Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Tuesday, 01 November 2011 13:47

አፍሪካን ትንሽ ቀለል ብሏታል ሦስተኛው አምባገነን ከጫንቃዋ ወርዶላታል!

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ድራፍት ቤት ውስጥ ሰብሰብ ብለን እንጠጣለን - ሰብሰብ እንበል እንጂ አንተዋወቅም፡፡ የሰበሰበን በጃምቦ እየተሞላ የሚሰጠን ድራፍት ነው፡፡ ርቆ የተሰቀለው የድራፍት ቤቱ ቴሌቪዥን (ኢቴቪ) የዜና እወጃ ፕሮግራሙን እያስተላለፈ ነው፡፡ በየመሃሉ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ፣ ሽብር፣ ከሻዕቢያ ጋር የሚሰሩ ተቃዋሚዎች ወዘተ የሚሉ የተለመዱ ቃላት ለብቻቸው ለጆሮዬ ይደርሳሉ፡፡ ከጐኔ ደግሞ በቅርቡ በግምገማ የተነሱ የኢህአዴግ ሃላፊዎችን በተመለከተ ክርክር ተነስቷል፡፡ አንደኛው የሃላፊዎቹን መነሳት የግል ጋዜጦች ቀድመው መዘገባቸው ትክክል አይደለም ብሎ ይከራከራል፡፡ የሚያጠግብ ማስረጃ ግን አላቀረበም፡፡ ይሄኔ ትዝ ያለኝ የአዲስ አበባ መገናኛ ብዙሃን ሹም ሽሩን በተመለከተ ያስተላለፈው ማስተባበያ ነበር፡፡ በግል ፕሬሶች የተዘገበው ሹም ሹር መሰረተ ቢስ መሆኑንና ከሃላፊነት የተነሳ አለመኖሩን ይገልፃል

- ማስተባበያው በጥቂት ቀናት ውስጥ ግን 3 የአዲስ አበባ የኢህአዴግ ሃላፊዎች በግምገማ ከስልጣን መነሳታቸው በዚያው መገናኛ ብዙሃን ተዘገበ፡፡
ይሄኔ እቺን መረጃ ማን ነው ያሾለካት በሚል ደግሞ ሌላ ግምገማ ተካሂዶ ይሆናል ብዬ አሰብኩ፡፡ ወዲያው ለምንድነው የኢህአዴግ ሰዎች የግሉን ፕሬስ እንዲህ የጠመዱት የሚል ጥያቄ በአዕምሮዬ ውስጥ ተጫረብኝ፡፡ ምናልባት ጠንካራ ትችት ስለሚሰነዝሩባቸው፣ ስህተታቸውን ነቅሰው ስለሚያጋልጡባቸው፣ ጐዶሎአቸውን ስለሚያጐሉባቸው ወዘተ. . ስብሰለሰል ከቆየሁበት የራሴ ሃሳብ የነቃሁት ዙሪያዬን የከበቡኝ ጠጪዎች እየተነሱ ሲወጡ ነው፡፡ እኔም ሂሳቤን ከፈልኩና ልወጣ ስል ዓይኔ ባንኮኒው ላይ የተለጠፈች ማሳሰቢያ መሰል ማስታወቂያ ላይ አነጣጠረ “ቅሬታዎትን ለኛ፤ አድናቆትዎን ለጓደኛ ይንገሩ” ትላለች፡፡
ምናልባት የኢህአዴግና የግል ፕሬሱ ግንኙነት በዚህ አባባል ላይ ቢመሰረት የተሻለ ይሆን እያልኩ ከድራፍት ቤቱ ወጣሁ - ያላለቀበት ድራፍት ቤት ፍለጋ፡፡
እስቲ አሁን ደግሞ ከኢትዮጵያ ወደ አህጉሪቷ ከፍ ብለን መብረር እንጀምር፡፡ ሰሞኑን ሦስተኛውን አምባገነን መሪዋን ከጫንቃዋ ላይ ያራገፈችው አህጉራችን አፍሪካ እንዴት ቅልል እንዳላት እያሰብኩ እኔ ራሴም ቅልል ብሎኝ ነበር የሰነበትኩት፡፡ አይገርምም ግን . . . አፍሪካ እንደቀልድ ከአምባገነን መሪዎች እየተላቀቀች እኮ ነው፡፡ በ30 እና በ40 ዓመት ያላገኘችውን ዕድል በአንድ ዓመት ውስጥ ተንበሸበሸችበት፡፡
መጀመሪያ የቱኒዚያው፣ ቀጥሎ የግብፁ፣ አሁን ደግሞው የሊቢያው ጋዳፊ የዘላለም ውርስ አድርገው ሲቆጥሩት ከነበረው ሥልጣናቸው ተሽቀንጥረው ተጣሉ - የግላቸው መኖሪያ ቪላ ከሚመስላቸው ቤተመንግስት ተባረሩ፡፡ እኔ የምለው . . . ቤተመንግስት የኪራይ ቤት ዓይነት መሆኑን የሚያውቁ የአፍሪካ መሪዎች ያሉ ይመስላችኋል? አከራዩ ህዝቡ ነው . . . ስለዚህ በቃኝ ከቤቴ ውጡልኝ ሲል መውጣት የግድ ነው፡፡ አምባገነን የአፍሪካ መሪዎች ግን እንኳን ቤተመንግስቱ ሙሉ አገሪቱም የራሳቸው እየመሰላቸው ሲሸወዱ (ራሳቸውን ሲሸውዱ) ኖረዋል፡፡ ግን እስከጊዜው ድረስ ነው፡፡ (ነበር) ይኸው ጋዳፊም ብለው ብለው ከስልጣንም ከቤተመንግስትም ከዓለምም ተሰናብተዋል፡፡
እውነቴን ነው የምላችሁ . . . የጋዳፊ መጨረሻ በጣም አሳዝኖኛል፡፡ የሞቱበትን ሁኔታ ማለቴ ነው እንጂ ከሥልጣን መውረዳቸውን አይደለም፡፡ ምንም እንኳን እሳቸው ከ40 ዓመት በላይ የሊቢያን ህዝብ አንቀጥቅጠው ከገዙ በኋላም “እኔን የራበኝ ሥልጣን ነው” እንዳሉ ህይወታቸው ቢያልፍም ሥልጣንን እንኳን እስኪበቃቸው ነበር ያጣጣሙት፡፡ የተገደሉበት ሁኔታና የመሪነት ክብር ሳያገኙ በምስጢር መቀበራቸው ግን ልብ ይነካል፡፡
አሁን በሥልጣን ላይ ያሉት የአህጉራችን አምባገነኖች ከጋዳፊ አሳዛኝ መጨረሻ ምን ተምረው ይሆን? እያልኩ ሳሰላስል ነበር፡፡ እንደው ዝም ብዬ አነሳሁት እንጂ አምባገነኖች ራሳቸውን በመሸወድ የተካኑ ስለሆኑ ምንም የሚማሩት እንደሌለ ግልፅ ነው፡፡
ለምሳሌ በአምባገነንነታቸው ዓለም ያጨበጨበላቸው የኢራኑ መሪ “የራሷ አሮባት የሰው ታማስላለች” እንዲሉ “እንዴት ሰው የራሱን ህዝብ በአውሮፕላን ያስደበድባል” ሲሉ ጋዳፊን ነቅፈው ነበር - በህዝብ አመፁ ጊዜ፡፡
መቼም ጋዳፊ ይሄን ሲሰሙ “ያልተነካ ግልግል ያውቃል” ብለው እንደተረቱ መገመት አያቅትም (የተለመደውን የጋዳፊ ዘለፋ ትተነው ማለት ነው) እናም አምባገነኖች ከሌላው መማር ሳይሆን ራሳቸውን መሸወድ ብቻ እንደሚያውቁ ለማስታወስ ያህል ነው፡፡
ልክ እንደጋዳፊ ሁሉ ዚምባቡዌ የራሳቸው የግል ንብረት የምትመስላቸው ሙጋቤ፤ ባለፈው ሳምንት ስለተገደሉት ጋዳፊ ቢጠየቁ ምን የሚሉ ይመስላችኋል? ፍርጥም ብለው “የእጁን ነው ያገኘው . . . እንደኛ ለህዝቡ ነፃነትና ዲሞክራሲ ቢያሰፍን ከውርደት ይድን ነበር” እንደሚሉ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ነው፡፡ እውነቱ ግን ሙጋቤም ከጋዳፊ ቢብሱ እንጂ የማያንሱ የለየላቸው አምባገነን መሆናቸው ነው፡፡ ለጊዜው ግን እሳቱ ወደሳቸው ቤት ስላልደረሰ ራሳቸውን እየሸወዱ ይቆያሉ፡፡ እሳቱ (የህዝብ ዓመፅ) የመጣ ጊዜ ግን ዕጣቸው ተመሳሳይ እንደሚሆን እሳቸው ሊያውቁ ባይፈልጉም እኛ እናውቃለን . . . (እግዚአብሔር ይሁናቸው!)
እኔ የምለው ግን እኚህ ጋዳፊ የ250ሺ ዶላር ስጦታ ያበረከቱላቸዉን ኮንዶሊዛ ራይዝ በቅርብ አግኝተው እንደሚያፈቅሯቸው ነግረዋቸው ይሆን ወይስ የሴትየዋን የፎቶ አልበሞች ታቅፈው ለብቻቸው ሲብሰለሰሉ ነው ህይወታቸው ያለፈው? የፋይናንስ አቅም ከተገኘ እኮ አሪፍ የሮማንቲክ ኮሜዲ ፊልም ይወጣው ነበር - ለኦስካር የሚታጭ!!
ተዓበኛ የነበሩት የሊቢያው መሪ ጋዳፊ፣ እንግሊዛዊው ባለቅኔና ፀሃፌ ተውኔት ሼክስፒር አረብ (ሙስሊም) ነበር ማለታቸውን ሰሞኑን በወጣ አንድ የእንግሊዝኛ ጋዜጣ ላይ አንብቤ ግርም አለኝ፡፡ ማስረጃቸው ደግሞ ምን መሰላችሁ? ሼክ የሚለው ሁለት የስሙ ፊደላት ናቸው፡፡ ይሄን እንኳን “ቢሆን ነው” ብለን ብናልፈው ሳይሻል አይቀርም፡፡ ያለዚያም ዜጋቸውን የተነጠቁት እንግሊዞች ይከራከሩበት እንጂ እኛማ በምን አቅማችን . . . ለማንኛውም ግን ሦስተኛውን አምባገነን የተገላገለችው አፍሪካችን ትንሽ ቀለል ብሏት ሰንብታለች፡፡ ግን ገና ብዙ ብዙ መገላገል የምትሻቸው አምባገነኖች እላይዋ ላይ እየጨፈሩባት ነው፡፡ እርግጥ ነው እነዚህ አምባገነኖች ከአፍሪካ ጫንቃ ላይ ራሳቸው ይወርዳሉ ተብሎ አይጠበቅም፡፡ በህዝብ ዓመፅ ከተባረሩትም ይማራሉ ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው፡፡
ከአፍሪካ ሦስት አምባገነን መሪዎች በቀይ ካርድ ሲሸኙ የየመንና የሶሪያ አምባገነኖች ግን አሁንም አሉ፡፡ እኒህና ሌሎች አምባገነኖች ቤተመንግስቱን ከህዝብ እንደተከራዩት ማን ይንገራቸው ይሆን?

 

Read 3636 times Last modified on Tuesday, 01 November 2011 13:52