Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 01 October 2011 12:40

ዋናው ችግር የነፃነት መታፈን ሳይሆን፤ ..የፈጠራ ችሎታ.. እጦት ነው

Written by 
Rate this item
(4 votes)

የፓርቲዎች ፉክክር፣ የተቃውሞ ሰልፍ፤ የነፃ ፕሬስ እድገት፤ የዜጎች ነፃ ውይይት ተረት ሆነዋል?
ባለፉት አመታት ነፃነት እየጠበበ፣ የመንግስት አላስፈላጊ የቁጥጥር አይነቶች እየተበራከቱ፤ የሚያሳርፉት ጫና እየከረረ መምጣቱ፤ በእውን ኑሯችን ምን እንደሚመስልና ምን  እንደሚል ማወቅ ይከብዳል? ሁሌም ከፖለቲካው ድባብ ጋር የሚፈካውንና የሚጠወልገውን ኢኮኖሚ በማየትም፤ የነፃነት መጥበብን መገንዘብ ይቻላል፡፡
ለነገሩማ፤ ነፃነት ሰፋ  እያለ ሲሄድ፤ ነቃ ከሚለው ኢኮኖሚ ጋር ተዳምሮ ምን እንደሚመስልም ከነጣእሙ... በትንሹም ቢሆን አንዳንዶቻችን እናውቀዋለን፡፡ ለአጭር ጊዜ ቢሆንም፤ የኋላ ኋላ መጨረሻው ባያምርም በእውን አይተነዋል - ያኔ ከአምስት አመታት በፊት፡፡ የ1997 አም ምርጫ ማለቴ አይደለም፡፡

የፓርቲዎች ፉክክር
ከ1994 አም ጀምሮ እስከ ታሪካዊው የምርጫ ጊዜ... እስከ 97ቱ ምርጫ ድረስ በመጠኑ እየተስፋፋ የመጣው ነፃነትና እየተነቃቃ የነበረው ኢኮኖሚ ትዝ አይላችሁም? የምርጫ ዘመቻውን ጨምሮ... በአገሪቱ ታሪክ ያልታየ የፓርቲዎች ብርቱ ፉክክር፣ በቲቪና በሬድዮ የሚተላለፍ የፓለቲካ መሪዎች ጠንካራ ክርክር፤ የየከተማው ደማማቅ ሰላማዊ ሰልፍ፣ የምሁራንና የዜጎች የተሟሟቀ ውይይት፤ በፍጥነት እየተሻሻለ የመጣ የነፃ ፕሬስ ዘገባ... ያ የጥንቱ ዘመን፤ ላይ ላዩን ብቻ ለሚያይ ሰው፤ ተስፋ ሰጪና ጣፋጭ ጊዜ ነበር፡፡ ይህችም ትዝታ ሆና፤ በትካዜ ማንጎራጎር አለብን?
በመንግስትና በገዢው ፓርቲ፤ በፖለቲከኞችና በተቃዋሚ ፓርቲዎች፤ በምሁራንና በማህበራት፣ በዜጎችና በሚዲያ ተቋማት በኩል ጉድለቶች አልነበሩም ለማለት አይደለም፡፡ ምን ይጠየቃል! እንዲያውም ስር ከሰደዱ የኋላቀር ባህልና የጭፍን እምነት ስሜቶች ጋር የተሳሰሩ፤ ትልልቅ ጉድለቶች፤ ከባባድ ጥፋቶች፤ በጣም ግዙፍ ስህተቶች በየአቅጣጫው በብዛት ስለተፈፀሙ ነው፤ ያ ተስፋ ሰጪ ጅምር በአጭር የቀረው፤ መጨረሻውም ያላማረው፡፡
ከዚያ በኋላማ፤ የፓርቲዎች ፉክክር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተዳከመ፤ ለምልክት ያህል እንኳ እየጠፋ መጥቷል፡፡ 170 ያህል የፓርላማ ወንበር (ከ30 በመቶ በላይ መቀመጫ) በምርጫ አሸንፈው የነበሩ ተቃዋሚ ፓርቲዎችኮ፤ የአዲስ አበባ መስተዳድር ምክር ቤትን በከፍተኛ ብልጫ ከማሸነፍ በተጨማሪ፤ በክልል ምክር ቤቶችም ብዙ ወንበሮችን አግኝተው ነበር - በ97 አም፡፡
በ2000 አም በተካሄደው የወረዳና የቀበሌ ምርጫ ላይ ግን፤ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ድምፅና ፉክክር ጠፋ፡፡ ከሶስት ሚሊዮን የወረዳና የቀበሌ ምክርቤት ወንበሮች መካከል፤ 3 ወንበሮችን ብቻ ነው ተቃዋሚ ፓርቲዎች ያሸነፉት፡፡ ኢህአዴግና አጋር ፓርቲዎች፤ ከ99.99 በመቶ በላይ በሆነ ውጤት አሸንፈዋል ማለት ነው፡፡ በ2002 የተካሄዱት የፓርላማና የክልል ምክርቤት ምርጫም ተመሳሳይ ነበር - ኢህአዴግና አጋር ፓርቲዎች ከ99.9 በመቶ በላይ ያሸነፉበት፡፡
ይህም ብቻ አይደለም፡፡ አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና አንዳንድ ፖለቲከኞች፤ የፓርቲ ፉክክርን ሳይሆን የፓርቲ መጠፋፋትን ሲመርጡ፤ ገዢው ፓርቲ በፊናው አሁን ያሉትን ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሙሉ በጅምላ ፀረ ዲሞክራሲና ፀረ ህገመንግስት ናቸው በማለት ሲፈርጃቸው ሰምተናል - እንዳያንሰራሩና በዚያው እንዲከስሙ ማድረግ አለብን ከሚል እቅድ ጋር፡፡  
..በተለምዶ.. የመድብለ ፓርቲ ስርአት ወይም ዲሞክራሲ እየተባለ የሚጠራው የፖለቲካ ስርአት ሲነሳ፤ ሁልጊዜ እንደመለያ ምልክት አብሮት የሚነሳ ጉዳይ አለ - የፓርቲዎች ፉክክር፡፡ ዛሬ ግን፤ የፓርቲዎች ፉክክር... በቃ ትዝታ ብቻ ሆኖብናል፡፡ ..በተለምዶ የፓርቲዎች ፉክክር እየተባለ የሚጠራው..... እያልን ካልተናገርን በቀር፤ ነገርዬው የማይጨበጥ የማይዳሰስ ተረት እየመሰለ ያስቸግረናል፡፡

የድጋፍና የተቃውሞ ሰልፍ
የእያንዳንዱን ሰው መብትና ነፃነት በማክበር ላይ የተመሰረተ ስልጡን የዲሞክራሲ ስርአት፤ ሌሎች ምልክቶችም አሉት - ለምሳሌ የድጋፍና ተቃውሞ ሰልፎች፡፡ በፓርቲ ፖለቲካ ዙሪያ ባጠነጠኑ ጉዳዮች ላይ ብቻ ሳይሆን፤ ከዚያ ውጭ በሆኑ ጉዳዮች ላይም፤ ዜጎች የድጋፍና የተቃውሞ ሃሳባቸውን በሰላም የማሰማት ነፃነታቸው መከበር የለበትም? ከአምስት አመታት በፊት በነበሩ ጊዜያት፤ በርካታ የድጋፍና የተቃውሞ ሰልፎችን እናይ ነበር - ከምርጫ ዘመቻ ውጭ የሆኑ፡፡ ከአምስት አመት ወዲህ ግን፤ የድጋፍ እንጂ የተቃውሞ ሰልፎችን አላየንም፡፡ እንግዲህ፤ ..በተለምዶ የተቃውሞ ሰልፍ እየተባለ ሲጠራ የነበረ..... ማለት ሊኖርብን ነው?

የነፃ ፕሬስ እድገት
ከ94 አም እሰከ 97 አም በነበሩ አመታት፤ የነፃነት አየር በመጠኑ ሰፋእያለ በመጣበት ወቅት የተመለከትነው ሌላ እውነታ፤ እንደአቅሚቲ የታየው የነፃ ፕሬስ እድገት ነው፡፡ ያኔ፤ የነፃ ፕሬስ ተቋማትና ጋዜጦች፤ በቁጥር ብቻ ሳይሆን በጥራት ደረጃም ፈጣን እድገት ሲያሳዩ እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ የፖለቲካ ፓርቲ ልሳን የመሳሰሉ ጋዜጦች አልነበሩም ማለት አይደለም፡፡ የመንግስት ወከባና እስር ቀላል ነበር ለማለትም አይደለም፡፡ ነገር ግን፤ በሰከነ መንፈስ ተፅእኖዎችን ተቋቁመው፤ ስልጡን የጋዜጠኝነት ሙያን እያዳበሩ ለመስራት የሚጣጣሩ ጋዜጦች ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸውና አቅማቸው እየጨመረ ነበር፡፡ ምን ያደርጋል! ይሄም ትዝታ ብቻ ሆኗል፡፡
ባለፉት አምስት አመታት፤ የጋዜጦች ቁጥር ቀንሷል፡፡ በስራ ላይ ካሉት ጋዜጦች መካከል ሙያቸውን የማያከብሩ ባይጠፉም፤ አብዛኞቹኮ የጥራት ደረጃቸውን ለማሻሻል ከመጣር ወደኋላ አላሉም፤ እድገታቸው ግን ተቋርጧል፡፡ በአንድ በኩል፤ በጭፍን ስሜታዊነት ጭፍን ድጋፍና ተቃውሞን ለማየት የሚፈልጉ አንዳንድ ዜጎች፣ ፖለቲከኞችና ፓርቲዎች አሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ፣ የመንግስት አካላት ተፅእኖና ወከባ ተባብሷል - በግላጭ ዛቻና ማስፈራሪያዎች ሲሰነዘሩ አይተን የለ? አያየን አይደል?
..እንትን ጋዜጣ እንደዚህና እንደዚያ አይነት ዘገባዎችን ወይም ፅሁፎችን የሚያሳትመው፤ ጋዜጠኞቹ ወደ ውጭ አገር መሰደድ ስለፈለጉ ነው፤ ጋዜጠኞቹ መታሰር ስለፈለጉ ነው..... እንዲህ አይነት ንግግር ሌላ ስም ሊኖረው አይችልም - ዛቻና ማስፈራሪያ እንጂ፡፡ እስቲ ይታያችሁ፤ ለመታሰር የሚፈልግ ጋዜጠኛ! ማሰር የሚፈልግ ሰው ጠፍቶ መታሰር የሚፈልግ ሰው የበዛበት ልዩ ዘመን ላይ ደርሰናል ማለት ነው?

የዜጎች ነፃ ውይይት
ሌላው የነፃነት ምልክት፤ የዜጎች ነፃና ቀና ውይይት ነው፡፡ ለዘመናት በጭፍን አስተሳሰብ አማካኝነት የተንሰራፋ ኋላቀር ባህል ጎልቶ በሚታይበት አገር፤ ከጭፍን ድጋፍና ተቃውሞ፤ ከጭፍን ጥላቻና ከመንጋ ቡድንተኝነት የፀዳ ነፃና ቀና የዜጎች ውይይት በስፋት ይኖራል ብሎ መጠበቅ አላዋቂነት መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ እንዲያም ሆኖ፤ ከ94 አም እስከ 97 አም ድረስ በነበሩት አመታት፤ ተስፋ ሰጪ ጅምሮች በየቦታው ብቅ  ሲሉ ተመልክተናል፡፡ ዛሬ ግን ትዝታ ብቻ ሆኗል፡፡ ከመንግስት አላስፈላጊ ቁጥጥሮችና ከነፃነት መጥበብ ጋር፤ ያ ተስፋ ሰጪ ጅምር ደብዝዟል፡፡ ብዙዎች፤ ተስፋ የለሽ ዝምታ ወይም ፍርሃት ተጫጭኗቸዋል፡፡
ለነገሩ፤ በጭፍን ስሜታዊነትና በመንጋ ጀብደኝነት ሲንደረደሩ የቆዩ አንዳንድ ዜጎች፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ ዥው ብለው ወደ ግድየለሽነትና ወደ ፍርሃት መሻገራቸው አይገርምም፡፡ በስሜታዊነትና በግድየለሽነት ዥዋዥዌ ነው እድሜያቸውን የሚጨርሱት - ወይም በመንጋ ጀብደኝነትና በመንጋ ፍርሃት፡፡ መፍትሄው፤ የሰከነ ስልጡን አስተሳሰብ እንደሆነ አላወቁም፡፡ እናማ፤  ከጭፍንነት የመላቀቅ ምልክት ይዞ የነበረው የዜጎች ነፃና ቀና ውይይት፤ ከጨቅላ ጅምርነት መዝለል ሳይችል ተዳፍኗል - በአላስፈላጊ የመንግስት ቁጥጥሮችና በኋላቀር ባህል ሳቢያ፡፡
ይህም ብቻ አይደለም፡፡ ከነፃነት መጥበብ ጋር፤ ትችትና ወቀሳ የሚሰነዝርብኝ የለም የሚል ስሜት፤ በተለያየ መጠን፤ በገዢው ፓርቲ ውስጥና በአንዳንድ ባለስልጣናት ዘንድ መፈጠሩ አይቀርም - ቸልተኝነትንና ማናለብኝነትን የሚያስፋፋ መጥፎ ስሜት፡፡
መጥፎነቱ ምን መሰላችሁ? በጥንቃቄ የመስራት ጥረት፣ ለማሻሻያ እርምጃዎች የመነሳሳት ብቃት፣ ስህተቶችን የማስተካከል ፍላጎት እየተሸረሸረ፣ የግብር ይውጣ፤ የሙስና ወይም የዘፈቀደ አሰራር እየጎላ ይሄዳል፡፡ እናማ፤ ነገ ከነገወዲያ ምን አይነት ህግ እና መመሪያ እንደሚወጣ ማወቅ እየከበደ፤ ይሄኛውና ያኛው ባለስልጣን ምን አይነት ውሳኔና ትእዛዝ እንደሚያስተላልፍ መገመት አስቸጋሪ እየሆነ ይመጣል፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ፤ የቢዝነስ ሰዎች የኢንቨስትመንትና የምርታማነት ተነሳሽነት አብሮ ይቀንሳል፤ ኢኮኖሚው እየተጎዳ የዜጎች ኑሮ እየከበደ ይሄዳል፡፡
ታዲያ ምን ተሻለ? አስቸጋሪ ጥያቄ! ግን ሁለት አማራጮች አሉ - ከባድ አማራጭ (..አድካሚ ስራ..) እና ቀላል አማራጭ (..የፈጠራ ችሎታ..)፡፡ ከባዱንና አስቸጋሪውን አማራጭ በጥቅሉ ጠቀስቀስ በማድረግ እንጀምር፡፡

..አስቸጋሪ አማራጭ..
ለችግሮቻችን መፍትሄ ለማበጀት፤ ጉዳዩን ከአጭርና ከረዥም ጊዜ አንፃር አስተሳስሮ መመልከት ያስፈልጋል፡፡ አሁን ያለንበትን ፈታኝ እና ጭላንጭል ሰጪ ሁኔታ አብጠርጥሮ መመርመር ብቻ ሳይሆን፤ ባለፈው ዘመን እየተገነባ ከመጣው የመጥፎ ባህል ሸክምና የመልካም ባህል አቅም ጋር፤ እንዲሁም ለመጪው ዘመን ሊኖሩን ከሚገቡ ራእዮችና ሃሳቦች ጋር አጣምሮ መተንተን ያስፈልጋል፡፡ በዜጎችና በቤተሰብ፣ በሚዲያ ተቋማትና በምሁራን፤ በማህበራትና በፖለቲከኞች፤ በፓርቲዎችና በመንግስት በኩል ሊከናወኑ የሚገባቸው ስራዎችና ሃላፊነቶችን አገናዝቦ መፈተሽንም ይጠይቃል፡፡
ለእውነታ በቅንነት መቆም፤ የራስንና የሰዎችን ህይወት ማክበር፤ የራስን ህይወት መምራት፤ የራስን መብትና ነፃነት ማስከበር፤ የሌሎችን መብትና ነፃነት ማክበር፤ በራስ ጥረት ህይወትን ማሻሻል... እነዚህን የመሳሰሉ ቅዱስ ሃሳቦች በምሁራንና በሚዲያ ተቋማት ካልተስፋፉ፤ በዜጎችና በቤተሰብ ዘንድ ጠንካራ መሰረት ካላገኙ፤ ነፃነትን የሚያስፋፋ ስልጡን ባህል በአገራችን ሊሰፍን አይችልም፡፡
ማህበራትና ፖለቲከኞችም፤ ነፃነትን የሚያስፋፋ ባህል እንዲዳብር የማመቻቸት ሃላፊነት አለባቸው፡፡ በተለይ ደግሞ ፓርቲዎች፤ ከፓርቲዎችም ውስጥ የመንግስት ስልጣን የያዘው ገዢ ፓርቲ ከፍተኛ ሃላፊነት ይኖርበታል፡፡ አላስፈላጊ ቁጥጥሮችን በየጊዜው እያበራከተ ነፃነትን ከማጥበብ መቆጠብ ብቻ ሳይሆን፤ በተቻለ ፍጥነትና በተቻለ መጠን፤ ነፃነትን የሚሰፉ የማሻሻያ እርምጃዎችን የመውሰድ ሃላፊነት አለበት፡፡ ከዚህም በተጨማሪ፤ ለእውነታና ለነፃነት ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጥ፤ የተሟላ የስልጡን ባህል አስተሳሰብ እንዲስፋፋ፤ ለመነሻነት ያህል የሚያገለግል የነፃነት ጅምር እንዲጠናከር መጣር ይጠበቅበታል - ገዢው ፓርቲ፡፡
ይህ ካልሆነስ? እንዲህ አይነት ትችቶችንና አቤቱታዎች፤ አስተያየቶችና ምክሮች ለመንግስት የማይጥሙት ከሆነና ውጤት የማያመጡ ከሆነስ? ምናልባት ባለፈው ሳምንት ..ዋናው ችግር የኑሮ ውድነት ሳይሆን፤ የፈጠራ ችሎታ እጦት ነው.. በሚል ርእስ እንደወጣው ፅሁፍ፤ የነፃነት ጉዳይ ላይም ተመሳሳይ ..የፈጠራ ችሎታዎችን.. ለመጠቀም መሞከር እንችላለን፡፡

..የፈጠራ ችሎታ..
..የፓርቲዎች ፉክክር በጅምር ተረት ሆነብን..፤ ..ሃሳቦችን በሰላማዊ ሰልፍ የመግለፅ እድል በአጭር ቀረብን..፤ ..የነፃ ፕሬስ እድገት በእንጭጩ ተቋርጦ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ትዝታ ሆነብን..፤ ..ነፃና ቅን የዜጎች ውይይት በጅምር ተዳፈነብን..... እያልን ዘወትር ከማማረር ይልቅ ..የፈጠራ ችሎታችን..ን በሚያስመሰክር መንገድ አማራጭ አቅጣጫዎችን እንሞክር?
ነፃና ቅን የዜጎች ውይይት ተዳፈነ ምናምን እያልን ከምንተክዝኮ፤ ስለ ፖለቲካና ስለ ኢኮኖሚ ባንወያይም፤ ስለ ፕሪሜር ሊግ በጥሞና ስልጡን ውይይት ማካሄድ አይሻለንም? በእርግጥ፤ በዚሁ ሰበብ የሚፈነካከቱ ወጣቶች መኖራቸው አሳሳቢ ነው፡፡ ቢሆንም... ይቻላል፡፡ በዚያ ላይ፤ የግድ የፓርቲዎችን ፉክክር ለማየት መጓጓት የለብንም፡፡ የማንቼና የአርሴ ፉክክር ብቻ ሳይሆን፤ እዚሁ በአገራችንም የጊዮርጊስና የቡና፤ ካስፈለገም የኢትዮጵያን አይዶል ፉክክሮችን ማየት እንችላለን፡፡
ዋናው ነገር፤ የፈጠራ ችሎታ እንጂ ብዙ የፉክክር አይነቶችን ማፍለቅ አያቅተንም፡፡ የውፍረት ውድድር፤ ለረዥም ሰአት የመሳቅ ፉክክር፤ መድረክ ለመምራት በተመረጡ ሰዎች መካከል የሚፈጠር ቅፅበታዊ ፉክክርና ትንቅንቅ ሳይቀር... ማለቂያ የለውም፡፡ በእነዚህ ጉዳዮች ዙሪያ ሁሉ፤ የድጋፍ ብቻ ሳይሆን የተቃውሞ ሰልፎችንም እንደልብ ማካሄድ ሳይቻል አይቀርም፡፡ የሚከለከልበት ምክንያት አይታየኝም፤ በዚያ ላይ በነፃ ፕሬስም እየፃፍን ማንበብ እንችላለን፡፡
ስለዚህ... በቃ፤ ፉክክሮችን እያየን፣ ሰላማዊ ሰልፍም እያካሄድን፤ በስልጡን መንገድ መወያየት! በፈጠራ ችሎታችን ችግሮቹን ሁሉ መፍታት አይከብደንም፡፡ በእርግጥ አንዳንድ ችግሮች ሊያጋጥሙን ይችላሉ፡፡ በኳስ ወይም በአይዶል ፉክክር የተጀመረው ውይይት፤ በየት አቅጣጫ እንዳሾለኩት ሳይታወቅ፤ ጭፍን የሃይማኖት ሙግት ወይም ጭፍን የዘር እንካሰላንተያ እንዲሆን የሚያደርጉ ሰዎች ጥቂት አይደሉም፡፡ በፖለቲካና በኢኮኖሚ ጉዳዮች ምትክ፤ ጭፍን የሃይማኖትና ጭፍን የዘር እንቶፈንቶዎች እንደትልቅ ጉዳይ ሲፍለቀለቁ የምናየው በዚህ ምክንያት ይሆን እንዴ?

 

Read 7267 times Last modified on Saturday, 01 October 2011 12:47