Administrator

Administrator

 ጥጋዊ፣ ጽንፋዊው፣ ዋልታዊ

          የቡድን ኅሊና -
በማህበራዊነትና በሉአላዊው ግለሰብ (Sovereign self)  መካከል ሁልጊዜ ውጥረት አለ። “እኔ” ያለ “እኛ” ትንፋሽ ሲያጥረው፣ “እኛ”ም “እኔ” ከሌለ ህልውናም የለውም። ተፈላላጊም ናቸው፣ ተጠፋፊም ናቸው። “እኛ” “እኔ”ን ውጦ አይጠረቃም፣ “እኔ”ም የ “እኛ” ፍላጎቱ አያቆምም። ባጭሩ ማህበራዊነት ያለ ግለሰብ፣ ግለሰብም ያለ ማህበራዊነት ሊኖሩ አይችሉም። ይሁን እንጂ ማህበራዊነትን የጠላ ግለሰብም ሆነ ግለሰብነትን ያጠፋ ማሕበረሰብ፣ አንዱ የተናጠል፣ ሌላውም የስብስብ ስነ ልቡና ቀውስ ይገጥማቸዋል። ከእነዚህ የቀውስ ምልክቶች አንዱና ግጭት ፈጣሪ ወይም የተፈጠረን ግጭት አሻቃቢ የሆነው “የቡድን ኅሊና” ግሩፕ ቲንክ ነው።
ትርጓሜው፦ “የቡድን ኅሊና ማለት ግለሰቦች በቅጡ ድብልቅ ያለ ቡድን ውስጥ ጭልጥ ብለው ሲቀላቀሉ፣ አንድ ድምጽ ለመሆን ሲባል አዙሮ ማሰብንና እውነታን ወግድ የሚልና አማራጭን የማያይ፣ “ይሆንን?” ተብሎ ያልተጠየቀ ተግባር የሚመራው አስተሳሰብ ነው።” ድንገት ማሰብ ከቻለም የሚያስበው ከእኩይ ድርጊቱ በኋላ ነው።
ክፋቱ የአንድ ዘመን ወቅት ሆኖ አለማለፉ ነው። በእኩያን የግብ መምቻ የተመረጡ ትርክቶች (Selected victims’ narrative) እየተመራ ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፍ የስብስብ ኅሊና (collective mindset) ባህል ይሆናል። በእውቀትና በኢኮኖሚ ድሆች በሆኑ አገሮች ለሰንሰለታማ ቍርቍስ ምክንያት ሆኖ የዘለቀ ቢሆንም በአጠቃላይ እውቀትና ብልጽግናም አይቸግራቸውም የምንላቸውን ምእራባውያንን የማይምር፣ የሰው ልጅ የተቻችሎ ኑሮ ጸር ነው።
አንድ ቡድን የሚከተሉት ስምንት ምልክቶች ካሉት የቡድን ኅሊና (Groupthink) እያዳበረ ነው ማለት ይቻላል።
ስምንት ባሕሪያት አሉት
ህልማዊ አይበገሬነት - Illusions of Invulnerability:
ሊደረግ አይችልም ተብሎ የሚታሰብን ተግባር ለማድረግ የሚያነሳሳ፣ ከልክ ያለፈ፣ የድላዊነት ስሜት የሚመራው ህልማዊ አይበገሬነት አለው።
ለማስጠንቀቂያዎች ምክንያት መስጠት Rationalization of Warnings:
ቡድኑ አለኝ የሚለውን ምግባር ልክነት የማይጠይቅ ስለሆነ የቡድኑ ውሳኔ በተግባር ለሚያስከትለው የሞራል እኩይ ውጤት ደንታ የለውም። “ከዚህም በፊት እንዲህ ተብሏል፣ ያኔም አሁንም ልክ” ብሎ ያልፋል።
ቸልተኛነት Complacency:
እንደ ቡድን ማስጠንቀቂያዎችን ዋጋ ያሳጣቸዋል። ቡድኑ የውሳኔውን አሉታዊ ውጤቶች ችላ ይላል።….
ባላጋራን የክፉ ተመሳስሎት ገጽታ መስጠት Stereotyping:
የጠላት ተብዬ መሪዎችን የክፉ ተመሳስሎት ገጽታ (Stereotype) እያበጁለት፣ እያሰየጠኑ (Demoniz) ወይም እያናናቍና እንደ ጅል እየቆጠሩ፣ የቡድኑ ሐሳብ አደናቃፊ እንደሆኑ እንዲታዩ ያደርጋሉ፤ እንዲህም በማድረግ ለሶስተኛ ወገን መካከለኛነት አስቸጋሪ ይሆናሉ።
የታማኝነት ተጽእኖ - Loyalty Pressure:
ውልፊጥ የሚል የቡድን አባልም ካለ ቀጥተኛ ተጽእኖ ይገጥመዋል፣ እያደርም ቡድኑ ይህንን ዓይነቱን አባል እንደ ከሀዲ እንዲቆጥረው ይደረጋል።
ራስን መገደብ/መቆጣጠር Self-Censorship:
ግለሰቦች ከቡድኑ የጋራ ስምምነት እንዳይወጡ ራሳቸውን ይቆጣጠራሉ። … ከቡድኑ የተለየ ማስተዋል እንዳላቸው ቢያውቁም ግለሰቦች ይህንን በመግለጥ መሳለቂያ ላለመሆን ራሳቸውን ያግታሉ።
ቡድኑ አንድ ድምጽ ያለው እንደሆነ የሚያስብ ቅዠት አለው Illusion of Unanimity:
የቡድን ኅሊና፣ ቡድኑ አንድ ድምጽ ያለው እንደሆነ የሚያስብ ቅዠት አለው። ይኽም በከፊል ግለሰቦች ለቡድኑ ያላቸውን ታማኝነት የሚያሳዩበት ሲሆን ከራስ ቍጥጥርም የሚመነጭ ስለሆነ ተቃውሞ የሌለበት ዝምታ ሁሉ ስምምነት እንደሆነ ያስባሉ።
የቡድን ኅሊና ጠባቂዎች Mind-guards:
ራሳቸውን የሾሙ የቡድኑን ኅሊና ጠባቂዎችም አሏቸው። እነዚህ ጠባቂዎችም ቡድኑ ከያዘው አቋም ከውጪም ሆነ ከውስጥ የሚመነጭን ይከላከላሉ።
ቡድኑ ተከታይ ነው እንጂ ሀሳብ አፍላቂ አይደለም፣ የተጫነ ነው። አንድ ወይንም ጥቂት መሪ እንዳዘዘው ይጓዛል፣ መነሻቸው አንድ ዓይነት ማህበራዊ ወይም ርእዮተ ዓለማዊ መነሻ መሆኑ ብቻ በቂ ነው፣ ጎሳም፣ ሃይማኖትም፣ የፖለቲካ ርእዮትም ሊሆን ይችላል። አንድ ቡድን አጋጥሞኛል ለሚለው ቀውስ ፈጣን ምላሽ መስጠት አለብኝ ብሎ ሲያምን፣ በዚህ እምነት ጥላ ሥር የሚሰባሰቡ ሁሉ መጀመሪያ የሚያጡት በእርጋታ የሚገኘውን ትክክለኛ የአስተሳሰብ ደረጃ ነው።
እንዴት ይፈጠራል? እንዴትስ ለግጭት ሽቅበት ምክንያት ይሆናል?
ተጠቅተናል ብሎ በቡድን የሚያስብ አንድ ጎራ ፍርሃት፣ ጭንቀትና ቍጣ ስለለበት ፈጣኑ ተግባር አጥቂ ተብዬውን መጉዳት ነው። ለዚህ ምክንያት በመሆን ወይም ከዚህ ተግባር በኋላ ደግሞ ሃፍረትና ውርደት የተባሉ የዝቅታ ስሜቶች ስለሚኖሩ በቀል የሚል ተግባር ይከተላል፣ ይህ ደግሞ አዳዲስ ማሕበራዊ ግጭቶችን ይፈጥራል፣ ወይም የተፈጠረ ግጭትን እንዲያሻቅብ ያደርጋል። ትንንሽ ቡድኖች፣ ተቋሞች፣ ወይም አገሮች፣ በጣም ተፎካካሪ የሆነ ግጭት ውስጥ ሲገቡ ከግጭቱ በፊት ከነበራቸው ሁኔታ በእጅጉ በብዙ ነገር በፍጥነት ይቀየራሉ፣ ይኽም ቅያሬአቸው ለግጭት ማሻቀብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል።
ጥጋዊ፣ ጽንፋዊው፣ ዋልታዊ ይሆናል፦ ውይይቶቻቸውና የቡድኑ አባላት በግንዛቤአቸውም ሆነ በባህሪያቸው ያከረሩና ጠላት ተኮር ይሆናሉ፦ አንድ ርእሰ ጕዳይ በቡድኑ መካከል ሲወሳ አባላት አባላት ቀድሞ ከነበራቸው ግንዛቤ የበለጠ የጠነከሩ ይሆናሉ፤ ከቡድናቸው ያልተቃረነ ተጨማሪ ማጠናከሪያ ያገኛሉ፤ እያንዳንዱም የሚያደርገው አስተዋጽኦ ቡድኑን የበለጠ የሚያከር እንዲሆን በማድረግ የቡድኑ አጠናካሪ በመሆን ተቀባይነት ማግኘት ይፈልጋል። ጥላቻና አለመተማመንም ወደዚያኛው ጎራ ይወረወራል።
ደንብ ይፈጥራል፦ ውዝግቡን በሚመለከት የቡድኑ ግንዛቤ በአብዛኛው አባላት አንድ ዓይነትነት ያለው ልማዳዊ ይሆናል። ወደ ሌላው ያለው አመለካከት አሉታዊ ግንዛቤ ያለው፣ የሌሎችን ጉዳት እንደትርፍ የሚቆጥርና (ዜሮ ሰም) እነዚህም ነገሮች በተፈጸሙ መጠን የጥንካሬና የድለኝነት መረጋጋት ስሜት የሚኖረው አስተሳሰብ ነው፣ እንዲህ ዓይነቱም ልማድ (ኖርም) የተፈጠረን ግጭት አሻቃቢ ይሆናል።
የማጥፊያ ግቦችን ያዳብራል፦ በግጭት ጊዜ ሌሎችን ማሸነፍ ወይንም ማጥፋት ቡድናዊ ተግባር ይሆናል። ይህ ተግባር ዑደታዊ ስለሆነ ያለፈ የቡድኑ ልምድ ይኸው ከሆነ አሁንም ግጭት ሲፈጠር እዚያው ማሸነፍና ወይም ማጥፋት ዑደት ውስጥ ይገባል። ይህ የቡድን ኅሊና የሚመራው ተግባር ቢያስፈልግ ከራሱ ውስጥ ንኡስ ቡድን በመፍጠር በግድ አሸናፊ ቡድን ይፈጥራል። የተፈጠረውን ግጭት ማሻቀብም በራሱ እንደ ድል ይቆጠራል።
የተመሳስሎት ግንባር ይፈጥራል፦ ይህ ግንባር ነክ ገጽታ አባል ማራኪ ነው። የተመሳሰለ ቡድን ከተሰባጠረ ቡድን የሚለየው ሌላውን ቡድን እንደ ተፎካካሪ ሳይሆን፣ እንደ ተቃዋሚ ስለሚቆጥር ትግሉ “ሁሉ” ዐመጻዊና አድማዊ ነው።
መለዮ ባይለብስም ይህ የቡድን ኅሊና ራሱን በወታደራዊ ገጽታ ያደራጃል
መደበኛ የሆኑና ተቀባይነት ያላቸው ግጭቶች ልዩ ልዩ ረብሻ አልባ ወደ ግብ መድረሻ መንገዶች ሲጠቀሙ የቡድን ኅሊና ያሰባሰበው ቡድን ያመነው ትራኬ፣ ከሃይማኖት ስለሚጠነክር ተአማኒ መሪ ተብሎ የሚሰየመው ከዲፕሎማሲ ክህሎትና ዝንባሌ ይልቅ ወታደራዊ ተክለ ማንነት ያለው ነው።    
ዓላማው መግባባት ያልሆነ ተቋማዊ አደረጃጀት ይደራጃል
አንደኛ፣ የእንቅስቃሴው ተነሳስቶት ማሸነፍና ማሸነፍ ብቻ ነው። ሁለተኛ፣ ብዙ መሪዎቹ “ረጅም ጊዜ” ባላጋራ ተብየውን ተገዳድሮ ለመጣል ሲጠባበቁ የነበሩ ናቸው።    
የቡድን ኅሊና ስህተት ብቻ ሳይሆን ክፉም ነው
የቡድን ኅሊና የማያጠፋው የለም፣ የተፈጠረው ሊያጠፉኝ ነው ከሚል ስጋት በመሆኑ ቀድሞ ማጥፋት ግቡ ነው። ጓደኝነት ትዳር ቤተሰብ፣ ቤተ እምነትንና አገርን የሚፈታ ነው። የራሳችን ኅሊና አብሮን ተፈጥሮ፣ ሳንኖርበት ዳኝነት ሳንሰጥበት፣ በጭፍልቅ ኖረን እንድንሞት የሚያደርገን፣ ያለ ዐዋጅ የተለቀቀብን ኮሚኒስት ነው፣ ይሆንን ብለን እንዳንጠይቅ፣ ነው የተባልነውን ሁሉ ይዘን እንድንንጋጋ የሚያደርገን፣ እኛው የሰጠነው እልፍ እግሮች ያለው የመዋጮ አንድ ጭንቅላት ነው። የቡድን ኅሊና ተንኮለኞች የሚፈጥሩት፣ ያልተፈጠረ ዓለም ወይም የተጋነነ ዓለም ውስጥ ገብተን፣ በህገ አራዊት እንድንኖር የሚያደርገን፣ የሕልም ዓለም ነው። ድንገት ስንባንን ያጠፋነው ጥፋት ሲታወሰን ቀጥሎ ያለውን የነቃውን ኑሯችንን ሲበጠብጠው ይኖራል።
እንዲህ ዓይነት ቡድኖች፣ የተግባሮቻቸው ገጽታ በራሱ እና በራሱ ብቻ ሲታይ ቅን ስለሚመስል ለወቀሳም ለሙገሳም አስቸጋሪ ነው፣ ከዚህም በተጨማሪ በየክስተቱ የሚሰለፉት ሰዎች በትምህርት ዘለቅነት፣ በነባርነት ወይም እንደ ገንዘብና ሥልጣን ባሉ በተመሳሳይ ማሕበራዊ እሴቶች የሚታወቁ ግለሰቦች በመሆናቸው በየአካባቢው በሚፈጠረው ችግር የፈጥኖ ደራሽ ጣልቃ ገብነታቸው ወዲያው ተቀባይነት ማግኘት ይችላል፣ የተጽእኖ አቅማቸው ግን እንደ የአካባቢው ይለያያል። አንዳንድ አካባቢዎች ትሥሥራቸው ጠንካራ ስለሆነ በቀላሉ አይደፈሩም። በግራም ሆነ በቀኝ ወደውም ሆነ ሳይወዱ፣ አስበውበትም ሆነ ሳያስቡ ግን በውጤቱ ተግባራቸው በአብዛኛው አፍራሽ ነው፣  አሰራራቸው ጀምስቦንዳዊ ነው  በድንገት ከፓራሹት እንደሚወርድ ይወርዳሉ፣ ባጭር ጊዜ ተደራጅተው የሚፈጽሙትን ፈጽመው ወደ ቀዬአቸው ይመለሳሉ፤ እንዲህ ዓይነት ኃይል ለመሆን የሚያስፈልጉ አብይ መስፈሪያዎች የሚከተሉት ናቸው፦
የተጨቋኝ/ተገፋሁ ባይ ትራኬ (Appealing narrative of the “oppressed”) እውነቱና ውሸቱ፣ የተደባለቀ ነው
የጨቋኝ ተብየው ስሱ ጎን (Vulnerability of the so called “oppressor”) ይህ የድል ተስፋ ማርኬቲንግ ማግኛ ነው።
የዘመቻ ፊት አውራሪዎች (Vanguards for a campaign)
በምግባራቸው ግብ እንጂ መርህ ጠያቂ ያልሆኑ አስተባባሪዎች (Pragmatic and goal oriented individual coordinators)
ኃይል፣ ሥልጣን፣ ታዋቂነት፣ ተጽእኖ ፈጣሪነትን የተጠሙ አንደበተ ርቱአንና ደፋር ተግታጊዎች (Power mongers, cheap popularity seekers,…) እነዚህ ራሳቸውን ሰውረው ሊቀላቀሉ ይችላሉ።  
ጥቂት የዋሃን አጃቢዎች “መናጆዎች” (Few innocent crowed)
ሌሎች ፍጆታዎችና የግለሰብ ዓይነቶች እንደ አስፈላጊነቱና በየደረጃው ጥቅም ላይ ይውላሉ፣ ዘመቻው ይዘመታል፤ የተፈለገው ግብ ዘንድ ይደረሳል:: ከዚያ በኋላ በሚኖሩ እንቅስቃሴዎች “ተመልካች አለ”፣ “ተሳስተን ሊሆን ይችላል”፣ “የምንሰራው ስራ የረጅም ጊዜ ችግር ይፈጥራል”፣ “ተዉ የሚሉንን ሰዎች እንስማ” እና የመሳሰሉት አስተሳሰቦች የሌሉበት “ቡልዶዘራዊ” አካሔድ መሔድ ነው።
በውጤቱም ዚሮ ሰም (Zero-sum)  ድምዳሜ ላይ ይደረሳል። ዋናው ቁም ነገር የግጭት ባለ ድርሻዎች በማንኛውም የድርድር መንገዶች አለመስማማት ላይ ሲደርሱ “አልቦ ግብ ድርድር”  ላይ ለመቆም ይወስናሉ (አልቦ ማለት ዜሮ ማለት ነው)። በዚህም ቡድኖች በሙሉ ይከስራሉ፣ ይሁን  እንጂ አንደኛው ወገን የሚጠቀመው፣ ከሌላው ወገን በሚቀነሰው ነገር ነው፣ ባጭሩ “ጥቅሜ ያለው ጉዳትህ ውስጥ ነው” ማለት ነው፣ ወይም “ጉዳትህ ጥቅሜ  ነው” እና “ኪሳራህ ትርፌ ነው” የሚል የግጭቱ ባለድርሻዎች አይቀሬ ጉዳት ላይ ያተኮረ የግጭት መፍትሄ ነው። እንዲህ በመሆኑ የግጭት ባለድርሻ አረጋግጦ መሔድ የሚፈልገው ጥቅሙ የሚመሰረተው በሌላኛው ወገን ጉዳት ላይ መሆኑን ነው። በፖለቲካውና በንግዱ ዓለም ይህንን ምርጫ ለመምረጥ የሚገደዱበት ጊዜ አለ። ማህበራዊ ኑሮን ግን ያንኮታኩታል።
ጥቂት እንደ መፍትሄ
የ“ባላጋራን” አመለካከት ለመረዳት መመርመር። ትክክልም ሆኖ የተገኘ ያልተመለሰ ጥያቄ ካለ መመለስ። በዚህም ሒደት ውስጥ እውቅና ሊሰጣቸው የሚገባቸው በደሎች ካሉ እውቅና መስጠት
ገንቢና የተሻለ የግጭት መንገዶችን መፍጠር ሶስተኛ ወገን መካከለኛነትን በባህላዊና በዘመናዊ መንገድም መፈጸም
የቡድን ኅሊናን የሚመሩ ሰዎችን ተጽእኖ ከመጀመሪያው መቅጨት - የቡድን ኅሊና ውጤት የሆኑ ተግባራትን በፍጥነትና በግልጽ ዋጋ እንደሚያስከፍሉ ማሳየት
ትክክለኛና ሊረጋገጡ የሚችሉ መረጃዎችን መስጠት። የማሕበራዊ ድረ-ገጾችንና የመገናኛ ብዙኻን አውታሮችን በመጠቀም ግለሰቦች ከቡድን ኅሊና ወደ ነጻ ራስ ገዝ ወይም በስምምነትና በውይይት በዳበረ የጋራ ሀሳብ እንዲያምኑ ማድረግ፣ ሆን ብሎ ሰው በመመደብ የተሳሳቱ ትራኬዎችን በጭብጦች እንደተፈተኑ በመጋበዝ የቡድን አባላት ወደ አስተውሎት የሚመጡበትን መንገድ ማመቻቸት።
የቡድን ኅሊና ወደ መዋቅራዊ ረብሻ/አመጽ/ (Structural violence) እንዳይሸጋገር የአገር ሰራዊትን፣ ፖለቲካውንና የኢኮኖሚውን መዋቅር የተሰባጠረ ቡድንን የሚያስተናግድ የሚሆንበትን ፖሊሲዎች መቅረጽ።
መካከለኛ የሆነን ቡድን ማብዛት፣ እንዲኖርም ጥረት ማድረግ፣ “ወይ ከኛ ጋር ነህ አለዚያ ተቃዋሚያችን ነህ” ከሚል አሰልቺ ሰንሰለት ተፈትቶ ሌሎችን መፍታት።

  በፍልስፍና መምህሩ ብሩህ አለምነህ የተሰኘ “ፍልስፍና 3” መጽሐፍ ላይ የዛሬ ሳምንት ከቀኑ 8፡00 ጀምሮ በብሔራዊ ቤተ-መፃሕፍትና ቤተ-መዛግብት ኤጀንሲ አዳራሽ ውይይት ይካሄዳል፡፡ በዕለቱ በመጽሐፉ 3 ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ውይይት ይደረጋል የተባለ ሲሆን ርዕሶቹም “ቅኔና ፍልስፍና” በመጋቤ ብሉይ አእመረ አሸብር፣ “ሀይማኖትና ዘመናዊነት” በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህሩ በአቶ ፋሲል መርሃዊ እንዲሁም “ሰሞነ ህማማትና የኢትዮጵያ ሙዚቃ”
በመሪጌታ ፅጌ መዝገቡ እንደሚሆኑ ታውቋል፡፡ ፍላጐት ያለው በውይይቱ ላይ እንዲሳተፍ አዘጋጅ ዘንባባ የማስታወቂያ ድርጅት ጋብዟል፡፡

 አፍሪካዊቷ ዚምባቡዌ ከአለማችን አገራት መካከል ለሞባይል ኢንተርኔት እጅግ ውድ ዋጋ በማስከፈል ቀዳሚነቱን መያዟንና በአገሪቱ ለአንድ ጊጋ ባይት ኢንተርኔት 75.20 ዶላር እንደሚከፈል አንድ ጥናት አመልክቷል፡፡
ተቀማጭነቱ በእንግሊዝ የሆነው ኬብል የተባለ ተቋም፣ በ230 የአለማችን አገራት ውስጥ የሰራውን ጥናት መሰረት አድርጎ ከሰሞኑ ይፋ ባደረገው መረጃ እንዳለው፣ ለአንድ ጊጋ ባይት የሞባይል ኢንተርኔት አገልግሎት ኢኳቶሪያል ጊኒ 65.83 ዶላር፣ ሴንት ሄለና 55.47 ዶላር፣ የፎክላንድ ደሴቶች 47.39 ዶላር፣ ጅቡቲ 37.92 ዶላር ዋጋ በማስከፈል በዋጋ ውድነት እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡
በአለማችን ለሞባይል ኢንተርኔት እጅግ በጣም አነስተኛውን ገንዘብ የምታስከፍለው ቀዳሚዋ አገር ህንድ መሆኗን የጠቆመው ተቋሙ፣ በአገሪቱ አንድ ጊጋ ባይት የሞባይል ኢንተርኔት 0.26 ዶላር ብቻ እንደሚያስከፍል አመልክቷል፡፡
ኬርጌዚስታን በ0.27 ዶላር፣ ካዛኪስታን በ0.49 ዶላር፣ ዩክሬን በ0.51 ዶላር፣ ሩዋንዳ በ0.56 ዶላር አንድ ጊጋ ባይት የሞባይል ኢንተርኔት በማቅረብ በዋጋ ርካሽነት እስከ አምስተኛ ደረጃ ይዘዋል ብሏል ጥናቱ፡፡ የሞባይል ኢንተርኔትን በርካሽ ዋጋ ከሚያቀርቡት ቀዳሚዎቹ 20 የአለማችን አገራት መካከል ግማሹ የእስያ አገራት መሆናቸውንም አክሎ ገልጧል፡፡

 ታዋቂው የፈረንሳይ የመኪና አምራች ኩባንያ ቡጋቲ የተመሰረተበትን 110ኛ አመት ምክንያት በማድረግ በልዩ ሁኔታ ያመረታትና ላ ቮይቸር ኖይር የሚል ስያሜ የተሰጣት የአለማችን እጅግ ውድ መኪና በ18.9 ሚሊዮን ዶላር መሸጧን ዋሽንግተን ፖስት ዘግቧል፡፡
ባለፈው በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ በስዊዘርላንድ በተከፈተው የጄኔቫ አለማቀፍ የሞተር አውደርዕይ ላይ ለጀመሪያ ጊዜ ይፋ የተደረገችውንና በልዩ ሁኔታ የተመረተችውን ይህችን ዘመናዊ የቅንጦት መኪና ይህን ያህል ገንዘብ ከፍሎ የገዛው ግለሰብ ወይም ተቋም ማንነት ለጊዜው ይፋ አለመደረጉን ዘገባው ገልጧል፡፡
የኩባንያው ፕሬዚደንት ስቴፋን ዊንኬልማን እጅግ የላቀ ቴክኖሎጂ፣ ወደር የለሽ ምቾትና ፍጹም ውበትን አጣምራ የያዘች የምንኮራባት ምርታችን ሲሉ በአድናቆት ያንቆለጳጰሷት  ጥቁር ቀለም ያላት ላ ቮይቸር ኖይር ባለ 16 ሲሊንደር ስትሆን 1 ሺህ 500 የፈረስ ጉልበት እንዳላትም ዘገባው አመልክቷል፡፡
መኪናዋ አንድ ለእናቱ እንደሆነችና ዳግም ተመርታ ለሌለ ሰው እንደማትሸጥ የጠዎመው ዘገባው፣ እ.ኤ.አ በ1909 የተመሰረተው የፈረንሳዩ የመኪና አምራች ኩባንያ ቡጋቲ በጀርመኑ ቮልስዋንገን ባለቤትነት እየተዳደረ እንደሚገኝም አክሎ ገልጧል፡፡


        በአለማችን ሰዎችን በብዛት ለሞት በመዳረግ  የልብ ህመም ቀዳሚውን ስፍራ እንዲሚይዝና በፈረንጆች አመት 2017 ለሞት ከተዳረጉት 56 ሚሊዮን ሰዎች መካከል 32.3 በመቶ ያህሉን ለሞት የዳረጋቸውም የልብ ህመም መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ አንድ አለማቀፍ ጥናትን ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ ከልብ ህመም በመቀጠል በገዳይነት ሁለተኛ ደረጃን የያዘው ካንሰር ሲሆን፣ ጥናቱ በአመቱ ለሞት ከተዳረጉት ሰዎች መካከል 16.3 በመቶ ያህሉ በካንሰር ሰሰብ እንደሞቱም ገልጧል፡፡ የመተንፈሻ አካል በሽታዎች፣ ስኳር በሽታ እንደ ቅደም ተከተላቸው 6.5 በመቶ እና 5.8 በመቶ ያህሉን ሰዎች ለሞት የዳረጉ በሽታዎች መሆናቸውንም ጥናቱ አመልክቷል፡፡ በ2017 በርካታ ዜጎችን ለሞት ከዳረጉ ምክንያቶች መካከል አንዱ የመኪና አደጋ እንደነበር ያስታወሰው ጥናቱ፣ በአመቱ በመላው አለም 1.2 ሚሊዮን ያህል ሰዎችን ለሞት እንደዳረገም አስታውቋል፡፡

 ጄፍ ቤዞስ በ131 ቢሊዮን ዶላር ዘንድሮም ቀዳሚ ናቸው

     ታዋቂው ፎርብስ መጽሄት የ2019 የፈረንጆች አመት የአለማችን ቢሊየነሮችን ዝርዝር ባለፈው ማክሰኞ ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ አሜሪካዊው ቢሊየነር ጄፍ ቤዞስ በ131 ቢሊዮን ዶላር የተጣራ ሃብት ዘንድሮም ቁጥር አንድ የአለማችን ባለጸጋ ሆነዋል፡፡
የኣማዞኑ መስራች ጄፍ ቤዞስ የኩባንያቸው የአክስዮን ዋጋ ከመጨመሩ ጋር በተያያዘ አምና ከነበራቸው ሃብት የ19 ቢሊዮን ዶላር ጭማሪ በማድረግ ዘንድሮም ቀዳሚው የአለማችን ባለሃብት ሆነው መቀጠላቸው የጠቆመው የፎርብስ ዘገባ፣ የማይክሮ ሶፍቱ መስራች አሜሪካዊው ቢሊየነር ቢል ጌትስ በ96.5 ቢሊዮን ዶላር በሁለተኛ ደረጃ ላይ መቀመጣቸውን አመልክቷል፡፡
ሌላው አሜሪካዊ ቢሊየነር ዋረን በፌት ምንም እንኳን የተጣራ የሃብት መጠናቸው አምና ከነበረው በ1.5 ቢሊዮን ዶላር ቅናሽ አሳይቶ 82.5 ቢሊዮን ዶላር ቢደርስም በፎርብስ ዝርዝር ውስጥ የሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡ የአውሮፓ ቁጥር አንድ ቢሊየነር የሆኑት በርናንድ አርኖልት በ76 ቢሊዮን ዶላር ከአለማችን ቢሊየነሮች የአራተኛነት ደረጃን ሲይዙ፣ ሜክሲኳዊው የቴሎኮም ዘርፍ ባለጸጋ ካርሎስ ስሊም በአምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡
አማኒኮ አርቴጋ በ62.7 ቢሊዮን ዶላር ስድስተኛ፣ ላሪ ኤሊሰን በ62.5 ቢሊዮን ዶላር ሰባተኛ ደረጃን ሲይዙ፣ አምና በአምስተኛ ደረጃ ላይ የነበረው የፌስቡኩ መስራች ማርክ ዙከርበርግ የሃብት መጠኑ በ8.7 ቢሊዮን ዶላር በመቀነሱ ዘንድሮ ወደ ስምንተኛ ደረጃ ዝቅ ብሏል፡፡ ፎርብስ መጽሄት ለ33ኛ ጊዜ ይፋ ባደረገው የአለማችን ቢሊየነሮችን ዝርዝር ውስጥ 2 ሺህ 153 ቢሊየነሮች የተካተቱ ሲሆን፣ የቢሊየነሮቹ አጠቃላይ ድምር የተጣራ ሃብትም 8.7 ትሪሊዮን ዶላር እንደሚደርስ ተነግሯል፡፡
የአለማችንን ቢሊየነሮች ዝርዝር ለመጀመሪያ ጊዜ ዘንድሮ የተቀላቀሉት አዳዲስ ባለጸጎች ቁጥር 195 እንደሆነ የጠቆመው ዘገባው፣ ከእነዚህ መካከል አንዱ የሆነውና 1 ቢሊዮን ዶላር ሃብት ያስመዘገበው የሪያሊቲ ቲቪ ሾው ባለቤቱ የ21 አመቱ ካይሊ ጄነር የዘንድሮው ቁጥር አንድ የአለማችን የልጅ ሃብታም ተብሏል፡፡
በዘንድሮው የፎርብስ ዝርዝር ውስጥ በድምሩ 3.1 ትሪሊዮን ዶላር ሃብት ያፈሩ 607 ቢሊየነሮችን ያካተተቺው አሜሪካ በርካታ ቢሊየነሮችን በማስመዝገብ ቀዳሚነቱን የያዘች ሲሆን፣ ቻይና 324፣ ጀርመን 114፣ ህንድ 106፣ ሩስያ 98 ቢሊየነሮችን በማስመዝገብ ይከተላሉ፡፡ በ16.6 ቢሊዮን ዶላር የተጣራ ሃብት ያፈሩት ናይጀሪያዊው ቢሊየነር አሊኮ ዳንጎቴ አምና ከነበሩበት የ103ኛነት ደረጃ በእጅጉ መሻሻል በማሳየት ዘንድሮ 64ኛ ደረጃን የያዙ ሲሆን፣ የአፍሪካ ቁጥር አንድ ባለጸጋ ሆነው ከመቀጠልም ሆነ በዝርዝሩ ውስጥ ከተካተቱት 13 ጥቁር ቢሊየነሮች መካከል አንደኛው ከመሆን የሚያግዳቸው ግን አልተገኘም፡፡  3.1 ቢሊዮን ዶላር የተጣራ ሃብት ያፈሩት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ አምና ከነበሩበት የ766ኛ ደረጃ ወደ 715ኛ ደረጃ ከፍ ማለታቸውን ተነግሯል፡፡
በዘንድሮው ዝርዝር ውስጥ ከተካተቱት የአለማችን ቢሊየነሮች መካከል 252 ሴቶች ሲሆኑ፣ አሜሪካ 87፣ ጀርመን 30፣ ቻይና 26 ሴት ቢሊየነሮችን በዝርዝሩ ውስጥ በማካተት ቀዳሚ ሆነዋል፡፡
በዝርዝሩ ውስጥ ከተካተቱት ቢሊየነሮች መካከል 994 ያህሉ የሃብት መጠናቸው አምና ከነበረበት ቅናሽ ማሳየቱን የጠቆመው ፎርብስ፣ ሃብታቸው አምና ከነበረበት በእጅጉ ቀንሶ በቢሊዮን ከመቆጠር ወደ ሚሊዮን የወረደባቸው 247 ያህል ባለሃብቶች ደግሞ ከዝርዝሩ ውጭ መደረጋቸውን አመልክቷል፡፡


  ከዕለታት አንድ ቀን ባልና ሚስት ማሳቸውን ሊያፀዱ እሳት ጫሩበት፡፡ ማሳው እንደ ሰደድ እሳት ተያያዘ፡፡ ለካ አንድ እንስሳ እንዳጋጣሚ ማሳው ውስጥ ኖሮ፣ ሰደድ እሳቱ ያዘው፡፡ ተቃጠለ፡፡ ራሱን ለማዳን ካለመቻሉ የተነሳ፣ ደህና ኦሮስቶ ጥብስ መስሎ ቁጭ አለ፡፡ ባልና ሚስት ደግሞ ርቧቸዋል፡፡
ባል ለሚስት - መቼም እንደዚህ ተርበን ይሄን የመሰለ አሮስቶ አንምርም
ሚስት - እኔማ እንደ ጉድ ነው የሞረሞረኝ
ባል - በይ እናወራርደዋ! ትሪም ቢላም አቀራርቢያ፡፡
ሚስት  ስትበር ሄደች፡፡
ሁሉም ነገር ቀራረበና እስኪጠግቡ ኮመኮሙት፡፡
ከዚያም ባል፤
እንግዲህ ስለዚህ ነገር ትንፍሽ ትይና ወየውልሽ
ሚስት - ኧረ እኔ ምን ቆርጦኝ!
በነጋታው ግን፤
ሚስት አላስቻላትምና በቀጣዩ ቀን፤ (በዜማ)
“ትላንትና ማታ የበላነው ሲሳይ” ብላ ጀመረች
ባል፤
አባይ!
ሚስት
ሸሆናው ድፍን አይደለም ወይ?
ባል፤
አባይ!
ሚስት
አንቱ ወላዋይ፤ ሊክዱኝ ነወይ?
ባል
አሁን ምን አስለፈለፈሽ
ሆድሽን ረገጡሽ ወይ
ሚስት
ዕውነቱን መናገር ነውር ሆነ ወይ
ባል
ይልቅ ተመከሪ
ሚስት
ምን ላድርግ እሺ?
ባል
ሰው ሳይሰማ ሰው ሳያይ
እብስ ጥርግ አርገሽ ወዲያ ጣይ!
***
ከቶም በምሥጢር የሠሩትን በአደባባይ ማውጣት የሚያጣላና የሚያቆራርጥ ጉዳይ ነው፡፡ ወይ ከናካቴው አለመመሳጠር፡፡ ወይ ኃላፊነቱን ማሰብ፡፡ ወይ በግልጽ “መናገሬ ነው” ብሎ ለተዋዋይ ወገኖች ማሳወቅ፡፡ እንጂ ቀን አመቸኝ ብሎ በሌላው ወገን ላይ ጥቅም ማካበት እጅግ ጐጂ ነው፡፡
የጥንቱ ሻምበል አፈወርቅ ዮሐንስ በነበረው የግጥም መድብል፤
“…ቅንዝንዝንና የቀን ጐባጣን
ስቀህ አሳልፈው ቢያምርህ ሰው መሆን”
ይለናል፡፡
“እላይ አንዳንድ ነገር
አለ አንዳንድ ነገር
በዚህ ቢሉት በዚያ ከመሆን የማይቀር..” የሚሉን ደግሞ ገጣሚና ደራሲ ከበደ ሚካኤል ናቸው፡፡
ከሁሉም እንማራለን፡፡ የሁሉንም ትምህርት ሥራ ላይ ለማዋል መሞከር መልካም መሆኑን እናውቃለን!
መንገዳችን ዛሬም ረዥም ነው፡፡ የበለጠ ረዥም የሚያደርገው ደግሞ ትውልድ የመቅረጽ ኃላፊነታችንን በቅጡ ባለመወጣታችንም ጭምር ነው፡፡ በትምህርት ያልታገዘ ትውልድ፣ ነገውን በሚገባ ስለማያስተውል ይደነጋገራል፡፡ ተስፋውን አያነብም፡፡ አገሩን ወደ ውስጥ ከማየት ይልቅ ውጪ ውጪውን ብቻ ያያል፡፡ በትምህርቱ ደካማ ይሆናል፡፡ ውጪ አገር ወርቅ ይታፈሳል ብሎ ያልማል!
ታላቁ ኢኮኖሚስት ካርል ማርክስ፤ (ፍትጉ እንደተረጐመው)
“እኔ መች ፈልጌ ህይወት ያለችግር
መንፈሴስ መች ሸቷት እራሷ ግርግር
አንፈልግም እኛ አሳረኛ ህይወት
የተሞነጨረች ባሣረኛ ብዕር
ይኑር እልህ ቁጭት ንዴትና በቀል
ህይወቴ ትሞላ ትሁን የትግል ድል” ይላል፡፡
ባሁኑ ጊዜ ስለ ሌሎች ክፉ ክፉውን በማውራት፣ ንፁህ ለመምሰል የሚሞክሩ በርካቶች መሆናቸውን እንገነዘባለን፡፡
ራስን መልካም አድርጐ የመቅረፅ ክህሎትን መቀዳጀት እንጂ ሌሎችን ማንቋሸሽን እንደ ሥራ በመያዝ ፍሬ ማፍራት አይቻልም፡፡ ይልቁንም “ይች ጐንበስ ጐንበስ፣ ሳር ፍለጋ ሳትሆን ዱባ ለመስረቅ ነው” የሚለው ተረት ሰለባ መሆናችንን በቅጡ የሚያረጋግጥ ነው!!
ከዚህ ይሰውረን!

ላለፉት 20 ዓመታት ገደማ “አዲስ አድማስ” ጋዜጣን ሲያሳትም የቆየው የ“አድማስ አድቨርታይዚንግ” ዋና ሥራ አስኪያጅ ላይ ፍ/ቤት የሰጠውን ፍርድ የተከሳሽ ጠበቃ “ህጋዊውን ሥርዓት የጣሰ ነው” ሲሉ ተቃወሙ፡፡
ከትላንት በስቲያ፣ የ2005-6 ዓ.ም የሽያጭ ሂሳብ የተሟላ አይደለም በማለት ፍ/ቤት በአድማስ አድቨርታይዚንግ ስራ አስኪያጅ ወ/ት ገነት ጎሳዬ ላይ የአንድ ዓመት ተኩል እስር የወሰነ ሲሆን፣ “የሚያስከስስ ማስረጃ አልቀረበበትም ተብሎ በተተወ ጉዳይ ላይ የተወሰነብን የቅጣት ፍርድ ህግን ያፈርሳል” በማለት የተቃወሙት የተከሳሽ ጠበቃ በበኩላቸው፤ “ተከላከሉ በተባልንበት ጉዳይ ግን በቂ ማስረጃ በማቅረብ ክሱ ውድቅ እንዲሆን አድርገናል” ብለዋል፡፡
አቃቤ ህግ ያቀረባቸው የክስ ነጥቦች በርካታ እንደነበሩና አብዛኞቹ ማስረጃ ስላልነበራቸው፣ በአንድ የክስ ነጥብ ላይ ብቻ መከላከያ እንድናቀርብ ነበር ፍ/ቤቱ የጠየቀን - ሲሉ አስረድተዋል ጠበቃው፡፡
በየሳምንቱ ሳይሆን የአንድ ዓመት ሂሳብ የሚከፍሉ ቋሚ የጋዜጣ ደንበኞችን በተመለከተ፣ በ2005 እና 2006 ዓ.ም የተሟላ ሂሳብ ባለመመዝገብ፣ የግብር ክፍያ አጓድላችኋል የሚል የክስ ነጥብ ላይ ብቻ መከላከያ ማስረጃ እንድናቀርብ ፍ/ቤቱ በጠየቀን መሰረት፣ በቂ ማስረጃ አቅርበናል ብለዋል - ጠበቃው፡፡
“የዓመት ሂሳብ የሚከፍሉ የጋዜጣ ደንበኞች፣ በአብዛኛው የመንግስትና አለም አቀፍ ተቋማት ትልልቅ ኩባንያዎችና ድርጅቶች መሆናቸውን ጠበቃው ገልፀው፣ ሳይመዘገብ የቀረ ሂሳብ እንደሌለ በበቂ ማስረጃ አስረድተናል፤ ፍ/ቤቱም ይህን በማረጋገጥ ተቀብሎታል” ብለዋል፡፡
“ይህ ከሆነ በኋላ ግን፣ ቀደም ሲል መከላከል ሳያስፈልገን በተተወና፣ ተከላከሉ ባልተባልንበት ሌላ የክስ ነጥብ ላይ ፍ/ቤት የቅጣት ውሳኔ አስተላልፎብናል” ሲሉ ጠበቃው ገልፀው፤ “በህግ የተከለከለና ህጋዊውን ስርዓት የጣሰ ውሳኔ ነው፤ ተከሳሽ ማስረጃ የማቅረብና የመከላከል መብት ተነፍጎ ነው፣ ያለ ዳኝነት ፍርድ የተወሰነብን” ሲሉ ጠበቃው ተቃውመውታል፡፡     

Wednesday, 06 March 2019 10:32

የግጥም ጥግደም በቃል አይገባም!ቀይ ነው አሉ እንጂ ቀይም መልክ የለውም
ቀይ ፅጌ ነው ቢሉም፣ ቀይ ውበት የለውም
ዕውነት እንደቃል ግን መኖሩ ይከብዳል
ስዕልም ሲቀባ ቀላል ነው እንዳበባ፣ ቀላል እንደቀለም
አድዋማ ቀይ ነው ብሎ አይነገርም!
ደም ነው የተኳለው ያማረውም አፅም!
ቀይ ሞትን አያቅም ቀለም የለውም አፅም!
አበውን ነው እንጂ እኛን ገልፆ አይረካም!
ከአድዋ፤ እስከ ኮሚውን ድንበር
ኸማህል እስከ ዳር አገር
ስንቱ ቆስሎ
ስንቱ ሞቶ
እናት አባት ተሰውቶ
“እናትና አባቴን በጊዜ ቀብሬ
መንግስት እጦራለሁ አንጀቱን አስሬ”
ተብሎ ተብሎ ሁሉ መንዝሮ ዘር
በሞተችውማ አገር ትግል ያልነው ግርግር
ህይወት ባወራንበት ሞት - ቀመር
ያፈራን መስሎን ስንቀብር
ስናደነቁር በፍቅር
ስንደነቁር በጦር ጣር
ኖርን ስንል በሞት ዳር
ሞትን ቋምጠን ሳንሞት
ተምታቶ ቀብርና ዕርገት
ያየን መስሎን አለማየት
ዕድገት ብለን አለ - መክሊት
ኑሮን መጮህ እንደዘበት በባዶ አንጀት ፍል መለከት
የለም የዛን ያህል መርገምት!!
መርገምት አልሻሻል አለን
መርገምትን አጉል ለመድን!
ነፃነት አለን እያልን
ባንዲራም አለን እያልን
መንገድም አለን እያልን
ብርሃን አፀናልን እያልን
ፍፃሜው ግን ጨለመብን!!
ይህ ትዝብትም ብርሃን ነው፣ ድንገት ለነገ ቢሆነን!
ማፅንስ እንጂ ጨንግፈን
አልመን፤ መተኮስ እምቢኝ ብሎን
ፍሬ እንዴት እሺ ይበለን?!
ፍቅርም እኛን ባከለ
ፍትህ እኛን በመሰለ
እኩልነትም ከኛ እኩል፣ ስለ እኩልነት ባወቀ
አድናቆት ከራሱ በላይ፣ ድንቅነትን ካሳለቀ
ዕውንም ሞትስ ራሱን እንጂ እኔና አንቺን የት አወቀ፣
ይሄን ያለ በምድር እንጂ፣ በገሃነም መች ፀደቀ?
እስቲ እንንቃ ጎበዝ ለነገዋ ፀሐይ
እንንጋም አንንጋም ትታይም አትታይ!
“ጥንትም ወርቅ በእሳት እኛም በትግላችን
እየተፈተንን”
ወደድሽም
ጠላሽም
ብትመጪም ብትቀሪም
 “እናሸንፋለን
እናቸንፋለን!”
ትላንትም ብለናል    ብለን ተፈጠምን
ዛሬም እንላለን፡-     የፍትጉ እጅ ነን!
“ከማዕበል በፊት የባህር እርጋታ
ከመናገር በፊት የአርምሞ ፀጥታ
ዛሬም ያገሬ ሰው ያንዳፍታ ዝምታ፡፡
ነገ ግን ይዋጋል መታገሉ አይቀርም
ታግሎም ያቸንፋል አንጠራጠርም!!”
ብለን ነበር አሁን ያው ነው ቃሉ ብሂሉ
መቼም መቼም ቢሆን፣ አይቀርም
ትላንት ነገ ያልኩት ለካ ዛሬ ሆነ
ያለፈው በአሁን አፍ ይሄው ተኮነነ
የላዩ ስር ሆኖ የስሩ ተጫነ!
ገዳሙ ዕምነት በቃው ከተማው መነነ
አድዋችን ይሄው ነው
እኛ እሱን ሆነናል እሱም እኛን በሆነ!
የካቲት 6 ቀን 2011 ዓ.ም     

በሰምና ወርቅ ኢንቴርቴይንመንትና ኢቨንትስ አዘጋጅነት በየወሩ የሚካሄደው 15ኛው ዙር “ሰምናወርቅ” የኪነ ጥበብ ምሽት የፊታችን ሐሙስ የካቲት 28 ቀን 2011 ዓ.ም ከቀኑ 11፡00 ጀምሮ በቫምዳስ መዝናኛ ማዕከል ይካሄዳል፡፡በዕለቱ ዶ/ር ስርግው ገላው፣ ዶ/ር ዕሌኒ ገ/ መድህን፣ ወ/ሮ ሰሎሜ ታደሰ፣ ፀሐፊ ተውኔትና አዘጋጅ መዓዛ ወርቁ፣ መምህርት ዕፀገነት ከበደ፣ጋዜጠኛ ደግአረገ ነቃጥበብ፣ ተማሪ ዮናስ ዘውዴ ኮሜዲያን ምትኩ ፈንቴ፣ ገጣሚ የዓለምወርቅ አየለ እና ሌሎችም የጥበብ ሰዎች በመሶብ ባህላዊ ባንድ ታጅበው ስራቸውን እንደሚያቀርቡ አዘጋጆቹ ገልፀዋል፡፡

Page 9 of 428