Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 08 October 2011 09:18

ለወሬና ለፍርድ” የሚያስቸግሩ የአገራችን ገጠመኞች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

አንድ ፓርቲ የገነነበት ፓርላማአሉታዊ፡- ፓርላማው በገዢ ፓርቲና ለስልጣናት የተዘጋጁ ህጎችን ብቻ    ያፀድቃል፤ ሁሌም። ፓርላማ ለምን አስፈለገ?” ያሰኛል። አወንታዊ፡- በአለም ህዝብ ፊት “ፓርላማ የሌለው ኋላቀር አገር” ከምንባል ይሻላል።ቴሌ የመንግስት መሆኑአሉታዊ፡- ቴሌ በከፍተኛ ወጪ የተከላቸው የመንገድ ስልኮች በአብዛኛው አይሰሩም። የባከነው ከፍተኛ ገንዘብም ይቆጫል። አወንታዊ፡- የተተከሉት “የስልክ ቤቶች” ባይሰሩም ለመጠለያነት እያገለገሉ ነው።የቢፒአር ነገርለአመታት ብዙ መቶ ሚ. ብሮችን  የፈጀ  የቢፒአር ሪፎርም፤ ዘላቂ ለውጥ  አላመጣም ሲባል ያስደነግጣል። የባከነው ጊዜና ገንዘብስ?

ደግነቱ፤ ሌላ አዲስ የሪፎርም ፕሮግራምለመጀመር ጥናቶች ተጠናቀዋል ተብሏል።አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ
ዩኒቨሪሲቲው ለፈተና ጠርቶን ከየክልሉ  ስንመጣ፤ በዋዜማው እለት ፈተናው ተራዝሟል ተባለ። ዝርክርክነቱ  አያሳዝንም?
ደግነቱ፤ ስርአት የያዘ ሳይንስና የአመራር ጥበብ የምንማረው ከዩኒቨሪሲቲው ነው።

ገዢው ፓርቲና አጋር ድርጅቶች ከ99.9 በመቶ በላይ የተቆጣጠሩት ፓርላማ፤ የዘንድሮ የመጀመሪያ ስብሰባውን ሰኞ እለት ያካሂዳል። የፓርላማና የፌደሬሽን ምክርቤት አመታዊ የጋራ ስብሰባ የሚከፈተው በፕሬዚዳንቱ ነው፤ በተለምዶ ጠ/ሚሩ በሚገኙበት።
በነገራችን ላይ የፌደሬሽን ምክርቤት፤ ሙሉ ለሙሉ የኢህአዴግና የአጋር ድርጅት አባላትን ብቻ የያዘ ሆኗል። የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት የሉበትም። ለነገሩ የክልል ምክርቤቶች ሁኔታም ተመሳሳይ ነው።  ድሮ ድሮ፤ መንግስት “ዲሞክራሲያዊ ስርአት እየገነባሁ ነው” ብሎ ለማሳመን ምን ይል እንደነበር ታስታውሳላችሁ? “ይሄው ተመልከቱ፤ በርካታ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ወደ ፓርላማና ወደ ክልል ምክርቤቶች ገብተዋል” ይል ነበር። ዛሬስ? “ይሄው ተመልከቱ፤ ምክርቤቶቹ ከተቃዋሚ ፓርቲ የፀዱ ሆነዋል” ሊባል ነው?
በስልጣኔ ደህና የተራመዱ አገራት ውስጥ እንደምናየው ቢሆን ኖሮ፤ ፓርላማና ምክርቤት ሲባል... የተለያዩ ተፎካካሪ ፓርቲዎችና ፖለቲከኞች መናሃሪያ እንደማለት ነው። አንደኛው ፓርቲ ወይም ፓለቲከኛ፤ ከሌላው በልጦ ለመገኘትና የተሻለ ሃሳብ ለማቅረብ ሲከራከሩ የምናይበት ነው - ፓርላማ ወይም ምክርቤት።
ስልጣን የያዘው ፓርቲ ወይም ፖለቲከኛ፤ ጠቅላላ የፖሊሲ ሃሳቦችን ሲመርጥ፣ ህጎችን ሲያዘጋጅና እቅዶችን ሲያወጣ፣ ሁሉም ነገር አልጋባልጋ አይሆንለትም። ፓርላማ ውስጥ ከፈታኝ ጥያቄዎች ጋር ይፋጠጣል - ከተፎካካሪ ፓርቲዎች በኩል በሚሰነዘሩ ጥያቄዎች፣ ሃሳቦችና መከራከሪያዎች። በዚህም ምክንያት ነው፤ በሰለጠኑት አገራት ውስጥ ገዢ ፓርቲዎችና የፖለቲካ መሪዎች፤ የመንግስት እቅድ ሲያወጡም ሆነ ህግ ሲያረቁ፤ በእጅጉ ለመጠንቀቅና ህጉን በጥራት ለማዘጋጀት የሚጣጣሩት። አለበለዚያ ያረቀቁት ህግ ውድቅ ይደረጋል፤ ከዜጎች የሚያገኙት ድጋፍም ይወርዳል - ተቃዋሚ ፓርቲዎች የተሻለ ሃሳብ ካቀረቡ። ይህም ብቻ አይደለም። እቅድ ለመተግበር የሚያከናውኗቸው ስራዎችና በየእለቱ የሚፈፅሟቸው ነገሮች ላይም፤ ገዢው ፓርቲና ባለስልጣናቱ በጣም መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል። ጎደሎ ወይም ብልሹ እቅድ፤ ውጤት አልባ ወይም አባካኝ ተግባር ከተገኘባቸው፤ ሸፋፍነው ማለፍ አይችሉም - ፓርላማ ውስጥ “በመረጃና በማስረጃ” ፍርጥርጡ እንደሚወጣ ይታወቃላ። ይህንን  የሚከታተሉ ዜጎችም፤ ለገዢው ፓርቲ ድጋፍ መስጠታቸውን እያቆሙ፤ ወደ ሌሎች ፓርቲዎች ሊሳቡ ይችላሉ - ተቃዋሚ ፓርቲዎች የተሻለ ሃሳብና እቅድ፤ አሳማኝ መረጃና መከራከሪያ የሚያቀርቡ ከሆነ።
ገዢውን ፓርቲና ባለስልጣናትን ለመፈተንበት፣ ለመመርመርና ለመፈተሽ ብቻ አይደለም የፓርላማ አገልግሎት። በዚያው መጠን፤ ዜጎች ተቃዋሚ ፓርቲዎችንና ፖለቲከኞችንም በግላጭ እንዲፈትሹና እንዲመዝኑ እድል ይሰጣቸዋል - በምርጫ ወቅት ለእያንዳንዱ ፓርቲ ዋጋውን ለመስጠት።
በአጠቃላይ ፓርላማ፤ ከየትኛውም ፓርቲ በኩል ለሚመጡ ጉድለቶች መፍትሄ ለማበጀት፤ መልካም ጥንካሬዎችን ደግሞ ለማበረታታት እንደሚጠቅም፤ ከሰለጠኑት አገራት ታሪክ መገንዘብ እንችላለን። ጭፍን ሃሳቦች፣ የተሳሳቱ ህጎች፣ ጎጂ  እቅዶችና የጥፋት ድርጊቶች በጊዜ ውድቅ የሚደረጉበትና የሚወገዱበት እድል ይፈጥራል። ምክንያታዊ ሃሳቦች፣ ትክክለኛ ህጎች፣ ጠቃሚ እቅዶችና የስኬት ድርጊቶች ተቀባይነት አግኝተው እውን የሚሆኑበት እድል ለማግኘትም ያገለግላል - ፓርላማ።
ይሄን ሁሉ የምለው፤ በስልጣኔ ደህና የተራመዱ አገራት ውስጥ የሚገኙ ፓርላማዎችንና ምክርቤቶችን በማየት እንደሆነ ልብ በሉ። የአገራችን ፓርላማና ምክርቤቶች ከዚህ በእጅጉ ይለያሉ። ከ99.9 በመቶ በላይ በገዢው ፓርቲና በአጋሮቹ የተያዙ ናቸውና። የአንድ ፓርቲ ገናናነት ሰፍኖባቸዋል። ምን ይሄ ብቻ?
እያንዳንዱ የፓርላማና የምክርቤት አባል፤ ከራሱ ህሊና ውጭ ለማንም ተገዢ እንደማይሆን በህገመንግስት ውስጥ ቢሰፍርም፤ የአገራችን ፓርቲዎች ይህንን አሰራር አይፈቅዱም። በፓርቲ መሪዎች በኩል (በማእከላዊና በስራ አስፈፃሚ ኮሚቴዎች በኩል) ተዘጋጅተው የሚመጡ ሃሳቦችንና ህጎችን በመደገፍ ማፅደቅ እንጂ፤ መቃወምና ሌላ ሃሳብ ማቅረብ አይቻልም። በገዢው ፓርቲ አሰያየም፤ “ማእከላዊነት” ይባላል ይህ የተዋረድ አሰራር። እንግዲህ ፍረዱ። የአንድ ፓርቲ ገናናነት የነገሰበት ፓርላማ ላይ፤ የ”ማእከላዊነት” አሰራት ሲጨመርበት አስቡት።
እንደምናየው፤ ፓርላማው ሁሌም በገዢው ፓርቲ የበላይ አካላትና በባለስልጣናት ተዘጋጅተው የሚመጡ ሃሳቦችንና ህጎችን ብቻ ያፀድቃል። የተሳሳቱና ጎጂ ህጎችን ውድቅ ለማድረግ፤ በእነዚሁ ምትክም በተሻሉ ሃሳቦች የተረቀቁ ህጎችን ለምቀረብ የሚቻልበት እድል አይኖርም። “ታዲያ፤ ፓርላማ እና ምክርቤቶች ለምን አስፈለጉ?” የሚል ጥያቄ መምጣቱ አይቀርም። የገዢው ፓርቲ የበላይ አካላትና ባለስልጣናት በቀጥታ ህጎቹን ቢያፀድቁና ቢያውጁ ልዩነት አለው? ልዩነት ከሌለውኮ፤ (ሌላውን ሌላውን ሁሉ ጉዳት ለጊዜው ብንተወው እንኳ)፤ በየአመቱ ለፓርላማ የሚመደበው መቶ ሚሊዮን ብር ገደማ ገንዘብ በከንቱ እየባከነ ነው ያስብላል። ለሌሎቹ ምክርቤቶች የሚወጣውንም ገንዘብ አስቡት። ብዙ ነው። የዜጎች የሚሰበሰብ ቀረጥና ግብር እንደሆነ አትርሱ። በስልጣኔ እንደተራመዱት አገራት የፓርላማ ጥቅሞችን ለማግኘት አለመቻላችን ያነሰ ይመስል፤ በከንቱ ገንዘብ ሲባክን ማየት ያስቆጭ ይሆናል።
ግን ደግሞ፤ ጉዳዩን በሌላ በኩል ስናየው፤ አወንታዊ ገፅታዎች ሊኖሩት ይችላል። ለምሳሌ፤ በቃ ... እንዲሁ... በአለምአቀፍ ደረጃ፤ “ኢትዮጵያኮ ፓርላማ አላት” ሲባል አያስደስትም? “ለአገር ገፅታ ግንባታ” ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ብሎ መገመትም ይቻላል። እየቀለድኩ አይደለም፤ እንደ ግማሽ ቀልድ ይሆንባችሁ ይሆናል። ግን እየቀለድኩ አይደለም።
... ማለቴ በ”ፅንፈኝነት” አሉታዊና ደካማ ጎኖችን ብቻ ሳይሆን አወንታዊና ጠንካራ ጎኖችንም ማየት እንዳለብን በተደጋጋሚ ሲነገር ሰምታችሁ የለ? አንዳንዴ ስታስቡት፤ (“በአንድ በኩል... በሌላ በኩል...” ማለት ሳያስፈልግ) የተበላሹ ነገሮች እንዲስተካከሉ መተቸትና ሃሳብ መስጠት ... ለብቻው፤ ጉዳት እንደሌለው ይታያችሁ ይሆናል። ሌላ ጊዜ ደግሞ፤  በጣም የተበላሹ ጉዳዮች ሲያጋጥሟችሁ፤ አወንታዊና ጠንካራ ጎን ማግኘት አስቸጋሪ እየሆነ ያስጨንቃችሁ ይሆናል። ቢሆንም ግን፤ እንደምንም ተጣጥረን፤ አወንታዊና ጠንካራ ጎኖችን ለማግኘት ሞካክረን ብናየው አይከፋም።ለምሳሌ፤ የፓርላማ ጥቅሞችን ለማግኘት ባንችልም፤ ለፓርላማው ብዙ ሚሊዮን ብር ወጪ እየተደረገ ቢሆንም፤ ፖርላማ የሚባል ነገር መኖሩ ራሱ፤ እንደ አንድ አወንታዊና ጠንካራ ጎን ብናየውስ? ፓርላማ የሌላቸው አገሮችኮ አሉ። ለምሳሌ ኤርትራ። በዚያ ላይ፤ የወደፊቱን መመልከት ይኖርብናል። ዛሬ የምናየው ፓርላማ፣ ቅርፅና ስም ብቻ ሊሆን ይችላል። ወደፊት ደግሞ... “በሂደት” ... የቁምነገር ይዘትና ጥቅም ይጨመርበት ይሆናል።
ሌሎቹንም ጉዳዮች በዚሁ “አቅጣጫ” አሉታዊና አወንታዊ ጎኖቻቸውን መተንተን ትችላላችሁ። ለምሳሌ እንደ አብዛኞቹ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሁሉ፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨሪሲቲ ውስጥ የሚታየውን ዝርክርክነትን ተመልከቱ። የማታ ክፍለጊዜ (የኤክስቴንሽን) ተማሪዎች የምዝገባ ጊዜ መቼ እንደሆነ ለመግለፅ፤ ዩኒቨሪሲቲው ማስታወቂያ ሲያስነግር ታዝባችሁ ይሆናል። ብዙዎቹ ተማሪዎች የዩኒቨሪሲቲውን ጣጣ ስለሚያውቁ፤ ይዋል ይደር አላሉም። ቶሎ ለመመዝገብ ሄደዋል።
መቼም ዩኒቨሪሲቲዎች በአስተሳሰብና በሳይንስ፣ በአመራርና በቴክኖሎጂ ሁሉንም ቀድመው የሚራመዱ ተቋማት እንዲሆኑ ብታስቡ ነውር የለውም። በኢንተርኔት (በኦንላይ) የተሟላ መረጃ ማሰራጨት ብቻ ሳይሆን፤ ምዝገባዎችንም በኢንተርኔት ማከናወን ይጀመራል እየተባለ ሲወራ ስንት አመት አለፈው? መረጃውም በወጉ በተገኘ!
የሆነ ሆኖ፤ የማታ ተማሪዎቹ፤ እንደየትምህርቱ አይነት በክፍለጊዜ እየተሰላ የሚከፍሉትን ገንዘብ ይዘው ለምዝገባ መጥተዋል። ቢሆንም፤ የማባዛትና የመደመር ችሎታ የሌላቸው ይመስል፤ “ፎርም” ከሞሉ በኋላ፤ “ክፍያ አስተምኑ” ተብለው ይሰለፋሉ። አምና ለአንድ ሴሚስቴር፤ አምስት መቶ ብር ገደማ ይከፍሉ የነበሩ ተማሪዎች፤ አሁን 700 ብር ገደማ እንዲከፍሉ ተተመነባቸው። “እንዴት?” ብለው ሲጠይቁ፤ በቃ ክፍያ ጨምሯል ተባሉ - (ለምሳሌ በአንድ የትምህርት አይነት የአንድ ክሬዲትአወር ክፍያ ከ43 ብር ወደ 58 ብር ጨምሯል። 35 በመቶ ማለት ነው)። ታዲያ፤ የምዝገባ ማስታወቂያ ስታስነግሩ፤ ክፍያ እንደጨመረ ለምን አትገልፁም ነበር? “እኔ አያገባኝም፤ ማስታወቂያ አስነጋሪዎቹን ጠይቃቸው”። ሌላው ቢቀር፤ በዩኒቨሪሲቲው ዌብ ሳይት ላይ፤ በሁለት መስመር ፅሁፍ መረጃውን መግለፅ ይከብዳል? ለመመዝገብ የመጡት አብዛኞቹ ተማሪዎች በቂ ገንዘብ ስላልያዙ በከንቱ ደክመው ተመለሱ።ዩኒቨሪሲቲው ለፈተና ጠርቷቸው ከየክልሉ የመጡ በርካታ ሰዎች ደግሞ ይበልጥ ተቸግረዋል። አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ፤ ፈተናው እንደነገ ሆኖ፤ ዛሬ ፈተናው እንደተራዘመ ተነገራቸው። ለዚያውም ዩኒቨሪሲቲው ውስጥ በግልፅ በማይታይ ቦታ ላይ በተለጠፈች ማስታወቂያ ነው የተነገራቸው - ፈተናው ለሁለት ሳምንታት ተራዝሟል። ለፈተና ከየከተማው የመጡ ሰዎች፤ እስከዚያው በማን ወጪ የት መቆየት ይችላሉ? እሱ የራሳቸው ጉዳይ ነው።እነዚህን ምሳሌዎች የማነሳው፤ የዩኒቨሪሲቲውን ስርአት የለሽና የዘፈቀደ ዝርክርክር አሰራሮችን በመዘርዘር፤ አሉታዊና ደካማ ጎኖቹን ብቻ ለማሳየት አይደለም። በእርግጥ እንዲህ አይነት አሰራር የሚከተል ዩኒቨሪሲቲ፤ እንዴት ብሎ ስርአት ያለው ሳይንሳዊ እውቀትና አስተሳሰብ ሊያስተምር ይችላል ከሚል ጥያቄ ጋር መፋጠጣችን አይቀርም። ስለ ኢንፎርሜሽን ሳይንስና ስለአመራር ጥበብ ከመጀመሪያ ዲግሪ አንስቶ እስከ ዶክትሬት ድረስ አስተምራለሁ የሚል የአገሪቱ ቁንጮ ተቋም፤ በኢንፎርሜሽን እጥረትና በአመራር ዝርክርክነት አርአያ የሚሆን ከሆነ... ነገሩ ሁሉ ጨዋታ ሆኖ ሊታያችሁ ይችላል።ቢሆንም... አወንታዊና አሉታዊ ጎኖችንም ማየት ያስፈልጋል ተባብለን የለ? ለምሳሌ፤ በዩኒቨሪሲቲው ከምናየው ጉድለትና ዝርክርክነት የምንቀስመውን ትምህርት እንደቁልፍ አወንታዊ ጎን ልንቆጥረው እንችላለን። በዚያ ላይ፤ ዩኒቨርሲቲ የሚባል ነገር መኖሩ ራሱ ትልቅ ነገር ነው። አይደለም?
የቢፒአር እና የመንገድ ላይ ስልኮች ጉዳይም እንዲሁ፤ አሉታዊ ጎናቸውን ብቻ ሳይሆን፤ እንደምንም አወንታዊ ጎናቸውንም ለማየት በመጣር ለመተንተን መሞከር ትችላላችሁ።

 

Read 5366 times Last modified on Saturday, 08 October 2011 09:24