የሚሸጋገርባት ከተማ ጨርሶ እንዳልሆነች የተረዳው ከዚህ ጊዜ በኋላ ነበር፡፡ ሃፍቶም ጅቡቲ ውስጥ ባሳለፈው ጊዜ ጫካ ውስጥ ካሉት ሁለት ጅግራዎች ይልቅ በእጅ የተያዘችው አንዲት ወፍ የበለጠ ዋጋ እንዳላት መረዳት ችሏል፡፡ ተስፋ ግን ሁሌም ተስፋ ነው፣ ህይወትን ይደግፋል፡፡ ህይወት እስካለ ጊዜ ድረስም ተስፋ ማድረግ ይቀጥላል፡፡ እናም ሃፍቶም ጅቡቲን ትቶ ሳኡዲ አረቢያን እንደአዲስ ህይወት ተስፋ ማድረግና ማለም ጀመረ። ሶማሊላንድንም የሳኡዲ አረቢያ መግቢያ ዋና በር አድርጎ መረጣት፡፡
(ይቀጥላል)

Read 3309 times