Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 08 October 2011 10:30

ላባ አልባዋ ዶሮ እንደወፍ በራለች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በአለማችን በየአመቱ ከሚከናወኑት በርካታ አለምአቀፋዊ ጉባኤዎችና ስብሰባዎች አንዱ የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ ነው፡፡ በየአመቱ አንድ ወር ለሚጠጋ ጊዜ በድርጅቱ ዋና ጽሕፈት ቤት በሚከናወነው በዚህ ጠቅላላ ጉባኤ፤ በርካታ የሀገራት መሪዎች እየተገኙ መናገር አለብን ያሉትን ንግግር አድርገው ይመለሳሉ፡፡ በዚህ በአሁኑ የተባበሩት መንግስታት 66ኛ ጠቅላላ ጉባኤም የበርካታ ሀገራት መሪዎች በወጣላቸው ፕሮግራም መሠረት ንግግራቸውን አሠምተዋል፡፡

በዚህ ጉባኤ ከዚህ በፊት ድራማ አከል ድርጊት በመፈፀም ከተመደበላቸው ጊዜ ውጪ እጅግ ረጅምና የተንዛዛ ንግግር በማድረግ፣ ባላንጣዬ ያሉዋቸውን ሀገራት መሪዎች ከዲፕሎማሲ ስነምግባር ውጭ በሆነ ሁኔታ የሚዘልፉና የሚሳደቡ፤ ራሱን የተባበሩት መንግስታትንና ቻርተሩን የማይረባ በማለት በአደባባይ ቀደው የሚጥሉና ለጊዜውም ቢሆን የአለምን ትኩረት የሚስቡ እንደ ፊደል ካስትሮ፣ ሁጐ ቻቬዝ ሞሃመድ አህመዲ ነጃድና ሙአመር ጋዳፊን የመሳሰሉ መሪዎች በገጠማቸው የህይወት እጣ ምክንያት መገኘት ባይችሉና የተለመደውን ትርኢታቸውን ባያሳዩንም የተለያዩ መሪዎች ትኩረት ያገኙ ንግግራቸውን አሠምተውናል፡፡
ለምሳሌ የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ፤ በሶስት ገጽ ወረቀት በተፃፈ ንግግራቸው አሁን ያለንበት ጊዜ በመሸነጋገል ወይም በግትርነት የምናሳልፈው ሳይሆን ወጣቶቻችን የወደፊቱ ህይወታቸው ብሩህና አስተማማኝ እንዲሆን በሁሉም መስክ ለማብቃት ዝግጁ የምንሆንበትና በተግባርም የምንቀሳቀስበት ጊዜ መሆኑን አስገንዝበውናል፡፡
ይህ የወዲ አፎም ቅልብጭ ያለ ንግግር፣ በአዳራሹ ውስጥ ላሉትና በኤርትራ ለሚኖሩ ህዝባቸው ያለው ትርጉም ለየቅል ነው፡፡ በአዳራሹ የታደሙት የተለያዩ ሀገራት እድምተኞች ንግግሩን የፕሬዚዳንቱን የለውጥ ፍላጐትና ቁርጠኝነት ማሳያ የመጀመሪያው ምልክት አድርገው ሲወስዱት የሀገራቸው ህዝብ ግን ለሃያ አመታት ከብረት በጠነከረ መዳፍ፣ በተከታታይ ጦርነትና ከፍተኛ የኢኮኖሚ ድቀት የገደሉትን የሀገራቸውን ወጣት የነገ ተስፋ ከየት ቦታ፣ በየትኛው አይነት ተአምር እንደሚያመጡት በአግራሞት አምላካቸውን ጠይቀዋል፡፡ ባለፉት ሃያ አመታት ወደር በሌለው ትጋትና የአፈፃፀም ብቃት የህዝባቸውን በተለይ ደግሞ የወጣቷ ኤርትራ የነገ ተስፋና መመኪያ ይሆናሉ ተብለው ተገምተው የነበሩትን ወጣቶቻቸውን ህልምና ተስፋ በቀላሉ እንዳያንሰራራ አድርገው፣ ለጦርነት ማግደው በመግደል፣ ኤርትራን በመላው አለም በትልቅነቱ ወደር ወደአልተገኘለት ትልቅ እስር ቤትነት ለመለወጥ ለአፍታም ያላመነቱት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ፤ በተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ መድረክ ላይ ቆመው ከላይ የተገለፀውን እንከን የለሽ ማሳሰቢያና ምክር ለመላው አለም ለማቅረብ ጨርሶ አላመነቱም፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ያደረጉት ያ እንከን አልባና ምርጥ ንግግር ንግግር ሳይሆን ማስመሠልና ለበጣ ነበር፡፡ ያ ንግግራቸው ለአመታት ደምና አጥንት ገብረው ያገኙት ነፃነታቸው ድንገት እንደ ጧት ጤዛ በኖ በጠፋባቸው ኤርትራውያን ላይ የተደረገ ተራ ንቀትና ማላገጥ ነበር፡፡ ለመሆኑ የነፃነታችን አባት ብለው ሲዘምሩለትና በከፍተኛ ፍቅር ሲያሞካሹት በነበረው በገዛ መሪያቸው ማብቂያው ወደማይታወቅ መከራና እንግልት ለገቡት ምስኪን ኤርትራውያን ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ የበለጠ ጠላት ከየት ፈልጐ ማግኘት ይቻላል?
የዘንድሮው የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ፣ የሌሎች መሪዎችን አስገራሚ ንግግሮችንም አስተናግዷል፡፡ እንደ አሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ፣ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ናታንያሁና እንደ ፍልስጤም ባለስልጣን ፕሬዚዳንት ማህሙድ አባስ ቀልብን የገዛ ግን አልነበረም፡፡
የእነዚህ ሶስት መሪዎች ንግግር ያለንበትን ዘመን የአለም አቀፍ ዲፕሎማሲ መገለባበጥና ፍትህ አልባነት በገሀድ ያሳየ ነበር፡፡
ፕሬዚዳንት ማህሙድ አባስ፤ የሀገራቸውንና የህዝባቸውን የሉአላዊ ሀገርነት ጥያቄ ሲያቀርቡ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ናታንያሁ በበኩላቸው፤ በተዋጣለት የመድረክ ቅንብር የፍልስጤም ነፃ መንግስትነት ዘመን ገና እንዳልተፀነሰ ጠቅሰው በእስራኤሎች መልካም ፈቃድና ውሳኔ ገና ተጠፍጥፎ እንዳልተሰራ አስረድተዋል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማም ባቀረቡት ንግግር፤ በዓለም የዲፕሎማሲ መድረክ ያላቸውን የመገለባበጥ ችሎታ በግልጽ አሳይተውበታል፡፡ ኦባማ የፍልስጤምንና  የእስራኤልን ጉዳይ በሚመለከት ወደው የገቡትን ቃልና በቅርቡም ያነሱትን ሀሳብ መቶ በመቶ በማጠፍ፣ የፍልስጤምን የነፃ ሀገርነት ጥያቄ እንደማይቀበሉትና በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ቢቀርብ ድምጽን በድምጽ በመሻር መብታቸው እንደሚቃወሙት ሳያመነቱ ተናግረዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ኦባማ ይህን ሀሳባቸውን የገለጹበት ንግግር መቼም ድንቅና ቋንቋውም ከሚገባው በላይ ገላጭ ነበር፡፡
የመከራከሪያ ሀሳቦቹም ግልጽና አሳማኝ፣ አቀራረባቸውም እንከን አልባ ነበሩ፡፡
ነገርየው ልክ እንደ አንድ የጥበብ ስራ የሚታይ ነው፡፡ የማስመሠል የጥበብ ስራ፡፡ በንግግራቸው ውስጥ የእስራኤልንና የፍልስጤምን ጉዳይ ያቀረቡበት ክፍል ሙሉ በሙሉ ውሸት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ፕሬዚዳንቱም ሆነ በአዳራሹ ውስጥ ታድሞ ያዳምጣቸው የነበረው ሁሉ ጠንቅቀው የሚያውቁት የለየለት ውሸት፡፡
ፕሬዚዳንት ኦባማ ልክ እንደ አንድ የሞራል ሰው፣ ያን ንግግር ሲያደርጉ አዕምሯቸውም ሆነ መንፈሳቸው ሊታወክ በተገባው ነበር፡፡ እንደ አንድ ፕራግማቲክ ግለሰብና ፖለቲከኛ በአገራቸው በድጋሚ ለፕሬዚዳንትነት መመረጥ ከፈለጉ ግን ሰውየው ምን ማድረግ እንዳለባቸው ጠንቅቀው የሚያውቁ ናቸው፡፡ ያደረጉትን ሁሉ ያደረጉትም በዚሁ ምክንያት ነበር፡፡ ድርጊቱ መልካም ነው ባይባልም መቸስ ምን ይደረግ የፖለቲካ ነገር እንዲህ ነው ይላሉ ታዛቢዎች፡፡
የሆኖ ሆኖ ፕሬዚዳንት ኦባማ የእስራኤልንና የፍልስጤምን ጉዳይ ያቀረቡበት ንግግራቸው በበርካታ ስህተቶች የተሞላ ነበር፡፡ ፕሬዚዳንት ኦባማ በዚያ ንግግራቸው ፍልስጤምንና እስራኤልን ያቀረቧቸው ባላቸው ጥንካሬ ልክ እኩል እንደሆኑ ሀገራት አድርገው ነው፡፡ ይሁን እንጂ ለፕሬዚዳንት ኦባማ የተንገላቱትና እየተንገላቱ ያሉት እስራኤላውያን ብቻ ናቸው፡፡ የተሰደዱት የተጨፈጨፉት እስራኤላውያን ብቻ ናቸው፡፡ የሮኬት ጥቃት ያንዣበበባቸው እስራኤላውያን ህፃናት ብቻ ናቸው፡፡ በለየለት የአረብ ጥላቻ ተከበው የሚገኙት የእስራኤል ህፃናት ብቻ ናቸው፡፡ እንዴት ያሳዝናል?  
ለፕሬዚዳንት ኦባማ ወረራ፣ የሠፈራ ግንባታ፣ የ1967 ዓ.ም ድንበርና ናቅባ ብሎ ነገር የለም፡፡ በእስራኤል የቦንብ ድብደባ የተገደለና ቀን ብሌት በፍርሃት የሚርድ ፍልስጤማዊ ህፃን ጨርሶ የለም፡፡ ኦባማ በንግግራቸው የተጠቀሙባቸው ቃላት፣ ትረካና የመሟገቻ  ሀሳቦች ከእስራኤል የቀኝ ክንፍ ፕሮፖጋንዳ ጋር አንዳችም አይነት ልዩነት አልነበረበትም፡፡ እናም ያኔ በጉባኤው ላይ ንግግር ሲያደርጉ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሳይሆን አንድ የእስራኤል የቀኝ ክንፍ ፖለቲከኛን ነበር የሚመስሉት፡፡
ፍልስጤማውያን በእርግጥ የራሳቸው የሆነ ሉአላዊ ሀገር ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ነገር ግን እንዲህ መጣደፍ አልነበረባቸውም፡፡ አሜሪካንን እንዲህ ማሳፈር አልነበረባቸውም፡፡ እውቅና ፍለጋ ወደተባበሩት መንግስታት መምጣት አልነበረባቸውም፡፡ ልክ እንደሠለጠነ ህዝብ ከእስራኤሎች ጋር ቁጭ ብለው መነጋገርና የሠጧቸውን ተቀብለውና እጅ ነስተው መሄድ ነበረባቸው፡፡ ለኦባማና ለአሜሪካ የሚፈለገው ይህ እንዲሆን ነበር፡፡ የሠለጠነ በግ ከሠለጠነ ተኩላ ጋር ቁጭ ብሎ ለእራት ምን አይነት ምግብ መቅረብ እንዳለበት ሲደራደሩ አልታያችሁም?
ፕሬዚዳንት ኦባማ በዚያ ንግግራቸው ተገቢውን ሙሉ አገልግሎት ለእስራኤልና ለእስራኤል ደጋፊ የአሜሪካ ከባባድ የፖለቲካ ማሽኖች ሠጥተዋል፡፡ እንዲህ ያለ አገልግሎት የሰጠ ወሸኔ አገልጋይ ደግሞ ምንዳው የሚከፈለው በቅድሚያ ነው፡፡ ፕሬዚዳንት ኦባማ ለዚህ ወደር የለሽ አገልግሎታቸው ክፍያቸውን ያገኙት በሰአታት ልዩነት ወዲያውኑ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ናታንያሁ፤ በቴሌቪዥን ካሜራ ፊት ለፊት ከፕሬዚዳንት ኦባማ ጋር ቁጭ በማለት ለምርጥ ጥቅስ የሚበቃ የፍቅርና የሙገሳ ዝናብ አዝንበውላቸዋል፡፡
የዚህ ዋና ጉዳይ አሳዛኙ ጀግና የፍልስጤሙ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ማህሙድ አባስ ናቸው፡፡ በተባበሩት መንግስታት ጉባኤ ባደረጉት ንግግርና ባቀረቡት የእውቅና ጥያቄ፤ ታላቋንና ጉልበተኛዋን አሜሪካንን ለመጋፈጥ ፈቃደኛ የሆነና ትልቅ፣ ብሔራዊ ጉዳይ ባዘለ አጋጣሚ ጥቅሙን ለማስጠበቅ ደፋርና የማያመነታ ተዋናይ ሆኖ በድንገት ብቅ ማለት ብዙዎችን ያስገረመና ያስደነቀ ነበር፡፡ ቤንያሚን ናታንያሁ መሆናቸው እንጂ አርየል ሻሮን ለአመታት ከዘለቀው ኮማቸው ድንገት ነቅተው ይህንን ነገር አይተው ቢሆኑ ኖሮ በከፍተኛ መደነቅ ራሳቸውን ስተው ይወድቁ ነበር፡፡
ከአመታት በፊት “ላባዋ የተነጨ ዶሮ” የሚል ስም ለማህሙድ አባስ ያወጡላቸው አሪየል ሻሮን ነበሩ፡፡ ነገር ግን ባለፉት ሳምንታት የአለምን የፖለቲካ ቀልብ ገዝተው የከረሙት ማህሙድ አባስ ነበሩ፡፡ በተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ ያሠሙት ንግግር፤ ነገሮች ባስከተሉት መዘዝ እንደተፈጠረ አንድ ሁነት ተደርጐ ተቆጥሮላቸዋል፡፡ እንኳን ላባው ለተነጨ ዶሮ ለባለሙሉ ላባዋም ቢሆን ከበቂ በላይ ነው፡፡
የማህሙድ አባስ በአለም የፖለቲካ መድረክ በመሪነት ብቅ ማለት ሟቹን የግብጽ ፕሬዚዳንት አንዋር ሳዳትን ያስታውሰኛል፡፡
ፕሬዚዳንት ጋማል አብደል ናስር በ1970 ዓ.ም ባልተጠበቀ ሁኔታ በሀምሳ ሁለት አመታቸው እንደሞቱና ምክትላቸው የነበሩት አንዋር ሳዳት የፕሬዚዳንትነቱን ቦታ እንደያዙ የፖለቲካ ኤክስፐርት የተባለ ሁሉ “ሳዳት ለመሆኑ ማን ነው?” በማለት  ሳዳትን አናንቋቸው ነበር፡፡ ያኔ ሳዳት ምንም ሁነኛ ስልጣን የሌለው፣ ሁለተኛው ሰው ከመባል ውጭ “ቢኖር የማይጠቅም ቢሞት የማይጐዳ” አይነት ሰው ተደርገው ነበር የተቆጠሩት፡፡ ያኔ የቀልድና የቀልደኞች ሀገር የሆነችው ግብጽ፤ በአንዋር ሳዳት ላይ የቀልድ አይነት ፈብርካ አስወርታባቸው ነበር፡፡ ከቀልዶቹ አንዱ በሳዳት ግንባር ላይ ያለውን ጠቆር ያለ ቆዳ የሚመለከት ነበር፡፡ ምልክቱ እንደሌላው ሙስሊም ሶላት ሲሰግዱ የወጣባቸው ሳይሆን በስብሰባና በሌላ አጋጣሚ ሁሉ ሳዳት አንድ ነገር ሊናገሩ ብድግ ሲሉ፣ ናስር “ቁጭ በል ሳዳት” እያሉ በጣታቸው ግንባራቸውን እየገፉ ሁሌም ስለሚያስቀምጧቸው ነው ተብሎ በቀልድ ተወራባቸው፡፡ መጨረሻ ግን እንደ አይረቤ የሚቆጠሩት ሳዳት ነበሩ የ1973ቱን የጥቅምት ጦርነት በማስጀመርና በዋነኛ ጠላታቸው በእስራኤል ፓርላማ ተገኝተው ማንም ያላሰበውን አጃኢብ ንግግር በማድረግና የሠላም ስምምነት በመፈራረም አለምን ያስደመሙት፡፡
በያሲር አራፋት ስር ማህሙድ አባስ የነበራቸው ደረጃ ሳዳት በናስር ጊዜ ከነበራቸው ብዙም አይለያይም፡፡ የተለየ ነገር ይፈለግ ቢባል አራፋት ምክትላቸውን ሾመው አለማወቃቸው ብቻ ነበር፡፡ ስለዚህ አባስ አራፋትን ሊተኩ ይችላሉ እየተባሉ ከሚታሰቡት አራት ሰዎች አንደኛው ነበሩ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ በሚስቱና በልጆቹ ፊት በእስራኤል ኮማንዶዎች ባይገደል ኖሮ የመጀመሪያው ተመራጭ አቡጂሃድ ነበር፡፡ ከሱ ቀጥሎ ደግሞ በፍልስጤም ሽብርተኞች የተገደለው አቡ አያድ ነበር፡፡ አራተኛው ሰው ይህን ያህል ስለማይታወቅ የቀረው ወራሽ አቡማዘን ወይም ማህሙድ አባስ ነበሩ፡፡
እንደ ማህሙድ አባስ አይነት ከታዋቂ መሪ ጥላ ስር ድንገት ብቅ የሚሉ መሪዎች በሁለት ይከፈላሉ፡፡ አንደኛው የሁልጊዜም ምስኪን ቁጥር ሁለት ሲሆኑ ሌላኞቹ አስገራሚዎቹ አዲስ መሪዎች ናቸው፡፡ የሁለቱን አይነት መሪዎች ምሳሌ መጽሐፍ ቅዱስም ይሰጠናል፡፡ አንዱ የታላቁ ጥበበኛ ንጉስ የሰሎሞን ልጅና ወራሽ ሮብአም ነው፡፡ ሮብአም ህዝቡን ሰብስቦ “አባቴ ይገርፋችሁ የነበረው በጅራፍ ነበር፡፡ እኔ ግን የምገርፋችሁ በጊንጥ ነው” በማለት ከአባቱ የተለየ ንጉስ መሆኑን አሳውቋቸዋል፡፡ ሌላኛው አይነት ደግሞ የሙሴ ወራሽ በሆነው በእያሱ ይወከላል፡፡ እያሱ ሁለተኛው ሙሴ አልነበረም ነገር ግን በራሱ ብዙ ገድል የፈፀመ መሪ ነበር፡፡
ዘመናዊው የአለማችን ታሪክ ደግሞ የምስኪኑን እንግሊዛዊ ፖለቲከኛ የአንቶኒ ኤደንን አሳዛኝ ታሪክ ይነግረናል፡፡ አንቶኒ ኤደን ለረጅም ጊዜ ያለአንዳች ክብርና እውቂያ በእንግሊዝ የፖለቲካ መድረክ ተዋናይ የነበረ፣ የዊኒስተን ቸርችል ሁለተኛ ሰው ነበር፡፡ ምንም ቢሠራ ያው የጠቅላይ ሚኒስትር ሁለተኛው ሰው ብቻ ነበር መታወቂያው፡፡
በወቅቱ የጣሊያን መሪ የነበረው ቤኒቶ ሙሶሎኒ ከእሱም ብሶ ከአንቶኒ ኤደን ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ተገናኝቶ ከተወያየ በኋላ ለጓደኞቹ ያማው “በደንብ የተሠፋ ደደብ ሰው ነው” ብሎ ነበር፡፡ ማንም አንቱ ብሎ እንኳ አይጠራውም፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩትን ዊኒስተን ቸርችልን ተክቶ፣ በተራው ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሆነ በከፍተኛ ቁርጠኝነት ግብግብ የገጠመው ቸርቺልን ለማከል ነበር፡፡ ወዲያውኑም ታዲያ እንግሊዝን የማገዳት በ1956 ዓ.ም በተካሄደው የስዊዝ ካናል ቀውስ ውስጥ ነበር፡፡
አሜሪካዊው ሀሪ ትሩማንም የአሠላለፍ ደረጃው በሁለተኛው ዲቪዚዮን ነበር፡፡ የታላቁ ፕሬዚዳንት የፍራንክሊን ዴላኖ ሩዝቬልት ቁጥር ሁለት፡፡ እሱ ግን ፕሬዚዳንት ከሆነ በኋላ የማያወላውል ቆራጥ መሪ መሆኑን ለሀገሩም ሆነ ለአለም በሚገባ ማሳየት ችሏል፡፡
የፍልስጤሙ ማህሙድ አባስም ከመጀመሪያው ጐራ የተመደቡ መስለው ነበር፡፡ ነገር ግን ድንገት የሁለተኛው ጐራ አባልና ጠንካራ መሪ መሆናቸውን ማስመስከር ችለዋል፡፡ ዛሬ አለም የምታስተናግዳቸው አዲስ በተገኘው ክብር ነው፡፡ ትንሽ ቅር የሚያሰኘው ነገር ቢኖር እኚህ አዲሱ ማህሙድ አባስ የተገኙት በመጨረሻው የታሪክ ዘመናቸው ጊዜ መሆኑ ነው፡፡ ማህሙድ አባስ እኮ እየሸመገሉ ነው፡፡
እንዲህም ሁሉ ሆኖ ማህሙድ አባስ የፍልስጤምን የነፃነት ጥማትና የረጅም ጊዜ ጥያቄ ያለ አንዳች ማመንታት በአለም አቀፍ የዲፕሎማቲክ ጠረጴዛ ላይ ማስቀመጥ ችለዋል፡፡
ላለፉት ሳምንታት ፍልስጤም የአለምን የፖለቲካ ቀልብ ሠቅዛ ይዛው ከርማለች፡፡ የአለም ብቸኛዋ ልዕለ ኃያል አሜሪካም በፍልስጤም ጉዳይ ራሷን ባተሌ አድርጋ ባጅታለች፡፡ ለአንድ ብሔራዊ ንቅናቄ በእርግጥም ከዚህ የበለጠ ጠቃሚ ነገር የለም፡፡
አንዳንድ ጨለምተኞች ታዲያ “ምን ይጠበስ? ከዚህ ምን ጠብ የሚል ነገር ተገኘ?” በማለት ነገሩን ሊያጣጥሉት ይችላሉ፡፡ ግን እኮ ጨለምተኞች ሞኞች ናቸው፡፡ አንድ የነፃነት ንቅናቄ በአለም ሚዲያ ተገቢውን እውቅናና ትኩረት ሲያገኝ አለምም ተገቢውን ትኩረት ሲለግሰው፣ የመላው አለም ህዝብ ህሊና በነፃነት ንቅናቄው አላማና ትግል ጉዳይ ላይ ስሜቱ ይነቃቃል፡፡
ይህም የተጨቆነውን ህዝብ ሞራል በማነሳሳት፣ የነፃነት ትግሉን በአንድ እርምጃ ወደ ግቡ ያቀርበዋል፡፡
ጭቆና መድረኩን ይነጥቃል፤ ያጨልማል፡፡ ወረራ፣ ህገወጥ ሠፈራና የዘር ማጥራትን የሚያስቡት በጨለመ መድረክ ነው፡፡ የቀኑን ብርሃን ለማየት የሚናፍቁትና የሚመኙት የተጨቆኑ መሬታቸው በጉልበተኞች የተነጠቀባቸው ናቸው፡፡ ለጊዜውም ቢሆን የማህሙድ አባስ እርምጃ ለእነዚህ አይነት ህዝቦች የብርሃን ጭላንጭል ፈንጥቆላቸዋል፡፡
የፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ንግግር ግን ፋይዳ ቢስ ሆኖ ታይቷል፡፡ የአረቡ አለም አዲሱ አብዮት፤ አሜሪካ በመካከለኛው ምስራቅ ያላት አቋምና ሁኔታ እንዲያገግም አንድ እድል ፈጥሮላት ነበር፡፡ ከትንሽ ጊዜ ማመንታት በኋላም ቢሆን ኦባማ ይህንን አዲስ እድል ተገንዝበውት ነበር፡፡ የግብፁ አምባገነን ሆስኒ ሙባረክ ከስልጣን መንበሩ ዞር እንዲሉ ጥሪ አቅርበውላቸው ነበር፡፡ ሊቢያውያን ፈላጭ ቆራጭ መሪያቸውን ሙአመር ጋዳፊን እንዲያስወግዱ የተግባር እርዳታ አድርገውላቸዋል፡፡ የሶሪያውን አምባገነን መሪ በሻር አልአሳድን በተመለከተም ጥቂት ጩኸት ቢጤ ማሠማት ችለው ነበር፡፡ በአረቡ አለም ከበሬታን በማግኘት በመላው አለም ያላቸውን ተሰሚነትና ከበሬታ መጨመር እንደሚገባቸው ተረድተውት ነበር፡፡ ታሪክም የልብ አውቃ ይመስል ይህንን አመቻችታላቸው ነበር፡፡ ነገር ግን ፕሬዚዳንቱ ይህን እድል ምናልባትም ለሁሌም አበላሽተውታል፡፡ በንግግራቸው የተቆጩ አረቦች፣ ሰውየው የምስኪን ፍልስጤማውያንን ጀርባ በጩቤ እንደወጉት ሊቆጥሩባቸውና ቂም ሊይዙባቸው ይችሉ ይሆናል፡፡ የአረቦችን በተለይም ደግሞ የመላውን ሙስሊሞችን አመኔታ ለማግኘት አሜሪካ ያደረገችውን ጥረት ሁሉ የእኒህ ሰው ንግግር በአንዴ እፍ ብሎ አጥፍቶታል፡፡ ኦባማ ይህን ሁሉ ነገር ያደረጉት ግን ሳያውቁ ሳይሆን በድጋሚ በፕሬዚዳንትነት ለመመረጥ ሲሉ ብቻ ነው፡፡ ፕሬዚዳንት ኦባማ በዚያ ንግግራቸው የጐዱት አሜሪካንን ብቻ ሳይሆን እስራኤልንም ጭምር ነበር፡፡ እንዴ… እስራኤል እኮ ሠላምን ትፈልጋለች፡፡ ከአረቡ አለምም ሆነ ከፍልስጤማውያን ጋር ጐን ለጐን በሠላምና በመተባበር መኖር ትፈልጋለች፡፡
እስራኤል አቅሟና ግርማ ሞገሷ ዕለት ተዕለት እየቀነሰ የመጣውን የአሜሪካን ያልተቋረጠ ድጋፍ ተማምና አሁን በያዘችው አቋም ለዘላለም መኖር አትችልም፡፡ ፕሬዚዳንት ኦባማም ይህን ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ ምንም እንኳ የእስራኤሉ መሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ናታንያሁ ጠንቅቀው ባያውቁትም ኦባማ ለእስራኤል ምን እንደሚያስፈልጋት ያውቃሉ፤ ይሁን እንጂ የመኪናውን ቁልፍ ያስረከቡት ጥንብዝ ብሎ ለሰከረው ሹፌር ነው፡፡ ነገ ዛሬ ብሎ ትክክለኛውን ቀን በእርግጠኝነት ለመተንበይ ቢያስቸግርም ሀገረ ፍልስጤም መመስረቷ አይቀርም፡፡ ያለፉት ሳምንታት ሁኔታዎች ይህን ነገር ጨርሶ ማስወገድ እንደማይቻል በግልጽ አሳይተዋል፡፡ ናታንያሁም ሆነ ኦባማ መረሳታቸው አይቀርም -  ያው ሌሎች እንደተረሱት ሁሉ፡፡ አቡ ማዘን እያሉ ህዝባቸው የሚጠሩዋቸው ማህሙድ አባስ ግን በዚያ ታሪካዊ ድርጊታቸውና ንግግራቸው ይታወሳሉ፡፡ ላባ አልባዋ ዶሮ በእርግጥም እንደ ወፍ በራለች፡፡

 

Read 4778 times Last modified on Saturday, 08 October 2011 10:33