Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 15 October 2011 13:00

የቴቬዝ ጉዳይ አለየለትም

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ቴቬዝ በማን ሲቲ የመሰለፉ ጉዳይ አብቅቶለታል ያለው ማንቺኒ ትናንት አስተያየቱን ለስለስ በማድረግ ተጨዋቹ ለክለቡ ይጫወት አይጫወት የማውቀው ነገር የለም ሲል ተናገረ፡፡ ሮበርቶ ማንቺኒ ሰላም መፈለጉን በሚያሳይ ሁኔታ ቴቬዝን በቤቱ ተገኝቶ እንዲያወያየው የጋበዘ መሆኑን ከሰሞኑ የተሰሙ ዘገባዎች እያናፈሱ ቢሆኑም ተጨዋቹ በዚህ ጉዳይ ላይ ምንም ምላሽ አልሰጠም፡፡ ቴቬዝ በጉዳዩ ላይ ይቅርታ ከጠየቀ ወደ ዋናው ቡድን ሊመለስ እንደሚችልም ፍንጭ የሰጠው ማንቺኒ አሁን ትኩረቱ ክለቡ ስለሚያደርጋቸው ጨዋታዎች መሆኑን እየገለፀ ነው፡፡ የማን ሲቲ አስተዳደር በቴቬዝና በማንቺኒ በጉዳዩ ላይ የሚያደርገውን ምርመራ አጠናቅቋል የተባለ ሲሆን ቴቬዝ ቃሉን መስጠቱ እየተጠበቀ ነው፡፡ በቴቬዝ ላይ ቀጣይ የ4 ሳምንት እግድና 1.5 ሚሊዮን ፓውንድ ክፍያ ቅጣት ሊተላለፍ እንደሚችል እየተገለፀ ሲሆን ቴቬዝ በዚህ ውሳኔ ላይ ይግባኝ ጠይቆ ክርክሩን እንደሚቀጥልም ተወርቷል፡፡

ቴቬዝ ለ2 ሳምንት በእግድ የቆየበትን ቅጣት ጨርሶ ማንችስተር ከተማ የገባው በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ነው፡፡ ቴቬዝ በማን ሲቲ ለገጠመው ውዝግብ ማናጀሮቹ በትርጉም ችግር የተፈጠረ መሆኑን እየገለፁ የክለቡ አስተዳደር በሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታው ከአሰልጣኝ ማንቺኒ ጋር ሲጋጩ ምን አጋጥሞ እንደነበር ሙሉ ቃሉን እንዲሰጥ ቀጠሮ ይዞለታል፡፡ ውዝግቡ በዚህ ሁኔታ ላይ ሲገኝ እየወጡ ያሉ ዘገባዎች በክለቡ የሁለት ዓመት ኮንትራት እየቀረው ቴቬዝ በመጪው የፈረንጆች አዲስ ዓመት መግቢያ ላይ ክለቡን ሊለቅ እንደሚችል ፍንጭ እየሰጡ ናቸው፡፡ ጁቬንትስ፤ ፓሪስ ሴንት ጀርመን፤ ሪያል ማድሪድ፤ ኮረንቲያስ፤ አንዚህልና ዌስትሃም የተጨዋቹን ዝውውር ከፈለጉ ክለቦች መካከል ይገኙበታል፡
ካርሎዝ ቴቬዝ በሳምንቱ አጋማሽ በዘመናዊው የካሪንግተን ስልጠና ማዕከል ተገኝቶ መጠነኛ ልምምድና የአካል ብቃት ምርመራ ማድረጉን የዘገበው ዴይሊ ሜል ተጨዋቹ ከሌሎች የክለቡ ተጨዋቾች ጋር እንዳይገናኝ መደረጉ ነገሮችን እያወሳሰበ ነው ብሏል፡፡ የሲቲ አስተዳደር ቴቬዝ አልገባም ብሎበታል ከተባለው ከባየር ሙኒክ ጋር የተከናወነው ጨዋታ በተያያዘ እነ ከክለቡ ጋር ባለው ኮንትራት ዙርያ በተፈጠሩ አለመግባባቶች ቃሉን እንዲሰጥ ሲያደርግ ቴቬዝ የሲቲ አምበል ቪንሰንት ኮምፓኒ የፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጨዋቾች ማህበር ተወካይ እንዲገኙለት ጥያቄ ማቅረቡም ታውቋል፡፡ ሲቲ ተጨዋቹን ለ2 ሳምንት ሲያግድ ምንም አይነት ክፍያዎቹን ያልከለከለው ሲሆን ይህን ያደረገው በአወዛጋቢው ጉዳይ ላይ በቂ ማስረጃ ለማሰባሰብ በማቀዱ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ቴቬዝ በክለቡ ውሳኔ ላይ ያስገባው ይግባኝ መፍትሄ ካላገኘ ጉዳዩን ወደ ፕሪሚዬር ሊግ አስተዳደር እንደሚወስድ የተገለፀ ሲሆን በጉዳዩ ላይ ያለው ክርክር ምናልባትም ለሚቀጥሉት ወራት እንደሚቀጥል ተገምቷል፡፡
ሳም አላድይስ ቴቬዝ በጃንዋሪ የዝውውር መስኮት ቴቬዝ በሻምፒዮንሺፕ ክለብ እየተወዳደረ ለሚገኘው የቀድሞ ክለቡ ዌስትሃም ቢገባ ይሻለዋል ያሉ ሲሆን የሲቲ ሃላፊዎች ይህን ዝውውር በፍፁም እንደማይቀበሉ ገልፀዋል፡፡የሩሲያው ክለብ አንዚሂ ማካህቻካላ ቴቬዝ በክለቡ የገጠመውን ችግር በመገንዘብ ለተጨዋቹ በደህና ክፍያ የዝውውር ጥያቄ የማቅረብ ፍላጎት እንዳለው ተዘግቧል፡፡ አንዚሂ በአሁኑ ግዜ በቀድሞው ብራዚላዊ ተጨዋች ሮበርቶ ካርሎስ እየሰለጠነ ሲሆን ሳሙኤል ኤቶ እና የራሽያው ምርጥ ተከላካይ ዩሪ ዞርኮቭ በክለቡ ይገኛሉ፡
የብራዚሉ ክለብ ኮረንቲያስም በመጭው ጃንዋሪ ላይ ቴቬዝን ለማስፈረም ፍላጎት ቢኖረውም ለተጨዋቹ ከቀረበው 40 ሚሊዮን ፓውንድ የዝውውር ሂሳብ እጅግ በሚያንስ ክፍያ እንደሚሆን ገልፃል፡፡ የዱባዩ አልዋሰል አሰልጣኝ ዲያጎ ማራዶና በበኩሉ የክለቡ ሃላፊዎች የቴቬዝን አለመረጋጋት ተንተርሰው የማስፈረም ፍላጎት እንዳለው እንደጠየቁት ሰሞኑን ሲናገር ብንፈልግ እንኳን ያለው በጀት ለሱ ከሚጠየቀው ሂሳብ 5 በመቶውን እንኳን እንደማይሸፍን እንደገለፀላቸው ተናግሯል፡፡
ማን ሲቲ በመጪው የጃንዋሪ ዝውውር ገበያ ላይ ካርሎስ ቴቬዝን ዋጋውን ቀንሶ በ20 ሚሊዮን ፓውንድ ያሰናብተዋል እየተባለ ያለው መረጃ በየዘገባው እያመዘነ ሲሆን ይህም በክረምቱ የዝውውር ገበያ ለቴቬዝ የቀረበው ሂሳብ 50 ሚሊዮን ፓውንድ በእጥፍ የወረደ ነው፡፡ በቴቬዝ ባህርይ የሲቲ ተጨዋቾች ግራ የተጋቡ ሲሆን ባለፉት ሁለት ዓመታት ለክለቡ በኮከብ ግብ አግቢነትና በአምበልነት ከፍተኛ ሚና ሲጫወት በመቆየቱ በኢስትላንድ የተነሳውን እሳት ለማብረድ ጨንቋቸዋል፡፡
የቴቬዝ ተግባር በፕሮፌሽናል እግር ኳስ ታሪክ በርካታ ህዝብ በሚከታተለው የቴሌቭዠን ስርጭት መተላለፉ ከባድ ትችት አስከትሎበታል፡፡ አንዳንድ ዘገባዎች ቴቬዝ በሲቲ በቀረው ኮንትራት እስከ 60 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ሊኖረው የሚችል ሲሆን እንደተወራው በጃንዋሪ ሊያባርረው ከወሰነ ከፍተኛ የካሳ ክፍያ ሊሰጠው ይገደዳል፡
የ27 ዓመቱ ካርሎስ ቴቬዝ ከ2009 ጀምሮ በማንችስተር ሲቲ በ91 ግጥሚያዎች ሲጫወት 53 ጎሎችን ከመረብ አዋህዷል፡፡ ካርሎስ ቴቬዝ ማን ዩናይትድን በመልቀቅ ወደ ቅርብ ተቀናቃ’ኙ ሲቲ ሲገባ ለ5 ዓመታት ኮንትራት በመፈረም ሲሆን ለዝውውሩ 47 ሚሊዮን ፓውንድ ወጥቶበታልመ ቢባልም አልተረጋገጠም፡፡ ቴቬዝ ማን ሲቲ በገባ የመጀመርያ የውድድር ዘመኑ በክለቡ ሁለት የክብር ሽልማቶችን የኢትሃድ የዓመቱ ምርጥ ተጨዋች እና የተጨዋቾች ምርጫ ምርጥ ተብሎ ተሸልሟል፡፡

Read 3240 times