Print this page
Saturday, 24 September 2011 10:32

የኢራንና የሰሜን ኮሪያ አዲሱ ፍቅር ምዕራባዊያንን ስጋት ላይ ጥሏል

Written by  ጥላሁን አክሊሉ
Rate this item
(5 votes)

ከሁለተኛ የዓለም ጦርነት በኋላ አምስቱ ሃያላን አገሮች ማለትም አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ ሩሲያ፣ ፈረንሣይና ቻይና ብቻ ለረጅም ዓመታት የኒውክሊየር ጦር መሣሪያ ባለቤት በመሆን ቢቆዩም፣ ካለፉት 30 ዓመታት ወዲህ ግን በርካታ አገራት በዓለም ላይ የበላይነትን ለማሳየትና እነዚህ መሣሪያዎች የሚያቀዳጁትን ክብርና ኃያልነት ለማግኘት በሚያደርጉት እሽቅድምድም የኒውክሊየር ጦር መሣሪያ ባለቤት ለመሆን በቅተዋል፡፡
እ.ኤ.አ በ1970 ዓ.ም የኒውክሊየር ጦር መሣሪያዎችን መዛመት የሚያግደው ውል (Nuclear Non-proliferation treaty) በስራ ላይ ሲውል፣ 140 አገራት ውሉን ፈርመው ነበር፡፡ ስምምነቱ እንደገና በ1990 ዓ.ም ሲታደስ ደግሞ፣ አንዳንድ አገራት ውሉን ለመፈረም ፍቃደኛ አልሆኑም፡፡ እነዚህ አገራት ላለመፈረማቸው ያቀረቡት ምክንያትም እንደ አሜሪካና ሩሲያ ያሉ አገራት የኒውክሊየር ባለቤት ሆነው እኛ ለምን እንታገዳለን? የሚል ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት፤ በአሁኑ ወቅት፤ እንደ ሕንድ፣ ፓኪስታን፣ ብራዚል፣ አርጀንቲና፣ እስራኤል እና ሰሜን ኮሪያ የኒውክሊየር ጦር መሣሪያ እንዳላቸው ሲገለፅ፣ በቅርቡ ደግሞ ኢራን የኒውክሊየር ባለቤትነት እሽቅድምድም ውስጥ መግባቷ በስፋት እየተነገረ ይገኛል፡፡

በተለይም አሜሪካ ኃላፊነት አይሰማቸውም በማለት ደጋግማ ከምትገልፃቸው አገሮች ውስጥ እንደ ሰሜን ኮሪያና ኢራን የመሳሰሉ አገራት የኒውክሊየር ጦር መሣሪያ እጃቸው መግባቱ ለዓለም ሰላም እጅግ አስጊ እና አደገኛ ነው፤ በማለት ትገልፃለች፡፡
አሜሪካ እ.ኤ.አ በ1945 ዓ.ም የጃፓን ከተሞች በሆኑት ሂሮሺማና ናጋሲኪ ላይ የአቶሚክ ቦንብ በመጣሏ፣ የ110,000 ጃፓናዊያን ሕይወት ተቀጥፏል፡፡ ከአቶሚክ ቦንቡ ድብደባ በኋላም ቢሆን፣ በራዲየሽን እና በራዲዮ አክቲቭ ጨረር የተጋለጡ ጃፓናዊያን የተዛባ ዲ.ኤን.ኤ ቀውስ በመዳረጋቸው ለአካል ጉዳተኝነት ተጋልጠዋል፡፡ ጃፓን በአሜሪካ ከተመታች ከሦስት አሰርት ዓመታት በኋላ፤ ማለትም እ.ኤ.አ በ1980 ዓ.ም፤ በዓለም ላይ ያለው የኒውክሊየር ክምችት 50,000 የደረሰ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ደግሞ ከ100 ሺህ በላይ እንደሆነ ይገመታል፡፡
በቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት ወቅት፤ የቀድሞ ሶቭየት ሕብረትና ዩናይትድ ስቴትስ ለዓለም ሰላም ለማምጣት እንዲሁም በመካከላቸው ያለውን የርዕዮተ ዓለም ልዩነት ለማጥበብ በጋራ የኒውክሊየር የጦር መሣሪያ ቅነሳን (Nuclear disarmament) በተለያየ ጊዜያት ቢያካሂዱም በዓለም አቀፍ ደረጃ የተጠበቀው ሰላም አልመጣም፡፡ እንዲያውም፤ የቀዝቃዛው ዓለም ጦርነትን ተከትሎ የተለያዩ ሀገሮች ከምዕራባዊያን በተቃራኒ በመሆን ወደ ዓለም መድረክ ብቅ ሊሉ ችለዋል፡፡ አክራሪነትና ሽብርተኝነትም ከቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ በኋላ የተስፋፉ ሁነቶች ናቸው፡፡
እ.ኤ.አ 1985 ዓ.ምትን የተባበሩት መንግስታት የሰላም ዓመት ብሎ ቢሰይመውም፣ በዚያው ዓመትም ሆነ ከዚያ በኋላ በተከተሉት አመታት ዓለም አቀፍ ሰላም አልመጣም፡፡ የኒውክሊየር ጦር መሣሪያና ሌሎች አውዳሚ የጦር መሣሪያዎች ባለቤት ለመሆን የሚካሄደው ፉክክርም አሁንም ድረስ በስፋት እንደቀጠለ ይስተዋላል፡፡ የርዕዮተ ዓለም ልዩነት መኖሩ ደግሞ፤ የጦር መሣሪያ ክምችቱን ሚስጢራዊና በድብቅ እንዲካሄድ አድርጐታል፡፡ ለዚህም ተጠቃሽ ከሚሆኑት አገራት መሀል ሁለቱ ሰሜን ኮሪያና ኢራን ሲሆኑ፣ ሁለቱም ከምዕራባዊያን በተቃራኒ ጐራ የተሰለፉ አገሮች ናቸው፡፡
በየካቲት ወር 2009 ዓ.ም፤ ኢራን ኢስላማዊ አብዮትን የጀመረችበትን 30ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ ወደ ሕዋ ሳተላይት ማምጠቋ ይታወሳል፡፡ ኢራን ያመጠቀችው ሳተላይት ለምርምርና ለቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት እንደሚውል ብትገልፅም፣ አሜሪካና እንግሊዝ ግን፣ ለኒውክሊየር ጦር መሣሪያ ግንባታ እንዲያግዛት ትጠቀማለች በማለት ተቃውሞ አቅርበውባት ነበር፡፡ የኢራኑ መሪ አህመዲን ነጃድ፤ በኢራን መንግስታዊ ቴሌቪዥን ባቀረቡት ንንግር:- «የእስላም ሃያልነት የታየበት ቀን ነው» ብለው ነበር፡፡
በአንድ ወቅት «እስራኤል ከካርታ ላይ መጥፋት አለባት» በማለት የተናገሩት አህመዲን ነጃድ፤ ፀረ-ጽዮናዊ አቋም ያላቸው ከመሆኑ ባሻገር፣ ለምዕራባዊያን አገራት የማይመቹ መሪ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ፤ የጋዳፊ ደጋፊ እንደሆኑ የሚታወቁት የቬኔዙዌላው ፕሬዝዳንት የሁጐ ቻቬዝ ጠንካራ ወዳጅ ናቸው፡፡
በኢራን አፍቃሪ ምዕራባዊ የነበሩት ንጉስ ሻሃ እ.ኤ.አ በ1979 ዓ.ም በኃይል ከስልጣን እንዲለቁ ከተደረገ በኋላ፣ አገር ጥለው ሲሰደዱ፣ ወዲያው የኢራን እስላማዊ አብዮት (Iran Islamic Revolution) በአገሪቱ ተቀጣጠለ፡፡ ከዚያም፤ ኢራን በእስልምና ሕግ የምትመራ አገር ሆነች፡፡ በንጉስ ሻሃ ዘመን ይነበቡ የነበሩት የምዕራባዊያን መፅሐፍት ታገዱ፡፡ የሆሊውድ ፊልሞችና ሙዚቃዎችም በአገሪቱ እንዳይታዩ እገዳ ተጣለባቸው፡፡ ከአብዮቱ በፊት የነበሩት የሴቶች መብት ተገፎ በሸሪአ ሕግ እንዲመሩ ተደረገ፡፡
በኢራን የአገሪቱ መንፈሳዊ መሪም ከሃይማኖት መሪነታቸው በተጨማሪ በአገሪቱ ሕግና ፖለቲካ ውስጥ የላቀ ተሳትፎ አላቸው፡፡ ለምሳሌ በ2009 ዓ.ም አህመዲን ነጃድ በምርጫ ተሸንፈው ስልጣናቸውን እንደማይለቁ ሲያስታውቁ፤ ሕዝባዊ ተቃውሞ ተነስቶባቸው ነበር፡፡ ይሁንና፤ መንፈሳዊው መሪ ምርጫውን አህመዲን ነጃድ እንዳሸነፉ በመግለፅ ተቃዋሚ ሰልፈኞቹን አውግዘው ነበር፡፡ ፀረ አሜሪካ አቋም እንዳላቸው የሚታወቁት መንፈሳዊ መሪ፣ ኢራን ለምታደርገው የኒውክሊየር ግንባታም ትልቁን ሚና እንደሚጫወቱ ይገለፃል፡፡
ራሷን ከሙስሊም አገራት በላይ ሃያል አገር አድርጋ የምትቆጥረው ኢራን፣ የኒውክሊየር ጦር መሣሪያ ባለቤት የመሆን ምኞቷንም ከእስላማዊ አብዮት ፈር ቀዳጅነቷ ጋር በማያያዝ፣ በመካከለኛው ምስራቅ የላቀ ሚና የመጫወት ሕልም እንዳላት አንዳንድ ተንታኞች ያስረዳሉ፡፡ አረቦች ላለፉት 60 ዓመታት በእስራኤል የደረሰባቸው ሽንፈት ከፈጠረባት እልህና ቁጭት በመነሳት ሃያላን አገራት የበላይነታቸውን የሚያንፀባርቁበትን የኒውክሊየር ጦር መሣሪያ በእጇ ለማስገባት ወደ ኋላ እንደማትል ይነገራል፡፡ ከሁሉም በላይ የአህመዲን ነጃድ ወደ ስልጣን መምጣት ኢራን ከምዕራባዊያን ጋር የነበራት ግንኙነት ከድጡ ወደ ማጡ እንዲሆን አድርጓል፡፡ በአንድ ወቅት ከቢ.ቢ.ሲ ጋዜጠኛ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ «…እነርሱ (ሃያላን አገሮች) የኒውክሊየር ባለቤት እንዲሆኑ የፈቀደውና እኛ ደግሞ እንዳንይዝ የሚከለክለን ማነው?» ብለው ነበር፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ ሮይተርስ ደግሞ በቅርቡ “West fears possible Iran - North Korea nuclear links” በሚል ርእስ ባስነበበው ፅሁፍ፤ ኢራንና ሰሜን ኮሪያ አዲስ የኒውክሊየር ወዳጅነት መጀመራቸው አስነብቧል፡፡ ሰሜን ኮሪያና ኢራን አዲስ የጀመሩት የኒውክሊየር ግንኙነት ፍቅር፣ ለምዕራባዊያን አገራት ትልቅ ራስ ምታት ሆኗል፡፡
የኒውክሊየር ጦር መሣሪያ ቴክኖሎጂ ከቁጥጥራቸው ውጪ እየሄደ መምጣቱ ነው፡፡ ኮሪያና ኢራን እርስ በእርሳቸው የኒውክሊየርን ቴክኖሎጂን በመቀያየር የአቶሚክ ቦንብ እንዲኖራቸው የሚያስችላቸው ደረጃ ላይ ሊደርሱ ይችላሉ፤ የሚለው ዋነኛው ምክንያት ነው፡፡ በCarnage Endowment for International peace ተቋም ውስጥ፤ ኤክስፐርት የሆኑት ማርክ ሂብስ ሲናገሩ:- «የኢራንና የሰሜን ኮሪያ ግንኙነት ሁለቱንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ተብሎ ሊቀመጥ ይችላል» ብለዋል፡፡
ባለፈው ዓመት የተባበሩት መንግሥታት ሪፖርት እንደጠቆመው፤ ሰሜን ኮሪያ የኒውክሊየር ቴክኖሎጂን ለኢራን ከመስጠቷም በላይ፣ ሶሪያና በርማ በዓለም አቀፍ ደረጃ እገዳ የተጣለበትን የአቶሚክ ቴክኖሎጂ አሳልፋ ሰጥታለች በማለት ጠቅሷታል፡፡
ባለፈው ወር፤ አንድ የጀርመን ጋዜጣ በዘገባው፣ ኢራን የኒውክሊየር ጦር መሣሪያ መስሪያ የሚያገለግል የኮምፒዩተር ሶፍትዌር ፕሮግራም የሰጠቻት መሆኑን ገልጿል፡፡ በሌላም በኩል፤ የዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ (IAEA) እና የአንዳንድ መንግሥታት ምንጮች በኢራንና በሰሜን ኮሪያ መካከል የኒውክሊየር መሣሪያ የመገንባት ስምምነት መደረጉን ገልፀዋል፡፡
ሁለቱም አገራት ከባድ የኢኮኖሚ ማዕቀብ ቢጣልባቸውም፣ አሁንም ሚስጢራዊ ግንኙነት ከማድረግ አልተቆጠቡም፡፡
ይሁን እንጂ፤ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ታዋቂ የኒውክሊየር ሳይንቲስት የሆኑት ሴዮግፍሬድ ሄከር ሲናገሩ፤ «ኢራን እና ሰሜን ኮሪያ በኒውክሊየር ቴክኖሎጂ ዙሪያ ጠንካራ ጥምረት ፈጥረዋል እየተባለ ቢነገርም፣ አሁንም ቢሆን የፈጠሩት ጥምረት ምን አይነት እንደሆነ በግልፅ ለማወቅ አልቻልንም» ብለዋል፡፡
በአጭሩ፤ የሁለቱ አገራት ግንኙነት በጥቅሉ ሲመዘን፣ በሚሳኤል ጦር መሣሪያ ትብብር ያላቸው ጥምረት የሚጠቀስ ነው የሚሉት የኒውክሊየር ሳይንቲስት ሄከር፤ ሰሜን ኮሪያ (በተለይ ኢራን) የጦር መሣሪያ እንዲኖራትና ከዚሁ ጋር የተያያዘ ፋብሪካዎችን እንድትገነባ እርዳታ አድርጋላታለች በማለት ያብራራሉ፡፡
ሄከር፤ የምስራቅ እስያዋን አገር ሰሜን ኮሪያን በተደጋጋሚ የጐበኙ ሲሆን፣ በዋነኛነት በቴህራንና በፒዮንግያንግ ሽግግር እውን መሆን እጅግ አደገኛ በመሆኑ፣ ሁሉም ወገን ትኩረት ሊሰጠው የሚገባና የኒውክሊየር ጦር መሣሪያ ዝውውርን በመቆጣጠር ሃላፊነትን መወጣት ይገባል፤ ብለዋል፡፡
የኢራን የኒውክሊየር ፕሮግራም የተመሰረተው ዩራኒየም የተባለውን ንጥረ ነገር ከማበልፀግ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ይህም እንቅስቃሴ ለሲቪልና ለወታደራዊ አገልግሎት ለመጠቀም ያስችላል፡፡
በአንፃሩ፤ ሰሜን ኮሪያ ለሁለት ጊዜያት ያህል ከዩራኒየም የላቀውን የፕሎቶኒየም ንጥረ ነገር በመጠቀም ሙከራ ያደረገች ሲሆን፣ ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ ውግዘት እንዳስከተለባት አይዘነጋም፡፡
ምንም እንኳን ሰሜን ኮሪያ የኒውክሊየር ፕሮግራምዋ ዩራኒየምን በማበልፀግ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ብትገልፅም፣የአገሪቱ አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመሄዱ፣ የአቶሚክ ቦንብ ባለቤት ለመሆን ሁለተኛውን እርምጃ ፈፅማለች፡፡ በቅርቡ ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ዋና ጽ/ቤቱ በሚገኝበት በኦስትሪያ ቪየና ውስጥ በተካሄደ የአለም አቀፍ ዲፕሎማቶች ሴሚናር ላይ፤ ሳይንቲስቱ ሲዬግፍሬድ ቤከር የሰጡት ገለፃ፣ ሁለቱ አገራት ያላቸውን የኒውክሊየር ባለሙያዎች በጋራ ለመጠቀም ብዙ ርቀት ሄደዋል፤ በዚህ በኩል ልምዳቸውን በመለዋወጥ እያደረጉ ባለው ጥረት በርካታ ጠቃሚ መረጃዎች ተገኝተዋል፤ ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ሰሜን ኮሪያ አዲስ ባገኘችው ቀመር በመነሳት ሳይንቲስቶችዋም በኒውክሊየር ማስወንጨፊያ የሚጠቅሙ |ሪአክተርስ´ ለመገንባት ያስችላቸዋል፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ  ከሰሜን ኮሪያ በተገኘ ፕሮግራም በመታገዝ፣ ኢራንም የኒውክሊየር መሣሪያ መፈብረክ የሚያስችል ዕውቀት ታገኛለች ሲል ጋዜጣው አትቷል፡፡
ሰሜን ኮሪያ በ2006 እና በ2009 የኒውክሊየር መሣሪያ ሙከራ ብታደርግም፣ እስካሁን የኒውክሊየር ቦንብን ስለመስራቷ የጠቆመው ነገር የለም፡፡ የኒውክሊየር ኤክስፐርቶች እንደሚናገሩት፤ አገሪቷ ለ10 የኒውክሊየር ጦር መሣሪያ ማምረቻ በሚሆን ደረጃ ላይ ትገኛለች ይላሉ፡፡ ነገር ግን አገሪቱ ይህን አቅሟን ወደ ሚሳየል እንዳልቀየረች ይገልፃሉ፡፡
ሰሜን ኮሪያ ሁሌም ቢሆን የኒውክሊየር መሣሪያ ባለቤት ለመሆን ያላትን ፍላጎት አንድም ጊዜ ቢሆን ሚስጢር አድርጋው አታውቅም፡፡ በአንፃሩ፤ አሁን በምዕራባዊያን የሚደርስባትን ክስና ጫና እንዳለ ቢሆንም፣ የኒውክሊየር ጦር መሣሪያ የመገንባት ፍላጎት የለኝም፤ በማለት ክሱን ታጣጥላለች፡፡ ኢራን ሁሌም የኒውክሊየር ፕሮግራሟ ዓላማው የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ነው ብትልም በአንፃሩ ዩራኒየም ማበልፀጓን እንድታቋርጥ የሚደረግባትን ጫና አትቀበልም፡፡
ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ፤ በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት፣ የኢራን ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባና አገሪቷ የኒውክሊየር ሚሳይል ለመገንባት የሚያስችል አመቺ ሁኔታ ላይ እንደምትገኝ ጠቁሟል፡፡
ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ከምዕራባዊያን የስለላ ተቋማት ባገኘው መረጃ መሠረት፣ ኢራን ዩራኒየምን ለአመታት ለማበልፀግ ጥረት ስታደርግ መቆየቷን ጠቁሞ ዓላማዋም ለኒውክሊየር ጦር መሣሪያ መስሪያ ለመጠቀም እንደሆነ ገልጿል፡፡ ነገር ግን ኢራን አሁን የተሰነዘረባትን ክስ መሠረተ ቢስ በማለት በተደጋጋሚ አጣጥላለች፡፡
የኒውክሊየር ጦር መሣሪያ መስፋፋት ኤክስፐርት የሆኑት ማርክ ሬትዝፖትሪክ በበኩላቸው ሲናገሩ፤ ኢራንና ሰሜን ኮሪያ የኒውክሊየር የጦር መሣሪያን በትብብር ስለመስራታቸው ቁልጭ ያለ መረጃ ባይኖርም፣ ሁለቱም አገራት ለኒውክሊየር ግንባታ የሚያገለግሉ መረጃዎችን በመቀያየር የጦር መሣሪያ ንግድ በማድረግ የተካኑ በመሆናቸው ባላስቲክ ሚሳየልን ለኒውክሊየር ኃይል ሊጠቀሙ መቻላቸው አያጠራጥርም ብለዋል፡፡ ማርክ ፊትዝፖትሪክ አያይዘውም፣ የምዕራባውያን የስለላና የደህንነት ተቋማት ኢራንና ሰሜን ኮሪያ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ በጥንቃቄ ሊከታተሉት ይገባል፣ ምናልባትም፣ ማንኛውንም ከኒውክሊየር ጦር መሣሪያ ጋር የተገናኘ ሚስጢራዊ ንግድ ለማወቅ የስለላ ተቋማቱ ከጭድ ውስጥ መርፌ የመፈለግ ያህል ከፍተኛ ጥረት ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል፡፡
በአንድ ወቅት፤ ጆርጅ ቡሽ |የሴጣን አክሲሶች´ ያሏቸው እነዚህ አገራት፣ የሚፈጥሩት ወዳጅነት በቀላሉ ሊታይ እንደማይችል የሚታወቅ ሲሆን፣ ሁለቱም አገራት ከምዕራባዊያን በተቃራኒ የተሰለፉ በመሆናቸው ለዓለም ስጋት መሆናቸው አያጠያይቅም፡፡


 

Read 6968 times Last modified on Saturday, 24 September 2011 10:38