Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 29 December 2012 08:49

አነጋጋሪው የዘመናችን ጥያቄ! - “ገንዘብ ወይስ እውቀት?”

Written by 
Rate this item
(17 votes)

ባለፈው እሁድ በኢቲቪ የተሰራጨው የነ ሠራዊት ፍቅሬ ፕሮግራም በርካታ ተመልካቾችን አበሳጭቷል። ወይም ብዙዎችን አነጋግሯል ልንል እንችላለን - ለማሳመር ስንሞክር። “እንዳለመታደል ሆኖ፤ እሱ ላይ ነገር ይከርበታል” የምትል አድናቂ አጋጥማኛለች። እንዴት ነው? “ነገር ስለሚከርርበት” ይሆን እንዴ ትችትና ወቀሳ የበዛበት?
የጠፉ ነገሮች ላይ መከራከር
አንድ የስራ ባልደረባዬ እየተንጨረጨረ የተናገረውን ላካፍላችሁ። “ክርክርና ውይይትኮ ደስ ይለኛል። የነ ሠራዊት ፍቅሬ ክርክር ግን፤ ቀሽም ድራማ ሆነብኝ። የሌለ የምናብ አለም ፈጥሮ መከራከር አያስጠላም። ገና ድሮ የጠፉና የሌሉ ነገሮች ላይ፤ ወይም ሊጠፉ የተቃረቡ ‘ብርቅዬ’ ነገሮች ላይ መወያየት ምንም ጥቅም የለውም። የጠፉ ነገሮችን እንዳልጠፉ መቁጠርና መከራከር፤ በከንቱ ጊዜ ማጥፋት ነው።

የእውቀትና የገንዘብ ክፉኛ እጥረት ባለበት አገር፤ ‘ገንዘብ ይሻላል ወይስ እውቀት?’ ብሎ መከራከር የጤና አይመስለኝም። ከዚያ በፊት ያቀረቡት ክርክርምኮ ያው ነው። ‘ለቡና መጠራራት ጥሩ ነው መጥፎ?’ ... ድሮ የቀረ ነገር! ... በሌላኛው ሳምንት ደግሞ፤ ስለ አስተማሪና ተማሪ ግንኙነት ሲያከራክሩ ነበር። ... አሁን እዚህ አገር ትምህርት አልጠፋምና ነው? ትምህርት ሳይኖር፣ ስለ አስተማሪና ተማሪ ግንኙነት መከራከር ምን ይሉታል!”
ምሬቱና ትችቱን ያበዛው አይመስላችሁም? እሱ ግን፤ ገና መጀመሩ ነው። እነ ሰራዊት ፍቅሬ የድሮ አኗኗር ላይ ተቸክለው ቀርተዋል ባይ ነው - የስራ ባልደረባዬ።
ከድሮው ዘመን አልተላቀቁም  
“አስበው እስቲ፤ ስለ አስተማሪና ተማሪ ግንኙነት ሲያወሩ... ስለ ድሮው የመምህራን ግርፊያ ነው የሚያወሩት። ዘመኑ እንደተቀየረ አልገባቸውም። አሁንኮ ተማሪዎች በየትምህርት ቤቱ ፓርላማ አቋቁመዋል። በፓርቲ ተደራጅተዋል። በአንድ ለአምስት አደረጃጀት አስተማሪዎችን ማስፈራራት ይችላሉ። ... እነ ሠራዊት ፍቅሬ ግን የድሮውን የመምህራን ግርፊያ ብቻ ነው የሚያውቁት። ... እነሱ ለቡና መጠራራት በዝቷል ብለው የሚከራከሩት የትኛው ዘመን ላይ ሆነው ነው? ጭራሽ፤ ‘እውቀት ይበልጣል ወይስ ገንዘብ?’ የመድረክ መነባንብ አቀረቡልን። ድሮ የአራተኛ ክፍል ትምህርት ነው የመሰለኝ? መድረክ ላይ የመናገር ችሎታ ለማዳበር ‘ብዕር ይበልጣል ወይስ ጎራዴ?’ ብለን ስንከራከር ትዝ አይልህም? ወይስ የዘንድሮ አዋቂነትና የድሮ አራተኛ ክፍል ተመሳሳይ ሆነዋል?”
የስራ ባልደረባዬ ትችት በዚሁ ካልቋጨሁት ማቆሚያ አይኖረውም። “ሠራዊት ፍቅሬ ላይ ነገር ይከርበታል” ያለችኝ ልጅ ትክክል ትሆን እንዴ? ሁለተኛው ትችት አቅራቢም፤ አምርሮ ነው የሚናገረው። “ይሄኮ ክርክርም ውይይትም አይደለም። ጉንጭ ማልፋት ነው። ገና ድሮ ትርጉም ያጡ ነገሮች ላይ መነታረክ አይመስጠኝም” በማለት ይጀምራል።

ትርጉም ያጡ ነገሮችን እያነሱ መጣል
“በበዓል ቀን መስራትና አለመስራት በከተሞች ውስጥ አከራካሪ ጉዳይ መሆን ያበቃውኮ ድሮ ነው። ልክ እንደዚያው፤ ቡና መጠራራትም ገና ድሮ ትርጉም አጥቷል። በዚያ ላይ፤ የቡና ዋጋ ስለተወደደ፣ ተጠራርቶ መጠጣት... ብርቅ ቅንጦት እየሆነ መጥቷል። ጥዋትና ከሰዓት፣ ከአቦል እስከ በረካ ሲደጋግሙት መዋል ቀርቷል። በየመንገዱ የጀበና ቡና ንግድ የተስፋፋው ለምን ሆነና! መጠራራት ስለጠፋ ነው” ... ለነገሩ እውነቱን ነው። የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ መረጃ እንደሚያሳያው ባለፉት አምስት አመታት ብቻ የቡና ዋጋ ከአራት እጥፍ በላይ ጨምሯል። “ቡና መገኛ ምድር” በምትባለው በኢትዮጵያ፤ ቡና ብርቅ ሆናል! ይሄኛው ተቺ ግን፤ ትምህርትና እውቀት፤ ገንዘብና ብር ሁሉ በአገራችን ትርጉም አጥተዋል ባይ ነው።
“የአስተማሪና የተማሪ ነገር እንዲገባህ ከፈለግክ፤ የ10ኛ እና የ12ኛ ክፍል የፈተና ውጤቶችን መመልከት ነው። መቶ የምርጫ ጥያቄ ቢቀርብልህ፤ ....ኤ፣ቢ፣ሲ፣ ወይም ዲ... መርጠህ መመለስ ነው። ጥያቄዎቹን ማንበብ የማይችል ሰው፤ ‘በደመነፍስ’... አንዱን መልስ እየመረጠ ቢያጠቁር፣ ከመቶ ስንት እንደሚያገኝ ታውቃለህ? 25 ከመቶ የማግኘት እድል ይኖረዋል። ክፍል ገብተው የማያውቁ፣ አንድም ቀን ደብተር ያላነበቡ “መሃይማን” በአማካይ 25 ከመቶ ማግኘት ይችላሉ ማለት ነው። 10 እና 12 አመታትን በትምህርት ያሳለፉ ተማሪዎችስ ምን ያህል ውጤት አገኙ? አማካይ ውጤታቸው 30 ከመቶ ነው። ታዲያ የተማሪነት ትርጉም አልጠፋም?”
ለአመታት ሲማር በነበረና ፈፅሞ ባልተማረ ሰው መካከል ያለው ልዩነት የ5 ማርክ ብቻ ከሆነ፤ እውነትም የመማር ትርጉም ጠፍቷል። ግን ትችቱን ቀጠለ።
“ከተማሪዎቹ ውስጥ ደህና ውጤት ያስመዘገቡ፣ ዩኒቨርስቲና የቴክኒክ ተቋማት ውስጥ ገብተው በሰርቲፊኬት፣ በዲፕሎማና በዲግሪ ይመረቃሉ። ግን መመረቅ ማለት፤ ...እውቀትንና ብቃትን የማያመለክት ከሆነ ትርጉም የለውም” አለ።
እውነቱን ነው። የቴክኒክ ስልጠና አጠናቅቀው ከተመረቁ ተማሪዎች መካከል፤ አብዛኞቹ ብቃት እንደሌላቸው የትምህርት ሚኒስትር ሪፖርት ይመሰክራል። ባለፈው አመት 120ሺ ያህል ተመራቂዎች፤ የብቃት ማረጋገጫ ፈተና ወስደዋል። በተመረቁበት ሙያ ብቁ ሆነው የተገኙት ግን 30ሺ ያህሉ ብቻ ናቸው (25 በመቶ ያህሉ ብቻ) መሆናቸውን፤ ባለፈው ግንቦት ለፓርላማ የቀረበው የትምህርት ሚኒስቴር የ9 ወር ሪፖርት ይገልፃል - ገፅ 12። ሌላም አለ። የእንግሊዝኛ ቋንቋ አስተማሪዎችን ብቃት ለመመዘን፤ ለአራት ሺ መምህራን ፈተና ተሰጥቷል። ብቁ ሆነው የተገኙት አንድ ሺ አይሞሉም - ከ25 በመቶ በታች ማለት ነው (የሪፖርቱ ገፅ 6)።
“አስተማሪነትም ሆነ አዋቂነት ትርጉም እያጣ ነው አትሉም! ታዲያ የትምህርት ነገር ትርጉም ባጣበት ዘመን፤ ስለ አስተማሪና ስለ ተማሪ ግንኙነት ማውራት ምን ይፈይዳል? ክፍል መቁጠርና መመረቅ፤ እውቀትንና ብቃትን የማያመለክት ከሆነ፤ እውቀት ትርጉም አጥቷል። የገንዘብ ነገርማ ብንተወው ይሻላል፤ ትርጉም አጥቷል። የብር ኖቶች ላይ የሰፈረው ‘ላምጪው እንዲከፈል ህግ ያስገድዳል’ የሚለው ፅሁም ምንም ትርጉም የለውም” በማለት ትችቱን ይቀጥላል።

ብር ይዞ ለሚመጣ ምን ይከፈለዋል? ምንም
“በኛ አገር የገንዘብ ትርጉም ለመጥፋቱ ጥሩ ምስክር ከፈለግክ፤ ብሄራዊ ባንክ የሚያሳትመውን የአገራችን ገንዘብ ተመልከት። የብር ወረቀቶች (ኖቶች) ላይ “ላምጪው እንዲከፈል ህግ ያስገድዳል... payable to the bearer on demand” ... የሚል ፅሁፍ የሰፈረው ምን ለማለት ተፈልጎ ነው? ትርጉሙ አልገባኝም ብለህ አትጨነቅ። ትርጉሙን አጥቷል። አሳታሚው ተቋምም ትርጉሙን ሊነግርህ አይችልም። ብሩን ይዞ ለሚመጣ ምን ይከፈለዋል? ምንም። ማን ይከፍለዋል? ማንም...
“ለነገሩ የአማርኛው ፅሁፍ ጉድለት አለበት። እንግሊዝኛው ‘...on demand’ ይላል። የአማርኛውን ከእንግሊዥኛው ጋር እናጣጥመው ካልን፤ ‘አምጪው በፈለገ ጊዜ ይከፈለዋል’ ልንለው እንችላለን። ‘አምጪው በጠየቀ ጊዜ፤ እንዲከፈለው ህግ ያስገድዳል’ ብንለውም ስህተት አይሆንም። እንዲህ ተስተካክሎም፤ ትርጉም የለውም። የአምጪው ፍላጎት ወይም ጥያቄ ምን ሊሆን ይችላል? ምን እንዲከፈለው? ... ምንም መልስ የለም። ድሮ ድሮ ግን፤ ትርጉም ነበረው። ገንዘብ እንደ ዛሬ ባልረከሰበት ዘመን ማለት ነው...
“ድሮ፤ ገንዘብ ተጨባጭ መሰረት ነበረው - ወርቅ የሆነ መሰረት። ገዢና ሻጭ ሆነን የምንገበያየው፤ ወይም ደሞዝ የምንከፍለውና የሚከፈለን በወርቅ ቢሆን ብለህ አስበው። ለምሳሌ የአንድ ሺ ብር ደሞዝተኛ አንድ ግራም ወርቅ ይከፈለዋል - አንድ ሺ ሚሊ ግራም መሆኑ ነው። የአስር ብር ሳሙና ስንገዛ፣ አስር ሚሊ ግራም ወርቅ እንሰጣለን። ወርቅ በሚሊ ግራም ስንመዝንና ስንቆነጥር እንውላለን ብለህ አትስጋ። ዘዴው ምን መሰለህ? ያለንን ወርቅ ባንክ እናስቀምጣለን - አንዲት ሚሊ ግራምም ብትሆን። ባስቀመጥነው ወርቅ ልክ፤ ከባንኩ ምስክር ወረቀት እንቀበላለን - ድሮ ‘የባንክ ኖት’ ይባል ነበር...
“አንድ ሚሊግራም ወርቅ ስናስቀምጥ አንድ የባንክ ኖት እንቀበላለን ብለህ አስበው። እናም የአንድ ብር ኖት የሚል ስም አወጣንለት እንበል። አስር ሚሊ ግራም ወርቅ ስናስቀምጥ ባለ አስር ብር ኖት፤ መቶ ሚሊ ግራም ስናስቀምጥ ባለ መቶ ብር ኖት...። የባንክ ኖት፣ የብር ኖት፤ ተራ ወረቀት አይደለም ማለት ነው። ወርቅ ማስቀመጣችንን የሚመሰክር ወረቀት ነው። ኖቱን ይዘን ወደ ባንክ ብንመጣ ያንን ወርቅ መውሰድ እንችላለን። የምስክር ወረቀቱን ወይም የብር ኖቱን ይዘን እስከመጣን ድረስ፤ ‘በፈለግን ጊዜ፤ በጠየቅን ጊዜ’ ያንን ወርቅ መውሰድ መብታችን ነው። ‘ላምጪው እንዲከፈል ህግ ያስገድዳል’ ተብሎ ኖቶቹ ላይ ቢፃፍ እንዴት ትርጉም እንደሚኖረው አየህ?...
“በእርግጥ፣ ባንክ ሄደን ወርቅ ማውጣት አያስፈልገንም። ደመወዝ መክፈል ወይም እቃ መግዛት ሲያስፈልገን፤ የባንክ ኖቶቹን (የምስክር ወረቀቶቹን) እንጠቀማለን። ደሞዝ ስንቀበልም እንዲሁ ቀጣሪያችን የባንክ ኖቶችን ይሰጠናል። ወረቀቶች ቢሆኑም ዋጋ አላቸው ብለን አምነን እንቀበለዋለን። መተማመኛችን ምንድ ነው? ኖቶቹ ላይ... ‘payable to the bearer on demand ... ላምጪው እንዲከፈለው ህግ ያስገድዳል’ የሚል ተፅፎበታል። የብር ኖቶቹን ይዞ ለሚመጣ፣ ባንኩ ወርቅ ይከፍላል። ወረቀቶቹ ትርጉም የሚኖራቸው፤ ባንክ ውስጥ የተቀመጠውን ወርቅ ስለሚወክሉ ነው። ወርቅን የሚወክሉ ምስክር ናቸው። ትክክለኛው የገንዘብ ትርጉም ይሄ ነው። የሆነ አይነት ምርትን (ለምሳሌ ወርቅን) የሚወክል፣ መገበያያ የምስክር ወረቀት... እውነተኛ ገንዘብ ነው። አንደኛው ባንክ፣ ተቀማጭ ወርቅ ሳይኖረው የብር ኖቶችን በገፍ ላሳትም ቢልስ? አይችልም። ተቀማጭ ገንዘብ ሳይኖረው፤ ቼክ ፈርሞ እንደመስጠት ይሆናል። ኖቶቹን ይዞ ለሚመጣ ሰው ወርቅ መክፈል የግድ ነዋ። ‘ላምጪው እንዲከፈል ህግ ያስገድዳል’ ይሉሃል ይሄ ነው...
“ዛሬ ግን ይሄ ሁሉ ቀርቷል። የብር ኖቶች (የምስክር ወረቀቶች) በገፍ ይታተማሉ። ግን ምንንም አይወክሉም። ምስክርነታቸው የውሸት ነው። የልምድ ነገር ሆኖ፤ ‘ላምጪው እንዲከፈል ህግ ያስገድዳል’ ተብሎ ተፅፎባቸዋል። ግን የሚከፈል ነገር የለም። የሚከፈል ነገር ስለሌለም፤ የብር ኖቶችን በገፍ ማሳተም ይቻላል። የብር ኖቶቹ ቀስ በቀስ ዋጋ ያጣሉ፤ ብር ይረክሳል፤ የዋጋ ንረት የእለት ተእለት ሕይወታችን ይሆናል... ሆነ እንጂ...

የሰይፉ ፋንታሁን ትልቁ ችሎታ
“ዛሬ እውቀትም ሆነ ገንዘብ ትርጉም ያጡበት ዘመን ላይ ነን። በትክክለኛው ትርጉም እንሂድ ከተባለማ፤ ‘እውቀት’ ማለት የማምረት ብቃት ማለት ነው። ‘ገንዘብ’ ማለት ደግሞ፤ የምርት መጠን ማለት ነው - የምርት መጠንን የሚወክል ነው። ‘እውቀት ይሻላል ወይስ ገንዘብ? እውቀት ይበልጣል ወይስ ገንዘብ?’ ብሎ መከራከር ምን ማለት እንደሆነ ተመልከት። ‘የማምረት ብቃት ይበልጣል ወይስ የምርት መጠን?’ ብሎ እንደመከራከር ይሆናል። የማምረት አቅም (እውቀት) ከሌለ፤ ...የምርት መጠን መለኪያ (ገንዘብ) አይኖርም። የምርት መጠን ከሌለ፤ የማምረት ብቃት ዋጋ የለውም። እነ ሠራዊት ፍቅሬ፤ ‘እውቀት ወይስ ገንዘብ?’ ሲሉ የዋሉት በከንቱ ነው።
“በእርግጥ ጥያቄውና ክርክሩ መነሻ አለው። እነ ሠራዊት ፍቅሬ ከጥንት የፈላስፎች ጥያቄና ክርክር፤ ለወግ ያህል አንዷን አባባል ቀንጭበው ቁምነገረኛ ለመምሰል አልሞከሩም ማለቴ አይደለም። ግን፤ ለወግ ያህል ቁምነገረኛ መምሰል፤ ለማንም አያምርበትም። የግድ ፈላስፋ መሆን አለባቸውም አላልኩም። ሁሉም አቅሙን አውቆ፣ የአቅሙን ያህል እስከ ሰራ ድረስ ችግር የለም። ከምሳሌ ፕሮግራሙን የቀልድና የቧልት መዝናኛ ቢያደርጉት ይሻል ነበር...
“አንድ ያዝናናችኝ አባባል ልጠቅስልህ እችላለሁ። ‘እስቲ ሆቴል ግባና፤ በእውቀትህ ምግብ አዝዘህ ስትበላ እናያለን’ የሚል ነገር ሰምቻለሁ። ገንዘብ ከሁሉም ነገር እንደሚበልጥ ለማሳየት፤ ‘ገንዘብ ካለ የቦይግ መንገድ አለ’ ብሎ እንደመከራከር ነው። እውቀት ይበልጣል ብሎ የሚናገር ሌላኛው ተከራካሪ ደግሞ፤ ‘ከሰማይ የወረደ ፍርፍር የሚል መፅሃፍ አንብበሃል መሰለኝ። ፍርፍሩም ሆነ ቦይጉኮ በአዋቂዎች ነው የሚሰራው። የያዝከው ብር ላይ መሶብ ስላየህ ፍርፍር የሚሆንልህ መስሎሃል’ ብሎ ይከራከራል...። ትንሽ ያዝናናል። ለምሳሌ ሰይፉ ፋንታሁን

“ኢህአዴጐች ቆልፈው ቁልፉን ይውጡታል”
ፕሮግራሙን ቢይዘው፤ በቀልድና በቧልት ይበልጥ አዝናኝ ያደርገው ነበር። የሰይፉ ትልቁ ስጦታ ምን መሰለህ? ብዙም ወገኛነት አያጠቃውም። ከአቅሙ በላይ ቁምነገረኛ ለመምሰል ብዙም አይጣጣርም። አንዳንዴ ይሞክራል። ግን ወዲያው ወደ ቀልድና ቧልት አዝናኝነቱ ይመለሳል። በጣም ይሻላል”
ሠራዊት ፍቅሬ ላይ ነገር ይከርርበታል ይሉሃል ይሄ ነው።

Read 18764 times