Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 29 October 2011 15:12

“ቦንድ” ጉድ አፈላ - የግሪክ ቦንድ የገዙ 100 ቢሊዮን ዶላር ከሰሩ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ከቬኔዝዌላ እስከ ዩክሬን፣ ከፓኪስታን እስከ ጣሊያን... የመንግስታት እዳ አለምን አስጨንቋል
ለ”ቦንድ” ጣጣ መፍትሄ የሚያመጣ 7ሚ. ብር ሽልማት ተዘጋጅቷል
የኢትዮጵያ መንግስት እዳ እና የቦንድ ሽያጭስ እንዴት ነው?
በስልጣኔ ምንጭነት የምትታወቀው ግሪክ፤ ዛሬ ዛሬ... የኢኮኖሚ ቀውስ ቅፅል ስም ሆናለች። ቀውሱ ዛሬ ወይም ዘንድሮ የተፈጠረ ችግር አይደለም። መንግስታትና ባለስልጣናት፤ በየእለቱ “ፕሮጀክት” ይፈለፍላሉ። በማን ወጪ? ከዜጎች የሚወስዱት ከፍተኛ ቀረጥና ግብር አልበቃ ብሏቸው፤ በ”አገር” ስም እየተበደሩ እዳ ሲያከማቹ አመታትን አስቆጥረዋል። በወጪ ላይ ወጪ፤ በብድር ላይ ብድር ይከምራሉ።
አንዱ ፕሮጀክት (ለምሳሌ የውሃ ማቆር ፕሮጀክት) በገንዘብ ብክነትና በውድቀት ሲጠናቀቅ፤ በምትኩ ሌሎች ፕሮጀክቶችን ለመፈልፈል ሰበብ አይጠፋም - “ለህዝብ ጥቅምና ለስራ እድል ፈጠራ፣ ለአረንጓዴ ልማትና ለአካባቢ ጥበቃ፣ ለማህበራዊ አገልግሎትና ለመሰረተ ልማት ግንባታ” ወዘተ። የነፃ ገበያ ስርአትን የሚያንቋሽሹና የሶሻሊዝም አባዜ ያልለቀቃቸው ብዙ ምሁራን፤ በአጠቃላይ አብዛኛው ዜጋ፤ “መንግስት ኢኮኖሚ ውስጥ እጁን እያስገባ፤ እንዲህና እንዲያ ያድርግልን፤ ይሄንና ያንን ያሟላልን” እያሉ ይወተውታሉ። ብዙዎቹ ፖለቲከኞችና መንግስታትም ለዚህ ዝግጁ ናቸው። በሰበብ አስባቡ በየጊዜው የሚፈለፍሏቸው ተጨማሪ ፕሮጀክቶች ግን፤ ተጨማሪ ገንዘብ ያስፈልጋቸዋል።
በየጊዜው እያበጠ የሚሄደውን የመንግስት ወጪ ለመሸፈን፤ እንዲሁም የተጠራቀመውን ብድር ለመክፈል፤ ... በቀረጥና በግብር እያዋከቡ ዜጎችን ከማራቆት አልፈው፤ እየደጋገሙ ይበደራሉ - በእጥፍ በእጥፍ። ግን እስከመቼ? እዳው ተከማችቶ አበዳሪ እስኪጠፋ ድረስ? በእዳ ላይ እዳ እየቆለሉ ዘላለም መቀጠል አልተቻለም። ግሪክ የገባችበት ቀውስ ጥልቅ ከመሆኑ የተነሳ፤ በብዙ መቶ ሚሊዮን ዶላሮችም መፍትሄ የሚያገኝ አልሆነም።
ነገር ግን፤ ችግር የተፈጠረው በግሪክ ብቻ አይደለም። አውሮፓን ጨምሮ፤ የአለማችን በርካታ አገራት፤ ለማመን በሚያስቸግር ተመሳሳይ ቀውስ እየተነገዳገዱ ናቸው። የጣሊያን መንግስት የተከማቸ ብድር... ሁለት ትሪሊዮን፣ ስድስት መቶ ቢሊዮን ዶላር እዳ ... ለማመን አይከብድም? ከጣሊያን አመታዊ ምርት ጋር ሲነፃፀር፤ የመንግስት እዳ በሃያ በመቶ ይበልጣል - 120% መሆኑ ነው። ከኢትዮጵያ አመታዊ ጠቅላላ ምርት ጋር ሲነፃፀርማ በ80 እጥፍ ይበልጣል - የ80 አመት ምርት እንደማለት።
ለነገሩ፤ ከነ ጣሊያንና ከነግሪክ በፊት፤ እነኢትዮጵያ ይቀድማሉ - በቀውስ ለመዘፈቅ። ደግሞም አይገርምም። “ለልማት፤ ለስራ እድል ፈጠራ፤ ለህዝብ ጥቅም” በሚሉ ሰበቦች፤ የመንግስትን በጀት ማሳበጥ፤ ወጪውንም ለመሸፈን በገፍ ብድር መሰብሰብ... ኢትዮጵያን በመሳሰሉ የአፍሪካ አገራት ይብሳል። ለዚያም ነው፤ ከሁሉም ቀድመው በዘመናዊው የቀውስ ማእበል የተመቱት። የአፍሪካ መንግስታት የብድር ቀውስ፤ ከነ ግሪክ ቀውስ የባሰ እንደነበር ይገልፃል - የአለም ባንክ መረጃ። ለምሳሌ፤ በ1987 አ.ም የኢትዮጵያ መንግስት እዳ፤ ከጠቅላላ የአገሪቱ አመታዊ ምርት ይበልጥ ነበር - ወደ 150 በመቶ ያህል።
ታዲያ ኢትዮጵያን የመሳሰሉ የአፍሪካ አገራት፤ ያንን ግዙፍ የእዳ ቀውስ እንዴት ችለው ተወጡት? ...ችለው አልተወጡትም። አበዳሪዎቹ የምእራብ አገራት፤ የብድር ስረዛ ሲያደረጉላቸው፤ እዳው ከሞላ ጎደል ተቃለለ። በእርግጥ የአፍሪካ መንግስታት፤ ከእዳ ከተገላገሉ በኋላ አርፈው አልተቀመጡም። ከአገር ውስጥና ከውጭ፤ እንደገና እየተበደሩ እዳ መከመር ጀምረዋል - ለሌላ የቀውስ አዙሪት።
ለዛሬ ግን፤ የቀውሱ ባለተራ የአውሮፓ አገራት ናቸው። የአውሮፓ መንግስታት፤ እንደ አፍሪካ “አቻዎቻቸው” በለየለት እብደት እዳ ውስጥ ለመዘፈቅ ባይሯሯጡም፤ ወጪያቸውን እያሳበጡ፤ ቀስ በቀስ ዜጎችን በቀረጥ ማራቆታቸውና ብድር ማጋበሳቸው አልቀረም። ያው... ውለው አድረው ቀስ በቀስ ወደ ቀውስ አምርተዋል - በተለይ ጣሊያን፣ ስፔን፣ ፖርቱጋልና አየርላንድ።

የትሪሊዮንና የቢሊዮን እዳ
ጣሊያንን ተመልከቱ። አመታዊው የጣሊያናዊያን ጠቅላላ ምርት፤ 2.1 ትሪሊዮን ዶላር ገደማ ነው። ነገር ግን፤ አመታዊው ምርት ወደ ዜጎች ኪስ አይገባም። በየአመቱ፤ የመንግስት ፕሮጀክቶች እየተበራከቱና ወጪዎቹ እያበጡ በመጡ ቁጥር፤ በዜጎች ላይ የቀረጥና የግብር ጫና እየጨመረ ይሄዳል። ከአመታዊው የጣሊያናዊያን ምርት ውስጥ፤ 47 በመቶ ያህሉን፣ በቀረጥና በግብር መልክ፤ መንግስት ይወስደዋል። ቀላል አይደለም። ከ960 ቢሊዮን ዶላር በላይ ማለት ነው ... ሁለት መቶ የህዳሴ ግድቦችን ማስገንባት የሚችል ገንዘብ። ነገር ግን፤ መንግስት ይሄን ሁሉ ገንዘብ ከዜጎች እየወሰደም፤ በቃኝ አይልም። የበጀት ጉድለቱን ለማሟላት፤ በየአመቱ ከአገር ውስጥና ከውጭ ይበደራል - ቦንድ እየሸጠ (የብድር ምስክር ወረቀት እየሰጠ)። በእዳ ላይ እዳ ያከማቻል። ዎርልድ ኢኮኖሚክ ፎረም፤ በዘንድሮው ሪፖርቱ እንደገለፀው፤ የጣሊያን መንግስት ውዝፍ እዳ፤ ከአገሪቱ አመታዊ ምርት በላይ ሆኗል - በ2010 ከ2.6 ትሪሊዮን ዶላር በላይ።
ቀውሱ ፈጥጦ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ እየተተራመሰች ያለቸው ግሪክስ? ዘንድሮ፤ የግሪካዊያን አመታዊ ምርት 310 ቢሊዮን ዶላር ነው፤ የመንግስት ውዝፍ ብድር ደግሞ ግማሽ ትሪሊዮን (500 ቢሊዮን) ዶላር። የግሪክ መንግስት በቀረጥና በግብር ከዜጎች በአመት 100 ቢሊዮን ዶላር ያህል እየቧጠጠ ቢወስድም፤ ወጪዎቹን አደብ ሊያስገዛ ስላልፈለገ፤ የበጀት ጉድለቱን ለመሸፈን ተጨማሪ ብድር ከማግበስበስ ወደኋላ አላለም። የመንግስት ቦንድ (የመበደሪያ ምስክር ወረቀት) እየሰጠ፤ ብድር ይቀበላል።
እኤአ በ2000፤ የግሪክ መንግስት እዳ ሁለት መቶ ቢሊዮን ነበር። በአምስት አመት ውስጥ ውዝፍ እዳው በመቶ ቢሊዮን ዶላር ጨመረ። እንደገና ከሁለት አመት በኋላ ተጨማሪ መቶ ቢሊዮን ዶላር ... እየተበደረ እዳ የማከማቸት እርምጃው እየፈጠነ ... እንደገና ከአንድ አመት በኋላ ተጨማሪ መቶ ቢሊዮን ዶላር... ይሄው ግማሽ ትሪሊዮን ደርሷል። የመንግስት እዳ መጨረሻው ይሄው ነው - ፍሬንና መሪ እንደሌለው መኪና። በቃ... አዲስ ብድር ቢያገኝ እንኳ፤ ገንዘቡ እጁ ውስጥ ሊገባ ቀርቶ፤ የውዝፍ እዳ ወለድ ለመክፈል ሊበቃው አልቻለም። መፍትሄውስ?
ማምለጫ ዘዴ 1 -
“በቃ መክፈል አልችልም”

የአፍሪካ መንግስታት ከዚህም ከዚያም እየተበደሩ በቆለሉት እዳ ሳቢያ፤ አህጉሪቱ በኢኮኖሚ ቀውስ የተናጠች ጊዜ፤ ሁነኛ መፍትሄ አልተገኘም ነበር። መፍትሄ ሲጠፋ፤ “መክፈል አይችሉም” ተብሎ እዳው ተሰረዘ - በአበዳሪዎቹ የምእራብ መንግስታት። ታዲያ፤ ዛሬ ራሳቸው የምእራብ መንግስታት በእዳ ውስጥ ተነክረው የአውሮፓን ምድር በቀውስ ሲንጧትስ መፍትሄው ከየት ይመጣል?
በሰበብ አስባቡ ወጪያቸውን መረን እየለቀቁ፤ በእዳ ላይ እዳ የሚከምሩ መንግስታት፤ “ከቀውሱ ለማምለጥ” በተለምዶ የሚጠቀሟቸው አራት ዘዴዎች አሉ። አንደኛው ዘዴ፤ የአፍሪካ መንግስታት እንዳደረጉት፤ “እዳዬን መክፈል አልችልም” በማለት የብድር ስረዛ መጠየቅ ነው - ኪሳራውን ራሱ አበዳሪው እንዲችለው። ዘዴው ለአውሮፓ መንግስታት ይሰራል? አበዳሪዎቹኮ፤ የአውሮፓ ባንኮችና ዜጎች ናቸው።
የአውሮፓ መንግስታት እዳቸውን ካልከፈሉ፤ ዜጎች እንደምንም የቆጠቡት ተቀማጭ ሂሳብ ውሃ በላው ማለት ነው። አይን ካወጣ ዝርፊያ አይለይም። ዜጎች፤ የመንግስትን ቦንድ እየተቀበሉ ለመንግስት ገንዘብ ሲሰጡና ሲያበድሩ፤ ገንዘባቸውን ባንክ ውስጥ ለቁጠባ እንዳስቀመጡት ነው የሚቆጠረው። ባንኮችም ቢሆኑ፤ ለመንግስት ብድር የሚሰጡት፤ ከጓሮ ገንዘብ እየሸመጠጡ አይደለም - ባንክ ውስጥ ዜጎች ለቁጠባ የሚስቀምጡትን ገንዘብ በመጠቀም እንጂ። መንግስት እዳውን የማይከፍል ከሆነ፤ ዜጎች የያዙት ቦንድ ተራ ወረቀት ይሆናል። ባንኮች ይከስራሉ፤ የዜጎች የቁጠባ ሂሳብ ቀልጦ ይቀራል።
የአውሮፓ መንግስታት ያከማቹት ከ10 ትሪሊዮን ዶላር በላይ የእዳ ቁልል መልሰው የማይከፍሉ ከሆነ፤ በርካታ የአውሮፓ ባንኮች ከስረው፤ የብዙ ዜጎች ቁጠባ በአንድ ማግስት ብን ብሎ ይጠፋል። ሙሉ ለሙሉ ባይሆን እንኳ፤ በከፊል እዳቸውን ላለመክፈል ቢወስኑስ? የዚያኑ ያህል፤ ዜጎች የቁጠባ ገንዘባቸውን ያጣሉ። በከፊል የእዳ ስረዛ? ለመፍትሄ ያስቸገረው የግሪክ መንግስት እዳ፤ በዚሁ አቅጣጫ እንዲጓዝ ሃሙስ እለት ተወስኗል። ከግሪክ መንግስት፤ ቦንድ እየተቀበሉ ገንዘብ ያበደሩ ዜጎችና ባንኮች፤ ግማሽ ያህል ገንዘባቸው አይመለስላቸውም። አስር ሺ ዩሮ በቁጠባ ለማስቀመጥ ቦንድ የገዛ ሰው፤ ከአመት በኋላ ገንዘቡን ከነወለዱ ለመቀበል ሲጠብቅ፤ 5ሺ ዩሮ ብቻ ይመለስለታል - ቀሪው ቁጠባ ቀልጦ ይቀራል። ለግሪክ መንግስት ሲያበድሩ የነበሩ ዜጎችና ባንኮች በዚህ መንገድ፣ 100 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ ይደርስባቸዋል ተብሏል።

ታክስና ቀረጥ አያኮራም
ወደ ሁለተኛው ዘዴ እንሸጋገር - የአለም ኢኮኖሚክ ፎረም በዘንድሮ ሪፖርቱ ከጠቀሳቸው ዘዴዎች መካከል አንዱን በማስቀደም። ብዙ መንግስታት የተከማቸ እዳቸውን ለመሸፈን፤ ዜጎችን በቀረጥና በግብር ያዋክባሉ። ነገር ግን፤ ዘዴው በየትም አገር፤ በኢትዮጵያም ሆነ በአሜሪካ፤ በግሪክም ሆነ በጣሊያን፤ ጥፋትን እንጂ በጎ ውጤትን አያስገኝም። በጎ ውጤት ቢያስገኝ ኖሮማ፤ የአውሮፓ መንግስታት ገና ድሮ ችግሮቻቸውን መፍታት በቻሉ ነበር። ከጊዜ ወደ ጊዜ፤ ተጨማሪ ቀረጥና ግብር በዜጎች ላይ ሲጭኑ ነው የኖሩት። በአሜሪካም እንዲሁ።
ነገር ግን፤ መንግስት ተጨማሪ ቀረጥና ግብር ከዜጎች እየነጠቀ፤ ይበልጥ ገንዘብ ሲያባክን፤ የዜጎች ኢንቨስትመንት ይዳከማል፤ የስራ እድል ይመናመናል፤ የኑሮ ደረጃ ይወርዳል፤ ኢኮኖሚው ይዳከማል፤ ጭራሽ የመንግስት የቀረጥና ግብር ገቢም ይቀንሳል። የቀረጥና የግብር ጫና መከመር፤ በአውሮፓ አገራት እንደሚታየው፤ ውሎ አድሮ ችግርን ያባብሳል እንጂ፤ መፍትሄ አይሆንም።
አብዛኞቹ የአውሮፓ መንግስታት፤ ከዜጎች አመታዊ ገቢ ውስጥ ቢያንስ አንድ ሶስተኛውን በቀረጥና በግብር መልክ ይወስዳሉ። ከቢዝነስ ድርጅቶች ትርፍ፤ ሃምሳ በመቶ በላይ ወደ መንግስት ኪስ ይገባል። የአንዳንዶቹማ እስከ 65 በመቶ ይደርሳል። ታዲያ፤ በየጊዜው አዳዲስ የቀረጥ አይነት እየፈለፈሉና ነባሩንም ቀረጥ እያከበዱ የመጡ መንግስታት፤ በብድር ከመዘፈቅ ድነዋል? በጭራሽ። እንዲያውም፤ በታክስ ጫና ሳቢያ ቢዝነሶች እየተዳከሙ፤ ኢኮኖሚውም እየተሸረሸረ ስለሚሄድ፤ መንግስታት የተመኙትን ያህል ቀረጥ ማግበስበስ ያቅታቸዋል። እናም ይበደራሉ። ለነገሩ፤ በዜጎችና በቢዝነሶች ላይ የታክስ ጫናው ከመጠን በላይ ከመክበዱ የተነሳ፤ ተጨማሪ ጫና ማወጅ የትም እንደማያደርስ ብዙዎቹ መንግስታት ያውቁታል - አለበለዚያማ እየተስገበገቡ የቀረጥ አዋጆችን በየእለቱ ከመፈብረክ ወደኋላ አይሉም ነበር። አሁን ባለው ሁኔታ ከባድ ቀረጥ መጨመር፤ የስልጣን ዘመንን እንደሚያሳጥር ያውቁታል። በዝርፊያ ለተፈጠረ የእዳ ችግር፤ ተጨማሪ ዝርፊያ መድሃኒት አይሆንም።
“በአውሮፓና በአሜሪካ፤ ቀረጥ መክፈል ያኮራል” እየተባለ በአገራችን የምንሰማው ወሬ፤ ተራ የፈጠራ ፕሮፖጋንዳ ነው። የቀረጥ ጫና በእጅጉ የተጠላ መሆኑን ለማየት፤ በአሜሪካ ኮንግረስ ውስጥ የሚገኙ የሪፐብሊካ ፓርቲ አባላትን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል። “በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ፤ የቀረጥ ጭማሪን የሚያስከትል ህግ እንዳይፀድቅ እቃወማለሁ” በማለት ቃል እየገቡ ነው በምርጫ አሸናፊ ለመሆን የበቁት። የቀረጥ ጭማሪን እንደሚቃወም፤ በቃል ብቻ ሳይሆን በፊርማ ጭምር አቋሙን ያልገለፀ የሪፐብሊካ ፓርቲ ፖለቲከኛ፤ በምርጫ የማሸነፍ እድል የለውም ማለት ይቻላል። እንዲያውም የቀረጥ ጫናው ወደ 24 በመቶ እንዲቀንስ እጥራለሁ ብለው ቃል ይገባሉ። በቀጣዩ አመት ለፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እጩ ሆነው ለመቅረብ እየተወዳደሩ የሚገኙ ፖለቲከኞችማ፤ የቀረጥ ጫናው ወደ 15 በመቶ ወይም ወደ 9 በመቶ እንዲወርድ አደርጋለሁ በማለት ቅስቀሳ እያካሄዱ ነው። በአጠቃላይ፤ የቀረጥ ጭማሪ ለአውሮፓ መንግስታትም ሆነ ለአሜሪካ መፍትሄ ሊሆን አይችልም።

ነፃ ገበያ፤ ሁሉም የአቅሙን ያህል
ሶስተኛው ዘዴ፤ የመንግስት በጀት (ወጪ) እንዲቀንስ ማድረግ ነው። ያው... መንግስት፤ በየአቅጣጫው እጆቹን ኢኮኖሚ ውስጥ እያስገባ፤ የፕሮጀክቶች አይነት እየፈለፈለ፤ የቢዝነስ ስራ ለማሰናከል የቢሮክራቶች መአት እያጨቀ ... ገንዘብ ማባከኑን ማቆም አለበት - ወጪዎቹን መቀነስ ከፈለገ። አሁን የአሜሪካ ኮንግረስ፤ በተወሰነ ደረጃም የእንግሊዝ ጠ/ሚ፤ የመንግስትን ወጪ ለመቀነስ እየሞከሩ አይደል? እዳ እየተደራረበ እንደ ግሪክ ከመሆናቸው በፊት፤ የመንግስትን ወጪ በመቀነስ እዳ ማቃለል እንደሚያስፈልግ በርካታ የአሜሪካና የእንግሊዝ ፖለቲከኞች እየተገነዘቡ መጥተዋል።
ለምሳሌ፤ በአሜሪካ ለፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እጩ ለመሆን እየተወዳደሩ የሚገኙት ሮን ፖል፤ ስድስት አላስፈላጊ የሚኒስቴር መስርያ ቤቶችን በመዝጋትና 200ሺ አላስፈላጊ የመንግስት ቢሮክራቶችን በማሰናበት በአመት የ1 ትሪሊዮን ዶላር ወጪንና ብክነትን ማዳን ይቻላል ብለዋል። ወደ መንግስት ገብቶ ይባክን የነበረ 1 ትሪሊዮን ዶላር፣ ወደ ዜጎች ኪስ ተመልሶ ኢንቨስት ሲደረግ ምን ያህል የኢኮኖሚ ጥቅም እንደሚያስገኝ አስቡት። ግን የሮን ፖል እቅድ ተግባራዊ ይሆናል? በእርግጥ፤ የግሪክ ፖለቲከኞች፤ ባለቀ ሰአት የመንግስትን ወጪዎች ለመቀነስ መፍጨርጨር ጀምረዋል - ለምሳሌ ከ100ሺ በላይ አላስፈላጊ ቢሮክራቶችን በማሰናበት። እስቲ አስቡት፤ መጀመሪያውኑ ያ ሁሉ አላስፈላጊ የቢሮክራት መአት ለምን ታጨቀ? ስራ ፈጠራ?
መንግስት እጆቹን ኢኮኖሚ ውስጥ ከማስገባትና ገንዘብ ከማባከን እንዲቆጠብ ማድረግ፤ ትክክለኛው መፍትሄ ቢሆንም፤ ብዙዎቹ መንግስታት አይፈልጉትም። መረን የለቀቀ ወጪ... ሱስ ሆኖባቸዋል። የነፃ ገበያ ስርአትን የሚያንቋሽሹ በርካታ ምሁራንም ይህን ሁነኛ መፍትሄ አይወዱትም። በዚያ ላይ፤ መንግስት ኑሮሯቸውን የሚያሻሽልላቸው የሚመስላቸው ብዙ ዜጎች አሉ - የመንግስት ወጪ እንዳይቀንስ የሚጮሁ። ስለዚህ በርካታ መንግስታት ወጪያቸውን ከመቀነስ ይልቅ ሌላ ማምለጫ ዘዴ ይፈልጋሉ።

ወጪው ወረቀት ነው
- ገንዘብ ማተም
አራተኛው ዘዴ ላይ ደርሰናል። በጣም የተለመደና በተለያየ ጊዜ ሁሉንም አገራት ያዳረሰ የማምለጫ ዘዴ፤ የብር ህትመት ነው - የገንዘብ ኖት ህትመት። “የዋጋ ግሽበት” ይሉታል ይህንን ዘዴ አንዳንዶች (ለምሳሌ የአለም ኢኮኖሚ ፎረም፤ በዘንድሮው ሪፖርት ከዘረዘራቸው ሶስት የምምለጫ ዘዴዎች መካከል አንዱ፤ “የዋጋ ግሽበት” ነው ብሎ ጠቅሶታል)።
የዋጋ ንረት እና የገንዘብ ህትመት... ትርጉማቸው ያው ነው። የዋጋ ንረት እንዲሁ በአጋጣሚ የሚፈጠር ችግር ሳይሆን፤ መንግስታት ሆን ብለው የሚፈጥሩት የማምለጫ ዘዴ ነው። መንግስት በህትመት ገንዘብ ሲያባዛ፤ “ገንዘብ ይረክሳል፤ ይበረዛል”። የሸቀጦች ዋጋ ደግሞ ይንራል። ዘዴው መንታ ደረጃዎች አሉት። በቅድሚያ የወረቀት ገንዘብ አትሞ እዳውን መክፈል ይጀምራል - ፎርጅድ ብር አትማችሁ ብድር እንደመክፈል ቁጠሩት። በመንግስት ሲታተም ህጋዊ ከመሆኑ በስተቀር፤ ከፎርጅት ጋር ብዙም ልዩነት የለውም። ።
ገንዘብ በገፍ ሲታተም፤ በዜጎች እጅ ያለው ገንዘብ ይበረዛል፤ ይረክሳል፤ የዋጋ ንረት ይፈጠራል። እዚህ ላይ ነው፤ ሁለተኛውን ደረጃ የምናገኘው። የሸቀጦች ዋጋ ሲንር፤ የመንግስት እዳ ይቃለላል። እንዴት? ለምሳሌ ከአምስት አመት በፊት መንግስት ቦንድ አስይዞ 10ሺ ብር ተበደረ። አበዳሪዎቹ ዜጎች ናቸው - አስር የቢሮ እቃዎችን የሚገዙበትን ገንዘብ ቆጥበው ቦንድ የገዙ ዜጎችት።
ዛሬ ከአምስት አመት በኋላ፤ መንግስት ገንዘቡን ከነወለዱ 13ሺ ብር ይመልስላቸዋል። አበዳሪዎቹ አትርፈዋል ወይስ ከስረዋል? የሸቀጦች ዋጋ ከመቶ ስልሳ ፐርሰንት በላይ ስለናረ፤ አስር የቢሮ እቃዎችን ለመግዛት፤ 26ሺ ብር ያስፈልጋቸዋል። ስለዚህ አምስት ብቻ ነው መግዛት የሚችሉት። አስር የቢሮ እቃዎችን መግዛት ይችል የነበረ ገንዘብ አበድረው፤ ከአመታት በኋላ አምስት የቢሮ እቃዎችን መግዛት የሚችል ገንዘብ ተመለሰላቸው - ግማሽ ሃብታቸውን መንግስት ሳይመልስላቸው ቀርቷል ማለት ነው። ያው... የግሪክ መንግስት እንዳደረገው፤ “ያበደራችሁኝን ግማሽ ያህል ብቻ እመልሳለሁ” እንደማለት ነው። የተቆለለውን እዳ መክፈል ያቃተው መንግስት፤ በገፍ ገንዘብ ሲያትም፤ የዜጎችን ሃብት በከፊል እንደወሰደ ወይም እንደዘረፈ ይቆጠራል የሚባለው ለምን እንደሆነ አያችሁ? ገንዘብ ስለረከሰና ስለተበረዘ፤ የዜጎች ገንዘብ የድሮው ያህል ዋጋ አይኖረውም።
መንግስታት ከእዳ ለማምለጥ፤ የብር ህትመትንና የዋጋ ንረትን እንደማምለጫ ዘዴ ቢጠቀሙበትም፤ የዜጎችን ሃብት በመሸርሸርና ኢኮኖሚውን እያዳከመ ድህነትን ስለሚያባብስ፤ ዜጎችንም በኑሮ ውድነት ስለሚያማርር፤ ውሎ አድሮ ውጤቱ ለአገርም ለመንግስትም አይበጅም - አገርን ያናጋል፤ በምርጫ ወቅት የስልጣን እድሜንም ያሳጥራል። እንዲያም ሆኖ፤ የግሪክ እና የጣሊያን መንግስታት፤ በብር ህትመት አማካኝነት ከእዳ የማምለጥ እድል የላቸውም። እንዳሰኛቸው ገንዘብ ማተም አይችሉምና። በርካታ የአውሮፓ አገራት በጋራ የሚጠቀሙበትን ዩሮ፤ በዘፈቀደ ለማተም ከሞከሩ፤ ፎርጅድ እንደሰሩ ይቆጠራል - እንደ ዝርፊያ ወንጀል። ታዲያ ምን ተሻለ?

የሚያሸልም ጥያቄ
በእዳ የተዘፈቁት መንግስታት፤ ኢኮኖሚ ውስጥ እጃቸውን እያስገቡ ከማማሰል እየተቆጠቡ፤ መረን የለቀቀ ወጪያቸውን በመቀነስ ደረጃ በደረጃ እዳቸውን ለማቃለል ቢጣጣሩ አይሻልም? ከምር ቢጣጣሩ እንኳ፤ ለአመታት የተከማቸው ችግር ከባድ ፈተና ስለሆነ፤ ከነጀርመን ጊዜያዊ እገዛ ቢያገኙስ? እነ ጀርመንም ቢሆኑ፤ የራሳቸው ችግር አለባቸው። ከጀርመናዊያን በሚሰበሰብ ቀረጥ፤ አባካኝ መንግስታትን መደጎም ለዘለቄታው አያዋጣም። በዚያ ላይ ገደል አፋፍ ላይ የደረሱት የግሪክና የጣሊያን፤ የስፔንና የፖርቱጋል መንግስታት፤ ከእዳ ለመውጣት ከምር ለመጣጣር የቆረጡ አይመስሉም - እዚህና እዚያ የተወሰኑ ወጪዎችን ለመቀነስ ሞካከሩ እንጂ፤ ለዘለቄታው እጃቸውን ከኢኮኖሚው ውስጥ የማስወጣትና ወጪያቸውን ለዘለቄታው የመቀነስ ፅኑ ሃሳብ አይታይባቸውም። እዚህ ላይ ነው፤ 7 ሚ. ብር የሚያሸልም ጥያቄ የሚመጣው።
የግሪክ መንግስት ከእዳ ቀውስ መውጣት ካልቻለ፤ ከዚያም የጣሊያንና የስፔን መንግስታት ከተጨመሩበት... የኢኮኖሚ ቀውሱ በእነሱ ብቻ ታጥሮ አይቀርም። በዩሮ የሚገበያዩ 17 የአውሮፓ አገራት በሙሉ፤ በከፍተኛ የኢኮኖሚ ቀውስ.. አብረው ተባብረው እንጦሮጦስ ይወርዳሉ፤ ሌሎቹ የአውሮፓ አገራትም እንዲሁ። ከአለም ጠቅላላ ምርት ሩብ ያህሉን የሚያመርቱ አገራት በቀውስ ሲታመሱ፤ ሌሎች አገራትም መንገዳገዳቸው አይቀርም። ይህ ከመሆኑ በፊት፤ ገደል አፋፍ ላይ የደረሱት መንግስታት፤ ለምሳሌ ግሪክ ከሌሎቹ የዩሮ አገራት ተነጥላ እንድትወጣ ቢደረግስ?
ተያይዞ ገደል ከመግባት፤ ሁሉም የየራሱን ጣጣ እንዲችል በፍቺ መነጣጠል። እንግሊዝ ውስጥ የሚገኝ፤ ፖሊሲ ኤክስቼንጅ የሚባል የጥናትና ምርምር ተቋም ነው ይህን ሃሳብ ያቀረበው። የፍቺ ጉዳይ አፍጥጦ መምጣቱ አይቀርም የሚሉት የተቋሙ ዳሬክተር፤ በዘፈቀደ የሚከናወን የተዝረከረከ ፍቺ የአውሮፓንና የአለምን ኢኮኖሚ ስለሚያቃውስ ከወዲሁ ሊታሰብበት ይገባል። ግሪክ ከዩሮ ግብይት ብትነጠል፤ የግሪክ መንግስትም እዳውን ለመክፈል የራሱን ገንዘብ በገፍ ማተም ቢጀምር፤ ከዩሮ እና ከዶላር ጋር የሚኖረው የምንዛሬ መጠን ማሽቆልቆሉ አይቀርም። መንግስት የምንዛሬ መጠኑን በመመሪያ ልቆጣጠር ሲል የሚፈጠረው ችግር ምን ያህል ነው? በዩሮ የቁጠባ ሂሳብ ያስቀመጡ የግሪክ ዜጎች፤ ሃብታቸው በአንድ ማግስት የሚሟሟ ከሆነ፤ መፍትሄው ምን ይሆናል?
ጉዳዩ በበርካታ ፈተናዎች የተከበበ ከባድ ጥያቄ ነው። ለዚህ ጥያቄ አሳማኝ የመፍትሄ ምላሽና ትንታኔ የሚያቀርብ ሰው 250ሺ ፓውንድ ወይም 7ሚ. ብር ገደማ ሽልማት ያገኛል ብሏል - ተቋሙ።
የሽልማት ገንዘቡን ለተቋሙ ለመለገስ ሃሳብ ያቀረቡት እንግሊዛዊው የቢዝነስ ባለሃብት ሲሞን ወልፍሰን፤ አሁን የተዘጋጀው ሽልማት በኢኮኖሚክስ መስክ ከኖቤል ሽልማት ቀጥሎ ከፍተኛው እንደሆነ ተናግረዋል። መንግስታት ባከማቹት ችግር ምክንያት የተፈጠረው ጥያቄ፤ ከባድና ፈታኝ ነው። ያንን የሚመጥን ሽልማት ያስፈልጋል ብለዋል - ወልፍሰን። ውድድሩ እስከ ጥር መጨረሻ ድረስ ክፍት ነው - መወዳደር ለሚፈልግ ሁሉ።
ምናልባት፤ ለአገራችንም እንደአቅሚቲ ተመሳሳይ ውድድር ማዘጋጀት ሳይጠቅም አይቀርም - በዋጋ ንረቱና በኑሮ ውድነቱ ዙሪያ። የቦንድ ሽያጭ ጉዳይም ከወዲሁ ቢታሰብበት መልካም ነው። ሃያ ቢሊዮን ገደማ የኤልፓ ቦንድ እዳ፤ ለህዳሴ ግድብ የተሸጠ ከ7 ቢሊዮን ብር በላይ እዳ፤ የግል ባንኮች ቦንድ እንዲገዙ በሚያስገድድ መመሪያ የተወሰደ ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት እዳ... በየጊዜው ከቻይና የሚመጣው ብድር ሲጨመርበት... አሳሳቢነቱ አይጠራጠርም። የታሪክንና የአለም ሁኔታን በማየት ትምህርት መውሰድ፤ አስቀድሞ መመርመርና መዘጋጀት ያስፈልጋል። ደግሞስ፤ ሁነኛ መፍትሄ ይምጣ እንጂ፤ አገርን ለማዳን 7ሚ. ብር መሸለም ምንድነች? ቢሊዮን ብሮች በከንቱ እየባከኑ የለ!

Read 4536 times