Saturday, 30 March 2019 13:18

ቤተ መንግስት ከ6 ወር በኋላ ለጐብኚዎች ክፍት ይሆናል

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

 ከውጭ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ እድሣትና እየተከናወነበት የሚገኘው ታላቁ ብሔራዊ ቤተ መንግስት ከ6 ወር በኋላ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ሀገር ጐብኚዎች ክፍት እንደሚሆን ተገለፀ፡፡
በቤተ መንግስቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ እድሣት የሚደረግላቸውን ጥንታዊ ቤቶች፣ አዳራሾች ከትናንት በስቲያ ከተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን የተውጣጡ ጋዜጠኞች የተጐበኙ ሲሆን፤ በቤተመንግስቱ ቅጥር ግቢም ግዙፍ የእንስሳት ፓርክ እየተዘጋጀ መሆኑን መመልከት ተችሏል፡፡
በቤተ መንግስቱ ግቢ ውስጥ ግቢውን በሣርና ዛፎች ከማስዋብ ጀምሮ ጥንታዊ አዳራሾችንና ህንፃዎችን የማደስ ተግባራት እየተከናወኑ ነው፡፡
እድሣት ከሚደረግላቸው መካከል የአፄ ምኒልክ የግብር አዳራሽ ተጠቃሽ ሲሆን አዳራሹ ሙሉ ለሙሉ እድሣቱ ሲጠናቀቅ ጠ/ሚር ዶ/ር ዐቢይ በቅርቡ ሊያዘጋጁት ሸገርን እናስውብ የእራት ግብዣ ይከናወንበታል፡፡
ይህን አዳራሽ በቀጣይ ሠርገኞች እና የተለያዩ ፕሮግራም ያላቸው አካላት ተከራይተው ይጠቀሙበታል ተብሏል፡፡
እድሣት ከተደረገላቸው ጥንታዊ ቤቶች መካከል የአፄ ኃይለሥላሴ እና ቤተሰቦቻቸው መኖሪያ የነበሩ ቤቶች የሚገኙበት ሲሆን በደርግ ዘመነ መንግስት ቤቶቹ ለታሣሪዎች ማሰቃያነት ይውሉ እንደነበረና አሁን በተደረገው እድሣት ግን ለጐብኚዎች ገለፃ ማድረጊያ ማዕከል እንዲሆን ተወስኗል ተብሏል፡፡ ለዚህም እንዲረዳ ስክሪኖች በቤቶቹ ተገጥሟል፡፡
የቀድሞ ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ መኖሪያ ቤትም ወደ እንግዳ ማረፊያነት የተቀየረ ሲሆን አዳዲስ እና ዘመናዊ ሶፋዎች ገብተውበት ታላላቅ እንግዶችን እየጠበቀ ነው ተብሏል፡፡
ነገሮቹን ቤቶችና አዳራሾች ከማደስ ጐን ለጐን ለቤተመንግስቱ አዲስ ገጽታን የሚያላብቡ የተለያዩ አዳዲስ ግንባታዎችም እየተከናወነ መሆኑን መታዘብ ተችሏል፡፡
የቤተንግስቱ እድሣትና የፓርክ ግንባታው በቀጣይ 6 ወራት ውስጥ ተጠናቆ ጐብኚዎች በክፍያ የሚስተናገዱበት የጉብኝትና የመዝናኛ ማዕከል ይሆናል ተብሏል፡፡

Read 7247 times