Print this page
Saturday, 01 October 2011 12:56

ቪዛን በምርኩዝ

Written by  ከጌታሁን ሽፈራው
Rate this item
(0 votes)

ሀይመን ሱሌይማንና ኦሊቨር ትዊስት ውልደትና እድገታቸው ይመሳሰላል፡፡ በተለይ ውልደታቸው፡፡
ታላቁ እንግሊዛዊ ፀሐፊ ቻርልስ ዲከንስ “ኦሊቨር ትዊስት” በሚለው መጽሐፉ የኦሊቨርን ውልደት ሲገልጽ እንዲህ ብሎ ነበር የፃፈው |When He Was Born Oliver Cried As The New Comer Baby Did. If He Had Known He Was An Orphan He Would Cry Alot And Alot...
(ኦሊቨር ትዊስት ሲወለድ ማንኛቸውም ህፃናት ሲወለዱ እንደሚያለቅሱት ሁሉ እርሱም አለቀሰ፡፡ ወላጅ አልባ (የሙት ልጅ) መሆኑን ቢያውቀው ኖሮ ደግሞ የበለጠ እሪ ብሎ ያለቅስ ነበር እንደማለት ነው)
ሀይመንም አባቱ እርሱ ከመወለዱ ከአምስት ወራት በፊት በድንገተኛ አደጋ ሞተ፡፡ እናቱ ደግሞ ልክ እርሱን እንደወለደች ህይወቷ አለፈ፡፡

ሀይመን በአጐቱ እጅ እዚያው ሶማሌ ውስጥ እስከ 18 ዓመቱ ድረስ እየተማረ አደገ፡፡ አጐቱ በኮንትሮባንድ ንግድ ላይ በመሰማራቱ ይህንን እያየ ያደገው ሀይመን፤ የኮንትሮባንድ ንግድን እንደ ህጋዊ ሥራ እየቆጠረ ነበር ለአቅመ አዳምነት የደረሰው፡፡
አጐቱ ከሞተ በኋላ ሀይመንም ይበልጡኑ በህገወጥ ንግድና በኮንትሮባንድ ዝውውር በመዘፈቁ የተዘረፉ መኪናዎችን ወደ ኢትዮጵያ ምድር በአርቺቴክና በሌሎችም ኬላዎች ጥሶ በማስገባት ትልቁን ድርሻ አበርክቷል፡፡ በዚህ ሙያው ይበልጡኑ እንዲገፋ ያደረገው ደግሞ በዚያድ ባሬ መንግስትና በተቃዋሚ ሸማቂዎች መካከል ውጊያው እየከፋ የሶማሊያ ከተሞችም ህግ አልባ እየሆኑ መምጣታቸው ነበር፡፡  ኋላ ላይ ግን ሸማቂዎች ከተማዋን ሲቆጣጠሩ፣ እርሱም በሸማቂዎች አደን ውስጥ በመግባቱና በጥይት በመቁሰሉ ህይወቱ አደጋ ላይ ወደቀ፡፡ እናም ስደት ቤቱን ኢትዮጵያ ውስጥ ለማድረግ ተገደደ፡፡
ወደ ኢትዮጵያም ከመጣ በኋላ ደሙ ውስጥ የገባው ወንጀል ከነፍሱ ጋር በመቆራኘቱ በህገወጥ ስራዎች ውስጥ መሳተፉን ገፋበት፡፡ የዘወትር ተግባሩም አደጋን እየተጋፈጠ ማለፍ ሆነ፡፡ ምንም እንኳን በርካታ ብሮችን ቢያገኝም እጁ ወንፊት በመሆኑ ገንዘብ አይበረክትለትም ነበር፡፡ ዛሬ ባለ 4 ኮከብ ሆቴል ካደረ፣ በማግስቱ ተራና መናኛ ሆቴል ገብቶ ያድራል፡፡ ወዳጆቹ ‹ለነገህ አታስብም ወይ› ብለው ሲጠይቁት ‹ለነገዬ አላህ ያውቃል› ነው መልሱ፡፡
ሲኒማ ሲመለከት በተመስጦ ነው፤ ከልቡ ይወዳል፡፡ አንዳንዴ ከሲኒማ የቀሰመውን ትምህርት በገሀዱ ዓለም ለመተግበር ሲጣጣር ይታያል፡፡
ሀይመን ነጐድጓዳማ ድምጽ ሲኖረው ከፈጣን የንግግር ክህሎቱ፣ ከረጅም ቁመናውና ከአስፈሪው ግርማሞገሱ ጋር ተዳምሮ፣ ተደማጭነትና ታማኝነት እንዲያተርፍ ሲያስችሉት ውሸትን አቀናብሮ ሲናገር ሰውን በቀላሉ ማሳመን ከመቻሉ ሌላ የማይሞከሩና የማይደፈሩ ነገሮችን ሲያሳካና ለውጤት ሲያበቃ መታየቱ፣ ብዙዎቹን ያስደመሙ ችሎታዎቹ ሲሆኑ ሃይመን THE MAGICIAN (አስማተኛው) ለሚል ቅጽል ስም አብቅቶታል፡፡
ሀይመን ከሰባት ዓመት በፊት በተጭበረበረ ዶክመንት  ከአዲስ አበባ ወደ አሜሪካ ገብቶ ነበር፡፡ በመጨረሻው የአዲስ አበባ ቆይታው፣ ብር ጨርሶ ስለነበር ዛሬ ግን ሀይመን የበደላቸውን ክሶ፣ ልብ ገዝቶና ቁምነገረኛ ሆኖ፣ ባለቤቱንና የ10 ዓመት ወንድ ልጁን ወደ አሜሪካን ለመውሰድ ነው ወደ አዲስ አበባ የመጣው፡፡
በአሜሪካ ሰባት የስደት ዓመት ቆይታው ለአሜሪካን ፍርድ ቤቶች ያቀረባቸው ሰነዶችና አሳማኝ ምክንያቶቹ ተቀባይነት በማግኘታቸው፣ ሚስቱና ልጁ በስደት ከሚገኙበት የአዲስ አበባው  አሜሪካ ኤምባሲ ፎርም በጥንቃቄ ከሞላ በኋላ፣ የጋብቻና የልደት ሰርቲፊኬት አያይዞና የቪዛ መጠየቂያ ቅጽ ሞልቶ  ዛሬ ለቪዛ የተቀጠረበት ቀን ነበር፡፡
አሁን ሁሉን ነገር በጥንቃቄ እንዳከናወነ ተሰምቶታል፡፡ የሚቀረው ነገር ቢኖር ፈርሃን ልጁ መሆኑ የሚረጋገጥበት የDNA ናሙና ምርመራ ውጤት ብቻ ነበር፡፡
ልቡ በሃሴት እንደተሞላ የቪዛውን ውጤት ለመስማት ከኤምባሲው ቅጥር ግቢ ገባ፡፡ ከረጅም ቁመናው ጋር የሚስማማ ጥቁር ሰማያዊ ኮተሸሚዝና ሱሪ የለበሰው ሀይመን፤ ከቀርከሃ የተሰራ ከዘራ ይዟል፡፡ ሦስት ማዕዘን ያለው የፊቱ ቅርጽ ከሰልካካው አፍንጫው ጋር በጐን በኩል ሲታይ ፊቱን ይበልጡኑ ስለታማ ያስመስለዋል፡፡ በምርኩዙ እየተመራ የሚሳሳበው አካሄዱ የተመልካችን ቀልብ ይስባል፡፡
ምንም እንኳን ሀይመን የልጁንና የሚስቱን ቪዛ ያለጥርጥር እንደሚያገኝ እርግጠኛ ቢሆንም ባለቤቱ ዙቤይዳ ግን ልቧ በጥርጣሬና በስጋት እየደለቀ ነበር ከኤምባሲው ግቢ የደረሰችው፡፡ ፀጉርዋን ጉንጉን ቆልላውና በሻሽ ጠቅልላ በላዩ ላይ ሒጃብ አስራ፣  አብረቅራቂ ህብር ያለበት ድሪያ ለብሳ ተውባለች፡፡
ሀይመን ከቪዛ መጠየቂያ ክፍል እንደገባ ልጁንና ባለቤቱን መጠባበቂያ ወንበር ላይ አስቀምጦ፣ በረጅም መስታወት በተከለለ የቪዛ መጠየቂያ ክፍል የሚሰሩ የቪዛ ማዕከል ሰራተኞች የተቀጠረበትን የቀጠሮ መጠየቂያ ወረቀት፣ ከመሰል ዶክመንቶቹ ጋር አያይዞ አቀረበ፡፡
የቪዛ ማዕከል ሰራተኛው ከተራ መጠበቂያ ወንበሩ ላይ ሆኖ ተራውን እንዲጠብቅ ትዕዛዝ ሰጠው፡፡
ተራቸው እንደደረሰ ሃይመን ተጠርቶ ወደ ውስጥ ገባ፡፡
የቪዛ ክፍል ሃላፊው፤ የሀይመን ልጅና ባለቤት ዶሴን ከፊት ለፊቱ ካለው ጠረጴዛ ላይ ዘርግቶ እያገለባበጠ ከተመለከተው በኋላ ቀና ብለው ወደ ሀይመን ተመለከቱና “ሚስተር ሃይመን ለመሆኑ ወደዚህ የመጣህበትን ምክንያት በትክክል ታውቀዋለህ?” ሲሉ ቀዝቀዝ ባለ አስተያየት እየተመለከቱት ጥያቄ አቀረቡለት፡፡
“ማለት... ለልጄና ለባለቤቴ ባመለከትኩት የቪዛ መጠየቂያ መሰረት በቀጠሮዬ ቀን ነው የመጣሁት፡፡ ሲል  ግራ መጋባት  እየታየበት ለጥያቄው መልስ ሰጠ፡፡
“ይህን የቪዛ መጠየቂያ ስታስገባም ሆነ የአሜሪካን ፍርድ ቤቶች ለማሳመንና ልጅና ባለቤትህን ለመውሰድ የተጠቀምካቸው ስልቶች እጅግ አሳማኝና ጥንቃቄ የተሞላባቸው እንደሆኑ ለመገንዘብ ችያለሁ፡፡ ነገር ግን አሉና ለአፍታ ፀጥ አሉ፡፡
ሀይመን፤ የቪዛ ክፍል ሃላፊው ነገር ግን ማለታቸውን አልወደደውም፡፡ በአንድ ወቅት በማጭበርበር ወንጀል ተከሶ፣ ዳኛው “ስደተኛ ነህ ሪከርድ የለብህም” ካሉ በኋላ “ነገር ግን” ብለው እንደተለወጡበት ታወሰው፡፡ ነገር ግን ማለት አፍራሽና መጥፎ ነገር ይዞ የሚመጣ ቃል እንደሆነ ማመን ከጀመረ ቆይቷል፡፡ አሁን እኚህ ሃላፊም ነገር ግን     የሚል ቃል ስለተጠቀሙ በጐውን ነገር ሊያፈርሱት እንደሆነ ጠረጠረ፡፡
“ነገር ግን ከዚያ ጋር የሚጣረስ የጅል ስራ እዚህ ጋር መስራትህ አስደንቆኛል፡፡ ለመሆኑ ይህንን የቪዛ ማመልከቻ ስታስገባ ባንተና ልጄ በምትለው መካከል የDNA ምርመራ እንደሚደረግስ ታውቅ ነበር?
“በሚገባ” በማለት ሀይመን ፍርጥም ብሎ ተናገረ፡፡
“እና ታዲያ ይህን እያወቅ” የጅል ስራ እየሰራህ ለምን ጊዜህን አባከንክ?”
“የሚሉት ነገር አልገባኝም”
“ፈርሃን የወለድከው የአብራክህ ልጅ እንዳልሆነ እያወቅህ ለምን ጊዜህን ማባከን አስፈለገህ”
“ፈርሃን ልጅህ አይደለም ለማለት ፈልገው ነው? ይሄ ፈጽሞ የማይመስል ነገር ነው፡፡ እንዴት ይህንን ታላቅ ነገር በማታለል እራሴን የማሞኝ ይመስሎታል?´
“እኔም የገረመኝ ይሄው ነው፡፡ ያንተ ዓይነት አስተሳሰብ ያላቸው የቪዛ አመልካቾች አልፎ አልፎ ይከሰታሉ፡፡ ሀቁ ግን ፈርሃን ልጅህ ሳይሆን በገንዘብ አልያም በዝምድናና ጥቅማ ጥቅም የመጣ ልጅ መሆኑን የ DNA የምርመራ ውጤቱ ይመሰክራል፡፡ ስለዚህ ወደ አሜሪካን ኤምባሲ ቪዛ ለመጠየቅ ስትመጣ እውነተኛ በመሆን፤ የተጨበጠና ተዓማኒነት ያለው ነገር ይዘህ ለመምጣት ብትሞክር የተሻለ ነው፡፡ የተሳሳተ አካሄድ መከተልህ ባንተም የመኖሪያ ፈቃድ ላይ ሌላ ጥያቄ ሊያስከትል ይችላል፡፡ ስለሆነም ትክክለኛ በሆነ መንገድ ቪዛ የመጠየቅ የወደፊት መብትህ የተጠበቀ ነው፡፡ ወደ አሜሪካ ለመግባት ቪዛ ከሚያስከለክሉ አብዛኛዎቹ እዚህ ወረቀት ውስጥ ሰፍረዋል፡፡” አሉና ሃሳባቸውን እንደመቋጨት ብለው አንድ በወረቀት ላይ የሰፈረ ዝርዝር መረጃ አውጥተው እየሰጡት ይበልጡኑ ወደ ሃይመን ተመለከቱ፡፡
ሃይመን ፊቱ በንዴት ተለዋውጦ፣ ቁና ቁና እየተነፈሰ ምርኩዙን በአገጩ እንደተደገፈ፣ በአግራሞትና በድንጋጤ ዓይኑን እያጉረጠረጠ አንገቱን ወደ ቪዛ ክፍል ሃላፊው የበለጠ ሲያሰግግ ተመለከቱትና “ምን እየሆንክ ነው ለነገሩ አዲስ የሆንክ ይመስል የተበሳጨህና ግራ የተጋባህ ትመስላለህ” ሲሉ በመገረም ጠየቁት፡፡
‹ፈርሃን ያንተ ልጅ አይደለም እያሉኝ እንዴት አልገረም? ይህ ፈጽሞ የማይታመንና የማይገመት ነው፡፡ ልጄ ሲወለድ ሆስፒታል ውስጥ ተለወጠ ወይስ ሚስቴ ከሌላ ወንድ አምጥታው ነው ለመሆኑ ይህ የ DNA  ምርመራ ውጤት ምን ያህል ፐርሰንት በሳይንስ ተቀባይነት አለው?” ሲል መላ ሰውነቱ በንዴት እየተርገፈገፈ ጠየቀ፡፡
በሁኔታው ግራ የተጋቡት ሚስተር ሃዋርድ “ይህ የኛ ጉዳይ አይደለም፤ ሀቁን የምታውቁት አንተና ባለቤትህ ብቻ ናችሁ፡፡ እኛ የምናውቀው የ DNA  የምርመራ ሳይንስ የዘር መረጃን የያዘ ንጥረ ነገር ሲሆን ዲኦክሲሪ ባውኑክሊክ የተባለ አሲድ ሲሆን መቶ በመቶ ተጨባጭ ሀቅ መሆኑን ብቻ ነው፡፡ ሌሎች ባለጉዳዮች ስላሉብን ጊዜያችንን ባታባክን ጥሩ ነው፡፡ እንዲያውም ባለቤቴ ናት ላልካትም ሴት ያቀረብከውን የቪዛ ጥያቄ ሌላ ተጨማሪ ማጣሪያ ውስጥ እንድንገባ አታስገደድን፡፡” አሉ የቪዛ ክፍል ሃላፊው ሚስተር ሃዋርድ፤ ትዕግስታቸው ያለቀ በሚመስል አኳኋን፡፡
በዚህ ጊዜ ሃይመን እመር ብሎ ተነሳና እየጮኸ የተራ መጠባበቂያ ወንበሩ ላይ ተቀምጠው ወደነበሩት ሚስትና ልጁ አመራ፡፡ በአካባቢው ያሉት የቪዛ አመልካቾችና የቪዛ ክፍል ሰራተኞች በሀይመን ጩኸትና ጠቅላላ ሁኔታ ቀልባቸው ተስቦ እያስተዋሉት ነበር፡፡
በዚህ ቅጽበት ሃይመን በአንድ እጁ የባለቤቱን ሻሽ ከነፀጉርዋ ጠቀለለና ጠምዝዞ ከጣላት በኋላ በያዘው ከዘራ ጭንቅላቷን መቀጥቀጥ ጀመረ፡፡ ህፃኑ ፈርሃን በጩኸት እየሮጠ “እናቴን ገደላት” እያለ እሪታውን አቀለጠው፡፡
በአካባቢው የነበሩ ሰዎችና የቪዛ ክፍል ሰራተኞች በሃይመን ላይ መረባረብ ጀመሩ፡፡ አንዳንድ ሰራተኞችም የፀጥታ ጥበቃ ሰራተኞችን በጥድፊያ እንዲመጡ ደወሉን በመጫን ጥሪ አደረጉ፡፡ ሃይመን  ለገላጋይ እያስቸገረ ድምፁን ከፍ አድርጐ “ባለቤቴ ናት ብዬ አምኜ፣ ልጄ ነው ብዬ ተቀብዬ ከ10 ዓመታት በላይ አታለለችኝ፡፡ በስደት ከምኖርበት ሀገር ባለቤቴና ልጄ ብዬ ስጃጃል ከረምኩኝ አሁን ግን ክህደቷን ደረስኩበት የመጣው ይምጣ እንጂ የትም ትግባ  እርሷን ገድዬ እጄን ለመንግስት እሰጣለሁ፤ ከዚህ ወዲያ ምን ቀሪ ነገር አለኝ” እያለ አዳራሹን ቀወጠው፡፡
ዘቤይዳም ከወደቀችበት ሆና “አድኑኝ ይገለኛል፤ ጨካኝ ነው” እያለች ጮኸች፡፡
ፈርሃንም “አባዬ ምን አገኘህ ምን ብለውህ ነው?” እያለ ሲያለቅስ የሦስቱም ጩኸትና አምባጓሮ አዳራሹን አልፎ ከደጅ ይሰማ ነበር፡፡ ወዲያውኑ ግን የፀጥታ አስከባሪዎች ዘቤይዳን አንስተው ሃይመንን አፋፍሰው በመውሰድ በአንዲት አነስተኛ ክፍል ውስጥ ሲዘጋበት ዘቤይዳና ፈርሃን እንዲረጋጉ ከተደረገ በኋላ ዙቤይዳ የቪዛ ክፍል ሃላፊው ቢሮ ተጠርታ ገባች፡፡
የቪዛ ክፍል ሃላፊው ሚስተር ሃዋርድ በጽሞና ካስተዋሏት በኋላ “ጉዳት ተሰምቶሽ ከሆነ ህክምና ታደርጊያለሽ” ሲሉ ጠየቋት፡፡
“አይ ደህና፤ ጭንቅላቴን ነው የመታኝ ፀጉሬ ባይከላከልልኝ ኖሮ ገሎኝ ነበር፡፡ አሁን ትንሽ ደህና ነኝ” በማለት መለሰች፡፡
“እስቲ በጋብቻችሁ መካከል ስለነበረው ክፍተትና ስለፀባችሁ መንስኤ ከመጀመሪያው አንስቶ ምንም ሳትደብቂኝ ግለጪልኝ፤ አጠር አድርገሽ… ምናልባት የተከሰተው ችግር አሳማኝ ከሆነ ችግሩን ለመፍታት ፈቃደኛ ነኝ”
ዙቤይዳ ለአፍታ ያህል ከየት መጀመር እንዳለባት ስታሰላስል ከቆየች በኋላ “ጥሩ” አለችና ጉሮሮዋን ጠራርጋ፤ “በኔና በሀይመን መካከል ምንም አይነት ያለመተማመን ችግር የለም፤ ዳሩ ግን በሰሜን ሶማሊያ አብረን በፍቅር በምንኖርበት ወቅት የአሜሪካ ሰላም አስከባሪ ሀይል በርስ በርስ ጦርነት በምትታመሰው ሶማሊያ ከገቡ በኋላ፤ ሀይመን ከአሜሪካ ሰላም ሀይሎች ጋር ይግባባ የነበር ሲሆን የምዕራባዊያንን አስተሳሰብ የሚደግፍ አቋም አልፎ አልፎ ይታይበት ነበር፡፡ ስለሆነም የፋራሀይዲድ ደጋፊዎች ጥርሳቸውን ሲነክሱበት በመቆየታቸው አመቺ ወቅት ጠብቀው ሊገድሉት ሞከሩና አቁስለውት አመለጣቸው፡፡ ከኔ ጋር ግንኙነት እንዳለው ስለሚያውቁ አንድ ምሽት አድብተው ሲመጡ ደብቄ አስመለጥኩት፡፡ ይህንን ስላወቁ በዚህ የተነሳ አንድ በቅርብ የማውቀው ጐረቤቴ፣ የፋራሀይዲድ ደጋፊ ታጣቂ ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ቤቴን ሰብረው ገብተው፣ እርሱን በማጣታቸው ይሄው ግለሰብ አስገድዶ ደፈረኝ፤ ከዚያ በኋላ ህይወታችን አደጋ ላይ በመውደቁ ወደ ኢትዮጵያ ተሰደድን፤ ነገር ግን የኔን ተገድዶ መደፈር ለሀይመን ከመናገር ተቆጠብኩ፡፡ ምክንያቱም ሃይመን እልኸኛና ሀይለኛ በመሆኑ፣ ይህንን ከሰማ ጊዜ ጠብቆና አድፍጦ እኔን የደፈረውን ሰው ከመግደል ወደ ኋላ እንደማይል ስላወቅኩኝና በዚህ የተነሳ ደግሞ ጥቂት ብንቆይና ስህተት ቢፈጠር ሊገድሉት ስለሚችሉ ነገሩን ሳልነግረው ቀረሁ፡፡ ከዚያም ስደት ወደ አዲስ አበባ ሆነ፤ ጥቂት ቆየና ማርገዜን አወቅሁ፡፡ ሆኖም ከሀይመን ይሆናል ብዬ ስላሰብኩ ብዙም አልተጨነኩም፡፡ ልጁ ሲወለድ ግን እየቆየ የደፈረኝን ሰው እየመሰለ ሲመጣ እኔም ጭንቀቴ እየባሰ መጣ፡፡ ቢሆንም ግን ሙሉ ለሙሉ እስከዛሬው ቀን ድረስ እርግጠኛ አልነበርኩም፡፡ ዛሬ ግን የ DNA  ውጤቱ ተነግሮት ተናዶ ሲመጣ የደበቅኩት ሀጢያቴ ስጋ ለብሶ እንደመጣ ታወቀኝ” አለችና ተንፈስ አለች፡፡
ሚስተር ሃዋርድ በጽሞና ካዳመጧት በኋላ በሀዘኔታ ጭንቅላታቸውን ነቀነቁና “እና አሁን መፍትሔው ምንድን ነው” ሲሉ ጠየቁ፡፡
“በምንም መልኩ ችግሩ አይፈታም፤ እርሱ ጨካኝና ቂመኛ ነው ሰዎች ሲዋሹት እንኳን ምህረት የለውም፡፡ እንኳን በትዳር መሃል ይቅርና፡፡” አለችና ሳግ ተናንቋት አለቀሰች፡፡
“የምንችለውን በማድረግ አንቺን ከአደጋ ለመታደግ ዝግጁ ነን” አሉ፡፡ በሀዘኔታ ዘቤይዳ ትንሽ በሀሳብ ቆዘመችና “ያለው አማራጭ አንድ ብቻ ነው፡፡ ይኸውም የ DNA ውጤቱ በስም መመሳሰል ስህተት የተሰራ መሆኑ ተነግሮን ይቅርታ በመጠየቅ ለኔና ለልጄ ቪዛ መስጠት ብቻ ነው፡፡ የሚያስቸግር ካልሆነ…” ስትል በሃዘንና ልመና መልክ ሃሳብ አቀረበች፡፡
ሚስተር ሃዋርድ “እኛ እውነት ብቻ ነው የምንፈልገው፤ ከመረጃ ጋጋታ ይልቅ እውነቱ ደግሞ እርሱ ባይወልደውም ልጄ ነው ብቻ ብሎ ማመኑ ለኛ በቂ ነው” ካሉ በኋላ ሀይመን እንዲጠራ አዘዙ፡፡
ከ10 ደቂቃ በኋላ ሃይመን ፊቱ እንደጠቆረ፣ በፀጥታ ሰዎች ታጅቦ ወደ ሚስተር ሃዋርድ ክፍል ገባ፡፡
ከ20 ደቂቃ በኋላ የጠቆረው ፊቱ በደስታ እንደፈካ ዙቤይዳን አቅፎ ይቅርታ እንድታደርግለት እያግባባት ወጣ፡፡
በአዳራሽ የነበሩት ሰዎች በአግራሞት የተፈፀመውን የተምታታ ትዕይንት በመንሾካሾክ ሲወያዩ ይስተዋሉ ነበር፡፡
ወዲያው ዙቤይዳና ፈርሃን ተጠርተው ወደ ውስጥ ከዘለቁ በኋላ ወደ አሜሪካን የሚያስገባ ቪዛ ተመትቶላቸው ወጡ፡፡ ሦስቱም ከአዳራሹ በፈገግታ እንደታጀቡ ግቢውን አቋርጠው ወደ ትልቁ ዋናው የግቢ በር እያመሩ ሳለ፤
“የኔ ፍቅር ጐዳሁሽ እንዴ?” ሲል ሀይመን ጠየቃት
“የመጀመሪያው ምርኩዝ ያረፈው ግንባሬ ላይ ስለነበር ተሰምቶኛል፤ በተረፈ ሆን ብዬ ፀጉሬን ወደ ላይ ቆልዬው ስለነበር ምርኩዙ ሁሉ ፀጉሬ ላይ ነበር ያረፈው” አለች ዙቤይዳ “አየሽ እነኚህ አሜሪካዊያንን ለማሳመን ያልተመደ ዘዴ መጠቀም አለብሽ፤ በሎጂክ ለሚያምኑ ቀድመሻቸው ካልተገኘሽ ርህራሄ የሚባል ነገር እነርሱ ጋ አይሰራም፡፡ ይሄን የቀርከሃ ምርኩዝ ውስጡ ባዶ እንደሆነ አያውቁም፤ በደንብ ፍቆ ለዚሁ ተግባር ስላሰራሁት ከባድ ዱላ ነው የመሰላቸው፡፡ እናም ማንም ሰው እነርሱን ለማሳመን ብሎ ይህንን እንደማያደርግ ቶሎ ይረዳሉ፡፡” አለና ሀይመን ወደ ትንሹ ፈርሃን ተመልክቶ ንግግሩን ቀጠለ፤ “አንተም በትክክል የተሰጠህን የትወና ሥራ ተወጥተኸዋል” አለው ፀጉሩን ዳበስ ዳበስ እያደረገው፡፡
“አጐቴ፤ ከዚህ በኋላ የቀረን ወደ አሜሪካ በረራ ብቻ ነው” በማለት ፈርሃን ጠየቀ፡፡
“ከዚህ ግቢ እስክንወጣ አባቴ ነው ማለት ያለብህ...በዚህ ግቢ ውስጥ እንደ እባብ ዓይን የሚሽከረከር ካሜራና ድምጽ የሚያነፈንፍ መሳሪያ ገጥመዋል” አለው ሀይመን ዝቅ ባለ ድምጽ፡፡
ፈርሃን በፍርሃት እንደመሸማቀቅ አለና “አባቴ አንተ እኮ ከዲኔሮና ከአልፓቺኖ የማይተናነስ የትወና ችሎታ አለህ” አለው፡፡ ቀጠለና “ባለፈው ጊዜ አብረን ያየነውን ፊልም አስታወስከው? የምርመራ ቢሮ መርማሪዎችን በሙሉ ሸውዶ ከእስር ቤት የወጣው አክተር?
“ኦ ኬቪን ስፔሲ ነው USUAL SUSPECT በተባለው ፊልም ላይ” አለ ሀይመን “አንተም እኮ እንደሱ ነው የሸወድካቸው” አለ ፈርሃን ለአጐቱ ያለውን አድናቆት በሚገልጽ ስሜት እያየው፡፡
በዚህን ጊዜ ሁሉም ከልባቸው እየሳቁ ስለነበር የኤምባሲው የመውጪያው በር  ላይ እንደደረሱ እንኳን ረስተውት ነበር፡፡

 

Read 4473 times Last modified on Saturday, 01 October 2011 13:06