Saturday, 08 October 2011 10:26

የቀድሞውና የወደፊቱ የራሺያ ፕሬዚዳንት

Written by  አልአዛር ኬ.
Rate this item
(0 votes)

ለአፍሪካውያን መሪዎች ተመራጭ የሥልጣን ዕድሜ ማራዘምያ
የዛሬ አምስት አመት ገደማ በራሽያ በተደረገ ብሔራዊ የፕሬዚዳንትና     የፓርላማ ምርጫ ያሁኑ ፕሬዚዳንት ዲሚትሪ ሜድቬዴብ በአሸናፊነት የፕሬዚዳንትነት መንበሩን በመቆጣጠር፣ የቀድሞውን አለቃቸውን ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲንን ጠቅላይ ሚኒስትር አድርገው መሾማቸው የቀድሞው ፕሬዚዳንት ፑቲንም አዲሱን የጠቅላይ ሚኒስትርነት ስልጣኑን ተቀብለው ለመስራት የመስማማታቸው ዜና በመላው አለም እንደተሰማ፣ ቭላድሚር ፑቲን በራሽያም ሆነ በተቀረው አለም እምብዛም ያልታየ አዲስ አይነት የምርጫና የህገመንግስቱን የስልጣን መገደቢያ አንቀጾች በርካታ የአለማችን ሀገራት መሪዎች እንደሚያደርጉት ወይም ለማድረግ እንደሚጥሩት ፍጥጥና  ድርቅ ብለው ሳይደልዙ ስልጣንን መልሰው ሲይዙ የሚችሉበት ዘዴና የአሠራር አብዮት እያካሄዱ እንደሆነና ምናልባትም በታሪክ የመጀመሪያው የቀድሞውና የወደፊቱ የራሽያ ፕሬዚዳንት ሊሆኑ እንደሚችሉ የነበረኝን ግምት በማንሳት በዚሁ ጋዜጣ ላይ ተጨዋውተን ነበር፡፡

ያኔ ከአመታት በፊት የገመትነው ግምት እነሆ የራሱን ሂደት ተጉዞና የራሱን ጊዜ ቆጥሮ እውን ሆኖ በተግባር ልናየው በእጅጉ ተቃርበናል፡፡ ካሳለፍነው ሳምንት ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ በጠቅላይ ሚኒስትር ፑቲን የሚመራው የዩናይትድ ራሽያ ወይም የተባበረችው ሩሲያ ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤውን በማካሄድ፣ ከጥቂት ወራቶች በኋላ በሚካሄደው የራሽያ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ፓርቲውን ወክለው እንዲወዳደሩ የቀድሞውን ፕሬዚዳንትና የአሁኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ቭላድሚር ፑቲንን በዋና እጩነት ለማቅረብ መወሰኑን በይፋ አስታውቋል፡፡  
ቭላድሚር ፑቲን ፕሬዚዳንት ሳሉ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ያገለገሉትና የአሁኑ ፕሬዚዳንት ድሚትሪ ሜድቬዴቭም በመጪው ምርጫ ለሁለተኛ ዙር ፕሬዚዳንትነት እንደማይወዳደሩና የፑቲንን ፕሬዚዳንታዊ እጩነት በሙሉ ልብ በመደገፍ፣ በመጪው ምርጫ ድል እንዲቀናቸው፣ እንኳን በፕሬዚዳንት ስልጣናቸው ይቅርና በጾም በፀሎትም ቢሆን እንደሚያግዟቸው በፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ ወቅት ስሜት ፈንቅሏቸው፣ ሲቃ እየተናነቃቸው ይፋ አድርገዋል፡፡  
ፕሬዚዳንት ሜድቬዴቭ በጉባኤው ወቅት እንዲያ በስሜት እየተወራጩ፣ የፑቲንን   የላቀ የአዕምሮና የመሪነት ብቃት፤ የነጠረ አቻ የለሽ የፖለቲካ ሰውነት ሲተርኩ ለወደር የለሹ ቭላድሚር ፑቲን፤ እንኳን ራሱ የሰጠኝን የፕሬዚዳንትነት ስልጣን ይቅርና ሞቴንም ቢሆን ከፑቲን በፊት ያድርገው እያሉ አምላካቸውን የሚማፀኑ ይመስል ነበር፡፡
የፕሬዚዳንት ሜድቬዴቭን እንዲህ መሆን የታዘቡ፣ የራሽያን ፖለቲካ ነገረ ስራ በቅርብ የሚያውቁና የላይ ታች ሂደቱን የሚከታተሉ ተረበኛ ተንታኞች ..ወደሽ ነው ቆማጢት ንጉስ ትመርቂ.. እንደሚባለው የፉተታ አነጋገር ..ወዶ ነው ሜድቬዴቭን የንጉሱን የፑቲንን ትዕዛዝ ተቀብሎ ከምርጫ እጩነት ራሱን የማያወጣና ላንተ የተባለው አረር በእኔ በአሽከርህ ግንባር ይሰካ.. ብሎ ጃሎ መገኔ የማይለው? እንዴ... ቀድሞ ነገር ፕሬዚዳንት ሜድቬዴቭ እኮ የፑቲን የእጅ ስራ ውጤት እኮ ነው፡፡ ከተራ የመንግስት ኩባንያ መሪነት አንስቶ የፖለቲካ ሰብዕናውን በራሱ አምሳልና ፍላጐት ጠፍጥፎ የፈጠረውና የዛሬ ማንነቱ ባለቤት እንዲሆን ያደረገው፣ ወልዳ ያሳደገችው እናቱ ሳትሆን ንጉሱ ፑቲን ነው፡፡ ታዲያ እንኳን በእጁ የሰጠውን የፕሬዚዳንት ስልጣን መልሶ ማስረከብና ሞቴን ካንተ በፊት ያድርገው ማለት አይደለም ሌላስ ነገር ቢለው ምናለ? በማለት ፕሬዚዳንት ዲሚትሪ ሜድቬዴቭን በአደባባይ ሲያሽሟጥጧቸውና ሲቦጭቋቸው ባጅተዋል፡፡
የወደፊቱ የፖለቲካ እጣ ፈንታቸው በጠቅላይ ሚኒስትር ቭላድሚር ፑቲን እጅ ውስጥ እንዳለና ወሳኙ ሰውም ራሳቸው ሳይሆኑ ፑቲን ብቻ እንደሆኑ ጠንቅቀው የሚያውቁት ፕሬዚዳንት ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ የተቺዎቻቸው እንዲህ ያለው ሽሙጥና ሀሜት ቁብም አልሰጣቸው፡፡ ይልቁንስ ይህን ሽሙጥና ሀሜት ሰምቶ እንዳልሠማ ቸል በማለት ዋና ትኩረታቸውን ያደረጉት ንጉሱ ፑቲን በቀጣይ ሊወስዱት ባሰቡት እርምጃና ባቀዱት እቅድ ላይ ብቻ ነበር፡፡
በገዢው የተባበረው ሩሲያ ፓርቲ መሪነታቸው በተዘጋጀላቸው ወንበር ላይ ተቀምጠው የፕሬዚዳንቱን የሜድቬዴቭን እንዲያ ያለ በስሜት የተሞላ ንግግር ከጀርባ ቁልቁል ሲያዳምጡ የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ፑቲን፤ የሳቸውን ፕሬዚዳንታዊ እጩነት ያለአንዳች ማንገራገርና የሚታይ የስሜት ለውጥ በመቀበል ላሳዩት ቁርጠኝነትና የማያወላዳ ታማኝነት የተሰማቸው ደስታ በግልጽ የሚታይ ነበር፡፡ የፓርቲያቸውን ፕሬዚዳንታዊ እጩነት በይፋና በሙሉ ልብ መቀበላቸውን ለመግለጽ ባደረጉት ንግግርም፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ፑቲን ፕሬዚዳንት ሜድቬዴቭን ገዢውን ፓርቲያቸውNÂ ላለፉት አምስት አመታት ሀገሪቱን በፕሬዚዳንት በመምራት ያደረጉትን አስተዋጽኦ በማድነቅ የሙገሳ ብድራቸውን መልሰዋል፡፡ ፑቲን በዚያ ንግግራቸው በሙገሳ ብቻ አላበቁም፡፡
በመጪው ምርጫ በለስ ቀንቷቸው ቢያሸንፉ (እርሳቸው ለይሉኝታ ብለው ድንገት ባሸንፍ ይበሉ እንጂ ህዝቡም ሆነ የፖለቲካ ተንታኞች የእሳቸው በከፍተኛ አብላጫ ድምጽ ማሸነፋቸው የተበላ እቁብ አይነት ነገር ነው ይላሉ) ፕሬዚዳንት ሜድቬዴቭን በጠቅላይ ሚኒስትርነት እንደሚሾሟቸው ለአፍታም ቢሆን የማያጠራጥር ያለቀ የደቀቀ ነገር እንደሆነ ያኔውኑ ግልጽ አድርገውላቸዋል፡፡
ቀደም ብሎ እንደተገለፀው የወደፊት የፖለቲካ እጣፈንታቸው ያለውና የሚወሰነው በንጉሱ በፑቲን እጅ መሆኑን በሚገባ የሚያውቁት ፕሬዚዳንት ሜድቬዴቭ፤ ከምርጫው በኋላ ከቀድሞ ፕሬዚዳንትነት ወደ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትርነት በመዛወር፣ ከቀድሞ ፕሬዚዳንትነትና ጠቅላይ ሚኒስትርነት እንደገና ወደ አዲሱ የራሽያ ፕሬዚዳንትነት የተሸጋገሩትን የጌታቸውን የፑቲንን ሞገስና ቅርበት ሳያጡ፣ የሀገሪቱ ሁለተኛው ቁልፍ ሰው እንደሆኑ የመቀጠላቸው ዜና በደስታ ራሳቸውን ሊያስታቸው ደርሶ ነበር፡፡ እናም የፑቲንን እቅድና ግብዣ በከፍተኛ የደስታ ስሜት እንደተቀበሉት ያስታወቁት እዚያው የጉባኤው አዳራሽ ውስጥ እንዳሉ ከመቅጽበት ነበር፡፡
ከቀድሞው ውስብስብነቱ በተጨማሪ ፑቲን ወደ ፖለቲካው ስልጣን ከመጡ በኋላ በዘረጉት የተለየ የፖለቲካ የስልጣን ድር የበለጠ በተወሳሰበው የራሽያ ፖለቲካ ውስጥ የፕሬዚዳንትነት ዘመን ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ስልጣን የመታጨት ዜና፣ በእርግጥም የተለየ እና ሳይታሰብ ከሰማይ ድንገት እንደወረደ መና ያህል የሚቆጠር ነበር፡፡
ንጉሱ ፑቲን ግን ያለአንዳች ፖለቲካዊ እንገጭ እጓና ህገመንግስታዊ ውዝግብ፣ ከአምስት አመታት በፊት ራሳቸው በግላቸው አቅደውና መርጠው ላዘጋጇቸው ተተኪያቸው በፀባይ ያስረከቡትን የፕሬዚዳንትነት ስልጣን በድጋሚ ያለ አንዳች ፖለቲካዊ ውጣ ውረድና ኮሽታ መልሰው የሚረከቡበትን የምርጫና ህገመንግስታዊ አብዮት ጀምረው ባጥጋቢ ሁኔታ በማሳካት፣ አለሙን ሁሉ እንዳስገረሙት ሁሉ ፕሬዚዳንት ሜድቬዴቭን እንደገና አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትራቸው ለማድረግ በመወሠን ወደፊት ደግሞ ምን አይነት የስልጣን ሽግግር ስርአት ሊዘረጉ እንዳሰቡ፣ ለፖለቲካ ተንታኞችና ለተቃዋሚዎቻቸው አዲስ የቤት ስራ ሰጥተዋቸዋል፡፡ ይህን ጉዳይ እንደ ቀላል የቤት ስራ የሚቆጥሩት ቢኖሩ የፑቲንና የፓርቲያቸው ደጋፊዎች ብቻ ናቸው፡፡ ለእነዚህ ሰዎች ንጉስ ፑቲን የፖለቲካና የስልጣን ዋዛ ፈዛዛ የማያውቁ ቆፍጣና መሪ ናቸው፡፡ ለእነዚህ ሰዎች ብላድሚር ፑቲን ከሶቪየት ህብረት መፈራረስ በኋላ ራሽያ ያጣችውን ክብር በማስመለስ ከቀደሙት ገናና የራሽያ ነገስታት በተሻለ በአለም የፖለቲካና የኢኮኖሚ መድረክ ተገቢና የላቀ የክብር ቦታ እንድትጐናፀፍ ያስችለናል ብለው በእርግጠኛነት የሚተማመኑባቸውና ያንን የተቀደሰ ቀንም በተስፋ የሚጠባበቁላቸው መሪ ናቸው፡፡  
እንደ እውነቱ ከሆነ በዘመነኛ የፖለቲካ ታሪኳ ሩሲያ እንደ ቭላድሚር ፑቲን ያለ ጮሌና ቆቅ ፖለቲከኛ ወልዳ አታውቅም፡፡ ሟቹ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ቦሪስ የልሲን   በጠቅላይ ሚኒስትርነት እስከተሾሙባት ጊዜ ድረስ የኬጂቢ ኮሎኔል ከመሆናቸውና ረዘም ላለ ጊዜም በቀድሞዋ ምስራቅ ጀርመን ውስጥ ተመድበው ከመስራታቸው ውጭ ስለ ቭላድሚር ፑቲን የፖለቲካ ማንነት እምብዛም የሚታወቅ ነገር አልነበረም፡፡
በዚህ የተነሳም በፕሬዚዳንት የልሲን የስልጣን ዘመን ድንገት ብቅ ብለው ወዲያውኑ ከመድረኩ ሲጠፉ እንደነበሩት የተለያዩ ፖለቲከኞች፤ የፑቲን እጣም ከእነሱው የተሻለ እንደማይሆን በበርካቶች ዘንድ በእርግጠኝነት ተገምቶ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ከተገመተው እጅግ በተቃራኒው ከሌሎች ፖለቲከኞች ብቻ ሳይሆን በጠቅላይ ሚኒስትርነት ከሾሟቸው ከፕሬዚዳንት የልሲንም በእጅጉ የተለዩና በእጅጉም የተሻሉ የፖለቲካ መሪ መሆናቸውን ለማሳየት የፈጀባቸው ጊዜ በራሽያ የፖለቲካ ታሪክ ረገድ ሲመዘን የብርሃን ፍጥነት ያህል ነበር፡፡  
ከልጅነት ጊዜአቸው ጀምሮ እየተጐነጩት ባደጉት የራሽያ ቮድካ ከፍተኛ ፍቅር እንደወደቁና በራሽያ የመሪዎች ታሪክ በጣጤ (ሠካራም) ፕሬዚዳንትነት ክብረወሰኑን እንደጨበጡ በግልጽም በሹክሹክታም ይታሙ የነበሩት ፕሬዚዳንት የልሲን፤ ይሄው ቮድካ ደፋሪነታቸው በዋናነት ባመጣባቸው ፈርጀ ብዙ የጤና እክል ምክንያት አለምን በሞት ከተሰናበቱበት ጊዜ በኋላ፣ ባለፉት ሁለት አመታት ውስጥ ቭላድሚር ፑቲን ማንም ባላሰበውና ባልገመተው ሁኔታ የፖለቲካ መድረኩን በቀላሉና በፍጥነት ሊሠናበቱ የማይችሉ፣ ይልቁንስ ውስብስቡን የራሽያ የፖለቲካና የስልጣን ሁኔታ በዋናነት የሚመሩና ሂደቱንም በወሳኝ መልኩ የሚወስኑ፣ ንቁ እጅግ ብልጥና በረቀቀ የፖለቲካና የስልጣን ድራማ ጥበብ የተካኑ ጮሌ ፖለቲከኛ ሆነው እንደ አዲስ ብቅ ማለት ቻሉ፡፡
ያረጀና የበሰበሰ ነው እየተባለ በህዝቡ ጣት ከሚቀሰርበት የቦሪስ የልሲን ዘመን፤  የፖለቲካ ፓርቲ አሠራርና የአመራር ዘይቤ ተጽእኖ በመጠኑም ቢሆን ራሳቸውን  ለማላቀቅና አዲስ የፖለቲካ ምስልና ማንነት ለመፍጠር የተባበረው ሩሲያ የተሰኘ አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ በማቋቋም፣ ሁለት ተከታታይ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫዎችን በማሸነፉ፣ የዘመኑ የራሽያ ፖለቲካ አዲሱና ዘመናዊው ዛር መሆናቸውን ለወዳጅም ሆነ ለጠላት ማስረገጥ ቻሉ፡፡ ጥርሳቸውን የነቀሉበት የቀድሞው የሶቪየት ህብረት የደህንነትና የስለላ ድርጅት የምርጦች ምርጥ የስለላ መኮንኔ እያለ ለምን ይጠራቸው እንደነበር፤ በፖለቲካውም መስክ በማያወላውል ቆራጥ አመራራቸው ከከበርቴ ነጋዴ እስከ የፖለቲካ መሪ ድረስ የተቃወሟቸውን ሁሉ አሽመድምዶ ልክ በማስገባትና የእግር መትከያ ቦታ በመንሳት፣ የእሳት ልጅ ረመጥ መሆናቸውን በገሃድ ማሳየት ቻሉ፡፡  
በዚህ ጊዜ ውስጥ የፑቲን ደጋፊዎች ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫቸው የነበረው ሁለተኛ ዙር የስልጣን ዘመናቸው ሲጠናቀቅ ማን ይተካቸው ይሆን የሚለው ሲሆን ተቃዋሚዎቻቸው ደግሞ የራሽያ ህገመንግስት እንደ¸ÃSgDdW\ ፕሬዚዳንት ፑቲን በስልጣን ዘመናቸው ማብቂያ እውን ስልጣናቸውን ያስረክቡ ይሆን በሚል በጥርጣሬ መብሰክሰክና ያችን የመጨረሻ ቀን እንደ እርጉዝ በጭንቀት መቁጠር ነበር፡፡ የፖለቲካ ተንታኞች ግን በራሽያ ዱማ (ፓርላማ) ፓርቲያቸው ያለውን አብላጫ መቀመጫ በመጠቀም ህገመንግስቱን በማሻሻል፣ በስልጣን ላይ ለተጨማሪ አመታት ይቆያሉ እንጂ እንዲህ ያለ የረባ ተቃዋሚ ለአመታት የተዘባነኑበትን ስልጣን በቀላሉ ጥለው ጡረታ ጨርሶ ሊወጡ አይችልም የሚል የተቃዋሚውን ጐራ ጭንቀትና ጥርጣሬ የሚያባብስ ሙያዊ ግምት ነው ያሉትን አቀረቡ፡፡ የሁለተኛው ዙር የስልጣን ዘመናቸው የመጨረሻ ቀን ሲደርስ በተቃዋሚዎችና በፖለቲካ ተንታኞች እንደተገመተው፤ ፕሬዚዳንት ፑቲን ህገመንግስቱን በመደለዝ በስልጣን የሚቆዩበትን ዘዴ ያመቻቻሉ ተብሎ ቢጠበቅም  እሳቸው ግን ተቃራኒውን በማድረግና ስልጣናቸውን በምርጫ ላሸነፉት የፓርቲያቸው አባልና ጠቅላይ ሚኒስትራቸው ለነበሩት ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ በማስረከብ ተቃዋሚዎቻቸውN ተችዎቻቸውን ሁሉ ኩም አደረጓቸው፡፡
ቭላድሚር ፑቲን ይህን ሲያደርጉ ግን ያስረከቡትን የፕሬዚዳንትነት ስልጣን ያለ አንዳች የህገ መንግስት ድለዛና የፖለቲካ አተካሮ፣ የህገ መንግስቱን ክፍተቶችና ትንሽ የፓርቲያቸውን ጨዋታ በመጫወት ብቻ መልሰው የሚቆጣጠሩበትን አዲስ አይነት የምርጫና የስልጣን ሽግግር አብዮት ለመጀመር የሚያስችለውን እቅድ ያለአንዳች ኮሽታ ነድፈው ጨርሰው ነበር፡፡  
የራሺያ ህገ መንግስት፣ አንድ ፕሬዚዳንት በፕሬዚዳንትነት በተከታታይ ከሁለት ዙር በላይ በስልጣን ላይ እንዳይቆይ ይከለክላል፡፡ ከአንድ የፕሬዚዳንት ዙር ቆይታ በኋላ ግን እንደ አዲስ መወዳደርና ለተከታታይ ሁለት ዙሮች በፕሬዚዳንትነት ስልጣን ላይ እንዲቆይ ይፈቅዳል፡፡
ይህን በቀላሉ ለማሳካት ደግሞ ከፕሬዚዳንትነት በቀር ሌላ የመንግስት ስልጣን በመያዝ ስልጣኑ አካባቢ ዞርእያሉና መንገዱን እያስተካከሉና እየደለደሉ መቆየት እጅግ ይጠቅማል፡፡ ለዚህም ነበር የፖለቲካ ስብዕናቸውን በገዛ እጃቸው ጠፍጥፈው ያበጁዋቸውን ዲሚትሪ ሜድቬዴቭን ራሳቸው ለፕሬዚዳንትነት እጩ አድርገው ያቀረቡትና ከምርጫው በሁዋላ የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ቦታ በመያዝ የዳግም የፕሬዚዳንትነት የስልጣን ጉዞውን ቀናና የማይጐረብጥ ያደረጉት፡፡
ብዙውን ጊዜ እንዴት አይነት ሠው እንደሆኑና ምን ለማድረግ እንደሚፈልጉ ከንግግር ይልቅ በድርጊት መግለጽ ይቀናቸዋል የሚባሉት ቭላድሚር ፑቲን፤ ደጋፊዎቻቸው አዲሱ ዛር ወይም ንጉስ እያሉ ለምን አዘውትረው እንደሚጠሯቸውና ከዲሚትሪ ሜድቬዴቭ ጋር ስላቀናበሩት በአብዛኛው ያልተለመደ አይነት የስልጣን ክፍፍል ጉዳይ ግልጽ አቋማቸውን ለመጀመሪያ ጊዜ የተነፈሱት በአብዛኞቹ ዘንድ የፑቲን የግል ዜና መዋዕል ፀሀፊ ተደርጐ ለሚቆጠረው የኮመርሳንት ጋዜጣ ዘጋቢ ለአንድሬ ኮለስኒኮቭ ብቻ ነው፡፡ በተከታታይ የህይወት ታሪካቸውን በመፃፍ ለሚታወቀው ለጋዜጠኛ አንድሬ ኮለስኒኮቭ ፑቲን የነገሩት ..አየህ... የፖለቲካ መሪ ለመሆን ከመወሰንህ በፊት የጠራ ግብና ወደ ግብህ የሚያደርስህ ዝርዝር፣ ነገር ግን ቀላል የሆኑ የድርጊት መርሀ ግብር ሊኖርህ የግድ ነው፡፡ አለበለዚያማ ስራህ ሁሉ የጨለማ ውስጥ ጥቅሺያ ይሆንብሐል፡፡ ይህ ቀለል ባለና በለስላሳ ቋንቋ ሲገለጽ ነው፡፡ እውነቱ ግን ያለ ጥሩ ግብና ግልጽ የድርጊት መርሀ ግብር ወደ ፖለቲካው ባህር ከገባህ፣ የሻርክ ሲሳይ የምትሆነው ገና የአንድ ተጨማሪ ቀን ጀንበር እንኳ ሳታይ ነው፡፡ እኔም እያደረኩት ያለሁት ይህንኑ ነው፡፡ በራሺያ የፖለቲካ መድረክ በተጨማሪ ላሳካው የምፈልገው የጠራ ግብና ወደዚያ ግብ የሚወስደኝ ግልጽና ቀላል የድርጊት መርሀ ግብር አለኝ፡፡ የፕሬዚዳንትነት ስልጣኔ እንዳበቃ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ለማገልገል ስሾም ጨርሶ አላንገራገርኩም፡፡ እውነቱን ለመናገር ያህል ሹመቱን ሳላንገራግር መቀበሌ ወደየት እንደሚወስደኝ በሚገባ አውቅ ስለነበር ነው፡፡ አሁን የተጨማሪው ግቤ አናት ላይ እንደደረስኩ ይሠማኛል፡፡ ይህን ታላቅና ባለታሪክ ሀገር እንደገና በፕሬዚዳንትነት ለማገልገል ፓርቲዬ የሠጠኝን ሀላፊነት ተሸክሜ በመጪው ብሔራዊ ምርጫ ለፕሬዚዳንትነት እወዳደራለሁ፡፡ የድል በለስ ከቀናኝ እሰየው፡፡ ካልሆነም ትግላችንን እንደገና አቀጣጥለን እንገፋለን፡፡ በቃ፡፡ ይሄው ነው፡፡.. ብለው ነው፡፡
የፑቲንን ገለፃ በጥሞና ያዳመጠው ጋዜጠኛ አንድሬ ኮለስኒኮቭ ..ነገሩ ሁሉ እንዲህ ከሆነ የዛሬ አምስት አመት ግድም የጀመሩት ይህ የተለየ የምርጫና የስልጣን ሽግግር አብዮት ግቡን በሚገባ እንደመታ ልንቆጥረው እንችላለን፡፡ ስለዚህ በአለም የመሪዎች ታሪክ በአሁኑ ጊዜ የቀድሞው ፕሬዚዳንትና የወደፊቱ ፕሬዚዳንት ተብለው መጠራት የቻሉ የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት መሆንዎ ነዋ!.. በማለት ለጠየቃቸው ጥያቄ የቭላድሚር ፑቲን መልስ ..አዎ! እንግዲህ እንዳልከው መሆኔ ነው.. የሚል አጭርና ቁጥብ መልስ ነበር፡፡ ይህ ምንም ጥርጥር የሌለው እውነት ነው፡፡ ቭላድሚር ፑቲን አሁን በእርግጥም የቀድሞውና የወደፊቱ የራሺያ ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ ከምርጫው በሁዋላ ደግሞ የቀድሞውና የአሁኑ ፕሬዚዳንት እያልን እንጠራቸዋለን፡፡
የቭላድሚር ፑቲን ወደ ፕሬዚዳንትነት ስልጣን ዳግመኛ የመመለሳቸው ነገር እርግጥ መሆኑ እንደታወቀ ምድረ ራሺያዊ በፌስቡክና በትዊተር እንደየ ፖለቲካዊ ዝንባሌው ስሜቱን ገልል፡፡ የፑቲን ደጋፊዎች በደስታ ሲቦርቁ፣ የድህረ ሶቭየት ህብረት ተስፋቸው የበነነባቸውና የፑቲንን ፓርቲ መቋቋም ያልቻሉ ተዋቃሚዎች ደግሞ በከፍተኛ ተስፋ መቁረጥ ..አምላክ ሩሲያን ለምን እንዲህ ይጠላል.. በማለት ተነጫንጨዋል፡፡ ሌሎች ያደረጉት ደግሞ ፑቲን ለመጨረሻ ጊዜ በ2024 ዓ.ም ስልጣን ሲለቁ የስንት አመት እድሜ ባለፀጋ እንደሚሆኑ ማስላት ነው፡፡ አብዛኞቹ በፑቲን ንቁ የጥበቃ አይኖች ስር እንደሆኑ እንደሚያረጁ ሲገልፁ፤ ጥቂቶቹ ደግሞ በአዲሱ የፑቲን የክፍል ሁለት የስልጣን ዘመን አዲሱን ፑቲንን እንደሚያዩና ያለፉትን ስህተቶች እንደ¥ይደግሟ ቸው ያላቸውን መልካም ተስፋ ገልፀዋል፡፡ በንጭንጩና በተስፋው መሀል ሁሉም ቢወዱትም ቢጠሉትም በአንድ የማይቀር እውነታ ላይ ተስማምተዋል፡፡ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ፑቲን በክፍል ሁለት የስልጣን ዘመናቸው የቀድሞው ፕሬዚዳንት ብቻ ሳይሆን የአሁኑም ፕሬዚዳንት ተብለው በቅርቡ ብቅ ይላሉ፡፡  
በመጨረሻ አንድ ጥያቄ ላንሳ፡፡ በርካታ ሀገራት በተለይ ደግሞ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች ወደ ስልጣን ከመምጣታቸው በፊት አምርረው ሲያወግዙት የነበሩትን ህገመንግስት እየደለዙ በስልጣን ላይ ለረጅም ጊዜ የመቆየት ሙከራ ወደ ስልጣን ከመጡ በሁዋላ ራሳቸው በዚህ ጉዳይ ላይ ተጠምደው ደፋ ቀና ሲሉ ታዝበናል፡፡ መቼም ስልጣንን የሚያጠናክርና የሚያራዝም ነገር ከሆነ ከየትም ቦታ ቢመጣ ለመኮረጅ እንደ አፍሪካ ሀገራት መሪዎች ትጉህና ፈጣን ስለማይገኝ፣ የቭላድሚር ፑቲንን የስልጣንን ህገመንግስት ሳይደልዙ መልሶ የማግኘት ዘዴ የትኛው የአፍሪካ ሀገር ፕሬዚዳንት ቀድሞ በመኮረጅ ለራሱ ይሞክረው ይሆን?

 

Read 3408 times Last modified on Saturday, 08 October 2011 10:32