Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 15 October 2011 12:38

ሶርያ የተሰራችውእንዲህ ነው!

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ቱኒዚያን ከሀያ አመታት በላይ ሠጥ ለጥ አድርገው ሲገዙ የነበሩትን አበዲን ቤን አሊን ለስደት፤ ግብጽን ለአርባ አመታት በማይበገር የብረት ክንድ ጨብጠው በአምባገነንነት ያስተዳደሯትን ሞሀመድ ሆስኒ ሙባረክን ከሥልጣን መንበር አባሮ ለፍርድ ያበቃው፤ ሊቢያን በፍፁም ፈላጭ ቆራጭነት ከአርባ ዓመት በላይ ሲገዙዋት የነበሩትን ኮሎኔል ሙአመር ጋዳፊን ደግሞ ከሚያፈቅሩት የስልጣን ወንበራቸው ነቅሎ በነፍሴ አውጭኝ የገቡበትን ያሰወረው አዲሱ የአረብ አብዮት ሶሪያንም መለብለብ ከጀመረ እነሆ መንፈቅ ሞላው፡፡

በዚህ ጊዜ ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ሶሪያውያን አደባባይ በመውጣትና መንግስታቸውን በመቃወም ለአዲስ ለውጥ ያላቸውን ፍላጐት በግልጽ ቢያስታውቁም፣ የፕሬዚዳንት በሻር አልአሳድ መንግስት ለጥያቄአቸው የሰጣቸው መልስ ጥይት ብቻ ነው፡፡ የለውጡ አብዮት ከተቀጣጠለ ጊዜ ጀምሮ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሶሪያውያን በመንግስት ወታደሮች ተገድለው ህይወታቸውን ሲያጡ፣ ከሞቱት በብዙ እጥፍ የሚበልጡት ደግሞ ለእስርና ለከፍተኛ እንግልት ተዳርገዋል፡፡  
የሶሪያ ህዝብ ግን አንድ ተስፋ ሰንቆ ነበር፡በሊቢያ በተቀሰቀሰው ተመሳሳይ አመጽ ሕዝባቸውን በጥይት ከመፍጀት ወደ ኋላ ያላሉትን ጋዳፊን ከቤተመንግስታቸው ተባረው እንዲወጡ ለተቃዋሚዎቻቸው ድጋፍ የሰጠው ኔቶ ፊቱን ወደ ሶሪያ አዙሮ የበሻር አልአሳድን ወታደራዊ ኃይል ቀንዱን ይሠብርልናል የሚል ተስፋቸው ግን አንዳች ጠብ የሚል ነገር እንደሌለው በቅጡ ተረድተውታል፡፡
ባለፈው ሠሞን የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት፤ በፕሬዚዳንት በሻር አልአሳድ መንግስት ላይ እንዲወሠድ ታቅዶ የነበረው የማዕቀብ እርምጃ፣ በራሺያና በቻይና ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ውድቅ ሲደረግ ሶሪያውያን ተመልክተው በንዴት ቆሽታቸዉ አርሯል፡፡
ይህን ያዩት ፕሬዚዳንት በሻር አልአሳድም ከአባታቸው የወረሱትንና ላለፉት አስር አመታት የአይን ሀኪምነታቸውን ትተው በፈላጭ ቆራጭነት የተዘባነኑበትን ስልጣናቸውን ሊነጥቋቸው የተነሱባቸውን ሁሉ “ከእንግዲህ የትኛው የአለም መንግስት መጥቶ እንደሚያስጥላችሁ አየዋለሁ” በሚል አይነት ፉከራ ለእምቦቃቅላ ህፃናት እንኳ ሳይራሩ የህዝባቸውን አናት በአልሞ ተኳሽ አንጋቾቻቸው ጥይት (በአረብ የጁምአ ሶላት ላይ ሳይቀር) እየበረቀሱ መጣሉን ቀጥለውበታል፡፡
የአለም ምንዱባኖችን ነገር በተመለከተ ሆዳችን አይችልም የሚሉት የአሜሪካና የአውሮፓ ሀገራትም እንደለመዱት ትርፉና ኪሳራቸውን አስልተው፣ አልፎ አልፎ ከሚያሠሙት የይስሙላ ጩኸት በቀር ሶሪያንና በአምባገነኑ መሪያቸው ቁም ስቅላቸውን የሚያዩት ሶሪያውያንን “ስራህ ያውጣህ” ብለው ትተውታል፡፡
ሶሪያውያን የፈለጉትን ያህልና በፈለጉት መጠን ቢያልቁ በአለም አቀፉ ህብረተሰብ በተለይ ደግሞ በአሜሪካና የአውሮፓ ሸሪኮቿ ዘንድ ከሊቢያውያን እኩል ሞገስ እንደማያገኙ በእርግጠኝነት ያወቁት ይመስላሉ፡፡ እናም አሁን የድረሱልንና የአግዙን ተማጽኖአቸውን ወደ አምላካቸው አዙረውታል፡፡
የአሜሪካንና የአውሮፓ ሸሪኮቿን ልብ አለመጠን የሚያስመታውና ደማቸውን የሚያዘዋውረው የነዳጅ ዘይት ሀብት መሆኑን የዘመናት የአለማችን ታሪክ በተደጋጋሚ በግልጽ አሳይቶናል፡፡ የአሜሪካ የልብ ትርታ የሚሠማው ከነዳጅ ማውጫ ጉድጓድ ጫፍ ላይ ነው፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖ ይህን የነዳጅ ሀብት ሊቢያ እንጂ ሶሪያ በበቂ የላትም፡፡ እናም የአሜሪካንና የአውሮፓ ሸሪኮቿን አይንና ቀልብ ማማለል አልቻለችም፡፡ ስለዚህም ሶሪያ የአሜሪካውያንም ሆኑ አውሮፓውያን ሊሞቱላት የሚሽቀዳደሙላት አይነት ሀገር ጨርሶ አይደለችም፡፡ ከተራበ አሳ አጥማጅ በቀር ስለሞተ አሳ የሚጨነቅ ከቶ ከየት ይገኛል? የሶሪያም ነገር እንዲህ ነው፡፡
በግብጽ አብዮት የጦር ኃይሉ የነበረውን ሚና የሚያስታውሱ ሰዎች፤ የሶሪያ ጦር ሀይል ህዝቡን ከመደገፍና የለውጡን አብዮት ከግብ ከማድረስ ይልቅ የገዛ ህዝቡን በመግደልና አስሮ በማሠቃየት ላይ ለምን አተኮረ በማለት ይጠይቃሉ፡፡ የሶሪያን ህብረተሠብና ፖለቲካዊ አወቃቀር በቅርብ እናውቃለን የሚሉት ደግሞ ፕሬዚዳንት በሻር አልአሳድ፤ ከጠቅላላው የሶሪያ ህዝብ አስር ከመቶ እንኳ በቅጡ የማይሞላው የኦላዋይት አናሳ የህብረተሠብ ክፍል አባል ሆነው ዘጠና ከመቶ የሚሆነውን የህብረተሰብ ክፍል ሠጥ ለጥ አድርገውና አንቀጥቅጠው ለመግዛት እንዴት ቻሉ በማለት የበኩላቸውን ሞጋች ጥያቄ ያቀርባሉ፡፡ እነዚህ ሁለት ጥያቄዎች ተራ ጥያቄዎች ሊመስሉን ይችላሉ፡፡ ነገር ግን አሁን ያለውን የሶሪያ ወቅታዊ ሁኔታና የፕሬዚዳንት አልአሳድን የስልጣን ምስጢር ፍንትው አድርጐ ሊፈታልን የሚችለው ቁልፍ ያለው በእነዚህ ሁለት ጥያቄዎች ውስጥ ነው፡፡
ፕሬዚዳንት በሻር አልአሳድ እጅግ አናሳ የሆነው አላዋይት ህብረተሠብ ክፍል አባል ሆነው ሳለ አብዛኛውን የሶሪያ ህዝብ ቀጥ አድርገው እንዲገዙ ያስቻላቸው ሶሪያ የተዋቀረችበት የአሠራር ስርአት ነው፡፡ ይህንን በሚገባ ለመረዳት ደግሞ ከዛሬዋ ሳይሆን ከዛሬ ሀምሳ አመት በፊት ከነበረችው ሶሪያ መነሳት የግድ ይላል፡፡
ከ1960 እስከ 1970 አ.ም ድረስ በነበሩት አስር አመታት ሶሪያ አራት ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስቶችን አስተናግዳለች፡፡ መንግስቷ የተረጋጋው የመጨረሻውን መፈንቅለ መንግስት የዛሬው ፕሬዚዳንት የበሻር አባት ሀፌዝ አልአሳድ፤ በ1970 አድርገው የመሪነት ስልጣኑን ከተቆናጠጡ በሁዋላ ነበር፡፡ ፕሬዚዳንት ሀፌዝ አልአሳድ በሶሪያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ትልቅ አሻራቸውን ትተው ያለፉ ጨካኝ፣ በስልጣናቸው ከመጡባቸው ምንም አይነት ነገር ከማድረግ ጨርሶ የማይመለሱ “መሽቁቅ” ፖለቲከኛ ነበሩ፡፡
እኚህ ፕሬዚዳንት ከአርባ አመታት በላይ በዘለቀው የስልጣን ዘመናቸው፣ እሳቸው የተገኙበት አናሳው የኦላ ዋይት የጐሳ ክፍል የተቀረውን የሶሪያን ህዝብ ለዕድሜ ልክ አንቀጥቅጦ የሚገዛበትን ስልት የነደፉ ሰው ሲሆኑ በንድፋቸውም መሠረት ሶሪያን በእጃቸው ጠፍጥፈው እንደገና ሠርተዋታል፡፡
የሶሪያ ጦር ሀይል ከፍተኛ መኮንን የነበሩት ሀፌዝ አልአሳድ፤ በቅድሚያ የገነቡት የደህንነት ሀይላቸውን ነበር፡፡ ይህን የደህንነት ሀይላቸውን በተለያየ ደረጃ ካዋቀሩ በኋላም ከአዛዥ እስከ ታዛዥ የሞሉት በራሳቸው ጐሳ በኦላዋይት አባላት ብቻ ነበር፡፡የጦር ሀይሉ ራሱን የቻለ አንድ ወጥ ሳይሆን ከሶሪያ የተለያዩ የደህንነት ጥበቃ ሀይሎች የተውጣጣ ነው ፡፡ይህ በሚገባ ከተዋቀረ በኋላ ቀጥለው ያደረጉት የሶሪያን ብቸኛ የገዢ ፓርቲን እንደ አዲስ መገንባትና በደህንነትና በጦር ሀይላቸው ቁጥጥር ስር እንዲሆን ማድረግ ነበር፡፡ ይሄ ገዢ ፓርቲም ቢሆን የተሞላው በጐሳቸው በኦላዋይት ሰዎች ብቻ ነበር፡፡
ፕሬዚዳንት ሀፌዝ አልአሳድ ስልጣናቸውንና ደህንነታቸውን በሚገባ የሚያስጠብቅ፤ በራሳቸዉ ጐሳ ብቻ የተሞላ የደህነነት፣ የፖሊስና የጦር ኃይል ከገነቡ በኋላ ከዚህ መዋቅር ውጪ የሆኑትን የኦላዋይት ጐሳ አባላት፤ የቤተሠብና የአካባቢ ትስስርን በመጠቀም ታማኝነታቸውን መግዛት ችለዋል፡፡ ለፕሬዚዳንት ሀፌዝ አልአሳድ ታማኝነት ትልቅ ዋጋ ነበረው፡፡ ለእሳቸው ስልጣን በፍፁም የታመነ ተገቢውን ዋጋ ያገኛል፡፡
የሶሪያ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ለጐሳቸው ሠዎች ሁሌም ክፍትና ቅድሚያ የሚያገኙበት ቦታ ነው፡፡ የሌላ ጐሳ አባል፤ ነገር ግን ለፕሬዚዳንት አልአሳድ ታማኝ የሆነ ሠው ከኦላዋይት ጐሳ አባል ቀጥሎ ይስተናገዳል፡፡ ስለዚህ የመንግስት ስራ ለማግኘትና በተለያየ የመንግስት አገልግሎቶች ተጠቃሚ ለመሆን፣ በተለይ ደግሞ የግልና የቤተሠብን ደህንነት ለማስጠበቅ የኦላዋይት ጐሳ አባል መሆን አቻየለሽ ጠቀሜታ አለው፡፡ ከተቀረው ጐሳ አባል የሚጠበቀው ለፕሬዚዳንቱ ታማኝ መሆንና ይህንን ታማኝነቱንም በተግባር ማሳየት ነው፡፡
ፕሬዚዳንት ሀፌዝ አልአሳድ የራሳቸውን የአላዋይትን የጐሳ አባላት በሁሉም የመንግስት መዋቅሮች ውስጥ ቁልፍ ቦታዎችን ሲያስይዙ፣ በኢኮኖሚዉም መስክ አዋጭና አትራፊ የንግድ መስኮችን እንዲቆጣጠሩ ሲያደርጉ፣ ከቀረጥና ግብር ጫና ሲከላከሉላቸው፣ እግረ መንገዳቸውን እንደ ቀልድ የሚያስገነዝቧቸዉ ዋና ቁም ነገር፤ ይህን ሁሉ ልዩ ክብርና ጥቅም ያገኙት በእሳቸው አማካኝነት እንደ ሆነና ይህ የተለየ ክብርና ጥቅም እንዳለ የሚቀጥለው እርሳቸውና የሚመሩት መንግስት በስልጣን ላይ እስካለ ድረስ ብቻ መሆኑን ነበር፡፡
በዚህ የተነሳም በፕሬዚዳንቱ ላይ የተቃጣው አመጽና የነፍስ ግድያ ሙከራ የከሸፈው እጅግ በቀላሉ ነበር፡፡ ተጨማሪ መልእክት የቀረበለት የጦር ሀይሉና በተለይ ደግሞ የደህንነት ክፍሉ ነበር፡፡ እነዚህ ክፍሎች ፕሬዚዳንቱንና መንግስታቸውን በታማኝነትና በንቃት ከመጠበቅ ባሻገር በህዝቡ ላይ ከባድና ያልተቋረጠ ፍርሀት ማስፈን ይጠበቅባቸዋል፡፡ እነሱም በቀላል ተራ ወንጀል የተከሠሱ ሶሪያውያንን አስከፊና ዘግናኝ ቅጣት በመቅጣት በመንግስት ላይ ተቃውሞና አመጽ ያስነሳ ሠው ምን አይነት ቅጣት እንደሚጠብቀው ራሱ እንዲገምትና በፍርሀት አንገቱን ደፍቶ እንዲቀመጥ ለማድረግ በእጅጉ ጥረዋል፡፡
በ2000 አ.ም ፕሬዚዳንት ሀፌዝ አልአሳድ በልብ ህመም ከዚህ አለም በሞት እንደተለዩና ሁለተኛው ወንድ ልጃቸው በሻር አልአሳድ ስልጣናቸውን ወርሶ ፕሬዚዳንት እንደሆነ የፓርቲውን የመንግስቱንና የጦር ሀይሉን መዋቅር በወንድሞቹና በቅርብ ዘመዶቹ ቁጥጥርና የእዝ ስር ባሉት የደህንነት ሀይሎች ስር እንደገና መልሶ አዋቀራቸው፡፡ የባዝ ፓርቲውን ስራም የስለላና የቁጥጥር ስራ ብቻ አደረገው፡፡ ዛሬ በሁሉም የሶሪያ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ራሱን የቻለ የባዝ ፓርቲ መዋቅር ይገኛል፡፡ ዋና ስራውም መሠለልና መቆጣጠር ነው፡፡ ሶሪያውያን አሁን አሁን የባዝ ፓርቲን የሚያዩት እንደ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ሳይሆን ከደህንነቱ ሀይል እንደ አንዱ ክፍል አድርገው ነው፡፡
ወደ አራት መቶ ሺ ይደርሳል በሚባለው የሶሪያ የጦር ሀይል ውስጥ ከመቶ ሠላሳ ሺ በላይ የሚሆኑት የፕሬዚዳንቱ የኦላዋይት ጐሳ አባላት ናቸው፡፡ በዚህ የሶሪያ የጦር ሀይል ውስጥ የሌላ ጐሳ አባል የሆነ ከፍተኛ ማዕረግ ያለው መኮንን እንደልብ ፈልጐ ማግኘት እንደ ብርቅ ነገር ተደርጐ ይታያል፡፡ በፕሬዚዳንታዊው የጥበቃ ሀይል ውስጥ እንኳን ባለ ከፍተኛ ማዕረግ መኮንን ይቅርና ተራ ወታደር የሆነ የሌላ ጐሳ ወታደር ማግኘት አይቻልም፡፡ ይህ ልዩ የጦር ኃይል ከኦላዋይት ጐሳ ውጭ ለሌሎች ፈጽሞ የማይፈቀድ ነው፡፡
አሁን በያዝነው አመት ባለ መረጃ መሠረት፣ የኦላዋይት ጐሳ አባላት ከጠቅላላው የሶሪያ ህዝብ አስር በመቶ ያህላሉ፡፡ ነገር ግን የጦር ሀይሉን ስልሳ ሠባት ከመቶ፣ የደህንነቱን ሰባ ሠባት ከመቶ ይወክላሉ፡፡ ሀምሳ ከመቶ የሚሆነው የሶሪያ የሲቪል ሠራተኞች ቦታ የተያዘው ደግሞ በአናሳዎቹ የኦላዋይት ጐሳ አባሎች ናቸው፡፡ የሌላ ጐሳ የሆነ የሶሪያ የመንግስት ሠራተኛ መስሪያ ቤቱ የገዛለትን እርሳስ ሲሠብር መታየቱ ብቻ ከስራው ሊያስባርረው ይችላል፡፡ የፕሬዚዳንቱ ጐሳ አባላት ግን ከስራቸው ሊባረሩ የሚችሉበት አንዱና ብቸኛው ጥፋት፣ የመንግስቱን ጭቆና አልተባበርም ወይም አላግዝም ያሉ እንደሆነ ብቻ ነው፡፡ ያኔ የሚጠብቃቸው ክስ፣ ክህደትና ከመንግስት ጠላቶች ጋር መሞዳሞድ የሚል ነው፡፡ በቃ ሶሪያ የምትሠራው እንዲህ ነው፡፡ በእነዚህ አይነት ክሶች የተከሠሠ የኦላዋይት ጐሳ አባል ቅጣቱ ምንድን ነው ብሎ የሚጠይቅ ማንም ሶሪያዊ የለም፡፡ ለምን ቢባል በግልጽ ስለሚታወቅ ብቻ ነው፡፡ ፕሬዚዳንት በሻር አልአሳድ ልክ እንደ አባታቸው ሁሉ፣ እሳቸውም ለታማኝነት ትልቅ ዋጋ የሚሠጡ ሠው ናቸው፡፡ ከአባታቸው የተለዩ ናቸው እየተባሉ የሚታሙበት ነገር ቢኖር ከአባታቸው ጊዜ በበለጠ እርሳቸው ጥቂት የሱኒ እስልምና ተከታይ የሆኑ ሠዎችን በሚኒስትርነትና በመንግስት መስሪያ ቤቶች በኃላፊነት መሾማቸዉ ነው፡፡ የተሾሙት ሚኒስትሮችና ሀላፊዎች ግን ሹመታችን እንዲሁ ለይስሙላ ነው እያሉ ይነጫነጫሉ፡፡
በእርግጥ ነገሩ እውነትነት አለው፡፡ በሻር አልአሳድ ከጐሳቸው ውጭ ያሉ ሠዎችን ሲሾሙ የሚሠጧቸው ስሙን ብቻ እንጂ ስልጣኑን አይደለም፡፡ ስልጣን ሁልጊዜም ቢሆን መቀመጥ ያለበት በራሳቸው ጐሳ አባላት ብቻ ነው ብለው ያምናሉ፡፡ እናም አንድ የሌላ ጐሳ ሚኒስትር ሲሾም፣ ከስር ሆኖ የሚቆጣጠረውና የሚሠልለው ትክክለኛ ውሳኔውንም የሚወስን የኦላዊይት ጐሳ አባል የሆነ ምክትል ሚኒስትር አብሮ ይሾምለታል፡፡ በመንግስት መስሪያ ቤትም የሚደረገው እንደዚሁ ነው፡፡ የመስሪያ ቤቱ ስራ አስኪያጅ የሌላ ጐሳ አባል ከሆነ፣ ሁሉንም አይነት ውሳኔ የሚወስንና የሚከታተል የኦላዋይት ጐሳ አባል የሆነ ምክትል ስራ አስኪያጅ ወዲያውኑ ይመደብለታል ወይም ይመደብበታል፡፡ በሶሪያ ሁሉም ነጋዴዎች ግብርና ቀረጥ እንዲከፍሉ ህግ ይደነግጋል፡፡ የዚህ ህግ ድንጋጌ በተግባር የሚውለው ግን ለሌላ ጐሳ አባል ለሆኑ ነጋዴዎች ብቻ ነው፡፡ ለኦላዋይቶች ነገሩ ሁሉ ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ አይነት ነው፡፡ አንድ የኦላዋይት ጐሳ አባል ነጋዴ ችግር ቢገጥመው ከሱ የሚጠበቀው ወደሚመለከተው መስሪያ ቤት ሀላፊ ደውሎ የገጠመውን ማስረዳት ብቻ ነው፡፡ ችግሩ ለመፈታቱ አይጠራጠርም፡፡ እንዴት ቢባል የኦላዋይት ጐሳ አባል በገዛ ጐሳው አባል ላይ የሚጨክን አንጀት ከየት ሊያመጣ ይችላል፡፡ በዚህ የተነሳ የሶሪያን የቢዝነስ እንቅስቃሴ በዋናነት የተቆጣጠሩት የኦላዋይት ጐሳ አባላት ናቸው፡፡ በሶሪያ አውራው ፓርቲ የባዝ ፓርቲ ብቻ ነው፡፡ የሶሪያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከሞላ ጐደል ሁሉም በሚያስብል ሁኔታ የሚገኙት ከሀገራቸው ውጭ በስደት ነው፡፡ የባዝ ፓርቲ የተቃዋሚዎቹን የእግር መትከያ ቦታ ለማሳጣት ለዘመናት ቀን ከሌት ተግቶ በመስራት ተሳክቶለታል፡፡ የተሳካለት ግን በሠላማዊ የዲሞክራሲያዊ ውድድር አልነበረም፡፡ በፍርሀትና በሽብር እንጂ፡፡
አሁን ከመቸውም ጊዜ በበለጠ ሁኔታ በፕሬዚዳንት በሻር አልአሳድና በመንግስታቸው ላይ ህዝባዊ አመጽ ተቀስቅሶባቸዋል፡፡ ሶሪያውያን ለዘመናት ከተጫናቸው ፍርሀት ተላቀው ለተቃውሞ አደባባይ ቢወጡም የመንግስቱ ታማኝ የደህንነትና የጦር ሀይል የጭካኔ በትሩን በሠፊው መዞባቸዋል፡፡ የኦላዋይት ጐሳ አባላትም ፕሬዚዳንታቸዉና የሚመሩት መንግስት ከወደቀ የሚመጣውን ነገር አያውቁትምና ከተቃዋሚዎች በተቃራኒ ቆመው ለበሻር አልአሳድ ያላቸውን ድጋፍ በመግለጽ ላይ ይገኛሉ፡፡ ፕሬዚዳንቱም ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ “እኔ በሻር አልአሳድ እንጂ ቤንአሊ ወይም ሙባረክ አሊያም ደግሞ ጋዳፊ አይደለሁም” በማለት መፎከራቸውን ቀጥለዋል፡፡ የጦርና የደህንነት ሀይሉም የራሱን መንግስት ለማቆየትና ለመጠበቅ፣ እለት ተእለት የተቃዋሚዎችን አናት በጥይት መበርቀሱን ገፍቶበታል፡፡ የዚህን ግፍ መጨረሻ የሚያውቅ ባይኖርም አላዋይቶች ግን አንድ ነገር ይላሉ፡፡ ከፕሬዚዳንታችን ጐን ተሠልፈን አንድ ጥይትና አንድ ሠው እስኪቀር ድረስ ከእነዚህ ወሮበሎች ጋር እንፋለማለን፡፡

 

Read 5687 times Last modified on Saturday, 15 October 2011 12:42