Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 08 October 2011 09:07

ለስደት እየኖረ የሚሞት ትውልድ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በሰሜን ምስራቅ አማራ ክልል፣ ኦሮሚያ ዞን ጨፋ ሮቢት ወረዳ የሚገኙ ነዋሪዎች በአብዛኛው ከቤተሰባቸው ውስጥ አንዱን በበረሃ ጉዞ ወይም በባህር እንዳጡ ይናገራሉ፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች በተለይ ወጣቱ በየመን በኩል ወደ ሳዑዲ አረቢያ ለመሻገር ሁሌም ልባቸው እንደቆመ ነው፡፡ ያለምክንያት ግን አይደለም፡፡ የሚያውቁት የአካባቢያቸው ወጣት ከሳዑዲ አረቢያና ከየመን በሚልከው ገንዘብ የቤተሰቡን የሳር ጐጆ ወደ ቆርቆሮ ቤት አሻሽሎ ስለሚመለከቱ የእነሱንም ቤተሰቦች ኑሮ እንደ ጓደኞቻቸው ለመቀየር ያልማሉ፡፡ ምኞታቸውን አንግበው የሚገጥማቸውን ሁሉ ተጋፍጠው ባህር በመሻገር  በተገኘው ሥራ ተሰማርተው የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ህይወት ማሻሻልና መለወጥ ይፈልጋሉ፡፡ ክፋቱ ግን አይሳካም፡፡ አብዛኞቹ መንገድ ይቀራሉ፡፡ ከህልማቸውም ይሰናከላሉ፡፡

ወጣቶቹ በህይወት ይፈተናሉ፤ በበረሃ በሚኖሩ ሕገወጥ ዘራፊዎች ይዘረፋሉ፣ ሴቶቹ ከአንድ በላይ በሆኑ ወንዶች ይደፈራሉ፡፡ በህይወት አብረዋቸው ይጓዙ የነበሩ ጓደኞቻቸውን በሞት ከበረሃ እያንጠባጠቡ፣የቻሉ ቀብረው ያቃታቸው ደግሞ ለጓደኞቻቸው ነፍስ ገነትን ተመኝተው ጉዟቸውን ይቀጥላሉ - ኑሮአቸውን የተሻለ ለማድረግ ወደማያውቁት አገር፡፡
“ግማሽ ሰውነታቸው ብቻ አፈር ለብሶ፣ አስከሬናቸው ሳይቀበር አውሬና አሞራ እየተጫወተባቸው፣ አስከሬናቸው አባብጦ ያለቀባሪ የበረሃ ሲሳይ የሆኑ፣ ከሞት ጋር ትንቅንቅ ገጥመው በየመንገዱ ጣር ይዟቸው የሚተናነቁትን “አይዞህ” እያልን እናልፍ ነበር…” የአንድ ወጣት ትረካ ነው፡፡
የሌላኛው ትረካ ደግሞ ይቀጥላል፤ “ስንቱን በረሃ እና ባህር ስንሻገር ደህና እየሳቀ የነበረው ጓደኛዬ ተዝለፍልፎ ወደቀ፡፡ እዚያው ሞተብኝ፤ የመኖቹ አካፋና ዶማ አመጡልኝ፤ቆፍሬ እንደ አገራችን ቀበርኩት” ወጣቶቹ ወደውም፤ተገደውም የሚገቡበት የስደት ሰቆቃ ማብቂያ የለውም፡፡ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አበባየሁ ገበያው ወጣቶቹ ጓዛቸውን ጠቅልለው ለስደት ከሚወጡበት አነስተኛ ወረዳ ተገኝታ አነጋግራቸዋለች፡፡ ሙሉ ዘገባውን
ከኢትዮጵያ እስከ የመን እና ሳዑዲ አረቢያ - የስደት ጉዞ
በሰሜን ምስራቅ አማራ ክልል፣ ኦሮሚያ ዞን የጨፋ ሮቢት ወረዳ የሚገኙ ነዋሪዎች በአብዛኛው ከቤተሰባቸው ውስጥ አንዱን በበረሃ ጉዞ ወይም በባህር እንዳጡ ይናገራሉ፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች በተለይ ወጣቱ በየመን በኩል ወደ ሳዑዲ አረቢያ ለመሻገር ሁሌም ልባቸው እንደቆመ ነው፡፡ ያለምክንያት ግን አይደለም፡፡ የሚያውቁት የአካባቢያቸው ወጣት ሳዑዲ አረቢያና ከየመን በሚልከው ገንዘብ የቤተሰቡን የሳር ጐጆ ወደ ቆርቆሮ ቤት አሻሽሎ ስለሚመለከቱ የእነሱንም ቤተሰቦች ኑሮ እንደ ጓደኞቻቸው ለመቀየር ያልማሉ፡፡ ምኞታቸውን አንግበው የሚገጥማቸውን ሁሉ ተጋፍጠው ባህር በመሻገር  በተገኘው ሥራ ተሰማርተው የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ህይወት ማሻሻልና መለወጥ ይፈልጋሉ፡፡ ክፋቱ ግን አይሳካም፡፡ አብዛኞቹ መንገድ ይቀራሉ፡፡ ከህልማቸውም ይሰናከላሉ፡፡
እዚያው ጨፋ ሮቢት ያገኘሁት የ16 ዓመቱ ታዳጊ እንዴት የስደት ጉዞውን እንደጀመረ ሲናገር፡፡ “በግብርና ነበር የምተዳደረው ከቤተሰቦቹ የተሰጠኝን አንድ ጊደር በ5ሺ ብር ሸጬ ለመሄድ ተነሳሁ፤ በአካባቢው የሚኖሩ ጓደኞቼም ሆኑ ዘመድ አዝማዶቼ የሞቱት ሞተው የተረፉት በየመንና በሳዑዲ በአረም አራሚነት፣ በከብት ጠባቂነትና በመሳሰሉት ስራዎች ተሰማርተው ለቤተሰቦቻቸው የሚልኩት ገንዘብ ስላጓጓኝ ነው፤” የሚለው ታዳጊው፤ ሞት ለእኔ ደንታዬም አልነበረም ይላል፡፡ “እዚህም ሆነሽ እንደ ሃጃሽ ትኖሪያለሽ፡፡ በባህርም ሆነ በውሃ ጥም መንገድ ላይ የሞቱትም ሃጃቸው ነው” ብሏል ታዳጊው፡፡   
ታዳጊው ታሪኩን ሲያጫውተኝ ትክዝ ብሎ ነበር፡፡ “አራት ሆነን ነበር ከጓደኞቼ ጋር ከአካባቢያችን ተነስተን ወደ ባቲ በመኪና የተጓዝነው፤ ሎጊያ ለመድረስ እያንዳንዳችን ስድስት መቶ ብር ከፈልን፡፡ ከዚያም ከአፋር እስከ ጅቡቲ መንገድ የሚመራንን ሰው አግኝተን ጉዞ ጀመርን፡፡ በዱር በገደል እያደረግን ከተሳቢና ከሌሊት አውሬ እራሳችንን እየጠበቅን፤ ለ8 ቀናት በበረሃው ውስጥ ስንጓዝ የያዝነው 5 ሊትር ውሃ አልቆብን ተቸገርን፡፡ በየመንገዱ በአፋር በረሃ የሚኖሩ “የበረሃ ሰዎች” ብቅ ብለው ግብ ግብ ይገጥሙናል፡፡ ሲይዙን ገንዘብ ካለን የተወሰነ ሰጥተን እናልፋለን፤ ይህን ካላደረግን እንደሚደበድቡን /እንደሚገድሉን/ ተነግሮናል፡፡ ሲፈትሹን የልብሳችንን የጠርዝ ስፌት እንኳን ሳይቀር በጩቤያቸው እየተረተሩ ያዩ ስለነበር፣ በቃ ወጥቼ ቀረሁ እያልኩ እሰጋ ነበር፡፡ በዚህ ጭው ባለ በረሃ ሬሳ በየቦታው እናይ ነበር፡፡ በተመሳሳይ ከጅማ፣ ከአርሲና ከትግራይ የሚመጡ ወጣት ወንዶችና ሴቶች ሞተው፣ ግማሽ ሰውነታቸው ብቻ አፈር ለብሶ፤ አስከሬናቸው ሳይቀበር አውሬና አሞራ የተጫወተባቸው፤ ሞተው ሰውነታቸው አባብጦ ያለ ቀባሪ የበረሃ ሲሳይ የሆኑ፤ ከሞት ጋር ትንቅንቅ ገጥመው በየመንገዱ ጣር ይዟቸው የሚተናነቁትን “አይዞህ” እያልን እናልፍ ነበር፡፡ ያው ግን አቃስቶ አቃስቶ በውሃ ጥም፤  ይሞታል፡፡ በየመንገዱም ስንገናኝ ከየት ነው የመጣኸው፤ ከየት ነው የመጣሽው ተባብለን እንጠያየቃለን፡፡ “ለሁለት ደፈሩኝ፤ ተጫወቱብኝ፤ ፈትሸው ለቀቁኝ፤ የማይል የለም፡፡
“ተጆራ የምትባል የባህሩ ወደብ ስንደርስ ብሩ አለቀ፤ ወደ ቤተሰብ ደውዬ 1ሺ ስድስት መቶ ብር አሳወልኩ” አለኝ፤ ታዳጊው (ሃዋላ አስደረኩ ማለቱ ነው) በባንክ ሳይሆን ቤተሰቦቹ በአካባቢያቸው ለሚገኝ አንዱ ግለሰብ እንዲሰጡ የሰውዬው አድራሻና ስልክ ተሰጥቷቸው ነው፡፡ ግለሰቡ 1600 ብር ሲቀበል ለኢብራሂም የኤደን ባህረ ሰላጤን ለማቋረጥ የትራንስፖርት ገንዘብ ተከፈለለት ማለት ነው፡፡
“ጉዞ ወደ የመን ሆነ . . . ከጣውላና ከቀላል ነገር በተሰራችው ጀልባ /በዶኒክ/ ኩርትም ብለን ተጣጥፈን ተቀምጠን ነበር ጉዞ የጀመርነው፡፡ መላወስ የለም መነቃነቅ የለም፡፡ ግማሹ ወደ ላይ ግማሹ ወደ ታች ይለው ነበር፤ ግማሹ ባህር ውስጥ ገብቶ ለመሞት ይነሳ ነበር . . . አሁን አሁን የሆነ መሰለኝ፡፡ እንዴት እንደሆነ ታውቂያለሽ “የበሃሩ ጨዋማነትና ቅዝቃዜው፤ የባህሩ ውሃ ወደ ጀልባዋ ገብቶ ሲረጨን በአይናችንና አፋችን ይገባል፡፡ ሽታው፤ ቅዝቃዜውና ጨዋማነቱ ነፍስን የሚነጥቅ ነው የሚመልስሽ፤ ጭብጥብጥ ብለን እንደተቀመጥን የባህር ዳርቻ ላይ ደረስን፡፡  መሬት ላይ የተሰማኝ እፎይታ . . . ፊቱ ጨለማ ለብሶ፡፡ ስንቱን በረሃ፣ ያንን ባህር ስንሻገር  ደህና እየሳቀ የነበረው ጓደኛዬ ተዝለፍልፎ ወደቀ እዚያው ሞተብኝ፡፡ የመኖች፤ አካፋና ዶማ አመጡልኝ ቆፍሬ እንደ አገራችን ወግ ቀበርኩት፡፡ በጀልባ የመጣነው ሰዎች ገና ሳንበታተን ነው፤ ሳዑዲ ለሚገኝ ሰው ደውለን እገሌ ሞቷል ብለን የነገርነው፡፡ እሱ ወደ ኢትዮጵያ ደውሎ ለቤተሰቦቹ መርዶ አደረሰ፡፡ አብረውን የተጓዙ ከጅማና ከአሩሲ የመጡ ልጆችም ሞተዋል - እኛው ቀበርናቸው፡፡ ሃበሻ ለሃበሻ አንጨካከንም” ወደ ሳዑዲ  ገና  ለመሻገር ብዙ ጉዞና ፈተና የሚጠብቀው ኢብራሂም፤ እንዳሰበው ከቀናውና ከተሻገረ የመጀመሪያ ስራው ስልክ መደወል ነው፤ ሳውዲ አረቢያ ለሚኖር ወዳጅ ወይም ዘመድ፡፡ ስልክ ቁጥሩን ጽፎ ይዟል፡፡ ነገር ግን ከየመን እስከ ሳዑዲ ያለው ጉዞ ቀላል አይደለም፡፡ “የየመን ፖሊሶች ያዙኝና የሳዑዲ ቁጥርህን አምጣ አሉኝ፤ የለኝም አልኳቸው፡፡ እያዋከቡ ፈተሹኝ፡፡ የቤተሰቦቼን የኢትዮጵያ ስልክ ቁጥር አገኙብኝና ደወሉ፡፡ ሊያናግሯቸው ሞከሩ፡፡ “ኢብራሂም ሰኢድ እዚህ የመን ሲደርስ ይዘነዋል” ተደናገጡ፡፡ “40 ሺህ ብር በሃዋላ የማትልኩልን ከሆነ አይለቀቅም” አሏቸው፡፡ በእርሻ ስራ ወዲያ ወዲህ ሲሉ የነበሩ ቤተሰቦቼ ግን እንኳን 40ሺ ብር ሊኖራቸው ቀርቶ፤ በልቶ ማደርም ይከብዳቸዋል፡፡  እኔም ከሃገሩ የወጣ ሞትም ለሃጃው ነው አልኳቸው፡፡ ፖሊሶቹ ሶስት ቀንና ሌሊት ደበደቡኝ፡፡ ብቻዬን አይደለም የተያዝኩት፡፡ ሰማኒያ እንሆናለን፡፡ ፖሊሶቹ የየቤተሰባችንን ስልክ ቁጥር እየጠየቁ ይደውላሉ - ገንዘብ በሃዋላ እንዲልኩላቸው፡፡ ስናንገራግር ይገርፉናል፡፡ አንድ ምሽት ሽንቴ መጣ ብዬ ፍቃድ ስጠይቃቸው ደበደቡኝ፡፡ ግርግር ሆነ ሌሎችም አመፁ፡፡ አካባቢው ተረብሾ  ተበታተንባቸው፡፡ ተኮሱ . . . ያመለጠ አመለጠ፤ ያልተሳካለትም እዚያው ቀረ፡፡ በረሃ ለበረሃ በእግር ተጉዤ አስፓልት ጋ ስደርስ ደከመኝ፡፡ በእግር መቀጠል አልችልም፡፡ የመጣው ይምጣ ብዬ ወደ ሳውዲ አቅጣጫ የሚጓዙ መኪኖችን መለመን ጀመርኩ፡፡ መኪና እየለመንኩ ነው ሳዑዲ ድንበር የደረስኩት፡፡ እንደኔ ወደ ሳዑዲ ለመሻገር የሚሞክሩ ልጆች ነበሩ፡፡ የሳዑዲ ድንበር ጠባቂዎች ሃይለኞች ናቸው፡፡ ድንበሩ በሽቦ ታጥሯል፡፡ በዚያ ላይ ወደ ሽቦው ከተጠጋን፤ ከድንበር ጠባቂዎች ምልክት ይሰጣቸዋል፡፡ ከተያዝን ወደ የመን ወደብ ይመልሱናል፡፡ በዚህ በኩል መላ ስናጣ፤ ሃርዳ ወደምትባል ቦታ ሄድን፡፡ ከኢትዮጵያ ባህር አቋርጠው የመጡና የሚንከራተቱ አዲስ መጤዎች፤ ሳውዲ ድንበር ላይ የተያዙ እና ከተለያዩ ሳውዲ ከተሞች የተባረሩ ሰዎች የሚሰባሰቡባት ቦታ ነች፡፡ ቀይ መስቀል እና IOM የተባለ ድርጅት ተባብረው እርዳታ የሚሰጡበ ቦታ ስለሆነ ገባን፡፡ በቃ…ያሰብነው  ስላልተሳካ፤  ወደ አገራችን በአውሮፕላን እንድንመለስ ረዱን፡፡ ዛሬ ይሄው በህይወት አለሁ፡፡ የበረሃውና በየባህሩ ያየሁትን መከራ፤ እንደገና የመን ውስጥ የደረሰብኝን ስቃይ ድጋሚ ማየትና ማሰብ አልፈልግም፡፡  
ሌላው የ19 ዓመት ወጣት ሀሰን አህመድ ከኢብራሂም ጋር ከመነሻቸዉ እስከ ጅቡቲ /ተጆራ/ ድረስ አብረው ተጉዘዋል፡፡ ሀሰን ባህሩን ሲሻገር ከኢብራሂም ቀድሞ ነበር፤ ያኔ ተለያዩ፡፡ ግን ከሳዑዲ ፖሊሶች እጅ አላመለጡም፡፡
“ከየመን /ሃዱራ/ በተባለች ቦታ ድንበር በየበረሃው እያደርኩ ከአስር ቀን በኋላ ሳዑዲ ድንበር ደረስኩ፤ ወደ ሳዑዲ ስገባም የሳዑዲ ፖሊሶች ይዘውኝ ጊዛን ከተባለ እስር ቤት ለአንድ ወር ቆየሁኝ፡፡ ከዛም ከአንድ ወር በኋላ ልክ እንደ ቆሻሻ አውጥተው የመን ድንበር ላይ ጣሉን፡፡ አዲስ አበባ ባለው የከተማ አውቶቡስ ዓይነት፤ ሌሊት ሌሊት እየጫኑ ከከተማው አውጥተው ይጥሉን ነበር፡፡  
ሀሰን ስለ ሳዑዲ እስር ቤት ቆይታው እንዲህ ይላል፤ “እዚያ እስር ቤት ውስጥ ለሳዑዲ ፖሊሶች. . . ኢትዮጵያዊ ማለት ውሻ ማለት ነው፡፡ “…ያ ከልብ ያሃራሚ . . .” ብለው ነው የሚጠሩን፡፡ በእስር ቤቱ የሶማሊያ፣ የናይጀሪያ፣ የኢትዮጵያ ዜጐች ታጉረዋል፡፡ በአንዱ ክፍል እስከ ሰማኒያ ሰው ነው የታሰረው፡፡ ግን  ኢትዮጵያዊ ያበዛል፡፡  
ጣሪያው ድንጋይ ነው፤ በሩ ጠንካራ ብረት ነው፣ ሽንት ቤቱ በክፍላችን ውስጥ ነው አየር አናገኝም ነበር፤ ሙቀቱ በጣም ያቃጥላል፤ በካርቱን  ፊታችንን እናራግባለን፡፡ በየቀኑ ከየክፍሉ አራት ሰው ይሞታል - በአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ሬሳው ተነስቶ ማቀዝቀዣ ፍሪጅ ውስጥ እስከ ስድስት ወር ሳይቀበር ይቆያል” ሀሰን ሲናገር ፊቱ ይንቀጠቀጣል፡፡ “እስር ቤቱ ውስጥ በጣም  የሚዘገንነኝ፤ በክፍላችን ውስጥ የነበረው የሽንት ቤት ሽታ ነው፡፡ ሌሊት ስንተኛ ሞልቶ ስለሚፈስ . . . በመኝታችን ስር ይመጣል” ዘገነነው፤ ንግግሩን አቁሞ . . .”አየሽው አንገቴን? አሁን ጠባሳ ሆኗል፡፡ በሽንት ቤቱ ቆሻሻ ምክንያት ይሄ ሁሉ አባብጦ አንገቴና ፊቴን መለየት አይቻልም ነበር፤ ከሞት ነው የተረፍኩት፡፡
“አመመኝ ቆረጠኝ ለሳዑዲ ፖሊስ ፌዝ ነው፡፡ አትምጡብን ውሾች ይሉናል፡፡ ተይኝ…ማስታወስ አልፈልግም፡፡ ከአሁን በኋላ ስደትን አላስበውም፡፡ በቃኝ ሞቴን በሃገሬ!! ስለ ስደት በተስፋ የሚያወራ ብዙ አለ፤ ተይው . . .  ተይው ስለማያውቅ ነው . . በወንዶችማ የሚደርሰውን ግፍ . . አልነግርሽም . . . ተይው”
የ76 ዓመቱ አዛውንት አቶ መሃመድ አለሙ፤ የሃያ ሁለት ዓመት ልጃቸው የአህመዱን ታሪክ ማውራት እንደጀመሩ መቀጠል አልቻሉም፤ ሲያወሩ ከእንባቸው ጅረት ጋር የለቅሶ ሲቃቸው እያቋረጣቸው፡፡ አላስታመሙት ነገር… “አይድንም” ብለው ሞቱን አይጠብቁ፤አፈር ቆፍረው አልቀበሩት ነገር . .. ሰቀቀን ብቻ! “ልጄ በህይወት እያለ በጫት ንግዱ ነበር የሚተዳደረው፡፡ ሆኖም ከቀን ቀን የኑሮ መሻሻል ስላላየ፤ ኪሳራ ሲገጥመው እንደ ጓደኞቹ ባህር መሻገርን መረጠ፡፡ በመጀመሪያው ጉዞ ባህር ተሻግሮ በየመን ፖሊሶች ተይዞ መጣ፡፡  ለሁለተኛ ጊዜ መሄድ አለብኝ ብሎ ሲዘገጃጅ በመሃል የጋብቻ ኒካ አሰረ፡፡ ለትንሽ ጊዜ እዚሁ ቆየልኝ፡፡ ግን የመሄድ ሃሳቡን አልቀየረም፡፡ ከሚስቱ ጋር ተያይዘው መሄድ ፈለጉ፡፡ የወለዷትን ሴት ልጅ፤ የሚስቱ ቤተሰቦች ጋ አስቀምጠው ነው ጉዞ የጀመሩት፡፡ ምን ያደርጋል? የአላህ ነገር ሆነና በባህር ሲጓዙ አብረውት ከነበሩት ሰላሳ ሰዎች ጋር ውሃ በላው” በቁጭት ተንገበገቡ፤ በያዙት ምርኩዝ መሬቱን ይደበድባሉ፡፡ አይናቸው እንባ ያዘንባል፡፡ “እኔማ መቸ አይቼው . . . እዚያው የነበሩና አይተናል የሚሉ ሰዎች ናቸው ታሪኩን የነገሩኝ፡፡” . . . ጀልባው ሲገለበጥ ሚስቱን ለማትረፍ፤ አይዞሽ እያለ እየገፋ ዳር አደረሳት፤ እሷን ለማዳን ሲታገል ድንገት የባህሩ ማዕበል መጥቶ አለበሰው፡፡ እሷ ዳነች፡፡ የተቀሩት አለቁ፡፡ እንዴት ያለ ቁራንን ሁለት ጊዜ የቀራ ቃልቻ ነበር፡፡ እስኪ ተውኝ አታንሱብኝ” እንደአመሻሸ ብርሃን የደበዘዘ አይናቸውን ወዲህ ወዲያ ያንከራትታሉ፡፡ የስሙ ማስጠሪያ አንድ ልጅ ጥሎልኝ ሄደ፤ ያ ሰላም!! የልጄ ባህሪ እንዴት ያለ መሰለሽ” . . . ቤቱ እንደ አዲስ የለቅሶ ቤት መሰለ፡፡  አቶ መሃመድ በህይወት ያሉ ሁለት ልጆቻቸው ባህር አቋርጠው የመሄድ ሃሳብ እንዳይኖራቸው እንደ ገዘቷቸው ይናገራሉ፡፡ “ልጆች በዚህ አሰቃቂ መንገድ እንዲሰደዱ የሚፈቅድ ወላጅ፤ ሂዱና ሙቱልን የማለት ያህል ነው” ይላሉ፡፡  
በመርዶ ነጋሪ ተነግሯቸው የልጃቸውን ሞት አምነው ሳያምኑ የተቀመጡት አቶ መሐመድ፤ ከስደት የሚመለስ ሰው ሲያጋጥማቸው ስለ ልጃቸው ሳይጠይቁ አያልፉትም “ልጄን አይተኸው ከሆነ . . .  በየመን በሳዑዲ እስር ቤት በጭንቅ ካለ ጠቁመኝ” ይላሉ - ራሳቸው ተጨንቀው፡፡  
ወ/ሮ መርየም ሁሴን የሰባተኛ ክፍል ልጃቸውን ያሳደጓት ጥራጥሬ በመሸጥ ነበር፡፡  ኑሯቸው ከእጅ ወደ አፍ ነው፡፡ ልጃቸው በረሃ ለበረሃ ሄዳ፤ የኤደን ባህረ ሰላጤን አቋርጣ የመን ለመግባት ስትነሳም በቀላሉ ገንዘብ አላገኙም፡፡ “የመጓጓዣ ገንዘብ ከዚያም ከዚህም ለቃቅሜ አንዱ ሺ ብር ሰጠኋት” ይላሉ፡፡ “የኑሮ ጫናው የማይገፋ ሆነ፤ አንድ ልጅ የወለደችለት ባሏም ወደ የመን ሄዶ ነበር፤  የባህር መሸጋገሪያ ብሎ 1ሺ ብር ላከላትና ጨማምራ ሄደች” ስቅስቅ ብለው ያለቅሳሉ፡፡ በየደረሱበት ቦታ በሰበብ በአስባቡ የልጃቸውን ስም እያነሱ የሚያለቅሱት ወ/ሮ መርየም፤ በፀፀት አንገታቸውን ደፍተው ከእንባቸው ጋር ትንቅንቅ ተያያዙ፡፡ - “ውሃ የበላት ልጄ . . . ውሃ የበላት …18 ሆነው ሲሄዱ ነው ጀልባው የሰጠመው፡፡ የልጄን ሞት መርዶ ባሏ ደውሎ ነገረኝ፡፡ በዚህ አካባቢ ልጆቻቸውን በበረሃና በውሃ ያልተነጠቁ ቤተሰቦች የሉም ማለት ይቻላል፡፡ ጨፋ ሮቢትን ለሞትና ለመርዶ የማታንቀላፋ መንደር ይሏታል - ነዋሪዎቿ፡፡ በቤተሰብ ፍቃድም ሆነ ከቤተሰብ በመሰወር በርካታ ወጣቶችና ታዳጊዎች በህገወጥ መንገድ ባህር ተሻግረው የሚጓዙ ሲሆን በየትምህርት ቤቱም በቡድንና በግል እየተደራጁ ለስደት ጉዞ መነሳት የተለመደ እየሆነ መምጣቱን ሰምተናል፡፡
መሃመድ አሊ የኪችቾ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር ነው፡፡ አካባቢው ሰውም ሆነ ተማሪው (የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቆ ወደ ሁለተኛ ደረጃም) የደረሰው ዩኒቨርሲቲ ገብቶ ትምህርት የመዝለቅ ሃሳብ የለውም፡፡ ነገ አስተማሪ ወይም ሃኪም እሆናለሁ፤ የሚል አንድም ተማሪ አታገኝም ስልሽ ያለማጋነን ነው፤ የ15 ዓመቱ(ቷን) ልጅ ህልማችሁ ምንድነው ስትያቸው፤ ወደ ሳዑዲ ሄጄ ሥራ ሰርቼ፤ አስተማማኝ የመኖሪያ ገንዘብ ይዤ መምጣት ነው ይሉሻል፡፡ አገራዊ ህልም ያለው ተማሪ አታገኚም፡፡” ይላል፤ በቁጭት፡፡  
የወጣቶቹ ልብ ለስደት የሸፈተበትን ምክንያት ሲናገርም የአስኮብላዮች (ደላሎች) ስብከት ዋነኛው እንደሆነ የሚናገረው መምህሩ፤ ወላጆችም ልጆቻቸው ባህር እንዲሻገሩ ይገፋፋሉ ይላል፡፡ ወላጆች ሴት ከወለዱ “የቻይና ወፍጮ ተክያለሁ” ይላሉ የሚለው መምህር መሃመድ አሊ፤ ይሄም ሴት ልጆች አረብ አገር ሄደው በመስራት የሚልኩላቸውን ገንዘብ ለመጠቆም እንደሆነ ይናገራል፡፡ ጉዳዩ የከፋና ስር የሰደደ መሆኑን ሲገልፅም ልጁን ባህር አሻግሮ የሚመለስ ወላጅና፤ ተሰባስቦ የሚጓዝ ቤተሰብ እንዳጋጠመው ያወሳል፡፡ በዚሁ ሰሞን ከአንድ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ከአስረኛ ክፍል ሃያ ተማሪዎች፤ ከአንዱ ጐጥ ዘጠና ወጣቶች ወደ አረብ አገር መጓዛቸውን የጠቆመው መምህሩ፣ ህብረተሰቡ ስደትን በነቂስ ተያይዞታል ይላል፡፡  
“ተማሪዉ ብቻ እንዳይመስልሽ . . . ዲፕሎማ ኖሮት በመንግስት ደመወዝ እየተዳደረ የደሞዙ ማነስና የኑሮ ውድነቱ በፈጠረው ጫና የተነሳ መምህራኖችም የተማሪዎቻቸውን ዱካ ተከትለው እየተሰደዱ ነው፡፡ ተማሪዎቻቸው ደውለው “ጋሼ በዚህ ደሞዝ  ከምትሠራ ወጥተህ ብትለወጥ ይሻልሃል” ሲሏቸው ተቀብለው ወደ አረብ አገራት እየተጓዙ ነው” ብሏል - መምህሩ፡፡
መምህር መሀመድ አሊም ግን የበረሃንና የባህርን ጉዞ ያውቀዋል፤ ሳዑዲ ሁለት ዓመት ተኩል ሰርቶ ተመልሷል፡፡ “ስደት ክብር የሚዋረድበትና ርካሽ የምትሆኝበት መላ የሌለው ነገር ነው፤ በመጨረሻ ግን አገሬ ገብቼ በዲፕሎማ ተመረቅሁና መምህር ሆንኩ” የሚለው መሃመድ፤ ለተማሪውም ላስተማሪውም ይህን አካሄድ በመንቀፍ ብዙ ጊዜ ምክር እንደሚሰጣቸው ይናገራል፡፡ መንግስትና የሚመለከተው አካል የችግሩን አስከፊነት በመረዳት ዜጎቹን ከከፋ አደጋ እንዲጠብቅም አሳስቧል፡፡ ወጣት  ተማሪዎችንም ሆነ መምህራኖቻቸውን በህገ ወጥ መንገድ ባህር የሚያሻግሩትና የሚያዘዋውሩት ህገወጥ አዘዋዋሪዎች ወይም ደላሎች መሆናቸው ይታወቃል፡፡ አዘዋዋሪዎቹ በአካባቢው ሰንሰለት ሰርተው ከመነሻ እስከ መድረሻ የመንና ሳዑዲ ድረስ እንደሚንቀሳቀሱ የሚናገሩት ኢንስፔክተሩ አብዱ አንዱሪስ፤ በአሁኑ ሰዓት ሰዎችን በህገወጥ መንገድ በማዘዋወር ተጠርጥሮና ቅድመ ምርመራ ተደርጎበት የተያዘን ግለሰብ ለማስቀጣት የህግ ክፍተት መኖሩን ይገልፃሉ፡፡
“ከአንዱ መንደር ከአስር እስከ አስራ አምስት ሆነው ሰዎች ይንቀሳቀሳሉ፤ ግን ድንበር ስላልሆነ ወዴት ነው የምትሄዱት ለማለት ይቸግራል፤ ነገር ግን ሲታዩ ተጓዥ ስለሚመስሉ . . . የት እየሄዳችሁ ነው፤ ማን ነው የሚወስዳችሁ ብለን ስንጠይቃቸው እውነቱን አይናገሩም፡፡ ምክንያቱም ገንዘብ የከፈሉት ግለሰብ በርቀት እየተከታተላቸው ወይም እየመራቸው ይሆናል፡፡ ግን እንዲያዝ አይፈልጉም፡፡ እጅ ከፍንጅ ተጠርጥሮ - በማዘዋወር የተያዘውን ግለሰብ ፍ/ቤት አቅርበነው ምርመራ ከተደረገበት በኋላ እዛው እናስመሰክራለን፤ መዝገቡን ወደ ክልል ልከን እስኪታይ ፍ/ቤት የዋስትና መብት አይከለክልም፡፡ ሰውዬው ቃሉን ከሰጠ በኋላ በ7ሺ ብር ዋስ ይለቀቃል፡፡ 7ሺ ብር ግን ለእነሱ ምንም ማለት አይደለም፡፡ በቀጠሮ ቀን ሰውየው ይጠፋል፤ ገንዘቡ ለመንግስት ገቢ ይሆንና “ሰውየው ባለበት ይያዝ” ይባላል ብለዋል - ኢንስፔክተሩ - ስለፍርድ ሂደቱ ሲናገሩ፡፡  
ክልሉን የሚወክል አቃቤ ህግ ያለመኖሩም ፍርዱን ያዘገየዋል ያሉት ኢንስፔክተሩ፤ የፖሊስ አካላትም በህገወጥ ዝውውሩ ተባባሪ ሆነው እንደተገኙና ከስራ የተባረሩ እንዲሁም ከፍተኛ ቅጣት የተጣለባቸው እንዳሉም ጠቁመዋል፡፡

 

Read 5739 times Last modified on Saturday, 08 October 2011 13:14