Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 24 September 2011 10:54

ዋናው ችግር የኑሮ ውድነት ሳይሆን፤ የፈጠራ ችሎታ እጦት ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ስለ ዋጋ ንረትና ስለ ኑሮ ውድነት ስናወራ ስንት አመታችን? መሬት በራሷ ዛቢያ እየተሽከረከረችና ፀሃይን እየዞረች፤ እኛም በዋጋ ንረት እንዝርት እየሾርን፤ በኑሮ ውድነት ምህዋር እየዞረብን አመታት ተቆጠሩ፡፡ ቢሆንም ግን፤ ልንለምደው የቻልን አልመሰለኝም፡፡ ነጋ ጠባ፤  ቅሬታና ስሞታ፤ ተቃውሞና አቤቱታ፤ ምክርና ውትወታ ... በአይነት በአይነቱ መደጋገማችንን ቀጥለናል - ክረምት ከበጋ የማይቋረጥ መዝሙር ሆኗል ማለት ይቻላል፡፡ አንዳንዴም፤ በጣም ከመደጋገሙ የተነሳ የመዝሙሩ ዜማ እየፈዘዘ ወደ አስቀያሚ እንጉርጉሮነት ይቀየርብናል፡፡ ባስ ሲልም ኡኡታ ሊመስል ምንም አይቀረውም፡፡

ከጥቂት ቀናትና ሳምንታት በኋላ፤ የሸቀጦች ዋጋ እንደገና ሲንርና ኑሮ ሲወደድ፤ እንደገና ተመልሰን አቤቱታና ውትወታ፤ መዝሙርና እሪታ፤ እንደገና ተመልሰን ምክርና እሮሮ፤ በፅሁፍና በእንጉርጉሮ እናወርዳለን፡፡ ከዚሁ ..የሙከራ አዙሪት.. አልወጣንም - ከአመት አመት በሚቆጠቁጥ የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት ሳቢያ ከተፈጠረው ..የመከራ አዙሪት.. ጋር፡፡ የፈረንጆቹ አባባል እኛ ላይ ይሰራል ማለት ነው፡፡ ..በቁም የሚቃዠ ሰው ምን አይነት ነው?.. ብትሉ፤... ..ሁልጊዜ፤ ተመሳሳይ ነገር ደጋግሞ እየሞከረ፤ ከወትሮው የተለየ ውጤት የሚጠብቅ ሰው..፡፡ ለነገሩ፤ እየሞከረ ይመስለዋል እንጂ እየሞከረ አይደለም፡፡ ተመሳሳይ ድርጊት እያከናወነ ከሆነኮ፤ መሞከርን ከተወ ብዙ ቆይቷል ማለት ነው፡፡
እነዚያኑን ሙከራዎች ስንደጋግም ብንከርምም፤ ከመከራ አዙሪት የሚያላቅቁን አልሆኑም፡፡ አመታትን ባስቆጠርንበት በዚሁ መንገድ የምንቀጥል ከሆነ፤ ተመሳሳይ ድርጊት እየፈፀምን፤ የተለየ ውጤት የምንጠብቅ የቁም ቅዠት ሰዎች እንሆናለን - doing the same thing and expecting a different result  በሚለው አባባል መሰረት፡፡ ትንሽ መረር ያለ ይመስላል? እሺ፤ የቁም ቅዠት ምናምን የሚለውን እንተወው፡፡ ነገር ግን፣ እንዲህ አይነት ባህሪ ለትዝብት እንደሚዳርገን አትጠራጠሩ፡፡ ወደፊትም፤ ተመሳሳይ ድርጊት እየደጋገምን፤ የተለየ ውጤት የመጠበቅ ባህርይ ይዘን የምንቀጥል ከሆን፤ ቢያንስ የፈጠራ ችሎታችን ጥያቄ ውስጥ መግባቱ አይቀርም፡፡
የመመራመርና የመፈላሰፍ፤ አዲስ ዘዴና ያላረጀ መንገድ የመሞከር፤ በአጠቃላይ የፈጠራ ችሎታ እንደሌለን ከተረጋገጠኮ፤ ትልቅ ውርደት ነው፡፡ እስቲ አስቡት፡፡ በሳይንስ ግኝትና በቴክኖሎጂ ፈጠራ ተረስተናል፡፡ አዳዲስ የቢዝነስ ፈጠራዎችና የንግድ ሙከራዎችን ማየት ከናፈቀን ቆይቷል፡፡ በመዝናኛ ጥበቦች በኩልም የፈጠራ ስራ ተዳክሟል፡፡ የዜማና የግጥም፤ የሙዚቃና የድርሰት ፈጠራዎች፤ ተመናምነው እየጠፉ አይደል? ጌታቸው ጋዲሶ፤ እንዳለው ከሆነማ ያስፈራል - ከእንግዲህ የሙዚቃ ፈጠራ ተስፋ ስለሌለው፤ ዘፋኞችና ሙዚቀኞች ሌላ ሞያና ሌላ የንግድ ስራ ቢሞክሩ ይሻላል ብሏል - ጌታቸው፡፡ አትሌቲክስ ሳይቀር በድርቅ የተመታበት ዘመን ላይ ነን፡፡
ታዲያ በእነዚህ ውርደቶች ላይ፤ ተጨማሪ የፈጠራ ልምሻ እንደተጠናወተን ከተረጋገጠ፤ በዚህም ምክንያትም ከሰው ተራ የሚቆጥረን ብናጣ አያሳፍርም? ከዋጋ ንረትና ከኑሮ ውድነት የባሰ በጣም አሳሳቢ ጉዳይ እንደሆነ አያችሁ? የፈጠራ ችሎታችንኮ ነው ጥያቄ ውስጥ የሚገባው፡፡ ትንሽ ቆይቶ ደግሞ፤ ሰው ናቸው ወይስ ሮቦት ናቸው እያለ አለም በኛ ሲከራከር ይታያችሁ፡፡ ሰው የመሆንና ያለመሆን ነው ጥያቄው - "to be or not to be; that is the question"””
ስለዚህ፤ ይዋል ይደር ሳንል፤ የፈጠራ ችሎታዎቻችንን ማሳየት አለብን፡፡ በእርግጥ እስከዛሬ ምንም የፈጠራ ችሎታ አላሳየንም ማለት አይደለም፡፡ ለምሳሌ፤ የዋጋ ንረቱንና የኑሮ ውድነቱን ለመቋቋም፤ ብዙ ሰዎች የመመገቢያ ሰአታቸውንና ስታይላቸውን እንደቀየሩ ሁላችንም እናውቃለን - ቁርስንና ምሳን ለየብቻ ጥዋትና ቀትር ላይ ከመብላት ይልቅ፤ ረፋዱ ላይ አንዴ መብላት፡፡ ነገር ግን ይህ ፈጠራ ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ በዚያ ላይ፤ ረዥም ጊዜ ስለሆነው፤ አሁን እንደ ልማድና ባህል እንጂ እንደፈጠራ ሊቆጠር አይችልም፡፡ ብዙና አዳዲስ የኑሮ በዘዴ ፈጠራዎች ያስፈልጉናል፡፡
ለምሳሌ፤ በኑሮ ውድነት ላይ እንደገና ሰሞኑን የትራንስፖርት ዋጋ ጨምሯል፡፡ እንግዲህ ቀደም ሲል፤ የአዲስ አበባ ሚኒባስ ታክሲዎች፣ እንደየሰአቱና እንደየእለቱ ሁኔታ፤ ተሳፋሪ ወደሚበዛበት አካባቢ እየተሯሯጡ ሲሰሩ፤ ደህና ገቢ ያገኙ ነበር፤ ተሳፋሪዎችም ያለችውን ያህል የትራንስፖርት አገልግሎት ያገኙ ነበር፡፡
የቀጣናና የስምሪት ቁጥጥር ሲጀመር፤ ተሳፋሪ ወደሚበዛበት አካባቢ ተሯሩጦ መስራት ቀረ፡፡ ተሳፋሪዎች ከቀድሞ በባሰ የትራንስፖርት እጥረት ተቸገሩ፤ የታክሲዎቹም ገቢ ቀነሰ፡፡ ታክሲዎቹ ተሯሩጠው እንዲሰሩ በመፍቀድ የተሳፋሪዎችንም ሆነ የታክሲዎችን ችግር መፍታት እየተቻለ፤ የትራንስፖርት ታሪፍ እንዲጨምር ተደርጓል፡፡ የቁጥጥር መጨረሻው ይሄው አይደል? ይቅርታ... አቤቱታ ለማሰማትና ምክር ብጤ ለመስጠት በመሞከር፤ እንደገና ወደ አዙሪቱ መግባት የለብንም፡፡ በፈጠራ ችሎታ ነው፤ ችግሮችን መቋቋም የሚገባን፡፡ ደግሞስ፤ ስልጣኔን እያሰብን የትራንስፖርት እጥረት ትልቅ ችግር ከሚሆንብን፤ ከመቶ አመት በፊት ወደኋላ ተመልሰን እንደምንኖር በማሰብ ችግሩ ቀለል ብሎ እንዲታየን ማድረግ እንችላለን፡፡ ለመሆኑ፤ በእግር መሄድ እየቻልን ለምን በታክሲ እጦትና በዋጋ ጭማሪ እንጨነቃለን? እንዲሁ ስታስቡት፤ ሰው በእግሩ ምን ያህል ርቀት ለስንት ያህል ጊዜ መጓዝ እንደሚችል፤ ሞክራችሁ የማየት የእውቀት ጉጉት አይፈጠርባችሁም?
የማወቅ ጉጉት ባይኖራችሁ እንኳ፤ በተለይ ጥዋትበእግር መሄድኮ፤ እንደ ስፖርት ልንቆጥረው እንችላለን፡፡  ቁርስና ምሳ ሳይበሉ ረፋድ ላይ ምግብ ለሚቀማምሱ ሰዎች፤ በጥዋቱ በባዶ ሆድ በእግር መኳተን ይከብዳቸው ይሆናል፡፡ በዚያ ላይ፤ በእግር የሚጓዝ ሰው ሲበዛ፤ መንገዱ ሁሉ ሞልቶ ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ እንዳይመስልብን ያሰጋል፡፡ አምስት አመት ሙሉ የተረሳውን የተቃውሞ ሰልፍ፤ ሳናስበው በእግረኛ ብዛት ምክንያት ከፊት ለፊታችን ገጭ ያለ ሲመስለን ልንደነብር እንችላለን፡፡
እንግዲህ የፈጠራ ሃሳቦችን በሰበብ አስባቡ ውድቅ ለማድረግ የምትፈልጉ ከሆነ፤ ብዙ  ምክንያት ማቅረብ ትችላላችሁ፡፡ በባዶ ሆድ በእግር መሄድ አልችልም፤ እግረኛ ሲበዛ ሰላማዊ ሰልፍ ሊመስል ይችላል... እያላችሁ የፈጠራ ሃሳቡን ብታጣጥሉትም ... እሺ... የታክሲ ወጪ ከበዛብን፤ ለምን ብስክሌት አንጠቀምም? በእርግጥ የአዲስ አበባና የአንዳንድ ከተሞች ዳገት ለመውጣት ስንሞክር፤ ቆመን እንቀር ይሆናል፡፡ በዚያ ላይ ብስክሌት መግዛት ቀላል አይደለም፡፡ ግን ችግር የለውም፡፡ በቃ፤ ብልጭ የሚልልን ማንኛውም የፈጠራ ሃሳብ ተግባራዊ መሆን ባይችል እንኳ፤ እንዲሁ ማሰቡ አይሻልም? ለተግባር የማይረዳ ሃሳብ ምን ጥቅም አለው? ባይኖረውም ሌላ የፈጠራ ሃሳብ ለማምጣት መሞከር ነው ዋናው፡፡
ከአንድ ባልደረባዬ የሰማሁት የፈጠራ ሃሳብማ፤ ስም ሁሉ ወጥቶለታል - የኑሮ ቅሸባ የሚል፡፡ ለምሳሌ፤ ወተትና ቡና በተወደደበት ዘመን፤ በእረፍት ሰአት ወጣ እያሉ ማኪያቶ መጠጣት ከአቅም በላይ እየሆነ ያስቸግራል፡፡ ከተቻለ አለመጠጣት ነው፤ ግን ያ አስደሳች የማኪያቶ ጣእም ውል እያለ እረፍት ይነሳል፡፡ ታዲያ ምን ተሻለ? ንፁህ ወተትና ንፁህ ቡና የሚለውን ሃሳብ በመተው፤ ገብስ የተቀላቀለበት ቡና መጠቀም - የዱቄት ወተት ላይ፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡
ሳሙና ተወደደ ተብሎ፤ የቆሸሸ ልብስ ማድረግ ያስጠላ የለ? በዚህኛው ሳምንት አንዱ ልብስ ሲቆሽሽ ሌላ መቀየር ያስፈልጋል፡፡ እሱ ሲቆሽሽ ደግሞ፤ ያ ቆሽሿል ብለን ያስቀመጥነውን መልሶ መልበስ፡፡ በአንድ ዙር ብቻ ልብሶችን ባለማጠብ የኑሮ ውድነትን መቋቋም ይቻላል ለማለት ነው፡፡ የኑሮ ቅሸባ፤ ዘርፈ ብዙ ስለሆነ፤ የአቅማችንን ያህል የፈጠራ ችሎታችንን በመጠቀም በተለያየ መንገድ ተግባራዊ ለማድረግ ብንጥርስ?
ሌላ የተረሳ ዘዴ! የጓሮ አትክልት አለላችሁ - ፍቱን የኑሮ ውድነት መፍትሄ፡፡ ጓሮ ሳይኖረን፤ እንዴት የጓሮ አትክልት ይኖረናል ብትሉም ችግር የለም፡፡ ቤት ውስጥ ኤሌክትሪክና ቧንቧ፤ ስልክና መስኮት፤ ቲቪና ፍሪጅ ሲበላሽ በክፍያ ባለሞያ ከመጥራት ይልቅ፤ ከዘመድ ከጎረቤት የምናውቀውን ባለሞያ እያስቸገርን ብናሰራ ከብዙ ወጪ እንድናለን፡፡ በዚህ ዘመን ብልጣብልጥነት ያስፈልጋል፡፡
በእርግጥ እንዲህ አይነት ብልጣብልጥነት ውሎ አድሮ ሰው ሁሉ ስለሚነቃበት ሞኛሞኝነት ሆኖ ቁጭ ይላል፡፡ ጎረቤትና ዘመድ ላይ ሸክም ሆኖ መኖርም አይቻልም ካላችሁ፤ ለምን የተበላሹትን ነገሮች በራሳችን ለመስራት በመሞከር ወጪ አንቀንስም? ሞያውን ሳናውቅ ለመስራት ስንሞክር፤ ነገርዬውን ይበልጥ ስናበላሸውና ስንሰባብረው፤ የባሰ ወጪ ቢመጣብንስ? ቅድም እንደነገርኳችሁ፤ የፈጠራ ሃሳቦቹ በሙሉ ለኑሮ ውድነት መፍትሄ ባይሆኑ እንኳ፤ ስለመፍትሄ ማሰብና መሞከር ራሱ ከጭንቀት ፋታ ይሰጣል - ከኑሮ ፋታ ባናገኝበትም፡፡

 

Read 6231 times Last modified on Saturday, 24 September 2011 10:56