Saturday, 19 January 2019 00:00

ሎራን ባግቦ ከአለማቀፉ የወንጀለኞች ፍ/ቤት ክስ በነጻ ተሰናበቱ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 አለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በዜጎች ላይ ኢ-ሰብዓዊ የወንጀል ድርጊቶችን ፈጽመዋል በሚል ክስ መስርቶባቸው የነበሩትን የቀድሞውን የአይቬሪኮስት ፕሬዚዳንት ሎራን ባግቦን በነጻ ማሰናበቱን አስታውቋል፡፡
አለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት እ.ኤ.አ በ2010 በአይቬሪኮስት የተካሄደውን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ተከትሎ፣ በአገሪቱ በተቀሰቀሰውና ለወራት በዘለቀው የእርስ በእርስ ግጭት በርካታ ቁጥር ባላቸው ዜጎች ላይ ከፍተኛ ወንጀሎችን ፈጽመዋል በሚል ተከስሰው የነበሩትን የ73 አመቱን ሎራን ባግቦን ባለፈው ማክሰኞ በነጻ ማሰናበቱን የዘገበው ኒውዮርክ ታይምስ፤ ውሳኔው በብዙዎች ዘንድ ያልተጠበቀ መሆኑን ገልጧል፡፡
ባለፈው ማክሰኞ በሄግ የተሰየመው ችሎት የመሃል ዳኛው፣ ባግቦ ነጻ መሆናቸውን ይፋ ማድረጋቸውን ተከትሎ፣ በችሎቱ ታድመው የነበሩ የባግቦ ደጋፊዎች በደስታ መፈንጠዛቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ የምስራቹ ወደ አገሪቱ የኢኮኖሚ ከተማ አቢጃን በቅጽበት ደርሶ ጎዳናዎች በደስታ በሚዘምሩ የባግቦ ደጋፊዎች መሞላታቸውንም አመልክቷል፡፡
በአንጻሩ ደግሞ በባግቦ ዘመን የተቀሰቀሰው የእርስ በእርስ ግጭት ቤተሰቦቻቸውን ያሳጣቸውና ተጠቂ ያደረጋቸው በርካታ አይቬሪኮስታውያን በፍርድ ቤቱ ውሳኔ ክፉኛ መቆጣታቸውንና አለማቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች አምነስቲ ኢንተርናሽናልም ውሳኔውን መቃወሙን ዘገባው አስረድቷል፡፡
እ.ኤ.አ በ2000 ወደ ስልጣን ላይ የወጡትና አገሪቱን ለእርስ በእርስ ጦርነት በመዳረግና በአምባገነንነት የሚታወቁት ሎራን ባግቦ የአገሪቱ ህግ ከሚፈቅድላቸው ውጭ ለተጨማሪ አምስት አመታት በስልጣን ላይ ከቆዩ በኋላ፣ በ2010 በተካሄደው ምርጫ ቢሸነፉም በጠመንጃ ስልጣን ላይ ለመቆየት በማሰብ አገሪቱን ለደም መፋሰስ መዳረጋቸውንና በስተመጨረሻም ተዋርደው መውረዳቸውን ዘገባው አስታውሷል፡፡

Read 1388 times