Saturday, 08 October 2011 09:40

ታሪክንየማዛባትና ታላላቆችን የማዋረድ አባዜ

Written by  ከበረ
Rate this item
(0 votes)

አቶ አለማየሁ ገላጋይ የተባሉ ፀሐፊ በተለያዩ ጊዜያት በአዲስ አድማስ ጋዜጣ የፃፏቸውን ፅሁፎች አንብቤያቸዋለሁ፡፡ ቀደም ባሉት ጊዜያት የፃፏቸው ከስነ ፅሁፍ ጋር የተያያዙ ነበሩ፡፡ አሁን ደግሞ ወደ ታሪክ የተሸጋገሩ ይመስላል፡፡ ከስነ ፅሁፍ ጋር በተያያዘ ከፃፏቸው ፅሁፎች እንደታዘብኩት እሳቸው የሚያደንቁት አንድ ደራሲ ስራው በሚገባ አልታወቀም፣ በቂ አድናቆትም ሆነ ክብር አላገኘም፣ በሚል እንደ ቀሽም የእግር ኳስ ደጋፊ የሚወዱትን ደራሲ ለማወደስ ሌሎች ታላላቅ ደራሲዎችን መሳደብ፣ የሌላቸውን ስምና ስብዕና መስጠት ምናልባትም አድናቂዎቻቸውን ማብሸቅ ላይ ነበር ያተኮሩት፡፡

እነዚህ ፅሁፎች ከወጡ በኋላ ከአንድም ሁለቴ አስተያየት ለመፃፍ ካሰብኩ በኋላ በጥናትና ምርምር ያልተደገፈና በይዘት ላይ ሳይሆን ከግል ጥላቻ በመነጨና በግልብ ንባብ የግለሰቦችን ስብዕና ለማጉደፍ ለተፃፈ ፅሁፍ አስተያየት መፃፍ አግባብ አይደለም በሚል ትቼዋለሁ፡፡ ዝምታው ግን አቶ አለማየሁን የልብ ልብ የሰጣቸውና ልክ ነኝ ብለው እንዲያስቡ ያደረጋቸው ይመስለኛል፡፡ አቶ አለማየሁ በዝምታው ተደፋፍረው ያላዋቂ ስህተት እየፈፀሙ ይገኛሉ፡፡ ያላዋቂ ሳሚ እንዲሉ፡፡
ነሐሴ 28 ቀን 2003 ዓ.ም በወጣው ፅሁፋቸው፤ እኛ ኢትዮጵያውያን ከታሪካችን ደግ ደጉን ብቻ ነው የምናወራው፤ እኛ እንደምናስበው ሳይሆን እንደ ህዝብ ውሸታሞች አጭበርባሪዎች ነን ይህንንም መቀበል አለብን ብለዋል፡፡ ይህ እሳቸው እንደሚሉት ታሪክና ራስን የመውቀስ ጥበብ ሳይሆን ታሪክን የማዛባትና ታላላቆችን የማዋረድ አባዜ ነው፡፡ “እንግዳ ተቀባይ፣ ኩሩ፣ አክባሪ” በሚሉና በሌሎች ማጠቃለያዎች ራሳችንን ደብቀን ነው ያለነው፤ እውነታው ግን ይሄ ሳይሆን ሌሎች ለኛ የሰጡን መጥፎ መጥፎ ምስሎችና ገፅታዎች ናቸው፤ ይህንንም መቀበል አለብን እያሉ በመሞገት ላይ ናቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ የሚያቀርቡት መከራከሪያ በጥናትና ምርምር የተደገፈ መረጃ ሳይሆን ሃሳቤን ይደግፉልኛል ያሏቸው የፈረንጅ ተጓዦች ጭፍን ማጠቃለያዎች ናቸው፡፡ የእኛ ማጠቃለያዎች ውሸት፤ የፈረንጅ ተጓዦች ማጠቃለያዎች ግን እውነት የሆኑት በማንና በምን መስፈርት እንደሆነ ግራ ያጋባል፡፡ ፀሐፊው ምን ዓይነት የበታችነት ስሜት የተጠናወታቸው ቢሆኑ ነው ከማለት ሌላ ምን ይባላል፡፡ በመሰረቱ እንኳን የአንድን አገር ህዝብ ይቅርና አንድን ግለሰብ እንዲህ ብሎ ማጠቃለል አይቻልም፤ ምክንያቱም የሰው ልጅ ውስብስብ እና በቀላሉ ለመረዳት አስቸጋሪ ስለሆነ ነው፡፡ የማህበረሰብ አጥኚዎች “Do not take the face value” (ከፊት ለፊት የሚታየውን ብቻ አትመን) ይላሉ) በችኮላ ከተሳሳተ መደምደሚያ እንዳይዳረስ ለማስገንዘብ ሲሉ፡፡ እንደውም በማህበረሰብ ጥናት የሚመከረው በሚጠናው ማህበረሰብ ውስጥ እየኖሩ የማህበረሰቡን አመኔታ ካገኙ በኋላ የሚካሄድ ጥናት ነው፡፡ በዚህም በተለምዶ በሚጠኑ ጥናቶች ከሚገኙ ውጤቶች የላቁና አስደናቂ ውጤቶች ተገኝተዋል፡፡ የማህበረሰብ ጥናት ለሌሎች ሙያዎችም ግብዓት ሆኖ እየገለገለ ይገኛል፡፡ በተለይ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በሚተገብሯቸው ፕሮጀክቶች በጣም ወሳኝ ግልጋሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ በቀደሙት ዓመታት ፊት ለፊት የሚታዩ ችግሮችን መሰረት በማድረግ በአቅርቦት የሚመሩ (Supply driven) ፕሮጀክት ይተገበሩ ነበር፡፡ ሆኖም ተፈላጊውን ውጤት ሊያመጡ አልቻሉም፤ ምክንያቱም የማህበረሰቡን ፍላጎት ያላገናዘቡ በመሆናቸው ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በአሁኑ ጊዜ የማህበራዊ ጥናት ባለሙያዎች በተለያዩ መንገዶች ከህብረተሰቡ ጋር ጥልቅ ውይይቶችና ቃለ መጠይቆች በማድረግ የህብረተሰቡን ፍላጎት ለማወቅ ጥረት ያደርጋሉ፡፡
ጥናቶቹንም መሰረት በማድረግም ህብረተሰቡ ከእቅድ እስከ ትግበራ እንዲሁም ክትትልና ግምገማ ንቁ ተሳትፎ የሚያደርግባቸው በፍላጎት የሚመሩ (Demand driven) ፕሮጀክቶች እየተተገበሩ በተሻለም ውጤታማ እየሆኑ ይገኛሉ፡፡ የህብረተሰቡን ፍላጎት መሰረት ያላደረገና በጥናት ላይ ያልተመሰረተ፣ ፊት ለፊት የሚታየውን ችግር ለመፍታት የሚደረግ ጥረት ችግር እንዳለው ከዚህ በታች የቀረበው ጥሩ ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡ አንድ በጎ አድራጊ ድርጅት፤ መሬት ላይ እየተንፏቀቁ የሚለምኑ አካል ጉዳተኞች ለመርዳት ይወስንና ዊልቼር (Wheel chair) ገዝቶ ያድላል፡፡ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ በተደረገ ክትትል አብዛኞቹ አካል ጉዳተኞች ዊልቼሩን ትተው እንደቀድሞው በልመና ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡ ለአካል ጉዳተኞቹ ጋር በተደረገው ውይይት፤ ሰው አዘኔታ ተሰምቶት ገንዘብ የሚሰጣቸው መሬት እየተንፏቀቁ በሚለምኑበት ጊዜ እንደነበረና ዊልቼሩ ገቢያቸውን እንዳሳጣቸው ለመረዳት ተችሏል፡፡ በመጨረሻም በተደረገው ግምገማ ለአካል ጉዳተኞቹ ዊልቼሩን መስጠቱ ብቻ በቂ እንዳልነበረና የገቢ ማግኛ መንገድም አብሮ መፈለግ እንደነበረበት ለዚህም በቂ ጥናት ማድረግ ያስፈልግ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡
ከዚህ በላይ ስለማህበረሰብ ጥናት ለመግለፅ የሞከርኩት ያለጥናት ፊት ለፊት በሚታዩ ሁኔታዎች ብቻ የምንወስደው ግንዛቤ የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ ሊያደርሰን እንደሚችል፤ አንድን ማህበረሰብ ለመረዳትና እንዲህ አይነት ማህበረሰብ ነው ለማለት በቂ ጥናት እንደሚያስፈልግና አቶ አለማየሁ ስለ ኢትዮጵያዊያን ባህሪ ያስረዱልኛል ያሏቸው ተጓዦች ይህንን እንደማያሟሉ ለማሳየት ነው፡፡ አብዛኞቹ ተጓዦች መጀመሪያውንም የተሳሳተና በዘረኝነት ላይ የተመሰረተ ግንዛቤ ይዘው ነው የሚመጡት፤ ስለዚህም የሚያዩትን ነገር በገለልተኛነትና ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ለመፃፍ አይችሉም፡፡ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት በቅርቡ በካፒታል እንግሊዝኛ ጋዜጣ ላይ በተከታታይ ባወጡት ፅሁፍ በአውሮፓ የተማሩ ቀደምት ወጣት ኢትዮጵያዊያንን አስመልክቶ የፃፉ አንዳንድ የአውሮፓ ፀሐፊዎች ዕይታቸው በዘረኝነት ላይ የተመሰረተ እንደነበር፣ አንዳንዶቹም በዘረኝነታቸው የታወቁ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡ ከነዚህም መካከል በአቶ አለማየሁ ፅሁፍ፤ ውስጥ የተጠቀሰው ባሮን ሮማን ፕሮቼዝካ ይገኝበታል፡፡ June 5,2011 በካፒታል እንግሊዝኛ ጋዜጣ ላይ ሪቻርድ ፓንክረስት እንደፃፉት፣ ወጣት ኢትዮጵያውያኑ እ.ኤ.አ በ1920ዎቹ መጨረሻና 1930ዎቹ መጀመሪያ በአዲስ አበባ በጥብቅና ሙያ ተሰማርቶ በነበረውና በዘረኛነቱ በሚታወቀው፣ በዚሁም አደገኛ አስተሳሰቡ ምክንያት በ1934 ከአገር እንዲባረር ከተደረገው ቼካዊው ባሮን ሮማን ፕሮቼዘካ ክፉ እይታ ውስጥ ወድቀው ነበር፡፡ ፕሮቼዝካ ከአገር በተባረረ በቀጣዩ ዓመት ለፋሺስት ኢጣልያ ግልፅ ድጋፉን በመስጠት “ወጣት አቢሲኒያውያን” ብሎ በሚጠራቸው ኢትዮጵያውያን ላይ በጥላቻ የተመሰረተ ፅሁፍ በጀርመንኛ በመፅሃፍ መልክ አሳተመ፡፡ ፅሁፉ በጣልያንኛ እንዲሁም በእንግሊዝኛ “Abyssinia: The Powder Barrel” በሚል ርዕስ የተተረጎመ ሲሆን በሶስቱም ቋንቋዎች የተፃፉት ፅሁፎች በተደጋጋሚ ታትመው በስፋት ተሰራጭተዋል (አቶ አለማየሁ ይህንን መፅሃፍ እንደ ዋቢ መጥቀሳቸውን ልብ ይሏል) ፓንክረስት ፅሁፋቸውን በመቀጠል ራሱን “የጥቁር ዘር ነፃነትን” ከሚቃወም ወገን አድርጎ የሚገልፀወ ፕሮቼዝካ፤ ወጣት ኢትዮጵያውያኑን የመንግስት መሳሪያ አድርጎ የመመልከት ሁኔታ ይታይበት እንደነበር ገልፀዋል፡፡ በሌሎች ፀሃፊዎች ዘንድ ከዚህ በተለየ ወጣት ኢትዮጵያዊያኑን ከነበረው መንግስት ለይቶ የማየት እንደውም መንግስትን የሚተቹና በመንግስት ላይ የሚያሴሩ አድርጎ የመመልከት ሁኔታ ነበር፡፡ ፕሮቼዝካ ይህንኑ አስተሳሰቡን በማብራራት በመንግስት የሚደገፈው “ፀረ-ነጭ” የወጣት አቢሲኒያውያን እንቅስቃሴ ስልታዊ በሆነ መንገድ የነጭ ጥላቻ በመላው ህዝብ እንዲስፋፋ ያደርጋል ብሎ ፅፏል፡፡ በመቀጠልም ጥቁሮችን በተለይም በነጭ ቁጥጥር ስር ያልዋሉትንና የራሳቸውን ዕድል መወሰን የሚችሉትን በአውሮፓ የትምህርት አሰጣጥ ዘይቤ ማስተማሩ በውጤት አደገኛ እየሆነ መምጣቱን ፅፏል፡፡  ይህንንም አስተሳሰቡን በማጠናከር በአቢሲኒያ ይኖሩ የነበሩ ነጮች ለዓመታት የአገሬው ህዝብ ያደርስባቸው የነበረውን አረመኔያዊ ድርጊት ተቋቁመው መኖር ነበረባቸው በማለት ይከሳል፤ ለዚህም እንደማስረጃ “የአውሮፓ ልብስ የሚለብሱ ወጣት አቢሲኒያውያን ሁሌም አብረዋቸው ከማይጠፉት የአገሬው ተከታዮቻቸው” ጋር በመሆን በአውሮፓውያን ላይ ጥቃት ያድርሱ ነበር ማለቱን ፓንክረስት በፅሁፋቸው ገልፀዋል፡፡ ፕሮቼዝካ ብዙም ሳይቆይ ትኩረቱን በጀርመን ቁጥጥር ስር ወደነበረችው የትውልድ አገሩ ቼኮዝሎቫኪያ በማድረግ ለናዚ ጀርመን በባንዳነት አድሮ ሲያገለግል ቆየ፡፡ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያም ለዚሁ ድርጊቱ የሰባት ዓመታት እስራት ከከባድ የጉልበት ስራ ጋር ተፈርዶበት ይህንኑ መፈፀሙን ፓንክረስት ፅፈዋል፡፡ እንዲህ የለየለትን ለአገሩም የማይመለሰውን ዘረኛ ነው፣ አቶ አለማየሁ የኢትዮጵያዊያንን ባህሪ ያስረዳልኛል ብለው እንደ ዋቢ የሚያቀርቡት፡፡ ስለአንድ ህዝብ እንዲህ ነው ብሎ ለመናገር ለረጅም ጊዜ አብሮ መኖርን፣ ማህበረሰቡ የሚያደርጋቸውን ነገሮች ለምን እንደሚያደርግ ማየት፣ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነው በዚሁ በነሐሴ 28 ቀን 2003 ዓ.ም በወጣው አዲስ አድማስ ጋዜጣ፣ አንድ ጃፓናዊ ያቀረቡት ፅሁፍ ነው፡፡ ጃፓናዊው ካገራቸው እንደመጡ አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ውሾች ላይ ድንጋይ ሲወረውሩባቸው ሲመለከቱ ይደነግጡ እንደነበርና ምን አይነት ጨካኞች ቢሆኑ ነው ይሉ እንደነበር ጠቅሰው፤ አሁን ግን ምክንያቱ እንደገባቸው፣ ከራሳቸው ልምድ በመነሳት ገልፀዋል፡፡ እንግዲህ እኚህ ጃፓናዊ የአጭር ጊዜ ተጓዥ ቢሆኑና ኢትዮጵያ ያዩትን በጉዞ ማስታወሻ ቢፅፉት ምን አይነት መልክ ሊኖረው እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡ በአብዛኞቹ አውሮፓዊያንና አሜሪካዊያን፣  አፍሪካ ባጠቃላይ የጨካኞችና አረመኔዎች አህጉር ተደርጋ አሁን ድረስ እንድትታይ ያደረጉት በተለይ በቅኝ ግዛት ዘመን ወደ አፍሪካ ይመጡ በነበሩና በዘረኝነት በተለከፉ ተጓዦች በችኮላ የተፃፉ የጉዞ ማስታወሻዎች ናቸው፡፡ የአቶ አለማየሁ ጽሑፍ የተዛባ የሚሆነውም መረጃቸው እንዲህ የተዛቡ በመሆናቸው ይመስለኛል፡፡

Read 3766 times