Administrator

Administrator

በሶሪያ መላ የታጣለትን የእርስበርስ ጦርነት በመሸሽ ወደ ዮርዳኖስ የተሰደዱ እናቶች፣ ህይወት ፈተና ሆኖባቸው ሴት ልጆቻቸውን “ለጊዜያዊ ትዳር” እየሸጡ ነው፡፡ ስደተኛ ወላጆች በሴት ልጆቻቸው ላይ መጨከን እንደጀመሩ የዘገበው ሲኤስ፣ ኑሮን ለመግፋት የሚያስችላቸው ብቸኛ አማራጭ ሆኖ ያገኙት ሴት ልጆቻቸውን በሺዎች በሚቆጠሩ ዶላሮች ለጋብቻ መሸጥ ነው፡፡ ከዮርዳኖስም ሆነ በሌሎች የመካከለኛው ምስራቅ አገራት ጋብቻ ፈላጊ ወንዶች ለሴቷ ቤተሰቦች ገንዘብ የሚሰጡበት ባህል አለ፡፡ ይሄም ሆኖ ግን የሰሞኑ የዮርዳኖስ ስደተኛ ካምፖች “የጋብቻ ገበያ”፣ እርግጥም ወንዶች ሴቶችን ለዘላቂ ትዳር የሚገዙበት አይደለም፡፡ አብዛኛዎቹ “ትዳሮች” ከሳምንታት የዘለቀ ዕድሜ እንደማይኖራቸው የገለፀው ዘገባው፤ ይልቁንም “የወሲብ ገበያ” ሊባል የሚችል መሆኑን አስረድቷል፡፡

ይህንን የሴት ልጆች ሽያጭ ከሚያቀላጥፉትና ራሳቸውን “የጋብቻ ደላላ” ብለው ከሚጠሩት መካከል ሶሪያዊቷ ስደተኛ ኡም ማጄጅ አንዷ ናት፡፡ ኡም ማጄድ ከሰሞኑ እየጦፈ በመጣው የስደተኛ ልጃገረዶች ሽያጭ ገበያ ፋታ አጥታለች፡፡ የሞባይል ስልኳ በገዢዎች ጥሪ ተጨናንቋል፡፡ ኡም ማጄድ ከወላጆች ጋር በመነጋገር ለሽያጭ ከምታቀርባቸው ሴቶች ጠቀም ያለ ኮሚሽን ታገኛለች፡፡ ክብረ ንጽህናዋ ያልተገረሰሰ ልጃገረድ በሰሞኑ ገበያ እስከ 5ሺህ ዶላር ታወጣለች፡፡ አያ የተባለችዋ የ17 አመቷ ሶሪያዊት ስደተኛ አያ፤ ከቤተሰቦቿ ጋር በስደት ወደ ዮርዳኖስ ከመጣች አንድ አመት ያህል ሆኗታል፡፡

ይሄም ሆኖ ግን የስደት ኑሮ ለእሷም ሆነ ለቤተሰቧ አሳር ሲሆንባቸው፣ ብቸኛውን አማራጭ ለመውሰድ ተገደዱ፡፡ አያ ለ70 አመት ሳኡዲ አረቢያዊ “ትዳር ፈላጊ” ሽማግሌ በ3ሺህ 500 ዶላር ተሸጠች፡፡ ትዳር ፈላጊው ሽማግሌ ግን ከሙሽሪት አያ ጋር የመሰረተውን ትዳር ለማፍረስ የፈጀበት የአንድ ወር ጊዜ ብቻ ነበር፡፡ “ከእሱ ጋር ያሳለፍኩት አንድ አመት ልክ እንደ አስፈሪ ቅዠት ነበር፡፡ ግማሹን ወር በመራር ለቅሶ ነው ያሳለፍኩት፡፡ ከቤተሰቦቼ ጋር እንድገናኝና እንዳወራ አይፈቅድልኝም ነበር፡፡ ምርጫ አልነበረኝምና በሰቀቀን ነበር የምኖረው” ብላለች - አያ ስለ ሽያጩ ትዳሯ ስትናገር፡፡

እንዲህ ለጋ ልጃገረዶችን ለገበያ አቅርባ የምታሻሽጠው ኡም ማጄድ እየሰራችው ስላለችው ነገር ሃፍረትም ሆነ ፀፀት አይሰማትም፡፡ “መኖር የምችልበት ብቸኛው መንገድ ይህ “ስራ” ነው፡፡ ሶሪያውያን ስደተኞች በዮርዳኖስ ሌላ ስራ መስራትና ገቢ ማግኘት አንችልም፡፡ ስለዚህ ምን ማድረግ እንችላለን?...እንስረቅ?...እንግደል?” ትላለች ማጄድ፡፡ የሚገርመው ግን “አንቺስ የ13 አመት ልጃገረድ ልጅሽን ለመሸጥ ትፈቅጃለሽ?” ለሚለው የጋዜጠኞች ጥያቄ የሰጠችው መልስ ነው፡፡ “በፍፁም አላደርገውም!... ልጆቼን ከምሸጥ አይኖቼን አውጥቼ ብሸጣቸው እመርጣለሁ!” ነው ያለችው ማጄድ፡፡

Saturday, 18 May 2013 10:04

የ5 ሚሊዮን ብር መኪና

የዛሬ አርባ አመት ገደማ፣ ይህን ማዕረግ ለማግኘት የመኪናዋ አቅም 300 የፈረስ ጉልበት መሆን ነበረበት። ፍጥነቷም ቢያንስ ከ160 ኪሎሜትር በላይ። ዛሬ ይሄ ተቀይሯል። ሱፐርካር ለመባል ከ600 በላይ የፈረስ ጉልበት፣ እንዲሁም በሰዓት ከ350 ኪሎሜትር በላይ የመብረር አቅም ያስፈልጋል። ይህን መመዘኛ አሟልተው በአመቱ ከተመረቱት ልዩ መኪኖች መካከል፣ በማክማረን ኦቶሞቲቭ የተሰራው ስፓይደር የተሰኘው መኪና የ“ራብ ሪፖርት” ምርጫ ሆኗል።

ከመቼው የመኪናው ሞተር ተነስቶ፣ ከመቼው መብረር እንደሚጀምር ሲታይ ያስደንቃል። በሶስት ሴኮንድ ውስጥ፣ ፍጥነቱ ከ“95” በላይ ይሆናል። በሌላ አነጋገር፣ ቆሞ የነበረው መኪና… ገና 1፣ 2፣ 3 ብለን ቆጥረን ሳንጨርስ፣ ከ400 ሜትር በላይ ርቀት ተጉዟል። ከዚያማ ማርሽ እየቀየሩ ፍጥነት መጨመር ብቻ ነው - በሰባት ማርሽ። በአንድ ሊትር 10 ኪሎሜትር ይጓዛል። ታዲያ ዋጋው ቀላል አይደለም። 266ሺ ዶላር ነው (5 ሚሊዮን ብር ገደማ መሆኑ ነው)።

በመፅሄቱ ሪፖርት ላይ እንደዘረዘረው፣ የማክማረን ስሪት የሆነው “ስፓይደር”፣ እንደፌራሪና ላምቡርገኒ ከመሳሰሉ በጉልበትና በፍጥነት ከሚታወቁ የቅንጦት መኪኖች በምንም አያንስም። ለነገሩ ማክማረን የሚያመርታቸው የስፖርት ውድድር መኪኖችም፣ በአለም የሚታወቁ ናቸው። የተለያዩ ውድድሮችን በማሸነፍ፣ ከፌራሪ ቀጥሎ የሚጠቀሰው ማክማረን ነው ይላል ሪፖርቱ። በእርግጥ የስፖርት መኪኖቹ ዋጋ ከፍ ይላል። በ2013 መጨረሻ አካባቢ ከ“ስፓይደር” ጎን ለገበያ የሚቀርበው “ፒ1” የተሰኘ አዲስ የማክማረን የስፖርት መኪና፣ ዋጋው 1.1 ሚሊዮን ዶላር ነው - ሃያ ሚሊዮን ብር! ጉልበቱና ፍጥነቱ ግን እንደ ዋጋው ነው። በ960 የፈረስ ጉልበት፣ በሰዓት 400 ኪሎሜትሩን ፉት ብሎ መጨረስ ይችላል።

ወርዷ ክንፎቿንም ጨምሮ፣ ከአንድ ጣት ውፍረት ብዙም አይበልጥም። “ንብ የምታክል ሮቦት” ለማለትም ይመስላል፤ ስሟን RoboBee ብለው የሰየሟት። በእርግጥ ባለፉት አስር አመታት በተካሄዱ ጥናቶችና ምርምሮች ጥቃቅን በራሪ ማሽኖች (ሮቦቶች) ተፈጥረዋል። ሁለት ሶስት ግራም የሚመዝኑ ብቻ ሳይሆኑ፤ ከአንድ ግራም በታች ክብደት ያላቸው እንደ ነፍሳት ማንዣበብ ወይም መብረር የሚችሉ ሮቦቶች ተሰርተዋል። በሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ አራት የጥናት አመታትን የጠየቀው RoboBee (ሮቦንብ) ግን፣ ከእስካሁኖቹ ጥቃቅን በራሪዎች ሁሉ እጅጉን ያነሰ ነው። 12 በራሪዎች ቢመዘኑ፣ በድምር አንድ ግራም አይሞሉም።

የተመራማሪዎቹ ጥረት ተሳክቶ ሰሞኑን፣ እንደ ንብ ክንፉን የሚያርገበግብ በራሪ ሮቦት በይፋ አስመርቀዋል። ደግሞም፣ እንደ ንብ መንጋ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ “ንብ የመሰሉ ሮቦቶችን” ማምረት ቀላል እንደሆነ ተመራማሪዎቹ ገልፀዋል። “ድንቅ ፈጠራ” ተብሎ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ተቋማት የተደነቀው “ሮቦንብ”፣ በብዙዎች ዘንድ ስጋት ማሳደሩ አልቀረም። ትናንሽና ጥቃቅን በራሪ አካላት አሁን አሁን ቁጥራቸው እየተበራከተ መጥቷል። መንግስታት ለወታደራዊ ስለላና ለፖሊስ ቅኝት በራሪ “ሮቦቶችን” መጠቀም ጀምረዋል። ዜጎችን ለመሰለልና የአፈና ቁጥጥር የማካሄድ ጥማት ያለባቸው መንግስታት፤ በየከተማው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ትናንሽና ጥቃቅን በራሪ ሮቦቶችን ቀን ከሌት እንዳያዘምቱ ምን ያግዳቸዋል? አሳሳቢው ነገር ይሄ ነው።

“ እኔ ወደጋንዲ ሆስፒታል የመጣሁት ሁለት ሴት ልጆች የመደፈር ጥቃት ስለደረሰባቸው ነው፡፡ ልጆቹ የጎረቤት እና የራሴ ሲሆኑ የጎረቤ ልጅ የዘጠኝ አመት ስትሆን የእራሴ ግን የሰባት አመት ናት፡፡ ልጆቹ ለእኛ እንደነገሩን ከሆነ የመደፈር ጥቃት የተፈጸመባቸው አንድ ጊቢ አብሮን በሚኖር ሰው ነው፡፡ በእርግጥ ገና በህግ እስኪረጋገጥ እንዲህ ነው ማለት ባይቻልም የልጆቹ አንደበት የመሰከረው ይህንኑ ነው፡፡ አሁን በሕክምናው ታይተዋል፡፡ ቀጥሎ ደግሞ በፖሊስ መዝገብ ላይ ሁኔታው ሰፍሮ ወደ ፍትሕ እንሄዳለን፡፡ ጉዳዩ እጅግ በጣም ፈታኝ ነው፡፡ እኛም ተከራዮች ነን...እሱም ተከራይቶ የሚኖር ነው፡፡ ወደፊት እንዴት እንደምናደርግ አላውቅም” አሳካሚ እናት... የሴቶችና ሕጻናት የተቀናጀ የፍትህና የእንክብካቤ ማአከል በጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታል ከተቋቋመ ሚያዝያ 2005 ዓ/ም ልክ አንድ አመት ሆኖታል፡፡

ማእከሉ በዩኒሴፍ የገንዘብ እርዳታ እና በፍትህ ሚኒስር የበላይነት የተቋቋመው የዛሬ አመት ሚያዝያ 22/2004 ዓ/ም ነበር እንደ ዶ/ር ደረጀ አለማየሁ የጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር መረጃ ፡፡ይህ ማእከል ከመቋቋሙ በፊት በአገር አቀፍ ደረጃ የሚመለከታቸው መስሪያ ቤቶች ተወካዮች ያሉበት አንድ ኮሚ ተቋቁሞ ልምድ ለመቅሰም ወደ ደቡብ አፍሪካ እንዲሄድ ተደርጎ የነበረ ሲሆን በዚያ መሰረት ማእከሉ ተቋቁሞ አገልግሎት በመስጠት ላይ ነው፡፡ የሴቶችና ሕጻናት የፍትህና የእንክብካቤ ማእከል አገልግሎት የሚሰጠው ከፈቃዳቸው ውጭ በሆነ መንገድ የግዳጅ ወሲብ ለተፈጸመባቸው ሴቶች ሲሆን በዚህ አንድ አመት ውስጥ ወደ 1100/አንድ ሺህ አንድ መቶ የሚሆኑ ባለጉዳዮች ተስተናግደዋል፡፡ በእድሜም ከአንድ አመት ከአራት ወር ሕጻን እስከ 80/ሰማንያ አመት የእድሜ ባለጸጋ የሚሆኑ ሴቶች የአስገዳጅ ወሲብ ተፈጽሞባቸዋል፡፡

የዚህን ማእከል የስራ እንቅስቃሴ ለመመልከት በጋንዲ ሆስፒታል በተገኘንበት ወቅት የሁለት አመት ከስድስት ወር ሴት ሕጻን በዚሁ ጉዳይ በሐኪም እየታየች ነበር፡፡ አስተባባሪ ነርስ የሆነችው ሲስተር ሙሉነሽ ወልደመስቀል በማእከሉ ከአስተባባሪነት በተጨማሪ ከስነአእምሮ ጋር በተገናኘ ችግር ያለባቸውን እንዲሁም ከመደፈር ጋር ተያይዞ ጭንቀት የደረሰባቸውን ማረጋጋት እንዲሁም ሕክምና መስጠት የመሳሰለውን ሁሉ ትሰራለች፡፡ ሲስተር ሙሉነሽ እንደገለጸችው ሴቶች በቤታቸው፣ በስራ ቦታ እንዲሁም በተለያየ አጋጣሚ ሊደፈሩ ስለሚችሉ አገልግሎቱ የሚሰጠው የእድሜ ገደብ ሳይኖረው ለሁሉም ሴቶች ነው፡፡ የመደፈር ጥቃት በሴቶች ብቻ ሳይሆን በወንዶች ላይም እንደሚከሰት የታወቅ ሲሆን ማእከሉም እንደ ተከፈተ ብዙ ወንዶች የሐኪም መረጃ ለማግኘት ወደማእከሉ ቢመጡም ሊሟሉ የሚገባቸው ብዙ የህክምና አሰራሮች ስላሉ በአሁኑ ወቅት ግን የወንዶቹ ተቋርጦአል። ስለዚህ ወንዶቹ የሚሄዱት ወደሌሎች ሆስፒታሎች ሲሆን ጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታል የሴቶች እንደመሆኑ መጠን ሴቶቹ ሙሉ ለሙሉ ሕክምናው ይሰጣቸዋል ብለዋል፡፡

በማእከሉ የሚሰጠውን አገልግሎት ተዘዋውረን እንደተመለከትነው ከሆነ ሕጻናቱ የሚጫወቱባቸው ቁሳቁሶች እንዲሁም ቤተሰብ የሌላቸው ለተወሰኑ ቀናት የሚያርፉበት መኝታ ክፍል እና በተሟላ የምግብ አቅርቦት እንደሚስተናገዱ ለመመልከት ተችሎአል፡፡ ሲ/ር ሙሉነሽ ወልደመስቀል እንደተናገሩት ከሆነ ሕጻናቱን እና የተጎዱትን በማስተናገዱ ረገድ በክፍሉ ውስጥ ያሉት ነርሶች በሙሉ ፈቃደኝነት አገልግሎቱን እንደሚሰጡ ለመረዳት ተችሎአል፡፡ ዶ/ር ስንታየሁ ታከለ የማእከሉ አስተባባሪ ናቸው፡፡ ዶር ስንታየሁ እንደገለጹት ተጠቂዎቹ ሕጻናት ከሆኑ በቤተሰባቸው አማካኝነት አዋቂዎቹ ደግሞ እራሳቸው ወደማእከሉ ይቀርባሉ። ማንኛዋም ሴት ተደፍሬአለሁ ስትል ቃሉዋ ታማኝነት አለው። ስለዚህ ተጠቂዋ ካርድ በማውጣት የህክምናውን አገልግሎት ለላቦራቶሪ ፣ለመድሀኒት፣ ተኝቶ ለመታከም ...ወዘተ ሁሉንም ሙሉ በሙሉ በነጻ ታገኛለች፡፡ በተለይም ሴትዋ ጥቃቱ በተፈጸመ በቅርብ ቀን ድረስ ባለው ጊዜ ...ማለትም ፡- ጥቃቱ ከተፈጸመባት እስከ ሶስት ቀን ድረስ ባለው ጊዜ ወደማእከሉ ከመጣች ከኤችአይቪ ቫይረስ ለመከላከል የሚያስችለውን መድሀኒት እንድታገኝ ይደረጋል፡፡ ጥቃቱ በተፈጸመ እስከ አምስት ቀን ድረስ ወደ ሕክምናው ማአከል ከመጣች ያልተፈለገ እርግዝናን ለመከላከል የሚያስችል መድሀኒት ይሰጣታል፡፡ ጥቃቱ ከተፈጸመባት እስከ ሁለት ሳምንት ድረስ ባለው ጊዜ ከመጣች የአባላዘር በሽታ እንዳይይዛት የሚከላከል መድሀኒት ይሰጣታል፡፡

ዶ/ር ስንታየሁ እንደችግር የገለጹት ተጠቂዎቹ ሁሉም በቅርብ ቀን ውስጥ ወደህክምና ማእከሉ አለመምጣታቸውን ነው፡፡ ማእከሉ ከተከፈተ ጀምሮ እንደታየው ልምድ ከሆነ ሴቶች የሚመጡት ጥቃቱ በተፈጸመ ከሶስት እስከ ስድስት ወር እና ከዚያም ካለፈ በሁዋላ ነው፡፡ አንዳንዶቹ ወደማእከሉ የሚደርሱት ያልተፈለገ እርግዝና ከተከሰተባቸው በሁዋላ ሲሆን በአገሪቱ የውርጃ ሕግ መሰረት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚደረግ ቢሆንም በከፊል ይህንን እርዳታ ሊያገኙ የማይችሉ ይሆናሉ። ለምሳሌም እርግዝናው ከ28/ሀያ ስምንት ሳምንት በላይ ከሆነው ተንከባክበናት እንድትወልደው ከማድረግ ውጭ ሌላ እርዳታ ማድረግ አይቻልም፡፡ከዚያም ውጭ ሌሎች በሽታዎችን ለመከላከል ሲባል ሊያገኙ የሚገባቸውን እርዳታ እንዳያገኙ ይሆናሉ እንደዶክተር ስንታየሁ ማብራሪያ፡፡ ዶ/ር ስንታየሁ አክለውም ይህ ማእከል ከሚሰራቸው ስራዎች መካከል የህክምና ማስረጃ መስጠት ይገኝበታል፡፡ ይህ የህክምና ማስረጃ እንደቀድሞው በእንግሊዝኛ ሳይሆን በአማርኛ የሚጻፍ ነው፡፡ እንደቀድሞው በእንግሊዝኛ ተዘጋጅቶ ወደትርጉም ቤት የሚያስኬድ እና የሚያስቸግር ሳይሆን በወቅቱ በሴትዋ አካል ላይ የተገኘውን መረጃ መሰረት በማድረግ ወደፖሊስ የሚላበት ነው ፡፡

በእርግጥ ይህ ወንጀል ነው አይደለም የሚለውን የሚወስነው የፍትህ አካሉ እንጂ ሕክምናው አይደለም፡፡ በዚህ አጋጣሚ የምናገረው አሉ ዶ/ር ስንታየሁ ...ማንኛዋም ጥቃቱ የደረሰባት ሴት ችግሩ በደረሰ ውስን ቀናት ውስጥ ወደማእከሉ መቅረብ ብትችል መረጃውን በተሟላ ሁኔታ ማቅረብ ይቻላል፡፡ ነገር ግን ብዙዎቹ የቆሰለው አካላቸው ድኖ ገላቸውን ፣ልብሳቸውን ታጥበው እና ከቀናትም ባለፈ ወራት ፈጅተው ስለሚመጡ ምንም መረጃ የማይገኝበት አጋጣሚ ብዙ ነው ብለዋል ዶ/ር ስንታየሁ ታከለ የማእከሉ አስተባባሪ፡፡ በማእከሉ ያገኘናት የፖሊስ ባልደረባ ም/ሳይጅን ጽጌ ደግፌ ትባላለች፡፡ ም/ሳጅን ጽጌ ቢሮ ውስጥ አንድ ጥሩ አሻንጉሊት ፊት ለፊት ተቀምጦአል፡፡ እሱዋም እንደገለጸችው ይህ አሻንጉ ሊት ሴቶቹ በተለይም ህጻናቱ የደረሰባቸውን ችግር ለማስረዳት እፍረት ቢሰማቸውና ድብቅ ቢሆኑ እንዲናገሩ ለማጫወቻነት የተቀመጠ ነው፡፡

እንደ ምክትል ሳይጅን ጽጌ መግለጫ ቀደም ሲል በፖሊስ ጣቢያ ይህ ስራ በሚሰራበት ጊዜ መረጃው በፍጥነት ስለማይደርስና ባለጉዳ ዮቹም ከቦታ ቦታ በመዘዋወር እንግልት ስለሚደርስባቸው ጉዳዩ ፍትህ ሳያገኝ መዝገብ የሚዘጋበት እና ተከሳሾች ነጻ የሚወጡበት አጋጣሚ ይስተዋል ነበር፡፡ አሁን ግን ከአንድ አመት ወዲህ ይህ የፖሊስ ስራ ከህክምናው ጋር ተጣምሮ በአንድ ማእከል ውስጥ ሐኪም፣ አቃቤ ሕግ እና ፖሊስ በመሆን መስራት በመቻሉ ውጤቱን በፍጥነት በመቀባበል ተጎጂዎቹም ሳይንገላቱ መረጃው ለፍትህ አካላቱ እንዲደርስ አስችሎአል፡፡ ም/ሳይጅን ጽጌ የተጠቂዎችን የእለት ሁኔታ ስትገልጽ ከአስሩም ክፍለ ከተማ አንዳንድ ጊዜ ምንም ተጎጂ ላይመጣ ሲችል አንዳንዴ ደግሞ በቀን እስከ አስር እና ከዚያም በላይ ሴቶች ተጎጅዎች ወደ ማከሉ ሊመጡ ይችላሉ፡፡ በእድሜ ደረጃም በአብዛኛው ሕጻናት በተለይም እስከ አስራ አምስት አመት ድረስ ያሉት ተጎጂዎች ናቸው፡፡ በጋንዲ ሆስፒታል በተቀቋቋመው ማእከል ውስጥ አገልግሎት የሚያገኙ ተጎጂዎች ሕክምናውን ካገኙና የደረሰውን ችግር ካስረዱ በሁዋላ ወደመጡበት ክፍለ ከተማ በመሄድ የፖሊስ ሪፖርቱን እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡ ጉዳት ያደረሱት ሰዎች ተገቢውን የፍትህ እርምጃ እንዲያገኙና ተጎጂዎቹም በዚህ ፍትሕ እንዲረኩ ለማድረግ ዋናው የህክምናው ማስረጃ ሲሆን ለዚህም ተጎጂዎች በጊዜ ወደህክምና ማእከሉ በመቅረብ ተገቢውን ክትትል ቢያደርጉ ለአሰራር ይበልጥ አመቺ መሆኑን እንመሰክራለን፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከፍትሕ አካሉና ከህክምና ማእከሉ ጋር በመጣመር ይህንን ስራ ከጀመረ ወዲህ በሴቶችና በቤተሰብ ላይ የነበረው መንገላታት በእጅጉ መቀነሱን መመስከር ይቻላል ብላለች ም/ሳጅን ጽጌ ደግፌ፡፡ የሜዲካል ዳይሬክተሩ ዶ/ር ደረጀ አለማየሁ እንደሚሉት ፖሊስ፣ አቃቤ ህግና የህክምናው ዘርፍ በጋራ የሚሰሩበት ይህ የሴቶችና ሕጻናት የተቀናጀ የፍትህና የእንክብካቤ ማእከል በሀገራችን የመጀመሪያው ሞዴል ማእከል ነው፡፡ የጋንዲ ሆስፒታል የተመረጠበትም ምክንያት የሴቶች ሆስፒታል ስለሆነ እና አገልግሎቱን ከዚያ በፊትም ስለሚሰጥ ነው፡፡ በፌደራል ጤና ጥበቃ ሚኒስርና በጤና ቢሮ አማካኝነት ጥያቄው ሲቀርብ የህብረተሰቡ ትልቅ ችግር እና ሴት ሕጻ ናቱ የሚጎዱበት እንደመሆኑ ጋንዲ ሆስፒታልም የራሱን ግልጋሎት ሊሰጥ ይገባል በሚል ከስም ምነት ተደርሶ እነሆ ስራው ከተጀመረ አንድ አመትን አስቆጥሮአል፡፡

በአሁኑ ወቅት በአገራ ችን ከፍላጎታቸው ውጭ የወሲብ ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች የህክምና ማስረጃን ለፍትህ አካል የማ ቅረብ ስራን የሚሰራው ይህ በጋንዲ ሆስፒታል የሚገኘው የሴቶችና ሕጻናት የተቀናጀ የፍት ህና የእንክብካቤ ማእከል ብቻ ነው፡፡ ወንዶቹን በሚመለከት ግን የህክምናውን ማስረጃ በትክክል ከሚመለከተው ሐኪም የማግኘትን አሰራር በመከተል ወደ ጥቁር አንበሳ እና ዘውዲቱ ሆስፒታል እንዲሄዱ ይደረጋል ብለዋል ዶ/ር ደረጀ አለማየሁ የጋንዲ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር፡፡

በአዲስ ተስፋ የተዘጋጀ “የፊልም ድርሰት አፃፃፍ ብልሃት” የተሰኘ አዲስ መጽሐፍ ሰሞን ለንባብ በቅቷል፡፡ ረዳት ፕሮፌሰር ሙሉጌታ ጀዋሬ በመጽሐፉ ጀርባ ላይ በሰጡት አስተያየት፤ “የአገራችን የፊልም ኢንዱስትሪ በእውቀት የሚጽፉ ሙያተኞች እጅጉን ያስፈልጉታል፡፡

አሁን አሁን በፊልም ጥበብ ላይ የተዘጋጁ መፃሕፍት ታትመው ለንባብ እየበቁ ነው… የፈጠራ ጽሑፍ ተሰጥኦ እያላቸው አቅጣጫው (ቴክኒኩ) ለጠፋቸው ሁሉ እነሆ አቅጣጫው እላለሁ” ብለዋል፡፡ መጽሐፉ ከያዛቸው አብይ ርዕሰ ጉዳዮች መካከል “የድራማ ምንነትና ታሪክ”፣ “ፊልም ምንድነው?” “ፊልም እንዴት ይፃፋል” እና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡ በ171 ገፆች የተቀነበበው መጽሐፉ በ55 ብር እየተሸጠ ነው፡፡

ጥበብ ኢትዮጵያ የጥበባት ማዕከል አምስተኛውን “ኢትዮጵያ ታንብብ” የንባብ ፌስቲቫል ከትላንት በስቲያ የጀመረ ሲሆን ፌስቲቫሉ ለአምስት ቀናት በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚቀጥል ታውቋል፡፡ በተለያዩ የንባብ ፕሮግራሞች በሚካሄደው በዚህ ፌስቲቫል፤ በአንደኛ ደረጃ ት/ቤቶች ታላላቅ ደራሲያን የንባብ ልምዳቸውን የሚያካፍሉበት መድረክ የተዘጋጀ ሲሆን ስለአገራችን የንባብ ባህል ጥናታዊ ጽሑፍ እንደሚቀርብም ተገልጿል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ መጽሐፍ አሳታሚዎች፣ አታሚዎች፣ አከፋፋዮች፣ ቤተመፃሕፍትና ማተሚያ ቤቶች የሚሳተፉበት ለአምስት ቀን የሚቆይ የመጽሐፍ አውደርዕይ እና ባዛር እንደተዘጋጀም ለማወቅ ተችሏል፡፡

ተወዳጅነትን ያተረፈው “ግጥም በጃዝ” ፕሮግራም 22ኛ ዝግጅቱን የፊታችን ሪቡዕ ምሽት በራስ ሆቴል እንደሚያቀርብ አዘጋጆቸ አስታወቁ፡፡ አንጋፋው አርቲስት ተፈሪ ዓለሙን ጨምሮ አንዱዓለም ተስፋዬ፣ ምንተስኖት ማሞ፣ ደምሰው መርሻና ይሄነው ቸርነት የግጥም ሥራቸውን ሲያቀርቡ ሀብታሙ ስዩም ወግ ያቀርባል ተብሏል፡፡ በኃይሉ ገ/መድህን በበኩሉ ዲስኩር እንደሚደሰኩር ታውቋል፡፡

መጋቢት 29 ቀን 2005 ዓ.ም ማለዳ እንግዶች ለመቀበል ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ ነበርኩ፡፡ ግልፅ ባልሆነ ምክንያት እንግዶችን የሚቀበሉም ሆነ የሚሸኙ ሰዎች የሚገቡበት በር አልተከፈተም ነበርና ውጭ ለመቆም ተገደድኩ፡፡ ብዙ አውሮፕላኖች ስለአረፉ ተጓዦች፣ ሆስተሶችና ፓይለቶች ወደ ውጭ ይጎርፋሉ፡፡ ሆስተሶቹና አንዳንድ ፓይለቶች ቆመው ወደቤታቸው የሚወስዳቸውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ መኪና ይጠባበቃሉ፡፡ የሚጠብቁት መኪና ማቆሚያ ቦታ ላይ ሆነው ነው፡፡ ምንም መቀመጫ ስላልነበረም አንዳንዶቹ ሆስተሶች ሻንጣቸው ላይ ተቀምጠው አየሁ፡፡ ነገሩን ለመቀበል ስላዳገተኝ በሞባይሌ ጥቂት ፎቶዎች አነሳሁ፡፡

እነዚህ ሆስተሶች እዚህ የደረሱት ቢያንስ ከአራት ሰአት በረራ በኋላ ነው፡፡ ከዚያ በፊትም ዝግጅት ማድረግ ስለሚኖርባቸው ሌሊቱን ሳይተኙ ነው የመጡት ማለት ነው፡፡ በበረራው ጊዜም አንድ አውሮፕላን ህዝብ ሲንከባከቡ እንዳደሩ ግልጽ ነው፡፡ እንደኔ ግምት እነዚህ ሰዎች በዚያ ጠዋት የሚመኙት ዋና ነገር ቢኖር ወደቤታቸው ቶሎ ሄደው መተኛት ነው፡፡ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቢቻል እንደመጡ የሚወስዳቸው መኪና፣ባይቻል ደግሞ ከነክብራቸው የሚቆዩበት ማረፊያ ቦታ ማዘጋጀት ለምን ተሳነው? ነገሩን መቀበል ያቃተኝ እኔ ብቻ አልነበርኩም፡፡ አንድ ከፊቴ የቆመ ሰው “እስቲ አሁን ዝናብ ቢኖር እንዴት ነው እዚህ ሆነው የሚጠበቁት?” አለ፡፡

ሌላው ያስገረመኝ ነገር ደግሞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሆስተሶቹንና ፓይለቶቹን ለማጓጓዝ የሚጠቀምበት ብዙ ዓመታት ያገለገሉ መኪኖችን ነው፡፡ እቃ መጫኛ ስለሌለው ሻንጣም ሰውም አብሮ ነው የሚጫነው፡፡ አንድ ከሻንጣ ጋር የተጫነ ፓይለት እያየሁ እንዲህ ስል አሰብኩ “በመቶዎች የሚቆጠር ሰዎችን በጥንቃቄ ሲያበር ያደረን ሰው እንዲህ መጫን ምን ይባላል?” ስንት ከባድ ነገሮችን አቅዶ ለሚያሳካው አየር መንገድ ምክር ካስፈለገው ከኋላቸው የሚከፈቱ ሚኒባሶች ቢኖሩት ሰዎቹ ከፊት ከነክብራቸው ሲቀመጡ፣ ሻንጣዎች ከኋላ እንዲሆኑ ማድረግ ይቻል ይሆናል፡፡ አየር መንገዱን የላቀ አየር መንገድ ለማድረግ፣ለሠራተኞቹ አያያዝ ትኩረት መስጠት እንደሚገባው ባስታውሰው ከአጉል ድፍረት እንደማይቆጠርብኝ በመተማመን ነው፡፡

የዛሬ አስር ዓመት የአስራ ሰባተኛ ዓመት የልደት በአሏን ለማክበር አንድ ቀን ሲቀራት ለስራ እንደወጣች አልተመለሰችም- አሜሪካዊቷ አማንዳ ቤሪ፡፡ ደብዛዋ ከመጥፋቱ በፊት ግን እህቷ ጋ ደውላ ከምትሰራበት ቦታ ወደ ቤት የሚመልሳት መኪና እንዳገኘች ተናግራ ነበር፡፡ የ14 ዓመቷ ጂና ደግሞ የዛሬ ዘጠኝ ዓመት ትምህርትቤት እንደሄደች አልተመለሰችም፡፡ ናይት ከሁለቱ ቀደም ብላ በ2002 ዓ.ም ደብዛዋ የጠፋ የ20 አመት ወጣት ነበረች፡፡ ሶስቱ ሴቶች በተለያዩ ጊዜዎች የጠፉ ቢሆንም ተመሳሳይ ታሪክ አላቸው፡፡ ሶስቱም ፔድሮ ካስትሮ በተባለ ግለሰብ ታግተው በመኖሪያቤቱ ምድርቤት ውስጥ የተለያዩ ስቃዮችን አሳልፈዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለው ግለሰቡ ሴቶችን በመኪና ልሸኛችሁ (ሊፍት ልስጣችሁ) እያለ ነበር ወጥመድ ውስጥ ያስገባቸው፡፡

ሶስቱ ሴቶች እንደታገቱ በተለያዩ ክፍሎች ተነጣጥለው እንዲቀመጡ ያደረገ ቢሆንም በኋላ ላይ አንድ ላይ እንዳደረጋቸው ባለታሪኮቹ ይናገራሉ፡፡ በዓመታት የእገታ ቆይታቸው ተገደው ተደፍረዋል ፤ ለሳምንታት ምግብ ተከልክለዋል፤ ድብደባ ተፈፅሞባቸዋል ፤ በሰንሰለትም ታስረዋል፡፡ በፖሊስ መረጃ መሰረት ፤ ከሴቶቹ አንዷ አምስት ጊዜ ተገዳ ተደፍራ አምስት ጊዜ የፅንስ መጨናገፍ ደርሶባታል - በተፈፀመባት ድብደባ እና የምግብ ክልከላ የተነሳ፡፡ የሴቶቹ የመሰወር ምስጢር በቅርቡ እስኪታወቅ ታዲያ የተለያዩ ግለሰቦች ተጠርጥረው ፍርድ ቤት ቀርበዋል፡፡ እንስቶቹ ሞተዋል በሚል ግምትም ፖሊስ አስከሬናቸውን ለማግኘት ያልፈነቀለው ድንጋይ አልበረም፡፡ በቅርቡ ግን ሁሉም በህይወት ተገኝተዋል፡፡

ታጋቾቹ በእነዚህ ሁሉ ዓመታት ከክፍላቸው ወጥተው ውጭውን ያዩት አንድ ጊዜ ብቻ ነው - ያውም እዚያው ቤት ግቢ ውስጥ፡፡ ሰዎች ማንነታቸውን እንዳይለዩዋቸው መነጽር፤ ኮፊያ እና ዊግ እንዲጠቀሙ ተገደው እንደነበርም አስታውሰዋል - ለፖሊስ በሰጡት ቃል፡፡ በአሜሪካን ኦሃዮ ግዛት፤ ክሌቭላንድ ውስጥ ለ10 አመት ገደማ ታግተው የቆዩት ሴቶች ባለፈው ሰኞ ነው ነፃ የወጡት- ያገታቸው ግለሰብ ከቤት ሲወጣ አማንዳ ቤሪ ባሰማቸው የድረሱልን ጥሪ፡፡ ከዚያ በፊት ግን እንዲህ ያለ ሙከራ አድርገው እንደማያውቁ አማንዳ ለፖሊስ ገልፃለች፡፡ በመጀመርያ ሙከራዋ ውጤታማ መሆናም ጀግና አሰኝቷታል፡፡ ወደ ማገቻው መኖርያ ቤት የገቡት ሶስቱ ሴቶች ብቻ ቢሆኑም ሰሞኑን ነፃ ሲወጡ ግን የውጭውን ዓለም የማታውቅ የስድስት አመት ህፃንም አብራ ነበረች፡፡ ልጅቷ የቤሪ እንደሆነች የታወቀ ሲሆን አባቷ ማን እንደሆነ ለማወቅ ግን ምርመራ ይካሄዳል ተብሏል፡፡

የቤሪን ጩኸት ሰምቶ ሴቶቹን ነፃ እንዲወጡ የረዳቸው ቻርለስ ራምሴ የተባለ የካስትሮ ጎረቤት ነው፡፡ በዚህ መልካም ሥራውም ከመላው አሜሪካ ከፍተኛ አድናቆት እየጎረፈለት መሆኑ ታውቋል፡፡ ራምሴ የሚሰራበት ሬስቶራንት የፌስቡክ ገፅ ላይ የሰፈረው ፅሁፍ እንዲህ ይላል “በባልደረባችን መልካም ተግባር እጅግ ኩራት ተሰምቶናል፡፡ እሱ የክሌቭላንድ ጀግና ነው፡፡” ራምሴ ስለሁኔታው ሲገልፅም፤ “ድምፅ ሰምቼ ከቤቴ ስወጣ አንዲት ሴት ከጎረቤት ካለው ቤት ለመውጣት ስትታገል አገኘሁ፡፡ በሩን እየደበደበች ያለማቋረጥ የምትጮኸውን ሴት ከዚህ በፊት አይቻት አላውቅም፡፡ “እኔ ታግቼ ነው፡፡ እዚህ ቤት ለአመታት ተዘግቶብኝ ኖሬያለሁ፡፡ አሁን ነፃ መውጣት እፈልጋለሁ” አለችኝ ፡፡ ለምን 911 አትደውይም ስላት መውጣት እንደምትፈልግ አጥብቃ ነገረችኝ ፡፡ እኔና ሌላ ሰው በሩን በመክፈት ተባበርናት፡፡ እናም 911 በመደወል እኔና ቤሪ ሁኔታውን አስረዳን፡፡ ፖሊስ ሲመጣ ሌሎች ሁለት ሴቶች ውስጥ እንዳሉ ገልፃ ሁሉም ነፃ ወጡ” ብሏል፡፡ ራምሴ በአጋችነት የተጠረጠረውን ጎረቤቱን እንዲህ ያለ ተግባር ይፈፅማል ብሎ አስቦ አያውቅም፡፡

“ስለጎረቤቴ ምንም የተለየ ነገር አላውቅም ነበር፡፡ ብዙ ምሽቶችን ስጋ እየጠበስንና ሳልሳ ሙዚቃ እየሰማን አሳልፈናል፡፡ ግቢው ውስጥም ሁልጊዜ ከውሾቹ ጋር ሲጫወት ነው የማየው፡፡ ዛሬ ካየሁት ውጪ የሚያስገርም ነገር ሲያደርግ አይቼ አላውቅም” በማለት መገረሙን ገልጿል፡፡ የአውቶቡስ ሾፌሩ ካስትሮ፤ የፖርቶሪኮ ተወላጅ ሲሆን የላቲን ባንድ የሙዚቃ ተጫዋች ነበር፡፡ የዛሬ ስምንት ዓመት ገደማ በአሁኑ ወቅት አብራው በማትኖር ሚስቱ የድብደባ እና የግድያ ዛቻ ክስ ቢቀርብበትም ክሱ ውድቅ ተደርጓል፡፡ የፖሊስ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በ2000 እና በ2004 ዓ.ም ፖሊስ በደረሰው ጥቆማ በካስትሮ ቤት ላይ ፍተሻ አድርጎ ነበር፡፡ ነገር ግን ምንም ፍንጭ ሳያገኝ ተመልሷል፡፡ አሁን የሶስቱ ሴቶች ህይወት ተቀይሯል፡፡ አማንዳ ቤሪ የ27 አመት ሴት እና የስድስት አመት ልጅ እናት ሆናለች፡፡ እናቷን በህይወት ለማግኘት አልታደለችም፡፡

በልጃቸው ድንገተኛ መሰወር ልባቸው ክፉኛ የተሰወረው እናቷ ከጠፋችበት እለት አንስቶ ህይወታቸው እስክታልፍ ድረስ ያለመታከት ልጃቸውን ሲያፈላልጉ ቆይተዋል ሆኖም የልጃቸውን ዓይን ሳያዩ በደረሰባቸው የጤና እክል ህይወታቸው አልፏል፡፡ ሚሸል ናይት የ30 አመት ሴት ሆናለች፡፡ እሷ ከታገተች በኋላ የተወለደች አዲስ እህት አግኝታለች፡፡ እናቷ በሰጠችው አስተያየት፤ “ልጄን በህይወት ማግኘቴ ታላቅ ስጦታ ነው፡፡ ቶሎ እንድታገግም አግዛታለሁ” ብላለች፡፡ ከትምህርት ቤት ወደቤት ለመመለስ ዘጠኝ አመታት የፈጀባት ጂና፤ ቤተሰቦቿን የተቀላቀለችው የ23 አመት ወጣት ሆና ነው፡፡ በእነዚያ ዓመታት ብዙ ስቃዮችን ብታሳልፍም ፊቷን በሹራቧ ሸፍና የአውራ ጣቷን ወደ ላይ በመቀሰር ዳግም ከቤተሰቧ ጋር መቀላቀሏ የፈጠረባትን ደስታ ገልፃለች፡፡

ሦስቱም ሴቶች ከደረሰባቸው የአካልና የሥነልቦና ጉዳት ለማገገም ሆስፒታል ገብተው የነበረ ሲሆን ሁለቱ ህክምናቸውን አጠናቀው ሲወጡ እናቷን በሞት ያጣችው ናይት ግን አሁንም እዚያው ትገኛለች፡፡ መርማሪዎች ወደ ሁለት መቶ የሚጠጉ ማስረጃዎችን ከካስትሮ ቤት ሰብስበዋል፡፡ የክሌቭላንድ ከንቲባ ፍራንክ ጃክሰን፤ ሶስቱ ሴቶች በህይወት መገኘታቸው እንዳስደሰታቸው ገልፀው ሆኖም ያልተመለሱ ብዙ ጥያቄዎች አሉ ብለዋል፡፡ ለምን ተወሰዱ? እንዴት ተወሰዱ? ይህን ያህል ጊዜስ ያሉበት እንዴት ሳይታወቅ ቀረ የሚሉና ሌሎችም፡፡ ከንቲባው እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ ምርመራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ቃል ገብተዋል፡፡ ምንም እንኳን ቤሪ እናቷን ለማየት ባትታደልም እናት ለመሆን በቅታለች፡፡ ጂና እና ናይት ደግሞ ከእናቶቻቸው ጋር ለመገናኘት ችለዋል፡፡ እናም ሦስቱ ሴቶች ከአስር ዓመት እገታ በኋላ ነፃ መውጣታቸው ነገ ለሚከበረው “የእናቶች ቀን” መልካም ስጦታ ሆኖላቸዋል፡፡

በቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና መካከል ከተደረገው የጥሎ ማለፍ ጨዋታ በፊት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው እና የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ይቅር ተባባሉ፡፡ ከወር በፊት የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች እና ዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው አላግባብ በገቡት እሰጥ አገባ ተጠማምደው የነበረ ሲሆን ከትናንት በስቲያ በስታድዬም መላው ስፖርት አፍቃሪን ባስደሰተ ስፖርታዊ ጨዋነት ተታርቀዋል፡፡ በሌላ በኩል በኢትዮጵያ እግር ኳስ ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማድረግ ከሚታወቁት ክለቦች ግንባር ቀደም ተጠቃሽ የሆነው የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ነገ 36ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በድምቀት ያከብራል፡፡የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ እና የክለቡ ደጋፊዎች ማህበር ‹‹የኢትዮጵያ ቡና በአዲስ ጎዳና›› በሚል መርህ ከኮንታክት መልቲ ሚድያ ጋር በመተባበር ሰፊ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም እንዳዘጋጁ ታውቋል፡፡

ክለቡ በያዘው አዲስ አቅጣጫ ያለውን የደጋፊ ብዛት በመጠቀም በፕሮፌሽናል መንገድ በመደራጀት በስፋት ለመንቀሳቀስ ትኩረት እንዳደረገ ለማወቅ ተችሏል፡፡ኢትዮጵያ ቡና የተመሰረተው በ1975 ዓ/ም በቡና ቦርድ ስር ሆኖ ቡና ገበያ ስፖርት ክለብ በሚል ስያሜ ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ ክለቡ የቡና ላኪዎች ማህበር ከምርት ገበያ ጋር በመሆን በጀት እየመደቡለት በቦርድ በመመራት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ለ36 ዓመታት በኢትዮጵያ የክለብ ውድድሮች በነበረው ተሳትፎ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮናነት አንድ ጊዜ ብቻ በ2003 ዓ.ም ሲያስመዘግብ ሌሎች የዋንጫ ድሎቹ 1 ጊዜ በኢትዮጵያ ሻምፒዮና 4 ጊዜ በኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ሻምፒዮና ፤3 ጊዜ በኢትዮጵያ የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ እንዲሁም 1 ጊዜ የክለቦች ህብረት አሸናፊነት የተመዘገቡ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ቡና በአራት የአፍሪካ ውድድሮች የመሳተፍ እድል ያገኘ ክለብ ሲሆን በኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ውድድሮች በየጊዜው ሻምፒዮን የመሆን ልምድ አለው፡፡ ክለቡ ከዋናው ቡድን በተጨማሪ ተጠባባቂ የተስፋ ቡድን፤ በወጣት እና በሴቶች ቡድኖቹም እየሰራ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ በኢትዮጵያ እግር ኳስ የሚታወቀው ስታድየምን በማስዋብና በማድመቅ በሚታወቁት ደጋፊዎቹ ነው፡፡ የክለቡ ደጋፊዎች በአዲስ አበባ ስታድየም ቀኝ ጥላ ፎቅ፣ ካታንጋ እና ሚስማርተራ በብዛት ገብተው አስደናቂ የድጋፍ አሰጣጥ፤ ዝማሬ እና ህብረት በማሳየት የስፖርቱ አለኝታ ሆነው የቆዩ ናቸው፡፡

የሰውነትየምንግዜም ምርጥ አሰልጣኝነት? ለ3 አስርት ዓመታት በአህጉራዊ ውድድሮች አንቀላፍቶ የኖረውን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ወደ ተሳትፎ በማምጣት ውጤታማ በማድረግ ዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው አየተሳካላቸው ነው፡፡ የ61 ዓመቱ ሰውነት ቢሻው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለአንድ አመት መንፈቅ ሲያሰለጥኑ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ እና ዋና ውድድር፤ በዓለም ዋንጫ ማጣርያዎች እና በወዳጅነት በድምሩ 12 ጨዋታዎችን በማድረግ ከ10 አገራት ብሄራዊ ቡድኖች ጋር ተጋጥመዋል፡፡ በውጤታቸውም 6 ድል፤ 4 አቻ እና ሁለት ሽንፈት አስመዝግበዋል፡፡ ከቤኒን እና ከሱዳን ብሄራዊ ቡድኖች ጋር 2 ጨዋታዎችን ሲያደርጉ ሌሎቹ አንድ አንድ ጊዜ የገጠሟቸው ብሄራዊ ቡድኖች ደግሞ ሶማሊያ፤ ደቡብ አፍሪካ፤ መካከለኛው አፍሪካ ሪፖብሊክ፤ ቱኒዚያ ፤ዛምቢያ፤ቡርኪናፋሶ ፤ናይጄርያ እና ቦትስዋና ናቸው፡፡ ዘ ኢንስቲትዩት ኦፍ ፉትቦል ኮቺንግ የተባለ ተቋም ለዓለም አሰልጣኞች በሚያወጣው የብቃት ደረጃ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ባለፈው 1 ዓመት ተኩል ከነበሩበት የ350ኛ ደረጃ አሁን 120ኛ ላይ መድረሳቸውንም ያመለክታል፡፡

በትራንስፈርማርከት ድረገፅ ላይ በአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ስኬት ላይ በተሰራ አሃዛዊ ስሌት መሰረት የአሰልጣኝነታቸው ስኬትም ድል በ33.33 በመቶ፤ አቻ በ41.67 በመቶ እንዲሁም ሽንፈት በ25 በመቶ በመቶ ተተምኗል፡፡ ከ31 ዓመት በፊት በሊቢያው የአፍሪካ ዋንጫ በመንግስቱ ወርቁ አሰልጣኝነት ከተሳተፈች በኋላ 17 ዋና አሰልጣኞች በብሔራዊ ቡድኑ ኃላፊነት የተፈራረቁ ሲሆን ዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ባለፈው 1 ዓመት ተኩል ባስመዘገቡት ውጤት የኢትዮጵያ እግር ኳስ የምንግዜም ውጤታማው አሰልጣኝ እየሆኑ መምጣታቸውን እያረጋገጡ ናቸው፡፡ ከ1 ዓመት ተኩል በፊት የቤልጄማዊው ቶም ሴንትፌይት ረዳት የነበሩት አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው የብሄራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝ በመሆን መስራት የጀመሩት ለ2ኛ ጊዜ ነው፡፡

ከ2004 እሰከ 2006 እኤአ ብሄራዊ ቡድኑን በዋና አሰልጣኝነት ሲመሩ በ2005 እ.ኤ.አ በሩዋንዳ ላይ በዋና ብሔራዊ ቡድን እንዲሁም በ2004 እ.ኤ.አ ደግሞ አዲስ አበባ ላይ በወጣት ብሔራዊ ቡድን ሁለት የሴካፋ ዋንጫዎችን አሸንፈዋል፡፡ በ2001 እ.ኤ.አ ደግሞ በረዳት አሰልጣኝነት ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር የሴካፋን ዋንጫ ማግኘትም ችለዋል፡፡ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ከ7 ዓመት በፊት በብሔራዊ ቡድኑ ሲሰሩ በ5 ዓመት ውስጥ 3 የሴካፋን ዋንጫ ማግኘታቸው ትልቅ ስኬት ነበር፡፡ በተጨማሪም አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው የታዳጊ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆነው በመስራት ቦትስዋና ጋብሮኒ ላይ በተደረገ የአፍሪካ ታዳጊዎች ሻምፒዮና አራተኛ ደረጃ ለማግኘትም በቅተዋል፡፡ ባለፈው 1 ዓመት ተኩል ደግሞ ብሔራዊ ቡድኑን በኃላፊነት ይዘው ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ትንሳኤ የሚሆን ውጤት በማስመዝገብ እየተሳካላቸው ነው፡፡ የመጀመርያው ስኬታቸው ብሄራዊ ቡድኑ ከ31 ዓመታት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ እንዲያልፍ ማስቻላቸው ነው፡፡

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከ31 ዓመት በኋላ በአፍሪካ ዋንጫ ሲሳተፍ 3 ግጥሚያዎችን አድርጎ አንድ አቻ እና ሁለት ሽንፈት ፤ አንድ ጎል አግብቶ 7 ጎል ተቆጥሮበት ከምድቡ በጊዜ መሰናበቱ የሚታወስ ቢሆንም በውድድሩ ከፍተኛ አህጉራዊ ትኩረት ሊያገኝ የበቃ ነበር፡፡ በአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው የሚመራው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን እያገኘ ባለው ስኬት ከፍተኛ የሽልማት ገንዘብ፤ በስፖንሰርሺፕ የገቢ ምንጭ በመፍጠር እና ደረጃውን በማሻሻልም ሆኖለታል፡፡ሼህ መሃመድ አልአሙዲ ለብሄራዊ ቡድኑ 5 ሚሊዮን ብር ከመሸለማቸውም በላይ የቡድኑ አብይ ስፖንሰር የሆነው በደሌ ቢራ በስፖንሰርሺፕ ውል ለ2 ዓመት እስከ 24 ሚሊዮን ብር በመክፈል ቡድኑን ማጠናከር ተችሏል፡፡ ኤምቲኤን የተባለ ኩባንያም በ6 ሚሊዮን ብር ብሄራዊ ቡድን ስፖንሰር ማድረጉም ይታወቃል፡፡ በአሁን ጊዜ በ50ሺ በር ወርሃዊ ደሞዛቸው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ውዱ ተከፋይ የሆኑት ዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው 280 ሺ ብር የሚያወጣ ሊፋን መኪና በውጤታማነታቸው በማግኘትም ተጠቅመዋል፡፡

በአሰልጣኝ ሰውነት ሃላፊነት ዘመን በዋልያዎቹ ስብስብ ያሉ ተጨዋቾች በነፍስ ወከፍ በአማካይ 300ሺ ብር ለመሸለም እንደበቁም ይታወቃል፡፡ በሰውነት ቢሻው የሚመራው ብሄራዊ ቡድን ከአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ ባሻገር በ2014 እ.ኤ.አ ብራዚል ለምታስናግደው 20ኛው የዓለም ዋንጫ ለማለፍ በሚደረገው የምድብ ማጣሪያም በተስፋ ሰጭ ውጤት በመጓዝ ላይ ይገኛል፡፡ በዓለም ዋንጫ ማጣርያው ደቡብ አፍሪካ፤ ቦትስዋና እና መካከለኛው አፍሪካ ሪፖብሊክ የሚገኙበትን ምድብ የሰውነት ቢሻው ብሄራዊ ቡድን በ3 ጨዋታዎች ሰባት ነጥብ እና 3 የግብ ክፍያ በመያዝ እየመራ ነው፡፡

በብራዚል 2014 ላይ ለሚስተናገደው 20ኛው የዓለም ዋንጫ የሚደረገው የምድብ ማጣሪያ በ4ኛ ዙር ሲቀጥል የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ሰኔ መጀመርያ ላይ ከቦትስዋና ጋር ከሜዳው ውጭ ይጋጠምና በሳምንቱ ደግሞ ከደቡብ አፍሪካ ጋር በአዲስ አበባ ይጫወታል፡፡ በዓመቱ መገባደጃ ላይ ደግሞ በመጨረሻው የማጣርያ ጨዋታ ከሜዳው ውጭ ከመካከለኛው አፍሪካ ጋር ይጋጠማል፡፡ ዋልያዎቹ በቀሪዎቹ 3 ጨዋታዎች ያለሽንፈት ከተጓዙ ከአንድ ብሄራዊ ቡድን ጋር በደርሶ መልስ የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ድልድል በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ለዓለም ዋንጫ የሚሳተፉበትን እድል ይወስናሉ፡፡ ይህን ማሳካት ደግሞ ለዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው የምንግዜም ምርጥ አሰልጣኝነት ሁነኛ ማረጋገጫ ይሆናል፡፡