Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 15 October 2011 11:56

የአዱ ገነት ልማት ተጠቃሚው ማነው?

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ይህ ርእሰ ጉዳይ በዋንኛነት በአዲስ አበባ ከተማ በመካሄድ ላይ ያለውን የቤቶች ግንባታ መልሶ ማልማትን ብቻ የተመለከተ ነው፡፡ በከተማዋ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች እየተካሄዱ በመሆናቸው ለመዳሰስ የምሻው በመልሶ ማልማት ዙሪያ እየፈረሱ ስላሉት አንዳንድ የከተማችን ወረዳዎች ይሆናል፡፡ ይህ ትኩረትም በተለምዶ ባሻ ወልዴ ችሎት አካባቢ እየተባለ በሚጠራውና በመንግስት መዋቅር በአራዳ ክፍለ ከተማ በወረዳ 9 ያለውን የመልሶ ማልማት የተመለከተ ትዝብታዊ ምልከታም ነው፡፡ እንደ አንድ የከተማዋ ተወላጅና ነዋሪ ይመለከተኛል ያልኩትንና የከተማዋ መስተዳደር፤ ክፍለከተማና ወረዳው ቢያስተካክሉአቸው ልቤ የወደዳቸውን የአሰራር ግድፈቶች ማንሳቴን ሁሉም የመንግሥት አካላት በቀና ልቦና ይመለከቱት ዘንድም እጠይቃለሁ፡፡

ከተመሰረተች 125 ዓመት የሞላት አዲስ አበባ እንደ እድሜዋ ዘመነኛ አይደለችም፡፡ በህዝብ ብዛት ቁጥር፤ በዓለም ዓቀፍ ተቋማት መናሀሪያነት፤ እንደ ፌዴራል መንግስት መቀመጫነት፤ እንደ አፍሪካ መዲናነት… ወዘተ ወደፊት ከመሄድ ይልቅ ወደ ኋላ መመለስ የቀናት ከተማ ነች፡፡ እንደ ስሟ አዲስነት የሌለባት መሰረተ-ልማቷ ደካማ፤ የመልካም አስተዳደር እጦቷ መፍትሄ አልባ ግን ተወዳጅና ተናፋቂ ከተማም ነች፤ አዲስ አበባ፡፡ እነዚህ ለማሳያነት የጠቀስኳቸውን ችግሮች ብቻ መዘን ከተማዋን ወደ ተሻለ የመኖሪያ ከተማነት ለመቀየር ጥቂት የማይባሉ ዓመታት፤ በቢሊዮን የሚገመት የገንዘብ አቅም፤ የተማረና በልምድ የዳበረ የሰው ኃይል፤ ቆራጥ ፖለቲካዊ አመራር፤ የነዋሪዎቿ ቀና ትብብር እና ሌሎች ወሳኝ እልህ አስጨራሽ ግብአቶችን ትፈልጋለች፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንዳንድ አካባቢዎች የምናያቸው ተስፋ ሰጪ የልማት ጅምሮችም ለዚህ አባባል በጨለማ ውስጥ እንደሚታይ ቀጭን ብርሐን አይነት ማሳያዎች ናቸው፡፡ ሌሎች መንግስታዊ ያልሆኑ አካላት ካላቸው ድርሻ ባሻገርም መንግስትም በተለይም በቤቶች ግንባታ ዘርፍ የጀመራቸውን ውጥኖች እያበረታታን ነው ዛሬ ላይ መታረም የሚገባቸውን የአሰራር እንቅፋቶች መንቀል የሚገባን፡፡ ምክኒያቱም አካፋን አካፋ ለማለት አሁን ያልደፈረ ብእርና አንደበት ነገ ላይ ህመሙን አብሮ ከመታመም ባለፈ የመፍትሄው ተቋዳሽ የመሆን አቅም አይይኖረውም፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የበሽታውን ፍንጭ ለማግኘት የማይችልና ምንም ለማለት አቅም አይኖረውም ከሚል እምነት በመነሳት ነው፡፡
ከላይ በጠቀስኩትና በተለምዶ ባሻ ወልዴ ችሎት (4 ኪሎ) አካባቢን ከሁለት ዓመት በፊት ያያትና ሰሞኑን ዳግም በመንደሯ ብቅ ያለ ጐብኚ፣ ዛሬ መንደሯ ትዝታ ሆና ስለመቅረቷ ይገነዘባል፡፡ በቀድሞው አጠራር ቀበሌ 07 እና ቀበሌ 13 ውስጥ የሚኖሩ የነበሩ ነዋሪዎች ዛሬ በመልሶ ማልማቱ ምክኒያት መንደር ለውጠዋል፡፡ ጆሞ ቁጥር 1፤ ላፍቶ፤ ጐፋ፤ ፈረንሳይ ለጋሲዎንና አዲሱ ገበያ የቀድሞው አራት ኪሎ ነዋሪዎች የከተሙባቸው የኮንዶሚኒየም ጥቂት መንደሮች ናቸው፡፡ የቀበሌ ቤት የተሰጣቸውን፤ መሬትና ገንዘብ የተረከቡትን ሳይጨምር መሆኑ ነው፡፡ እንደዚያ ስመ ገናና የነበረችው መንደር ገናናነቷን ለአረም ማጀቢያነት ትታ ተሰናብታለች፡፡ በተለይም እንደ እኔ እትብታቸውን ለቀበሩባት ተወላጆች መልካም ትውስታዎቿ በቀላሉ አይለቁም፡፡
አካባቢው ከልደታ ቀጥሎ ለልማት ስራ መፈለጉን ተከትሎ ነዋሪው ቀዬውን ለቆ ቢወጣም እነዚያ መንደሮች አሁን ድረስ ምንም አይነት ግንባታ ሳይከናወንባቸው አረም ውጦአቸው፣ ለአላፊ አግዳሚው ገመናቸውን ገልጠው ተቀምጠዋል፡፡ በዋና ዋና መንገድ አካባቢ ያሉት ቆርቆሮ ጋርዶአቸው፣ የተቀሩት መለመላቸውን አሁን ድረስ አሉ፡፡ ለምን? የሚለውን ጥያቄ መመለስ የሚችለው የሚመለከተው ክፍል በመሆኑ እድሉን ለእርሱ እተዋለሁ፡፡ ቢሆንም ታድያ ነዋሪው አካባቢውን ለቆ ከተነሳ በኋላ ስፍራው ለግንባታ ያለውን አመቺነት ለማወቅ የአፈር ምርመራ ሲደረግ አስተዋልኩና «ከፈረሱ…» ብዬ አለፍኩት፡፡ ቀድሞ በአካባቢው የነበረው ነዋሪ ግን ለመኖሪያ ምቹ በሆነ የአኗኗር ዘይቤን መላመዱንስ ከኔ በላይ ማን ይመሰክራል፡፡ ቀዬአችንን ያን ያህል ብንወዳትም እንደው ኑሮአችን እኮ በእርሱ ፈቃድ እንደነበርም አዲሱ ኑሮአችን አስተምሮናል፡፡ ሰው ማንን ይመስላል ቢባል ማንን ይባላል?
በዚህ መልካም እሳቤ ውስጥ ሆኖ ታድያ ተረኛ የሆነው የቀበሌ 12 ነዋሪ ሰሞኑን በዚህ በመልሶ ማልማት እንቅስቃሴ ተውጦ ከርሟል፡፡ በዚህ ቀበሌ ያሉ ነዋሪዎች ከአካባቢው ስለመነሳታቸው እርግጡን አውቀዋል፡፡ መቼ ለሚለው ቁጥር ያለ ምላሽ ባያገኙም ማለት ነው፡፡ ለመኖሪያ ምቹ ባልሆኑ አካባቢዎች ከሚኖሩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች መሃከል የሚጠቀሱት እነዚህ ነዋሪዎች አካባቢውን ይለቁ ዘንድ በመስተዳደሩ፤ በክፍለ ከተማውና በቀበሌው አስተዳደር እየተሰሩ ያሉ ስራዎች አበረታች ቢሆኑም በቀደሙት ተነሺዎችም ሆነ አሁን በሚከተሉት ዘንድ የሚነሱ ቅሬታዎች ግን በእርግጥም ሁሉም ጆሮ ሊሰጡት የሚገባ ይመስለኛል፡፡ በወረዳው፤ በክፍለ ከተማውና በመስተዳድሩ መሃከልም መልሶ ማልማቱን ለማስፈፀም የመረጃ ክፍተት ካለ፣ ይህ የእኔ ትዝብት ክፍተቱን ለመሙላት እንደ አንድ የመረጃ ግብአትነት ሊያገለግልም ይችላል፡፡
የልማቱን ዓላማ ለነዋሪው ግልፅ ያለማድረግ
የከተማዋ ነዋሪ እንደ ነዋሪነቱ እንደ መብት ከሚቆጠሩለት ጉዳዮች መሃከል በከተማዋ ስለሚካሄዱ ማናቸውም እንቅስቃሴዎች ተገቢውን መረጃ ማግኘት ቀዳሚው ነው፡፡ በተለይ ለልማት ስራዎች ሲሆንም በበቂ እውቀትና መረጃ የተደራጀ ህብረተሰብ መንግስትም ሆነ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ለሚከውኗቸው ተግባራት ቀና ትብብሩን እንዲሰጥ በቂ መረጃ ማግኘቱ ያግዘዋል፡፡ በቂ መረጃ በማግኘቱም እርሱም የከተማዋ ነዋሪነት ክብር ይሰማዋል፡፡ በደፈናው አካባቢያችሁን መንግስት ለልማት ፈልጐታል የሚለው ግልፅ ያልሆነ መመሪያ ግን መስተዳድሩ ለሚሰራቸው ልማታዊ እንቅስቃሴዎች የህብረተሰቡን ድጋፍ አያስገኝለትም፡፡ በተቃራኒው ጥርጣሬን፤ ቀና አለማሰብን፤ ባይተዋርነትንና የእኔነት ስሜት ማጣትን ያስከትላል፡፡ ቀደም ሲል በመልሶ ማልማት የተነሱትንም ሆነ አሁን ለመነሳት በዝግጅት ላይ የሚገኙ ነዋሪዎችን ለማነጋገር የደፈረ የሚያገኘው መልስ ዝብርቅርቅ ያለ ይሆናል፡፡ ለዚህም ምክኒያቱ ነዋሪው ከመኖሪያ አካባቢው ለምን እንደሚነሳ ግልፅ መልስ የሚሰጠው፣ ስለጉዳዩ በቂ እውቀት ያለው የመንግስት አካል ያለማግኘቱ ስለመሆኑ በድፍረት መናገር ይቻላል፡፡ ለዚህ ስራ የተመደቡት አስፈፃሚዎች ከፍ ያለ ድካም ሲደክሙና ህብረተሰቡን ሲያስተባብሩ ቢከርሙም በየስብሰባዎቹ ከፍ ያሉ ሙግቶች የሚገጥሙአቸው መሆኑን ለመታዘብ ችያለሁ፡፡ ዓላማን በግልፅ ለማስቀመጥ ባለመቻልና ሲበዛ ሚስጥራዊ ለመሆን ከመጣር ከሚመጣ የተሳሳተ አሰራር መነሾነት፡፡ ነዋሪ ለምን ከመኖሪያው እንደሚነሳ፤ አካባቢው ለምን የልማት ዓላማ እንደሚውል ቢረዳ፤ ወዴት እንደሚሄድ ቢያውቅ ለመንግስት ዓላማ መፈፀም የራሱን እገዛ ያደርጋል ብዬ አምናለሁ፡፡
የስነ-ልቦና ዝግጅት እንዲደረግ በቂ ጊዜ ያለመስጠት
በዚህ የመልሶ ማልማት ስራ ውስጥ የተካተቱት አካባቢዎች የሚኖሩ ነዋሪዎች በቀላሉ ለ20 እና 30 ዓመታት በአካባቢው ኖረዋል፡፡ በእነዚህ አመታት ወልደው ስመዋል፤ ሐዘንና ደስታን በጋራ ተካፍለዋል፡፡ ጠንካራ ማህበራዊ ትስስር መስርተዋል፡፡ በስራ፤ በትምህርትና በመሰል ጉዳዮች ከአካባቢው ጋር ራሳቸውን አቆራኝተዋል፡፡ እነዚህን ለዘመናት የተላመዱዋቸውን የህይወት ዘይቤዎች ለመቀነስ፤ ወደተለየ አካባቢ ለመውሰድ፤ ወደ ዘመናዊና ለኑሮ ምቹ ወደ ሆነ የአኗኗር ዘይቤ ለመቀላቀል ልዩ ሐላፊነትን ይጠይቃል፡፡ ከእነዚህ ሃላፊነቶች አንደኛው ደግሞ የስነ-ልቦና ዝግጅት ማድረግ ነው፡፡ ወደ ልማት ስራው ለመግባት ከመጣደፍ በፊት በተለያዩ የማንቂያና የማስተማሪያ ስልቶች ነዋሪውን በስነ-ልቦና ማዘጋጀት ቀዳሚ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ለምሳሌ ያህል ቀደም ባሉት ሁለት ቀበሌዎች የመልሶ ማልማት ስራ ከመጀመሩ በፊት በተካሄዱ ስብሰባዎች ላይ ተካፍዬ ነበር፡፡ በክፍለ ከተማው ሃላፊዎችና በቀበሌው (ወረዳው) አመራሮች መሃከል በነበረ ስብሰባ ወቅት በህብረተሰቡ ዘንድ ከስነ-ልቦና ዝግጅት ማጣት ጋር ተያይዘው ይቀርቡ የነበሩ ጥያቄዎች ከተመለሱባቸው ዘዴዎች አንደኛው «የተለየ ተልእኮ ያላችሁ ሰዎች አዳራሹን ለቃችሁ ውጡ» የሚል ነበር፡፡ ይታያችሁ በስነ-ልቦና ዝግጁ ላልነበረና በጭንቀት የተለያዩ ጥያቄዎችን ለሚሰነዝር ነዋሪ፤ ይህ መሰሉ መልስ ሊፈጥርበት የሚችለውን ተጨማሪ የስነ-ልቦና ችግር ለመገመት ብዙ ማሰብን አይጠይቅም፡፡
ሰሞኑንም መስከረም 26 ቀን 2004 ዓ.ም በተካሄደ መሰል ስብሰባ ላይ ሰብሳቢዎቹ፤ ክፍለ ከተማው ከአራት ቀናት በኋላ ማለትም ጥቅምት 1 ቀን 2004 ዓ.ም ቤት ማፍረስ እንደሚጀምር ለተሰብሳቢው ነግሮአቸዋል፡፡ በዚህ ሃላፊነት በጐደለው ንግግርም የተሳታፊው መንፈስ ተለውጦ በመነጋገር ሊፈቱ የሚችሉ ችግሮችን ወዳልተፈለገ መንገድ መርቶአቸዋል፡፡ ይህ ንግግር የተደረገው ቤት ባልተሰጠበት፤ ዕጣ እንኳን ባልወጣበት፤ የቀበሌና የኮንዶሚኒየም ፈላጊ ባልተለየበት፤ የልጆች ት/ቤት፤ ስራና መሰል አስጨናቂ ብሶቶች መፍትሄ ባልተበጀላቸውና ምንም ስራ ባልተሰራበት ሁኔታ ውስጥ መሆኑ ደግሞ በነዋሪው ላይ የሚያሳድረውን ስነ-ልቦናዊ ጫና ማሰብ በራሱ ይበቃል፡፡ የቀደሙት ነዋሪዎች ከዚህ መሰሉ ፍርሐት የወጡትና የተሻለ ህይወት ለመኖር አካባቢያቸውን እንደለቀቁ የተረዱት እጅግ ዘግይተው ነበር፡፡ የሚመለከተው ክፍል ለመሰል መድረኮች የሚመድባቸው ሐላፊዎች ያላቸው የስራ ብቃት፤ እውቀት፤ ልምድና ሆደ ሰፊነት ሊጣመሩ እንደሚገባ ማሰብ የሚኖርበት ይመስለኛል፡፡ ግለሰባዊ ብቃት በወረደ ቁጥር መንገዱ ይበልጥ ዳገታማ ይሆናል፡፡የኢኮኖሚያዊ አቅም እጥረትን ለመቀነስ ያለመጣር የፌዴራል ስታትስቲክስ ኤጀንሲ የሚያወጣቸው ወርሐዊ መረጃዎች የሚያሳዩት፤ የኑሮው ውድነት የማይቀመስ መሆኑን ነው፡፡ አሁን… አሁን ኑሮን ለማሸነፍ የሚደረገው ትግል እንዲህ በዋዛ የሚዘለቅ አልሆነም፡፡ ነዋሪው ይህንን ዓለም አቀፍ እውነት ለመጋፈጥ የሚያበቃ የቁጠባ ባህልም ሆነ አቅም ባለቤት አይደለም፡፡ ሲያገኝ በልቶ ቢከፋው በጐጆው ሁሉን ችሎ ለመኖር በሚያደርገው መውተርተር ውስጥ ይሄን መሰል እድል ሲመጣ እድልነቱ ቀርቶ ዱብእዳ መሆኑ አይቀርም፡፡ በዚህ ወቅት እጅ ማጠሩም የተለመደ ነው፡፡ መንግሥት ለተነሺው ዘመናዊ የኮንደሚኒየም የጋራ መኖሪዎችን በምትኩ ሲያቀርብ በእድሉ ለመጠቀም የማይሻ የለም ለማለት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ፍላጐት ብቻውን “ሁሉን ቢናገሩት…“ ሆኖ ኑሮና እድል አልገጣጠም አሉ፡፡ በእርግጥ እድራትን የመሳሰሉ ማህበራዊ ተቋሞቻችን ይህን መሰል አቅምን ያገናዘበ የቁጠባ ልምድን ነዋሪው እንዲያዳብር ያለማድረጋቸው ጉዳቱ በገሐድ ታይቷል ለማለት ይቻላል፡፡ የአዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም ለዚህ መሰሉ እድለኞች ብድር ተጠቃሚነትን አመቻችቷል፡፡ ስጋቱ ግን ከዚህም አለፍ ይላል፡፡ ብድሩ ተወስዶ ቤትን ተረክቦ ዝም ማለት አይቻልም፡፡ ጊዜውን ጠብቆ እዳን መክፈል የግድ ይላል፡፡ ለእርሱ ሲታገሉ ደግሞ ንግድ ባንክም ድምሩን አስልቶ እጅህ ከምን ይላል፡፡ ልክ ነዋ! እርሱም ያበደረውን ገንዘብ መሰብሰብ ይኖርበታል፡፡ ይህን ችግር ለመቀነስ ተጨማሪ አማራጭ ሊኖር የሚችልበት ሁኔታም መታሰብ የሚገባው ሌላኛው የመስተዳድሩ የቤት ስራ ነው፡፡ ጣጣው እኮ . . . ብድሩ ቢገኝ እንኳን ዋስ ማበጀቱም በራሱ የዋዛ አይደለም፡፡
«ገንዘብ ካለ በሰማይ መንገድ አለ» የሚል መንፈስ መስፈኑ
ቀደም ባሉት ተነሺዎች ዘንድ በክፍለ ከተማውም ሆነ በቀበሌው አመራር ላይ ከታዩት እምነት ማጣቶች መሃከል ግንባር ቀደም የነበረው ሙስና ነው፡፡ በየቀበሌዎቹለ ነዋሪ ያልሆኑ፤ የግል መኖሪያ ያላቸው፤ በግለሰብ ቤት ተከራይ የነበሩ፤ በጥገኛ ስም የተመዘገቡ ነገር ግን የመንግስት የልማት አካል ያልሆኑ ግለሰቦች በገንዘባቸው ስለመንገሳቸው የአደባባይ ምስጢር ሆኖ ህብረተሰቡ ታዝቦትና ተጠቋቁሞበት አልፏል፡፡ የልማት ተነሺዎችን ስራ ማጠናቀቅን ተከትሎ በክፍለ ከተማው በተደረጉ ተከታታይ ግምገማዎችም ይህ እውነት መረጋገጡን መገናኛ ብዙሃን መዘገባቸውም የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡ በተቃራኒው በስማቸው መንግስት የመደበላቸውን ቤት የተነጠቁ፤ ዘመድ አልያም ገንዘብ ስላልነበራቸው መውደቂያ ያጡ፤ አለፍ ሲልም ፍርድ ቤት ድረስ ተጉዘው ፍትህ ያገኙትንም አይተን አልፈናል፡፡ በዚህኛው የመልሶ ማልማት እንቅሰቃሴ ወቅት ይሄን መሰሉን ድርጊት ሙሉ ለሙሉ ማቆም ባይቻል እንኳን መቀነስ ስለሚቻልበት ሁኔታ ከአሁኑ መዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ ኋላ እንደተለመደው «ሰርገኛ መጣ…» እንዳይሆን፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በተደራጁ የቤት አፍራሾች ስም የተካሄዱ የወንጀል ድርጊቶችና መሠል ህገ-ወጥ እንቅስቃሴዎችንም ቀድሞ ማየት ግድ ይላል፡፡ የአካባቢው ፖሊስና መስተዳድሩ ህብረተሰቡን በግልፅነት ባሳተፈ መልኩ መቀናጀትና አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግም የጋራ ሃላፊነታችን ሊሆን ይገባዋል፡፡ ታሪካዊና በቅርስነት ሊጠበቁ ስለሚገባቸው ቤቶችም መሰል ስህተትን ላለመድገም ቆም ብሎ የሚያስብ አካል ግድ ይላል፡፡
እኔ እንደ ትዝብቴና የከተማዋ ነዋሪነቴ የበኩሌን ወርውሬያለሁ፡፡ በጐደለው ሞልታችሁ፤ ከተረፈው ቀንሳችሁ ሌሎቻችሁም ሃሳብ አዋጡ፡፡ የአዱ ገነት ልማት ተጠቃሚው ማን ነው፡፡

Read 3948 times