Saturday, 08 October 2011 09:26

ህይወታችን በተአምራት ዓለም ‹‹መዝናናት፣ መዝናናት፣ አሁንም መዝናናት!›› ጓድ ሌኒን

Written by  ስብሃት ገ/ እግዚያብሔር.
Rate this item
(0 votes)

“To see the Universe in a grain of sand;
To live Eternity in the Here and Now”
Kung Fu Tze
አሀዱ
የተከበራችሁ አንባብያን፣
ይህን ጽሁፍ እንዳቀርብላችሁ ያነሳሳኝ የተፈጥሮና የአስተዳደግ ቅንጅት ይመስለኛል፡፡ ተፈጥሮን ለፈጣሪ እንተውለትና አስር አመት ሞልቶኝ ወደ አዲስ አበባ እስከመረሽኩበት ቀን ያደግኩት እልም ያለ ገጠር ውስጥ አንድ ሰላሳ የሚሆኑ ቤቶች የተሰሩባት መንደር ውስጥ ነው፡፡ ታቦታችን ሰማዕቱ ጊዮርጊስ፣ አባቴ የጆርጊስ ቀሲስ፡፡

ከዘመናዊው ስልጣኔ ትሩፋት የደረሱን መርፌ /ክሩ የራሳችን/ እና ጨርቅ /ጥጥ ያልሆነ/ እነዚህ ሶስቱ ብቻ ነበሩ፡፡ እና ምናልባት በየሁለት ሶስት ሳምንቱ ከሩቅ መኪና /የጭነት/ ሲያጓራ ወይም ሲያገሳ የሚመስል ድምጽ እንሰማለን፡፡ ከየት ወዴት እየተጓዘ ይሆን… አባቴ ብዙ ጊዜ ለራሳቸው ይቀድሳሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ብልጭ ሲልባቸው የግዜር የአምራት በተራ ነገሮች ውስጥ ተሸሽጎ ያሳዩኛል፡፡
እያት እቺን ሸረሪት፡፡ ለምግብ መሯሯጥ የለባትም፡፡ ሀር የመሸመን ጥበብ ሰጥቷታል፡፡ ዝምብ፣ ትንኝ ምናምን ሲንቀለቀል ድር ላይ ያርፋል ይጣበቃል፡፡ ስንቅ አልተላከላትም አገር ቤት መስከረም ሲጠባ፣ መሬት አደይ አበባ ስትለብስ፣ የበቆሎ እሸት ጥብስ ሲጣፍጥ!
አንድ ቀን ሁለታችን በቆሎ እሸት እየገነጠልን ስንሰበስብ አየኸው በቆሎን እንዴት እንደሚወዳት ማንም ማሽላ ጫፍ ላይ መለቃቀም የለመደች ወፍ እንዳትደርስበት ግንዱ ወገብ ላይ ተደብቋል፡፡ ደግሞስ በስንትና ስንት አረንጓዴ ቀሚስ እንደተጆበነ አይተሀል ምን ሊፈይድለት ይሆን እሳቸው እዝጌር የሚታያቸው የፈጠረውን ሁሉ እንደየአስፈላጊነቱ ሲጠብቀው፣ ሲያስውበው፣ ሌላ ዓይነት ፀጋ ሲያድለው ነው፡፡
ዝምብን እያት፡፡ እግዜር ንብን ሲፈጥር ሰይጣን ተደብቆ አይቶት ኖሮ፣ እኔም ንብ እሰራለሁ ብሎ ሲሞክር፣ ድግምቱ ከሸፈና ዝምብ ተፈጠረ ሲሉ ትሰማለህ፡፡ እሱ እሱ በማህሌተ ገምቦ የሰከረ ደብተራ ምናብ የሸመነው ውሸት ነው፡፡ ሰይጣን የመፍጠር ስልጣን የለውም፡፡ ዝምብን የፈጠረው እዝጌር ግን ምንኛ እንደሚወደውና እንደሚጠብቀው አስተውል፡፡ እስቲ አንዲት ዝምብ ለመያዝ ወይም ለመግደል ሞክር፡፡ አትችልም፡፡ ጠባቂ አለዋ
. የፈጣሪ ተአምራት እንደከበበን እንኖራለን፡፡ ግን በልጅነት አይናችንን ስንከፍት ጀምሮ በመሀሉ ስላደግን፣ ተአምርነቱ በልማድ አቧራ ይሸፈንብናል፡፡
የእግዚአብሔር ጥበብ ሲገለጥ እየው፡፡ ሰማይን ያለ ባላ የዘረጋ፣ ምድርን ያለ ካስማ የተከለ የሚለውን እያሰብክ፡፡ ከዚህ ከሰማያችን በላይ ያው ስድስቱ ሰማይምኮ ባላ የለውም፡፡ እንግዲህ እያንዳንዱ ሰማይ ከሌላው በታች ተንጠልጥሏል ያለ አንዳች ማንጠልጠያ ገመድ ወይ ክር፡፡ አንተ ልትደርስበት የምትችል አይደለም ምስጢር እምአልቦ /ካለመኖር ወደ መኖር/ ያሻገረውን ፈጣሪ ደግሞ ዳዊት ምን ይለዋል
ሰማይ መኖርያው፣ ምድር የመጫሚያው መረገጫ…
…እዚያ አገር ቤት ስናድግ በአራት አምስት አመታችን ጥጃ እንጠብቃለን፡፡ ሰባት ስምንት ዓመት ሲሆነን ከብት እናግዳለን፡፡ ማለት እኔ አንድ ትንሽ ፍጡር ይህን በአድማስ የተከበበውን አለም እያየሁ፣ ከአድማስ ባሻገር ስለሚገኘው እና ስፍር ቁጥር ማለቅያ ስለሌለው አለም እየሰማሁ፣ ተአምራቱ ባጋጣሚ ተራ በተራ ይታዩኛል፡፡ . የሾላና የጤፍ ቁመት ሰማይና ምድር ነው፡፡ ሾላውን በልተን ስጋውን ውጠን ፍሬዎቹን ስንተፋቸው ከጤፍ ፍሬ ዘር ምንም ያህል አይበላለጡም፡፡ አድገው ፍሬ ለመስጠት በሚበቁበት ወቅት ግን በግዝፈት መስፈርት ብናስተውላቸው፣ ጤፍ ከሳር የምትመደብ ትንሽ ፍጡር ናት፣ ሾላው ግን ከነዋርካ ጋር በንፋስ ሲወዛወዝ ሰማዩን ለመጥረግ እየተንጠራራ ይመስላል
. ሾላውን ስናረግፍ እዚያ ወድያ ለግጦሽ ያሰማራናቸውን ከብቶች በአየን እየቃኘን ነው፡፡ እዚያ ደግሞ የሚተወነው ድራማ /በእግዜሩ መድረክ ላይ/ ተአምራቱን ያስረሳናል፡፡
በሬዎቹ ገና የጥጃነቱን ዕድሜ እንዳለፉ፣ ሁሉም እንዳጋጣሚው አንድ ለአንድ ተዋግተው፣ ማን ማንን እንደሚያሸንፍ ይተዋወቃሉ፡፡ የስሪያ ሰዓት ሲደርስ፣ ላሚቱን የሚቀድስላቸው ያ የውጊያ ሻምፕዮን ነው፡፡
. ያ ሳር የሚያክለው ጤፍ ተዘርቶ፣ ማሳው ላይ ታርሞ /አረሙን እየነቀሉ ጥለውት/ ታጭዶ፣ ተከምሮ፣ በአውድማ ላይ ፈራርሶ በበሬዎች ተሂዶ፣ በንፋስ ተጣርቶ ተቀምጦ፣ ተፈጭቶ፣ ተቦክቶ አብሲት ተጥሎ፣ ተጋግሮ፣ ባለ መቶ አይን እንጀራ ላይ ፈሰስ ተደርጎ ይህን ሁሉ የጤፍ ገድል ከሜዳ እስከ ጓዳ ስንከታተል፣ ከምድሪቱ ተአምራት አንዱን እየተቋደስነው እንኖረዋለን…
ክልኤቱ
ይሄ የምድሪቱን በረከት የመቋደስ ጉዳይ፣ እውስጣችን በየእለቱ የሚካሄደውን፣ እኛ ግን የማናስተውለውን ተአምራት ሰውሮብን የሚኖር ምስጢር ነው፡፡ ይኸውና፣ የምንበላው ማናቸውም ምግብ /ክትፎን ጨምሮ/ የሞተ ነው፡፡ ህይወት ነበረው እንጂ ስንጎርሰው ህይወት የለውም፡፡ እኛ ታዲያ ስንትና ስንቱን ዓይነት ሙት እየበላን /ከቆሎ ኑፍሮ እስከ ጭቅና ዶሮ ወጥ እያግበሰበስን/ እንውጠዋለን፡፡ እውስጣችን የሚኖር መለስተኛ የመፍጠር ስልጣን ያለው ደመ-ነፍስ ያን ሁሉ እህል እየተቀበለ ወደ ፀጉራችን ወደ አይናችን ወደ ጥፍራችን ወደ ሁለመናችን ለውጦ ያከፋፍለዋል - አንዲት ነገር ሳትዛነፍ ተአምራቱ በጥልቀት ላይ ጥልቀትና ረቂቅነት ሲጨምር ያ ያግበሰበስነው ሙት ምግብ በቀን ወደ ሀሳብ ወደ ምናብ ይለውጣል፡፡ በሌሊት ወደ ህልምና ቅዠት፡፡ ውስጣችን ስጋ ቢሆንም ያን ያህል ረቂቅ ነው
ይሄ ወዴት ይወስደናል እንቅልፉን ወደሚተኛው ወደ ግዙፉ ረቂቅ ሰውዬ /ሴትዮ/…
…በረከቶችህን /ሽን/ አንድ በአንድ ቁጠር
ጧት ስትነቃ ጤናህን ደህና ነህ፡፡ በረከት አንድ በል /ሞተህ ልታድር ትችል ነበራ ወይም አንዱ በሽታ ቤትህ ገብቶ የአልጋ ቁራኛ አድርጎህ ሊያድር ይችል አልነበረም ከመኝታህ ተነስተህ ትንጠራራለህ፡፡ ተኝቶ ላደረ ገላ ያቺ መንጠራረት ውስጥ ያለው እፎይታ ደስታ እርካታ ስትተጣጠብ ስትፀዳዳ ውሀን የፈጠረ ይመስገን አትልም ሽንትህን ስትሸናም በረከት መሆኑን አትርሳ፡፡ ፊኛህን ታመህ አድረህ ቢሆንስ ኖሮ
ቀኑ የሚየመጣውን ለመጋተር ጉልበት ይሆንህ ዘንድ ደህና ቁርስ ትበላለህ፡፡ ሼክስፒር እንዳለው ወይ ምርጥ እህልና ስጋ ይሰጥህና ሆዱን ይነሳሀል ወይም ሆዱን ይሰጥህና የምትበላው እህል አይኖርህም ተመስገን አትልም ተጣጥበህ ተበጣጥረህ የዕለት እንጀራህን ለማሳደድ ትወጣለህ፡፡ አገሩ አማን ነው፡፡ እግረኛውም ኦቶቡስ ወይ ታክሲ ተሳፋሪውም፣ ባለ መኪናውም እንደ ሌላው ቀን ወደየጉዳያቸው ይጓዛሉ፡፡ ለዚህ ለሰላም በረከት አምላክህን ታመሰግናለህ፡፡ ሁኔታዎች በአፍሪካ ባህልና ደምብ ሌላ ሊሆኑ ይችሉ ነበራ ወደ ስራህ ለመሄድ ስትወጣ አገር ቀውጢ ሆናለች፡፡ ዝነኛው ጄኔራል ሰጣርጋቸው አይተንፍሱ ጨለማን ተገን በማድረግ የታንከኛ ክፍለ ጦሩን አስገብቶ መዲናይቱን በቁጠጥሩ ስር አውሏታል /አሳድሯታል ማለቴ/
ሁኔታዎች እስካሁን የት እንደደረሱ ለመገንዘብ የከተማው ኗሪዎች ብዙ ጊዜ አልወሰደባቸውም፡፡ የስልጣን ርክክብ መደረጉ አይቀርም፡፡ ስልጣናቸውን ለግል ጥቅም ማሳደጃ ሲያውሉ የነበሩ ባለስልጣናት ሳይርበተበቱ አይቀሩም፡፡ ምክንያቱም፣ ጄኔራል ሰጣርጋቸው አይተንፍሱ መጀመሪያ ይፋ ያደደጉት የአዲሱ መንግስት ባለ ስልጣን አቃቤ ህግ ሲሆን፣ እሳቸውም ዶክተር አለባቸው ያዛቸው ናቸው፡፡ የፀረ ሙስና ጽኑ ጥላቻቸውን በድርጊት ይገልፁታል፣ ያረጋግጡታል፡፡ የነብርን ጅራት አይይቁም፣ ከያዙም አይለቁም ደራሲ አበው
የቀመሰሽ እንጂ የጠገብሽ የለም ደራሲ አበው
በዚህ ዓይነቱ የለውጥና ልውውጥ ወቅት የስልጣን ደላላዎች ብዙ አኩሪ ላቮሮ ያደርጋሉ፡፡ እስር በርስ መጠራጠር ይበዛል፡፡ ሰዎች ወደ ቤተክርስትያንም፣ ወደ መስጊድም፣ ወደ ጠንቋይ ቤትም ይጎርፋሉ፡፡ ስምንተኛው ሺ በብዛት ይጠቀሳል እዚህ ላይ የፈጣሪ ደግነት ይመጣል፡፡ የእለት እንጀራህን ለማሳደድ ስትወጣ አገር አማን ነው፡፡ መሰረታዊ በረከቶችሀን ስትቆጥር፣ በጤና ከማደርህ ቀጥሎ አገር ሰላም መሆኑ ነው፡፡ ሰላም ምን ያህል ታላቅ እሴት መሆኑ የሚታየን ግን ስናጣው ነው፡፡
ሰለስቱ የሰው ዝሪያ በተአምራት አለም
ማን ነን ከየት መጣን ወዴት እየሄድን ነው ዘወትር የሚነዘንዘን ጥያቄ፡፡ እናታችን ሔዋን ትሁን ወይስ ሉሲ ወይስ ሌላ ሴት ትሁን፣ የጥያቄውን አንገብጋቢነት አይለውጠውም፡፡
Do I contradict myself?
Very well, then, I contradict myself.
I am more than one,
I am many, I am myriads,
I am a universe.
(walt Whitman “A song to Myself”)
ከላይ የተመለከትነው አንድ ሰው በተአምራት መሀል ህይወትን በግላዊነቱ ለብቻው እያጣጣመ ሲኖራት ነበር፡፡ ከዚህ በታች የምናየው ደግሞ ሰውየው የዝርያው አንድ አባል ስለሆነ፣ በአባልነት ደረጃ በሩብ ሚልዮን አመታት ውስጥ ከተከማቸው የዝርያ ጥበብ እና ሳይንሳዊ ወይም ቴክኖሎጂያዊ ግኝቶች የቻለውን ያህል በመውረስ ግላዊ ኑሮውን ያበለጽግባቸዋል፡፡ የዝርያችን ዕድሜ ሩብ ሚልዮን አመት ይሆናል ስንል፣ ሀሳብ ለመግለጽ ያህል ነው እንጂ፣ በተጨባጩ አለም የኖሩት ግን ግለሰቦች ብቻ ናቸው፡፡ እንግዲህ የሰው ዝርያ የሚባለው እንትን እያለ የሌለ ፍጡር ነው፡፡ወይም ነገሩ የአንፃር ጉዳይ ቢሆንስ ከላይ ያነበባችሁት በረከት ሁሉ በአንድ ግለሰብ ዕድሜ የተወሰነ ነው፡፡ ቀጥሎ የምትቃኙት ደግሞ በዝርያችን እድሜ /ሩብ ሚልየን አመት/ ውስጥ ቀስ በቀስ የተከማቸ ሳይንሳዊ ሀብትና ባህላዊ እሴት አለ፡፡ ያ ሁሉ ክምችት የዚሁ ግለሰብ የግል ንብረቱ ነው /የወል እየሆነም የግሉ ነው/
. የመጀመሪያው ፈጠራ እሳት ነበር /ይላ አንትሮፖሎጂስቶች/ ሰዎች ጨለማና ቀዝቃዛ  የነበረው ዋሳቸው ውስጥ ሙቀትና ብርሀን ጨምረው ተመቻቹበት፡፡ ብልሀቱ ሁለት በጣም የደረቀ እንጨት በኃይለኛ ፍጥነት ማፋተግ ላይ የተመሰረተ ነበር፡፡ የእንጨቱ ዓይነት በእርጥብነቱ ወራት እንደቀርከሀ የጠጠረ ሳይሆን፣ እንደ ሰንሰል የዋህ ነበር፡፡
. የመጀመሪያው ለማዳ እንሰሳ mans best friend /የሰው ሁነኛ ወዳጅ/ የሚባለው ውሻ ሆነ፡፡ ውሻ በነፃነት የዱር አራዊት ዘመን ተኩላ ነበር /የድሮ በደጉ ዘመን አለ ያረጀ ውሻ/
ወንዶቹ በቡድን አውሬ ለማደን ይወጣሉ እንበል፡፡ አንዲት የሳምንት ቡችላ የምታጠባ ተኩላ ያገኛሉ፡፡ ስለበዙባት በደመነብስ ትፈረጥጣለች፡፡ ወይ አባረው ይገድሉዋታል ወይ ታመልጣለት፡፡ ለማንኛውም፣ ቡችላውን ሲያዩ ያምራል፣ ያሳዝናል፣ እናቱን ሲጣራ ያባባል፡፡ ወስደው ዋሻቸው ውስጥ ያሳድጉታል፡፡ በሌላ ቀን ሌላ ቡችላ ያገኛሉ፣ ጾታው ሌላ የሆነ…
…የሰው ልጅ እንስሳትን በየዝርያው ያለመደው /የቀንድ ከብት፣ የጋማ ከብት/ በተመሳሳይ ዘዴና ሂደት በመጠቀም ነበር ብዙ ብዙ ትውልድ ያልፋል
. እንስሳትን ማልመድ ቀስ በቀስ እየተሻሻለና እያደገ ሄዶ ሄዶ ከብት ርቢ ይሆናል፡፡ አንዳንድ ከብት አርቢ ጎሳዎች ዘላን ይሆናሉ፡፡ ለምሳሌ ክረምት ሲመጣ ከብቶቻቸውን እየነዱ ወደ ቆላ ይወርዳሉ፣ ለበጋ ደግሞ ወደ ወይና ደጋ ይወጣሉ
. አንዳንድ አካባቢ የሚኖሩ ጎሳዎች በመልክአ ምድሩ ምክንያት፣ ለምሳሌ ለም አውላላ ሜዳ ቢሆንና በመሀሉ እየተጠማዘዘ የሚሄድ ወንዝ ቢኖረው፣ እርሻ ይጀምራሉ፡፡ መሬቱን በደረቅ ሹል እንጨት እየቆፈሩ እህል ይዘሩበታል ወይም ይተክሉበታል፡፡ዘመናት እየተንቀራፈፉ ያልፋሉ፣ ባለህበት ሂድ የተባሉ ይመስል ቀስ በቀስ በሬ ወይም ፈረስ ጠምደው ማረስ ጀመሩ፣ ጫፉ ሹል መሆነ ደረቅ አጣና፡፡ ግብርና መጣ፡፡ በአንድ ቀን ስራ የሚታረሰው ማሳ እየሰፋ፣ ምርቱ እየበዛ ሄደ፡፡. ገበሬዎቹ እየበዙ፣ አርሰው የሚኖሩበት አገር እየሰፋ ሄደ፡፡ ማሳው በጣም ምርታማ በሆነለት አመት፣ ገበሬ ከቤተሰቡ ምግብ የተረፈውን እህል ይሸጥና በምትኩ የሌላ ዘር እህል ይገዛል /አይነት በአይነት ይለዋወጣሉ እንጂ በነዚያ ዘመናት ገንዘብ እንኳን መገበያያ ሊሆን ቀርቶ በሀሳብም ሊመጣ አይችልም/
በርካታ ትውልዶች እያለፉ ጥላ ሲሄዱ፣ ቀስ በቀስ የአንድ ሰፊ አካባቢ ገበሬዎች ዋርካ ወይ ሌላ ትልቅ ዛፍ ጥላ ስር እየተገናኙ ምርቶቻቸውን ሲለዋወጡ፣ ሳይታወቃቸው ያ ስፍራ ቋሚ ገበያ ይሆናል፡፡
ከብት አርቢዎቹ ዘላኖች በዚያ አጠገብ በሚያልፉበት ወራት ገበያ መምጣት ይጀምራሉ፡፡ የስልጣኔ ወጋገን ሊያበራ ጀመረ፡፡
. አርሶ አደሩ ሕዝብ እየበዛ ሲሄድ፣ ስርዓተ ማህበሩ የጎሳ ዕድሜውን አልፎ በነገድ ይደራጃል፣ ከዚያ ንጉስና ሕዝብ ይሆናል፡፡በአንድ ፈርጅ ይሄ ሁሉ እየተካሄደ እያለ፣ በሌላ ፈርጅ በሌሎች የስልጣኔ እርምጃዎች እየተወሰዱ ቆይተዋል፡፡ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ግኝቶችና ፈጠራዎች ተከስተዋል፡፡ ይህ እንደምን ተደርጎ ተቻለ የህዝቡ ብዛትና መንግስት ግብር ሰብስቦ ለወል ጥቅም ማዋል የመቻሉ ሁኔታ የሚያመጣው መሰራተዊ እድገት አለ፡፡ አንዳንድ በተፈጥሮ ልዩ ችሎታ ወይም ተሰጥዖ ያላቸው ግለሰቦች ይወለዳሉ፡፡ ልዩ አስተያየት ይደረግላቸዋል፡፡ ከእርሻ ከባድ ስራ ይገለላሉ፡፡
ህዝቡን ለአመት የሚመግበው እህል ተተምኖ፣ ከዚያ በላይ የሆነው በግብር መልክ ተሰብስቦ፣ ለእድገት ይውላል፡፡ እነዚያ ልዩ ሰዎች ለማህበረሰቡ የሚያበረክቱት ፈጠራና ግኝት ከሚከተለው ዝርዝር ሊካሄድ ይችላል፡፡. ሰዎች  ልብሳቸው የእንሰሳ ቆዳ ነበረ፡፡ አንደ ቀን አንዷ ጥጥ በሚፈራበት ወራት መንፈስ ብልጭ አለባት፡፡ ከጥጥ ክርን ፈተለች፡፡ ትውልዶች ካለፉ በኋላ፣ ሌላዋ በክርና በቀርከሀ መሳይ እንጨት የሸማኔ እቃዎች ሰራች፡፡ የሰዎች ልብስ የጥጥ ሆነ፡፡ ቆዳ ልብስ መሆኑ ቀርቶ ተደራቢ ሆነ /ለጌጥም ለምቾትም/  
. ሰዎች ሲያርሱ ገበሬው የሚጨብጠው እርፍ ሹል አጣና ነበር፡፡ አንዱ /እንዲያም አንድ የተለየ ዓይነት አፈር በእሳት ቢያቀልጡት፣ ከዚያ ላይ ብረት ማውጣት ይቻላል በግለት የቀላውን ብረት ቢቀጠቅጡት ሹል ማረሻ፣ ደጋን ማጭድ፣ ስለታም ሰይፍ፣ ቢላዋ፣ የጦር ጫፍ፣ ወስፌ፣ እና ሌላ ሌላ መሳርያ ይወጣዋል
. የስልጣኔ ሂደት የመጀመሪያ እርምጃዎችንና አቅጣጫቸውን ከየን ለዛሬ ይበቃናል፡፡ ለመደምደም ያህል የጽህፈትን /በኋላ ፊደል የሚሆነውን/ አመጣጥ እንፈትሽ፡፡የጠቅላላ እውቀት ማዳበርያ ጥያቄ መጥቶ ጽህፈትን ምን ዓይነት ሰው ፈጠረ ቢላችሁ ምን ትመልሱለት ይሆን እኔ አንዱ የጥንት ደብተራ ነው ብዬ እመልስ ነበር፡፡ ብዙ ሰውም እንደዚሁ፡፡ ነገሩ ግን ጩኸቴን ቀሙኝ ሆኖ ነው እንጂ ፈር ቀዳጁስ ነጋዴ ነው፡፡በምናብ ብዙ ዘመናት ወደ ኋላ እንመለስ፡፡ አንድ ነጋዴ እዚህ በግ ይሸጣል እንበል፡፡ አምስት ወንዝ ተሻግሮ ወንድሙ በሬ ይሸጣል፡፡ ሶስት በሬ ላክልኝ ሲል፣ ጠፍጣፋ ስስ ድንጋይ ላይ ወይም የከብት አጥንት ላይ /ለምሳሌ ትከሻው አካባቢ/ የሶስት በሬ ስዕል ሰርቶ በታማኝ ባርያ /በዚህ ዓይነቱ ጉዳይ ጥንቃቄ ለመውሰድ ተብሎ ምላሱ የተቆረጠ/ ይልካል… ዘመናት ቀስ በቀስ ካለፉ በኋላ ተረኛ ይፈጠርና እንደፈረደበት ወደ ሀሁ ሂደታችንን አንድ ረዠም እርምጃ ሲጨምርበት፣ ሶስት በሬ ሳይሆን፣ ሶስት የበሬ ጭንቅላቶች… ከትውልዶች በኋላ የሶስት ቀንድ ስዕል ብቻ ይልካል…
ቸር ይግጠመን አሜን

 

Read 4877 times Last modified on Saturday, 08 October 2011 09:35