Saturday, 29 December 2012 09:14

ትሑቱ አገልጋይ ዶ/ር እንግዳ ዮሐንስ

Written by  በቴዎፍሎስ
Rate this item
(2 votes)

ድሮ ተፈሪ መኮንን ይባል በነበረው በዛሬው እንጦጦ ቴክኒክና ሙያ ት/ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ ወደ ት/ቤቱ ሲገቡ በሚታየው ሕንፃ ፊት ለፊት ባለው የዛፎች አፀድ ውስጥ አንድ ሐውልት ይገኛል። ሐውልቱ እዚያ ሄጄ ለመጐብኘት የቻልኩት አንድ በንጉሱ ጊዜ በታተመ መጽሐፍ ጠቋሚነት ነበር፡። በሐውልቱ ላይ በእንግሊዝኛና በአማርኛ እንደዚህ ተጽፏል:-
This monument was caused to be erected by Ato Yohannes Wolde Mariam in memory of his very dear son Dr.Engida Yohannes D.V.M Graduate of Cornell University, USA, Born on 14 August 1908 Died on 12 November 1944.
May He Rest in Peace.
የእንስሶች ወዳጅ

የቀንድ ከብትና የጋማ ከብት ሐኪም ለእንስሶች የሚራራ 
ለመሆኑ እኒህ ሐውልት የቆመላቸው ሰው ማን ነበሩ? ለምንስ ይህ ክብር ሊሰጣቸው ቻለ? ዶ/ር እንግዳ ዮሐንስ ከዶ/ር አለመወርቅ በየነ ጋር የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ የእንስሳት ሀኪም ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ የግብርናና የገጠር ልማት ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ጋር በመተባበር፤ ኢትዮጵያ ከደስታ በሽታ ነፃ መባሏን በማስመልከት ታህሳስ 22 ቀን 2002 ዓ.ም ካሳተማቸው አራት ቴምብሮች አንዱ እኒህን ሁለት ቀደምት ምሁራን ለመዘከር አውሎታል፡፡
በቴምብሩ ላይ የዶ/ር አለመወርቅ ፎቶ በጉልህ ይታያል፡፡ እኝህ ሰው ጥቁር አንበሳ የሚባለውን ፀረ ፋሽስት ሰራዊት በመምራት የታወቁ ስለነበሩ በአንፃራዊነት ይበልጥ ይታወቃሉ፡፡ ይኸው ፎቶግራፍም በባህሩ ዘውዴ የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ይገኛል፡፡ ወደ ዶ/ር እንግዳ ስንመጣ ግን ቴምብሩ ላይ ያለው ፎቶ እንጦጦ ት/ቤት የሚገኘው ሀውልት ላይ ያለው በመሆኑ ስለዚህ ሰው ብዙም የሚታወቅ ነገር እንደሌለ የሚጠቁም ይመስላል፡፡
በአንድ አጋጣሚ ደብረ ዘይት ከተማ በሚገኘው የእንስሳት ህክምና ዩኒቨርስቲ ሄጄ እኒህን ሀኪሞች የሚዘክር ነገር ወይም በስማቸው የተሰየመ ተቋም ወይም ሌላ ነገር እንዳለ ለመጠየቅ ብሞክርም ያናገርኳቸው ሰው ስማቸውንም እንኳን እንደማያውቁ ነው የነገሩኝ፡፡ እኚህ በሙያቸውና በፀረ ፋሽስት ትግላቸው የሚታወቁት ሁለት ሐኪሞች፤ ለጉዳዩ ቅርብ በሆኑ ተቋማት አለመታወቃቸው በጥቂቱ ቅር የሚያሰኝ በመሆኑ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አንድ ነገር እንዲያደርጉ በዚህ አጋጣሚ መጠቆሙ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ለጊዜው ግን ከሁለቱ የአንዱን ታሪክ ለመዘከር ያህል ስለ ዶ/ር እንግዳ ዮሐንስ ከተለያዩ ጥቂት ምንጮች የተሰባሰበ መረጃ ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡
ዶ/ር እንግዳ ዮሐንስ ነሐሴ 7 ቀን 1900 ዓ.ም አዲስ አበባ ውስጥ ተወለዱ፡፡ አባታቸው አቶ ዮሐንስ ወልደማሪያም በወቅቱ የስዊድን ሚስዮን ተብሎ ይጠራ በነበረ ትምህርት ቤት የእንግሊዝኛ አስተማሪ ሲሆኑ በጊዜው ዘመናዊ ትምህርት ከነበራቸው ጥቂት ሰዎች አንዱ ነበሩ፡፡ የተለያዩ የትምህርትና የታሪክ ጽሑፎችን በማዘጋጀት በወቅቱ በነበረው የምሁራን እንቅስቃሴ ጉልህ ድርሻም ነበራቸውም።
መርስዔ ኃዘን ወልደቂርቆስ “ትዝታዬ ስለራሴ የማስታውሰው” (1981-1923) በተባለው መጽሐፋቸው እንደሚዘክሩት፤ አስተማሪያቸው የኔታ ወልደ ጊዮርጊስ ጥበብን ለመቅሰም የማይቦዝኑ ትጉህ ሰው ስለነበሩ፤ የዕድሜያቸው መግፋት ሳይገድባቸው በ64 ዓመታቸው ከ አቶ ዮሐንስ ዘንድ እንግሊዝኛ ለመማር ሲያመላልሷቸው ያስከትሏቸው ነበር፡፡ የኔታ የዮሐንስ ወንጌልን በእንግሊዝኛ እያነበቡ ቋንቋውን ሲለማመዱ ያዩት ብላታ መርስዔ ኃዘን፤ ይህ ትምህርት ለምን ይረባል? ብለው ቢጠይቋቸው ብዙ ጥበብ የተፃፈበት ቋንቋ ስለሆነ ለብዙ ነገር ይጠቅማል፤ በመንፈሳዊም ብዙ መጽሐፍት ተጽፈውበታል ብለው ይመልሱላቸዋል፡፡ ከዚያም ከግዕዝ ትምህርት በቀር ሌላ ጠቃሚ ትምህርት ይገኛል የሚል አሳብ አልነበረኝምና ከየኔታ የሰማሁት ቃል አስገርሞኝ ፊደሉን ተመለከትኩት፡፡ ቀጥሎም ገና ጀማሪዎች የነበሩትን የአቶ ዮሐንስን ልጆች እንግዳና ገብረእግዚአሔርን እየጠየቅኩኝ ፊደሉን አጠናሁት ይላሉ (ገፅ 129)፡፡
አቶ ዮሐንስ፣ ገብረ እግዚአብሔር የተባለውን ልጃቸውን በህዳር በሽታ ሲነጠቁ እንግዳ ግን ተርፎላቸው በተፈሪ መኮንን ተማሪ ቤት እንግሊዝኛ፤ ፈረንሳይኛ፣ ታሪክ፣ ሒሳብ፣ ጆግራፊና ስነፍጥረት ተምሮ ሲጨርስ በንጉሠ ነገሥቱ ፈቃድ ወደ ቤይሩት ተላከ። በቤይሩት ሦስት ዓመት ተምሮ፣ ግብጽ ቪክቶሪያ ኮሌጅ ገባ፡፡ እዚያ አንድ ዓመት ከተማረ በኋላም ወደ እንግሊዝ በማቅናት ትምህርቱን እንዳስመሰከረ ዜና እረፍቱን የሚገልፀው የአዲስ ዘመን ጽሑፍ ይነግረናል። በመቀጠልም ወደ አሜሪካ በመሻገር በኮርኔል ዩኒቨርሲቲ በእንስሳት ህክምና ተመረቀ፡፡ በዚሁ ዩኒቨርስቲ ቆይታው ኮስሞፖሊታን በሚባል ማህበር በተማሪዎች ተመርጦ፣ ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆን ዘለግ ላለ ጊዜ አገለግሏል፡፡
የዕውቀቱን ብቃት በተግባር በማስመስከሩ በአሜሪካ አገር በነፃነት እንዲኖርና እንዲሰራ ፈቃድ ተሰጥቶትም ነበር፡፡
ዶ/ር እንግዳ ትምህርቱን በመቀጠል የሰው ሕክምና ለመማር እየተሰናዳ ሳለ፣ ጣሊያን ኢትዮጵያን የመውረሯ ዜና ስለተሰማ፣ ለአገሩ ነፃነት ለመታገል እዚያው አሜሪካ ሀገር ከሀዋርድ ዩኒቨርስቲ በህክምና ሙያ ከተመረቀው ከዶ/ር መልአኩ በያን ጋር በመሆን ወደ ኢትዮጵያ መጡ፡፡ እንደደረሰም ጦርነቱ ተፋፍሞ ነበርና ዶ/ር እንግዳ ከደጃች ነሲቡ ጋር ኡጋዴን ዘምቶ በቀይ መስቀል ማህበር ማገልግል ጀመረ፡፡ በዚያም በጦር ሜዳ የወደቁትን ቁስለኞች ወደ ደጋ ሀቡር በመኪና እያመላለሰ የበርካቶችን ህይወት ለማትረፍ ረድቷል፡፡ ከዘመቻው መልስ አዲስ አበባ ውስጥ፣ በታደሰ ዘወልዴና በሌሎች የተማሩ ኢትዮጵያዊያን ይመራ በነበረው የውስጥ አርበኞች ማህበር ተቀላቅሎ የመሪነት ድርሻውን ይወጣ ጀመር፡፡ ሆኖም በወቅቱ የተማሩ ኢትዮጵያዊያንን በዓይነቁራኛ ይከታተሉ የነበሩ ፋሽስቶች ውሎ አድሮ የጥርጣሬ ዓይናቸውን በርሱ ላይ መጣላቸው አልቀረም። ስለዚህም የጠላት ስለላና ምርመራ እረፍት ስለነሳው፣ ማንነቱን ለመሰወር ነጠላና የአቡጀዲ ሱሪ አሰፍቶ ራሱን አልባሌ በማስመሰል፣ ዶ/ር ላምቤ ተብሎ ይጠራ በነበረው ጉለሌ ሆስፒታል በላብራቶር ምርመራ መስራት ጀመረ፡፡
በጠላት የስለላ መረብ እንዳይገባም መኝታውም ምግቡም እዚያው ግቢ ውስጥ ሆኖ አንድ ክፍል ተሰጥቶት ነበር የሚሰራው፡፡ ይህም የሆነው ጥብቅ ወዳጁ በሆነው ስዊዲናዊ ሚስዮናዊ ሐኪም ሚ/ር ንስትሮም ትብብር ነበር፡፡ ዶ/ር እንግዳም በህቡዕ ከሚንቀሳቀሰው ማህበር ጋር ሆኖ በዱር የሚዋደቁትን አርበኞች ይረዳ ነበርና በተቋሙ መሥራቱ የፈጠረለትን አጋጣሚ በመጠቀም፣ ለሆስፒታሉ ዲሬክተር ዶ/ር ክራመር ከሆስፒታሉ የመድሃኒት ክምችት ለአርበኞች በሚስጥር ቢላክ ፈቃደኛ ይሆኑ እንደሆነ ይጠይቃቸዋል። እርሳቸውም በጥንቃቄ ይደረግ እንጂ እንደማይቃወሙ በመግለፃቸው በየዓይነቱ መድሀኒት እየመረጠ ማከማቸት ጀመረ፡፡
ታደሰ ዘወልዴ “የአባላሽኝ ዘመን በተባለ መጽሐፋቸው “በልዩ ልዩ ጊዜ የተወሰደው መድሃኒት ዋጋ ቢታሰብ በዚያን ጊዜ የኛ ዐቅም በገንዘብ ሊገዛው አይችልም ነበር፡፡ ”ይላሉ (ገፅ 45)፡፡ ህቡእ ማህበሩን ይረዱ የነበሩት ሌላው ኢትዮጵያዊ ሐጂ የሱፍ አቡበከርም በሳጥን የተዘጋጀውን መድሃኒት በራሳቸው መኪና ከሆስፒታሉ ያለምንም ፍርሃት ወደ ተፈለገበት ቦታ ያደርሱ እንደነበር ፀሃፊው ያስታውሳሉ። ዶ/ር እንግዳ መድሃኒት ከማሰባሰብም ባሻገር በውጪ አገር ጋዜጦች ስለ ኢትዮጵያ ከሚፃፉት ፅሁፎች ውስጥ ጠቃሚዎቹን እየመረጠ፣ ለአርበኞች እንዲደርስ ያደርግ ነበር፡፡ በተጨማሪም ማህበሩን በማማከርና የፖለቲካ አመራር በመስጠትም ጉልህ ሚና ተጫውቷል፡፡
ይሁንና የእነዚህ ህቡእ እንቅስቃሴዎቹ ወሬ ስለተሰማና ስለተደረሰበት ፋሽስቶች ሊይዙት እንደተዘጋጁ ሲረዳ፣ በዚያ ተሸሽጐ መቆየቱ ለስዊዲናዊው አደጋ ሊያስከትል የሚችል ሆኖ በመገኘቱ፣ ወደ ባላገር ሄዶ መደበቅ ግድ ሆነበት። በዚያው በተሸሸገበት ቦታ ሆኖም ከአርበኞች ጋር እየተላላከ አንዳንድ ሚስጥራዊ ስራ ያከናውን ነበር፡፡
ነፃነትን ለማስመለስ የእንግሊዝ ሠራዊት አዲስ አበባ በገባ እለት በአሜሪካዊያን ወዳጆቹ ጥያቄ በባላገር ከተደበቀበት ወጥቶ ለተቀረው አለም በሬዲዮ አጭር መልእክት እንዲያስተላልፍ ተጋበዘ፡፡ እርሱም “ስለሰው ልጆች ነፃነት የሚደረገው ትግል በጣም ያስደስታል። እኔ እንኳን ዛሬ ከተደበቅኩበት ጥሻ ወጥቼ ድምፄን ለማሰማት በመቻሌ ስለነፃነት ሲሉ ለሚዋጉት ሁሉ ምስጋናዬን አቀርባለሁ” ሲል ደስታውን ገልጿል፡፡
ከነፃነት በኋላ የኢትዮጵያ መንግስት ከ1934 ዓ.ም ጀምሮ የደስታ በሽታን ለመቆጣጠርና ለማጥፋት ልዩ ትኩረት በመስጠት የክትባት ሥራ እንዲሰራ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ነበር፡፡ ስለሆነም በጉለሌ የነበረው የእንስሳት ሕክምና ድርጅት ሥራ በዶ/ር እንግዳና እንግሊዝ አገር በእንስሳት ሕክምና ተመርቆ በመጣውና ጥቁር አንበሳ የተባለውን የአርበኞችን ግንባር በመምራትና በማስተባበር የታወቀውን ዶ/ር አለመወርቅ በየነ እንዲመራ አደረገ፡፡ ዶ/ር እንግዳ በእርሻ ሚንስቴር የቀንድ ከብትን የበግ፤ የፍየል፤ የዶሮ፤ የንብ ርቢ ብልሃትን ለሕዝብ በማስተማር በመስራት ላይ እያለ ነበር በሳንባ በሽታ የተያዘው፡፡ በዚህም ወቅት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ወደ ካርቱም ሄዶ የቀዶ ጥገና ህክምና እንዲደረግለት ከላኩት በኋላ፣ ሥራውን ለተወሰነ ጊዜ ለመቀጠል ችሎ ነበር፡፡ አየር ለመለወጥ ሐረር ሄዶ እንዲቆይ ቢደረግም ብዙም ስላልተሻለው ወደ አዲስ አበባ ተመለሰ። ከተመለሰም በኋላ ንጉሠ ነገሥቱ በሳህለስላሴ ቪላ ገብቶ እንዲታመም በማድረግ እየተመላለሱ ይጠይቁት ነበር፡፡ ሆኖም ሕመሙ ስለጠናበት በተወለደ በ36 አመቱ ህዳር 3 ቀን 1937 ዓ.ም አረፈ፡፡
በዜና እረፍቱ እንደተዘገበው “በዚህ ቀን የወጣቱና የተወዳጁ የእንግዳ ዮሐንስ ሞት በተሰማ ጊዜ፣ እንኳን የሚያውቋቸው የማያውቋቸውም ሰው ታላቅ የሀገር ጉዳት መሆኑን በማሰብ ያላዘነ አይገኝም፤ መሳፍንትና መኳንንት ባሉበት ወዳጅ ዘመድ ተሰብስቦ እያለቀሰላቸው በመናገሻ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን በታላቅ ክብር ተቀበሩ፡፡”
በዶክተሩ ሞት ሀዘናቸውን ከገለጡት አንዱ በግሪክ አገር ፍልስፍና ተምረው በወቅቱ በትምህርት ሚኒስትርና በጋዜጦች መምሪያ ይሰሩ የነበሩት ሰረቀብርሃን ገብረእግዚ “የኤርትራ ድምፅ” በተባለው ጋዜጣ የሚከተለውን ፅፈዋል፡- “ዶ/ር እንግዳ ዮሐንስ አይነተኛ ትምህርት ባላቸው በኢትዮጵያ ወጣቶች ሰልፍ ውስጥ በተለይ የሚታሰብ ከፍተኛ ትምህርት፣ የሥራ ችሎታ ያለው፣ የኢትዮጵያዊነቱ መንፈስ ከፍ ያለ፣ ሕይወቱን ላገር አገልግሎት የወሰነ ወጣት ነበር፡፡ በፃዲቅ አባቱ በአቶ ዮሐንስ ላይ የታዘዘው ፅዋ እጅግ መሪር ነው… ዶክተር እንግዳ ዮሐንስ የየዋህነት፣ የትህትና፣ የደግነት አብነት የነበረው ወዳጅ ጓደኛችን፤ ትህትናው ከእውቀቱ፤ እውቀቱ ከትህትናው በላይ የነበረው እንግዳ፤ ቅዱስ የነበረው ምግባሩን ዋጋ ለመቀበል በመላእክት ክንፍ ወደ እውነተኛው ህይወት አገር ተጉዟል፡፡ አቶ ዮሐንስ ኃዘንዎ ኃዘናችን የኢትዮጵያ ኃዘን ነው” (ህዳር 9 ቀን 1937)
ዶ/ር እንግዳ በባህሪውና በሙያው ምን ያህል የተወደደና የተከበረ እንደነበረ ለማሳየት በሀውልቱ ላይ የሰፈረውን የሚከተለውን ፅሁፍ በማቅረብ ይህን አጭር ታሪክ እቋጫለሁ፡-
“በተፈጥሮ ባህሪውና በትምህርቱ፣ በስራውና በእድሉ በነበረበትም የባእድ አገር ለራሱና ለአገሩ መልካም ስም በማትረፍ ወዳጅ ያፈራ፤ አገሩን ንጉሠ ነገሥቱን፣ ወገኑን፣ ሠንደቅ ዓላማውን አፍቃሪና አክባሪ፣ ታዛዥና ራሱን አሳልፎ ሰጪ፣ ትሁት፣ ቅን፣ እውነተኛ፣ ቀጥተኛ፣ ሁልጊዜ ብሩህና ሰው አፍቃሪ፣ ቅናት ምቀኝነትና ተንኮል በጠባዩ የሌለው ዶ/ር እንግዳ ዮሐንስ፤ ለአገሩና ለመንግሥቱ ደንበኛ ስራውን በመፈፀም ከዚህ ዓለም በሞት ስለተለየ፣ ከአሜሪካን ወዳጆቹ ለተላከ መታሰቢያ ማኖሪያ ይሆን ዘንድ በአሳደጉትና በአስተማሩት፣ በአስታመሙትም ንጉሠ ነገሥቱ መልካም ፈቃድና ትእዛዝ የቆመ ሐውልት - የካቲት 17-1946”

Read 4223 times