Saturday, 08 October 2011 09:49

116 የልጆች ጨዋታ በአንድ መጽሐፍ

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(9 votes)

ከወራት በፊት የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በተወያዩበት ወቅት በስብሰባው የተካፈሉ የቻሉ አንድ ደራሲ በአንድ መድረክ ሲናገሩ “በዕለቱ ጥያቄ የመጠየቅ ዕድል ቢሰጠኝ የነገ አገር ተረካቢ በሆኑ ሕፃናትና ወጣቶች አእምሮ ላይ የልማት ሥራ ሳይሰራ የህዳሴውን ግድብ ለማነው የምንገነባው?” እል ነበር በማለት ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሊሰጡ ሞክረዋል፡፡ ለሕፃናትና ወጣቶች ትኩረት አልተሰጠም የሚሉ አስተያየቶች፣ ቁuቶች፣ ጥያቄዎች በተለያየ መድረክና አጋጣሚ በተደጋጋሚ ሲቀርቡ ይሰማል፡፡

በአገራችን በሁሉም ዘርፍ ተያያiነትና ቀጣይነት ያለው ሥራ ስለማይሰራ ነው እንጂ ክፍተትና ጉድለት ያለባቸውን ዘርፎች ለመሙላት የተሞከሩ ነገሮች አይጠፉም፡፡ ዛሬ ለአንባቢያን ላስቃኘው የመረጥኩት መጽሐፍ አንድ ማሳያ ሆኖ ሊቀርብ ይችላል፡፡
የመጀመሪያው ከታተመ ከሁለት ዓመት በኋላ ተሻሽሎ በ1970 ዓ.ም ለሁለተኛ ጊዜ የታተመ መጽሐፍ ነው ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነኝ፡፡ በሥርዓተ ትምህርትና ሱፐር ቪiን መምሪያ የሰውነት ማጐልመሻ ትምህርት ቡድን ተዘጋጅቶ በት.መ.ማ.ማ ድርጅት አሳታሚነት የቀረበ የመምህሩ መምሪያ መጽሐፍ ሲሆን በ221 ገፆች 116 የጨዋታ ዓይነቶችን ይዟል፡፡
በሠዓሊ ኃይሌ ሀብተየስ የተዘጋጁ በርካታ ሥዕሎችን የያዘው መጽሐፍ፤ ከ1ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ላሉ ተማሪዎች በየደረጃቸው እንዲጠቀሙበት የቀረቡት ጨዋታዎች የሜዳ፣ የክፍል ውስጥ፣ በግልና በጋራ ተግባራዊ የሚሆኑ ናቸው፡፡ ጨዋታዎቹን አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ፣ የክፍል ደረጃን፣ ዕድሜን፣ ፆታን፣ የአካልና የአእምሮ መዳበርን በማመዛዘን ልጆቹ እንዲጠቀሙባቸው መጽሐፉ ያሳስባል፡፡
በአንድ ጥራዝ የተሰባሰቡት ጨዋታዎች፣  ከትውልድ ትውልድ ተላልፈው እንደመጡና  ቁም ነገርን በቀላል ዘዴ ለልጆች ለማስተላለፍ ተመራጭ እንደሆኑ የሚጠቁመው መጽሐፍ፤ ጨዋታዎቹ ሕጋቸው ቀላል፣ ውድ የሆኑ ቁሳቁስ የማያስፈልጋቸው መሆኑንም ይጠቁማል፡፡
በመምህራን በመጽሐፍ የቀረቡትን ጨዋታዎች፤ ተማሪዎቻቸው ተግባራዊ እንዲያደርጉት ከማዘዛቸው በፊት ልጆቹ ከጨዋታዎቹ ምን ጥቅም ሊያገኙ እንደሚችሉ፤ ሁሉም ተማሪዎች በግልና በጋራ የሚሳተፉበት መሆኑን፣ ጨዋታውን በተመለከተ መምህሩ ለተማሪዎቹ በቂ መመሪያና ድጋፍ ማቅረብ መቻል አለመቻሉን ማረጋገጥና፤ የተመረጠው ጨዋታ ልጆቹን የሚመጥን መሆኑን እርግጠኛ እንዲሆኑም ይመክራል፡፡
በመጽሐፉ የቀረቡት 116 ጨዋታዎች ለልጆች ምን ጥቅም ሊያስገኙ እንደሚችሉም ማብራሪያ ቀርቧል፡፡ ቀዳሚው የማህበራዊ ኑሮን ልምድ ለመገንባት ሲሆን፤ በዚህ ውስጥ የመንፈስ ጭንቀትን ለማስወገድ፣ የውድድር ስሜትን ለማዳበር፣ ሥነ ሥርዓትን ለመለማመድ፣ የኃላፊነት ስሜትን ለማዳበርና የግል ችሎታንም ለማወቅ ይጠቅማል፡፡
ቀጣዩ ጠቀሜታ የአካል ብቃትን ለመገንባት ሲሆን፤ ፍጥነት፣ ቅልጥፍና፣ ጥንካሬ የመሳሰሉትን ጠቀሜታዎች ሲያስገኙ፤ ሦስተኛው አእምሮን በዕውቀት ለማዳበር ያግዛል፡፡ በስፖርታዊ እንቅስቃሴ የዳበረ አእምሮ ያላቸው ልጆች የተማሩትን ትምህርት ለመረዳትና በተግባርም ለመግለጽ ፈጣን ይሆናሉ - ይላል መጽሐፉ፡፡
ጨዋታዎቹ በክፍል ውስጥም ይሁን በሜዳ ላይ ተግባራዊ ከመሆናቸው በፊት መደረግ ስላለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች ጥቆማ የሚሰጠው መጽሐፍ፤ የጨዋታ ሕጐችን ከቀላል ወደ ከባድ ማሳደግ፤ ተጫዋቾቹ የተለያዩ ቡድን ከሆኑ አንዱን ከሌላኛው መለያ አርማ (አልባሳት) ማዘጋጀት፤ የመጀመሪያውን ጨዋታ ንቁ የሆኑ ልጆችን መርጦ ማሳተፍ ሌሎችን ለማነሳሳት እንደሚያግዝ፤ ልጆቹ እንዲጫወቱት ለተመረጠላቸው ጨዋታ ያላቸው ስሜት ቀዝቃዛ ከሆነ ሌላ ጨዋታ መቀየር አስፈላጊ መሆኑንም ይገልፃል፡፡
ልጆች እንዲጫወቱ በሚደረግበት ወቅት አደጋ በሚያደርስባቸው ነገሮች እንዳይጎዱ ጥንቃቄ ሊደረግላቸው ይገባል የሚለው መጽሐፍ፤ ግምገማና ምዘና እንዴት መከናወን እንዳለበት ሲገልጽ “ጨዋታው ትምህርታዊ ውጤት ባለው ውይይትና ዕቅድ እንዲቀጥል ይገባል፡፡ ጨዋታው የሚሻሻልበትን መንገድ ልጆቹ ሐሳብ እንዲሰጡ ማበረታታት ያስፈልጋል፡፡ ግምገማ በጨዋታው መጨረሻ ሳይሆን በዕረፍት ጊዜ ወይም ቦታ በሚለዋወጡበት ወቅት መሆን አለበት፡፡ ጥሩ የመጫወት ችሎታ ያሳዩትንና በሥነ ሥርዓት የተጫወቱትን በማመስገን ማበረታታት ይገባል፡፡ …ልጆቹ የጨዋታውን ሥም ማወቃቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡”የመጽሐፉ አዘጋጆች የሰበሰቡትን ጨምሮ ከሰባት የተለያዩ ምንጮች የተገኙት 116 ጨዋታዎችን በአንድ ጥራዝ ያቀረበው መጽሐፍ፤ በምንጭነት ከጠቀሳቸው መሐል “የጨዋታዎች መምሪያ” በሚስተር ዲ ሰሪል ጆይንሰን ኬይ፤ የ1965 ዓ.ም የደብረ ዘይት የሰውነት ማጐልማሻ ትምህርት ኮርስ ተካፋዮች ያበረከቱት፤ “ጨዋታዎችና ውዝዋዜዎች ለአንደኛ ደረጃ” በሚስተር ማሪጀሪ ላቻው ከተዘጋጀው መጽሐፍ የትምህርት ሚኒስቴር የሰውነት ማጐልመሻ ክፍል በ1962 ዓ.ም ያዘጋጀው መጽሔት፤ “ጨዋታዎች ለመለስተኛና ለከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች” በሚስተር ሀዘል ኤ ሪቻርድስ፤ በ1966 ዓ.ም የጅጅጋ አውራጃ ትምህርት ቤቶች ያዘጋጁት መጽሔት ይገኙበታል፡፡ የጨዋታው ሥም፣ የተጫዋቾች ብዛት፣ ለጨዋታው የሚያስፈልጉት መሣሪያዎች፣ የጨዋታው ሕግ፣ የጨዋታው አተገባበር፣ ውጤቱ፣ ዓላማና ጥቅሙ ምን እንደሆነ ለእያንዳንዱ ጨዋታ የጽሑፍ መግለጫ የሚያቀርበው መጽሐፉ፤ ከ1ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ላሉ ልጆች ከቀረበው 117 ጨዋታዎች መሐል፤ እንስሳትን በድምጽ ማስመሰል፣ ኩኩሉ አልነጋም፣ ሰኞ ማክሰኞ፣ ኳስ ወደ ኋላ መወርወር፣ መሀረብ ድበቃ፣ ዛፍ ያጣ ጉሬዛ፣ ቀበሮና ፍየል፣ ዲሞ፣ ወጣ ገባ ሩጫ፣ ወንበዴን መማረክ፣ የአንድ እግር ሩጫ፣ ሾላ እርግፍ እርግፍ፣ ሰሎሜ ሰሎሜ፣ ከወጥመድ ማምለጥ፣ እንኮኮ፣ ተሸክሞ እሽቅድምድም፣ ምርኮኛን መጠበቅ፣ በእጅና በእግር መሄድ... ከፊሎቹ ናቸው፡፡ በመጽሐፉ ከተሰባሰቡት 116 ጨዋታዎች መሐል “ሚዳቋን መክበብ” በሚል ርዕስ የቀረበው ጨዋታ ያለ ምንም መሣሪያ ወይም ቁሳቁስ ተግባራዊ የሚሆን ነው፡፡ የጨዋታው አጀማመርና አፈፃፀም ምን እንደሚመስል በመጽሐፉ በገጽ 68 በዚህ መልኩ ቀርቧል፡፡ ሌሎችም ጨዋታዎች በተመሳሳይ መንገድ ነው በመጽሐፉ ውስጥ የሰፈሩት፡፡
ሚዳቋን መክበብ
የተጨዋቾች ብዛት - በቡድን 15-20
መሣሪያ -  ................
የጨዋታው አጀማመር - የክፍሉ ልጆች ክብ በመሥራት እጅ ለእጅ እንደተያያዙ አንድ ልጅ “ሚዳቋ” በመሆን በክቡ መሀከል እንዲቆም ማድረግ፡፡
ጨዋታው - “ሚዳቋው” በልጆቹ እጅ ላይ በመዝለል፣ በእጃቸው ሥር በመሹለክ ወይም እጆቻቸውን በመፈልቀቅ ለማምለጥ ይሞክራል፡፡ ሚዳቋው ካመለጠ ሁሉም ልጆች ያባርሩታል፡፡ በመጀመሪያ የነካው ልጅም ሚዳቋ ሆኖ ጨዋታውን እንደገና ይጀምራል፡፡
ውጤቱ - ሁሉም ልጆቹ “ሚዳቋ” በመሆን ጨዋታውን ለመጀመር በሚያደርጉት ፍላጐት በጨዋታው ተካፋይ ይሆናሉ፡፡
ዓላማውና ጥቅሙ - ሰውነትን እንደልብ ለማዘዝና የእጅ ጡንቻዎችን ለማጠንከር ይረዳል፡፡
ማሳሰቢያ፣ ተራ የደረሰው ልጅ ቢነካ ተራ ያልደረሰውን መርጦ ጨዋታውን ማስጀመር ነው፡፡
አንድ ልጅ ለብዙ ጊዜ “ሚዳቋ” ሆኖ ለማምለጥ ካልቻለ ጨዋታው አሰልች እንዳይሆን ተረኛ ልጅ መተካት ነው፡፡

 

Read 7853 times Last modified on Saturday, 08 October 2011 09:52

Follow us on twitter

Due to an error, potentially a timed-out connection to Twitter, this user's tweets are unable to be displayed.