Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 29 December 2012 08:54

“ኢህአዴጐች ቆልፈው ቁልፉን ይውጡታል” Featured

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

* በሰለጠነ አለም ውስጥ ብንሆንም በጨቋኝና ተጨቋኝ ስርአት ውስጥ ነን
* እኛ የምንለው በትክክል እንወዳደር ነው፤ ያንን ደግሞ ኢህአዴግ አልፈቀደውም
* አገሪቱ ውስጥ ትናንሽ አምባገነኖች እየተፈጠሩ ነው፤ ሲስተም መዘርጋት አለበት
ለበርካታ ዓመታት በተቃዋሚ ፓርቲ አመራርነት ያገለገሉት ዶ/ር ኃይሉ አርአያ፤ ከጤና ጋር በተያያዘ ምክንያት ከአንድነት ፓርቲ ሃላፊነታቸው የለቀቁት ከሳምንት በፊት ነበር፡፡ የፓርቲው አመራርም የእሳቸው ምክትል ሆኖ ሲሰራ የነበረውን አቶ ዳንኤል ተፈራን በቦታቸው ተተክቷል፡፡

በዚህም መሰረት በአሁኑ ሰዓት የ34 ዓመቱ ዳንኤል ተፈራ፤ የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ ሃላፊ በመሆን እየሰራ ይገኛል።፡ ባህርዳር ዩኒቨርስቲ በጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን የትምህርት ዘርፍ በዲግሪ ከተመረቀ በኋላ ፕሮፌሽናል ጋዜጠኛ የመሆን ፍላጎት እንደነበረው የሚናገረው ዳንኤል፤ በተለያዩ የግል ጋዜጦች ላይ በአምደኝነት ሲሰራ ግን የፕሬስ ነፃነት መታፈኑንና የሚያሰራ ሁኔታ እንደሌለ መገንዘቡን ገልጿል፡፡ ይህን ሁኔታም ለመለወጥ የፖለቲካ ትግል እንደሚያስፈልግ በማመንም የራሱን አስተዋፅኦ ለማበርከት አንድነት ፓርቲን እንደተቀላቀለ ይናገራል - ወጣቱ ፖለቲከኛ፡፡ ጋዜጠኛ ሰላም ገረመው በፖለቲካ ህይወቱ፣ በቅርቡ በተሰጠው ሹመት”፣ በመጪው ምርጫና ሌሎች ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ አነጋግራዋለች፡፡
በአንድነት ፓርቲ ውስጥ በምን በምን ሃላፊነቶች አገልግለሃል?
አሁን የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ ሃላፊ ነኝ፤ በፊት ምክትል ሃላፊ ነበርኩኝ፡፡ ከዛ በፊት ፓርቲው ውስጥ የኢዲቶሪያል አባል በመሆን የፍኖተ ነፃነት ጋዜጣ ሃላፊ ሆኜ ሰርቻለሁ፡፡ “ጽናት” የተሰኘችውን ልሳናችንን ከጀመሩት መካከል አንዱ ሆኜ” በሪፖርተርነትም በዲዛይነርነትም አገልግያለሁ።
ፓርቲውን ከመቀላቀልህ በፊት የት ሠርተሃል?
ከባህርዳር ዩኒቨርስቲ በጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ከተመረቅሁ በኋላ የፖለቲካ ትንታኔ በመፃፍ በአምደኝነት ብዙ ቦታ ሰርቻለሁ፡፡ በተለይ ደግሞ “አውራምባ ታይምስ” እና “ፍትህ” ጋዜጣ ላይ ቋሚ አምደኛ ነበርኩ፡፡ እስኪዘጋ ድረስ አሁንም አዲስ ታይምስ ጋዜጣ ላይ እየፃፍኩ ነው፡፡
ወደ አንድነት ፓርቲ እንዴት ገባህ?
የኢትዮጵያ ነፃ ፕሬስ እንደተፈለገው ባለማደጉ ከሚቆረቁራቸው መካከል አንዱ ነበርኩ፡፡ በጋዜጠኝነት እንደተመረቅሁ ሃሳቤ ፕሮፌሽናል ጋዜጠኛ መሆን ነበር፡፡ ነፃውን ፕሬስ ቀረብ ብዬ ስመለከተው ግን ትልቅ ግብግብ ያለበት” ከወረቀት ያልዘለለ ነፃነት የተሰጠውና በአፈና ውስጥ የሚንቀሳቀስ መሆኑን ተረዳሁ፡፡ በፕሮፌሽናል ጋዜጠኝነት ለመስራት ሁሉም መንገዶች ዝግ ነበሩ፡፡ ምናልባት በኢትዮጵያ ውስጥ ሌሎችም ሙያዎች ዝግ ይመስሉኛል፡፡ ፕሮፌሽናል ጋዜጠኛ ብቻ ሳይሆን ፕሮፌሽናል ገበሬም መሆን የሚቻል አይመስለኝም፡፡ እንደ ወጣት ወደምፈልገው አቅጣጫ መሄድ አልቻልኩም፡፡ ይኼኔ ራሴን አንድ ጥያቄ ጠየቅሁት፡፡ “አንድ ወጣት የሚፈልገውንና የሚመኘውን ነገር ለመስራት ምንድነው ማድረግ ያለበት? ችግሩ ያለው የት ጋ ነው ?” በማለት፡፡ በመጨረሻም ችግሩ የሲስተም ችግር ሆኖ አገኘሁት፡፡
የሲስተም ችግር ስትል ምን ማለትህ ነው?
ብዙ ነገሮች በአንድ ቦይ እንዲፈሱ እየተደረገ ነው ያለው፡፡ ፕሮፌሽናል ለመሆን የሚያስችል ሁኔታ ከሌለ ያንን መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ይሄንን ደግሞ ለማድረግ የፖለቲካ ትግል ያስፈልጋል የሚል አቋም ላይ ደረስኩ። ፓርቲውን የተቀላቀልኩትም በዚህ መልኩ እንጂ ማንም ጠርቶኝ አይደለም፡፡ የራሴን አስተዋጽኦ ለማድረግ ስል ነው አንድነት ውስጥ የገባሁት፡፡ እዚህ አገር ወጣቶች በነፃነት የሚፈልጉበት ነገር ላይ ለመድረስ የሚችሉበት ሁኔታ እንዲፈጠር ስለምፈልግ ነው የፖለቲካ ትግል የጀመርኩት፡፡
ለአዲስ አበባና አካባቢ ምርጫ ምን ዝግጅት እያደረጋችሁ ነው?
ምርጫውን አስመልክቶ በሠላማዊ መንገድ የምንቀሳቀስ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደመሆናችን መጠን ሁል ጊዜም እንዘጋጃለን፡፡ እንዲሁ ምርጫ ሲደርስ ግርግር መፍጠር አይደለም፡፡ ምክንያቱም ዝግጅት ሲባል እንደ ፓርቲ አደረጃጀታችን የተስተካከለ መሆን አለበት፡፡ አደረጃጀቱ እስከወረዳ ወርዶ በደንብ መሠራት አለበት፡፡ በእኛ በኩል ዝግጅት ብናደርግም በኢህአዴግ በኩል ግን የእኛን ዝግጅት የሚያደናቅፍ ነገር ነው እየተሠራ ያለው። “እንዳያማህ ጥራው እንዳይበላ ግፋው” የሚል አባባል አለ፡፡ ያንን አይነት ሲስተም ነው የሚከተሉት፡፡ ከምር ተወዳድሮ መሸናነፍ እንዲኖር የሚፈልጉ አይመስለኝም፡፡ በቅርቡ 33 ፓርቲዎች ከምርጫው ዝግጅት በፊት ከምርጫ ቦርዱ ጋር መወያየት አለብን የሚል ጥያቄ አንስተዋል። ይሄ ጥያቄ መመለስ አለበት ብለን እናምንለን፡፡ እኛም አገራዊ ጉዳይ ላይ በትክክል ቁጭ ብለን ከኢህአዴግ ጋር መነጋገር አለብን የሚል እምነት አለን፡፡ ስለዚህ በምርጫው እንሳተፋለን አንሳተፍም የሚለው ነገር አሁን የሚወሰን አይደለም፡፡ ነገሩ በፓርቲ ደረጃ የሚወሰን ነው፤ ሆኖም እኛ ዝግጅታችንን እያደረግን ነው፡፡
በዚህኛው ምርጫ ተሳትፋችሁ ካላሸነፋችሁና በውድድሩ ጐላ ያለ ነገር ካላሳያችሁ በህዝቡ ዘንድ ልንረሳ እንችላለን የሚለው አያሳስባችሁም?
የፖለቲካ ፓርቲ እንደመሆናችን መጠን ምርጫ ውስጥ ገብተን መወዳደር እንፈልጋለን፤ ነገር ግን በምርጫ ለመወዳደር የተስተካከለ ቦታ አለ ወይ? መሠረታዊ ነገሮች ላይ እንነጋገርና እንወዳደር ነው እያልን ያለነው፡፡ የምንወዳደረው በኢትዮጵያ ህዝብ ፊት ነው፤ የኢትዮጵያ ህዝብ በትክክል የሚፈልገውን ይምረጥ፤ ከዛ በኋላ ከተሸነፍንም ካሸነፍንም የማንቀበልበት መንገድ የለም፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ነገሮችን ተመልከቺ--- ለምሳሌ አንድነት ፓርቲ “ፍኖተ ነፃነት” የተሰኘችው ልሳኑ ተዘግታበታለች፤ ሌሎች አማራጭ ሚዲያዎችም እንደዚህ አይነት እርምጃ ተወስዶባቸዋል፡፡ በሌላ በኩል ኢህአዴግ እንደፈለገው እንደመንግስትም እንደፓርቲም ባለየ መልኩ ሚዲያውን እንደፈለገ ነው የሚጠቀመው፡፡ የምርጫ ቅስቀሳ እያደረጉ መሆናቸውን አይናገሩ እንጂ በሚቆጣጠሯቸው ሚዲያዎች ቅስቀሳ እያደረጉ ነው፡፡
እኛ ግን ወደ ህዝብ የምንደርስበት፤ የአደረጃጀትና የቅስቀሳ ስራ የምንሰራበት፤ አባሎችና ደጋፊዎቻችንን የምናደራጅበት ጋዜጣ ተዘግቶብናል፡፡ እሱ ብቻ አይደለም፤ ሁልጊዜ አዲስ አባላት ወደዚህ ሲመጡ ተከትለው ያስፈራሯቸዋል፡፡ በአይን የሚታይ እና በአይን የማይታይ እርምጃ ነው እየወሰዱ ያሉት። የክበባት አይነት ስልት ነው የሚከተሉት፡፡ አዲስ አባላት ወደኛ ሲመጡ እየተከተሉ ማስፈራራት ማዋከብ ስራዬ ብለው ነው የያዙት፡፡ የምንናገርበት መድረክ ከሌለ ውድድሩስ እንዴት አይነት ውድድር ነው የሚሆነው? ማሸነፍና መሸነፍ የሚለው የሚመጣው ከውድድር በኋላ ነው፡፡ እኛ የምንለው በትክክል እንወዳደር ነው፤ ያንን ደግሞ ኢህአዴግ አልፈቀደውም፡፡
እኛ እኮ በጣም ብዙ ጥያቄ አይደለም የጠየቅነው። ለምንድነው የመሰብሰቢያ አዳራሽ የምንከለከለው? ለምንድነው የሆቴል ባለቤቶች አዳራሽ እንዳይፈቅዱልን የሚደረጉት? እንደዚህ አይነት አጥር አበጅቶ ኑ እንወዳደር ማለት የሚያስኬድ አይመስለኝም፡፡ የፖለቲካ ምህዳሩ ጠቧል የሚባለውም ይሄ እኮ ነው ሌላ ነገር አይደለም፡፡ እኛ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ማድረጋችንን አናቆምም፡፡ ለምሳሌ “ፍኖተ ነፃነት” ጋዜጣችንን ኦንላይን ጋዜጣ ለማድረግ እንቅስቃሴ እያደረግን ነው፡፡ እኛ ነጋዴዎች አይደለንም ፤ ነገር ግን አባሎቻችንን በዚህ መንገድ መድረስ እንፈልጋለን። በዘመናዊና የሰለጠነ አለም ውስጥ ብንሆንም በጨቋኝና ተጨቋኝ ስርአት ውስጥ ነው ያለነው፡፡ ጥያቄውና እና ቁልፉ ያለው በኢህአዴግ እጅ ነው፤ እነሱ ቆልፈው ቁልፉን ይውጡታል፡፡
ኢህአዴግ የስነ - ምግባር ደንቡን ካልፈረሙ ፓርቲዎች ጋር አልወያይም ይላል፡፡ እናንተ ደንቡን ብትፈርሙ የሚጐዳችሁ ነገር ምንድነው?
አንደኛ የስነምግባር ደንብ የተባለው ሙሉ አይደለም፡፡ ከያዘው ሦስት ክፍል አንደኛዋ ተቀንጭባ እንድትመች ተደርጋ የተዘጋጀች ናት፡፡ ስለዚህ ቁጭ ብለን በዚህ ጉዳይ ላይ እንነጋገርና ቁጭ ብለን እንደራደር ነው የምንለው፡፡ እነሱ ለምን የፃፍነውን ተቀበሉን ይላሉ፡፡ ሁለተኛ ተሯሩጠው ፓርላማ አጸድቀው የአገሪቱ ህግ አድርገውታል፡፡ የአገሪቱ ህግ እስከሆነ ድረስ ደግሞ ተቀብለነዋል ማለት ነው። ፈርሙ ማለቱ ምኑ ላይ ነው ጥቅሙ? እነሱ ይሄንን የሚጠቀሙት እንደማደናገሪያ ይመስለኛል፡፡ ከዛ ያለፈ አይመስለኝም፡፡ የፈረሙትም አይጠቅመንም ብለው ሲወጡ ነው ያየነው፡፡ ለዚህች አገር ፖለቲካ የሚጠቅመው ቀናነት ነው፡፡ እኛ አገር እየተሽሎኮሎኩ መሄድና የጮሌነት ባህሪ ይቀናናል፡፡ ይሄንን ባህሪ ማረቅ ያስፈልጋል፡፡ ፖለቲካ ለሚቀጥለው ትውልድ መሰረት መጣል የተስተካከለ ነገር ማስተላለፍ ማለት ነው፡፡ የተስተካከለና አንድነት ያለው ህዝብ ይኑረን ካልን ፖለቲከኛ መስተካከሉ ዋናው ጉዳይ ነው፡፡
ህዝቡ ስለ ፖለቲካ የመስማት ፍላጐቱ ቀንሷል። የፖለቲካ ድባቡን ለማነቃቃት ምን እያደረጋችሁ ነው?
ቀንሷል በሚለው አልስማማም፤ እንደውም የኢትዮጵያ ህዝብ ስለ ፖለቲካ ለመስማት የሚፈልግበት ደረጃ ላይ እንዳለ ነው የሚሰማኝ፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ ህዝብ የፖለቲካን ወሬ የሚያወራው ቤቱ ውስጥ ነው፡፡ ቤቱ ውስጥ ሁሉም ፖለቲከኛ ነው፤ የሚደርስበትን ብሶት ይናገራል፡፡ ይቺን የቤት ውስጥ ወሬ ወደ አደባባይ እንዲያወጡ እንዲተነፍሱ እንዴት ማድረግ ይቻላል የሚለው ዋና ጥያቄ ነው፡፡ ስለዚህ ጥያቄው መሆን ያለበት ህዝቡ ዝም ብሏል፤ ያንን ለማንቃት ምን አይነት እርምጃ ትወስዳላችሁ ይመስለኛል፡፡ ህዝቡን ለማነቃቃት ሁለት ዋና ዋና አካላት አሉ፡፡ መንግስታዊ ያልሆኑ አካላትና ሚዲያው ነው፡፡ ገዢው ፓርቲ ደግሞ እነዚህ ሁለት አካላት ህዝብን የማንቃት ስራ ስለሚሠሩ ትልቅ ጫና ጥሎባቸዋል፡፡ ሚዲያው እንዳይላወስ ተደርጓል፡፡ ሚዲያ ላይ እንደፈለገ የመናገር መብት የተነፈገ ህዝብ ዝም ነው የሚለው፡፡ ሌላው መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የተለያዩ ሃሳቦችን በማንሳትና ውይይት በማዘጋጀት ህብረተሰቡን የማወያየት ስራዎችን መስራት ስላልቻሉ እኛ ጋዜጣ ፈጠርን፡፡ ጋዜጣውን የመሰረትነው ለመሸጥ አይደለም፡፡ የሚዲያ እጥረት ስላለ አንድም እንደ ነፃ ሚዲያ እንድታገለግል ሁለትም አባላትና ደጋፊዎቻችንን በዛ መልኩ ለማግኘት ነበር፡፡ በየሳምንቱ ወቅታዊ ርዕሶችን እየመረጥን እናወያያለን። የፖለቲካ ስራን መስራት ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ስራን ከመስራትም ባለፈ እነዚህን ሁለት ስራዎችን እየሠራን ነው፡፡
የህብረተሰቡ ችግር ስራ አጥነት፣ የኢኮኖሚ ጥያቄ እና ሌሎች ጉዳዮች ናቸው፡፡ መፍትሔው ምንድነው?
አገሪቱ ላይ በርካታ ችግሮች ናቸው ያሉት፡፡ የስራ ማጣት ችግር፣ የትራንስፖርት ችግር፣ የኢኮኖሚ፣ በልቶ ያለማደር ችግር አለ፡፡ እኛ አገር ያለው ችግር በጣም ብዙ ነው፡፡ እነዚህ ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉት በጣም ቀና የሆነ የተስተካከለ የፖለቲካ ስርአት በመዘርጋት ነው፡፡ እኛ የምንታገለው፣ እኔ የምታገለው ለዚህ ነው። የተስተካከለ ፖለቲካ ካለ፣ የነቃ ማህበረሰብ ካለ፣ እኔ ነኝ የማስብልህና በዚህ መስመር ሂድ የሚባል ሳይሆን ማሰብና መፍጠር የሚችል የነቃ ማህበረሰብ መፍጠር ከቻልን እነዚህ ሁሉ ችግሮች ይቀረፋሉ፣ ምክንያቱም አምራች ሀይል ነው የሚፈጠረው፡፡ ነገር ግን በአንድ አካል ተጨቁኖ የተያዘ ስርአት ባለበት አገር ውስጥ ዜጐች ተጨብጠው ነው የሚኖሩት፤ ስለዚህ እኛ ብንሆን የምናደርገው መጀመሪያ ነፃ ማህበረሰብ መፍጠር ነው፡፡ በዚህ ነው ድህነትንና ስራ አጥነትን መቅረፍ የሚቻለው፡፡ ኢህአዴግ እኔ ብቻ ነኝ የማውቀው፤ በዚህ መንገድ ብቻ ሂዱ ብሎ በማፈን፣ በማስጨነቅ እና አንቆ በመያዝ ችግሮችን ማባባስ ነው የያዘው፡፡ ግን ነፃ ማህበረሰብ በመፍጠር ችግሩን መቅረፍ ይቻላል፡፡
ፓርቲያችሁ በወረዳና በቀበሌ ያደራጃል?
የአንድነት ፓርቲ አደረጃጀት ከላይ ወደታች ነው። ሁሉም ወረዳዎች ላይ አደረጃጀቶች አሉን፡፡ አንድ አባል ለመመዝገብ ሲመጣ በወረዳው በኩል ነው የሚመጣው፤ ወርሃዊ መዋጮንም በወረዳው በኩል ነው የሚፈጽመው፡፡ የተሳካና ጥሩ አደረጃጀት እንዳለን ነው የምናውቀው፡፡
አንድ አባል አንድነት ፓርቲን ሊመርጥ የሚችልበትን ነገር ንገረኝ---
አንድነት ፓርቲ ተመራጭ ፓርቲ ነው ስንል ከመሬት ተነስተን አይደለም፤ ትግሉ ከስሜት በተላቀቀና በደንብ በተደራጀ መልኩ ወጣቱንና የተቀረውን የኢትዮጵያ ህዝብ ተሳታፊ የሚያደርግ እንዲሆን ነው የምንሰራው። ይሄንን ስናቅድ ደግሞ ዝም ብለን አይደለም፤ የአምስት አመት እቅድና ስትራቴጂ አለን፡፡ በዚህ በአምስት አመት እቅድና ስትራቴጂያችን ውስጥ ምንድነው መስራት ያለብን፣ ምን ምን ስራዎችን ነው ማከናወን ያለብን የሚለው በዝርዝር ተቀምጧል፡፡ ሁለተኛ የራሳችንን ሚዲያ ገዢው ፓርቲ ዘጋብን እንጂ አሁንም እየቀጠልን ነው፡፡ አደረጃጀቱ የውስጥ ዲሞክራሲ አለው፡፡ የውስጥ ዲሞክራሲ ሲባል የውስጥ ዲሞክራሲያዊ አሠራር ነው፡፡ ስለዚህ ወደ አንድነት ፓርቲ የሚመጡ አባላት በጠቅላላ ጥሩ ልምድ አግኝተው፣ የራሳቸውን ነገር ቀርፀው ነው ወደ ማህበረሰቡ ሄደው የራሳቸውን ስራ የሚሠሩት፡፡
ስለዚህ አንድነት ፓርቲ የፖለቲካ ትግል የሚካሄድበት ብቻ ሳይሆን ብዙ ነገር የሚገኝበት ተቋም ነው፡፡ ከዚህ በፊት የነበረውን የፖለቲካ ሂደት በማጥናት ይሄ መንገድ ትክክል አልነበረም፣ በበሰለ ምሁራዊ መንገድ መሄድ አለብን የሚለውን እየሠራን ስለሆነ ተመራጭ ያደርገናል፡፡
በቀድሞ ጠ/ሚኒስትትና በአሁኑ ጠ/ሚኒስትር መካከል ያለው ልዩነት ምንድነው ትላለህ?
ከመልክ ልዩነት በቀር በእነዚህ ሁለት መሪዎች መካከል ያለው ልዩነት የጐላ አይደለም፡፡ አቶ ሃይለማርያም ከመለስ ስር ሆኜ ተምሬያለሁ ነው የሚሉት፣ ስለዚህ የአስተሳሰብ ልዩነት የላቸውም። በጣም ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው ለመጀመሪያ ጊዜ ፓርላማ በቀረቡበት ወቅት አቶ ሃይለማርያም የአነጋገር ዘይቤያቸው፣ የሚጠቁሙት ቃል ሳይቀር የአቶ መለስን ይመስል ነበር፡፡ ለምሳሌ አቶ መለስ “ህገወጥነትና ህጋዊነትን አቀላቅሎ መሄድ አይቻልም” ሲሉ አቶ ሃይለማርያም “ሁለት ባርኔጣ እያቀያየሩ ማድረግ አይቻልም” ወደሚለው ቀይረውታል፡፡ ይሄ ግን ጉልህ ልዩነት አይደለም፡፡ አቶ ሃይለማርያም በተሃድሶ ሲስተም ተቀርፀው ነው የመጡት፡፡ ለዚህ ነው በአቶ መለስና በአቶ ሃይለማርያም መካከል ምንም ልዩነት የሌለው፡፡ አቶ ሃይለማርያም ፖለቲካዊ ለውጥ ያመጣሉ ብዬ ከማይጠብቁት ሰዎች አንዱ ነበርኩኝ። ምክንያቱም እሳቸውም ከአቶ መለስ ስር ቁጭ ብዬ ተምሬያለሁ በማለት ያለምንም ማስተካከያ እቀጥላለሁ የሚሉ ናቸው፡፡ መጥፎ ነገሮችን እያስወገድኩ ጠንካራ ነገሮችን ይዤ እቀጥላለሁ ቢሉ ትንሽ ተስፋ ይኖረው ነበር፡፡ ከመለስ የሚለያቸው እሳቸው ብቻቸውን ሲመሩ ነበር፤ አቶ ሃይለማርያም ግን እንደመለስ መጠቅለል አልቻሉም መሰለኝ፣ በክላስተር በክላስተር አስቀምጠው በህገመንግስቱ የማይታወቅ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮች ሾመዋል፡፡ እንደዚህ አይነት የአቅም ልዩነት ካልሆነ በስተቀር የማስፈፀም እና የአስተሳሰብ ልዩነት አለ ብዬ አላስብም፡፡
ከዶ/ር ሃይሉ የተረከብከው ስልጣን ምን ይመስላል?
ለኢትዮጵያ ከደከሙ፣ ዋጋ ከከፈሉና ሊመሰገኑ ከሚገባቸው ሰዎች መካከል አንዱ ዶ/ር ኃይሉ ናቸው፡፡ ዶ/ር ኃይሉ አርአያ ብዙ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ አሁን ከፓርቲው ወጥተዋል ማለት ግን አይደለም፤ አለቀቁም፡፡ ከእሳቸው ጋር የመስራት ዕድሉ ስለገጠመኝ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ በቅርበት ስለማውቃቸው ነው የምናገረው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ወጣቶች ወደፊት መምጣት አለባቸው፣ ቀረብ ብለው መምከር አለባቸው ከሚል ሃሳብ ተነስቶ ነው ይሄ ነገር የተወሰነው፡፡ እሳቸውን ለመተካት በመመረጤ ደስ ብሎኛል፡፡ ነገር ግን እዚህ ጋ እያደረግን ያለነው የስልጣን ጉዳይ አይደለም፤ የፖለቲካ ትግል ነው፤ ተሽከርካሪ ወንበር ላይ ተቀምጦ፣ ሱፍን አሳምሮ መግባትና መውጣት አይደለም፡፡ መሠረታዊ የሆኑ ዲሞክራሲያዊ እና ሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩ የራስን አስተዋጽኦ ማድረግ ነው፡፡ ዳንኤል ይሄንን ያደርጋል ተብሎ ሃላፊነት ነው የተሰጠኝ፤ ሸክም ነው የተሰጠኝ እንጂ ስልጣን አይደለም፤ አባባሉም አይጥመኝም። ሽግግሩ በጣም ጤነኛ ነው ብዬ ነው የማምነው፡፡ የፓርቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ የራሳቸውን ካቢኔ ሲያቋቁሙ ዶ/ር ሃይሉ “አሁን መስራት አልችልም” የሚል ደብዳቤ ያቀርባሉ፡፡ ስለዚህ እሳቸውን የሚተካ ሰው ተብዬ ነው የተተካሁት፡፡
በዚህ ቦታ ላይ ያልተሠራ እና እሠራዋለሁ ብለህ የምታስበው ነገር ካለ----
በየጊዜው የፖለቲካ አካሄድ ይቀየራል፤ ውስብሰብ ነገሮች ይኖራሉ፤ ቀና ነገሮች ይገጥማሉ፤ በእነዚህ መካከል ክፍተቶች ይኖራሉ፡፡ ፓርቲው ያስቀመጠው የአምስት አመት ስትራቴጂ አለ፤ ያንን ማስፈፀም ነው የእኔ ስራ፡፡ የምሰራው ስትራቴጂውን ተከትዬ ነው። የህዝብ ግንኙነት ስራ ወቅታዊ ነው፤ ለአንድነት ፓርቲ ወይም ለዶ/ር ስል ብቻ አይደለም የምሠራው፤ ከምር ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ለውጥ ያስፈልገናል፤ የስልጣን ሽግግር ያስፈልገናል፤ አንዱ ጨቋኝ ሌላው ተጨቋኝ የሚለው ማብቃት አለበት የሚል ጠንካራ አቋም አለኝ፡፡ አገሪቱ ውስጥ ትናንሽ አምባገነኖች እየተፈጠሩ ነው፤ ሲስተም መዘርጋት አለበት፡፡

Read 8491 times Last modified on Saturday, 29 December 2012 09:06