Administrator

Administrator

ታዋቂዋ አሜሪካዊት የፖፕ ሙዚቃ አቀንቃኝ ሪሃና የቤተሰቡ ስያሜ የሆነውን ፌንቲ የሚል ቃል ለኩባንያው ስያሜነት በመጠቀምና የኩባንያው ባለድርሻ ወይም የስራ አጋር እንደሆንኩ በማስመሰል ዝናዬን ተጠቅሞ በስሜ በመነገድ ያልተገባ ጥቅም አግኝቷል በማለት በወላጅ አባቷ ሮቢን ፌንቲ ላይ ክስ መመስረቷ ተነግሯል፡፡
ፌንቲ የሚለውን ቃል ለንግድ ምልክትነት ወይም ለኩባንያ መጠሪያነት የመጠቀም የባለቤትነት መብቱ የሪሃና እንደሆነ የዘገበው ቢቢሲ፤ ወላጅ አባቷ ግን በ2017 ፌንቲ ኢንተርቴይንመንት የተባለ የመዝናኛው መስክ ኩባንያ ከማቋቋም አልፎ እሷ በማታውቀው መልኩ በስሟ የሙዚቃ ጉዞ ለማዘጋጀት ከሌሎች ኩባንያዎች ጋር ከ15 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚገመት የድብቅ ድርድር እስከማድረግ መድረሱንና ድምጻዊቷም በዚህ ድርጊቱ አባቷን መክሰሷን አመልክቷል፡፡
አባትዬው የድምጻዊቷን የንግድ ምልክት ከመጠቀም ባለፈ ታዋቂነቷን ተጠቅሞ እሷ በማታውቀው ሁኔታ በስሟ የንግድ ድርድር ማድረጉ ህገወጥ ድርጊት እንደሆነ በግለሰቡ ላይ የተመሰረተው ክስ ያስረዳል፡፡
አለማቀፍ ዝናን ያተረፈቺው ድምጻዊቷ ሪሃና “ፌንቲ ቢዩቲ” እና “ሳቬጅ ኤክስ ፌንቲ”ን ጨምሮ በፌንቲ የንግድ ምልክት ስር ባቋቋመቻቸው የተለያዩ የንግድ ኩባንያዎች ትርፋማ ስራዎችን ስታከናውን እንደቆየችም ዘገባው አስታውሷል፡፡

 አለማቀፉ የብድር መጠን በከፍተኛ ሁኔታ በማደግ 244 ትሪሊዮን ዶላር መድረሱንና ይህም መጠን ከአጠቃላዩ አለማችን ኢኮኖሚ ከሶስት እጥፍ በላይ እንደሚበልጥ መነገሩን ብሉምበርግ ዘግቧል፡፡
ኢንስቲቲዩት ኦፍ ኢንተርናሽናል ፋይናንስ የተባለው ተቋም ባለፈው ማክሰኞ ይፋ ያደረገውን አለማቀፍ ሪፖርት ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፤ በአለማቀፍ ደረጃ የብድር መጠን ከአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት በ318 በመቶ ብልጫ ይዞ ይገኛል፡፡
የአለማችን አጠቃላይ ብድር በ2018 የመጀመሪያዎቹ ወራት 247.7 ትሪሊዮን ዶላር በመድረስ ክብረወሰን አስመዝግቦ እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፤ በሶስተኛው ሩብ አመት ወደ 244 ትሪሊዮን ዶላር ዝቅ ካለው አጠቃላይ አለማቀፍ ብድር ውስጥ 65 ትሪሊዮን ያህሉ የመንግስት ብድር ሲሆን፣ 72 ትሪሊዮን ያህሉ ደግሞ ፋይናንስ ነክ ያልሆኑ ኩባንያዎች ብድር ነው ብሏል፡፡
የብድር ወለድ መጠን በአለማቀፍ ደረጃ እያደገ መምጣቱን ተከትሎ አለማቀፉ የገንዘብ ተቋም አይኤምኤፍ በቅርቡ ባወጣው መግለጫ፣ መንግስታት የሚወስዱትን ብድር በመመጠን እያደገ የመጣውን አለማቀፍ ብድር ለመግታት የራሳቸውን ሚና እንዲጫወቱና  በዕዳ ጫና ከሚመጣ ቀውስ ለመዳን የሚያስችሉ ስራዎችን እንዲያከናውኑ ጥሪ ማቅረቡንም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

በአዲሱ የፈረንጆች አመት 2019 የአለማችን ፈተናዎች ይሆናሉ ከተባሉት ዋነኛ ጉዳዮች መካከል ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያያዥ ችግሮች ቀዳሚነቱን መያዛቸውንና እንደ ትራምፕ ያሉ ህዝበኛ መሪዎች መግነናቸውም አለማችንን እንደሚያሰጋት መነገሩን ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
ሰሞኑን ይፋ የተደረገውን የአለም የኢኮኖሚ ፎረም አለማቀፍ የስጋት ሪፖርት ጠቅሶ ሲኤንኤን እንደዘገበው፣ ከአመቱ አምስት ቀዳሚ የአለማችን ፈተናዎች መካከል አራቱ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያያዥነት ያላቸው አደጋዎች ናቸው፡፡
የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከልና የመቋቋሚያ መንገዶችን ለመቀየስ በቂ ስራዎች አለመሰራታቸው አለማችንን በአመቱ ለከፋ አደጋ ሊያጋልጣት እንደሚችል የጠቆመው ሪፖርቱ፤ የተፈጥሮ አደጋዎችም አለማችንን በከፍተኛ ሁኔታ ሊያጠቁ እንደሚችሉ አመልክቷል፡፡
ከአመቱ የአለማችን ዋነኛ ፈተናዎች መካከል አንዱ እንደሆነ በሪፖርቱ የተጠቀሰው ሌላው ጉዳይ ደግሞ፣ የአሜሪካውን ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕንና የብራዚሉን አቻቸውን ቦልሶናሮን የመሳሰሉ ህዝበኛ መሪዎች እየገነኑ መምጣታቸው እንደሆነም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

 በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ተቋማት ተቀጥረው ከሚሰሩ ሰራተኞች መካከል 33 በመቶ ያህሉ ባለፉት 2 አመታት የተለያዩ አይነት የወሲባዊ ትንኮሳ ድርጊቶች እንደተፈጸሙባቸው የሚያሳይ አዲስ የጥናት ውጤት ይፋ መደረጉን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ባለፈው ማክሰኞ ይፋ የተደረገውንና ከ30 ሺህ በላይ በሚሆኑ የተመድ ሰራተኞች ላይ የተሰራውን አዲስ የጥናት ውጤት ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፤ በርካታ የተመድ ሰራተኞች በቢሯቸውና በመስክ ስራቸውን በማከናወን ላይ እያሉ የስራ ባልደረቦችና አለቆችን ጨምሮ በተለያዩ ግለሰቦች ወሲባዊ ትንኮሳዎች እንደተደረጉባቸው ተናግረዋል፡፡
በሰራተኞቹ ላይ ወሲባዊ ትንኮሳ ፈጽመዋል ከተባሉት ሰዎች መካከል 60 በመቶ ያህሉ ወንዶች መሆናቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ ትንኮሳ ከተፈጸመባቸው መካከል በተንኳሾች ላይ እርምጃ የወሰዱት ደግሞ 30 በመቶው ያህል ብቻ ናቸው መባሉን አመልክቷል፡፡

በኢትዮጵያ አመታትን ጠብቀው የሚከበሩ ሀይማኖታዊ በዓላት ከእምነት ፋይዳቸው ባለፈ በውስጣቸው በያዙት መስህባዊ ተፈጥሮ ምክንያት በርካት የውጭና የሀገር ውስጥ ጎብኚዎችን ይስባሉ። ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ደግሞ የጥምቀት በዓል ነው። የስነ መለኮት ምሁራን ጥምቀት ለሚለው ቃል መነከር፣ መታጠብ፣ መረጨትና  የመሳሰሉትን ትርጓሜዎች ይሰጡታል፡፡ የጥምቀት ዋዜማ ከተራ ይባላል፡፡ የከተራ እለት /ጥር 10 ማለት ነው/ ከቀኑ 9 ሰዓት ጀምሮ በሚሰማው የደውል ጥሪ ታቦታቱ፤ የተለያዩ ህብረ ቀለማት ያላቸው አልባሳት በለበሱ ህዝበ ክርስቲያን ታጅበው ጉዞአቸውን ወደ ጥምቀተ ባህር ያደርጋሉ፡፡
በሀገራችን ታቦት ተሸክሞ፣ ወንዝ ወርዶ የክርስቶስን በዓለ ጥምቀት ማክበር የተጀመረው በአፄ ገብረመስቀል ዘመነ መንግስት እንደሆነ ሊቃውንት ያስረዳሉ፡፡ ይህንን ታሪክ በመከተል አፄ ነዖድም (1486 – 1500 ዓ.ም) ማንኛውም የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ተከታይ የሆኑ ሁሉ ታቦተ ህጉ ወደ ጥምቀተ – ባህሩ በሚወርድበት ጊዜ እና ከጥምቀተ – ባህሩ ወደ ቤተ መቅደሱ በሚመለስበት ጊዜ አጅቦ መውረድና መመለስ እንዳለበት አዋጅ አስነግረው ነበር፡፡ በአዋጁ መሰረትም ህዝቡ በየአመቱ ታቦተ ህጉን በማጀብ ወንዶች በጭፈራና በሆታ፣ ሴቶች ደግሞ በእልልታ ሲያከብሩ ኖረዋል ፤ አሁንም እያከበሩት ይገኛል፡፡
በከተራው ዕለት ድንኳን ተተክሎ፣ ዳሱ ተጥሎና ውኃው ተከትሮ ሁሉም ነገር ከተስተካከለ በኋላ፤ ታቦተ ህጉ የሚንቀሳቀስበት ሰዓት ሲደርስ የየቤተ መቅደሱ ታቦታት በወርቅና በብር መጎናፀፊያ እየተሸፈኑ፤ በተለያየ ህብር በተሸለሙ የክህነተ አልባሳት በደመቁ ካህናትና የመፆር መስቀል በያዙ ዲያቆናት ከብረው፣ ከቤተ መቅደስ ወደ አብሕርት /መጥማቃት/ ለመሄድ ሲነሱ መላው አብያተ ክርስቲያናት የደውል ድምፅ ያሰማሉ፡፡ ምዕመናንም ከልጅ እስከ አዋቂ በአፀደ ቤተ ክርስቲያን እና ታቦታቱ በሚያልፉባቸው መንገዶች ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ እንደሚባለው ያማረ ልብሳቸውን ለብሰው በዓሉን ያደምቃሉ፡፡
ታቦታት ከቤተ መቅደሳቸው ወጥተው በህዘበ – ክርስቲያኑ ታጅበው ማደሪያ ቦታቸው ይደርሳሉ። በዚያን ጊዜ ዳቆናትና ቀሳውስት በባህረ ጥምቀቱ ዙሪያ ሆነው ከብር የተሰሩ መቋሚያና ፅናፅን እንዲሁም ከበሮ ይዘው በነጫጭና በወርቅ ቀለም ባሸበረቁ እጥፍ ድርብ አልባሳት አምረውና ተውበው፤ የክርስቶስን የጥምቀት ታሪክ የሚያወሱ ወረብና መዝሙሮችን ጣዕም ባለው ዜማ ያቀርባሉ። ሌሊቱን ስብሀተ – እግዚአብሔር ሲደርስ አድሮ ከዚያም ስርዓተ ቅዳሴው ይፈፀማል፡፡ በወንዙ /በግድቡ/ ዳር ፀሎተ- አኩቴት ተደርሶ 4ቱ ወንጌላት ከተነበቡ በኋላ ባህረ ጥምቀቱ በብፁዓን አባቶች ተባርኮ ለተሰበሰበው ህዝበ – ክርስቲያን ይረጫል፡፡ ለዚህ በዓል ህዝበ ክርስቲያኑ ልዩ ትኩረት ይሰጠዋል፡፡ ምክንያቱም በዓሉ እየሱስ ክርስቶስ በፈለገ ዮርዳኖስ የተጠመቀበትን ተምሳሌት በማሰብ ስለሚከበር፡፡
የጥምቀት በዓል ሀይማኖታዊ ስርዓቱን ከባህላዊ ወግና ስርዓት ጋር አጣምሮ የያዘ ነው፡፡ በዚህም በርካታ ብሄር ብሄረሰቦች ህብረ – ቀለማዊ የሆነ ጨዋታቸውን በልዩ ልዩ ቋንቋዎች ያቀርባሉ፡፡ በዓሉን ለማክበር ወደ ጥምቀተ ባህር የሚሄዱ ሰዎች ከበዓሉ በፊት ተዋወቁም አልተዋወቁም በዚያን ዕለት በጋራ ሆነው ጥዑም ዜማዎችን ያንቆረቁራሉ፡፡ ይህ ዕለት ማንም ሰው ሳያፍርና ሳይሸማቀቅ የውስጡን የሚገልፅበትና በጋራ የሚጫወትበት ዕለት ነው። ከዚሁ ጋር ተያይዞም በጓደኝነት ለመተጫጨት ለሚፈልጉ ወጣቶች መልካም አጋጣሚን ይፈጥራል፡፡ ህዝበ – ክርስቲያኑ ይህንን በዓል ዘርና ቀለም ሳይለዩ በአንድነት ያከብሩታል፡፡ በመሆኑም በዓሉ ህዝብን ያቀራርባል፤ የመረዳዳት ባህልንም ያሳድጋል፡፡
የጥምቀት በዓልን ለማክበር የተለያዩ ሀገር ዜጎች፣ ዲፕሎማቶች፣ አምባሳደሮችና ከፍተኛ ባለስልጣናት እንዲሁም የቤተክርስቲያን አባቶችና ምዕመናን ይታደማሉ፡፡ ይህ በዓል በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚከበር ቢሆንም በተለይ በአፄ ፋሲል መዋኛ፣ በላልይበላ፣ በመቀሌ ፣ በአክሱምና በአዲስ አበባ ከተሞች በተዘጋጀላቸው የክብር ቦታ ህዝበ – ክርስቲያኑ ከውጪ ከሚመጡ ቱሪስቶች ጋር በዓሉን በደመቀ ሁኔታ ያከብሩታል፡፡ ታዲያ በዚህ በዓል ላይ ያስገረማቸውን ነገር በማስታወሻነት ለማስቀመጥ የተለያዩ ሰዎች የፎቶና የቪዲዮ ካሜራዎቻቸውን ደግነው እያነሱና እየቀረፁ ያስቀራሉ፡፡  በመጨረሻም በሀገራችን የሚከበሩ ሀይማኖታዊ በዓላት የመረዳዳትና የመደጋገፍ ባህልን ያዳብራሉ፡፡ ከዚህም ባሻገር አገሪቱ ከቱሪዝም ኢንዱስትሪው ተጠቃሚ እንድትሆን ያስችሏታል፡፡ ስለዚህ ተገቢውን ትኩረት ልንሰጣቸው ይገባል፡፡
(ከተስፋዬ አበበ ፌስቡክ የተወሰደ)

 (ለብሩህ ዓለምነህ የተሰጠ መልስ)
                   መጋቤ ብሉይ አእመረ አሸብር


     ብሩህ ዓለምነህ ‹‹ፍልስፍና ፫፡ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የወደ ፊት ፈተና ምንድን ነው?›› በሚል ርእስ በስድስት ክፍሎችና በዐሥራ ዐምስት ርእሶች አዋቅሮ ያሳተመው መጽሐፍ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሁሉም ርእሶች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን የሚመለከቱ ጉዳዮችን የያዘ ነው፡፡ ከእነዚህ ርዕሶች ውስጥ የመጀመሪያው ክፍል ‹‹ቅኔና ፍልስፍና›› የሚል ሲሆን፣ በዚህ ክፍል ውስጥ ከገጽ 5-18 የምናገኘው ‹‹ለመሆኑ ቅኔ ፍልስፍና መሆን ይችላል?›› የሚለው ርዕስ፣ ስለ ቅኔና ፍልስፍና ግንኙነት ወይም ቅኔ ፍልስፍና ሊባል ይገባል ወይስ አይገባም በሚለው ክርክር ላይ የራሱን አቋም አቅርቧል፡፡
በመጀመሪያ፣ ብሩህ በኢትዮጵያ የፍልስፍና ታሪክ ውስጥ የራሱን አሻራ ለማኖርና የራሱን አስተዋጽኦ ለማበርከት በሚያደርገው ትጋት በጣም እደንቀዋለሁ፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ፍልስፍና›› የሚለውን መጽሐፉን ከተማሪዎቼ ጋር ሰፋ ያለ ውይይት አድርገንበታል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ፍልስፍና›› ላይ ያለኝን አስተያየት ለሌላ ጊዜ ላቆየውና ለዛሬ ግን ‹‹ፍልስፍና ፫›› መጽሐፉን አንብቤ አስተያየት ለመስጠት እግዚአብሔር ረድቶኛል፡፡
ብሩህ ‹‹ፍልስፍና ፫›› ብሎ በሰየመው መጽሐፉ ‹‹ለመሆኑ ቅኔ ፍልስፍና መሆን ይችላል?›› ብሎ ላነሣው ጥያቄ የሰጠው መልስ አሉታዊ ነው፤ ማለትም ‹‹ቅኔ ፍልስፍና መሆን አይችልም›› የሚል ነው፡፡ የደረሰበትን ድምዳሜ ሲያስረዳም ‹‹እኔ ‘ቅኔ ፍልስፍና መሆን አይችልም፤ የኢትዮጵያን ፍልስፍናም ከቅኔ ውስጥ ማግኘት አይቻልም፤ ቅኔን ወደ ፍልስፍና ማጠጋጋት ሳያስፈልግ፣ በራሱ ውበት እንደ አንድ የሥነ ጽሑፍ ዘውግነት መታየት አለበት’ ብለው ከሚከራከሩ ሰዎች ውስጥ ነኝ›› ይላል (ገጽ11)፡፡
ለዚህ ድምዳሜ ምክንያት አድርጎ ያቀረባቸው ደግሞ ሁለት ማስረጃዎች ናቸው፡፡ አንድኛው፣ የቅኔ ትርጕም ሲሆን ቅኔን እንደ ግጥም ብቻ በመተርጎምና በትርጉሙ ላይ ብቻ በመመሥረት ‹‹ቅኔ ፍልስፍና ሊሆን አይችልም›› የሚል ሐሳብ አቅርቧል፡፡ በሁለተኛነት መሠረታዊ ብሎ የጠቀሰው ምክንያት ደግሞ ‹‹ቅኔያችን የተለያዩና የተበታተኑ (ብዙ ጊዜም እርስ በእርስ የሚጣረሱ) ሐሳቦችን መያዙ ነው›› የሚለው መከራከሪያ ነጥብ ነው፡፡
ምንም እንኳን እኔ የፍልስፍና ተማሪ ባልሆንም በሥነ መለኮት፣ በማኅበረ ሰብ ሳይንስ (ሶሽዮሎጂ)፣ በሕግና በአፍሪካ ጥናት ትምህርት ባለፍኩባቸው ጊዜያት የወሰድኳቸው የፍልስፍና ትምህርቶች፣ ይልቁንም ጉዳዩ የተሻለ አውቀዋለሁ ከምለው ከቅኔ ትምህርት ጋር የተያያዘ በመሆኑ ምክንያት አስተያየት ለመስጠት በጣም ተገፋፍቻለሁ፡፡ ምንም እንኳ ለዛሬ አስተያየት የማቀርበው ከቅኔ ጋር ለተያያዘው ርዕሰ ጉዳይ ቢሆንም፣ በሂደት ግን በሁሉም የመጽሐፉ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ተመሳሳይ አስተያየት ይኖረኛል፡፡
የግእዝ ቅኔ ትምህርት የግጥም ትምህርት ነውን? ወይስ ቅኔ ግጥም ብቻ ነውን? የሚለው ሐሳብ በጣም መሰረታዊ ስለሆነ ጥያቄያችንን ከእሱ እንጀምር፡፡ ስለ ግእዝ ቅኔ ትምህርት ስንናገር፣ ስለ ግእዝ ቋንቋ ትምህርትና ስለ ሥርዐተ ትምህርቱ እንዲሁም ስለ ማስተማሪያ ዘዴው (methodology) አጠቃላይም ስለ ትምህርት ፍልስፍናው እየተናገርን ነው፡፡ በቅኔ ትምህርት ውስጥ ሃይማኖት፣ ታሪክ፣ ባህል፣ ቋንቋ፣ ዜማ፣ ሌላው ቀርቶ ኢትዮጵያዊ ማንነት ጭምር አለ፡፡ በዚህም የተነሳ ቅኔ የትምህርት ሥርዐት እንጂ ግጥም አይደለም፡፡ ‹‹ቅኔ ቤት›› ሲባልም ‹‹ግጥም ትምህርት ቤት›› ማለት አይደለም፡፡
እኔ እስከ ማውቀው ድረስ ብሩህ በመፅሀፉ ውስጥ መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ የሰጡትን ትርጉም ጠቅሶ ማርዬ ይግዛው ያቀረበው ‹‹ቅኔ አንድ ሰው ስለ አንድ ነገር ወይም ድርጊት ያገኘውን ዕውቀት ወይም ምሥጢር ምሳሌ መስሎ፣ ምስጢር ወስኖ፣ቃላት መጥኖ በአዲስ ግጥም የሚያቀርብበት ድንገተኛ ድርሰት ነው›› (ገጽ 10)  የሚለው ትርጕም ቅኔን ለመግለጥ በቂ አይደለም፡፡ ይህ ትርጉም፣ የቅኔ ድርሰትን እንጂ ራሱን ቅኔን አይተረጕምም፡፡ የአንድ ሰው ትርጕም መሆኑ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የግእዝ ቅኔን የማይገልጥ ጠባብ ትርጕም ነው፡፡
የግእዝ ቅኔ ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት እንደሚረዱት ቋንቋን፣ ሃይማኖትን፣ ባህልን፣ ትምህርትን፣ የሰው ልጅ አስተሳሰብን፣ወዘተ የያዘ አንድ ራሱን የቻለ የትምህርት ይዘት፣ ሥርዐተ ትምህርትና የማስተማር ዘዴ ያለው ሥርዐት (Sysytem) እንጂ ግጥም አይደለም፡፡ በድርሰትነቱ ሲታይ፣ ግጥምነቱ በድርሰት ጊዜ ወጥ የሆነ የዜማ ስልት እንዲኖረው ለማድረግ ታስቦ የተሠራ የዜማ ልክ ያለው ስለሆነ እንጂ ቅኔና የቅኔ ትምህርት የተለካ ግጥም ብቻ መሆኑን አያመለክትም፡፡ አስቀድሜ እንዳልኩት ቅኔ የራሱ የትምህርት ይዘት፣ ሥርዐተ ትምህርትና የማስተማር ዘዴ ያለው የትምህርት መስክ (discipline or system) እንጂ በፍጹም ግጥም አይደለም፡፡ ስለዚህ ብሩህ ቅኔን በዚህ ጠባብ ትርጕም ላይ ተመሥርቶ ፍልስፍና ነው/አይደለም በሚለው ክርክር ላይ አቋም መውሰዱ ተገቢ መስሎ አልታየኝም፡፡
ኢትዮጵያዊ ሥርዐተ ትምህርት የሚባለው የንባብ፣ የዜማ፣ የትርጓሜ መጻሕፍትና የሃይማኖት፣ እንዲሁም የሥርዐተ ጽሕፈት ትምህርት ሁሉ በቅኔ ትምህርት ውስጥ ያለ ነው፡፡ አንድ ተማሪ ቅኔ መማር የሚጀምረው ፊደል መማር ሲጀምር ነው፡፡ ዜማ ሲማርም ቅኔን ይማራል፤ ቅኔ ሲማርም ዜማን ይማራል፤ትርጓሜ ሲማርም ቅኔን ይማራል፡፡ ያለ ቅኔ ትምህርት እነዚህን ሁሉ ማወቅ አይቻልም፡፡
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሥርዐተ ትምህርት የተወራረሰ፣ እርስ በእርሱ የተሳሰረ እንጂ የተበታተነ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያዊ ፍልስፍና በቅኔ ትምህርት አለ ወይ? የሚለውን አጠቃላይ ትምህርቱን አጥንቶ አለ/የለም ማለት እንጂ በአንድ ነጠላ ትርጕም ላይ ተመሥርቶ በሂደቱ ያለፉ ሰዎች ስለ ቅኔ ትምሀርት ፍልስፍናነት የሚሰጡትን አስተያየት በተቃራኒ መከራከር ጥልቀት ያለው ሐሳብ መስሎ አልታየኝም።
በኔ አስተያየት ቅኔ አንዱ የኢትዮጵያዊ ፍልስፍና ምንጭ ነው፡፡ የፍልስፍና ምንነትን በምዕራባዊው አስተሳሰብ መዝነን አንድ ፍልስፍና እናውጣ ማለት እንደማይቻልና ይሄም ሐሳብ እንደ ቀረ ይታወቃል። ኢትዮጵያዊው ፍልስፍናም ሙሉ በሙሉ የተለየ ኢትዮጵያዊ መሆን እንደማይችል አምናለሁ፡፡ በዚህ መሠረት ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት በቅዱሳት መጻሕፍት፣ በታሪክ፣ በባህልና በራሳቸው አመክንዮ በደረሱበት ደረጃ ያደራጁት የእምነታቸው፣ የትምህርት ፍልስፍናቸውና ዘዴያቸው፣ የፈጠራ ችሎታቸው፣ የሚገለጥበት የግእዝ ቅኔ ሰፊ የትምህርት ዘርፍ እንጂ ግጥም አይደለም፡፡ ስለዚህ ቅኔ ግጥም ነው በሚል ትርጉም ላይ ተመሥርቶ የግእዝ ቅኔ የፍልስፍና ምንጭ አይሆንም የሚለው አቋም አላሳመነኝም፡፡
ሁለተኛው የብሩህ ምክንያት፣ ቅኔያት የተበታተኑ ብሎም እርስ በእርሳቸው የሚጣረሱ ሐሳቦችን የያዙ ናቸውና ‹‹ቅኔ ፍልስፍና አይደለም›› የሚል ነው፡፡ ቅኔያት የሚላቸው ድርሰቶችን በተናጠል እንደ ሆነ መረዳት ችያለሁ፡፡ ለምሳሌ፣ አንድ ጉባኤ ቃና ወይም መወድስ ድርሰት በራሱ ቅኔ ይባላል፡፡ ከዚህ አንጻር የአንድ ሰው ቅኔ ከሌላ ሰው ቅኔ ጋር ሙሉ በሙሉ የሚቃረን አቋም ሊኖረው ይችላል፡፡ የአንድ ሰው ፍልስፍና ከሌላ ሰው ፍልስፍና ሊለይ ቢችል ብሎም ቢቃረን እንኳን ፍልስፍና አይባልም ማለት አንችልም፡፡ ይህን ብሩህም በጽሑፉ በግልጥ አስፍሮታል፡፡
ነገር ግን፣ የአንድ ሰው ሐሳብ በድርሰቶቹ ከተቃረኑ ወጥ የሆነ ፍልስፍና አለው ማለት አንችልም፡፡ ብሩህ እንዳለው፤ ተዋነይ በቅኔዎቹ ወጥ የሆነ ሐሳብ አይታይበትምና ፈላስፋ መባል የለበትም፤ ቅኔውም ፍልስፍና አይባልም ነው፡፡ የተዋነይ ሐሳብ ብሩህ እንዳለው በየቅኔው መሠረታዊ የሚባል ሐሳቡን እየቀየረ የሚመጣ ከሆነ፣ ትክክል ነው ቅኔው ፍልስፍና ለመባል መጀመሪያ ወጥ የሆነ ሐሳብ ሆኖ መገኘት አለበት፡፡
መጀመሪያ ብሩህ የጠቀሳቸው ሁለት የተለያዩና ‹‹እርስ በእርሳቸው የሚጣረሱ›› የተባሉ ቅኔዎችን እንመልከት፡፡
የአምን ወይገኒ
ኵሉ ዓለም በዘፈጠረ ለሊሁ፡፡
ብዙኃን እንዘ ይገንዩ ይስግዱ ቅድሜሁ፡፡
ለነጽሮ ዝኒ ከመ እስራኤል ይፍርሁ፡፡
ሙሴ ፈጠረ ፈጣሪሁ፡፡
ወፈጣሪ ፈጠረ ኪያሁ፡፡
(ትርጕም)
ብዙዎች እየተገዙ በፊቱ ይሰግዱ ዘንድ ዓለም ሁሉ ራሱ በፈጠረው ያምናል፤ ይገዛልም፡፡
ይህን ነገር ለማስተዋልም እስራኤል ይፈሩ ዘንድ ሙሴ ፈጣሪውን ፈጠረ፤ ፈጣሪም ሙሴን ፈጠረው፡፡  
ተቃራኒ ብሎ የጠቀሰው ቅኔ ደግሞ በአማርኛው እንደጠቀሰው
ሰው-ባዶ ሰው፣ ራቁት ሰው፤
በረዶ ለበረዶ፣መብረቅም ለመብረቅ ተገዥ እንዳለው፤
በኀጢአተኛው የሚፈርድበት፣
አምላክ በኢዮር (ሰማይ) ላይ መኖሩን ልቡናህ ሲያውቀው፣
የሕይወቱ ዓመት በፍጥነት ለሚያልቅ ለዚያው ለባዶ ሰው፣
አጥንቱ መቃብር ለሚወርድ ለዚህ ለራቁት ሰው፣
በወርቅ ለመገዛት ልብህ እንዴት ከጀለ፣ ነገ አፈር ለባሹ አምላክ እንዲሆነው፡፡
ነገር ግን፣ እኔ እንደተረዳሁት እነዚህ ሁለቱ ቅኔዎች የሚቃረኑ አይደሉም፡፡ ብሩህ በገጽ 13 የጠቀሰው ‹‹ሙሴ ፈጠረ ፈጣሪሁ፤ ወፈጣሪ ፈጠረ ኪያሁ›› የሚለው ቅኔና በገጽ 15 የጠቀሰው ‹‹ሰው ሁሉ ፈጣሪ (አምላክ) እንዳለ መካድ አይችልም›› የሚል ድምዳሜ ያለው ቅኔ የሚቃረን ሐሳብ የላቸውም፡፡
የመጀመሪያው ቅኔ ‹‹ፈጣሪ የለም›› አይልም። ‹‹ሙሴ ፈጣሪውን ፈጠረ›› ማለት ራሱ ሙሴ አምላክ የሚለውን ወይም ‹‹የደረሰበትን አመለከ›› የሚል ነው እንጂ አንድ ‹‹አምላክ የለም›› አይልም። የመጀመሪያው ቅኔ ዋና ሐሳብ እያንዳንዱ ሰው ፈጣሪን የሚረዳው በራሱ መንገድ ነው የሚል ነው፡፡ ለዚህም “የአምን ወይገኒ ኵሉ ዓለም በዘፈጠረ ለሊሁ” ባለው ይታወቃል፡፡ እያንዳንዱ ሰው ‹‹አምላክ ነው ብሎ ባሰበው ነገር ላይ ያምናል›› ማለት አንድ እውነተኛ አምላክ የለም ማለት አይደለም፡፡ ሙሴ የተጠቀሰው አንድን የታወቀ የእምነት መስመር ምሳሌ አድርጎ ለማሳየት ነው፡፡ ሁለተኛው ቅኔ ግን ‹‹አንድ አምላክ አለ፤ ይህም አምላክ መኖሩን ልቡናህ ያውቀዋል፤ ስለዚህ ለወርቅና ለብር ብለህ ለሰው አትገዛ›› የሚል ነው፡፡
በሌላ በኩል እነዚህ ቅኔዎች ተቃራኒ የሆኑ አቋሞችን የያዙ ቢሆን እንኳን ሁለቱም ቅኔዎች ሁለት የአስተሳሰብ መስመርን የሚገልጡ የተለያዩ ሰዎች ቅኔዎች እንጂ የአንድ ሰው ቅኔዎች ለመሆናቸው አፈ ታሪኩን ይዘን ከመከራከር ያለፈ ማስረጃ ማቅረብ አይቻልም፡፡ ራሱ ተዋነይ የተባለው ሰው ኢትዮጵያዊ ባለ ቅኔን የሚወክል የሆነ አፈ ታሪክ (ፈጠራ) እንጂ ታሪኩ የተረጋገጠ ሰው ላይሆን ይችላል፡፡
እኔ በሁለቱ ቅኔዎች ውስጥ ያየሁት ተቃርኖ፣ ሁለቱ ቅኔዎች የአንድ ሰው የተዋነይ ናቸው ባለ ሰው አእምሮ ውስጥ ያለን የአስተሳሰብ ተቃርኖ ነው፡፡ በቅኔዎች ውስጥ ተቃርኖ አለ ብሎ የሚያምነው ሰው ራሱ ቅኔዎች የአንድ ሰው ቢሆኑ እንኳን ዐሳባቸው እንደማይቃረን አለማስተዋሉን እንጂ በእርግጥም የተዋነይ ሁለት የሚቃረኑ ሐሳቦች አድርጌ አይደለም።
በቅኔ የትምህርት ሥርዐት ውስጥ አንድ ባለ ቅኔ እንዲህ አይነት ተቃርኖን የሚያስወግድባቸው የቅኔ ት/ቤት ሕጎች አሉ፡፡ በአንድ ሰው የሚታይ እንዲህ አይነት የተገለጠ የሐሳብ ተቃርኖ ይቅርና የዘዴ ተቃርኖ እንኳን ቢከሠት ምን ችግር እንዳለበት ትምህርቱ በራሱ ያስተምራል፡፡
ስለዚህ ቅኔዎች የተለያዩና የሚጣረሱ ሐሳቦችን ይዘዋል ቢባል እንኳን በተዋነይ ውስጥ ወጥ የሆነ አስተሳሰብ አለመኖሩን የሚያመለክቱ ሳይሆን ሁለት የተለያዩ ብሎም ብሩህ እንዳለው፣ እርስ በእርስ የሚጣረሱ የአስተሳሰብ መስመሮችን እንጂ የአንድን ባለ ቅኔ እርስ በእርስ የሚቃረኑ ሐሳቦች አድርጌ አላየውም፡፡
ስለዚህ፣ ቅኔን በተመለከተ ‹‹በፍልስፍና ፫›› የተነሡ መከራከሪያ ነጥቦችም ሆነ ድምዳሜው የግእዝ ቅኔን በተመለከተ ተገቢ ነው ብዬ አላስብም፡፡

 ለስምንት አመታት ወደኖረባትና ህገወጥ ስደተኛ ተብሎ ወደተመለሰባት እስራኤል በድጋሚ ለማቅናት በጉዞ ላይ የነበረው የኒጀሩ ስደተኛ ኢሳ ሙሀመድ፤ ለቀጣይ ጉዞ እረፍት ባደረገበት የቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ በቁጥጥር ስር ከዋለበት ጊዜ አንስቶ ከ2 ወራት በላይ የስቃይ ኑሮን እየገፋ እንደሚገኝ ተዘግቧል፡፡
በኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ተሳፍሮ ወደ እስራኤል ለመግባት በጉዞ ላይ የነበረውና በህዳር ወር መጀመሪያ ላይ ቦሌ አየር ማረፊያ ውስጥ ለትራንዚት ባረፈበት ወቅት በኢትዮጵያ ፖሊሶችና በእስራኤል መንግስት ተወካዮች ትብብር ህገወጥ ስደተኛ ነህ ተብሎ በቁጥጥር ስር የዋለው ኢሳ መሀሙድ፣ ከአየር ማረፊያው ሰራተኞች የሚሰጠውን ምግብ እየተመገበና ወንበሮች ላይ እያደረ ከሁለት ወራት በላይ የስቃይ ኑሮን በመግፋት ላይ እንደሚገኝ ግሎባል ቮይስስ ዘግቧል፡፡
ኢሣ ሙሀመድ ባለፈው የፈረንጆች ዓመት 2008 ሁለት ጊዜ ከእስራኤል መባረሩን ይናገራል። በመጀመሪያው ተባርሮ አገሩ ኒጀር ሲመለስ የእስራኤል ህጋዊ የጉዞ ሰነድ ስለነበረው፣ ወደ እስራኤል ዳግም ተመልሶ ተጓዘ፡፡ እስራኤል ሲደርስ የጉዞ ሰነዱን ነጥቀው ወደ አገሩ መለሱት፡፡ አገሩ ሲገባ ኒጀርነቱን ወይም እስራኤልነቱን የሚያረጋግጥ ህጋዊ የጉዞ ሰነድ ማቅረብ አልቻለም፡፡ ለ8 ቀናት በቁጥጥር ስር ከዋለ በኋላ በኢትዮጵያ በኩል፣በኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ እስራኤል እንዲመለስ ተደረገ፡፡ ቦሌ ዓለማቀፍ አየር መንገድ ሲደርስ ግን የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ከእስራኤል መንግስት ጋር በመተባበር ወደ እስራኤል ተሳፍሮ እንዳይጓዝ አገዱት፡፡
የ24 አመቱ ኢሣ ሙሀመድ ምንም እንኳን በኢትዮጵያ ፖሊስ ባይታሰርም የሚሄድበት በማጣቱ እስካሁንም በአየር ማረፊያው ውስጥ እንደሚገኝ የጠቆመው ዘገባው፤ስደተኛው በአዲስ አበባ የሚገኘው የኒጀር ኢምባሲ ድጋፍ እንዲያደርግለት ቢጠይቅም የአገሪቱ ዜጋ መሆኑን የሚያረጋግጥ ህጋዊ ሰነድ ባለመያዙ ሊሳካለት እንዳልቻለ ገልጧል፡፡

Saturday, 26 January 2019 13:28

ማራኪ አንቀጾች

በወንዶች አለም ውስጥ አንዲት ሴት


     የአዲስ አበባ ወንድ የመልበሻ ቤት መስተዋት ሆኗል፡፡ ሴቶቹ በሱ ፊት ላይ አለባበሳቸውን ያያሉ፤ የአዲስ አበባ መንገዶች፣ ካፌዎች፣ ባሮች፣ ቢሮዎች፣ ሆቴሎች፣ የፀሎት ቤቶች … አለባበስ ማሳያ መድረኮች ሆነዋል፡፡
ወንዱ የጥሞና ጊዜ ተነፍጓል፡፡ ሲበላ፣ ሲጠጣ፣ ሲሰራ፣ ሲፀልይ፣ ታክሲ ሲጠብቅ … በሞዴሎች ተከቦ ነው፡፡ ህይወቱ የናይት ክለብ ውስጥ እስረኛ ሆናለች፡፡ ሲወለድ ሳውና ባዝ የገባ ሲሞት ይወጣል፡፡ ኑሮው በላብ መጠመቂያ ስፍራው ሆናለች፡፡ አይኑ ሸሽቶ የትም አይደርስም፡፡ እድሜ ልኩን መስክ መካከል እንደቆመ ሁሉ በአበባ ተሰላችቷል፡፡ …ትቢያ… ናፍቆታል፡፡
ሴቶች፤ የወንዶች አገልግሎት አቅራቢ ድርጅት ሆነዋል፡፡ አይኑን ያገለግላሉ፣ ልቡን ያገለግላሉ፣ ስሜቱን ያገለግላሉ … የሴቶች የመጨረሻ አማራጭ … የወንዶች ገበያ .. እንደሚፈልገው ሆኖ መገኘት ነው። ህይወታቸው በወንዶች ህልም የተፈበረከ ነው፡፡ ከሰው የሚጠበቀው ከዘንድሮ ሴቶች አይገኝም፡፡ ወንድ የሚፈልገውን ግን አያጣም። አይኑ፣ ጆሮው፣ አፍንጫው፣ ምላሱ … በሴቶች ትጋት ሥር ተጠምዶ ተደናቅፏል፡፡ አንዲት ሴት ከአንዲት አበባ ጋር በንፅፅር ቆማለች፡፡ የወንድ ቀልብ እንደ ንብ ሲጠመድላት ከማየት ውጭ ሌላ ህልም የላትም፡፡
እንግሊዛዊው ደራሲ ዲ.ኤች ላውረንስ ይሄንን ታዝቦ አንዲት የመረረች መጣጥፍ አቅርቦ ነበር፡፡ “Give her a pattern” ይላል ርእሱ “The real trouble about women is that they must always go on trying to adapt themselves to men’s theories of women, as they always have done.” ብሏል፡፡ (የሴቶች ዋነኛ ችግር ወንዶች ስለሴቶች የሚኖራቸውን ፅንሰ ሃሳብ አሟልተው ለመገኘት ሁልጊዜም መጣራቸው ነው)
የዘንድሮ ሴቶች ሴት የመሆን መብት የላቸውም፤ ወንድ የሚፈልገው አይነት ሴት እንጂ፡፡ ሴቶች የወንዶችን ህልም ለመተርጎም ህይወታቸውን የሚሰዉ ጭዳዎች ናቸው። በመሰልጠን ስም እራሳቸውን ለፆታ ባርነት አጋልጠዋል፡፡ ኧረ እንዳውም ከባርነት ወርደው ለአሻንጉሊትነት ተዳርገዋል፡፡ ሁኔታውን “Living Doll” ይለዋል Cliff Richard የተባለ አቀንቀቃኝ፡፡ … ህያው አሻንጉሊት … እንደማለት ነው፡፡ “I got myself a sleeping, walking, crying, talking Doll” (እራሴን የምትተኛ፣ የምትሄድ፣ የምታለቅስ፣ የምታወራ አሻንጉሊት ሆኜ አገኘሁት) የዘንድሮ ሴቶች ሰው መሆናቸው የሚረጋገጠው ስለሚተኙ፣ ስለሚሄዱ፣ ስለሚያለቅሱና ስለሚያወሩ ብቻ ነው፡፡ እንደ አበባ … ንብ.. መጥራት የህይወት ትርጉማቸው ሆኗል፡፡  
(ከዓለማየሁ ገባላይ
“መለያየት ሞት ነው”
2010 ዓ.ም፤ የተቀነጨበ)

Saturday, 19 January 2019 00:00

የጥር ቅዳሜ

 ታክሲ ውስጥ ከተዋወቅን በኋላ በአካለ ሥጋና በመጠነ ሐሳብ ለመገናኘት ዛሬ የመጀመሪያ ቀጠሮዋችን ነው…
ፒያሳ
Five town
ቀደም ብዬ እየጠበኩት ነው፡፡ እንደሚመጣ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ሌላ… ብዙው ምክንያት ቢቀር እንኳ ከእኔ ለመገናኘት ዛሬ… የመጀመሪያው ቀጠሮዋችን ስለሆነ… ይመጣል… የተንቀዠቀዡ ዐይኖች ቢኖሩትም የኔን ውበት ለማክበር እንደማይዘገይ ተስፋ አደርጋለሁ… ስለዚህ እጠብቀዋለሁ …እዚህ ፒያሳ “Five house” (በነገራችን ላይ ይሄን ቤት በጣም እወደዋለሁ…ሌላ…ብዙ …ምርጥ…ቤቶች …ሳላይ ቀርቼ አይደለም…ያየኋቸው…ምርጥ መሸታ ቤቶች ዶሮ ማነቂያ ውስጥ ስላለሆኑ ከዚህ ቤት አይልቁብኝም…) እዚያ…ነኝ…
የተለያዩ የውስኪ ዓይነቶች ለምሳሌ…white horse, Red label, Black label, Jock Daniel…የተለያዩ የቮድካ ዓይነቶች… Smirnoff, stochilyna, Absolute vodka, witer palace, የወይን …የምናምን…የመጠጥ ዓይነቶች ለዐይን ማራኪ በሆነ መልኩ ከተደረደሩበት ፊት ለፊት ባልኮኒው አጠገብ ተቀምጬ እየጠበኩት ነው…
በቤቱ ውስጥ በየትኛውም የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ …ጥንዶች …ነጠላዎች …ተመሳሳይ ነጠላዎች (ሴት ጓደኛማቾች…ወንድ ጓደኛማቾች)…ነጠላ ብቸኞች (ብቻውን የሚጠጣ… ወንድ ብቻዋን የምትጠጣ ሴት) እንደየ መልካቸው እንደየ ዐይነታቸው አሉ፡፡ ከዚህ ፒያሳ…በፊት - ለፊት ስትሄዱ ሽቅብ ከላይ (ከጀርባ) ከመጣችሁ ቁልቁል ያለው ቤት…እርሷም እዚህ ነበረች፡፡
እርሱም ወደዚያው ገባ፡፡ ተደራጅቶ እየተቀመጠ በጣም አስተዋላት “ዓይኖቿ የፈገግታ የበኩር ልጆች” ይመስላሉ…ቀኝ ዐይኗ ሰላም፤ ግራዋ ማስተዋል..የሚባሉ መንታዎች … ሁለመናዋ ሳቅ ነበረ (ታክሲ ውስጥ እንዳዋራት እንጂ እንዳላስተዋላት ገባው) የሚገርመኝ ነገር ብዙ ጊዜ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ባላውቅም፣ እነዚህ ዓይናቸው ወደ ጐን ረዝሞ የሚታዩ ሴቶች …ሌላ ሦስት ረዣዥም ነገሮች አላቸው፡፡ ከናፍራቸው ረዘም ብሎ ወፈር ያለ፤ የጥርሶቻቸው …ሰልፍ …ብዙ ጥርሶች ያላቸው ሲያስመስላቸው …ንጣቱ …የ”ታቦርን ፀዳዳ”.. ቁመታቸው  …ጉንጮቻቸው መጠጥ ያሉ ይሆኑና … ከዐይኖቻቸው ስር ያሉት አጥንቶቻቸው ጉልህ ስጋ ያልከደናቸው … ዓይነት፡፡ ብዙ ጊዜ ብዙዎቹ እንዲህ ናቸው…ከብዙዎቹ አንዷ እርሷ ነች፡፡
“እንደሱ አትመልከተኝ…” አለችው
“ለምን?”
“እፈራለሁ… (ሳቅ… እያለች …ዐይኑን እየሸሸች) እፈራለሁ…ዐይን ሲበዛብኝ…እደነግጣለሁ አለ አይደል … የሆነ ምናምን ነገር…(ይሄ ምናምን ነገር የሚሉት አወራር …በዚያ ጊዜ የሴቶቹ ሁሉ የወሬ አዝማች የአነጋገር ስልት ምናምን ነገር ነበር)
“እንደዚህ የማይሽ…ሁሉ ነገርሽን ለማወቅ…ስለምፈልግ…ይሆናል”
“ማለት?”
የሆነ የተሰቀለ ስዕል የሚመራመር …ይመስል …ከበስተጀርባዋ በኩል ዐይኖቹን ለአትኩሮት ካዘገያቸው… በኋላ… “የሆነ …የማውቃት ልጅ …ያየሁ…መስሎኝ ነበር… (ውሸቴን ነው ምንም የማውቃት ሴት አላየሁም …ሆነ ብዬ ነው…ትንሽ ቅናትና ፉክክር ቢጤ ለመፍጠር ነው)
ኦ! ምን እንደሆነ ታውቂያለሽ …ዐይኖቻችን ውስጥ ሁሉም ነገሮች አሉ … ይሄ የፊታችን አጥንት ላይ ማንነታችንና ምንነታችን በጉልህ ተጽፏል…እርሱን ማንበብ ፈልጌ ይሆናል፡፡ የፊታችን ስሙ ፊት ነው፡፡ …ወደ ልብ መውረድ የሚቻለው በፊታችን በኩል ነው፡፡ ፊትን ማስተዋል …የማይችል ልብን አያገኝም…ፊታችን ሁሉንም ነው… ጽድቃችንንና ሐጢአታችንን… ንጽህናችንንና …ውርደታችንን…በጐነታችንንና ክፋታችንን… የያዘ …የፃፈ “ፊታችን”… እሱን ነው ማየው፡፡”
ሲጋራዋን በረዥሙ ስባ …ቮድካዋን እየተጐነጨች፤ “እርሱን ነገር እኔም ትንሽ…ትንሽ…አምንበታለሁ …አንዳንዴ …ዝም ብዬ የማላውቀውን ሰው ሄጄ… አዋሪው… የሚያሰኝ… መልካምነት…የሚታይበት … ጋባዥ የሆነ ፊት…አለ አንዳንዴ …ደግሞ…እንዲህ ዓይነት ፊት ያለበት …ቦታ…ልቀመጥ…አልችልም…ብዬ …ገና …ከርቀት ባየሁት ፊት የምጠላው…የምሸሸው…ሥፍራ አለ…በፊት፡፡  …ግን…አሁን…ሁሉንም…እኔ…ስለምነግርህ...”
(የሆነ …የሚያምር ነገር አላት…ሲጋራዋን ወደ ከናፍሯ ስትልክ ራሱን የቻለ …ጥበብና ውበት…መልዕክት ጭምር አለው…ሌላ ዓይነት አምሮት የሚቀሰቅስ…ሁኔታ…ሲጋራዋን ከከናፍሯ…ስታላቅቅ …የሆነ…ከከናፍሯ ወደ ሲጋራው…ጫፍ የሚለቀው የሊፒስቲኳ ቅላት በራሱ አንድ ትርጉም አያጣም)
“ምናልባት አንቺ… የምትነግሪኝ …ሕይወት ውስጥ ….የተፃፈብሽን አልያም ለመኖር የፃፍሽውን የትውስታ ማንነትሽን ይሆናል …እኔ ማወቅ የምፈልገው …የማይታየውን ነው.. ብትኖሪው ደስ የሚልሽን… ያልኖርሽውን የምትመኝውን”
“ታውቃለህ ቃላቶችን ማሽኮርመም ትወዳለህ…የሆነ ስዕል ምናምን ማድረግ”
(በመሃል የሆነ …ኮትና ሱሪ የለበሰ …ወይም ረዘም ያለ… የፊት ጥርሱ በትንሹ የተሸረፈ …ሰውዬ ነገር አለባበሱና ነገረ ስራው ወጣትነቱን አስጐልሞሶታል) ይቅርታ እያለ ወደ መሃላቸው ገባ…
ልጅቷን …ሲጨብጣት …አንገቱ ተበጥሶ የሚወድቅ ይመስል ነበር፡፡ “እኔ ምልሽ እንደዚህ ይጠፋል እንዴ? ኧረ…ልክ አይደለሽም ገብሬልን”…እርሷ ሳትፈልግ መዳፏን ለመሃላ አንስቶ እየመታ፡፡
“ጠፋን አይደል… ተዋወቀው ጓደኛዬ ነው” አለች…ወደኔ እየጠቆመችው…እየጨበጠኝ “እንዴት ነው ቤቱ ተመቻችሁ?” አለኝ ተፈጥሮአዊ… ባልሆነ ማን እንዳዋሰው በማላውቀው የድምጽ ልስላሴና የወገብ ስበራ (እንዲህ ዓይነት ሰው ዕጣ ክፍሌ አይደለም … እንዲህ ዓይነት ፊት ራሱ አልወድም … የራስ ያልሆነ…ማስመሰል የተላበሰ ፈገግታ ወደ ላይ ይለኛል…የዚህ ደቃቃ ሰው ዘዴ…እንኳን …ሲያደርገው ሲያስበው የሚያስታውቅ ተራ ዘዴ ነው…”እንዴት ነው …ቤቱ ተመቻችሁ?”…ይገባኛል ባለቤቱ ነኝ…እያለኝ…ነው፡፡ ከቆንጆ ሴት ጋር መሆኔን አትርሱ) ከብትነቱ ስለገባኝ ፈጠን ብዬ፤
“አሪፍ ነው በጣም ተመችቶናል” አልኩት፤ ፊቴን ወደ ቢራዬ እያዞርኩኝ፡፡
አንዳችና ከወገቡ እየተከፈለ “ተጫወቱ” ብሎን ሲሄድ፣ እርሷን በመቅለቅለስ እየተመለከተ ነበር፡፡
“ትንሽ ደደብ ቢጤ ይመስላል”
“ምን መምሰል ብቻ ነው’ንጂ … ከተማ በህይወቱ የሚችለው ነገር ቢኖር፣ ከአንድ እስከፈለግኸው ድረስ መቁጠር ብቻ ነው … ብርር….1,2,3,4,5,6,7…” እየሳቀች “በፊት ከጓደኞቼ ጋር እንመጣ ነበር፡፡”
“በጣም ትውውቅ አላችሁ እንዴ?” ትንሽ የቅናት ነገር ሳይሰማኝ… አልቀረም…
“ብዙ ጊዜ እኮ ሠውን ለመረዳት በጣም ማወቅ አያስፈልግም…ማወቅን የማይጠይቁ፣ የሚያስታውቁ ብዙ ነገሮች አሉ…ቅድም እንዳወራኸኝ የአጥንትና የፊት ዐይነት ነገር … ይልቅስ … እኔ ምልህ…” በእጁ የያዘውን ግማሽ የደረሰ…ሲጋራ እየተቀበለችው
“አንቺ የምትይኝ?”
“አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ እችላለሁ”
“የፈለግሽውን” አለ…ወደ ጆሮዋ እየተጠጋ፡፡
በቤቱ… ውስጥ… የነበረው… ሙዚቃ… በጣም ጩኸታም … ነበር፡፡ ሙዚቃው… ጩኸታም…ሙዚቀኛው…አድማጩ…ሁሉም…የተሳሳተበት ሙዚቃ፡፡
“ሆ”
“ሆ”
“ሆ” ብቻ የሚሉ… ጩኸቶች… እየዋ… የሁሉም ነገር ጩኸቶች… ሁለቱን የፍቅር መንገደኞች ስለረበሻቸው… አማራጩ ሁለቱም በየተራ ጆሮዋቸውን እየተዋዋሱ ማውራትና መስማማት ነበር…ወደ ጆሮው ተጠግታ፤
“አፍቅረህ…ታውቃለህ?” አለችው፡፡
ሊያልቅ ያለ ሲጋራዋን…እየተቀበላት  (ይህን በጆሮ ተጠግቶ ማውራት ሁለቱም የወደዱት ይመስላል…አንዳች ዓይነት ልዩ…ስሜት …የመቀስቀስ…ሃይል…አለው፡፡ የሆነ ሰውነት የሚወር ምናምን ነገር)…በግራ ጆሮዋ…በኩል…
“እውነቱን ልንገርሽ?“
“እንዳትዋሸኝ”
“እሺ…አንድ ጥያቄ እኔም ልጠይቅሽ?”
“ደስ እንዳለህ”…
“አብሬያቸው… የተኛኋቸውን …ማለትሽ ነው?…ወይስ… አብረውኝ …የወደቁትን ጭምር”
ልትጠጣው ያነሳችውን… መልሳ…እያስቀመጠች… የምትጠይቀውን ሳይሆን የሚመልሰውን  ለመስማት… እየተፋጠነች “ቃላቶችህ.. ተሳከሩብኝ… ግልጽ አድርጋቸው…”
“አየሽ…እኔ…ብዙ…ሴቶች አውቃለሁ … እጅግ ብዙ (ያጋነንኩት ሆን ብዬ ነው…ቅናት ለማጋባት) እና ግልጽ እንዲሆንልሽ ፈልጌ ነው… አንዳንዴ …እንዲህ በመሆኑ ራሴን የማልረባ አድርጌ እቆጥረዋለሁ…ሁሉንም…ዓይነት ሴቶች አይቻለሁ… ከሀ እስከ ፐ” (አሁንም ሆነ ብዬ ነው…ምክንያቱም ይህ የዚህ ዘመን የሀበሻ …ወንዶች…የማጥመጃ …መረብ …ነው…እኔም ከነርሱ አንዱ ነኝ) ለምን …መሰላችሁ…እኔ …ብቻ…ነኝ ያላየሁት ወይም ብዙ ዓይነት…የሴት ዕድል …ስላለው … ይህ ሰው የኔ ዕጣ ፈንታ ነው ብላ እንድታስብ …ፈልጌ፡፡ ስለፈለግኋት፡፡
“ለእኔ አብሬያት የተኛኋት ሴት… እርሷ ያፈቀርኳት የወደድኳት ናት፡፡ ልቤ ላይ የተሰማኝን በዚህ መልክ በተለያዩ ጊዜያት ከተለያዩ…ሴቶች ጋር…እጅግ …መልካም ጊዜያቶች …ነበሩኝ፡፡ ሙሉ ደቂቃዎች…በተረፈ …ሌሎቹ የወደቅኩባቸው ወይም የወደቁብኝ ናቸው…ምናልባት…ለደቂቃዎች…ለሰአታት…ለወራት…ያልተሰሙኝ፡፡ ፊደል አልባ … መልካም ሰሌዳዎች… ልቤ ላይ…ያልተፃፉ ትዝታዎች…እ…ከአመታት በፊት ይሄ …ቀን ሲያምር!...ብለሽ…ታውቂያለሽ?”
“እጅግ ብዙ ጊዜ” አለች- ፈጠን ብላ…
“እና ካቻምና የዛሬው ቀን ሲያምር ያልሽበትን ቀን ታስታውሽዋለሽ?”
“እኔ - እንጃ! አይመስለኝም”
“በቃ ለኔም …አብረውኝ የወደቁት - ሴቶች…እንደዛ …ናቸው… ደስ ሲል እንደተባለው ቀን…ከ አሪፍ ነበረች… ከ ቆንጆ ነበረች ከፍ የማይሉ”
“ቃላቶችህን በጣም ነው የምወዳቸው … ታውቃለህ “Your saying is so poetic” (እንደ ሴትነቴ የሆነ ግራ መጋባት ዐይነት ውስጥ ነኝ፡፡ አብሬው መሆን ግን እፈልጋለሁ፡፡ ከርሱ የምልቅ የህይወት ሰው ነኝ…የዚህን ሰው ወሬውን መስማት … ዳሩን ማየት…መሃሉን ማሳየት እፈልጋለሁ፡፡ ግን እኔም ከመውደቅ ያለፈ …ታሪክ እንደሌላቸው ሴቶች መሆን ፈራሁ…እንደዚያ ብዙ ሆኛለሁ…የሆነች ልጅ…ነበረች…ቆንጆ ነበረች…ተኝቻት…ነበር…ይህን …ማንም …ይለዋል…ከዚህ ከፍ ማለት እፈልጋለሁ…ሴትነቴን ወደ ሰው ከፍ ማድረግ…ደግሞም እኔ ቆንጆ…ሸክላ…ብቻ አይደለሁም…በውስጤ…ህይወት አለ…”ውሃ”…የዚህ ሰው ቃላቶች…በሸክላው ያለውን …ማይ…ሲንጠው ይሰማኛል … የገንቦ …ማዕበል ነገር … ቃላቶቹ!!!) እኔ እንጃ…የሆነ ደስ የሚል ነገር እየተሰማኝ ነው … ማርያምን! ደግሞም ግልጽ ነገር ነው…ክፍት … የተዘጋጉ ነገሮች የሉትም፡፡ (ዛሬ ግን ቮድካ …ሳላበዛ… አልቀረም)… አዲስ የተቀዳውንና ዐዲስ የተከፈተውን መጠጣቸውን አጋጭተው እኩል ተጎነጩ፡፡ በቤቱ ውስጥ የነበረው የቅድሙ ጩኸት ትንሽ ጋብ ብሏል … ምናልባት ከዚያ በኋላ የነበረው የሙዚቃ መንፈስ የተረጋጋ ስለሆነ ይሆናል… አሁን ከ Seal Paul ጋር Rihana እየጮኸች ነው …
“You don’t know how I love you
Now even how to kiss me…
Um still in love with you boy…
ወደ ጆሮው ተጠግታ በተለሳለሰ ድምፅ “እኔ ምልህ?” አለች፡፡ ወሬዋን እንድትቀጥል አንገቱን ከፍ ዝቅ አደረገላት፡፡  “በተኛሃት ሴትና በወደቅህላት ሴት መሃል ልዩነቱን ትነግረኛለህ?” (በልቤ በመጠኑም ቢሆን እኔ የትኛዋን ዓይነት ሴት ነኝ የሚል ጥያቄ አለ። ግን እኔ የትኛዋ ነኝ? ብዬ ልጠይቀው አልፈልግም፡፡ ስለ ራሴ ብጠይቀው የወንዝ ርዝመት ያህል ቁመት ያላት ሞኝ የሆንኩ ይመስለኛል፡፡ ስለ እኔ ከጠየኩት ሊመልስ የሚችለው ግልፅ ነው - ምክንያቱም ቢያንስ ለዛሬ እንኳ ይፈልገኛል፡፡ ስለዚህ መጠየቅ ያለብኝ ምን ዓይነት ልዩነት አላቸው? ብዬ ነው፡፡ በልዩነቱ የራሴን ቀለም መለየት እችላለሁ… ዛሬም ባይሆን ነገ ተነገ ወዲያ)
ሊያወራት ሲጀምር የተጎነጨው ቢራ ትን አለው። ከቢራው ጠርሙስ አፍ ደግሞ ነጭ የቢራ አረፋ ወጣ… የጠርሙስ ትንታ መስሎ … እንደ ቸኮለ ስሜት ገንፍሎ … የቢራውን አፍ እየጠረገ “በተኛኋትና በወደቅኋት ሴት መሃል ልዩነት ባይኖርማ ቃላቶቹም ባልተለያዩ ነበር፡፡ የምተኛት ሴት የማፈቅራት ናት፤ በመተኛት ዕረፍት አለ እፎይታ፡፡ በምወድቃት ግን ፀፀት፡፡ ከምተኛት ሴት መርፌና ክር ሆኜ ነው የማነጋው፡፡ (ወድጃታለሁና) ከወደቅኋት ሴት ጋር ግን “ኤክስ” (X) እሰራለሁ፡፡ እርሷ ወደ ምዕራብ … እኔ ወደ ምስራቅ እግሮቻችንን አጣጥፈን .. የተንጋደደ መስቀል ሠርተን …”
“እሺ እንዲህ ከሆነ ታዲያ ፍቅር ላንተ ምንድነው?” … እያወራች ሲጋራ ልትለኩስ ስትል የመጀመሪያው ክብሪት ብልጭ ብሎ ጠፋ፡፡ ሁለተኛው የክብሪቱ አናት ተሰብሮ ወደቀ፡፡  ሦስተኛውን ልትሞክር ስትል ክብሪቱን ተቀብሏት ሲሞክር፣ የክብሪቱ አናት ነደደ … ሲጋራውን ለኩሶ እያቀበላት የክብሪቱን ቤት ከፍቶ ተመለከተው… ባዶ ነበር፡፡ ባዶ! …አገጩዋን በእጇ ይዛ ፊቷን ወደ ፊቱ እያዞረች “በላ ንገረኝ… ፍቅር ላንተ ምንድነው?”
“በጠዋት ተነስተሽ ታውቂያለሽ?”
“ብዙ ጊዜ”
“በቃ ለእኔ ፍቅር በማለዳ የሚገኘው ፈገግታ ነው። በጠዋት ስነሳ መጀመሪያ ያሰብኩት ሰው ከሆነ … ያኔ ፍቅር ውስጥ ነኝ ማለት ነው፡፡ እናም ልክ እንደ ህፃናት “ፈገግ” እላለሁ … ያለ ምክንያት! ያለ ምክንያት ፈገግ ስል ከታየሁ፣ ፍቅር ውስጥ ነኝ ማለት ነው፡፡ ሲነጋ የፀሐይ ጉዞ ሲጀመር … ከወፎች ጩኸት እኩል ሥነቃ … የመጀመሪያው የቤተ ክርስቲያን ደውል ሲሰማ… ከዐዛን ድምፅ ቀጥሎ ወይም ረፋድ ላይ የመጀመሪያውን ቡና ከመጠጣቴ በፊት … ማለዳ ጠዋት ፈገግ ማለት ከቻልኩኝ፣ ለእኔ ፍቅር እርሱ ነው፡፡ ያኔ አንድ ሕይወቴ ውስጥ የገባ ፀሐይ አለ ማለት ነው”
(እየሰከርኩ ነው … ቮድካውና ወሬው ናላዬን ሠማንያ ቦታ ከፍለውታል … ከዚህ ሠው ጋር በማለዳ ፈገግ ብዬ ቀናቶቼን እየሰራሁ አብሬው መሸበት አማረኝ … ውበቴ እስኪረግፍ … ፀጉሬ ጥጥ እስኪመስል …ከዚህ ሰው ጋር መሆን ፈለግሁኝ … ውስጤ እየተቅበጠበጠ ነው … ቮድካውንም በጨመርኩት ቁጥር እየጣፈጠኝ ነው … ግን ወሬው … ቃላቶቹ… ስሜቴ… ሠማይ ድረስ ይጠጋሉ ዋይ…)
“እኔ ምልህ ቃላቶቹን ከየት ነው የምታመጣቸው? ያምራሉ!” …
“አንቺም በጣም ውብ ነሽ … እስካሁን በውበት መናገር ያልቻልኩት ያንቺን ውበት ብቻ ነው፡፡ በጣም ትሰሚያለሽ… በብዙ ፀጥታ ታዳምጫለሽ። ስትናገሪም ጆሮ ይገዛልሻል …አየሽ ፍቅር ውስጥ መሆን ተስፋ ውስጥ መሆን ነው … ፍቅር ውስጥ ስሆን ለብቻዬ ደስተኛ ነኝ፡፡
ፍቅር ለእኔ እንዲህ ዓይነት ስሜት እንዲሰማኝ የሚያደርገኝ ሃይል ነው፡፡ በየትኛውም ሁኔታዎቼ… የትኛዎቹንም ሁኔታዎቼን የምትጋራኝ ጨረቃ አብራኝ ናት ማለት ነው … ሌሊት ባንኜ ከነቃሁ መጀመርያ ትዝ የምትለኝ ካለች ያኔ ወድቅያለሁ…ፍቅር ባህር ውስጥ፡፡ ያኔ ከእርሷ ጋር አልወድቅም… እተኛለሁ እንጂ … እፎይ ብዬ፡፡ ማለዳ በወፎች ዜማ ታጅቤ ከመኝታዬ ስነሳ … እቀሰቅሳትና … እተረጉምላታለሁ፡፡ የአዕዋፍን መዝሙር … “ከሴቶቹ ሁሉ እነሆ አንቺ ውብ ነሽ! ውብ ሴት ብቻ ሣትሆኝ … መልካም ሰው ጭምር ነሽ…” ይሉሻል … ብዬ ከቃላቶች የአልማዝ ሃብል አጠልቅላታለሁ፡፡ የማለዳ ሳቄ ናትና! …”
ሕዝቦች ሆይ … በጠዋት ፈገግ እንድትሉ ከሚያደርጋችሁ በላይ ለእናንተ መልካም ማነው?
(ዋው በመጠጡም በወሬውም ሞቅ እያለኝ ነው… የመሳም… የመታቀፍ ፍላጎት ፊቴ ላይ እየተሽከረከረ ነው፡፡ አብሶ ይሄ ድምፁን አለሥልሦ በጆሮዬ በኩል ሲያወራኝ ወደ “የሰውነቴ ባላ (መያያዣ) አካባቢ ሙቀትና ርጥበት ነገር ይሠማኛል … ከዚህ ጋር ምንም ብሆን አልፀፀትም… እንኳን ከ’ንዲህ ዓይነት “ሕይወተኛ” ቀርቶ… በመሠለኝና በይሆናል… ከዚያ ደደብ ጋር ሄጄ አልነበር… እናቱንና…) እና በቃ እንዲህ እያሰብኩ እያለሁ ወደ ጆሮዬ ተጠግቶ፤
“ዛሬ ለምን አልጠልፍሽም?” አለኝ
“በእውነት?” አልኩ … ሐሳቤ ሊሞላ ስለመሰለኝ እጄን እየሠጠሁት
“ትዕግስት ሙች!” መዳፌን በመዳፉ እየመታ፡፡ “ትዕግስት ሙች” ብሎ ስሜን ሲጠራው የለመድኩት የቅርቤ ዓይነት ሰው መሰለኝና ወደ ጆሮው ተጠግቼ “ታውቃለህ ለመሃላ … ስሜን ስትጠራው ከተዋወቅን መቶ ዓመት የሆነን መስሎ ተሰማኝ… እና ደግሞ የሆነ ጊዜ ላይ ድሮ በፊት … በነ አብርሃም… በነ ይስሐቅ… በነ ያዕቆብ ዘመን… የሆነ አገር ላይ ከጥርብ ድንጋይ መደዳው የተሠሩ መንደሮች ውስጥ… ጎረቤቶች ሆነን የኖርን… ማታ ማታ በጭለማ እየተገናኘን… ፍቅር የሠራን… ጎረቤታማቾች ምናምን! በአፄ ቴዎድሮስ ወይ በናፖሊዮን ወይ በነ ኢዛና ጊዜ … ብቻ የሆነ ቦታ ላይ ባሌ ሆነህ… የአስራ ዘጠኝ ልጆቼ አባት የነበርክ… ምናምን … አቦ ልሠክር ነው እንዴ? አንተ ነህ ያሠከርከኝ አይደል? … እሺ አሁን የምን መንቀርፈፍ ነው… አትጠልፈኝም? …እ?”
“ወዴት ልጥለፍሽ?”
“ወዴትም! ካንተ ጋር ወዴትም መጓዝ እችላለሁ… ወዴትም”
“የትም?”
“አዎ! የትም”
“ታምኚኛለሽ?”
“ፍቅርን የተረዳ ሠው ስለ እምነት አይጠየቅም … አይጠየቅም”
ሒሳብ ከፍለው እነርሱ ወደሚያውቁት እኛም ወደገመትነው ተጓዙ፡፡
ነግቷል፡፡
ረፋድ ላይ ነበረ… አራት ሰዓት ከሠላሳ ምናምን። ደስተኞች ነበሩ… ፊታቸው ላይ የተፃፈው… ሰክሮ ያደረ ሰው የዐይን ቅላት አልነበረም… ደስታ  ብቻ ነበር፡፡ ሕይወት ያለው ሣቅ፡፡
የጊዜ ወንዝ የት እንደሚጥላቸው… የት እንደሚያደርሳቸው… ባያውቁም… ነገር ግን ይህንን ዘመን በማይመጥን ሃይል… ፍቅር… መንገዳቸውን ጀምረዋል፡፡ ከዚህ ዘመን ቀለም ተነጥለዋል… ይህ ዘመን ዕውነት ለሆነ ነገር ቦታ የለውም፡፡
እነርሱ ግን ጀምረዋል… መንገዱን…
አስተናጋጁ ሁለት ወፍራም ቡና ጠረጴዛው ላይ አስቀመጠ፡፡
ቡናቸውን አንስተው… ተያዩ… እዚህ የተቀመጠበት (ካፍቴርያ ውስጥ የማለዳ ቡናና ማኪያቶ አፍቃሪዎችን ድምፅ አልፎ የሆነ መዚቃ ወደ ጆሮዋቸው ገባ…
“From this moment life has begun
from this moment you are the one…” የሻንያ ትዌይን ለስላሳ ውብ ሙዚቃ…
ተያይተው ፈገግ አሉ… አሁን ተፈጥሮ ራሡዋ የእነርሡ አጋዥ ሆናለች፡፡ በሁለቱም ልቦና ውስጥ የሚመላለሰው የትላንቱ ጨዋታቸው ነበር … በሁለቱም ገፅታ ላይ ከየትኛዎቹም ጊዜዎች ይልቅ ከፍ ያለ ፈገግታ ነበር፡፡
አስተናጋጁን ጠርተው ሒሣብ ሊከፍሉ ሲሉ ተከፍሏል ተባሉ … እዚያ ያሉት ሠውዬ ቢሉን ዘግተዋል… ሁለቱም ወደ ኋላቸው ዞሩ፡፡
የትላንቱ ሆቴል ባለቤት ነው… ዛሬም የተኮረጀ ትህትናውን ለብሶ ከአንገቱ ተቀነጠሰ፡፡
ቅሬታን ባዘለ… ደስ በማይል… ስሜት “እናመሰግናለን” ብለው ወጡ፡፡ ቅር ቢላቸውም… የዚህ ሰው ዓላማ ባይገባቸውም እንኳ … ጣልቃ ገብ ጊዜ የላቸውም… በራሳቸው አለማት ላይ ላሉት ለህይወት ጥያቄዎቻቸው እንኳ ሥፍራ የላቸውም… አሁን እነርሡ የሕይወት መሰረታዊ ጥያቄዎች መፋቀር ብቻ ቢሆን ደስተኞች ናቸው፡፡ ለነገሩ ይህንንም ለማሰብ ጊዜ የላቸውም፡፡
እውነቱን ነበረ…
ማለዳ ከመጀመሪያው ቡና በፊት ፈገግ ብለዋል። ቀኑም… አበቦቹም… ዛፎቹም… ወንዞቹም… ሁሉም ፍጥረታት ፈገግ ብለዋል .. ሠማዩ ከፍ ያለ… ደማቅ ነጭና ደማቅ ሠማያዊ የፈሰሰበት… ውብ የጥር ቅዳሜ ነበር፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሁፉ በአዲስ አድማስ ድረ ገጽ ላይ በጁን 2፣2012 ፖስት ተደርጎ የነበረ ሲሆን በድጋሚ ለንባብ ከመረጥናቸው አንዱ  መሆኑን እንገልጻለን፡፡

 • 251 ቀናት ቀርተዋል፤ በቴሌቭዥን ስርጭት እስከ 6 ቢሊዮን ድምር ተመልካች ተጠብቋል፡፡
  • ኳታር ከ236.2 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጭ አድርጋለች፡፡
  • በ2021 እ.ኤ.አ በአሜሪካ ዩጂን፤ በ2023 እ.ኤ.አ በሃንጋሪ ቡዳፔስት…
  • በ2025 በአፍሪካ ኬንያ ወይስ ናይጄርያ?
  • በ2019 እ.ኤ.አ ውጤታማ ይሆናሉ የተባሉ የኢትዮጵያ አትሌቶች ነፃነት እና ሰለሞን ናቸው፡፡
  • ባለፉት 16 የዓለም ሻምፒዮናዎች ኢትዮጵያ 77 ሜዳልያዎች ሰብስባለች፡፡ (27 የወርቅ፤ 25 የብርና 25 የነሐስ ሜዳልያዎች)


    የኳታር ዋና ከተማ ዶሃ ለምታስተናግደው 17ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና 251 ቀናት ቀርተዋል፡፡ በዓለም ሻምፒዮናው  ከ200 በላይ አገራትን የሚወክሉ ከ2000 በላይ አትሌቶች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል። በኳታር የዓለም ሻምፒዮና ብሄራዊ አዘጋጅ ኮሚቴ ልዩ እቅድ መሰረት ከመላው ዓለም ከ3ሺ በላይ የሚዲያ ተቋማት እንደሚጋበዙ እየተገለፀ ሲሆን፤ 200  መዳረሻዎችን በሚሸፍን የቀጥታ የቴሌቭዥን ስርጭት እስከ 6 ቢሊዮን ድምር ተመልካች ለማግኘት ተጠብቋል፡፡
ዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር በ2019 እኤአ የውድድር ዘመን ላይ በሚያካሂዳቸው አጠቃላይ  ሂደቶች ስኬታማ ለመሆን ይፈልጋል፡፡ ከ5 ሳምንት በኋላ በዴንማርክ ፤ አሁሩስ የሚካሄደው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና  ከዚያም በጃፓን ዮኮሃማ  የዓለም ዱላ ቅብብል ሻምፒዮና ዋናዎቹ ሲሆኑ፤ ዳይመንድ ሊግ፤ ዎርልድ ቻሌንጅ፤ በዎርልድ ኢንዶር ቱር እና ሌሎች ውድድሮች የተቀሩት  የውድድር ዘመኑ መርሃ ግብሮች ናቸው፡፡ ኳታር ከምታዘጋጀው 17ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና 10 ወራት በኋላ  ደግሞ በ2020 እኤአ ላይ ጃፓን የምታስተናግደው 33ኛው ኦሎምፒያድ ነው፡፡
በ17ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው ላይ ያለ ሚኒማ መሳተፍ የሚችሉት ያለፈው የዓለም ሻምፒዮኖች፤ የ2019 ዳይመንድ ሊግ አሸናፊዎች፤ የተለያዩ የአይኤኤፍ ዙር ውድድር ሻምፒዮኖች ናቸው፡፡ አይ.ኤ.ኤ.ኤፍ ለዓለም ሻምፒዮናው የተሳትፎ ሚኒማ የውድድር ዘመኑን ዓለም አቀፍ ደረጃ ለመጠቀም ከጅምሩ አስቦ ነበር፡፡ ይሁንና ከአትሌቶች፤ አሰልጣኞች፤ ማናጀሮችና ኤጀንቶች በቀረቡ አስተያየቶች አሰራሩን ዘንድሮ ተግባራዊ ላለማድረግ ወሰኗል፡፡ ስለሆነም በተለያዩ ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮች በመሳተፍ ለሻለም ሻምፒዮናው የሚያበቁ አስፈላጊ ሚኒማዎችን ለማሟላት እንደሚቻል አመልክቷል፡፡ በተለይ  በ10ሺ፤ በማራቶን፤ በርምጃ፤ በዱላ ቅብብል እና ሌሎች ድብልቅ ስፖርቶች ከማርች 15 እስከ ሴፕቴምበር 14 በአይኤኤኤፍ ስር በሚካሄዱ ውድድሮች የሚመዘገብ ሚኒማ ወሳኝ ሲሆን ለሌሎች የስፖርት አይነቶች ደግሞ ከሴፕቴምበር 12,2018 እስከ ሴፕቴምበር 14,2019 በአይኤኤፍ እውቅና በተሰጣቸው ውድድሮች በተመዘገቡ ውጤቶች እና ሰዓቶች ለመመረጥ ይቻላል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ላይ እስከ 15ኛ ደረጃ የሚያገኙ አትሌቶች የ10ሺ ሚኒማን እንዳሟሉ ይወሰድላቸዋል ተብሏል፡፡
የዓለም ሻምፒዮናው ከረጅም ጊዜ በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ በመስከረም ወር መጨረሻ ላይ ተጀምሮ ለ10 ቀናት የሚካሄድ ነው፡፡ ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር IAAF ለዓለም ሻምፒዮናው የትኬት ሽያጭ በመጀመርያ ምዕራፍ ከወር በፊት ሲያከናውን በጀርመን፤ በዩናይትድ ኪንግደም በአሜሪካ እና በአውስትራሊያ ከፍተኛ ሽያጭ አግኝቶ ነበር፡፡ ሁለተኛው ምእራፍ የትኬት ሽያጭ በሚቀጥለው ወር የሚቀጥል ሲሆን፤ በዶሃ የዓለም ሻምፒዮናው አዘጋጅ ኮሚቴ እቅድ መሰረት ልዩ ጥቅም የሚያስገኝ ሙሉ የጉዞ ፖኬጅ ለመላው ዓለም ይፋ ከመሆኑም በላይ የውድድሩን ምልክት mascotም ጎን ለጎን እንደሚተዋወቅም ይጠበቃል፡፡
የዓለም ሻምፒዮናን ማዘጋጀት በኳታርና  ከዚያ በኋላ…
ኳታር በዋና ከተማዋ ዶሃ የዓለም ሻምፒዮናውን ለማዘጋጀት ስትነሳ የስፔኗ ባርሴሎና እና የአሜሪካዋ ዩጂን ከተሞች ተፎካክረዋታል፡፡ ምርጫውን በፍፁም ብልጫ በማሸነፍ አዘጋጅነቱን ከ5 ዓመታት በፊት በይፋ ስትረከብ ግን ከብዙ ትችቶች ጋር ነበር፡፡ በ2022 እኤአ እንደምታስተናግደው 22ኛው የዓለም ዋንጫ ሁሉ የ17ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናውን አዘጋጅነትን ያገኘችበት ሁኔታ በተለያዩ አጀንዳዎች ተብጠልጥሎባታል፡፡ የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ማህበር በ2019 እኤአ የዓለም ሻምፒዮናውን የሚያዘጋጅ አገር ለመምረጥ ባካሄደው ጉባኤ ላይ   የኳታር መንግስትና የኳታር አትሌቲክስ ፌደሬሽን የተለያዩ አባል ፌደሬሽኖችን ድጋፍና ድምፅ ለመደለል ሙከራ አድርጓል የሚለው የውዝግብ አጀንዳ ከሁሉ ትችቶች የመጀመርያው ነበር፡፡ ኳታር የዓለም ሻምፒዮናውን ለማዘጋጀት ባቀረበችው ማመልከቻ በድምሩ ከ236.2 ሚሊዮን ዶላር በላይ በጀት መያዟን ይህም በስፖንሰርሺፕ 80 ሚሊዮን ዶላር በቴሌቭዥን ስርጭት እሰከ 29 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም የዓለም ሻምፒዮናውን የሽልማት ገንዘብ በመሸፈን እስከ 7.2 ሚሊዮን ዶላር ወጭ እንደምታደርግ አስታውቃ ነበር።  በምርጫው የመጨረሻ ሂደት ላይ መስተንግዶውን ለማግኘት የተፎካከሯትን ሌሎች አገራት ለማሸነፍ በማለት የብሄራዊ ባንኳን የ5 ዓመት ስፖንሰርሺፕ በ30 ሚሊዮን ዶላር ለመስጠት እና ለ21 አባል ፌደሬሽኖች ትራክ መስርያ እስከ 7 ሚሊዮን ዶላር ለመለገስ አይኤኤኤፍን በይፋ ጠይቃለች የሚሉ መረጃዎች መሰማታቸው በከፍተኛ ደረጃ አስተችቷታል፡፡ ለነገሩ በመካከለኛው ምስራቅና በአፍሪካ ከሚንቀሳቀሱ ግዙፍ የፋይናንስ ተቋማት አንዱ የሆነው የኳታር ብሄራዊ ባንክ የዓለም ሻምፒዮናው አብይ ስፖንሰር ሲሆን ለሚቀጥሉት 4 ዓመታት በአይኤኤኤኤፍ የአትሌቲክስ ውድድሮች አጋርነቱ ለመስራት መወሰኑ የሙስና ወሬዎቹን አብርዷቸዋል፡፡ በሌላ በኩል የኳታርን የዓለም ሻምፒዮና መስተንግዶ በውዝግብ የጠመደው ሌላው አጀንዳ ደግሞ ከመካከለኛው ምስራቅ እና ከዓለም ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ በተያያዘ የተነሱ እሰጥ አገባዎች ናቸው፡፡ የኳታር መንግስት ለሽብርተኞች ሙሉ ድጋፍ ይሰጣል በሚል አቋማቸው የአረቡ ዓለም ሃያል አገራትና ሌሎችም ዓለም ሻምፒዮናውን ላለማሳተፍ እንደሚወስኑ ሲገልፁ ነበር፡፡ በተለይ ሳውዲ አረቢያ፤ ዩናይትድ አረብ ኢምሬትስ፤ ባህሬንና ግብፅ ይህን አቋማቸውን በይፋ በማስተዋወቅ ተሳትፏቸውን እንደሚሰርዙ በይፋ እስከመግለፅ ቢደርሱም፤ የዓለም አትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር ፕሬዝዳንት እንግሊዛዊው ሴባስትያን ኮው በዓለም ሻምፒዮናው ተሳትፎ ላይ ተለዋዋጭ የፖለቲካ ውዝግቦች ተፅእኖ ማሳደር እንደሌለባቸው በመጥቀስ የሁሉንም አገራት ተሳትፎ እንደሚጠበቁ በመናገር ተሳትፎን መሰረዝ ለቅጣት እንደሚያበቃ ማሳሰባቸው ውሳኔያቸውን እንዲያጤኑ አስገድዷቸዋል፡፡ ከዚያም በኋላ  የኳታር ህዝብ ለስፖርት ብዙም ፍቅር ስለሌለው የዓለም ሻምፒዮናውን  የተመልካች ድርቅ ይገጥመዋል በሚል ስጋታቸውን በመግለፅም የተሟገቱም ነበሩ፡፡
ከሁሉም አወዛጋቢ አጀንዳዎች በኋላ የኳታር መንግስት እና ብሄራዊ አዘጋጅ ኮሚቴው የዓለም ሻምፒዮናው በዘመናዊ ስታድዬም፤ ቴክኖሎጂ፤ ምርጥ እና ዘመናዊ ትራክ፤ በልዩ ልዩ ጥቅሞች በተሞላ መስተንግዶ እንዲሁም በቲቪ ነስርጭት ከፍተኛ ድምቅት እንደሚኖረው በልበሙሉነት እየተናገሩ ቆይተዋል፡፡ ዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር የዓለም ሻምፒዮናው 1 ዓመት ሲቀረው የኳታርን አጠቃላይ ዝግጅት በመገምገም ፍጹም መርካቱን የገለፀ ሲሆን  ባለፉት 6 ወራት የ30 አገራት አትሌቲክስ ብሄራዊ ቡድን አመራሮችና አሰልጣኞች ዶሃን በመጎብኘት በነበራቸው ተመክሮም መደሰታቸውን በይፋ መናገራቸው ማስተማመኛ ሆኗል፡፡ በኳታር የስፖርት መሰረተልማቶች፤ የአየር ሁኔታ መቆጣጠርያ ቴክኖሎጂ ፤ በተሟላ የትራንስፖርት ፤ የሆቴል እና ሌሎች ዝግጅቶች በማድነቃቸው ነው፡፡
ኳታር ባለፉት 21 ዓመታት ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮች በማስተናገድ የተወሰኑ ልምዶችን አካብታለች፡፡ በአትሌቲክስ የመጀመርያው ዓለም አቀፍ የውድድር መስተንግዶዋ በ1997 የተዘጋጀው ግራንድ ፕሪ ሲሆን በ2010 እኤአ ላይም የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮናን በተሳካ ሁኔታ ማሰናዳቷም የሚጠቀስ ነው፡፡
በነገራችን ላይ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በኤሽያ አህጉር ሲዘጋጅ ኳታር አምስተኛዋ አገር ናት። ከኳታር በፊት በ2007 እኤአ የጃፓኗ ኦሳካ፤ በ2011 የኮርያዋ ዳጉ እንዲሁም በ2015 የቻይናዋ ቤጂንግ ሻምፒዮናውን አዘጋጅተዋል፡፡ በዓለም የአትሌቲክስ አስተዳደር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የዓለም ሻምፒዮናው በአፍሪካዊ አገር እንዲዘጋጅ እየተመከረ መሆኑን የተለያዩ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ካለፉት 17 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች ፊንላንድ በሄልሲንኪ በ1983 እና በ2005፤ ጃፓን በቶኪዮ እና በኦሳካ  ከተሞች በ1991 እና በ2007 እንዲሁም ጀርመን በስቱትጋርትና በበርሊን በ1993 እና በ2009 እኤአ ሁለት ጊዜ የማዘጋጀት እድል የተሰጣቸው አገራት ነበሩ፡፡ በጣሊያን ሮም በ1987፤ በስዊድን ጉተንበርግ በ1995፤ በ1997 በግሪክ አቴንስ፤ በ199 በስፔን ሲቪያ፤ በካናዳ ኤድመንተን በ2001፤ በፈረንሳይ ሴንትዴኒስ  በ2003፤ በደቡብ ኮርያ ዳጉ በ2011፤ በራሽያ ሞስኮ በ2013 ፤ በቻይና ቤጂንግ በ2015 እንዲሁም በእንግሊዝ ለንደን በ2017 ሌሎቹ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች ተካሂደዋል፡፡ ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር ከኳታር በኋላ በ2021 እኤአ 18ኛውን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናን የአሜሪካዋ ዩጂን እንዲሁም በ2023 እኤአ ደግሞ 19ኛውን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናን የሃንጋሪዋ ቡዳፔስት እንዲያዘጋጁ መርጧቸዋል፡፡  በ2025 እኤአ ላይ ግን  አፍሪካዊ አገር 20ኛውን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና  እንዲያዘጋጅ አይኤኤኤፍ ፍላጎት እንዳለው ለማወቅ ተችሏል። ይህን ተከትሎም 6 የአፍሪካ አገራት አልጄርያ፤ ግብፅ፤ ኬንያ፤ ሞሮኮ፤ ናይጄርያ እና ደቡብ አፍሪካ ለመስተንግዶው  ያላቸውን ፍላጎት አስታውቀዋል። ከመካከላቸው ብቁውን አስተናጋጅ አገር ለመምረጥ ሃላፊነቱ የአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌደሬሽን መውሰዱንም መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ አንድ አዘጋጅ አገር የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሲያዘጋጅ ከ30ሺ በላይ ተመልካች የሚያስተናግድ ዘመናዊ ስታድዬም፤ ተጨማሪ የልምምድ ማዕከልና ማረፊያ ሆቴሎች፤ ለሽልማት ገንዘብ፤ እንዲሁም ለፀጥታ፤ ለደህንነት እና ለአስቸኳይ ጊዜ አገልግሎት እስከ 30 ሚሊዮን ዶላር በጀት እንደሚያስፈልገው አይኤኤኤፍ ይገልፃል፡፡ በታሪክ የመጀመርያውን የዓለም ሻምፒዮና በአፍሪካ አህጉር ለማዘጋጀት የምስራቅ አፍሪካዋ ኬንያ እና የምእራብ አፍሪካዋ ናይጄርያ ከፍተኛ አቅምና ፍላጎት እንዳላቸው ተሰምቷል፡፡ ባለፈው አመት በሃምሌ ወር አጋማሽ ላይ የአይኤኤኤፍን ሀ 18 የዓለም አትሌቲክሰ ሻምፒዮና ያስተናገደችው ኬንያ በቀጣይነት ሀ 20  የዓለም አትሌቲክሰ ሻምፒዮና በቅርቡ እንድታዘጋጅ እድል ከተሰጣት በኋላ በቀጣይ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናን የምታዘጋጅበትን እቅድ እንድታስብ አስችሏታል፡፡ ኬንያ በ2007 ላይ የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮናን ከዚያም በኋላ ባለፈው ዓመት እና ዘንድሮ ሁለቱን የታዳጊና ወጣት የዓለም ሻምፒዮናዎች ያስተናገደችበት ልምዷ ምናልባትም በአፍሪካ ምድር ሊዘጋጅ የታሰበውን የዓለም ሻምፒዮና ያለተቃናቃኝ እንድትረከብ ይደግፋታል፡፡ ዋና ተፎካካሪ የምትሆነው በ2018 የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ተሳካ ዝግጅት ያስተናገደችው ናይጄርያ ስትሆን ለአዘጋጅነቱ ያላትን ፍላጎት በተደጋጋሚ እያስታወቀች ነው፡፡
ካሊፋ ዓለም አቀፍ  ስታድዬምና ልዩ ቴክኖሎጂዎቹ…
በኳታር የቀድሞ ኢሚር ካሊፋ ቢን ሃማድ አል ታህኒ መታሰቢያነት ካሊፋ ዓለም አቀፍ ስታድዬም በ90 ሚሊዮን ዶላር ወጭ የታነፀ  የኳታር ብሄራዊ ስታድዮም ሲሆን የዶሃ የስፖርት ከተማ ዘመናዊ ኮምፕሌክስ አካል ነው፡፡ ዘመናዊ ኮምፕሌክሱ ከስታድዬሙ በተጨማሪ አስፓየር አካዳሚ፤ ሃማድ አካውቲክ ማዕከልንና አስፓየር ታወርንም የሚያካትት ነው፡፡ በ2022 እኤአ ላይ ዓለም ዋንጫን ከሚያስተናግዱ ስታድዬሞች ቀድሞ አገልግሎት መስጠት የጀመረውና 48ሺ ተመልካች የሚይዘው ስታድዬሙ ከዓለም ሻምፒዮናው በፊት በሚያዚያ ወር በሚዘጋጀው የኤስያን ጌምስ ሙለሙሉ ብቃቱ የሚፈተሽ ይሆናል፡፡ ላለፉት 42 ዓመታት የኳታር ብሄራዊ ቡድን ዋና ሜዳ ሆኖ ሲያገለግል የቆየው ካሊፋ፤ በ2004 እኤአ የገልፍ ካፕ ኦፍ ኔሽን፤ በ2006 ኤስያን ጌምስ፤ በ2011 ላይ የኤስያ ካፕ የፍፃሜ ጨዋታ፤ በ2011 የፓን አረብ ጌምስን አስተናግዷል፡፡
በዘመናዊነቱ እያነጋገረ የሚገኘው ስታድዬሙ በአየር ማቀዝቀዝ ቴክኖሎጂው፤ ለተመልካች በሚመች ዲዛይኑ ሻምፒዮናውን እንደሚያደምቅ እየተገለፀ ነው፡፡ በስታድዬሙ ዙርያ የተገጠሙት ከ500 በላይ የጄት ሞተር የመሰሉ ማሽኖች የሚሰራው ቴክኖሎጂ ለተመልካች እና ለአትሌቶች ምቹ አየር ንብረት የሚፈጥርና የንፋሱን መጠን የሚቆጣጠር እንደሆነ የገለፁት አዘጋጆች ከሌሎች የማቀዝቀዛ ቴክኖሎጂዎች በ40 በመቶ የሚቀንስ ኃይል የሚጠቀም መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በኳታር ከባድ ሙቀት የተነሳ አንዳንድ የአጭር ርቀትና የማራቶን ውድድሮች በእኩለ ሌሊት ለማድረግ መታሰቡ ግን ጥርጣሬ ፈጥሯል፡፡ በስታድዬሙ የተገጠመው የአየር ማቀዝቀዣ ቴክኖሎጂ በውጭ ያለውን ሙቀት ከ40 ወደ 20 እና 26 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በማውረድ ሙቀቱን ለውድድር የሚመች አድርጎ እንደሚያስተካክል በበርካታ ሙከራዎች ቢረጋጋገጥም የአንዳንድ አገራት ፕሮፌሽናል አትሌቶች ስጋታቸውን ከመግለጽ አልተቆጠቡም፡፡ በውድድር ወቅት በስታድዬሙ ውስጥ አየሩ ሊስተካከል ቢችልም ከውድድር በፊት በሚኖር ቆይታ በብቃታቸው ላይ ተፅእኖ ሊያሳድር የሚችል የአየር ንብረት መኖሩ አሳስቧቸዋል፡፡ በሌላ በኩል የዓለም ሻምፒዮናውን የተሳካ ያደርጋሉ ከተባሉ ቴክኖሎጂዎች የሚጠቀሰው በስታድዬሙ የተነጠፈው ባለወይንጠጅ ቀለም የመሮጫ ትራክ ነው፡፡ ሞንዶ ትራክ Mondotrack WS የተባለው ይህ የመሮጫ ትራክ በዓለም ሻምፒዮናው የአትሌቲክስ ውድድሮች ፈጣን ሰዓቶች እንዲመዘገቡ ያበረታታል ተብሏል፡፡  በኳታር የዓለም ሻምፒዮናው ብሄራዊ አዘጋጅ ኮሚቴ በውድድሩ ሰሞን በዘመናዊ ድሮን ካሜራዎች የሚነሱ ምስሎችና የቪድዮ ቀረፃዎች አዲስ ምዕራፍ የሚከፈትባቸው እንደሚሆኑ ሲገልፅ፤ የሻምፒዮናው አጠቃላይ ሂደት በጥልቅና የተሟላ የብሮድካስት ተግባራት ሰፊ ሽፋን እንደሚያገኝ እና በማህበራዊ ሚዲያው የተጧጧፈ ትኩረት ለመፍጠር ከፍተኛ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም አስታውቋል።  የካሊፋ ዓለም አቀፍ ስታድዬም በግንቦት ወር የዳይመንድ ሊግ ውድድር በሚያዚያ የኤሽያን አትሌቲክስ ሻምፒዮና በማዘጋጀት እነዚህን ልዩ ቴክኖሎጂዎች እና የዓለም ሻምፒዮና መሰናዶዎች ላይ የመጨረሻ ግምገማ እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡
ኢትዮጵያ ከኳታር በፊት እና የዓለም ሻምፒዮና ታሪኳ
በኳታር ዋና ከተማ ዶሃ በሚካሄደው 17ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያ በሚኖራት ተሳትፎ መዘናጋት ይስተዋላል፡፡ የዓለም ሻምፒዮናው መካሄጃ ወቅት መቀየር፤ የኳታር ሞቃታማ የአየር ንብረት፤ የብሄራዊ ቡድን በቂ እና የተሟላ ትኩረት በተሰጠው ዝግጅት አለመስራት እንዲሁም በአትሌቶች ዲስፕሊን ያሉ ችግሮች ስጋት የሚፈጥሩ ናቸው፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ከወዲሁ መጀመር አለበት፡፡
በ2019 የውድድር ዘመን በዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ የውድድር መድረኮች ውጤታማ እንደሚሆኑ ከተጠበቁ የኢትዮጵያ አትሌቶች መካከል በተለይ ሁለቱ በተደጋጋሚ ስማቸው እየተነሳ ይገኛል፡፡ በሴቶች አትሌት ነፃነት ጉደታ በወንዶች አትሌት ሰለሞን ባረጋ  ናቸው፡፡ በ2018 የዓለም የግማሽ ማራቶን ሪከርድን በሆነ ጊዜ ያስመዘገበችው አትሌት ነፃነት ጉደታ ከዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው በፊት በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ሊሳካላት እንደሚችል ተገምቷል፡፡ ነፃነት በዓለም ሻምፒዮናው በየትኛው የውድድር መደብ እንደምትሳተፍ ግልጽ ባይሆንም ፤ ከ18 ዓመታት በላይ ሳይሰበር የቆየውን የፓውላ ራድክሊፍ ሪከርድ ማሻሻል ከሚችሉ አትሌቶች ግንባር ቀደም ሆና እየተጠቀሰች ናት፡፡ በሌላ በኩል ባለፈው ዓመት በዳይመንድ ሊግ የ5ሺ ሜትር ሻምፒዮን ሊሆን የበቃው አትሌት ሰለሞን ባረጋ በ2019 ከፍተኛ ስኬት ያገኛል በሚል በአይኤኤኤፍ አዳዲስ ኮከቦች ተርታ ተጠቅሷል፡፡ በውድድር ዘመኑ ከ20 ዓመት በታች ምርጥ የኢትዮጵያ አትሌት ሆኖ የሚቀጥለው ሰለሞን ባረጋ በ5ሺ ሜትር ለዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው የሜዳልያ ውጤት ከመጠበቁም በላይ ሳይሰበር ለ12 ዓመታት የቆየውን የ5ሺ ሜትር ሪከርድ እንደሚያሻሽል ግምት አግኝቷል፡፡
ከ2 ዓመት በፊት የእንግሊዟ ለንደን ባስተናገደችው 16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያ በ13 የተለያዩ ውድድሮች 46 አትሌቶችን በማስመዝገብ የተሳተፈች ቢሆንም የሚያስደስት ውጤት አልነበራትም፡፡ ለኢትዮጵያ በሴቶች 10ሺ ሜትርና በወንዶች 5ሺ ሜትር የተመዘገቡት 2 የወርቅ ሜዳልያዎች ብቻ መሆናቸው ከሁለት ተከታታይ የዓለም ሻምፒዮናዎች በኋላ የተመዘገቡ አዳዲስ ስኬቶች ነበሩ፡፡ በሌላ በኩል በሴቶች 10ሺ ሜትር፤ በወንዶች ማራቶን እና በሴቶች 5ሺ ሜትር  3 የብር ሜዳልያዎች በተጨማሪ ተገኝተዋል፡፡ ከሜዳልያ ውጤቶች ባሻገር ደግሞ በ2 አራተኛ ደረጃዎች፤ በ3 አምስተኛ ደረጃዎች፤ በ1 ስድስተኛ ደረጃ፤ በ3 ሰባተኛ ደረጃዎች እንዲሁም በ2 ስምንተኛ ደረጃዎች 11 ዲፕሎማዎች ለኢትዮጵያ ቡድን ተመዝግበዋል፡፡ ከ16ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በኋላ ኢትዮጵያ በሻምፒዮናው የተሳትፎ ታሪኳ ያስመዘገበቻቸው 77 ሜዳልያዎች የደረሱ ሲሆን (27 የወርቅ፤ 25 የብርና 25 የነሐስ ሜዳልያዎች) ናቸው፡፡ በተጨማሪ 20 ጊዜ 4ኛ ደረጃዎች፤ 18 ጊዜ 5ኛ ደረጃዎች፣ 14 ጊዜ 6ኛ ደረጃዎች ፣ 21 ጊዜ 7ኛ ደረጃዎች እንዲሁም 15 ጊዜ 8ኛ  ደረጃዎች ተመዝግበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ውጤታማ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና አትሌቶች
በወንዶች ኃይሌ ገሥላሴ 4 የወርቅ፣ 2 የብር፣ 1 የነሀስ ሜዳሊያዎች
በሴቶች ጥሩነሽ ዲባባ  5 የወርቅ - 1 የብር፣ 1 የነሐስ ሜዳሊያዎች
በኢትዮጵያ አትሌቶች የተያዙ የዓለም ሻምፒዮና ሪከርዶች
ብርሃኔ አደሬ በ10 ሺ ሜትር 30፡10.18 (2003 እ.ኤ.አ)
ቀነኒሳ በቀለ በ10 ሺ ሜትር 26፡46.31 (2009 እ.ኤ.አ)
አልማዝ አያና በ5 ሺ ሜትር 14፡26.83 (2015 እ.ኤ.አ)
የኢትዮጵያ 27 የወርቅ ሜዳልያዎች በ16 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች
ኢትዮጵያ ከ1983 እሰከ 2017 እኤአድረስ በተካሄዱት 16 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች 27 የወርቅ ሜዳልያዎች አስመዝግባለች፡፡እነዚህን  የዓለም ሻምፒዮና 27 የወርቅ ሜዳልያዎች ያስመዘገቡት 15 የተለያዩ አትሌቶች የተጎናፀፏቸው ሲሆን 14 በሴቶች እንዲሁም 13 በወንዶች የተገኙ ናቸው፡፡ 16 የወርቅ ሜዳልያዎች በ10ሺ ሜትር (9 በወንዶች እና 7 በሴቶች)፤ 7 የወርቅ ሜዳልያዎች በ5ሺ ሜትር (5 በሴቶች  እና 2 በወንዶች)፤ 2 የወርቅ ሜዳልያዎች በማራቶን (1 በወንዶች እና 1 በሴቶች)፤ 1 የወርቅ ሜዳልያ በ1500 ሜትር (በሴቶች) እንዲሁም 1 የወርቅ ሜዳልያ በ800 ሜትር (በወንዶች) ናቸው፡፡
ጥሩነሽ ዲባባ  5 የወርቅ ሜዳልያዎች-በ10ሺ ሜትር 3 የወርቅ ሜዳልያዎች (በ2005 እኤአ ሄልሲንኪ፤ በ2007 እኤአ ኦሳካ እንዲሁም በ2013 እኤአ ሞስኮ) በ5ሺ ሜትር 2 የወርቅ ሜዳልያዎች (በ2003 እኤአ ፓሪስ እና በ2005 እኤአ ሄልሲንኪ)
ቀነኒሳ በቀለ 5 የወርቅ ሜዳልያዎች -በ10ሺ ሜትር4 የወርቅ ሜዳልያዎች (በ2003 ፓሪስ፣ በ2005 ሄልሲንኪ፤ በ2007 እኤአ ኦሳካ እና በ2009 እኤአ በርሊን) በ5ሺ ሜትር 1 የወርቅ ሜዳልያ ( በ2009 እኤአ በርሊን) ሳላዲን
ኃይሌ ገብረስላሴ4የወርቅ ሜዳልያዎች - በ10ሺ ሜትር 4 የወርቅ ሜዳልያዎች (በ1993 እኤአ ስቱትጋርት፤ በ1995 እኤአ ጉተንበርግ፤ በ1997እኤአ አቴንስ  እንዲሁም በ1999 እኤአ ሲቪያ)    
መሰረት ደፋር 2 የወርቅ ሜዳልያዎች- በ5ሺ ሜትር (በ2007 እኤአ ሄልሲንኪ እና በ2013 እኤአ ሞስኮ)
ገዛሐኝ  አበራ 1 የወርቅ ሜዳልያ- በማራቶን(በ2001 እኤአ ኤደመንተን)
ማሬ ዲባባ 1 የወርቅ ሜዳልያ- በማራቶን (በ2015 እኤአ ቤጂንግ)
ጌጤ ዋሚ 1 የወርቅ ሜዳልያ- በ10ሺ ሜትር(በ1999 እኤአ ሲቪያ)
ደራርቱ ቱሉ 1 የወርቅ ሜዳልያ- በ10ሺ ሜትር (በ2001 እኤአ ኤድመንተን)
ብርሃኔ አደሬ1 የወርቅ ሜዳልያ - በ10ሺ ሜትር (በ2003 እኤአ ፓሪስ)
ኢብራሂም ጄይላን 1 የወርቅ ሜዳልያ - በ10ሺ ሜትር (በ2011 እኤአ ዴጉ)
አልማዝ አያና 2 የወርቅ ሜዳልያ - በ10ሺ ሜትር (በ2017 እኤአ ለንደን)
በ5ሺ ሜትር (በ2015 እኤአ ቤጂንግ)
ገንዘቤ ዲባባ  1 የወርቅ ሜዳልያ- በ1500  ሜትር (በ2015 እኤአ ቤጂንግ)
መሐመድ አማን 1  የወርቅ ሜዳልያ- በ800 ሜትር (በ2013 እኤአ ሞስኮ)
ሙክታር ኢድሪስ 1 የወርቅ ሜዳልያ በ5ሺ (በ2017 እኤአ ለንደን)

Page 13 of 426