Sunday, 03 March 2019 00:00

ፑንት ላንድ እና ሳውዲ አረቢያ ከ1 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያንን በኃይል ከሃገራቸው አባረሩ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)


በጅቡቲ የሚገኙ ስደተኞች ወደ ሃገር ቤት እየተመለሱ ነው


ሳውዲ አረቢያ እና ፑንት ላንድ ከሰሞኑ 1 ሺህ ያህል ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን በግዳጅ ወደ ሃገር ቤት የመለሱ ሲሆን በጅቡቲ የሚኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችም በገዛ ፈቃዳቸው በብዛት ወደ ሃገር ቤት እየተመለሱ መሆኑን የአለማቀፉ የስደተኞች ተቋም ሪፖርት አመልክቷል፡፡
በተለይ ባለፈው ጥር 21 ቀን 2011 ዓ.ም ከ50 በላይ ኢትዮጵያውያን ከጅቡቲ ወደ የመን የባህር ጉዞ ላይ እያሉ በጀልባ መገልበጥ ህይወታቸው ማለፉን ተከትሎ በጅቡቲ የተለያዩ ህገ ወጥ የስደተኞች ማከማቻ ውስጥ የሚገኙና ተራቸውን የሚጠባበቁ ከ3 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያን ወደ ሃገር ቤት ለመመለስ ለአይኦኤም የእርዳታ ጥሪ ማቅረባቸው ታውቋል፡፡
ጅቡቲ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ለቀጣይ የባህር ላይ ጉዞ የሚዘጋጁባት ዋነኛ ቦታ መሆንዋን የጠቆመው የአለማቀፉ የስደተኞች ተቋም ሪፖርት የስደተኞች ስቃይ የሚጀምረው በዚህችው ሃገር ነው ብሏል፡፡
በጥር ያጋጠመውን የጀልባ አደጋ ሳይጨምር በ5 ዓታት ውስጥም ሁለት በመቶ ያህል ዜጎች በጅቡቲው ኦቦክ የባህር ዳርቻ ከጀልባ ተወርውረው የባህር ሲሳይ መሆናቸውን ሪፖርቱ አትቷል፡፡
እድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች የሆኑ ታዳሚ ወጣቶች እያንዳንዳቸው እስከ 15 ሺህ ብር ለደላላ በመክፈል ወደ ጅቡቲ እንደሚያቀኑ ያተተው ሪፖርቱ የጥሩ የጀልባ አደጋን ተከትሎ ከ3 ሺህ በላይ ስደተኞች ወደ ሃገራቸው ለመመለስ ፍላጎት እንዳላቸው የገለፁ ሲሆን እስካሁን 1,327 ያሉ በአይኦኤም እርዳታ ተመልሰዋል ብሏል፡፡
በሌላ በኩል ጎረቤት ፑንትላንድ 415 እንዲሁም ሳውዲ አረቢያ 6 መቶ ያህል ህገ ወጥ ያሏቸውን ኢትዮጵያውያን ከሰሞኑ በኃይል ወደ ሃገር ቤት መመለሳቸው ታውቋል፡፡
ከሶማሊያ ተገንጥላ ራስ ገዝ ግዛትነቷን ያወጀችው ፑንትላንድ ሰሞኑን ጠርዛ ወደ ሃገር ቤት ከመለሰቻቸው ኢትዮጵያውያን በተጨማሪ 517 ኢትዮጵያውያን በቁጥጥር ስር ማዋሏንና ከሰሞኑ ወደ ሃገራቸው እንደምትመልስ አስታውቃለች፡፡
አለማቀፉ የስደተኞች ተቋም (አይኦኤም) በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያውያን ስደተኞን ወደ ሃገር ቤት በመመለስ ስራ መወጠሩን አስታውቋል፡፡

Read 4970 times